በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 98

በደብረ ዘይት ተራራ ላይ

በደብረ ዘይት ተራራ ላይ

ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ይታያል። አብረውት ያሉት አራት ሰዎች ደግሞ ሐዋርያቱ ናቸው። እነዚህ ሐዋርያት ወንድማማች የሆኑት እንድርያስና ጴጥሮስ እንዲሁም ሌሎቹ ወንድማማቾች ማለትም ያዕቆብና ዮሐንስ ናቸው። በርቀት የሚታየው ደግሞ በኢየሩሳሌም የሚገኘው የአምላክ ቤተ መቅደስ ነው።

ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ከሄደ ሁለት ቀናት አልፈዋል። ዕለቱ ማክሰኞ ነው። በዚህ ዕለት ጠዋት ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ነበር። እዚያ ሳለ ካህናቱ ኢየሱስን ይዘው ለመግደል ፈልገው ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝቡ ኢየሱስን ይወዱት ስለነበረ ካህናቱ ይህን ለማድረግ ፈሩ።

ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹን ‘እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች!’ ብሎ ጠርቷቸዋል። ከዚያም ኢየሱስ በፈጸሟቸው መጥፎ ነገሮች ምክንያት አምላክ እንደሚቀጣቸው ተናገረ። ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጣ፤ ከዚያም እነዚህ አራቱ ሐዋርያት ጥያቄዎች ይጠይቁት ጀመር። ኢየሱስን ምን እየጠየቁት እንዳሉ ታውቃለህ?

ሐዋርያቱ ወደፊት ስለሚፈጸሙ ሁኔታዎች እየጠየቁት ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ ያለውን ክፋት በሙሉ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ ያውቃሉ። ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው መቼ እንደሆነ ለማወቅ ፈልገው ነበር። ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ለመግዛት ዳግመኛ የሚመጣው መቼ ነው?

ኢየሱስ ዳግመኛ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ ያሉት ተከታዮቹ ሊያዩት እንደማይችሉ ያውቃል። በዚያ ጊዜ ኢየሱስ በሰማይ ስለሚሆን ሊያዩት አይችሉም። ስለዚህ ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ሲገዛ በምድር ላይ የሚከናወኑትን አንዳንድ ነገሮች ለሐዋርያቱ ነገራቸው። ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

ኢየሱስ ታላላቅ ጦርነቶች እንደሚኖሩ፣ ብዙ ሰዎች እንደሚታመሙና እንደሚራቡ፣ ወንጀል እየባሰ እንደሚሄድ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሚከሰት ተናገረ። በተጨማሪም ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ምሥራች በምድር ዙሪያ እንደሚሰበክ ገለጸ። እነዚህ ነገሮች በጊዜያችን ሲፈጸሙ ተመልክተናል? አዎ፣ ተመልክተናል! ስለዚህ ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ በሰማይ እየገዛ እንዳለ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በቅርቡ ክፋትን በሙሉ ከምድር ላይ ጠራርጎ ያጠፋል።