በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንተ ራስህ ሲፈጸም ያየኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት

አንተ ራስህ ሲፈጸም ያየኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት

ምዕራፍ 10

አንተ ራስህ ሲፈጸም ያየኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት

ዛሬ ያሉት ሁኔታዎች ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት በፊት ከነበሩት በጣም የተለዩ የሆኑት ለምን ይሆን ብለህ አስበህ ታውቃለህ? አንዳንድ ነገሮች ተሻሽለዋል። ያኔ ሰው ይጨርሱ የነበሩት በሽታዎች ዛሬ በብዙ አገሮች ውስጥ በቀላሉ ይፈወሳሉ። በዛሬው ጊዜ ያለው የኑሮ ደረጃ አያት ቅድመ አያቶቻችን ፈጽሞ አልመውትም ሆነ አስበውት የማያውቁት ነው ለማለት ይቻላል። በአንጻሩ ደግሞ በዚህ በእኛ ዘመን እጅግ አስከፊ ጦርነቶችና በሰው ዘር ታሪክ ከደረሱት አሰቃቂ እልቂቶች ሁሉ የከፉ ድርጊቶች ታይተዋል። ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት፣ የአካባቢ መበከልና በዓለም ዙሪያ በብዛት ተከማችተው የሚገኙት የኑክሊየር፣ ባዮሎጂያዊና ኬሚካላዊ ጦር መሣሪያዎች የሰውን ልጅ ብልጽግና አልፎ ተርፎም ሕልውናውን ሥጋት ላይ ጥለውታል። ይህ ሃያኛው መቶ ዘመን ከቀደሙት መቶ ዘመናት ሁሉ ይህን ያህል የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?

1. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) (ሀ) ሃያኛው መቶ ዘመን ከዚያ ቀደም ከነበሩት መቶ ዘመናት የሚለየው እንዴት ነው? (ለ) ጊዜያችን ልዩ የሆነበትን ምክንያት እንድንገነዘብ የሚረዳን ምንድን ነው?

የዚህ ጥያቄ መልስ አንተ ራስህ ሲፈጸም ካየኸው አንድ አስገራሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር የተዛመደ ነው። ይህ ኢየሱስ ራሱ የተናገረው ትንቢት መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ በዓለም ላይ እጅግ አስገራሚ ለውጥ ሊካሄድ በተቃረበበት ዘመን ላይ እንደምንኖር የሚጠቁም ነው። ይህ ትንቢት ምንድን ነው? ፍጻሜውን እያገኘ እንዳለስ እንዴት እናውቃለን?

ታላቁ የኢየሱስ ትንቢት

2, 3. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን የጠየቁት ጥያቄ ምን ነበር? የሰጠውን መልስስ የት ላይ እናገኘዋለን?

2 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ኢየሱስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ደቀ መዛሙርቱ በኢየሩሳሌም ስለ ነበረው ድንቅ የቤተ መቅደስ ሕንጻ ይወያያሉ። በቤተ መቅደሱ ግዝፈትና ጥንካሬ ተደንቀው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፣ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።”​—⁠ማቴዎስ 24:​1, 2

3 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በዚህ አባባሉ ተገርመው መሆን አለበት። ደቀ መዛሙርቱ ትንሽ ቆየት ብለው መጡና ተጨማሪ ጥያቄ አቀረቡለት:- “ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ? የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ምንድን ነው?” (ማቴዎስ 24:​3 NW) ኢየሱስ የሰጠው መልስ በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 ውስጥ ይገኛል። እነዚሁ ነገሮች በማርቆስ ምዕራፍ 13 እና ሉቃስ ምዕራፍ 21 ውስጥም ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከተናገራቸው ትንቢቶች ሁሉ ይበልጥ በጣም አስፈላጊ ትንቢት ነው።

4. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያቀረቡት ጥያቄ የትኞቹን የተለያዩ ነገሮች የሚመለከት ነው?

4 እርግጥ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የጠየቁት ስለ አንድ ነገር ብቻ አልነበረም። በመጀመሪያ ያነሱት ጥያቄ “እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ?” የሚል ነው። በሌላ አባባል ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደስዋ የሚጠፉት መቼ ነው? ማለታቸው ነበር። ከዚህም በተጨማሪም ኢየሱስ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ በመሆን በሥልጣኑ መገኘቱንና የዚህ የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ መቅረቡን የሚያሳዩትን ምልክቶች ለማወቅ ፈልገው ነበር።

5. (ሀ) የኢየሱስ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር? ይሁን እንጂ የተናገራቸው ነገሮች ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት መቼ ነው? (ለ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ላነሱት ጥያቄ የሰጠውን መልስ የጀመረው እንዴት ነው?

5 የኢየሱስ መልስ እነዚህን ሁለት ነጥቦች ያካተተ ነበር። ኢየሱስ የተናገራቸው ብዙዎቹ ነገሮች በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው አሰቃቂ ጥፋት በፊት በነበሩት ዓመታት ውስጥ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። (ማቴዎስ 24:​4-22) ይሁን እንጂ ይህ ትንቢት በተለይ ለእኛ ዘመን ከዚያ የበለጠ ትርጉም ያዘለ ነው። ታዲያ ኢየሱስ ምን አለ? መልሱን የጀመረው በቁጥር 7 እና 8 ላይ ተመዝግበው በሚገኙት ቃላት ነበር:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፣ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።”

6. በማቴዎስ 24:​7, 8 ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት የትኛውን ተመሳሳይ ትንቢት ያስታውሱናል?

6 ኢየሱስ ሰማያዊ ንጉሥ ሆኖ በሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት ጊዜ በምድር ላይ ታላቅ ሁከት እንደሚሆን ግልጽ ነው። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ስለ አራቱ ፈረሰኞች የሚናገረው ከዚህ ጋር ተጓዳኝ የሆነው ትንቢት ይህ ሁኔታ እንደሚኖር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። (ራእይ 6:​1-8) ከእነዚህ ፈረሰኞች የመጀመሪያው የሚያመለክተው ድል አድራጊ ንጉሥ የሆነውን ኢየሱስን ነው። ሌሎቹ ጋላቢዎችና ፈረሶቻቸው ኢየሱስ መግዛት ሲጀምር በምድር ላይ የሚከሰቱትን እንደ ጦርነት፣ ረሃብና በተለያዩ ምክንያቶች በሞት መቀጨት የመሳሰሉትን ሁኔታዎች የሚያመለክቱ ናቸው። ዛሬ እነዚህ ሁለት ትንቢቶች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ነውን?

ጦርነት!

7. በራእይ ውስጥ በተገለጸው ሁለተኛ ፈረሰኛ በትንቢታዊ ሁኔታ የተመሰለው ነገር ምንድን ነው?

7 እስቲ እነዚህን ትንቢቶች በጥልቀት እንመርምር። በመጀመሪያ ኢየሱስ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል” ብሏል። ይህ ስለ ጦርነት የተነገረ ትንቢት ነው። ከአራቱ የራእይ ፈረሰኞች መካከል ሁለተኛውም እንዲሁ ጦርነትን የሚያመለክት ነው። እንዲህ እናነባለን:- “ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፣ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው።” (ራእይ 6:​4) የሰው ልጅ ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲዋጋ ኖሯል። ታዲያ እነዚህ ቃላት ለእኛ ዘመን ልዩ ትርጉም እንዲኖራቸው የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?

8. ጦርነት የምልክቱ ጉልህ ገጽታ ይሆናል ብለን የምንጠብቀው ለምንድን ነው?

8 ጦርነት ብቻውን ለኢየሱስ መገኘት ምልክት እንደማይሆን አስታውስ። ምልክቱ በጥቅሉ ሲታይ በተመሳሳይ ወቅት የሚፈጸሙትን በኢየሱስ ትንቢት ውስጥ የተዘረዘሩትን ክንውኖች ሁሉ ያቀፈ ነው። ይሁን እንጂ ከምልክቱ ገጽታዎች መካከል መጀመሪያ የተጠቀሰው ጦርነት በመሆኑ ትኩረታችንን በሚስብ አስገራሚ መንገድ ፍጻሜውን ያገኛል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። ጥንት የተደረጉት ጦርነቶች በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ከተደረጉት ጦርነቶች ጋር ፈጽሞ እንደማይተካከሉ የሚክድ ሰው አይኖርም።

9, 10. ጦርነትን በሚመለከት የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘት የጀመሩት እንዴት ነው?

9 ለምሳሌ ያህል ጥንት የተደረጉት ብዙዎቹ ጦርነቶች የቱንም ያህል ጭካኔ የሞላባቸውና ብዙ ውድመት ያስከተሉ ቢሆኑም እንኳ ያደረሱት ጥፋት በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ከታዩት ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ጋር መተካከል ቀርቶ ጨርሶ አይቀርቡም። እንዲያውም አንደኛው የዓለም ጦርነት ከብዙዎቹ አገሮች ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር የሚበልጥ የሰው ሕይወት ማለትም የ14 ሚልዮን ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። እውነትም “ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን” ተሰጥቶታል ማለት እንችላለን።

10 እንደ ትንቢቱ አገላለጽ ከሆነ በጦርነት ለተመሰለው ለሁለተኛው የራእይ ፈረሰኛ ‘ትልቅ ሰይፍ ተሰጥቶታል።’ ይህ ምን ማለት ነው? የጦር መሣሪያዎች ከበፊቱ እጅግ የከፋ እልቂት የሚያስከትሉ ይሆናሉ። በታንክ፣ በአውሮፕላን፣ ገዳይ በሆኑ መርዘኛ ጋዞች፣ በሰርጓጅ መርከቦች እንዲሁም ብዙ ኪሎ ሜትሮች በሚወነጨፉ ሚሳይሎች የታጠቀው የሰው ልጅ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መሰሉን በቀላሉ ለመግደል የሚያስችለው ደረጃ ላይ ደርሷል። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ደግሞ የራዲዮ መገናኛዎች፣ ራዳሮች፣ የተራቀቁ ጠብመንጃዎች፣ ባክቴሪያዊና ኬሚካላዊ የጦር መሣሪያዎች፣ እሳት የሚተፉ መሣሪያዎች፣ የናፓልም ጋዞች፣ አዳዲስ የቦምብ ዓይነቶች፣ አሕጉር አቋራጭ ተምዘግዛጊ ሚሳይሎች፣ ኑክሊየር ተሸካሚ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች፣ የተራቀቁ አውሮፕላኖች እንዲሁም ግዙፍ የጦር መርከቦች በመሠራታቸው ‘ታላቁ ሰይፍ’ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አውዳሚ ሆኗል።

“የምጥ ጣር መጀመሪያ”

11, 12. አንደኛው የዓለም ጦርነት “የምጥ ጣር መጀመሪያ” ብቻ ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

11 የኢየሱስ ትንቢት የመጀመሪያዎቹ ቁጥሮች የሚደመደሙት “እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው” በሚሉት ቃላት ነው። ይህ በተለይ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እውነት ሆኖ ታይቷል። የአንደኛው ዓለም ጦርነት በ1918 ማብቃቱ ያስገኘው ሰላም ላፍታም አልቆየም። ወዲያው በኢትዮጵያ፣ በሊቢያ፣ በስፔይን፣ በሩስያ፣ በሕንድና በሌሎችም አገሮች ላይ መለስተኛ መጠን የነበራቸው ነገር ግን አስከፊ ውጤት ያስከተሉ ወታደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል። ከዚያ በኋላ ደግሞ 50 ሚልዮን የሚያክሉ ወታደሮችንና ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈውና እጅግ አስፈሪ የነበረው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈንድቷል።

12 ከዚህም በላይ ጊዜያዊ የሰላም ስምምነቶች ቢደረጉና ጦርነቶች አንዳንዴ ጋብ ቢሉም ዛሬም የሰው ልጅ ከጦርነት አላረፈም። በ1987 ሪፖርት እንደተደረገው ከ1960 ወዲህ የተደረጉት 81 ትላልቅ ጦርነቶች የ12,555,000 ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ሕይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆነዋል። በ1987 የተካሄዱት ጦርነቶች መጠን ከዚያ ቀደም በነበረ በየትኛውም ዓመት ከተደረጉት ጦርነቶች ቁጥር እጅግ የሚበልጥ ነበር።1 ከዚህም በላይ ለጦር ዝግጅቶችና ወታደራዊ ወጪዎች በየዓመቱ የሚወጣው ጠቅላላ ገንዘብ ወደ 1,000,000,000,000 የአሜሪካ ዶላር የደረሰ ሲሆን ይህም የዓለምን ኤኮኖሚ የሚያዛባ ነው።2 ኢየሱስ ‘ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል’ ሲል የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም። ዳማው የጦርነት ፈረስ በምድር ላይ አስፈሪ ግልቢያውን ቀጥሏል። ይሁን እንጂ ስለ ምልክቱ ሁለተኛ ዘርፍ ምን ማለት ይቻላል?

የምግብ እጥረት!

13. ኢየሱስ ስለ የትኛው አሳዛኝ ሁኔታ አስቀድሞ ተናግሯል? ስለ ሦስተኛው የራእይ ፈረሰኛ የተሰጠው መግለጫስ የእርሱን ትንቢት የሚደግፈው እንዴት ነው?

13 ኢየሱስ “ራብም [“የምግብ እጥረትም።” NW] . . . በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል” ሲል ተንብዮአል። ይህ ሁኔታ በራእይ ላይ ከተገለጸው ሦስተኛ ፈረሰኛ ግልቢያ ጋር እንዴት እንደሚስማማ ልብ በል። ይህን ፈረሰኛ በሚመለከት እንዲህ የሚል ሐሳብ ተጠቅሶልናል:- “አየሁም፣ እነሆም፣ ጒራቻ ፈረስ ወጣ፣ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ:- አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፣ ዘይትንና ወይንንም አትጒዳ ሲል ሰማሁ።” (ራእይ 6:​5, 6) አዎን፣ ከባድ የምግብ እጥረት እንደሚኖር የሚያሳይ ነው!

14. የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረጉት ከ1914 ወዲህ የተከሰቱት የትኞቹ ታላላቅ ረሃቦች ናቸው?

14 አንዳንድ አገሮች ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በደረሱበት በዛሬው ጊዜ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ ነው ለማለት ይቻላልን? የመላውን ዓለም ሁኔታ መለስ ብሎ መቃኘት ለዚህ ጥያቄ የማያሻማ መልስ ይሰጠናል። ከታሪክ መረዳት እንደምንችለው የረሃብ መንስኤዎች ጦርነትና የተፈጥሮ አደጋዎች ናቸው። እንግዲያው ከአቅሙ በላይ የተፈጥሮ አደጋዎችንና ጦርነቶችን እያስተናገደ ያለው ይህ የእኛ መቶ ዘመን በተደጋጋሚ በረሃብ አለንጋ መገረፉ ምንም አያስገርምም። ከ1914 ወዲህ ብዙዎቹ የዓለም ክፍሎች በእነዚህ አደጋዎች ተጠቅተዋል። አንድ ሪፖርት እንደዘገበው ከ1914 ወዲህ ተራርቀው በሚገኙ በግሪክ፣ በኔዘርላንድስ፣ በቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት፣ በናይጄርያ፣ በቻድ፣ በቺሊ፣ በፔሩ፣ በባንግላዴሽ፣ በቤንጋል፣ በካምፖዲያ፣ በኢትዮጵያና በጃፓን 60 ከባድ ረሃቦች እንደደረሱ ተመዝግቧል።3 ከእነዚህ ረሃቦች መካከል አንዳንዶቹ በርከት ላሉ ዓመታት የዘለቁ ሲሆን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወትም ቀጥፈዋል።

15, 16. ዛሬ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተል ላይ ያለው ሌላው የምግብ እጥረት የትኛው ነው?

15 አስከፊ የረሃብ አደጋዎች ሲከሰቱ ጉዳዩ ሰፊ መወያያ ይሆንና ከጥቂት ጊዜ በኋላ ችግሩ ሲያልፍ ከረሃቡ የተረፉት ሰዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ወደ ቀድሞው ኑሯቸው ይመለሳሉ። ይሁን እንጂ በ20ኛው መቶ ዘመን ሌላ ዓይነት አስጊ የምግብ እጥረት ብቅ ብሏል። ይህ የዚያን ያክል የከፋ ባለመሆኑ ብዙውን ጊዜ በቸልታ ይታለፋል። ነገር ግን ችግሩ ከዓመት ዓመት ይቀጥላል። ይህ ከፕላኔታችን ነዋሪዎች መካከል አንድ አምስተኛውን የሚያጠቃ የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጦት ችግር ሲሆን በየዓመቱ ከ13 እስከ 18 ሚልዮን ለሚያክሉ ሰዎች ሞት ምክንያት ይሆናል።4

16 በሌላ አባባል ከእንዲህ ዓይነቱ የምግብ እጥረት የተነሣ በሂሮሽማ በአቶም ቦምብ የሞቱትን ሰዎች የሚያክል ብዛት ያላቸው ሰዎች በየሁለቱ ቀን ይሞታሉ። እንዲያውም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከረሃብ የተነሣ የሚሞቱት ሰዎች ብዛት በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከሞቱት ወታደሮች ጠቅላላ ቁጥር ይበልጣል። ከ1914 ወዲህ ‘በልዩ ልዩ ቦታ የምግብ እጥረት’ ነበረን? አዎን፣ ነበር!

የመሬት መንቀጥቀጦች

17. ከ1914 በኋላ ብዙም ሳይቆይ የተከሰተው ከፍተኛ ውድመት ያስከተለ የመሬት መንቀጥቀጥ የትኛው ነው?

17 አንደኛው የዓለም ጦርነት ከተጀመረ ከጥቂት ወራት በኋላ በጥር 13, 1915 በኢጣሊያ አብሩዚ ከተማ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ የ32,610 ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። ይህ ከፍተኛ አደጋ በኢየሱስ መገኘት ጊዜ ከሚታዩት ጦርነቶችና ረሃብ በተጨማሪ የሚታየውን ሌላ ክስተት ያስታውሰናል:- “የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል።” እንደ ጦርነቱና ረሃቡ ሁሉ በአብሩዚ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥም ‘የምጥ ጣር መጀመሪያ’ ብቻ ነበር። *

18. ኢየሱስ የመሬት መንቀጥቀጥን በሚመለከት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

18 ሃያኛው መቶ ዘመን የመሬት መንቀጥቀጦች ዘመን ሆኗል። ከፍተኛ እድገት ያደረገው የመገናኛ ብዙሐን ምስጋና ይግባውና የሰው ዘር በሙሉ እነዚህ የመሬት መንቀጥቀጦች ስለሚያደርሱት ጉዳት አሳምሮ ያውቃል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል በ1920 ቻይና ውስጥ በመሬት መንቀጥቀጥ 200,000 ሰዎች ሲሞቱ በ1923 በጃፓን 99,300 ሰዎች፣ በ1935 ደግሞ በሌላ የመሬት መንቀጥቀጥ በዛሬዋ ፓኪስታን 25,000 ሰዎች አልቀዋል። በ1939 በቱርክ 32,700 ሰዎች፣ በ1970 በፔሩ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ 66,800 ሰዎች ሞተዋል። እንዲሁም በ1976 በቻይና ታንግሻን ወደ 240,000 ሰዎች (ወይም እንደ አንዳንዶቹ ምንጮች 800,000) ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በ1988 ደግሞ በአርሜኒያ በተከሰተው ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ 25,000 የሚያህሉ ሰዎች ሞተዋል። * በእርግጥም ‘በልዩ ልዩ ስፍራ የመሬት መንቀጥቀጥ’ ተከስቷል!6

‘ቀሳፊ በሽታዎች’

19. ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረለትና አራተኛው የራእይ ፈረሰኛ ጥላ የሆነለት የትኛው የምልክቱ ክፍል ነው?

19 ሌላው በኢየሱስ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰው ነገር በሽታ ነው። ወንጌላዊው ሉቃስ በዘገባው ውስጥ ኢየሱስ “በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር” ይሆናል ሲል እንደተነበየ መዝግቧል። (ሉቃስ 21:​11) ይህም ቢሆን ከራእይ አራት ፈረሰኞች ትንቢታዊ ራእይ ጋር ይስማማል። የአራተኛው ፈረሰኛ ስም ሞት ነው። በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰተውን ድንገተኛ ሞት የሚያመለክት ሲሆን ‘ቀሳፊ በሆኑ በሽታዎችና በምድር አራዊት’ የሚሞቱትንም ይጨምራል።​—⁠ራእይ 6:​8 NW

20. ኢየሱስ ስለ ቸነፈር የተናገረው ትንቢት በከፊል ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያስቻለው የትኛው ጎላ ብሎ የሚጠቀስ ወረርሽኝ ነው?

20 በ1918 እና 1919 ቁጥራቸው ከ1,000,000,000 በላይ ሰዎች በኅዳር በሽታ ተይዘው ከ20,000,000 የሚበልጡት ሞተዋል። በሽታው የገደላቸው ሰዎች ቁጥር በታላቁ ጦርነት ከሞቱት ሰዎች በልጦ ተገኝቷል።7 ከዚህም ሌላ ዛሬ የሕክምናው መስክ እጅግ አስገራሚ መሻሻሎችን ያደረገ ቢሆንም ‘ቀሳፊ በሽታዎች’ ወይም ‘ቸነፈሮች’ ይህን ትውልድ ማሰቃየታቸውን አላቆሙም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ድሃ አገሮች ከሳይንሳዊ እድገት ተጠቃሚ የመሆን አጋጣሚያቸው ውስን መሆኑ ነው። ድሃ የሆኑ ሰዎች በቀላሉ ታክመው ሊድኑ ሲችሉ የገንዘብ አቅማቸው ስለማይፈቅድ ብቻ ታመው ይሞታሉ።

21, 22. በሃብታምም ሆነ በድሃ አገሮች የሚገኙ ሰዎች ‘ቀሳፊ በሆኑ በሽታዎች’ የተጠቁት እንዴት ነው?

21 ከዚህ የተነሣ በምድር ዙሪያ ከ300 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በወባ በሽታ ይሰቃያሉ። 200 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ደግሞ በቢልሃርዚያ ተለክፈዋል። 20 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ሻጋዝ በሚባለው በሽታ ተለክፈዋል። 126 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ሪቨር ብላይንድነስ በሚባል ዓይን በሚያሳውር በሽታ ሊጠቁ በሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታዎች በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን እንደ ቅጠል ያረግፋሉ።8 ሳንባ ነቀርሳና ሥጋ ደዌ ዛሬም ቢሆን ከባድ የጤና ችግሮች ናቸው። ‘በልዩ ልዩ ሥፍራ የሚከሰተው ቸነፈር’ ግምባር ቀደም ተጠቂዎች የዓለማችን ድሆች ናቸው።

22 ይሁን እንጂ ሃብታሞች አይነኩም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል ኢንፉሌንዛ ሀብታም ድሃ ሳይል ሁሉንም ያጠቃል። በ1957 የተከሰተው ኢንፉሌንዛ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ 70,000 ሰዎችን ገድሏል። ጀርመን ውስጥ ከስድስት ሰዎች አንዱ በካንሰር እንደሚሰቃይ ተገምቷል።9 በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ሃብታሞችንም ሆነ ድሃዎችን ያጠቃሉ። ጨብጥ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተደጋጋሚ ከሚታዩት ተላላፊ በሽታዎች አንዱ ሲሆን በአፍሪካ አንዳንድ ክፍሎች ውስጥ እስከ 18.9 በመቶ የሚያክለውን ነዋሪ የሚያሰቃይ በሽታ ነው።10 በፆታ ግንኙነት ከሚተላለፉትና ሰፋ ባለ አካባቢ ተዛምተው ከሚገኙት ‘ወረርሽኝ በሽታዎች’ መካከል ቂጥኝ፣ ክላሚዲያ እንዲሁም በጾታ ብልት አካባቢ የሚወጣው ኸርፕስ የሚባል ቫይረስ ይገኙበታል።

23. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜና አውታሮችን ትኩረት የሳበው ‘ቀሳፊ በሽታ’ የትኛው ነው?

23 ከ1980ዎቹ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ‘ቀሳፊ በሽታ’ የሆነው ኤድስ በዚህ ‘የቸነፈር’ ዝርዝር ላይ ተጨምሯል። ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ኤድስ ምንም መድሃኒት ያልተገኘለት በመሆኑና የሰለባዎቹ ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ አስፈሪ በሽታ ሆኗል። ዘ ወርልድ አልማናክ ቡክ ኦቭ ፋክትስ 1997 እንደገለጸው “በምድር ዙሪያ 21.8 ሚልዮን ሰዎች በኤድስ በሽታ ተይዘዋል ወይም በኤድስ አማጪው ቫይረስ (በኤች አይ ቪ) ተለክፈዋል። . . . 5.8 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች ደግሞ በኤድስ ሞተዋል።”11 በጽሑፍ የሰፈረ አንድ ሌላ ግምታዊ ዘገባ እንደሚጠቁመው በእያንዳንዱ ደቂቃ አንድ አዲስ ሰው በኤድስ ቫይረስ ይጠቃል። በእርግጥም ‘ቀሳፊ በሽታ’ ነው! ይሁን እንጂ በምድር አራዊት ምክንያት የሚከሰት ሞት እንደሚኖር የሚገልጸውን ትንቢት በሚመለከትስ ምን ማለት ይቻላል?

‘የምድር አራዊት’

24, 25. (ሀ) ነቢዩ ሕዝቅኤል የተናገረው ስለ ምን ዓይነት ‘አራዊት’ ነው? (ለ) ኢየሱስ እርሱ በሚገኝበት ጊዜ በምድር ላይ ስለሚኖሩት ‘አራዊት’ ምን ብሏል?

24 ዛሬ በአብዛኛው በጋዜጦች ላይ የምናነበው ከምድር ገጽ እንዳይጠፉ የሚያሰጋቸው ወይም ሊጠፉ የተቃረቡ የአራዊት ዝርያዎች አሉ የሚል ዜና ነው። ዛሬ የሰውን ልጅ የሚያሰጉት “የምድር አራዊት” መሆናቸው ቀርቶ በተቃራኒው የሰው ልጅ የእነርሱን ሕልውና አደጋ ላይ እየጣለ መጥቷል። ያም ሆኖ ግን በሕንድ የሚገኙትን የነብር ዝርያዎች የመሳሰሉ እንስሳት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ሕይወት ያጠፋሉ።

25 ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ስጋት የፈጠሩ ሌሎች አራዊት እንዳሉ ይጠቁመናል። ነቢዩ ሕዝቅኤል ዓመፀኛ የሆኑ ሰዎችን ከአራዊት ጋር በማወዳደር እንደሚከተለው ብሏል:- “በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኩላዎች ናቸው።” (ሕዝቅኤል 22:​27) ኢየሱስ ‘የዓመፃ ብዛት’ እንደሚኖር ትንቢት ሲናገር እርሱ በሥልጣኑ በሚገኝበት ወቅት እንደነዚህ ያሉ ‘አራዊት’ በምድር ላይ እንደሚኖሩ መግለጹ ነበር ለማለት ይቻላል። (ማቴዎስ 24:​12) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስም “በመጨረሻው ቀን” ሰዎች “ገንዘብን የሚወዱ . . . ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች መልካም የሆነውን የማይወዱ” እንደሚሆኑ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-3) ከ1914 ወዲህ ይህ ነገር ተከስቷልን?

26-28. እንደ “አራዊት” ያሉ ወንጀለኞች በምድር ላይ እያደቡ መሆናቸውን የሚያሳዩት ከዓለም ዙሪያ የተገኙት ሪፖርቶች የትኞቹ ናቸው?

26 በትክክል ተከስቷል። በዓለም ዙሪያ ካሉት ትላልቅ ከተሞች በአንዱ የምትኖር ከሆነ ይህ ለአንተ አዲስ አይደለም። ይሁን እንጂ የምትጠራጠር ከሆነ በቅርቡ በጋዜጦች ላይ ከወጡ ዘገባዎች የተወሰዱትን ሐሳቦች ተመልከት። ከኮሎምቢያ:- “ባለፈው ዓመት ፖሊስ . . . 10,000 የሚያክሉ ነፍስ ግድያዎችንና 25,000 የሚያክሉ በመሣሪያ የተፈጸሙ የዝርፊያ ወንጀሎችን መዝግቧል።” ከቪክቶሪያ፣ አውስትራሊያ:- “የከባድ ወንጀሎች መጠን በእጅጉ ጨምሯል።” ከዩናይትድ ስቴትስ:- “በኒው ዮርክ የሚፈጸመው ግድያ እስካሁን ታይቶ ወደማይታወቅ ከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ ነው።” “ባለፈው ዓመት ዴትሮይት በመላው የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት ካሉት ትላልቅ ከተሞች መካከል ከነዋሪው ቁጥር አንጻር ከፍተኛውን የነፍስ ግድያ ቁጥር በመያዝ የቀዳሚነቱን ስፍራ ከጌሪ ተረክባለች። ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል 58 የሚሆኑት ግድያ ተፈጽሞባቸዋል።”

27 ከዚምባቡዌ:- “የሕፃናትን ሕይወት የማጥፋት ወንጀል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።” ከብራዚል:- “እዚህ የሚፈጸመው ወንጀልም ሆነ መሣሪያው በገፍ ስለሆነ ዓመፅ እንደተፈጸመ መስማት የሚያስገርም ዜና መሆኑ ቀርቷል።” ከኒው ዚላንድ:- “የፆታ ጥቃቶችና ሌሎች ከባድ ወንጀሎች ፖሊስን በእጅጉ እያሳሰቡ መጥተዋል።” “በኒው ዚላንድ ውስጥ አንዱ በሌላው ላይ የሚፈጽመው የወንጀል ዓይነት እጅግ አረመኔያዊ እየሆነ መጥቷል።” ከስፔይን:- “ስፔይን እየጨመረ ከመጣው ወንጀል ጋር ትንቅንቅ ይዛለች።” ከኢጣሊያ:- “የሲሲሊያ ወንበዴዎች ከገጠማቸው ሽንፈት ዳግም አንሰራርተው የግድያ ዘመቻ እያካሄዱ ነው።”

28 ይህ መጽሐፍ ከመዘጋጀቱ ትንሽ ቀደም ባሉት ዓመታት በተነበቡ ጋዜጦች ላይ የወጡት እነዚህ ዘገባዎች እንዲሁ ለናሙና ያክል ብቻ የቀረቡ ናቸው። በእርግጥም ‘የምድር አራዊት’ በምድር ላይ እያደቡ በመሆናቸው ለሰዎች ደህንነት ከፍተኛ ስጋት ፈጥረዋል።

የምሥራቹ ስብከት

29, 30. በኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያለው ሃይማኖታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?

29 ኢየሱስ በሥልጣኑ በሚገኝበት ወቅት በሚኖረው በችግር የታመሰ ጊዜ ውስጥ ሃይማኖትስ ምን ያደርግ ይሆን? በአንድ በኩል ኢየሱስ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ እንደሚጨምር ትንቢት ተናግሯል:- “ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ።” (ማቴዎስ 24:​11) በሌላ በኩል ደግሞ በጥቅሉ ሲታይ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ሰዎች ለአምላክ እምብዛም ደንታ የሌላቸው እንደሚሆኑ ተናግሯል። “የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች።”​—⁠ማቴዎስ 24:​12

30 ይህ ዛሬ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ነገር ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው። በአንድ በኩልም ዋና ዋናዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ድጋፍ እያጡ መጥተዋል። በአንድ ወቅት ጠንካራ የፕሮቴስታንቶች ይዞታ በነበረው በሰሜን አውሮፓና በእንግሊዝ ሃይማኖት የተረሳ ነገር ሆኗል። በተመሳሳይም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በካህናት እጥረት እንዲሁም የደጋፊዎቿ ቁጥር በመመናመኑ ችግር ላይ ወድቃለች። በሌላ በኩል ደግሞ ትናንሽ ሃይማኖታዊ ወገኖች በፍጥነት እየተበራከቱ ነው። ከምሥራቃውያን ሃይማኖቶች የሚወጡ ኑፋቄዎች እንደ አሸን ፈልተዋል። ስስታም የቴሌቪዥን ወንጌላውያንም በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር ያጋብሳሉ።

31. ኢየሱስ ዛሬ ያለውን እውነተኛ ክርስትና ለይተን ለማወቅ የሚያስችለን ምን ነገር ተንብዮአል?

31 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ስላቋቋመውና ሐዋርያቱ ስለሰበኩት ሃይማኖት ማለትም ስለ እውነተኛው ክርስትናስ ምን ማለት ይቻላል? ኢየሱስ በሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜም ይኖራል፤ ይሁን እንጂ ተለይቶ የሚታወቀው እንዴት ነው? እውነተኛው ክርስትና ተለይቶ የሚታወቅባቸው ነገሮች በርካታ ሲሆኑ አንደኛው በኢየሱስ ታላቅ ትንቢት ውስጥ ተገልጾ እናገኘዋለን። ይህ እውነተኛ ክርስቲያኖች በዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ የሚጠመዱበት ወቅት ነው። ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ሲል ተንብዮአል።​—⁠ማቴዎስ 24:​14

32. በማቴዎስ 24:​14 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የኢየሱስ ትንቢት የፈጸመው የትኛው ቡድን ብቻ ነው?

32 በአሁኑ ጊዜ ይህ የስብከት ሥራ በከፍተኛ መጠን እየተከናወነ ነው! ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች በመባል የሚታወቁት ሃይማኖታዊ ሰዎች በክርስትና ታሪክ ታይቶ በማያውቅ ከፍተኛ መጠን የስብከቱን ሥራ እያከናወኑ ነው። (ኢሳይያስ 43:​10, 12) በ1919 ፖለቲካዊ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች መጨረሻው ያላማረውን የቃል ኪዳኑን ማኅበር ሲያሞካሹ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ምድር አቀፍ የስብከት ዘመቻ ለማጧጧፍ ተዘጋጅተው ነበር።

33, 34. የመንግሥቱ ምሥራች በመላዋ ምድር የተሰበከው እስከ ምን ድረስ ነው?

33 በወቅቱ የነበሩት ምሥክሮች 10,000 ብቻ ቢሆኑም ሥራው መሠራት እንዳለበት ተገንዝበው ነበር። በድፍረት የስብከቱን ሥራ ተያያዙት። ቀሳውስትና ምዕመናን ተብሎ መከፋፈል ከመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ጋር ብቻ ሳይሆን ሐዋርያት ከተዉትም ምሳሌ ጋር እንደማይጣጣም ተገንዝበው ነበር። ከዚህ የተነሣ ከላይ እስከ ታች ድረስ ሁሉም ለጎረቤታቸው ስለ አምላክ መንግሥት መናገርን በመማራቸው የሰባኪዎች ድርጅት ሆነዋል።

34 ጊዜው እየገፋ ሲሄድ እነዚህ ሰባኪዎች ከፍተኛ ተቃውሞዎችን መጋፈጥ አስፈልጓቸዋል። አውሮፓ ውስጥ ከነበሩ የተለያዩ አምባገነን መንግሥታት ተቃውሞ ደርሶባቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስና ካናዳ ውስጥ ክስ ተመሥርቶባቸዋል፤ እንዲሁም የሕዝብ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። በሌሎች አገሮች ደግሞ አክራሪ ሃይማኖተኞች የሚያንጸባርቁትን መሠረተ ቢስ ጥላቻና ጨካኝ ፈላጭ ቆራጭ አስተዳደሮች ያደረሱባቸውን ምህረት የለሽ ስደት መቋቋም ነበረባቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ እየተስፋፋ የመጣውን ጥርጣሬ የሞላበትና ራስህን አስደስት የሚል መንፈስ መጋፈጥ አስፈልጓቸዋል። ይሁን እንጂ በመጽናታቸው ዛሬ ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ከአምስት ሚልዮን ተኩል በላይ ሆነዋል። ምሥራቹ የአሁኑን ያህል በስፋት የተሰበከበት ጊዜ አለመኖሩ በዚህ ረገድ የተነገረው ትንቢት አስገራሚ ፍጻሜውን እንዳገኘ ያረጋግጣል!

ታዲያ ይህ ሁሉ ምን ያሳያል?

35. (ሀ) በዛሬው ጊዜ የትንቢቶች ፍጻሜ መጽሐፍ ቅዱስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያስረዳው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ የሰጠው ምልክት ፍጻሜውን ማግኘቱ ለዘመናችን ምን ትርጉም አለው?

35 ኢየሱስ የሰጠው ታላቅ ምልክት ፍጻሜውን ሲያገኝ እንደተመለከትን ምንም አያጠራጥርም። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ይህንን ከሚያህል ረጅም ዘመን በፊት በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ምን ነገሮች እንደሚከናወኑ አስቀድሞ ሊናገር የሚችል ሰው አይኖርም። ከዚህም በላይ እነዚህ ምልክቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ኢየሱስ በሥልጣኑ በተገኘበትና የዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ በቀረበበት ዘመን ላይ እንደምንኖር የሚያሳይ ነው። (ማቴዎስ 24:​3 NW) ይህስ ምን ትርጉም ይኖረዋል? የኢየሱስ መገኘት ምን ነገሮችን ይጨምራል? የሚደመደመው የነገሮች ሥርዓትስ የትኛው ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ መሆኑን የሚያሳየውን ሌላ ጠንካራ ማስረጃ ይኸውም አስገራሚ የሆነውን የመጽሐፉን የእርስ በርስ ስምምነት መመርመር ይኖርብናል። ቀጥለን ይህን ጉዳይ በመመርመር የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ ታላቅ ፍጻሜውን ሊያገኝ የተቃረበው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 ከ1914 እስከ 1918 ባለው ጊዜ ውስጥ በአብሩዚ ከደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ የሚበልጡና በሬክተር መለኪያ 8 ወይም ከዚያ በላይ የደረሱ ቢያንስ አምስት የመሬት መንቀጥቀጦች ተከስተዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ርዕደ መሬቶች የተሰሙት ርቀው በሚገኙ የምድር ክፍሎች በመሆኑ እንደ ኢጣሊያው የመሬት መንቀጥቀጥ እምብዛም ትኩረት አልተሰጣቸውም።5

^ አን.18 በአንዳንዶቹ አደጋዎች ወቅት የሞቱትን ሰዎች ቁጥር በሚመለከት የተለያዩ አኃዞች ሪፖርት ተደርገዋል። ይሁን እንጂ ሁሉም አደጋዎች ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]