በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 88

ዮሐንስ ኢየሱስን አጠመቀው

ዮሐንስ ኢየሱስን አጠመቀው

ወደ ሰውየው ራስ እየወረደች ያለችውን ርግብ ተመልከት። ሰውየው ኢየሱስ ነው። አሁን 30 ዓመት ገደማ ሆኖታል። ከእሱ ጋር ያለው ሰው ደግሞ ዮሐንስ ነው። ቀደም ሲል ስለ እርሱ የተማርነው ነገር ነበር። ማርያም ዘመዷን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ሄዳ በነበረበት ጊዜ በኤልሳቤጥ ማኅፀን ውስጥ የነበረው ሕፃን በደስታ ዘልሎ እንደነበረ ታስታውሳለህ? ይህ ገና በማኅፀን ውስጥ የነበረው ሕፃን ዮሐንስ ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ዮሐንስና ኢየሱስ እያደረጉት ያሉት ነገር ምንድን ነው?

ዮሐንስ ኢየሱስን በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ካጠለቀው በኋላ ኢየሱስ ገና ከውኃው መውጣቱ ነበር። አንድ ሰው የሚጠመቀው በዚህ መንገድ ነው። በመጀመሪያ ውኃው ውስጥ እንዲጠልቅና ከዚያም ከውኃው እንዲወጣ ይደረጋል። ዮሐንስ ሕዝቡን በዚህ መንገድ ያጠምቅ ስለነበረ አጥማቂው ዮሐንስ ተብሎ ይጠራ ነበር። ይሁን እንጂ ዮሐንስ ኢየሱስን ያጠመቀው ለምንድን ነው?

ዮሐንስ ያጠመቀው ኢየሱስ ራሱ እንዲያጠምቀው ስለጠየቀው ነው። ዮሐንስ በሠሯቸው መጥፎ ነገሮች መጸጸታቸውን ለማሳየት የሚፈልጉ ሰዎችን ያጠምቅ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሚጸጸትበት መጥፎ ነገር ሠርቶ ያውቃል እንዴ? በፍጹም፣ ኢየሱስ ከሰማይ የመጣ የአምላክ ልጅ ስለሆነ መጥፎ ነገር ሠርቶ አያውቅም። ስለዚህ ዮሐንስን እንዲያጠምቀው የጠየቀው በሌላ ምክንያት ነበር። መጠመቅ የፈለገበት ምክንያት ምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ኢየሱስ ወደ ዮሐንስ ከመምጣቱ በፊት አናጢ ሆኖ ይሠራ ነበር። አናጢ ጠረጴዛዎችን፣ ወንበሮችን፣ አግዳሚ መቀመጫዎችንና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ከእንጨት የሚሠራ ሰው ነው። የማርያም ባል የሆነው ዮሴፍ አናጢ ነበር፤ ኢየሱስንም አናጢነት አስተምሮታል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ልጁን ወደ ምድር የላከው አናጢ እንዲሆን አይደለም። አንድ ልዩ ሥራ ሰጥቶት ነበር፤ ይህን ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ ደግሞ ደርሶ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ መምጣቱን ለማሳየት ዮሐንስን እንዲያጠምቀው ጠየቀው። አምላክ በዚህ ተደስቶ ነበርን?

አዎ፣ ተደስቶ ነበር፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ከውኃው ውስጥ ከወጣ በኋላ ከሰማይ የመጣ አንድ ድምፅ ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው’ ብሎ ነበር። በተጨማሪም ሰማያት ተከፍተው በኢየሱስ ላይ ርግብ ወረደ። ሆኖም ርግብ የሚመስል ነገር እንጂ የእውነት ርግብ አልነበረም። በኢየሱስ ላይ የወረደው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ነው።

በዚህ ወቅት ኢየሱስ ብዙ የሚያሰላስለው ነገር ስለነበረው ሰው ወደሌለበት አካባቢ ሄዶ 40 ቀናት ያህል ቆየ። እዚያ እያለ ሰይጣን ወደ እርሱ መጣ። ኢየሱስ የአምላክን ሕግ የሚያስጥስ ነገር እንዲፈጽም ለማድረግ ሰይጣን ሦስት ጊዜ ሞክሮ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ሰይጣን ያለውን አላደረገም።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ሲመለስ የመጀመሪያ ተከታዮቹ ወይም ደቀ መዛሙርቱ የሆኑትን ጥቂት ሰዎች አገኘ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ እንድርያስ፣ ጴጥሮስ (ስምዖን ተብሎም ይጠራል)፣ ፊልጶስና ናትናኤል (በርተሎሜዎስ ተብሎም ይጠራል) ናቸው። ኢየሱስና እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ወደ ገሊላ አውራጃ ሄዱ። ገሊላ ሲደርሱ በናትናኤል የትውልድ ከተማ በቃና ለተወሰነ ጊዜ ቆዩ። በዚህች ከተማም ኢየሱስ በአንድ ትልቅ የሠርግ ግብዣ ላይ ተገኘና የመጀመሪያውን ተአምር ፈጸመ። ይህ ተአምር ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ውኃውን ለውጦ ወይን አደረገው።