በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 105

በኢየሩሳሌም ሆኖ መጠባበቅ

በኢየሩሳሌም ሆኖ መጠባበቅ

እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ ተከታዮች ናቸው። ኢየሱስን በመታዘዝ በኢየሩሳሌም ቆዩ። ሁሉም አንድ ላይ ተሰብስበው ሲጠባበቁ አንድ ኃይለኛ ድምፅ ቤቱን ሞላው። ኃይለኛ ዐውሎ ነፋስ የመጣ ይመስል ነበር። ከዚያም በእያንዳንዱ ደቀ መዝሙር ራስ ላይ የእሳት ነበልባል መታየት ጀመረ። በእያንዳንዳቸው ራስ ላይ ያለውን የእሳት ነበልባል አየኸው? ይህ ምን ያመለክታል?

ይህ ተአምር ነው! ኢየሱስ ወደ ሰማይ ተመልሶ ከአባቱ ጋር ነው፤ እንዲሁም የአምላክን ቅዱስ መንፈስ በተከታዮቹ ላይ እያወረደ ነው። ይህ መንፈስ ምን እንዲያደርጉ እንደገፋፋቸው ታውቃለህ? ሁሉም በተለያዩ ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ።

በኢየሩሳሌም የነበሩ ብዙ ሰዎች ኃይለኛ ዐውሎ ነፋስ የሚያሰማውን ዓይነት ድምፅ ሰምተው ምን እየተከናወነ እንዳለ ለማየት መጡ። አንዳንዶቹ ጰንጠቆስጤ በሚባለው የእስራኤላውያን በዓል ላይ ለመገኘት ከሌሎች አገሮች የመጡ ነበሩ። እነዚህ ጎብኚዎች ምንኛ ተደንቀው ይሆን! ደቀ መዛሙርቱ አምላክ ስላከናወናቸው አስደናቂ ነገሮች በእነርሱ ቋንቋዎች ሲናገሩ ሰሙ።

ጎብኚዎቹ ‘እነዚህ በሙሉ የገሊላ ሰዎች ናቸው፤ እኛ በምንኖርበት አካባቢ የሚነገሩትን የተለያዩ ቋንቋዎች እንዴት ሊናገሩ ቻሉ?’ ሲሉ ተናገሩ።

በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ስለ ሁኔታው ሊያብራራላቸው ተነሳ። ኢየሱስ እንዴት እንደ ተገደለና ይሖዋ እንዴት ከሞት እንዳስነሳው ድምፁን ከፍ አድርጎ ለሰዎቹ ነገራቸው። ጴጥሮስ ‘አሁን ኢየሱስ በሰማይ በአምላክ ቀኝ ተቀምጧል፤ ቃል በገባውም መሠረት መንፈስ ቅዱስን አፍስሷል። እነዚህን ተአምራት ያያችሁትና የሰማችሁት በዚህ ምክንያት ነው’ አለ።

ጴጥሮስ እነዚህን ነገሮች ሲናገር ብዙዎቹ ሰዎች በኢየሱስ ላይ በተፈጸመው ነገር በጣም አዘኑ። ‘ማድረግ ያለብን ነገር ምንድን ነው?’ ብለው ጠየቁ። ጴጥሮስ ‘አኗኗራችሁን መለወጥና መጠመቅ አለባችሁ’ አላቸው። ስለዚህ በዚያው ቀን ወደ 3, 000 የሚጠጉ ሰዎች ተጠመቁና የኢየሱስ ተከታዮች ሆኑ።