በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች

ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች

ምዕራፍ 9

ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች

የሰው ልጆች ስለ ወደፊቱ ጊዜ በእርግጠኛነት መተንበይ አይችሉም። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለመተንበይ ያደረጓቸው ጥረቶች በተደጋጋሚ ጊዜያት ከሽፈዋል። በመሆኑም ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችን የያዘ መጽሐፍ ትኩረታችንን እንደሚስበው የታወቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ነው።

1. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችን መዝግቦ መገኘቱ ምን ያረጋግጣል?

ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በጥቃቅን ዝርዝር ጉዳዮች ሳይቀር በትክክል ፍጻሜያቸውን በማግኘታቸው ተቺዎች ትንቢቶቹ የተጻፉት ከተፈጸሙ በኋላ ነው ብለዋል። ይሁን እንጂ ይህ አባባል ከእውነት የራቀ ነው። አምላክ ሁሉን ማድረግ የሚችል ስለሆነ ትንቢት ለመናገር ምንም አያዳግተውም። (ኢሳይያስ 41:​21-26፤ 42:​8, 9፤ 46:​8-10) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት እንደ ተጻፉ የሚያረጋግጥ እንጂ ከተፈጸሙ በኋላ የተጻፉ መሆናቸውን የሚያሳይ አይደለም። ከዚህ ቀጥሎ ፍጻሜያቸውን ያገኙ አንዳንድ አስገራሚ ትንቢቶችን እንመለከታለን። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ እንጂ የሰው ቃል እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ይሆነናል።

በባቢሎን በግዞት መቀመጥ

2, 3. ንጉሥ ሕዝቅያስ በቤቱና በግዛቱ ያለውን ንብረት ሁሉ ከባቢሎን ለመጡት መልእክቶች እንዲያሳይ ያደረገው ነገር ምን ነበር?

2 ሕዝቅያስ 30 ለሚያክሉ ዓመታት በኢየሩሳሌም ላይ ነግሦአል። በ740 ከዘአበ በሰሜን በኩል የምታጎራብተው እስራኤል በአሦራውያን እጅ ስትጠፋ ተመልክቷል። በ732 ከዘአበ አሦራውያን ኢየሩሳሌምን ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ ከሽፎ ወራሪው ሠራዊት ከፍተኛ ውድቀት በደረሰበት ጊዜም የአምላክን የማዳን ኃይል አይቷል።​—⁠ኢሳይያስ 37:​33-38

3 ከዚያም ከባቢሎን ንጉሥ ከመሮዳክ ባልዳን የተላኩ መልእክተኞች ወደ ሕዝቅያስ መጡ። እንዲሁ ከላይ ሲታይ መልእክተኞቹ የመጡት ሕዝቅያስ ከገጠመው ከባድ ሕመም በማገገሙ እንኳን ደስ ያለህ ለማለት ይመስሉ ነበር። ይሁንና መሮዳክ ባልዳን የዓለም ኃያል የሆነችውን አሦርን ለመውጋት ሕዝቅያስ አጋር ይሆነኛል ብሎ ሳያስብ አልቀረም። ሕዝቅያስ እንዲህ ዓይነቱን አሳብ ለማጥፋት ከመሞከር ይልቅ ጭራሽ ባቢሎናውያኑ ጎብኚዎች በቤቱና በግዛቱ ያለውን ነገር ሁሉ እንዲያዩ አደረገ። ምናልባት እርሱም አሦራውያን ድንገት ተመልሰው ቢመጡ የሚረዳኝ ያስፈልጋል ብሎ አስቦ ይሆናል።​—⁠ኢሳይያስ 39:​1, 2

4. ኢሳይያስ ትንቢት የተናገረው ሕዝቅያስ የፈጸመው ስህተት የሚያስከትለውን የትኛውን አሳዛኝ ውጤት አስመልክቶ ነበር?

4 ሕዝቅያስ ያደረገው ነገር ጥበብ የጎደለው መሆኑን በወቅቱ የነበረው ታዋቂ ነቢይ ኢሳይያስ አስተውሎ ነበር። ሕዝቅያስ አስተማማኝ ጥበቃ ማግኘት የሚችለው ከባቢሎን ሳይሆን ከይሖዋ እንደሆነ ኢሳይያስ ያውቅ ስለነበር ሀብቱን ለባቢሎናውያን ማሳየቱ አሳዛኝ ውጤት እንደሚያስከትልበት ነግሮታል። ኢሳይያስም “እነሆ፣ በቤትህ ያለው ነገር ሁሉ፣ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል” አለው። ይሖዋም “ምንም አይቀርም” ሲል ተናገረ።​—⁠ኢሳይያስ 39:​5, 6

5, 6. (ሀ) ኤርምያስ የኢሳይያስን ትንቢት የሚያረጋግጥ ምን ነገር ተናግሯል? (ለ) የኢሳይያስና የኤርምያስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው?

5 በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኛል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ሆኖ ታይቷቸው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከአንድ መቶ ዓመታት በኋላ ሁኔታው ተለወጠ። ባቢሎን አሦርን በመተካት የዓለም ኃያል መንግሥት ስትሆን ይሁዳ ደግሞ ሃይማኖታዊ ሁኔታዋ በጣም ስላዘቀጠ አምላክ በረከቱን ከእርሷ ወስዶ ነበር። በዚህ ጊዜ ኤርምያስ የሚባል ሌላ ነቢይ በመንፈስ ተነሳስቶ ኢሳይያስ የተናገረውን ማስጠንቀቂያ ደግሞ ተናገረ። ኤርምያስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በዚህችም ምድር በሚቀመጡባትም ሰዎች . . . [ባቢሎናውያንን] አመጣባቸዋለሁ፤ . . . ይችም ምድር ሁሉ ባድማና መደነቂያ ትሆናለች፤ እነዚህም አሕዛብ ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ።”​—⁠ኤርምያስ 25:​9, 11

6 ኤርምያስ ይህንን ትንቢት ከተናገረ ከአራት ዓመት በኋላ ባቢሎናውያን ይሁዳን የግዛታቸው ክፍል አድርገው ጠቀለሏት። ከዚያ ሦስት ዓመት ቆይቶ በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ የተወሰነ ሀብትና ጥቂት ምርኮኞችን ወደ ባቢሎን ወሰዱ። ከስምንት ዓመታት በኋላ ደግሞ ይሁዳ በማመፅዋ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በድጋሚ ተወረረች። በዚህ ጊዜ ከተማዋም ሆነች ቤተ መቅደሷ በሙሉ ወደሙ። ኢሳይያስና ኤርምያስ አስቀድመው እንደተናገሩት ሀብቷም ሆነ አይሁዳውያኑ ራሳቸው ርቃ ወደምትገኘው ወደ ባቢሎን ተወሰዱ።​—⁠2 ዜና መዋዕል 36:​6, 7, 12, 13, 17-21

7. ኢሳይያስና ኤርምያስ ኢየሩሳሌምን አስመልክቶ የተናገሯቸውን ትንቢቶች ፍጻሜ በሚመለከት አርኪኦሎጂ ምን ማረጋገጫ ይሰጣል?

7 ዚ አርኪኦሎጂካል ኢንሳይክለፒዲያ ኦቭ ዘ ሆሊ ላንድ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው አስፈሪ የነበረው የባቢሎናውያን ጥቃት ሲያበቃ “ከተማዋ [ኢየሩሳሌም] እንዳልነበረች ሆና ወድማለች።”1 አርኪኦሎጂስቱ ደብልዩ ኤፍ ኦልብራይት እንዲህ ብለዋል:- “በይሁዳ አካባቢ የተደረጉት ቁፋሮዎችና የምድር ገጽ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት የይሁዳ ከተሞች ከለዳውያን ባደረጓቸው ሁለት ወረራዎች ሙሉ በሙሉ መውደም ብቻ ሳይሆን ለብዙ ትውልድ ባድማ ሆነው ቀርተዋል። እንዲያውም ባብዛኛው ከዚያ በኋላ ጭራሽ ሰው አልኖረባቸውም።”2 በመሆኑም አርኪኦሎጂ የዚህን ትንቢት አስገራሚ ፍጻሜ ያረጋግጣል።

የጢሮስ ዕጣ

8, 9. ሕዝቅኤል በጢሮስ ላይ ምን ትንቢት ተናግሯል?

8 በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ትንቢቶችን የመዘገበው ሌላው ጸሐፊ ደግሞ ሕዝቅኤል ነው። ከሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ አንስቶ እስከ ስድስተኛው መቶ ዘመን ድረስ ማለትም ኢየሩሳሌም ከመጥፋቷ በፊት በነበሩት ዓመታትና አይሁዳውያን በባቢሎን በምርኮ በነበሩባቸው የመጀመሪያ አሥርተ ዓመታት ወቅት ትንቢት ይናገር ነበር። በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ተቺዎችም እንኳ ሳይቀሩ መጽሐፉ በዚያ ዘመን አካባቢ እንደተጻፈ ይስማማሉ።

9 ሕዝቅኤል የእስራኤል ሰሜናዊ አጎራባች የነበረችውን የጢሮስን ጥፋት በሚመለከት አንድ አስገራሚ ትንቢት መዝግቧል። በመጀመሪያ የአምላክ ሕዝቦች ወዳጅ የነበረችው ጢሮስ በኋላ ተገልብጣ ጠላት ሆናባቸው ነበር። (1 ነገሥት 5:​1-9፤ መዝሙር 83:​2-8) እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ጢሮስ ሆይ፣ እነሆ፣ እኔ በአንቺ ላይ ነኝ፣ ባሕርም ሞገድዋን እንደምታወጣ እንዲሁ ብዙ ሕዝብን አወጣብሻለሁ። የጢሮስንም ቅጥሮች ያጠፋሉ ግንቦችዋንም ያፈርሳሉ፤ ትቢያዋንም ከእርስዋ እፍቃለሁ፣ የተራቆተ ድንጋይም አደርጋታለሁ። . . . ድንጋይሽንና እንጨትሽን መሬትሽንም በባሕር ውስጥ ይጥላሉ።”​—⁠ሕዝቅኤል 26:​3, 4, 12

10-12. የሕዝቅኤል ትንቢት በመጨረሻ ፍጻሜውን ያገኘው መቼ ነው? እንዴትስ?

10 ይህ በእርግጥ ተፈጽሟልን? ሕዝቅኤል ይህን ትንቢት ከተናገረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ጢሮስን ተቆጣጠረ። (ሕዝቅኤል 29:​17, 18) ይሁንና ጢሮስን የተቆጣጠረው በቀላሉ አልነበረም። የጢሮስ ከተማ ገሚሱ ክፍል (አሮጌው ጢሮስ እየተባለ የሚጠራው) የተቆረቆረው በዋናው የብስ ላይ ቢሆንም ገሚሱ ክፍል የሚገኘው ከውኃው ዳርቻ 800 ሜትር ርቆ በሚገኝ ደሴት ላይ ነበር። ናቡከደነፆር ሙሉ በሙሉ ከተማዋን በቁጥጥሩ ሥር ከማድረጉ በፊት ደሴቲቱን ለ13 ዓመታት ከብቦ ቆይቷል።

11 ይሁንና የሕዝቅኤል ትንቢት አንድ በአንድ ፍጻሜውን ያገኘው በ332 ከዘአበ ነበር። በዚህ ወቅት የመቄዶንያው ባለ ድል ታላቁ እስክንድር እስያን በመውረር ላይ ነበር። ጢሮስ ደሴት ላይ በመሆኗ እጁዋን ሳትሰጥ ቀርታ ነበር። ታላቁ እስክንድር የኋላ ኋላ አደገኛ ጠላት ሆና ልትነሣበት የምትችለውን ጢሮስን ትቶ መሄድ አልፈለገም። በሌላ በኩል ደግሞ ናቡከደነፆር እንዳደረገው ጢሮስን ከብቦ ብዙ ዓመታት ማጥፋትም አልፈለገም።

12 ታዲያ ይህን ወታደራዊ ችግር የሚፈታው እንዴት ይሆን? ወታደሮቹ ተሸጋግረው በደሴቲቱ ከተማ ላይ ጥቃት መሰንዘር እንዲችሉ ደሴቲቱን ከዋናው የብስ የሚያገናኝ መሻገሪያ ደለደለ። ሆኖም ይህን መሻገሪያ ለመደልደል በምን እንደተጠቀመ ልብ በል። ዚ ኢንሳይክለፒዲያ አሜሪካና “በ332 በዋናው የብስ ላይ ያለችውን ከተማ ካጠፋ በኋላ ፍርስራሿን ባሕር ውስጥ በመደልደል ደሴቲቱን ከዋናው የብስ ጋር የሚያገናኝ ሰፊ የየብስ መሻገሪያ ሠራ” ሲል ዘግቧል። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አጭር ከሆነ ከበባ በኋላ የደሴቲቱ ከተማ ተደመሰሰች። ከዚህም በላይ የሕዝቅኤል ትንቢት አንድ በአንድ ፍጻሜውን አግኝቷል። የጥንቷ ጢሮስ ‘ድንጋይዋ፣ እንጨትዋና መሬቷ’ ሳይቀር ‘በባሕር ውስጥ ወድቀዋል።’

13. አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ተጓዥ የጥንቷ ጢሮስ የነበረችበትን ቦታ የገለጸው እንዴት አድርጎ ነው?

13 አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ተጓዥ በእርሱ ዘመን ከጢሮስ ከተማ የተረፈው ነገር ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ሰሎሞንና የእስራኤል ነቢያት ከሚያውቋት ከጥንቷ ጢሮስ የተረፈ ነገር ቢኖር በተራራው ጥግ ያለው ከድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራው መቃብርና የመሠረት ድንጋይ ብቻ ነው። . . . ታላቁ እስክንድር የደሴቷን ከተማ በከበበ ጊዜ በደሴቲቱና በዋናው የብስ መካከል ያለውን ውኃ በመደልደል የባሕር ሰርጥ ያደረጋት ደሴት እንኳ ከመስቀል ጦርነቶች በፊት ስላለው ዘመን የሚዘክር ምንም ቅሪት አይገኝባትም። በአንጻራዊ ሁኔታ ስትታይ አዲስ የሆነችው የዛሬዋ ከተማ የምትገኘው በአንድ ወቅት ደሴት በነበረው ሰሜናዊ ክፍል ላይ ሲሆን የቀረው ግን ምን እንደነበረበት እንኳ መለየት በሚያስቸግር ፍርስራሽ የተሞላ ነው።”3

የባቢሎን ተራ

14, 15. ኢሳይያስና ኤርምያስ ባቢሎንን በሚመለከት ምን ትንቢት መዝግበዋል?

14 አይሁዳውያን በባቢሎን አገዛዝ ሥር እንደሚወድቁ የተናገረው ነቢዩ ኢሳይያስ በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ሌላ አስገራሚ ነገር ተንብዮ ነበር። ይህም ባቢሎን ሙሉ በሙሉ እንደምትደመሰስ የሚገልጽ ነበር። ግልጽ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ተንብዮአል። “እነሆ፣ . . . ሜዶናውያንን በላያቸው አስነሣለሁ። እግዚአብሔርም ሰዶምንና ገሞራን ባፈረሰ ጊዜ እንደነበረው፣ የመንግሥታት ክብር የከለዳውያንም ጌጥ ባቢሎን እንዲሁ ትሆናለች። ለዘላለም የሚቀመጥባት አይገኝም፣ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ሰው አይኖርባትም።”​—⁠ኢሳይያስ 13:​17-20

15 ነቢዩ ኤርምያስም እንዲሁ ባቢሎን እንደምትወድቅ ተንብዮአል። ይህ ከብዙ ዓመታት በኋላ ፍጻሜውን የሚያገኝ ትንቢት ነበር። የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ ዝርዝር ጉዳይም ጨምሮ ተናግሯል:- “ድርቅ በውኆችዋ ላይ ይሆናል እነርሱም ይደርቃሉ። . . . የባቢሎን ኃያላት መዋጋትን ትተዋል በአምባዎቻቸውም ውስጥ ተቀምጠዋል፤ ኃይላቸውም ጠፍቷል [“ደርቋል፣” NW]።”​—⁠ኤርምያስ 50:​38፤ 51:​30

16. ባቢሎን ድል የተደረገችው መቼ ነበር? በማንስ?

16 በ539 ከዘአበ ብርቱው የፋርስ ገዥ ቂሮስ በሜዶናውያን ጦር እየታገዘ በከተማይቱ ላይ በዘመተ ጊዜ የባቢሎን የዓለም ኃያልነት አከተመ። ይሁን እንጂ ቂሮስ የገጠመው ነገር ቀላል ነበር ማለት አይደለም። ባቢሎን በጣም ግዙፍ በሆነ ቅጥር ተከብባለች፤ የምትደፈር አትመስልም። ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝም የሚያልፈው በከተማዋ መሀል በመሆኑ ለከተማዋ መከላከያ የማይናቅ አስተዋጽኦ ነበረው።

17, 18. (ሀ) ‘የባቢሎን ውኃዎች ደርቀዋል’ ለማለት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ‘የባቢሎን ኃያላን መዋጋት የተዉት’ እንዴት ነው?

17 ቂሮስ ይህን ሁኔታ እንዴት እንደተወጣው ሲገልጽ ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶተስ እንዲህ ብሏል:- “የተወሰኑ ወታደሮችን ውኃው ወደ ከተማ በሚገባበት ቦታ ላይ፣ ሌሎቹን ደግሞ ውኃው ከከተማዋ በሚወጣበት ቦታ ካቆመ በኋላ ውኃው ጎድሎ ለመሻገር አመቺ ሲሆን ወዲያው ወንዙን አቋርጠው ወደ ከተማይቱ እንዲዘልቁ ትእዛዝ ሰጠ። . . . የኤፍራጥስንም ወንዝ በቦይ አድርጎ ረግረግ ወደነበረው ጎድጓዳ ስፍራ [በቀድሞው የባቢሎን ገዥ ወደ ተቆፈረ ሰው ሠራሽ ሐይቅ] እንዲፈስ አደረገው። ወንዙ በጣም ስለጎደለ በዚያ መሻገር ቀላል ሊሆን ችሏል። በዚህ ጊዜ ለዚሁ ዓላማ ሲባል በባቢሎን ወንዝ አጠገብ የቀሩት የፋርስ ወታደሮች ውኃው ቀንሶ እስከ ጭን በሚደርሰው ወንዝ አቋርጠው ወደ ከተማይቱ ዘለቁ።”4

18 ኤርምያስና ኢሳይያስ እንዳስጠነቀቁት ከተማይቱ በዚህ መንገድ ወደቀች። ነገር ግን ይህ ትንቢት አንድ በአንድ ፍጻሜውን እንዳገኘ ልብ በል። ቃል በቃል ‘ድርቅ በውኆችዋ ላይ ሆኗል፤ እነርሱም ደርቀዋል።’ ቂሮስ ወደ ከተማዋ እንዲዘልቅ ያስቻለው የኤፍራጥስ ወንዝ መጉደል ነው። ኤርምያስ አስቀድሞ እንዳስጠነቀቀው ‘የባቢሎን ኃያላን መዋጋት ትተው ነበርን?’ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ግሪካውያኑ ታሪክ ጸሐፊዎች ሄሮዶተስና ዜኖፎን እንደመዘገቡት የፋርስ ሰዎች ወረራውን ባካሄዱ ጊዜ ባቢሎናውያኑ ድል ያለ ድግስ ደግሰው በመደሰት ላይ ነበሩ።5 የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ፊደላት የተቀረጸውና የናቦኒደስ ዜና ታሪክ በመባል የሚታወቀው ኦፊሴላዊው ዘገባ እንደሚገልጸው የቂሮስ ወታደሮች ወደ ባቢሎን የገቡት “ያለ ጦርነት” ነው። ይህ ሲባል ያን ያህል ከባድ ውጊያ ሳይደረግ ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው።6 ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው የባቢሎን ኃያላን ከተማቸውን ለመጠበቅ ብዙም ያደረጉት ነገር አልነበረም።

19. ባቢሎን ‘ዳግመኛ የሚቀመጥባት አይገኝም’ የሚለው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷልን? አብራራ።

19 ባቢሎንን “ዳግመኛ የሚቀመጥባት አይገኝም” የሚለውን ትንቢት በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ይህ ትንቢት ከ539 ከዘአበ በኋላ ወዲያውኑ ፍጻሜውን አላገኘም። ይሁን እንጂ ትንቢቱ ምንም ዝንፍ ሳይል ተፈጽሟል። ባቢሎን ከወደቀችበት ጊዜ አንስቶ በ478 ከዘአበ በአሕሻዊሮስ እስከጠፋችበት ጊዜ ድረስ የበርካታ ዓመፆች መናኸሪያ ሆና ቆይታለች። በአራተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ታላቁ እስክንድር መልሶ ሊገነባት አቅዶ የነበረ ቢሆንም ሥራው እምብዛም ሳይገፋ እርሱ ሞተ። ከዚያ ጊዜ በኋላ ከተማዋ እያሽቆለቆለች ሄደች። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ሳይቀር በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ዛሬ ከጥንቷ ባቢሎን የቀረ ነገር ቢኖር በኢራቅ የሚገኘው የፍርስራሽ ክምር ብቻ ነው። ፍርስራሿ በከፊል ቢጠገን እንኳ የጎብኚዎች መስዕብ ትሆን እንደሆነ እንጂ ሞቅ ደመቅ ያለች ከተማ አትሆንም። ባድማ የሆነው አካባቢዋ በእርሷ ላይ የተነገረው ትንቢት የመጨረሻ ፍጻሜውን እንዳገኘ ያረጋግጣል።

የዓለም ኃይሎች መፈራረቅ

20, 21. ዳንኤል የዓለም ኃያላንን መፈራረቅ በተመለከተ ምን ትንቢታዊ ራእይ ተመልክቷል? ይህስ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

20 አይሁዳውያን በባቢሎን በምርኮ በነበሩበት በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ዳንኤል የሚባል ሌላ ነቢይ በመንፈስ ተነሳስቶ ወደፊት የዓለም ሁኔታ ምን መልክ እንደሚኖረው የሚጠቁሙ አስገራሚ ራእይዎችን መዝግቧል። ዳንኤል ከእነዚህ ራእይዎች በአንዱ ውስጥ አንዳቸው ሌላውን እያስለቀቁ ወደ ዓለም መድረክ ብቅ ስላሉ ምሳሌያዊ እንስሳት ገልጿል። አንድ መልአክ እንደገለጸው እነዚህ እንስሳት ከዚያ ጊዜ አንስቶ የሚፈራረቁትን የዓለም ኃይሎች የሚያመለክቱ ናቸው። ስለ መጨረሻዎቹ ሁለት እንስሳት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ባየኸው በአውራው በግ ላይ የነበሩ ሁለቱ ቀንዶች እነርሱ የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ናቸው። አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው፤ በዓይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው። እርሱም በተሰበረ ጊዜ በእርሱ ፋንታ አራቱ እንደ ተነሱ፣ እንዲሁ ከወገኑ አራት መንግሥታት ­ይነሣሉ፣ ነገር ግን በኃይል አይተካከሉትም።”​—⁠ዳንኤል 8:​20-22

21 ይህ ትንቢታዊ መግለጫ በትክክል ፍጻሜውን አግኝቷል። የባቢሎናውያን አገዛዝ በሜዶ ፋርስ ሲገለበጥ ከ200 ዓመታት በኋላ ደግሞ ሜዶ ፋርስ የዓለም ኃይል ሆኖ ብቅ ላለው ለግሪክ ቦታውን ለቅቋል። የግሪክ መንግሥት የሚመራው ‘በታላቁ ቀንድ’ ማለትም በታላቁ እስክንድር ነበር። ይሁን እንጂ እርሱ ከሞተ በኋላ ጄኔራሎች ለሥልጣን መሻኮት ጀመሩ። በመጨረሻም ሰፊ የነበረው ግዛቱ በአራት ትናንሽ ግዛቶች ማለትም ‘በአራት መንግሥታት’ ተከፋፈለ።

22. ከዓለም ኃያላን መፈራረቅ ጋር በተያያዘ ስለ የትኛው ተጨማሪ የዓለም ኃይል ትንቢት ተነግሯል?

22 በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይም ገና ከረጅም ጊዜ በኋላ ፍጻሜውን ማግኘት የነበረበት ተመሳሳይ ትንቢት ተገልጿል። የባቢሎናውያን የዓለም ኃይል በአንበሳ፣ የፋርስ በድብ እንዲሁም የግሪክ ጀርባዋ ላይ አራት ክንፎች ባሏት ባለ አራት ራስ ነብር ተመስለዋል። ከዚያም ዳንኤል ‘የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች አሥር ቀንዶችም የነበሩዋት’ አውሬ ተመለከተ። (ዳንኤል 7:​2-7) አራተኛዋ አውሬ ጥላ የሆነችለት ኃያል የነበረው የሮም አገዛዝ ብቅ ማለት የጀመረው ዳንኤል ትንቢቱን ከጻፈ ሦስት መቶ ዘመናት ገደማ ቆይቶ ነው።

23. በዳንኤል ትንቢት ውስጥ የተገለጸችው አራተኛዋ አውሬ ‘ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ የተለየች’ የሆነችው በምን መንገድ ነው?

23 መልአኩ ሮምን በሚመለከት ትንቢት ተናግሯል:- “አራተኛይቱ አውሬ በምድር ላይ አራተኛ መንግሥት ትሆናለች እርሱም ከመንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፣ ምድሪቱንም ሁሉ ይበላል፣ ይረግጣታል ያደቅቃትማል።” (ዳንኤል 7:​23) ኤች ጂ ዌልስ ኤ ፖኬት ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል:- “በሁለተኛውና በአንደኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በምዕራቡ ዓለም የበላይነትን ተቀዳጅቶ ብቅ ያለው ይህ አዲሱ የሮም ኃይል እስካሁን ድረስ በሰለጠነው ዓለም ከታዩት ከየትኞቹም ታላላቅ ግዛቶች ሁሉ በበርካታ መንገዶች የተለየ ነው።”7 አጀማመሩ እንደ ሪፐብሊካዊ አገዛዝ ቢሆንም በመጨረሻው ንጉሣዊ አገዛዝ ሆኗል። እንደ ሌሎቹ ግዛቶች በአንድ ድል አድራጊ የተፈጠረ ሳይሆን ለብዙ መቶ ዘመናት የማያቋርጥ እድገት ሲያደርግ የኖረ መንግሥት ነው። ከዚያ ቀደም ከነበሩት መንግሥታት የግዛት ዘመን ሁሉ ለሚበልጥ ጊዜ የዘለቀና ግዛቱም ከየትኛውም መንግሥት የበለጠ ስፋት የሚያካልል ነበር።

24, 25. (ሀ) የአውሬው አሥር ቀንዶች ብቅ ያሉት እንዴት ነው? (ለ) ዳንኤል በአውሬው ቀንዶች መካከል ስለሚደረገው ስለየትኛው ትግል አስቀድሞ ተመልክቷል?

24 ይሁን እንጂ ስለዚህ ግዙፍ የሆነ አውሬ አሥር ቀንዶችስ ምን ማለት ይቻላል? መልአኩ እንዲህ ብሏል:- “አሥሩም ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡ አሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነርሱም በኋላ ሌላ ይነሣል፣ እርሱም ከፊተኞች የተለየ ይሆናል፣ ሦስቱን ነገሥታት ያዋርዳል።” (ዳንኤል 7:​24) ይህስ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

25 በአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የሮማ ግዛት እየተዳከመ መሄድ ሲጀምር ወዲያውኑ በሌላ የዓለም ኃይል አልተተካም። ከዚህ ይልቅ ወደተለያዩ “አሥር መንግሥት” ተከፋፈለ። በመጨረሻም የብሪታንያ ግዛት ተቀናቃኝ የነበሩትን ሦስቱን የስፔይን፣ የፈረንሳይና የኔዘርላንድስን መንግሥታት ድል በማድረግ ዋና የዓለም ኃይል ሆነ። በዚህ መንገድ አዲስ የመጣው ‘ቀንድ’ ሌሎቹን “ሦስቱን ነገሥታት” አዋርዷቸዋል።

የዳንኤል ትንቢቶች​—⁠ከክንውኑ በኋላ የተጻፉ ናቸውን?

26. ተቺዎች ዳንኤል መጽሐፉን ጽፏል የሚሉት በየትኛው ጊዜ ነው? ለምንስ?

26 መጽሐፍ ቅዱስ የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈው በስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እንደሆነ ይጠቁመናል። ይሁን እንጂ ትንቢቶቹ ፍጹም ትክክለኛ የሆነ ፍጻሜያቸውን ከማግኘታቸው የተነሣ ተቺዎች ትንቢቱ የተጻፈው በትንቢቱ ውስጥ ያሉት በርካታዎቹ ነገሮች ከተፈጸሙ በኋላ በ165 ከዘአበ ገደማ መሆን አለበት ብለዋል።8 እንዲህ ለማለት ያበቃቸው ብቸኛውና እውነተኛው ምክንያት የዳንኤል ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ቢሆንም የዳንኤል ትንቢት ተጻፈ የሚባልበት ይህ ዘመን እንደ ትክክለኛ ወቅት እንደሆነ ተቆጥሮ በብዙ የማመሳከሪያ ጽሑፎች ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል።

27, 28. የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈው በ165 ከዘአበ እንዳልሆነ የሚያረጋግጡት አንዳንድ ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?

27 ይሁንና ይህን አባባል የሚቃረኑትን የሚከተሉትን እውነታዎች ማጤን ይኖርብናል። በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፉ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በተዘጋጁ እንደ መቃባውያን የመጀመሪያ መጽሐፍ ባሉት የአይሁዳውያን የጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቅሶ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ በግሪክ ሰፕቱጀንት ትርጉም ውስጥ ተካትቷል። የዚህ ትርጉም ሥራ የተጀመረው በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነው።9 በሦስተኛ ደረጃ የዳንኤል መጽሐፍ ቅጂ ቁርጥራጮች በሙት ባሕር ከተገኙት ጥቅልሎች መካከል በተደጋጋሚ የሚታይ ሲሆን እነዚህ ቁርጥራጮች ደግሞ በ100 ከዘአበ የተዘጋጁ እንደሆኑ ይታመናል።10 የዳንኤል መጽሐፍ ተጻፈ በሚባልበት ዘመን በሰፊው የሚታወቅና ከፍተኛ አክብሮት ያተረፈ ሆኖ ነበር። ይህም ተቺዎቹ ከሚሉት ዘመን ከረጅም ጊዜ በፊት እንደተጻፈ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

28 ከዚህም በተጨማሪ ዳንኤል በሁለተኛው መቶ ዘመን የሚኖር ጸሐፊ ሊያውቃቸው የማይችላቸውን ታሪካዊ ሁኔታዎች ይዞ እናገኘዋለን። ከነዚህ መካከል ሊጠቀስ የሚገባው ባቢሎን በ539 ከዘአበ በወደቀች ጊዜ የተገደለው የባቢሎን ገዥ የብልጣሶር ጉዳይ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ስለ ባቢሎን መውደቅ መረጃ የምናገኝባቸው ጉልህ ምንጮች ሄሮዶተስ (አምስተኛው መቶ ዘመን)፣ ዜኖፎን (አምስተኛውና አራተኛው መቶ ዘመን) እንዲሁም ቤሮሰስ (ሦስተኛው መቶ ዘመን) ናቸው። ከእነርሱ መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ስለ ብልጣሶር የሚያውቁት ነገር የለም።11 ከእርሱ በፊት የነበሩት እነዚህ ጸሐፊዎች ሊያውቁ ያልቻሉትን ነገር በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበረ ጸሐፊ እንዴት ሊያውቅ ይችላል! በዳንኤል ምዕራፍ 5 ላይ ብልጣሶርን በሚመለከት የሰፈረው ታሪክ ዳንኤል ­መጽሐፉን የጻፈው እነዚህ ጸሐፊዎች የጽሑፍ ሥራዎቻቸውን ከማዘጋጀታቸው አስቀድሞ እንደሆነ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው። *

29. የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈው በውስጡ የያዛቸው ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ካገኙ በኋላ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?

29 በመጨረሻም በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ከ165 ከዘአበ ብዙ ቆይተው ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ ትንቢቶች ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል የሮማን መንግሥት በሚመለከት የተነገረውና ቀደም ሲል የጠቀስነው ትንቢት ይገኝበታል። ሌላው በጣም አስደናቂ ትንቢት ደግሞ ስለ መሲሑ ስለ ኢየሱስ መምጣት የሚናገረው ትንቢት ነው።

የመሲሑ መምጣት

30, 31. (ሀ) መሲሑ ስለሚገለጥበት ጊዜ የሚናገረው የትኛው የዳንኤል ትንቢት ነው? (ለ) በዳንኤል ትንቢት መሠረት መሲሑ የሚገለጥበትን ዓመት ማስላት የምንችለው እንዴት ነው?

30 ይህ ትንቢት ተመዝግቦ የሚገኘው በዳንኤል ምዕራፍ 9 ላይ ሲሆን እንዲህ ይነበባል:- “በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ [የዓመታት ሳምንታት ወይም 490 ዓመታት] ተቀጥሮአል።” * (ዳንኤል 9:​24 ዚ አምፕሊፋይድ ባይብል) በእነዚህ 490 ዓመታት ውስጥ የሚከናወነው ነገር ምንድን ነው? እንዲህ እናነባለን:- “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ ቅቡዕ [መምጣት] ድረስ ሰባት ሱባዔና [የዓመታት ሳምንታት] ስድሳ ሁለት ሱባዔ [የዓመታት ሳምንታት] ይሆናል።” (ዳንኤል 9:​25 ኤቢ) በመሆኑም ይህ ‘የተቀባው’ መሲሕ የሚመጣበትን ጊዜ የሚጠቁም ትንቢት ነው። ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

31 ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ‘ትእዛዝ የወጣው’ የፋርስ ንጉሥ በነበረው “በንጉሥ አርጤክስስ በሃያኛው ዓመት” ሲሆን ይህም በ455 ከዘአበ ነው። (ነህምያ 2:​1-9) 49ኛው ዓመት (7 የዓመታት ሳምንታት) ሲያበቃ ኢየሩሳሌም አብዛኛውን ክብሯን መልሳ አግኝታለች። ከ455 ከዘአበ ተነስተን ሙሉውን 483 ዓመታት (7 እና 62 የዓመታት ሳምንታት) ስንቆጥር ወደ 29 እዘአ እንደርሳለን። ይህ ደግሞ ‘ጢባሪዮስ ቄሣር የነገሠበት አሥራ አምስተኛ ዓመት’ ሲሆን ኢየሱስ በመጥምቁ ዮሐንስ የተጠመቀው በዚሁ ጊዜ ነበር። (ሉቃስ 3:​1) በዚህ ወቅት ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑ በይፋ ታውቆ ለአይሁድ ብሔር ምሥራቹን በመስበክ አገልግሎቱን ጀምሯል። (ማቴዎስ 3:​13-17፤ 4:​23) ‘ቅቡዕ’ ወይም መሲሕ የሆነው በዚህ ጊዜ ነበር።

32. በዳንኤል ትንቢት መሠረት የኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ለምን ያህል ጊዜ የሚዘልቅ ነው? ይህ ጊዜ ሲፈጸምስ ምን ነገር ይከናወናል?

32 ትንቢቱ በመጨመር እንዲህ ይላል:- “ከስድሳ ሁለት [የዓመታት] ሳምንትም በኋላ የተቀባው ይገደላል።” አክሎም “እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሳምንት [ሰባት ዓመታት] ያደርጋል፤ በሳምንቱም እኩሌታ መሥዋዕቱንና ቁርባኑን ያስቀራል።” (ዳንኤል 9:​26, 27, ኤቢ) ከዚህ ትንቢት ጋር በሚስማማ መንገድ ኢየሱስ የሄደው ወደ ‘ብዙዎች’ ማለትም ወደ ሥጋዊ አይሁዳውያን ብቻ ነበር። በተወሰነው የቅዱስ ጽሑፉ ክፍል ያምኑ ለነበሩት ነገር ግን ከዋናው የአይሁድ እምነት ተገንጥለው የራሳቸውን ወገን ለመሠረቱት ሳምራውያንም የሰበከባቸው ወቅቶች ነበሩ። ከዚያም ‘በሳምንቱ እኩሌታ’ ማለትም ለሦስት ዓመት ተኩል ከሰበከ በኋላ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ሰጠ፣ በሌላ አባባል ‘ተቆረጠ።’ ይህም የሙሴ ሕግ ከነመሥዋዕቱና ቁርባኑ ወደ ፍጻሜው እንደመጣ የሚያሳይ ነበር። (ገላትያ 3:​13, 24, 25) ­በመሆኑም ኢየሱስ በሞቱ ‘መሥዋዕቱና ቁርባኑ’ እንዲቀር አድርጓል።

33. ይሖዋ ትኩረቱን በአይሁዳውያን ላይ ብቻ አድርጎ የሚቆየው እስከ መቼ ነበር? ይህ ጊዜ እንዳበቃ ያሳየውስ ምንድን ነበር?

33 የሆነ ሆኖ አዲሱ የክርስቲያን ጉባኤ ለተጨማሪ ሦስት ዓመት ተኩል ለአይሁዳውያን ብቻና ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ለሚዛመዱት ሳምራውያን ሰብኳል። ይሁን እንጂ ሰባው የዓመታት ሳምንታት በ36 እዘአ ሲያበቁ ሐዋርያው ጴጥሮስ ከአሕዛብ ወገን ለነበረው ለቆርኔሌዎስ እንዲሰብክ መመሪያ ተሰጥቶታል። (ሥራ 10:​1-48) ከዚህ በኋላ ‘ከብዙዎች ጋር የተደረገው ቃል ኪዳን’ ለአይሁዳውያን ብቻ የተወሰነ መሆኑ ቀረ። ላልተገረዙትም አሕዛብ ጭምር መዳን ተሰበከላቸው።

34. ከዳንኤል ትንቢት ጋር በሚስማማ መንገድ ሥጋዊ እስራኤላውያን መሲሑን ለመቀበል አሻፈረን በማለታቸው ምን ደሶባቸዋል?

34 የአይሁድ ብሔር ኢየሱስን አልቀበልም በማለቱና እንዲገደል በማሴሩ ሮማውያን መጥተው በ70 እዘአ ኢየሩሳሌምን ሲያጠፉ ይሖዋ ሳያስጥላቸው ቀርቷል። በዚህ መንገድ የሚከተሉት የዳንኤል ቃላት ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል:- “የሚመጣውም ሌላው አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጎርፍ ይሆናል፣ እስከ መጨረሻም ድረስ በጦርነት ይሆናል።” (ዳንኤል 9:​26 ኤቢ) ይህ ሁለተኛው “አለቃ” ኢየሩሳሌምን በ70 እዘአ ያጠፋው ሮማዊው ጄኔራል ቲቶ ነው።

በመንፈስ አነሳሽነት የተነገረ ትንቢት

35. ስለ ኢየሱስ የተነገሩት የትኞቹ ተጨማሪ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል?

35 በዚህ መንገድ ዳንኤል ስለ ሰባው ሳምንታት የተናገረው ትንቢት በአስገራሚ ሁኔታ በትክክል ፍጻሜውን አግኝቷል። እርግጥ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙት ብዙዎቹ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ነው። ከእነዚህ መካከል በርከት ያሉትም ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ትንቢቶች ናቸው። ኢየሱስ የሚወለድበት ቦታ፣ ለአምላክ ቤት የሚኖረው ቅንዓት፣ የስብከት እንቅስቃሴው፣ በ30 ብር አልፎ እንደሚሰጥ፣ አሟሟቱ፣ በልብሱ ላይ ዕጣ መጣጣላቸውና የመሳሰሉት ዝርዝር ሁኔታዎች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በትንቢት ተነግረዋል። እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ያለ ምንም ጥርጥር ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ያረጋገጠ ሲሆን ትንቢቶቹም በመንፈስ አነሳሽነት የተነገሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ነበር።​—⁠ሚክያስ 5:​2፤ ሉቃስ 2:​1-7፤ ዘካርያስ 11:​12፤ 12:​10፤ ማቴዎስ 26:​15፤ 27:​35፤ መዝሙር 22:​18፤ 34:​20፤ ዮሐንስ 19:​33-37

36, 37. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ምን ነገር ያስተምረናል? ይህንንስ ማወቃችን ምን ትምክህት እንድናሳድር ያደርገናል?

36 መፈጸም የነበረባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በሙሉ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ሁሉም ነገሮች ልክ መጽሐፍ ቅዱስ በተናገረላቸው መሠረት ተፈጽመዋል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው። እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ይህን ያህል ትክክል ሊሆኑ የቻሉት ከበስተጀርባ ያለው ኃይል ከሰብዓዊ ጥበብ እጅግ የላቀ ነገር በመሆኑ ነው።

37 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዚያ ዘመን ፍጻሜያቸውን ያላገኙ ሌሎች ትንቢቶችም ይገኛሉ። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ትንቢቶች የሚፈጸሙት በዚህ በእኛ ዘመንና ገና ወደፊት በመሆኑ ነው። የጥንቶቹ ትንቢቶች አስተማማኝ ሆነው መገኘት እነዚህ ሌሎች ትንቢቶችም ያለምንም ጥርጥር እንደሚፈጸሙ ማረጋገጫ ይሆነናል። ደግሞም ይህ አባባል እውነት እንደሆነ በሚቀጥለው ምዕራፍ ውስጥ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.28 “ብሉይ ኪዳን ምን ያህል ተዓማኒነት አለው?” የሚለውን ምዕራፍ 4 አንቀጽ 16ና 17 ተመልከት።

^ አን.30 በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ በቅንፍ የተቀመጡት ሐሳቦች ተርጓሚው ነጥቡን ግልጽ ለማድረግ የጨመራቸው ናቸው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 133 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መፈጸም የነበረባቸው ትንቢቶች ሁሉ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ሁሉም ነገሮች ልክ መጽሐፍ ቅዱስ በተናገረላቸው መሠረት ተፈጽመዋል

[በገጽ 118 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ጨርሶ እንዳጠፋት አርኪኦሎጂስቶች ደርሰውበታል

[በገጽ 121 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዘመናችን ያለችው ጢሮስ ፎቶግራፍ። የእስራኤል ነቢያት ከሚያውቋት ጢሮስ አንዳች የቀረ ነገር የለም

[በገጽ 123 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንቷ ባቢሎን የነበረችበትን ቦታ የሚጎበኙ ሰዎች በከተማዋ ላይ የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን ስለማግኘቱ ምሥክሮች ናቸው

[በገጽ 126 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳንኤል የዓለም ኃያላንን መፈራረቅ በተመለከተ የተናገረው ትንቢት በትክክል ፍጻሜውን ከማግኘቱ የተነሣ የዘመናችን ተቺዎች ትንቢቱ የተጻፈው ነገሮቹ ከተፈጸሙ በኋላ ነው ብለው አስበዋል

ባቢሎን

ፋርስ

ግሪክ

ሮም

ብሪታንያ

[በገጽ 130 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳንኤል መሲሑ በእስራኤል የሚገለጥበትን ትክክለኛ ጊዜ በትንቢት ተናግሯል