በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የላቀ የጥበብ ምንጭ

የላቀ የጥበብ ምንጭ

ምዕራፍ 12

የላቀ የጥበብ ምንጭ

“አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፣ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች።” (መዝሙር 104:​24) ዕጹብ ድንቅ ከሆነው ግዙፍ አጽናፈ ዓለም አንስቶ በጣም ውብ እስከሆነችው አበባ ድረስ ፍጥረት በሙሉ አቻ የሌለውን የፈጣሪውን ጥበብ ይመሰክራል። የዚህ የ20ኛው መቶ ዘመን ቴክኖሎጂ ከአምላክ ሥራዎች አንጻር ሲታይ ከቁጥር የሚገባ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ከሆነ ከሰው ልጅ ችሎታ በላይ የሆነ ጥበብ የሚንጸባረቅበት መጽሐፍ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ጥበብ ተንጸባርቆበታልን?

1. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) (ሀ) አምላክ ወደር የለሽ ጥበብ እንዳለው የሚያረጋግጥልን ነገር ምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብን በተመለከተ ምን ምክር ይሰጣል?

መጽሐፍ ቅዱስ የጥበብን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ይገልጽልናል። እንዲህ ይላል:- “ጥበብ ዓይነተኛ ነገር ናትና ጥበብን አግኝ፤ ከሀብትም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ።” (ምሳሌ 4:​7) በተጨማሪም እኛ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ጥበብ እንደሚጎድለን የሚገልጽ ከመሆኑም ሌላ እንዲህ የሚል ማበረታቻ ይሰጠናል:- “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጐድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን።”​—⁠ያዕቆብ 1:​5

2. አንድ ሰው ጥበቡን ማሳደግ የሚችለው እንዴት ነው?

2 አምላክ ‘ጥበብን በልግስና የሚሰጠው’ እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን እንድናነብና ከዚያ ትምህርት እንድንቀስም በማበረታታት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ እንዲህ በማለት አጥብቆ ያሳስበናል:- “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ . . . እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና።” (ምሳሌ 2:​1, 2, 5, 6) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ሥራ ላይ ስናውልና ምክሩ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ስንመለከት መለኮታዊ ጥበብ ያለበት መጽሐፍ መሆኑን እንገነዘባለን።

ጥበብ ያለባቸው ምክሮች

3, 4. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን መውደድ ከንቱ ስለ መሆኑ ምን ይነግረናል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብ ስላለው ዋጋ በሚሰጠን ምክር ረገድ ግሩም ሚዛናዊነት ያሳየው እንዴት ነው?

3 ይህን ጉዳይ ይበልጥ ለመረዳት እንድንችል እስቲ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመልከት። የሚከተለውን ጥበብ ያለበት ምክር ልብ በል:- “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ . . . በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና።” (1 ጢሞቴዎስ 6:​9, 10) እስቲ ይህን አባባል ሰዎች ከሁሉ በፊት ገንዘብን እንዲያሳድዱ ከሚያበረታታው ከጊዜያችን (ቢያንስ በምዕራቡ ዓለም ከሚታየው) አመለካከት ጋር አወዳድረው። የሚያሳዝነው ብዙዎች የጓጉለትን ሃብት ቢያገኙም በውስጣቸው የሚሰማቸውን የባዶነትና እርካታ የማጣት ስሜት መፋቅ አልቻሉም። አንድ የስነ ልቦና ሐኪም እንዲህ ብለዋል:- “ስመ ጥርና ሃብታም መሆን ደስታና እርካታ እንድታገኝ እንዲሁም የሰዎችን አክብሮትና ፍቅር እንድታተርፍ ያደርግሃል ማለት አይደለም።”1

4 አስተዋይ ሰው ከነአካቴው ገንዘብ አያስፈልግም አይልም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት በጣም ሚዛናዊ የሆነ ጥበብ የተንጸባረቀበት ሐሳብ ይሰነዝራል:- “የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፤ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን እንድትሰጥ ነው።” (መክብብ 7:​12) በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብ አስፈላጊ ነገር ቢሆንም ከምንም ነገር ይበልጥ አስፈላጊ ነው ማለት እንዳልሆነ እንድናስተውል ይረዳናል። አንዳንድ ነገሮችን ለማከናወን ብቻ የሚያስችል ነገር ነው። ያም ቢሆን በተገቢው መንገድ ለመጠቀም የሚያስችል ጥበብ ከሌለን የሚኖረው ጠቀሜታ ውስን ነው።

5, 6. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ከክፉ ባልንጀርነት እንድንርቅ የሚሰጠው ምክር ጥበብ የሞላበት ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ‘ከጠቢባን ጋር በመሄዳችን’ ጥቅም የምናገኘው እንዴት ነው?

5 የሚከተለውም የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል እውነት ነው:- “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።” (ምሳሌ 13:​20) ባልንጀሮቻችን በእኛ ላይ ምን ያህል ብርቱ ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው ልብ ብለሃል? የእኩዮች ተጽዕኖ ወጣቶችን ወደ ስካር፣ ወደ ዕፅ ሱሰኝነትና ወደ ፆታ ብልግና መርቷቸዋል። የብልግና ንግግር ከሚናገሩ ሰዎች ጋር የምንውል ከሆነ የኋላ ኋላ እኛም የእነርሱን የብልግና ንግግር እንቀዳለን። የእምነት ማጉደል ድርጊት ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር ወዳጆች ከሆንን እኛም እንደ እነሱ የእምነት አጉዳይነት ዝንባሌ ሊጠናወተን ይችላል። እውነትም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​33

6 በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ ባልንጀርነት እንድንሻሻል ሊያደርገን ይችላል። ‘ከጠቢባን ጋር የምንሄድ ከሆነ’ እኛም ጠቢባን እንሆናለን። እንደ መጥፎ ጠባይ ሁሉ መልካም ጠባይም ከአንዱ ወደ ሌላው ይጋባል። መጽሐፍ ቅዱስ ባልንጀሮቻችንን በጥንቃቄ እንድንመርጥ ማበረታታቱም ጥበብ እንዳለበት የሚያሳይ ነው።

7. መጽሐፍ ቅዱስን በምክር ሰጭነቱ ልዩ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?

7 መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችንን ለመምራት የሚያስችሉንን እነዚህን የመሰሉ ብዙ መመሪያዎች ይዟል። በምክር ሰጭነቱ አቻ የለውም። ምክሩ ምንጊዜም መሬት ጠብ አይልም። ምክሩ እንዲሁ ተግባራዊነት የሌለው ቲዮሪ ብቻ ወይም ደግሞ እኛን የሚጎዳ ምክር አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ያህል ሰፊ ዘርፍ የሚዳስስ ምክር አናገኝም። ይህን ምክር በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ የሚያደርጉና ምክሩን ሁልጊዜ ጠቃሚ ሆኖ ያገኙት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የጥበብ ምንጭ መሆኑን ይገነዘባሉ።

ጥበብ ያለባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች

8. መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ በውስጡ ባልተጠቀሰ ጉዳይ እንኳ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

8 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ያልተጠቀሰ ጉዳይ ቢገጥመንስ? ብዙውን ጊዜ ብዙ ነገር ሊጠቀልሉ የሚችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች እናገኛለን። ለምሳሌ ያህል ትንባሆ የማጨስ ልማድን በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ የሚገጥማቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ትንባሆ ኢየሱስ በነበረበት ወቅት በመካከለኛው ምሥራቅ የሚታወቅ ነገር ስላልነበር መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የሚለው ነገር የለም። የሆነ ሆኖ በዚህ ረገድ ጥበብ ያለበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አሉ።

9-11. ትንባሆ ማጨስንም ሆነ ማኘክን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት የጥበብ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው? እነዚህንስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በመከተል እንዴት እንጠቀማለን?

9 ትንባሆ ማጨስ እርካታ ይሰጣል እየተባለ ይነገርለት እንጂ የሚበክል ነገር ወደ ሳንባችን መሳብ ማለት ነው። አንድ ትንባሆ የሚያጨስ ሰው ሰውነቱንና ልብሱን እንዲሁም በዙሪያው ያለውን አየር ይበክላል። ከዚህም በተጨማሪ ትንባሆ ማጨስ ሱስ ነው። ብዙውን ጊዜ ማቆም የሚፈልጉ ሰዎች ለማቆም የሚያደርጉትን ትግል ቀላል ሆኖ አያገኙትም። ይህን በአእምሮአችን በመያዝ መጽሐፍ ቅዱስ ትንባሆ ማጨስን በሚመለከት ጥበብ ያለበት መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚረዳ ምን መሠረታዊ ሥርዓት እንዳለው እንመልከት።

10 በመጀመሪያ የሱሰኛነትን ችግር እንመልከት። ጳውሎስ ምግብን በሚመለከት “ለማናቸውም ነገር ባሪያ ሆኜ አልገዛም” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 6:​121980 ትርጉም) ጳውሎስ የፈለገውን ምግብ የመብላት ነፃነት ነበረው። ይሁን እንጂ በጊዜው ሕሊናቸው በቀላሉ የሚጎዳ ሰዎች እንደነበሩ አውቋል። በመሆኑም ሌሎችን ላለማሰናከል ሲል አንዳንድ ምግቦችን መተው ቢያስፈልገው መተው እስኪያቅተው ድረስ ለምግቦቹ “ሱሰኛ” እንዳልሆነ ተናግሯል። አንድ ሰው ትንባሆ ማጨሱን ወይም ማኘኩን ማቆም ካቃተው ‘ለዚያ ነገር ባሪያ ሆኗል’ ማለት ነው። ስለሆነም ጳውሎስ ምግብን በሚመለከት የተናገረው ነገር ትንባሆ ማጨስንም ሆነ ማኘክን በተመለከተ ጥሩ መመሪያ ይሆነናል። የአንድ ልማድ ባሪያዎች ልንሆን አይገባም።

11 በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሚበክል ነገር መሆኑን ልብ በል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” ይላል። (2 ቆሮንቶስ 7:​1) ትንባሆ ማጨስ ስጋን ማርከስ ወይም መበከል ማለት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። በየዓመቱ አንድ ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች በትንባሆ ምክንያት ያለ ዕድሜያቸው እንደሚቀጩ የሚገልጸው የዓለም የጤና ድርጅት ዘገባ ይህ ብክለት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ ያሳያል። ሥጋን ከሚያረክሱ ነገሮች በመራቅ ንጽሕናችንን ስለመጠበቅ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ብንከተል ትንባሆ ማጨስ እንዲሁም አደገኛ ዕፆችንና ሌሎች የሚያረክሱ ነገሮችን መውሰድ ከሚያስከትላቸው ከባድ የጤና ችግሮች እንጠበቃለን።

ጠቃሚ ምክሮች

12. የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሁልጊዜ ከእኛ አካላዊና ስሜታዊ ደህንነት ጋር የተዛመደ የሆነው ለምንድን ነው?

12 የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል ከአካላዊ ጤንነት አንጻር ጠቀሜታ ያስገኝልናል መባሉ ሊያስገርመን አይገባም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ምክር ከአምላክ የተገኘ ነው። እርሱ ደግሞ ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ስለ አሠራራችንም ሆነ ስለሚያስፈልገን ነገር ያለው እውቀት እጅግ ጥልቅ ነው። (መዝሙር 139:​14-16) ምክሮቹ ሁልጊዜ ከእኛ አካላዊና ስሜታዊ ደህንነት ጋር የተዛመዱ ናቸው።

13, 14. መጽሐፍ ቅዱስ ውሸት ከመናገር እንድንቆጠብ የሚሰጠንን ምክር መከተል የጥበብ ጎዳና የሆነው ለምንድን ነው?

13 መዋሸት እንደሌለብን የተሰጠን ምክር ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው። ውሸት ይሖዋ ከሚጠላቸው ሰባት ነገሮች አንዱ ሲሆን በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የሚዋሹ ሰዎች በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር እንደማይፈቀድላቸው ተገልጿል። (ምሳሌ 6:​19፤ ራእይ 21:​8) ይህ ምክር ቢሰጥም መዋሸት በሰፊው የተለመደ ነገር ነው። አንድ የንግድ መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “ዩናይትድ ስቴትስ በታሪኳ ውስጥ የአሁኑን ያህል የከፋ ማጭበርበርና ማታለል እንዲሁም መሰል ብልሹ ድርጊት ገጥሟት አያውቅም።”2

14 መዋሸት በሰፊው የተለመደ ነገር ቢሆንም ለማኅበረሰቡም ሆነ ለግለሰቡ ጎጂ ነገር ነው። ክሊፎርድ ሎንግሌ የተባሉ አንድ የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ እንደሚከተለው ሲሉ በትክክል ተናግረዋል:- “ውሸት በሰው ሐሳብና በእውነታው መካከል ያለው ወሳኝ ተዛምዶ እንዲበጠስ ስለሚያደርግ የዋሸውንም ሆነ ውሸቱ የተነገረውን በእጅጉ ይጎዳቸዋል።”3 ዚ አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ሳይካትሪ ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “ውሸቱ በተነገረው ሰው ላይ የሚያስከትለው ስነ ልቦናዊ ተጽእኖ ከባድ ሊሆን ይችላል። እውነት ናቸው ብሎ ባመናቸው የሐሰት መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ በሕይወቱ ውስጥ ከባድ ውሳኔዎችን ያደርግ ይሆናል። ውሸት በሚዋሸው ሰው ላይም እንዲሁ ጎጂ ውጤት ይኖረዋል።”4 መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን የጥበብ ምክር በመከተል እውነቱን መናገር ምንኛ የተሻለ ይሆናል!

15, 16. ለሌሎች ፍቅር እንድናሳይ የሚጠይቀውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተል የሚጠቅመን እንዴት ነው?

15 መጽሐፍ ቅዱስ አዎንታዊ በሆነ መልኩ ደግሞ ለሌሎች ሰዎች አሳቢነትና ፍቅር ልናሳይና ልንረዳቸው እንደሚገባ ይነግረናል። “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት በሰፊው የታወቁ ናቸው።​—⁠ማቴዎስ 7:​12

16 እያንዳንዱ ሰው ይህን መመሪያ ቢከተል ኖሮ ዓለማችን እጅግ የተሻለ ሁኔታ በኖራት ነበር! ከዚህም በላይ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተደረገ አንድ ስነ ልቦናዊ ጥናት እንደሚያሳየው ሰዎች ጥሩ ስሜት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ጥናቱ የተካሄደባቸው 1,700 ሰዎች ሌሎች ሰዎችን መርዳታቸው የመረጋጋት ስሜት እንደፈጠረላቸውና ከጭንቀት ጋር ተያይዘው ከሚመጡት እንደ ራስ ምታትና የድምፅ መስለል ካሉት ችግሮች እፎይታን እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል። ሪፖርቱ እንዲህ በማለት ይደመድማል:- “ከዚህ አንጻር ሲታይ ለሌሎች አሳቢ መሆን ለራስ አሳቢ የመሆንን ያህል የሰብዓዊ ተፈጥሮ ክፍል ይመስላል።”5 ይህ ነገር “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ያስታውሰናል። (ማቴዎስ 22:​39፤ ከዮሐንስ 13:​34, 35 ጋር አወዳድር።) ራሳችንን መውደዳችን ተፈጥሮአዊ ነገር ነው። ይሁን እንጂ በስሜት ጤናሞች እንድንሆን መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም መውደድ እንዳለብን ይነግረናል።

ጋብቻና ሥነ ምግባር

17. አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ጊዜ ያለፈበት መስሎ የሚታየው ለምንድን ነው?

17 መጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር የሚሰጥ ቢሆንም ሰዎች ሁልጊዜ በምክሩ ይደሰታሉ ማለት አይደለም። ብዙውን ጊዜ እንዲያውም ጊዜ ያለፈበት ነው የሚል ነቀፋ ይሰነዘርበታል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለራሳችን ዘለቄታዊ ጥቅም የሚያስገኝ ቢሆንም ይህንን ምክር ሥራ ላይ ማዋል ብዙውን ጊዜ ራስን መገሰጽን እንዲሁም የራስን ፍላጎት መካድን ስለሚጠይቅና በዛሬው ጊዜ እነዚህን ባሕርያት ማሳየት የሚፈልጉ ሰዎች እምብዛም በመሆናቸው ነው።

18, 19. መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻንና ሥነ ምግባርን በተመለከተ ያለው የአቋም ደረጃ ምንድን ነው?

18 ለምሳሌ ያህል የጋብቻንና የሥነ ምግባርን ሁኔታ ተመልከት። በዚህ ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃ ጥብቅ ነው። አንድ ባል ለአንድ ሚስት ብቻ መሆን እንዳለበት በግልጽ ይናገራል። መፋታት ወይም ተለያይቶ መኖር የሚቻልባቸው አንዳንድ ከአቅም በላይ የሆኑ ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቢናገርም በአጠቃላይ ጋብቻ የዕድሜ ልክ ጥምረት መሆኑን ይገልጻል። “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፣ አለም:- ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።”​—⁠ማቴዎስ 19:​4-6፤ 1 ቆሮንቶስ 7:​12-15

19 ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የሚቻለው በጋብቻ ውስጥ ብቻ እንደሆነ ይናገራል። ከጋብቻ ውጭ የሚደረጉትን እንዲህ ዓይነት ግንኙነቶች ይከለክላል። እንዲህ እናነባለን:- “ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ . . . ­የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10

20. መጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ምግባርን በሚመለከት ያለው የአቋም ደረጃ ዛሬ በሰፊው ቸል የተባለው በምን መንገዶች ነው?

20 ዛሬ እነዚህ የአቋም ደረጃዎች በሰፊው ቸል ተብለዋል። የኅብረተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ዴቪድ ማክ እንዲህ ብለዋል:- “በዚህ በእኛ መቶ ዘመን ባሕላችን ከፍተኛ ለውጥ ተካሂዶበታል። የብዙዎቹም ጥንታዊ ባሕሎችና ተቋማት መሠረታቸው ተናግቷል። ጋብቻም የገጠመው እጣ ከዚህ የተለየ አይደለም።”6 ልቅ የሥነ ምግባር ድርጊቶች የተለመዱ ሆነዋል። እየተቀጣጠሩ የሚጫወቱ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ወጣቶች የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው እንደ ስህተት አይታይም። ከጋብቻ በፊት ‘እርግጠኛ ለመሆን’ በሚል ፈሊጥ አብሮ መኖር የተለመደ ነው። ከተጋቡ በኋላም ልቅ የሆኑ የፆታ ድርጊቶችን መፈጸም እንግዳ ነገር መሆኑ ቀርቷል።

21. መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻንና ሥነ ምግባርን በሚመለከት ያለው የአቋም ደረጃ በሰፊው ቸል መባሉ ምን አስከትሏል?

21 ይህ ልቅ የሆነ የሥነ ምግባር ሁኔታ ደስታ የሚያመጣ ሆኖ ተገኝቷልን? በፍጹም። ኃዘንንና የቤተሰብ መፈራረስን ያስከተለ እጅግ ከፍተኛ ትርምስ ከመፍጠር በቀር የፈየደው ነገር የለም። ልቅ በሆነ የፆታ ሥነ ምግባር ምክንያት ብቻ የሚመጡ የአባለዘር በሽታዎችም እንደ ወረርሽኝ እንዲዛመቱ አድርጓል። እንደ ጨብጥ፣ ቂጥኝና ክላሚዲያ ያሉት እንዲሁም የሌሎች መሰል በሽታዎች ስርጭት ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዝሙት አዳሪነትና ግብረሰዶም የኤድስ ሥርጭት እንዲፋጠን አድርገዋል። ወጣት ልጃገረዶች ራሳቸው ከልጅነት ዕድሜ ሳይወጡ የልጆች እናት መሆናቸውም እንደ ወረርሽን እየተስፋፋ መጥቷል። ሌዲስ ሆም ጆርናል እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “በስድሳዎቹና በሰባዎቹ ዓመታት በሰፊው የተንጸባረቀው ፆታን አጋንኖ የመመልከት ዝንባሌ የሰውን ልጅ ከባድ ሰቆቃ ላይ ጣለው እንጂ ደስታ እንዲያጭድ አላደረገውም።”7

22. የሥነ ምግባር ጉዳይን በሚመለከት ከፍተኛ ደስታ የሚያስገኘው ነገር ምንድን ነው?

22 ከዚህ የተነሣ የኅብረተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ካልፍሬድ ቢ ብሮደሪክ የሰጡን ዓይነት አስተያየቶች እንሰማለን:- “ምናልባትም ዛሬ ከጋብቻ በፊት ተቆጥቦ መኖር የሚለውን ሐሳብ የዜጎቻችንን ፍላጎት እንዲሁም ከሕመምና ካልተፈለገ እርግዝና ነፃ የመውጣት መብታቸውን የሚያስጠብቅ ከሁሉ የተሻለ ፖሊሲ አድርገን ማራመዳችን የተሻለ መሆን አለመሆኑን ማመዛዘን የምንችልበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስላል።”8 በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃ የኋላ ኋላ ከሁሉ የላቀ ደስታ የሚያስገኝ መሆኑ ተረጋግጧል።

ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች

23. (ሀ) በትዳር መካከል ደስታ ሲጠፋ ብቸኛው አማራጭ ፍቺ ነውን? (ለ) ደስታ የሰፈነበት የሰከነ ትዳር ለመመሥረት የሚያስችሉት ሁለት ቁልፍ ነጥቦች ምንድን ናቸው?

23 ጋብቻ የዕድሜ ልክ ጥምረት በመሆኑ የተሳካ እንዲሆን ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል። አንዳንድ ሰዎች ደስታ በሌለበት ትዳር ውስጥ መከራ እያዩ ከመኖር ትዳሩን አፍርሶ መገላገል የተሻለ ነው ብለው ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ ሌላ አማራጭ አለ። ይኸውም በትዳር ውስጥ ደስታ እንዲጠፋ ያደረጉትን ችግሮች ለመፍታት መጣር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህም ረገድ ቢሆን ይረዳናል። ለትዳር ጓደኛችን እንዴት የታመንን መሆን እንዳለብን የሚሰጠውን ምክር ቀደም ሲል ተመልክተናል። የሰከነና ደስታ የሰፈነበት ትዳር እንዲኖር የሚያስችለው አንዱ ቁልፍ ይህ ነው። ሌላው ደግሞ በጋብቻ ውስጥ ሊኖር የሚችለው ራስ አንድ ብቻ እንደሆነ አምኖ መቀበል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ራስ መሆን ያለበት ባል እንደሆነ ይናገራል። ሚስት ባሏን የምትደግፍ እንጂ ቦታውን የምትጋፋ መሆን እንደሌለባት ተመክራለች። በሌላ በኩል ደግሞ ወንዱ ሥልጣኑን ሚስቱን በሚጠቅም መንገድ ሊሠራበት እንደሚገባ እንጂ ራስ ወዳድ መሆን እንደሌለበት ተነግሮታል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 11:​3፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:​11-14

24, 25. መጽሐፍ ቅዱስ ባልና ሚስት በትዳር ውስጥ የየበኩላቸውን ተገቢ ድርሻ እንዲወጡ የሚያበረታታው እንዴት ነው?

24 መጽሐፍ ቅዱስ ባሎችን በሚመለከት ሲናገር “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና” ይላል። (ኤፌሶን 5:​28, 29) አፍቃሪ የሆነ ባል ሥልጣኑን የሚጠቀምበት አሳቢነት በተሞላበት መንገድ ነው። የቤት ራስ እርሱ ቢሆንም የሚስቱንም ሐሳብ ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለበትና ሊያማክራት እንደሚገባው አይዘነጋም። ትዳር የጓደኛሞች ጥምረት እንጂ የአምባገነንነት ሥርዓት አይደለም።

25 መጽሐፍ ቅዱስ ለሚስቶች የሚሰጠው ምክር “ሚስትም ለባልዋ ጥልቅ አክብሮት ሊኖራት ይገባል” የሚሉትን ቃላት ይጨምራል። (ኤፌሶን 5:​33 NW) ባሏ ያለውን ቦታ ግምት ውስጥ በማስገባት ታከብረዋለች። እርሱ የሚያሳያት አሳቢነት ለእርሷ ያለውን ፍቅር እንደሚያረጋግጥ ሁሉ እርሷም እርሱን በመደገፍ እንደምታከብረው ታሳያለች። ዘመናዊ አስተሳሰብ ያላቸው ብዙዎቹ ግለሰቦች እንዲህ ያለውን ምክር አይቀበሉትም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ምክር መሠረት በፍቅርና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት ሁልጊዜ ደስተኛ ናቸው።

26. ጋብቻን የሚመለከቱት ቅዱስ ጽሑፋዊ የአቋም ደረጃዎች በእርግጥ ተግባራዊ ናቸውን? በምሳሌ አስረዳ።

26 ከሳውዝ ሲ የተገኘው ተሞክሮ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ የሚሰጠው ምክር ጠቃሚ እንደሆነ ያረጋግጥልናል። በዚያ አገር የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ለአሥር ዓመት አብረው ከኖሩ በኋላ ጋብቻቸው ባለበት መልኩ ሊቀጥል እንደማይችል ተሰምቷቸው ነበር። በመሆኑም ተለያይተው ስለ መኖር ማውጠንጠን ይጀምራሉ። ከዚያም ሚስትየው ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ትነጋገራለች። ይህች ሴት ከምሥክሯ ጋር ሆና መጽሐፍ ቅዱስ ለተጋቡ ወንድና ሴት የሚሰጠውን ምክር አጠናች። ባልየው እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ሚስቴ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እየተማረች ስትሄድ በሕይወቷ ውስጥ እነዚህን ተግባራዊ ለማድረግ ትጥር ጀመር። በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ አንዳንድ ለውጦች እንዳደረገች ማስተዋል ጀመርኩ።” እርሱም ስለ ነገሩ የማወቅ ጉጉት ስላደረበት ከሚስቱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ይስማማና መጽሐፍ ቅዱስ ላገቡ ወንዶች ምን ምክር እንደሚሰጥ ይማራል። ይህስ ምን ውጤት አስገኘ? እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ደስታ የሰፈነበት እውነተኛ የቤተሰብ ሕይወት ለመመሥረት የሚያስችለው ቁልፍ ምን እንደሆነ አውቀናል።”

27. የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ክርስቲያኖች ሊረዳቸው የሚችለው የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ነው?

27 መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ድህነትን በማሸነፍ ረገድም ጠቃሚ መሆኑ ታይቷል። ለምሳሌ ያህል ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጩት እንደ ትንባሆ ማጨስና ሰካራምነት የመሳሰሉት ድርጊቶች አንድ ሰው ያለውን ጥሪት ያሟጥጣሉ። (ምሳሌ 23:​19-21) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ትጉዎች እንድንሆን ያበረታታናል። ደግሞም ከሰነፍ ሰው ወይም ተስፋ ቆርጦ እጁን አጣጥፎ ከሚቀመጥ ሰው ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ አንድ ታታሪ የሆነ ሠራተኛ ቤተሰቡን ለመመገብ የሚያስችለውን ነገር አያጣም። (ምሳሌ 6:​6-11፤ 10:​26) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በክፉዎች ላይ እንዳንቀና’ የሚሰጠውን ምክር መከተል አንድ ሰው ከድህነት ለመውጣት ሲል እንደ ወንጀል ወይም ቁማር ባሉት ነገሮች ውስጥ እንዳይጠላለፍ ይጠብቀዋል። (መዝሙር 37:​1) እንዲህ ያሉት ተግባሮች ከገንዘብ ችግር በቅጽበት የሚያላቅቁ መስለው ይታዩ እንጂ የሚያስከትሉት ውጤት ቶሎ የማይፋቅና እጅግ መራራ ነው።

28-30. (ሀ) አንዲት ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋሏ ድህነትን እንድታሸንፍ የረዳት እንዴት ነው? (ለ) የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ሁኔታ ምን ያረጋግጣል?

28 ይህ ምክር በከፋ ድህነት የሚኖሩትን ሰዎች በእርግጥ ይረዳቸዋል ወይስ ምንም ተግባራዊነት የሌለው ሐሳብ ብቻ ነው? ከዓለም ዙሪያ የተገኙት ብዙ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ይህ ምክር ይሠራል። አንድ ምሳሌ ብቻ ለመጥቀስ ያህል በእስያ የምትኖር አንዲት ክርስቲያን ሴት ባሏ ሲሞት እርሷና ሕፃን ልጅዋ ምንም ገቢ አልነበራቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ እርሷንና ልጅዋን የረዳቸው እንዴት ነው?

29 መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ትጉ ስለነበረች ልብስ እየሠራች መሸጥ ጀመረች። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመከተልም ሐቀኛና እምነት የሚጣልባት ሰው ስለነበረች ብዙም ሳይቆይ ቋሚ ደንበኞች አገኘች። (ቆላስይስ 3:​23) ከዚያም በቤቷ ውስጥ የሚገኘውን አንዱን ክፍል ምግብ ቤት በማድረግ በየዕለቱ ጠዋት አሥር ሰዓት እየተነሣች የምትሸጠውን ምግብ መሥራት ጀመረች። ይህም ገቢዋን ለማሳደግ ረድቷታል። “እንደዚህም ሆኖ ቀላል ኑሮ መኖራችን የግድ ነበር” ስትል ተናግራለች። ነገር ግን “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፣ እርሱ ይበቃናል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንዳስታወሰች ተናግራለች።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:​8

30 እንዲህ በማለት ጨምራ ተናግራለች:- “ምንም እንኳን ኑሮዬ ከድህነት ብዙም ፈቅ ያላለ ቢሆንም በዚህ ቅር አልሰኝም ወይም አልመረርም። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አዎንታዊ አመለካከት እንድይዝ ረድቶኛል።” ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ የሰጠው ታላቅ ተስፋ ለእርሷ እንደተፈጸመላት አስተውላለች። ኢየሱስ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ [የሚያስፈልጋችሁ ቁሳዊ ነገር] ይጨመርላችኋል” ብሏል። (ማቴዎስ 6:​33) በሕይወቷ ውስጥ የአምላክን አገልግሎት በማስቀደሟ በዚህም ሆነ በዚያ ሁልጊዜ የሚያስፈልጋትን ሰብዓዊ ነገር አጥታ አታውቅም። የዚህች ክርስቲያን ሴት ተሞክሮ ከሌሎች ቁጥር ስፍር የሌላቸው የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ክርስቲያኖች ሁኔታ ጋር ተዳምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በእርግጥም እንደሚሠራ የሚያሳይ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሆነናል።

31. የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል ምን ያስገኛል? ይህስ ሐቅ ምን ነገር ያረጋግጣል?

31 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ ካለው በጣም ከፍተኛ የምክር ክምችት መካከል ጥቂቱን ብቻ ነው። ምክሩ ተግባራዊ እንደሚሆን የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎችንም ተመልክተናል። ከላይ ያሉትን ዓይነት በሺህ የሚቆጠሩ ተሞክሮዎች መጥቀስ ይቻላል። አሁንም ቢሆን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ነገር ከተከተሉ ይጠቀማሉ። ችላ ሲሉት ግን መከራ ይደርስባቸዋል። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም የሰው ዘር ያላንዳች ልዩነት የሚሠራና ሁሉንም የሚጠቅም ሌላ ጥንታዊም ሆነ ዘመናዊ ምክር አይገኝም። እንዲህ ያለው ጥበብ የሞላበት ምክር እንዲሁ ከአባቶች የተወረሰ ጥበብ ሊሆን አይችልም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ባለው ጥበብ የተሞላ መጽሐፍ መሆኑ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 168 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሌሎችን የመርዳት ዝንባሌ መያዝ ይጠቅመናል

[በገጽ 163 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጠቢባን ጋር መሄድ ጠቢብ ያደርጋል፤ ይሁን እንጂ የሰነፎች ባልንጀራ መሆን ለችግር ይዳርጋል

[በገጽ 165 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትንባሆ ማጨስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚቃረን በመሆኑ ልንርቀው ይገባል

[በገጽ 171 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በትዳራቸው ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር የሚከተሉ ሁሉ ደስተኛ እንዲሆኑ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ይኖራቸዋል

[በገጽ 173 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የከፋ ድህነት የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመቋቋም ያስችላል