በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 90

ከአንዲት ሴት ጋር በውኃው ጉድጓድ አጠገብ

ከአንዲት ሴት ጋር በውኃው ጉድጓድ አጠገብ

ኢየሱስ በሰማርያ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ አረፍ አለ። ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ለመግዛት ወደ ከተማ ሄደው ነበር። ኢየሱስ እያነጋገራት ያለችው ሴት የመጣችው ውኃ ለመቅዳት ነው። ኢየሱስ ‘ውኃ አጠጪኝ’ አላት።

ይህ ሴትየዋን በጣም አስደነቃት። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? ኢየሱስ አይሁዳዊ ሲሆን እሷ ግን ሳምራዊት ስለነበረች ነው። አብዛኞቹ አይሁዳውያን ደግሞ ሳምራውያንን አይወዷቸውም። ሌላው ቀርቶ አያነጋግሯቸውም ነበር! ኢየሱስ ግን ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ይወድ ነበር። ስለዚህ ‘ውኃ አጠጪኝ ብሎ የጠየቀሽ ሰው ማን እንደሆነ ብታውቂ አንቺ ትለምኚው ነበር፤ እርሱም ሕይወት የሚያስገኝ ውኃ ይሰጥሽ ነበር’ አላት።

ሴቲቱ ‘ጌታዬ ሆይ፣ ጉድጓዱ ጥልቅ ነው፤ አንተ ደግሞ መቅጃ እንኳ የለህም። ታዲያ ይህን ሕይወት የሚያስገኝ ውኃ ከየት ታገኛለህ?’ አለችው።

‘ከዚህ የውኃ ጉድጓድ ብትጠጪ እንደገና ትጠሚያለሽ፤ እኔ የምሰጠው ውኃ ግን የዘላለም ሕይወት ያስገኛል’ ሲል ገለጸላት።

ሴቲቱ ‘ጌታዬ ሆይ፣ ይህን ውኃ ስጠኝ! ከዚያ በኋላ ዳግመኛ አልጠማም። ውኃ ለማግኘትም ወደዚህ ቦታ መምጣት አያስፈልገኝም’ አለችው።

ሴቲቱ ኢየሱስ በቀጥታ ስለ ውኃ እየተናገረ እንዳለ አድርጋ አስባ ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ስለ አምላክና ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን እውነት አስመልክቶ ነበር። ይህ እውነት ሕይወት የሚያስገኝ ውኃ ነው። የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝ ይችላል።

ኢየሱስ ሴቲቱን ‘ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ተመለሺ’ አላት።

ሴቲቱ ‘ባል የለኝም’ ብላ መለሰችለት።

ኢየሱስ ‘ልክ ነሽ። ቀደም ሲል አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን አብሮሽ የሚኖረው ሰው ግን ባልሽ አይደለም’ አላት።

የተናገረው ሁሉ እውነት ስለነበረ ሴቲቱ ተደነቀች። ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች እንዴት ሊያውቅ ቻለ? አዎ፣ ኢየሱስ አስቀድሞ ቃል በተገባው መሠረት በአምላክ የተላከ ሰው በመሆኑ አምላክ ይህን እንዲያውቅ አድርጎት ነበር። በዚህ ጊዜ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተመለሱ። ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ሲነጋገር በማየታቸው በጣም ተገረሙ።

ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን? ኢየሱስ ለሁሉም ዘሮች እንደሚያስብ ያሳያል። እኛም እንደ እርሱ መሆን አለብን። ሰዎችን በዘራቸው ልንጠላቸው አይገባም። ኢየሱስ ሁሉም ሰዎች ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውነት እንዲያውቁ ይፈልጋል። እኛም ሰዎች እውነትን እንዲማሩ መርዳት አለ⁠ብን።