በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 112

አንዲት መርከብ በአንድ ደሴት አጠገብ ተሰበረች

አንዲት መርከብ በአንድ ደሴት አጠገብ ተሰበረች

ተመልከት! ጀልባዋ ችግር አጋጥሟታል! እየተሰባበረች ነው! ወደ ውኃው ዘለው የወጡትን ሰዎች አየሃቸው? አንዳንዶቹ ከባሕሩ ወደ ደሴቲቱ እየወጡ ነው። ያ ሥዕሉ ላይ የሚታየው ጳውሎስ ነው? እስቲ ምን ሁኔታዎች እንዳጋጠሙት እንመልከት።

ጳውሎስ በቂሣርያ ሁለት ዓመት ታስሮ እንደቆየ አስታውስ። ከዚያም እሱና ሌሎች እስረኞች ጀልባ ላይ ተጭነው ወደ ሮም መጓዝ ጀመሩ። በቀርጤስ ደሴት አጠገብ ሲያልፉ አንድ ኃይለኛ ዐውሎ ነፋስ መታቸው። ነፋሱ በኃይል ይነፍስ ስለ ነበር ሰዎቹ ጀልባዋን መቆጣጠር አልቻሉም። በተጨማሪም ቀን ፀሐይን ማታ ደግሞ ከዋክብትን ማየት አልቻሉም። በመጨረሻም፣ ከብዙ ቀናት በኋላ በጀልባዋ ላይ የነበሩት ሰዎች ተስፋ ቆረጡ።

ከዚያ በኋላ ጳውሎስ ተነሳና እንዲህ አለ:- ‘ጀልባዋ ብቻ ትጠፋለች እንጂ ከእናንተ መካከል ማንም ሰው አይሞትም። ሌሊት የአምላክ መልአክ ወደ እኔ መጥቶ “ጳውሎስ ሆይ፣ አትፍራ! በሮማ ገዥ በቄሣር ፊት መቅረብ ይገባሃል። አምላክ ከአንተ ጋር እየሄዱ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ያድናቸዋል” ብሎኛል።’

ዐውሎ ነፋሱ መንፈስ በጀመረ በ14ኛው ቀን እኩለ ሌሊት ገደማ ሲሆን ጀልባው ላይ የነበሩት ሰዎች የውኃው ጥልቀት እየቀነሰ እንደመጣ ተገነዘቡ! ጨለማ ስለነበረ ከአለት ጋር እንዳይጋጩ በመፍራት መልሕቅ ጣሉ። በነጋታው ጠዋት አንድ ባሕረ ሰላጤ አዩ። ጀልባዋን እንደ ምንም ወደዚህ የባሕር ዳርቻ ለመቅዘፍ ወሰኑ።

ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲቃረቡ ጀልባዋ ከአሸዋ ክምር ጋር ተጋጭታ ተቀረቀረች። ከዚያም ማዕበሉ ይመታት ጀመር፤ በዚህ ጊዜ ጀልባዋ መሰባበር ጀመረች። ኃላፊ የነበረው የመቶ አለቃ ‘በመጀመሪያ መዋኘት የምትችሉ ሁሉ ወደ ባሕሩ እየዘለላችሁ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ዋኙ። የተቀራችሁት ከእነሱ በኋላ ዝለሉና የምትንሳፈፉበት የጀልባ ስባሪ ይዛችሁ ከባሕሩ ውስጥ ውጡ’ አለ። ሰዎቹም እንደተባሉት አደረጉ። በዚህ መንገድ በጀልባዋ ላይ የነበሩት 276 ሰዎች በሙሉ መልአኩ ቃል በገባው መሠረት በደህና ወደ ባሕሩ ዳርቻ ደረሱ።

ደሴቲቱ መላጥያ ትባላለች። ሰዎቹ በጣም ደጎች ነበሩ፤ ከጀልባው ለወረዱት ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ አደረጉላቸው። የአየሩ ጠባይ ሲስተካከል ጳውሎስ ሌላ ጀልባ ላይ ተጫነና ወደ ሮም ተወሰደ።