በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ህልውናውን ለማስጠበቅ ያደረገው ትግል

መጽሐፍ ቅዱስ ህልውናውን ለማስጠበቅ ያደረገው ትግል

ምዕራፍ 2

መጽሐፍ ቅዱስ ህልውናውን ለማስጠበቅ ያደረገው ትግል

መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። እያንዳንዱ ማስረጃ በተናጠል ሲታይ ጠንካራ ቢሆንም ሁሉም አንድ ላይ ሲጣመሩ የሚኖራቸው ጥንካሬ ይበልጥ አስተማማኝ ይሆናል። በዚህና በሚቀጥለው ምዕራፍ ውስጥ አንዱን ማስረጃ ብቻ እንመለከታለን፤ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ ያሳለፈው ታሪክ ነው። ይህ አስገራሚ መጽሐፍ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ መቆየቱ ራሱን የቻለ አንድ ተዓምር ነው። እስቲ ሁኔታዎችን አንተ ራስህ መርምር።

1. መጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት መጽሐፍ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁ አንድ ተራ መጽሐፍ አይደለም። ሕግን፣ ትንቢትን፣ ታሪክን፣ ግጥሞችን፣ ምክሮችንና ሌሎች ብዙ ነገሮችን አካተው የያዙ 66 አጫጭርም ሆኑ ረጃጅም መጻሕፍት የተሰባሰቡበትና ብዙ እውቀት የሚገኝበት ቤተ መጻሕፍት ነው። ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያዎቹ 39 መጻሕፍት የተጻፉት ክርስቶስ ከመወለዱ የተወሰኑ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ሲሆን በአብዛኛው የተጻፉት በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው። የጻፏቸው በወቅቱ የነበሩ የታመኑ አይሁዳውያን ወይም እስራኤላውያን ናቸው። ይኸኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ብዙውን ጊዜ ብሉይ ኪዳን እየተባለ ይጠራል። የመጨረሻዎቹን 27 መጻሕፍት በግሪክኛ የጻፏቸው ክርስቲያኖች ሲሆኑ አዲስ ኪዳን በመባል በሰፊው ይታወቃሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ማስረጃም ሆነ በጣም ጥንታዊ የሆኑት ወጎች እንደሚጠቁሙት እነዚህ 66 መጻሕፍት የተጻፉት ግብጽ ኃያል ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ ሮም የዓለም ኃያል መንግሥት እስከ ነበረችበት ዘመን ባሉት 1,600 ዓመታት ውስጥ ነው።

የተረፈው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው

2. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ መጻፍ ሲጀመር እስራኤላውያን የነበሩበት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? (ለ) በተመሳሳይ ወቅት ተዘጋጅተው የነበሩት ሌሎች የጽሑፍ ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?

2 ከዛሬ 3,000 ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ መጻፍ ሲጀመር እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ ከነበሩት ብዙ ብሔራት መካከል አንድ ትንሽ ብሔር ነበረች። በዙሪያቸው የነበሩት ብሔራት ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ወንድና ሴት አማልክት ሲያመልኩ የእነርሱ አምላክ ይሖዋ ነበር። በዚያ ዘመን ሃይማኖታዊ ጽሑፍ ያዘጋጁት እስራኤላውያን ብቻ አልነበሩም። ሌሎቹ ብሔራትም በሃይማኖታዊና ብሔራዊ ቅርሶቻቸው ላይ ያተኮሩ የጽሑፍ ሥራዎች ነበሯቸው። ለምሳሌ ያህል ከሜሶጶጣሚያ የተገኘውና በአካዲያውያን ቋንቋ የሠፈረው የጊልጋሜሽ አፈ ታሪክና በኡጋሪያውያን ቋንቋ (በዛሬዋ ሶርያ ሰሜናዊ ክፍል ይነገር በነበረው ቋንቋ) የተዘጋጀው የራስ ሻምራ ጽሑፍ በወቅቱ በጣም ታዋቂ እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚያ ዘመን ከነበሩት ብዙ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መካከል ዚ አድሞኒሽንስ ኦቭ ኢፑ-ዌር እንዲሁም ዘ ፕሮፌሲ ኦቭ ኔፈር-ሮሁ የተባሉት በግብጻውያን ቋንቋ የተዘጋጁት ጽሑፎች፣ በሱሜሪያውያን ቋንቋ ለተለያዩ አማልክት የተገጠሙት ዜማዎች እንዲሁም በአካዲያውያን ቋንቋ የተዘጋጁ የትንቢት ጽሑፎች ይገኙባቸው ነበር።1

3. በተመሳሳይ ወቅት በመካከለኛው ምሥራቅ ከተዘጋጁት ሌሎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎች መጽሐፍ ቅዱስን የሚለየው ምንድን ነው?

3 ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ የመካከለኛው ምሥራቅ የጽሑፍ ሥራዎች አንድ ዓይነት ዕጣ ገጥሟቸዋል። ጽሑፎቹ ተረስተዋል፣ ሌላው ቀርቶ ተጽፈውበት የነበረውም ቋንቋ ሞቷል። አርኪኦሎጂስቶችና የቋንቋዎችን አመጣጥ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች እነዚህ ቋንቋዎች እንደነበሩና እንዴት እንደሚነበቡ ያወቁት አሁን በቅርቡ ነው። በአንጻሩ ግን በመጀመሪያ የተጻፉት የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እስከ ዘመናችን ቆይተው በሰፊው ለንባብ በቅተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የዕብራይስጥ መጻሕፍት ከዚያ ቀደም ከነበሩት የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች የተቀዱ ሳይሆኑ አይቀሩም የሚሉ ምሁራን አልጠፉም። ይሁን እንጂ ከእነዚያ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መካከል አብዛኞቹ ሲጠፉ የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ተጠብቆ መቆየቱ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ የተለየ መጽሐፍ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

የቃሉ ባለአደራዎች

4. የመጽሐፍ ቅዱስን ሕልውና ጥርጣሬ ላይ የጣሉት የትኞቹ እስራኤላውያን የነበሩባቸው ከባድ ችግሮች ናቸው?

4 በሰብዓዊ አመለካከት ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ የገጠሙትን ፈተናዎች ሁሉ ያልፋል ብሎ ማሰብ ዘበት ነበር። ለመጽሐፍ ቅዱስ መገኘት ምክንያት የሆነው ብሔር የገጠመውን የከፋ ስደትና መራራ ተቃውሞ ላስተዋለ የመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ መቆየት ልዩ ትንግርት ነው። ከክርስቶስ መምጣት በፊት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን (“ብሉይ ኪዳን”ን) ያዘጋጁት አይሁዳውያን በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በጣም ትንሽ ብሔር ነበሩ። አንዱ በሌላው ላይ የበላይነት ለመቀዳጀት እርስ በርሳቸው በሚጎሻሸሙ ኃያላን የፖለቲካ መንግሥታት መሀል በሥጋት የሚኖሩ ሕዝቦች ነበሩ። እስራኤላውያን ሕልውናቸውን ለማቆየት እንደ ፍልስጤም፣ ሞዓብ፣ አሞን እንዲሁም ኤዶም ካሉት ብሔራት ጋር በየጊዜው ውጊያ ለመግጠም ተገደዋል። ዕብራውያኑ ለሁለት መንግሥት ተከፍለው በነበረበት ዘመንም ጨካኙ የአሦር አጼያዊ አገዛዝ የሰሜናዊውን መንግሥት ሙልጭ አድርጎ ያጠፋ ሲሆን ባቢሎናውያን ደግሞ የደቡቡን መንግሥት በመደምሰስ ሕዝቡን በምርኮ ወስደዋል፤ ከእነዚህ መካከል ቀሪዎቹ ከምርኮ የተመለሱት ከ70 ዓመታት በኋላ ነበር።

5, 6. ዕብራውያን ልዩ ሕዝቦች በነበሩበት ወቅት ሕልውናቸውን ስጋት ላይ የጣሉ ምን ሙከራዎች ተደርገው ነበር?

5 እንዲያውም በእስራኤላውያን ላይ የዘር ማጥፋት ሙከራም ተደርጎ እንደነበር የሚያሳዩ ታሪኮች አሉ። በሙሴ ዘመን ፈርዖን አዲስ የሚወለዱት ሕፃናት ወንዶች ከሆኑ እንዲገደሉ አዝዞ ነበር። ይህ ትእዛዝ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ውሎ ቢሆን ኖሮ ዕብራውያኑ ዘራቸው ጨርሶ ይጠፋ ነበር። (ዘጸአት 1:​15-22) ከዚህ በኋላም ብዙ ጊዜ ቆይቶ አይሁዳውያኑ በፋርስ ግዛት ሥር በነበሩበት ጊዜ ጠላቶቻቸው እነርሱን ጨርሶ ለማጥፋት የሚያስችል ሕግ እንዲወጣ ለማድረግ ሴራ ጠንስሰውባቸዋል። (አስቴር 3:​1-5) አይሁዳውያኑ የዚ​­ህን ሴራ መክሸፍ እስከዛሬም ድረስ የፑሪም በዓል ብለው ያከብሩታል።

6 ከዚያም በኋላ ቢሆን አይሁዳውያኑ በሶርያ ግዛት ሥር ወድቀው ሳለ ንጉሥ አንጢኦከስ 4ኛ የግሪክን ባሕል እንዲከተሉና የግሪክን አማልክት እንዲያመልኩ በማስገደድ ብሔሩን በግሪካውያን አስተሳሰብ ለመቅረጽ ታግሎ ነበር። እርሱም ቢሆን አልተሳካለትም። አይሁዳውያኑ ጨርሰው መጥፋታቸው ወይም በሌሎቹ ብሔሮች መዋጣቸው ቀርቶ ጭራሽ በዙሪያቸው የነበሩት አብዛኛዎቹ ብሔራት ተራ በተራ ከዓለም መድረክ ሲጠፉ እነርሱ ተርፈዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችም ከእነርሱ ጋር ሊተርፉ ችለዋል።

7, 8. በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው መከራ የመጽሐፍ ቅዱስን ሕልውና ስጋት ላይ የጣለው እንዴት ነው?

7 ሁለተኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል (“አዲስ ኪዳን”) ያዘጋጁት ክርስቲያኖችም እንዲሁ ግፍ የተፈጸመባቸው ወገኖች ነበሩ። መሪያቸው ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ተገድሏል። ከእርሱ ሞት በኋላ በነበሩት ዓመታት በጳለስጢና ምድር የነበሩት የአይሁድ ባለ ሥልጣኖች የክርስቲያኖችን እንቅስቃሴ ለማፈን ሞክረዋል። ክርስትና ወደ ሌሎች አገሮች እየተስፋፋ ሲሄድ አይሁዳውያኑ የክርስቲያኖችን የሚስዮናዊነት ሥራ ለመገደብ በማሰብ ክርስቲያኖችን ማደኑን ተያያዙት።​—⁠ሥራ 5:​27, 28፤ 7:​58-60፤ 11:​19-21፤ 13:​45፤ 14:​19፤ 18:​5, 6

8 ስለ ክርስቲያኖች ብዙም ግድ የማይሰጣቸው የሮማውያን ባለሥልጣኖች አመለካከት በኔሮ ዘመነ መንግሥት ተለውጧል። ታሲተስ ይህ ጨካኝ ንጉሠ ነገሥት በክርስቲያኖች ላይ ስለፈጸመው “አሰቃቂ ቅጣት” እንደ ጀብድ አድርጎ ተናግሮለታል። ከእርሱ ዘመን አንስቶ ክርስቲያን መሆን በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ሆኖ ነበር።2 በ303 እዘአ ደግሞ ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅላጥያን መጽሐፍ ቅዱስን በቀጥታ የሚጻረር ተግባር ፈጽሟል። * ክርስትናን ለማጥፋት በማሰብ የተገኙት የክርስትና መጽሐፍ ቅዱሶች በሙሉ እንዲቃጠሉ የሚል ትእዛዝ አውጥቶ ነበር።3

9. አይሁዳውያንንም ሆነ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የተደረጉት ዘመቻዎች ተሳክተው ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ምን ይሆን ነበር?

9 እነዚህ የጭቆናና የዘር ማጥፋት ዘመቻዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ሕልውና ስጋት ላይ የሚጥሉ ጥቃቶች ነበሩ። አይሁዶች የፍልስጤማውያንና የሞዓባውያን ዕጣ ደርሶባቸው ቢሆን ኖሮ ወይም ደግሞ በመጀመሪያ አይሁዳውያን ከዚያም የሮማ ባለ ሥልጣኖች ክርስትናን ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት ሰምሮላቸው ቢሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስን ሊጽፍና ተንከባክቦ ሊያቆየው የሚችል ማን ይገኝ ነበር? የሚያስደስተው ግን መጽሐፍ ቅዱስን በባለአደራነት የተቀበሉትን ወገኖች ማለትም በመጀመሪያ አይሁዶችን በኋላ ደግሞ ክርስቲያኖችን ጨርሶ ማጥፋት ስላልተቻለ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ አሁን ድረስ ተጠብቆ ሊቆይ ችሏል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን ሕልውና ባይሆንም እንኳ ንጽሕናውን ትልቅ ሥጋት ላይ የሚጥል ሌላ አደገኛ ሁኔታ ነበር።

ስህተት ሊገኝባቸው የሚችሉ ቅጂዎች

10. መጽሐፍ ቅዱስ ከጅምሩ ተጠብቆ ሊቆይ የቻለው እንዴት ነው?

10 ቀደም ሲል ከጠቀስናቸውና ከጊዜ በኋላ ከተረሱ ጥንታዊ የጽሑፍ ሥራዎች መካከል ብዙዎቹ በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ወይም በጠንካራ የሸክላ ጽላት ላይ የተጻፉ ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንደዚያ አልነበረም። በመጀመሪያ የተጻፈው በፓፒረስ ወይም በብራና ላይ ሲሆን እነዚህ ደግሞ ከድንጋዩና ከሸክላው አንጻር ሲታዩ በቀላሉ ሊበላሹ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። በመሆኑም የመጀመሪያዎቹ ጸሐፊዎች ያዘጋጁአቸው ቅጂዎች ከጠፉ ዘመን የላቸውም። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዛሬ ተጠብቆ ሊቆይ የቻለው እንዴት ነው? በብዙ ድካም በእጅ የተገለበጡ ብዙ ሺህ ቅጂዎች ተዘጋጅተው ስለ ነበር ነው። የኅትመት መሣሪያዎች ባልተፈለሰፉበት በዚያ ዘመን መጻሕፍት የሚዘጋጁበት ሌላ ዘዴ አልነበረም።

11. ጽሑፎች በእጅ ሲገለበጡ ምን ነገር መከሰቱ አይቀርም?

11 ይሁን እንጂ በእጅ መገልበጥ ደግሞ የራሱ የሆነ አደጋ አለው። ታዋቂ አርኪኦሎጂስት የሆኑትና በብሪታንያው ቤተ መዘክር ውስጥ ዐቃቤ መጻሕፍት ሆነው የሚሠሩት ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል:- “አንድን ረጅም የሥነ ጽሑፍ ሥራ ሙሉ በሙሉ ያለምንም ስህተት መገልበጥ የሚችል የሰው እጅና አእምሮ እስካሁን ድረስ አልተገኘም። . . . ስህተቶች እንደሚገኙ ግልጽ ነው።”4 አንድ በእጅ የተገለበጠ ቅጂ ስህተት ካለው ሌላ ቅጂ ለማዘጋጀት ከዚህ ቅጂ በቀጥታ በሚገለበጥበት ጊዜ ስህተቱ ይደገማል። በረጅም የጊዜ ሂደት ውስጥ ብዙ ቅጂዎች ሲዘጋጁ በሰብዓዊ ድክመት የተነሳ በርከት ያሉ ስህተቶች ተሠርተዋል።

12, 13. የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠብቆ የማቆየቱን ኃላፊነት የወሰዱት እነማን ነበሩ?

12 በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ከመዘጋጀታቸው አንጻር ሲታይ የማባዛቱ ሥራ በመጽሐፉ ይዘት ላይ ፈጽሞ ሊስተዋል የማይችል ለውጥ እንዳልተደረገ እንዴት እናውቃለን? ለምሳሌ ያህል የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ ማለትም ‘ብሉይ ኪዳንን’ ተመልከት። በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ አይሁዳውያኑ በምርኮ ከቆዩባት ከባቢሎን ሲመለሱ ሶፌሪም በመባል የሚታወቁ ዕብራውያን ምሁሮች ማለትም “ጻፎች” የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ የመንከባከቡን ሥራ በኃላፊነት ወሰዱና በጋራም ሆነ በግል ለሚከናወነው የአምልኮ ሥርዓት የሚያገለግሉ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎችን የማዘጋጀቱን ሥራ ጀመሩ። እነዚህ ጠንካራ ውስጣዊ ግፊት የነበራቸው በሙያው የተካኑ ወንዶች ሲሆኑ ሥራቸውም ከፍተኛ ጥራት ነበረው።

13 ከሰባተኛው እስከ አሥረኛው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ባለው ጊዜ ውስጥ በሶፌሪሞች እግር የተተኩት ደግሞ ማሶሬቶች ናቸው። ስማቸውን ያገኙት “ባሕል” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ነው። በመሠረቱ እነርሱም ራሳቸው ጥንታዊውን የዕብራይስጥ ጽሑፍ ጠብቀው የማቆየት ተልእኮ የተሰጣቸው ጻፎች ነበሩ። ማሶሬቶች እጅግ ጠንቃቆች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል አንድ ጸሐፊ ለመገልበጥ እንደ ዋና ቅጂ አድርጎ የሚጠቀምበት ጽሑፍ ትክክለኛነቱ በሚገባ የተረጋገጠ መሆን ያለበት ሲሆን ምንም ነገር በቃሉ አስታውሶ መገልበጥ አይፈቀድለትም። ከመጻፉ በፊት እያንዳንዱን ፊደል ማረጋገጥ ነበረበት።5 ፕሮፌሰር ኖርማን ኬ ጎትዋልድ እንዲህ ሲሉ ዘግበዋል:- “አዲሶቹ የእጅ ግልባጭ ቅጂዎች በሙሉ እንደገና ተነብበው ስህተት የተገኘባቸው ቅጂዎች ጨርሶ እንዲወገዱ የሚጠይቀው የረቢዎች መስፈርት ሥራቸውን በምን ዓይነት ጥንቃቄ እንዳከናወኑ ይጠቁማል።”6

14. ሶፌሪሞችና ማሶሬቶች የሠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን የመገልበጥ ሥራ ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ያስቻለው የትኛው ግኝት ነው?

14 የሶፌሪሞችና የማሶሬቶች ጽሑፉን እየገለበጡ የማስተላለፍ ሥራ ምን ያህል ትክክለኛ ነበር? በጣም ጥንታዊ ይባል የነበረው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂ በአሥረኛው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የተዘጋጀ ስለነበር እስከ 1947 ድረስ ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት አስቸጋሪ ነበር። ይሁን እንጂ በ1947 በሙት ባሕር አቅራቢያ በሚገኙ ዋሻዎች ውስጥ የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ አካል የሆኑ አንዳንድ ክፍሎች ጨምሮ በጣም ጥንታዊ የሆኑ ቅጂዎች ቁርጥራጭ ተገኝቷል። አንዳንዶቹ ቁርጥራጮች ከክርስቶስ ዘመን በፊት የተዘጋጁ ናቸው። ጽሑፎችን የመገልበጡ ሥራ ምን ያህል ትክክለኛ እንደነበር ለማረጋገጥ ምሁራኑ እነዚህን ቅጂዎች በእጅ ካሉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ጋር አወዳድረዋል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ?

15. (ሀ) በሙት ባሕር የተገኘውን የኢሳይያስ ጥቅልል ጥንታዊ ቅጂና የማሶሬቶችን ጽሑፍ በማወዳደር ምን ውጤት ተገኝቷል? (ለ) በሙት ባሕር የተገኙት አንዳንድ ጥንታዊ ቅጂዎች በተወሰነ መጠን የአቀማመጥ ለውጥ ማሳየታቸውን በመመልከት የምንደርስበት መደምደሚያ ምን ሊሆን ይገባል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

15 ከተገኙት ጥንታዊ ሥራዎች መካከል አንዱ ሙሉው የኢሳይያስ መጽሐፍ ሲሆን ዛሬ በእጃችን ከሚገኘው የማሶሬቶች መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ጋር ያለው ስምምነት እጅግ የሚያስገርም ነው። ፕሮፌሰር ሚለር ባሮውስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “[በቅርቡ በተገኘው] የቅዱስ ማርቆስ የኢሳይያስ ጥቅልል እና በማሶሬቶች ጽሑፍ መካከል ያሉት ብዙዎቹ ልዩነቶች ሲገለበጥ የተፈጠሩ ስህተቶች ናቸው ለማለት ይቻላል። ከዚህ በተረፈ ግን በጥቅሉ ሲታይ በመካከለኛው ዘመን ከተዘጋጁት ቅጂዎች ጋር ድንቅ ስምምነት አለ። ይህን ያህል ዕድሜ ካለው ቅጂ ጋር እንዲህ ዓይነት ስምምነት መኖሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግረው የመጡት ቅጂዎች በአጠቃላይ ሲታይ ትክክለኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።”7 ባሮውስ አክለው እንዲህ ብለዋል:- “ይህን የሚያክሉ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት አልፈውም በጽሑፉ ላይ የተደረገው ለውጥ እጅግ ጥቂት መሆኑ የሚያስገርም ነው።” *

16, 17. (ሀ) የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ይዘት እንዳልተዛባ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ይዘት በሚመለከት ምን ተናግረዋል?

16 ክርስቲያኖች በግሪክኛ ወደጻፉትና አዲስ ኪዳን እየተባለ ወደሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መለስ ስንል ደግሞ ገልባጮቹ በሙያው ከፍተኛ ሥልጠና እንደነበራቸው የተካኑ ሶፌሪሞች ሳይሆኑ ተሰጥኦ የነበራቸው አማተሮች ይመስላሉ። ሥራቸውን ያከናወኑት ከባለ ሥልጣናቱ ቅጣት ይደርስብናል የሚል ሥጋት እያለባቸውም ቢሆን እንኳ አክብደው ተመልክተውታል። ዛሬ በእጃችን ላይ ያለው ጽሑፍ የመጀመሪያዎቹ ጸሐፊዎች ካሰፈሩት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ የሚያረጋግጡ ሁለት ማስረጃዎች አሉን። በመጀመሪያ ደረጃ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በተለየ መልኩ የግሪኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መጀመሪያ ከተጻፈበት ጊዜ ጋር በጣም የሚቀራረቡ በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች አሉን። እንዲያውም አንዱ የዮሐንስ ወንጌል ቁራጭ የተዘጋጀው በሁለተኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ሲሆን ዮሐንስ ወንጌሉን ጽፎበታል ተብሎ ከሚታሰብበት ጊዜ 50 ዓመት ከማይሞላ ጊዜ በኋላ ማለት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እስከ ዛሬ ድረስ የቆዩት በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች በብዛት መገኘታቸው የጽሑፉን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ጠንካራ ማስረጃዎች ናቸው።

17 ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን ይህን ጉዳይ በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “የመጽሐፍ ቅዱሱ ይዘት የተረጋገጠ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በተለይ ደግሞ የአዲስ ኪዳን። በእጅ የተገለበጡ የአዲስ ኪዳን ጥንታዊ ቅጂዎች፣ ከእነዚህ ቅጂዎች የተሠሩት የመጀመሪያ ትርጉሞች እንዲሁም የጥንቶቹ የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች ጠቅሰው የጻፏቸው ሐሳቦች በጣም ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ አጠራጣሪ የነበሩት ምንባቦች ትክክለኛ አቀማመጥ ሳይቀር ከእነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች መካከል በአንዱ ወይም በሌላው ውስጥ ተጠቅሶ ስለሚገኝ አስተማማኝነቱ ተጨባጭ ነው። በዓለም ውስጥ እንዲህ ሊባልለት የሚችል ሌላ ጥንታዊ መጽሐፍ ጨርሶ ሊገኝ አይችልም።”10

ሕዝቦችና ቋንቋዎቻቸው

18, 19. መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ብቻ ተወስኖ ያልቀረው እንዴት ነው?

18 መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸው የመጀመሪያ ቋንቋዎች ራሳቸው ከጊዜ በኋላ ለሕልውናው እንቅፋት ሆነዋል። የመጀመሪያዎቹ 39 መጻሕፍት በአብዛኛው የተጻፉት በእስራኤላውያን ቋንቋ በዕብራይስጥ ነው። ይሁን እንጂ የዕብራይስጥ ቋንቋ በሰፊው የሚሠራበት ቋንቋ አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ቋንቋ ብቻ ተወስኖ ቢቀር ኖሮ ተጽዕኖ የሚያሳድረው በአይሁድ ብሔርና ይህን ቋንቋ ማንበብ በተማሩ ጥቂት የባዕድ አገር ሰዎች ላይ ብቻ ይሆን ነበር። ይሁን እንጂ በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በግብጽ እስክንድርያ ለሚኖሩት ዕብራውያን ሲባል የዕብራይስጡን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወደ ግሪክኛ የመተርጎም ሥራ ተጀመረ። ግሪክኛ በወቅቱ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ሆኖ ነበር። በዚህ መንገድ አይሁዳዊ ያልሆኑት ሰዎችም የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያገኙበት አጋጣሚ ተከፈተ።

19 ሁለተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚጻፍበት ጊዜ ሲደርስም ግሪክኛ በሰፊው የሚነገር ቋንቋ ስለነበረ የመጨረሻዎቹ 27 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በዚሁ ቋንቋ ተጽፈዋል። ይሁን እንጂ ሁሉም ሰው የግሪክኛ ቋንቋ ይችላል ማለት አልነበረም። በመሆኑም የዕብራይስጡም ሆነ የግሪክኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ቀደም ባሉት በእነዚያ መቶ ዘመናት ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በሚግባቡባቸው እንደ ሲሪያክ፣ ኮፕቲክ፣ አርመን፣ ጆርጂያ፣ ጎቲክና ግዕዝ ባሉት ቋንቋዎች እየተተረጎሙ ብቅ ማለት ጀመሩ። የሮማ ግዛት ኦፊሴላዊ ቋንቋ ላቲን ስለነበርና በዚህ ቋንቋ ብዙ ትርጉሞች ተዘጋጅተው ስለነበረ አንድ “እውቅና የተሰጠው ትርጉም” እንዲዘጋጅ ተደረገ። ይህ ትርጉም በ405 እዘአ የተጠናቀቀ ሲሆን ቩልጌት (ትርጓሜው “የታወቀ” ወይም “የተለመደ” ማለት ነው) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

20, 21. የመጽሐፍ ቅዱስን ህልውና የተፈታተኑት እንቅፋቶች ምን ነበሩ? እነዚህንስ መወጣት የተቻለው እንዴት ነው?

20 ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ወደዚህኛው የመጀመሪያ መቶ ዘመን የደረሰው ብዙ እንቅፋቶችን ተቋቁሞ ነው። መጽሐፉን ያዘጋጁት በጥላቻ በሚያዋክባቸው ዓለም ውስጥ በመከራ ይኖሩ የነበሩ የተናቁና ይሰደዱ የነበሩ አናሳ ወገኖቸ ነበሩ። ቅጂዎች ሲገለበጡ በቀላሉ ብዙ ሐሳብ ሊዛባ ይችል ነበር፤ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነት ሁኔታ አልተፈጠረም። ከዚህም በላይ የተወሰነ ቋንቋ በሚናገሩ ሰዎች ዘንድ ብቻ ተወስኖ ከመቅረትም አምልጧል።

21 የመጽሐፍ ቅዱስ ህልውና ይህ ተፈታታኝ ሁኔታ የገጠመው ለምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ‘ዓለምም በሞላው በክፉው ተይዟል’ ይላል። (1 ዮሐንስ 5:​19) ከዚህ አንጻር ዓለም በጽሑፍ ለሰፈረው እውነት ጠላት ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፤ ደግሞም ጠላት ሆኗል። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ችግር ያልገጠማቸው ሌሎች ብዙ ትናንሽ ጽሑፎች ደብዛቸው ጠፍቶ ተረስተው ሲቀሩ መጽሐፍ ቅዱስ የተረፈው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህም ጥያቄ ቢሆን መልስ ይሰጣል። እንዲህ ይላል:- “የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ጴጥሮስ 1:​25) መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም የአምላክ ቃል ከሆነ የትኛውም የሰው ኃይል ሊያጠፋው አይችልም። ደግሞም ይህ እውነታ እስከዚህ 20ኛ መቶ ዘመን ድረስ በግልጽ ታይቷል።

22. በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጀመሪያ ላይ ምን ለውጥ ተከሰተ?

22 ይሁን እንጂ በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በአዲስ መልክ የተሰነዘረ ጥቃት ብቅ ያለ ሲሆን ይህ በአውሮፓውያን ታሪክም ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ዲዮቅላጥያን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን በሙሉ ለማጥፋት ከሞከረ ከአሥር ዓመታት በኋላ የአገዛዙ ፖሊሲ ተለወጠና “ክርስትና” ሕጋዊ እውቅና አገኘ። ከአሥራ ሁለት ዓመታት በኋላም ማለትም በ325 እዘአ አንድ የሮማ ንጉሠ ነገሥት በኒቂያ የተካሄደውን “የክርስትና” ጉባኤ በሊቀ መንበርነት መርቷል። ይህ ጥሩ ጅምር መስሎ የሚታይ ሁኔታ ለመጽሐፍ ቅዱስ አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ “ዓ.ዓ.” እና “ዓ.ም.” ከሚሉት የተለመዱ መግለጫዎች ይልቅ ይበልጥ ትክክል የሆኑትን “እዘአ” (እንደ ዘመናችን አቆጣጠር) እና “ከዘአበ” (ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት) የሚሉትን መግለጫዎች ተጠቅመናል።

^ አን.15 በሙት ባሕር የተገኙ ጥንታዊ ቅጂዎች በሙሉ አሁን ካሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ ማለት አይደለም። አንዳንዶቹ ብዙ የይዘት ለውጥ ይታይባቸዋል። ይሁን እንጂ የጥቅሱ መሠረታዊ ትርጉም ተዛብቷል ማለት አይደለም። በአሜሪካ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ፓትሪክ ደብልዩ ሰኬሃን እንደገለጹት አብዛኛዎቹ ለውጦች “[የመጽሐፍ ቅዱሱ ጥቅስ] መሠረተ ሐሳቡን ሳይለቅ ያንኑ መልእክት ሰፋ አድርጎ ለመግለጽ የተደረጉ ለውጦች ናቸው። . . . ከዚህ ሥራ በስተጀርባ የተንጸባረቀው እንደ ቅዱስ ተደርጎ ለሚታየው ጽሑፍ ከፍተኛ አክብሮታዊ ፍርሃት የማሳየትና (እንደ እኛ አገላለጽ) መጽሐፍ ቅዱስን በመጽሐፍ ቅዱስ የማብራራት ዝንባሌ ነው።”8

ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- “እርግጠኛ መሆን የማይቻልባቸው ነገሮች መኖራቸው ባይካድም ዛሬ በእጃችን ላይ ያለው ጽሑፍ በጥቅሉ ወደ ሦስት ሺህ ከሚጠጉ ዓመታት በፊት የኖሩትን (አንዳንዶቹ) ጸሐፊዎች ትክክለኛ ቃላት በበቂ ሁኔታ የሚያንጸባርቁ መሆናቸው የማይታበል ሐቅ ነው። በይዘቱ ላይ የተደረጉት በርከት ያሉ ለውጦች ብሉይ ኪዳን የያዘውን መልእክት ጠቃሚነት ይቀንሱብናል የሚል ስጋት ሊያድርብን አይገባም።”9

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠ ነው

የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት ምን ያህል በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑን ለመገንዘብ ከጥንት ወደ ዘመናችን ከደረሰ ሌላ ቀደምት የግሪክ ወይም የሮም ጽሑፍ ጋር ማወዳደራችን ብቻ ይበቃል። እንዲያውም ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ከተጠናቀቁ በኋላ የተጻፉ ናቸው። በግሪካውያንም ሆነ በሮማውያን ላይ የተሰነዘረ የዘር ማጥፋት ሙከራ እንደነበር የሚገልጽ ምንም ዘገባ የለም፤ የጽሑፍ ሥራቸውም ቢሆን እስከዚህ ዘመን እንዳይደርስ የሚፈታተን ስደት አልገጠመውም። ይሁንና ፕሮፌሰር ኤፍ ኤፍ ብሩስ ምን አስተያየት እንደሰጡ ተመልከት:-

“ጋሊክ ዎር (በ58 እና በ50 ከዘአበ መካከል የተዘጋጀ ነው) የተባለው የቄሣር ጽሑፍ የተወሰኑ ቅጂዎች እጃችን ላይ የሚገኙ ቢሆንም በጥሩ ሁኔታ ላይ ያሉት ዘጠኝ ወይም አሥር ብቻ ናቸው፤ ከእነርሱም መካከል በጣም ጥንታዊ ነው የሚባለው ከቄሣር ዘመን 900 ዓመት በኋላ የተዘጋጀ ነው።

“ሊቪ ስለ ሮማውያን የዘገበውን ታሪክ ከያዙት 142 መጻሕፍት (59 ከዘአበ-17 እዘአ) መካከል የተረፉት 35 ብቻ ናቸው፤ ስለ እነዚህም ቢሆን ማወቅ የቻልነው ከሃያ ከማይበልጡ ጥንታዊ ቅጂዎች ሲሆን ከእነዚህ መካከል በአራተኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀው አንዱ ብቻ ነው። እርሱም የያዘው ከመጽሐፍ 3-6 ያሉትን ቁጥርጥራጮች ብቻ ነው።

“ታሲተስ ከጻፋቸው (100 ዓ.ም. ገደማ) ሂስትሪስ የተባሉ አሥራ አራት መጻሕፍት መካከል የተረፉት አራትና አንድ ሌላ ግማሽ ብቻ ናቸው። አናልስ ከተባሉት አሥራ ስድስት መጻሕፍቱ መካከል ደግሞ አሥሩ ሙሉ በሙሉ እንዲሁም ሁለቱ በከፊል ተርፈዋል። እስከ ዛሬ የቆዩት የእነዚህ ሁለት ታላላቅ የታሪክ ሥራዎቹ ይዘት ሙሉ በሙሉ በሁለት ጥንታዊ ጽሑፎች ላይ የተመካ ሲሆን አንዱ በዘጠነኛው፣ ሁለተኛው ደግሞ በአሥራ አንደኛው መቶ ዘመን የተዘጋጁ ናቸው። . . .

“ስለ ቱሳይዳደስ (460-400 ከዘአበ ገደማ) ታሪክ የምናነበው ከስምንት ጥንታዊ ቅጂዎች ሲሆን በጣም ቀደምት ነው የሚባለው በ900 ዓ.ም. ገደማ የተዘጋጀና ሌሎቹ ጥቂት የፓፒረስ ቁርጥራጮች ደግሞ በክርስትና ዘመን መጀመሪያ ላይ የተዘጋጁ ናቸው።

“የሄሮዶተስን (488-428 ከዘአበ) ታሪክ ሁኔታም ከዚሁ ጋር ይመሳሰላል። ይሁንና የሄሮዶተስንም ሆነ የቱሳይዳደስን ሥራ የሚዘግቡት ጥንታዊ ጽሑፎች ከመጀመሪያው ቅጂ 1,300 ዓመታት ካለፉ በኋላ የተዘጋጁ ናቸውና ለእኛ ምንም ትርጉም ቢኖራቸው የታሪኩ ትክክለኛነት አጠራጣሪ ነው የሚል ክርክር ቢነሣ ከጥንቶቹ ምሁራን መካከል ለዚህ ሐሳብ ጆሮውን የሚሰጥ አይገኝም።”​—⁠ዘ ቡክስ ኤንድ ዘ ፓርችመንትስ፣ ገጽ 180

ተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አካል የሆኑ በሺህ የሚቆጠሩ ጥንታዊ ቅጂዎች መኖራቸውን ከዚህ ሁኔታ ጋር አወዳድር። እንዲያውም ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጥንታዊ ቅጂዎች መካከል አንዳንዶቹ የመጀመሪያው ጽሑፍ ከተዘጋጀ በኋላ ከአንድ መቶ ዓመት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ የተዘጋጁ ናቸው።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዕብራውያን ዘወትር ከሌሎች ኃያላን ብሔራት ዛቻ የሚሰነዘርባቸው አነስተኛ ብሔር ነበሩ። እነዚህ ጥንታዊ የተቀረጹ ምስሎች እስራኤላውያን በአሦራውያን ተማርከው ሲወሰዱ ያሳያሉ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኅትመት መሣሪያዎች ከመፈልሰፋቸው በፊት ቅዱሳን ጽሑፎች የሚገለበጡት በእጅ ነበር

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኔሮ ክርስቲያን መሆን በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል እንዲሆን ደንግጎ ነበር

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሙት ባሕር በተገኘው የኢሳይያስ ጥቅልል ላይ የተደረገው ጥናት እንዳረጋገጠው ከ1,000 የሚበልጡ ዓመታት ቢያልፉም መጽሐፉ መሠረታዊ ለውጥ አልተገኘበትም

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅላጥያን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ቀርቷል