በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስና አንተ

መጽሐፍ ቅዱስና አንተ

ምዕራፍ 14

መጽሐፍ ቅዱስና አንተ

የዘመናችን ተቺዎች መጽሐፍ ቅዱስ ኢ-ሳይንሳዊና እርስ በርሱ የሚጋጭ እንዲሁም ተረት የሞላበት መጽሐፍ ነው ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:​17) የተገኙት ማስረጃዎች ግን የተቺዎችን አባባል ሳይሆን የኢየሱስን አባባል የሚደግፉ ናቸው። ሐቁ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪካዊ እውነተኝነት ይመሠክራል። ከዚህም በላይ አስገራሚ የሆነ ስምምነቱ፣ እውነተኛ ትንቢቶቹ፣ ጥልቅ የሆነው ጥበቡና በሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይሉ መጽሐፍ ቅዱስ በጽሑፍ የሰፈረ የአምላክ ቃል መሆኑን በግልጽ ያረጋግጣሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳሰፈረው “ቅዱስ መጽሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው።”​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16 የ1980 ትርጉም

1. (የመግቢያውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።) (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከት እውነታዎቹ ምን ያረጋግጣሉ? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል ነው የሚለው አባባል ምን አንድምታ አለው?

መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ቃል ሳይሆን የአምላክ ቃል መሆኑ ብዙ አንድምታ አለው። አምላክ ከሰዎች ጋር የሐሳብ ግንኙነት አድርጓል ማለት ነው። ብዙዎቹን ጥያቄዎቻችንን መልሶልናል ለብዙዎቹም ችግሮቻችን መፍትሔው ምን እንደሆነ ጠቁሞናል ማለት ነው። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተጠቅሰው የሚገኙት ተስፋዎች እውነት ናቸው ማለት ነው። የአምላክ መንግሥት በእርግጥ መግዛት ስለ ጀመረ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እዚች ምድር ላይ ያለውን የፍትሕ መጓደል፣ ጭቆናና መከራ ሁሉ ጥርግርግ አድርጎ ለማስወገድ እርምጃ ይወስዳል ማለት ነው።

2. መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ማወቅህ ምን እንድታደርግ ሊያንቀሳቅስህ ይገባል?

2 አሁን የሚነሳው ጥያቄ ይህን ነገር ካወቅህ በኋላ ምን ታደርጋለህ? የሚል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ስለ መሆኑ ያገኘኸው እውቀት ቢያንስ ቢያንስ እንድትመረምረው ሊያነሳሳህ ይገባል። መዝሙራዊው እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ደስታ እንደሚያገኙ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW] ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፣ . . . ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል።”​—⁠መዝሙር 1:​1, 2

እርዳታ ያስፈልግሃል

3, 4. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እንደሚገልጽልን መጽሐፍ ቅዱስ ስናነብ ግልጽ ያልሆነልን ነገር ካጋጠመን ምን ማድረግ ይገባናል? (ለ) ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በተሻለ መንገድ እንዲረዱት ለማገዝ ሁልጊዜ ዝግጁ የሆኑት እነማን ናቸው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ ግልጽ የማይሆንልህ ነገር እንደምታገኝ የታወቀ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:​16) የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው አንድ ታሪክ ይህ ነገር እንግዳ ሊሆንብን እንደማይገባ ያሳያል። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አንድ ኢትዮጵያዊ በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች ያነብ ነበር። ክርስቲያኑ ወንጌላዊ ፊሊጶስ ወደዚህ ሰው ቀረብ ብሎ “በእውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢትዮጵያዊው ሰው የሚያነበውን ነገር ስላላስተዋለው ፊሊጶስ እንዲረዳው ጠየቀ።​—⁠ሥራ 8:​30, 31

4 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ሴት የገጠማትም ሁኔታ ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ነበር። ሳታቋርጥ መጽሐፍ ቅዱስ ታነብ የነበረ ቢሆንም ብቻዋን ልትረዳቸው ያልቻለቻቸው ብዙ ወሳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ነበሩ። የአምላክን መንግሥት አስፈላጊነት እንዲሁም መንግሥቱ ለሰው ዘር የሚያመጣቸውን ብዙ በረከቶች ጨምሮ መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መረዳት የቻለችው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መወያየት ከጀመረች በኋላ ነበር። አንተም ከጋበዝካቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ያነበብከውን ነገር በተሻለ መንገድ እንድታስተውለው ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ሥራበት

5. መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ደስታ የሚያስገኘው የትኛው አካሄድ ነው?

5 መጽሐፍ ቅዱስ እንድናነብ ብቻ ሳይሆን ያነበብነውን ነገር እንድንሠራበትም ጭምር ማበረታቻ ተሰጥቶናል። (መዝሙር 119:​2) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያበረታታናል:- “እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW] ነው።” (መዝሙር 34:​8) በሌላ አባባል አምላክን እንድንፈትነው እየጋበዘን ነው ለማለት ይቻላል። የአምላክን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተከትለህ ለመኖር ሞክር። ይህም ለአንተ የሚበጀውን የሚያውቀው አምላክ መሆኑን እንደምታምን ያሳያል። ትክክለኛው መንገድ ይህ መሆኑን እርግጠኛ የምትሆነው ያኔ ነው። በአምላክ ላይ እንዲህ ዓይነት ትምክህት ያላቸው ሰዎች በእርግጥም ደስተኞች ናቸው።

6. በዛሬው ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃዎች ተከትሎ መኖር ይቻላልን? አብራራ።

6 አንዳንድ ሰዎች በዚህ ሐቀኝነት በጎደለው፣ በሥነ ምግባር በተበላሸና ዓመፀኛ በሆነ ዓለም ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተከትሎ መኖር የሚችል ሰው የለም ይላሉ። ይሁንና ብዙ ሰዎች በዚህ መንገድ መኖር ችለዋል። እነማን? አንድ በአፍሪካ የሚኖር ወጣት እንዲህ ዓይነት ሰዎች ያሉበት ቡድን እንዳለ አስተውሏል። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “በዚህ በዚምባቡዌ ውስጥ በእርግጥ የክርስቶስን ምሳሌ ለመከተል የምትጥሩ ሰዎች እናንተ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ መሆናችሁን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ማስተዋል ችያለሁ። . . . በቃላችሁና በጽሑፋችሁ ብቻ ሳይሆን በኑሯችሁም ጭምር ስለ አምላክ ፍቅር እንድረዳና ወንጌሉ ያለውን ኃይል እንዳስተውል ልታሳምኑኝ የቻላችሁት እናንተ ብቻ ናችሁ። ወንጌልን የሚሰብኩ ነገር ግን በዚያ መሠረት የማይኖሩ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች ቢኖሩም ወንጌልን ተከትላችሁ የምትኖሩና የምትሰብኩ እናንተ ናችሁ።”

ያለውን ሥልጣን ተቀበል

7. ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር የሚቃረኑ ምን የተለመዱ ድርጊቶች አሉ?

7 ሐዋርያው ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስ “ለትምህርት፣ ለተግሣጽ፣ ነገሮችን ለማቅናት” እንደሚጠቅም ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​16 NW) ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ሁሉ በሰፊው ተቀባይነት ያገኛል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ግብረሰዶምን ቢያወግዝም ይህ ተግባር በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው አኗኗር ተደርጎ ይታያል። (ሮሜ 1:​24-27፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​9-11፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:​9-11) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ያልተወለደ ሕፃን ሕይወት ትልቅ ዋጋ እንዳለው በመግለጽ ሆን ብሎ ይህን ሕይወት ማጥፋት እንደማይገባ የሚገልጽ ቢሆንም በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ከ50 ሚልዮን የሚበልጡ ውርጃዎች ይፈጸማሉ። (ዘጸአት 21:​22, 23፤ መዝሙር 36:​9፤ 139:​14-16፤ ኤርምያስ 1:​5) እኛ በግላችን መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህ ነገሮች ረገድ የሚናገረውን ነገር መቀበል ቢከብደንስ?

8, 9. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሐሳቦችን መጀመሪያ ላይ መቀበል ቢቸግረን ምን ነገር ማስታወስ ይገባናል? ሁልጊዜ ልንቀበለው የሚገባን የማንን የአቋም ደረጃ ነው?

8 ክርስቲያኖች ምንጊዜም ቢሆን የአምላክን ቃል መከተል ጥበብ እንደሆነ ተምረዋል። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ነገር መከተል የኋላ ኋላ ጥቅሙ ለራሳችን ነው። (ምሳሌ 2:​1-11) የሰው ልጆች ያላቸው ጥበብ ውስን ነው። አብዛኛውን ጊዜ የሚያደርጉት ነገር የሚያስከትለውን ውጤት ከወዲሁ ማስተዋል አይችሉም። ኤርምያስ እንደሚከተለው ሲል እውነቱን ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።”​—⁠ኤርምያስ 10:​23

9 ይህ አባባል እውነት መሆን አለመሆኑን ለመረዳት ዙሪያችንን መቃኘት ብቻ ይበቃናል። ዓለምን እያሰቃዩ ያሉት አብዛኞቹ ችግሮች ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን ምክር ባለመከተላቸው የመጡ ናቸው። በችግር የተሞላው ረጅሙ የሰው ታሪክ እንደሚያሳየው ሰዎች ለራሳቸው የሥነ ምግባር ደንብ ሊያወጡ አይችሉም። አምላክ ከእኛ እጅግ የላቀ ጥበብ አለው። በራሳችን ጥበብ ከምንመካ ይልቅ እርሱ የሚነግረንን ለምን አናዳምጥም?​—⁠ምሳሌ 28:​26፤ ኤርምያስ 17:​9

ፍጹም የሆነ ሰው የለም

10, 11. (ሀ) ከመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተን ለመኖር ስንጥር ችግር የሚፈጥርብን የትኛው የራሳችንና የምንኖርበት ዓለም ሁኔታ ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ከእነማን ጋር እንድንወዳጅ ያበረታታናል? እንዲህ ዓይነቱን ወዳጅነትስ የምናገኘው የት ነው?

10 መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ እርዳታ የሚሻበትን ሌላም መስክ ይጠቁመናል። ሁላችንም የኃጢአት ዝንባሌ ወርሰናል። “የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነው።” (ዘፍጥረት 8:​21፤ ሮሜ 7:​21) የምንኖርበት ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለመከተል የማይፈልግ በመሆኑ ችግሩ ተባብሶ ይታያል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ብቻ ሳይሆን የተማርነውን ነገር በሥራ ላይ ለማዋልም እርዳታ ማግኘት ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላካዊ የአቋም ደረጃዎችን ተከትለው ለመኖር ከሚሹ ሰዎች ጋር አብረን እንድንሰበሰብ የሚያበረታታንም ከዚህ የተነሣ ነው። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የክፉዎችን ማኅበር ጠላሁ፣ ከዝንጉዎችም ጋር አልቀመጥም። . . . አቤቱ በማኅበር አመሰግንሃለሁ።” ሌላው መዝሙር ደግሞ “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፣ እነሆ፣ መልካም ነው፣ እነሆም ያማረ ነው” ይላል።​—⁠መዝሙር 26:​5, 12፤ 133:​1

11 መሰብሰብ የይሖዋ ምሥክሮች ጉልህ ሥፍራ የሚሰጡት የአምልኳቸው ክፍል ነው። መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ ሆነው የሚያጠኑባቸውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ መሆን ስለሚችሉበት መንገድ የሚወያዩባቸው በርከት ያሉ ሳምንታዊ ስብሰባዎች እንዲሁም በየወቅቱ የሚደረጉ ትላልቅ ስብሰባዎች አሏቸው። ዓለም አቀፍ ‘የወንድማማች ማኅበር’ የመሠረቱ ሲሆን በዚህ አማካኝነት እያንዳንዳቸው የላቁትን የመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ጠብቀው ለመመላለስ የሚያስችል ማበረታቻና እገዛ ያገኛሉ። (1 ጴጥሮስ 2:​17 NW) ከስብሰባዎቻቸው በአንዱ ላይ ተገኝተህ እንዲህ ያለው ማኅበረሰብ አንተንም ጭምር እንዴት ሊረዳህ እንደሚችል ለምን አትመለከትም?​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 25

የአምላክን ቃል መመሪያህ አድርገው

12. መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ከማወቅ የሚገኙት በረከቶች ምንድን ናቸው?

12 እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ማወቅ በረከትም ኃላፊነትም ያመጣል። የትም ልናገኘው የማንችለውን ለዕለታዊ ሕይወታችን የሚሆን መመሪያ ስለሚሰጠን ተባርከናል። በተጨማሪም አምላክ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ሲል የገዛ ልጁ እንዲቤዠን በማድረግ ስላሳየን ፍቅር እንማራለን። (ዮሐንስ 3:​16) ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ እንዳለና በቅርቡም ክፋትን ከምድር ሁሉ እንደሚያስወግድ እንገነዘባለን። አምላክ ራሱ ቃል የገባውን ጽድቅ የሰፈነበት “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” በእርግጠኝነት እንጠብቃለን።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​13

13. መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን አምነን መቀበላችን ምን ኃላፊነት ያስከትልብናል?

13 ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናትና የሚናገረውን ነገር በቁም ነገር የመመልከት ኃላፊነት እንዳለብንም አትዘንጋ። አምላክ ራሱ “ልጄ ሆይ፣ ሕጌን አትርሳ፣ ልብህም ትእዛዜን ይጠብቅ” በማለት አጥብቆ ያሳስበናል። (ምሳሌ 3:​1) አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሰው ቃል አድርገው ቢመለከቱትም እኛ ‘ሰው ሁሉ ውሸተኛ ቢሆን እግዚአብሔር እውነተኛ መሆኑን’ ማሳየት መቻል አለብን። (ሮሜ 3:​4) ሕይወትህ በአምላክ ጥበብ እንዲመራ አድርግ። “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን . . . በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ።” (ምሳሌ 3:​5, 6) በዚህ መንገድ የአምላክን ቃል በጥበብ መከተልህ ለአሁኑም ሆነ ለዘላለማዊ ሕይወትህ ይጠቅምሃል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 187 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ብቻ ሳይሆን ያነበብነውን ተግባራዊ ማድረግ ይገባናል

[በገጽ 188 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን መከተል ሁልጊዜ ጥቅሙ ለእኛ ነው