በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 99

ፎቅ ላይ በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ

ፎቅ ላይ በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ

ሐሙስ ማታ ነው፤ ከሁለት ቀናት በኋላ መሆኑ ነው። ኢየሱስና 12 ሐዋርያቱ የማለፍን በዓል ለማክበር የተዘጋጀውን እራት ለመብላት ፎቅ ላይ ወደሚገኘው ወደዚህ ሰፊ ክፍል መጥተዋል። ወደ ውጪ እየወጣ ያለው ሰው አስቆሮቱ ይሁዳ ነው። ካህናቱ ኢየሱስን እንዴት ሊያገኙት እንደሚችሉ ሊነግራቸው እየሄደ ነው።

ይሁዳ ከአንድ ቀን በፊት ወደ ካህናቱ ሄዶ ‘ኢየሱስን ለመያዝ እንድትችሉ ብረዳችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?’ ብሎ ጠይቋቸው ነበር። ‘ሠላሳ የብር ሳንቲሞች እንሰጥሃለን’ አሉት። ስለዚህ ይሁዳ ሰዎቹን መርቶ ኢየሱስን ለማስያዝ እየሄደ ነው። አያሳዝንም?

የማለፍ በዓልን ለማክበር የተዘጋጀውን እራት ተመግበው ጨረሱ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሌላ ልዩ እራት አዘጋጀ። ለሐዋርያቱ ዳቦ ሰጠና ‘ይህ ለእናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ብሉት’ አላቸው። ከዚያም ወይን ጠጅ ቀድቶ ሰጣቸውና ‘ይህ ለእናንተ የሚፈሰው ደሜ ነው፤ ጠጡት’ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ‘የጌታ እራት’ ብሎ ይጠራዋል።

እስራኤላውያን በግብፅ ሳሉ የአምላክ መልአክ የእነርሱን ቤቶች ‘አልፎ’ በግብፃውያን ቤቶች ውስጥ የሚገኙትን የበኩር ልጆች የገደለበትን ጊዜ ለማስታወስ የማለፍ በዓልን ያከብሩ ነበር። አሁን ግን ኢየሱስ ተከታዮቹ እሱንና ለእነርሱ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠበትን ሁኔታ እንዲያስታውሱ ለማድረግ ፈለገ። ይህን ልዩ በዓል በየዓመቱ እንዲያከብሩ ያዘዛቸውም በዚህ ምክንያት ነው።

የጌታን እራት ከበሉ በኋላ ኢየሱስ ተከታዮቹን ደፋር እንዲሆኑና ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው ነገራቸው። በመጨረሻም ለአምላክ ዘመሩና ወጡ። በዚህ ጊዜ በጣም መሽቶ ነበር፤ እኩለ ሌሊት ሳያልፍ አይቀርም። ወዴት እንደሚሄዱ እስቲ እንመልከት።