በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር” የሚቻለው እንዴት ነው?

“ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር” የሚቻለው እንዴት ነው?

ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲገባቸው በመርዳት ረገድ የምንከተለው ኢየሱስ ክርስቶስና የእርሱ ሐዋርያት የተዉልንን ምሳሌ ነው። ኢየሱስ ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች መልስ ይሰጥ የነበረው ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሰ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን እንዲቀበሉ ለመርዳት ተስማሚ በሆኑ ምሳሌዎች ይጠቀም ነበር። (ማቴ. 12:1–12) ሐዋርያው ጳውሎስ በሚያስተምርበት ጊዜ ‘ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሰ ምክንያቱን ያብራራ፣ በጥቅሶች በመጠቀም ያስረዳና ማረጋገጫ ያቀርብ’ ነበር። (ሥራ 17:2, 3 አዓት) በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የቀረቡት ሐሳቦች የኢየሱስ ክርስቶስንና የሐዋርያትን የማስተማሪያ ዘዴ እንድትከተል የሚረዱ ናቸው።

ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለው ይህ መጽሐፍ በእያንዳንዱ ርዕስ ላይ ሰፊና አጠቃላይ የሆኑ ሐሳቦችን ከመስጠት ይልቅ በአሁኑ ወቅት ብዙ ሰዎች ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ቅድሚያ ትኩረት ይሰጣል።

ይህ መጽሐፍ ለእውነት አክብሮት የሌላቸውን ሰዎች “በክርክር ለመርታት” እንዲረዳ ተብሎ የተዘጋጀ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ምክንያቱን እያስረዱ ለማወያየት የሚጠቅም ሐሳብ ይሰጣል። አንዳንድ ሰዎች አጥጋቢ መልስ ሊያገኙላቸው የሚፈልጉ ጥያቄዎችን ይጠይቁ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ በምታነጋግራቸው ጊዜ የግል እምነታቸውን ይገልጹ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከራሳቸው አመለካከት የተለየ ሐሳብ ሲነገራቸው ለማዳመጥ ፈቃደኞችና ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎች ናቸውን? ከሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ልትነግራቸው ትችላለህ። ይህንንም የምታደርገው እውነትን የሚወዱ ሁሉ ልባቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን በደስታ ይቀበላል በሚል ጽኑ እምነት ነው።

ከዚህ መጽሐፍ የምትፈልገውን አንድ ሐሳብ እንዴት ለማግኘት ትችላለህ? ብዙውን ጊዜ ማብራሪያ የተሰጠበትን ጉዳይ የሚወክለውን ዋና ርዕስ በቀጥታ በማውጣት የምትፈልገውን ሐሳብ ለማግኘት ትችላለህ። በሁሉም ዋና ርዕሶች ሥር የሠፈሩትን ዐበይት ጥያቄዎች ማግኘት አያስቸግርም። እነዚህ ጥያቄዎች የገጾቹን የግራ ጠርዝ ይዘው ጎላ ጎላ ባሉ ፊደላት ተጽፈዋል። የምትፈልገውን ሐሳብ በፍጥነት ማግኘት ካልቻልክ ከመጽሐፉ በስተመጨረሻ ባሉት ገጾች ላይ የሚገኘውን ማውጫ ተመልከት።

ከሰዎች ጋር ለምታደርገው ውይይት በቅድሚያ መዘጋጀት ምን ጊዜም ቢሆን ጠቃሚ ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ ክፍሎች ገና በደንብ የማታውቃቸው ቢሆንም እንኳ በሚገባ ልትጠቀምባቸው ትችላለህ። እንዴት? ልትወያይበት ከምትፈልገው ነጥብ ጋር የሚዛመደውን ጥያቄ በምታገኝበት ጊዜ ከጥያቄው ሥር የሰፈሩ ንዑስ ርዕሶች እንዳሉ ተመልከት። እነዚህ ንዑስ ርዕሶች ዋናው ጥያቄ ከተጻፈበት መሥመር ገባ ብለው ጎላና ጋደል ባሉ (በደማቅ አይታሊክ) ፊደላት ተጽፈዋል። ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ቀደም ብለህ የምታውቀው ነገር ካለ ንዑስ ርዕሶችን መከለስና ከሥር የቀረቡትን ሐሳቦች በፍጥነት ማየት ብቻ ሊበቃህ ይችላል። እነዚህ ንዑስ ርዕሶች ጠቃሚ ምክንያቶችን ይደረድራሉ። ሐሳቡን በራስህ አነጋገር ከመግለጽ ወደኋላ አትበል።

ተጨማሪ ሐሳብ መስጠት፣ ምናልባትም የተጠቀሰውን ጥቅስና ጥቅሱን ለማብራራት የቀረበውን ሐሳብ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ቃል ምክንያታዊ መሆኑን ለማስረዳት የቀረቡትን ምሳሌዎችና የመሳሰሉትን ነገሮች መጨመር የሚያስፈልግ ሆኖ ይሰማሃልን? ከሆነ ለምታነጋግረው ሰው ከዚህ መጽሐፍ ላይ ያገኘኸውን ሐሳብ ልታሳየውና እርሱ ላቀረበው ጥያቄ የተሰጠውን መልስ አብራችሁ ለማንበብ ትፈልግ ይሆናል። ይህን ርዕስ ቀደም ብለህ ያላነበብከው ቢሆንም አጥጋቢ መልሶች ለመስጠት ልትጠቀምበት ትችላለህ። ማንኛውም ነገር በቀላልና እጥር ምጥን ባለ መንገድ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቀርቧል።

ይህ መጽሐፍ ለእርዳታ ብቻ የተዘጋጀ መሆኑን አትዘንጋ። ለትምህርታችን መሠረት አድርገን የምንጠቅሰው መጽሐፍ ቅዱስን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ ሐሳቦች በሚኖሩበት ጊዜ የምታነጋግረው ሰው የተጠቀሰው ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መሆኑን እንዲያውቅ አድርግ። በተቻለ መጠን የምትናገረው ነገር በራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሚገኝ ማየት እንዲችል የራሱን መጽሐፍ ቅዱስ ገልጦ እንዲመለከት ጠይቀው። በብዙ ሰዎች ዘንድ የታወቁ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አንድን ቁልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ለየት ባለ መንገድ በሚተረጉሙበት ጊዜ የአተረጓጎም ልዩነት መኖሩ ተገልጿል። ለማስተያየት እንዲቻል የሌሎች በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጎሞች አተረጓጎም ቀርቧል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለአቴና ሰዎች ሲሰብክ “ለማይታወቅ አምላክ” የተሠራውን መሠዊያና ሌሎች የታወቁ ዓለማዊ ታሪኮችን በመጥቀስ ከተወልን ምሳሌ ጋር በመስማማት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከዓለም ታሪክ፣ ከኢንሳይክሎፔድያ፣ ሃይማኖት ነክ ከሆኑ መጻሕፍትና ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት የተጠቀሱ ማስረጃዎች በመጠኑ ይገኛሉ። (ሥራ 17:22–28) ስለዚህ ይህ መጽሐፍ የሐሰተኛ ሃይማኖታዊ ልማዶችን አጀማመር፣ ወይም የአንዳንድ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን አመጣጥ፣ ወይም የአንዳንድ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላትን ትርጉም ለማስረዳት ከመሞከር ይልቅ ይህ መጽሐፍ ለተናገርናቸው ነገሮች ማስረጃ የሚሆኑ ምክንያቶችን ያቀርባል። ይሁን እንጂ ሰዎች መሠረታዊው የእውነት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን እንዲገነዘቡ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሌሎች ለማካፈል የምትችልበትን መንገድ ለማመቻቸት ሲባል በዚህ መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ “ለመስክ አገልግሎት የሚጠቅሙ መግቢያዎች” እና “ውይይት የሚያስቆሙ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ እንዴት መልስ መስጠት” እንደሚቻል የሚገልጹ ነጥቦች ተዘርዝረዋል። “ውይይት የሚያስቆሙ” ሌሎች ሐሳቦች ብዙውን ጊዜ ከአንዳንድ ሃይማኖታዊ እምነቶች ጋር የተዛመዱ ስለሆኑ እነዚህ ሰዎች የሚያቀርቡት የተቃውሞ ሐሳብ ከእነዚህ እምነቶች ጋር ግንኙነት ባላቸው ዋና ክፍሎች መጨረሻ ላይ ቀርቧል። እዚህ ላይ የተሰጡት መልሶች በቃላችሁ እንድታጠኗቸው ታቅደው የቀረቡ አይደሉም። ይሁን እንጂ ሌሎች እነዚህን ሐሳቦች ለምን ጥሩ ውጤት እንዳገኙባቸው ብትመረምር ብዙ እንደምትጠቀም አያጠራጥርም። ከዚያም በኋላ ሐሳቡን በራስህ አነጋገር ለመግለጽ ሞክር።

በኪስ ሊያዝ በሚችለው በዚህ መጽሐፍ መጠቀምህ ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክንያቱን የማስረዳት ችሎታህን ለማዳበርና ሌሎች ሰዎች ስለ “አምላክ ታላላቅ ነገሮች” እንዲማሩ ለመርዳት በቅዱሳን ጽሑፎች በሚገባ ለመጠቀም ሊረዳህ ይገባል ብለን እናምናለን።—ሥራ 2:11 አዓት