በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዝግመተ ለውጥ

ዝግመተ ለውጥ

ፍቺ:- የመጀመሪያው ሕይወት ያለው አካል የተገኘው ሕይወት ከሌለው ነገር ነው የሚለው ንድፈ ሐሳብ ኦርጋኒክ ኢቮሉሽን (ሕይወት ያላቸው ነገሮች ዝግመተ ለውጥ) ይባላል። የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ያ ሕይወት ያለው ነገር እየተራባ ሲሄድ ወደተለያዩ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ተለወጠና በመጨረሻ በዚህች ምድር ላይ እስከ አሁን የኖሩትን ሁሉንም የዕፅዋትና የእንስሳት ዓይነት አስገኘ ይላል። ይህ ሁሉ የተከናወነው ከፍጥረታት በላይ የሆነ የፈጣሪ ጣልቃ ገብነት ሳይኖር ነው ይባላል። አንዳንድ ሰዎች አምላክ ፍጥረታትን የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ነው በማለት በአምላክ ማመንን ከዝግመተ ለውጥ ሐሳብ ጋር ለማዋሃድ ይሞክራሉ። የመጀመሪያዎቹ ዝቅተኛ ሕይወት ያላቸው ነገሮችና በኋላም የተገኙት ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ሕያዋን ነገሮች፣ ሰውም ጭምር የተገኙት በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ነው ይላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም።

 ዝግመተ ለውጥ በእርግጥ ሳይንሳዊ ነውን?

“ሳይንሳዊ ዘዴ” የሚባለው የማረጋገጫ መንገድ እንደሚከተለው ነው:- የሚሆነውን ነገር መመልከትና ማስተዋል፤ በታየውና በተስተዋለው ነገር ላይ ተመርኩዞ እውነት ይሆናል ተብሎ የሚታሰበውን ነገር በንድፈ ሐሳብ መልክ ማቅረብ፤ በንድፈ ሐሳብ መልክ የቀረበውንም ተጨማሪ ነገሮችን በመመልከትና በቤተ ሙከራ በመፈተሽ የንድፈ ሐሳቡን ትክክለኛነት መፈተን፤ ከዚያ በንድፈ ሐሳቡ ላይ የተመሠረተው ትንበያ በትክክል ይፈጸም እንደሆነ ለማየት ክትትል ማድረግ። በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑና ዝግመተ ለውጥን የሚያስተምሩ ሰዎች የሚከተሉት ይህንን ዘዴ ነውን?

የጠፈር ተመራማሪ የሆኑት ሮበርት ጃስትሮው እንዲህ ብለዋል:- “[የሳይንስ ሊቃውንትን] ተስፋ ያስቆረጣቸውና ቁርጥ ያለ መልስ እንዳይኖራቸው ያደረጋቸው ነገር፣ ኬሚስቶች ተፈጥሮ አድርጋለች እንደሚባለው ሕይወት ከሌለው ነገር ሕይወት ያለው ነገር አስገኝተው ለማሳየት አለመቻላቸው ነው። ሳይንቲስቶች ሕይወት ያለው ነገር ሕይወት ከሌለው ነገር እንዴት ሊገኝ እንደቻለ የሚያውቁት ነገር የላቸውም።”—ዘ ኢንቻንትድ ሉም:- ማይንድ ኢን ዘ ዩኒቨርስ (ኒው ዮርክ፣ 1981)፣ ገጽ 19

የዝግመተ ለውጥ አራማጅ የሆኑት ሎረን አይስሌ እንዲህ በማለት ሐቁን አምነዋል:- “ሳይንስ ሃይማኖተኞችን እውነተኝነት በሌላቸው ነገሮችና በተአምራት የሚያምኑ ናቸው በማለት ከዘበተባቸው በኋላ ሳይንስ ራሱ ያልተጨበጠና በአፈ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ፈጥሯል። ከረጅም ዘመናት ጥረት በኋላ እንኳን ትክክለኛነቱ ሊረጋገጥ ያልቻለውን ግምታዊ አስተሳሰብ በጥንት ዘመን ተፈጽሞ ነበር ይላል።”—ዘ ኢሜንስ ጀርኒ (ኒው ዮርክ፣ 1957)፣ ገጽ 199

ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “ቁጥራቸው እየጨመረ ያሉ በርካታ ሳይንቲስቶች፣ በተለይም በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ ሳይንቲስቶች . . . የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ፈጽሞ እውነተኛ ሳይንሳዊ ንድፈ ሐሳብ አይደለም በማለት ይከራከራሉ። . . . ይህን የመሰለ ትችት የሚያቀርቡት በጣም የተከበሩ ምሁራን ናቸው።”—ሰኔ 25, 1981፣ ገጽ 828

የፊዚክስ ምሁር የሆኑት ኤች ኤስ ሊፕሰን እንዲህ ብለዋል:- “እንዴት ተገኘን? ለሚለው ጥያቄ ተቀባይነት ያለው መልስ ፍጥረት ብቻ ነው። ይህን አባባል የፊዚክስ ምሁራን እንደሚጠሉት አውቃለሁ፤ እኔም ብሆን አልወደውም። ይሁን እንጂ የቤተ ሙከራ መረጃ የሚደግፈው ከሆነ የማንወደውንም ንድፈ ሐሳብ መቀበል ይኖርብናል።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።)—ፊዚክስ ቡለቲን፣ 1980፣ ጥራዝ 31፣ ገጽ 138

  የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አራማጆች እርስ በርስ ይስማማሉን? ይህስ ስለሚያስተምሯቸው ነገሮች ምን እንዲሰማህ ያደርጋል?

ኦሪጅን ኦቭ ስፒሽስ ለተባለው የዳርዊን መጽሐፍ መቶኛ ዓመት መታሰቢያ የወጣው ጽሑፍ (ለንደን፣ 1956) በመግቢያው ላይ እንዲህ ይላል:- “እንደምናውቀው በባዮሎጂ ምሁራን መካከል ለዝግመተ ለውጥ መንስኤ ስለሆኑት ምክንያቶች ብቻ ሳይሆን ስለ ሂደቱም ቢሆን ሰፊ የሐሳብ ልዩነት አለ። ይህ ልዩነት ሊኖር የቻለው መረጃው አጥጋቢና የተረጋገጠ ድምዳሜ ላይ ሊያደርስ የሚያስችል ባለመሆኑ ነው። ስለዚህ በሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ ለማይሳተፈው ተራ ሕዝብ በዝግመተ ለውጥ ላይ የተፈጠረውን አለመስማማት ማሳወቅ ትክክልና ተገቢ ነው።”—የኮመን ዌልዝ ኢንስቲትዩት ኦቭ ባዮሎጂካል ኮንትሮል ዲሬክተር የነበሩት ደብልዩ አር ቶምሰን፣ ኦታዋ፣ ካናዳ

“ዳርዊን ከሞተ ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ እንኳን ዝግመተ ለውጥ እንዴት እንደተከናወነ በትንሹ እንኳን የምናሳይበት መረጃ ወይም ምክንያታዊ የሆነ መግለጫ ለማቅረብ አልቻልንም። በዚህም ምክንያት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ላይ ብዙ ክርክር ተነሥቷል። . . . በራሳቸው በዝግመተ ለውጥ አማኞች መካከል ግልጽ የሆነ ጦርነት ተፈጥሯል። እያንዳንዱ [የዝግመተ ለውጥ አማኞች] አንጃ አንድ ዓይነት አዲስ ማሻሻያ እንዲደረግ ይወተውታል።”—ሲ ቡከር (የለንደን ታይምስ ጋዜጣ ጸሐፊ)፣ ዘ ስታር (ጆሐንስበርግ)፣ ሚያዝያ 20, 1982፣ ገጽ 19

ዲስከቨር የተባለው ሳይንሳዊ መጽሔት “ዝግመተ ለውጥ . . . ጥቃት የተሰነዘረበት ከአክራሪ ክርስቲያኖች ብቻ አይደለም። የታወቁ ሳይንቲስቶችም ትክክለኛነቱን ተጠራጥረዋል። ቅሪተ አካልን ከሚያጠኑት ሳይንቲስቶች መካከል አንዳንዶች በዝግመተ ለውጥ እንደማያምኑ እየገለጹ ናቸው” ብሏል።—ጥቅምት 1980፣ ገጽ 88

 የቅሪተ አካላት መረጃ የትኛውን አመለካከት ይደግፋል?

ዳርዊን “የበርካታ ፍጥረታት ወገኖች . . . የተገኙት በአንድ ጊዜ ከሆነ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ውሸት ይሆናል ማለት ነው” ብሎ ነበር። (ዘ ኦሪጅን ኦቭ ስፒሽስ፣ ኒው ዮርክ፣ 1902፣ ክፍል ሁለት፣ ገጽ 83) የተገኘው ማስረጃ የሚያሳየው “በርካታ ፍጥረታት” በአንድ ጊዜ እንደተገኙ ነው ወይስ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እንደሚለው ቀስ በቀስ እየተሻሻሉ እንደመጡ?

አስተማማኝ ከሆነ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ በቂ ቅሪተ አካላት ተገኝተዋልን?

የስሚትሶንያን ኢንስቲትዩሽን ሳይንቲስት ፖርተር ኬር እንዲህ ብለዋል:- “በምድር ዙሪያ በሚገኙ ሙዚየሞች ውስጥ ተለይተውና ተመዝግበው የተቀመጡ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ቅሪተ አካላት ይገኛሉ።” (ኒው ሳይንቲስት፣ ጥር 15, 1981፣ ገጽ 129) ኤ ጋይድ ቱ ኧርዝ ሂስትሪ (የምድር ታሪክ መምሪያ) በተጨማሪ እንዲህ ይላል:- “የቅሪተ አካል አጥኚዎች በቅሪተ አካላት እየተረዱ ጥንት ስለነበሩት ሕያዋን ፍጥረታት የሚገልጽ ውብ የሆነ ሥዕል ሊያቀርቡልን ይችላሉ።”—(ኒው ዮርክ፣ 1956)፣ ሪቻርድ ካሪንግተን፣ በሜንቶር የታተመ፣ ገጽ 48

ቅሪተ አካላቱ ምን ያሳያሉ?

የቺካጎ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ቡለቲን እንዲህ ብሏል:- “የዳርዊን [የዝግመተ ለውጥ] ንድፈ ሐሳብ ከቅሪተ አካሎች ከሚገኘው መረጃ ጋር በቅርብ የተያያዘ ነው። ብዙ ሰዎች የዳርዊናዊውን የሕይወት አመጣጥ ታሪክ አብራርቶ ለማስረዳት ቅሪተ አካሎች ከፍተኛ ድጋፍ ያበረክታሉ ብለው ያስቡ ይሆናል። የሚገርመው ግን ይህ እውነት አለመሆኑ ነው። . . . እንደ ሰንሰለት በሚገባ የተያያዘና ደረጃውን ጠብቆ ቀስ እያለ እያደገ የመጣ የዝግመተ ለውጥ መረጃ ድሮም ሆነ አሁን ከጂኦሎጂ ጥናት አልተገኘም።”—ጥር 1979፣ ጥራዝ 50፣ ቁጥር 1፣ ገጽ 22, 23

ኤ ቪው ኦቭ ላይፍ (የሕይወት አመለካከት) እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የካምብሪያን ዘመን ተብሎ ከሚጠራው ጊዜ ጀምሮ ለ10 ሚልዮን ዓመታት ያህል ሁሉም የጀርባ አጥንት የሌላቸው ፍጥረታት በምድር ላይ ሆኖ በማያውቅ መጠን በአንድ ጊዜ የተለያየ መልክና ቅርጽ ይዘው በብዛት ብቅ ብለዋል።”—(ካሊፎርኒያ፣ 1981) ሳልቫዶር ኢ ሉሪያ፣ ስቴፈንስ ጄይ ጐልድ፣ ሳም ሲንገር፣ ገጽ 649

የቅሪተ አካል ተመራማሪ የሆኑት አልፍረድ ሮመር እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “[ከካምብሪያን ዘመን] በታች በካምብሪያን ዘመን የተገኙት የእንስሳት አባቶች ይገኙበታል ተብሎ የሚታሰብበት በርካታ የደለል ክምችት ይገኛል። ሆኖም ግን ይገኛሉ የተባሉት ቅሪተ አካላት ሊገኙ አልቻሉም። በዚህ ዘመን ሕይወት ያለው ነገር ይኖርበት እንደነበረ የሚያመለክት ምንም መረጃ አልተገኘም። አጠቃላይ ሁኔታው በካምብሪያን ዘመን መጀመሪያ ላይ ልዩ በሆነ መንገድ ፍጥረት ተፈጥሯል ከሚለው ሐሳብ ጋር ይስማማል ሊባል ይቻላል።”—ናቹራል ሂስትሪ (የተፈጥሮ ታሪክ)፣ ጥቅምት 1959፣ ገጽ 467

ስለ እንስሳት ሕይወት የሚያጠኑት ሐሮልድ ኮፊን እንዲህ በማለት ይናገራሉ:- “ከቀላል ወደ ውስብስብ እያደገ የመጣው ዝግመተ ለውጥ ትክክል ቢሆን ኖሮ፣ በካምብሪያን ዘመን የተገኙት ሕያዋን ፍጥረታት ወላጆች ቅሪተ አካላት በተገኙ ነበር። እስከ አሁን ግን አልተገኙም፣ ወደፊትም ይገኛሉ የሚል ተስፋ እንደሌለ ሳይንቲስቶች አልሸሸጉም። ከመሬት ውስጥ ተቆፍረው በተገኙትና እስካሁን በተሰበሰቡት ተጨባጭ ማስረጃዎች መሠረት ዋናዎቹ ፍጥረታት የተገኙት አንድ ጊዜ በተከናወነ የፍጥረት ሥራ ነው ከሚለው ንድፈ ሐሳብ ጋር በትክክል ይስማማል።”—ሊበርቲ፣ መስከ ረም/ጥቅምት 1975፣ ገጽ 12

ካርል ሳጋን ኮስሞስ በተባለው መጽሐፋቸው “ከቅሪተ አካላት የተገኘው መረጃ ታላቅ ንድፍ አውጭ አለ ከሚለው ሐሳብ ጋር ሊስማማ ይችላል” በማለት በግልጽ አስታውቀዋል።—(ኒው ዮርክ፣ 1980)፣ ገጽ 29

የዝግመተ ለውጥ ሂደቶች የተከናወኑት በዘር ባሕርያት ተሸካሚዎች (ጂንስ) ላይ በደረሰ ቅጽበታዊና ታላቅ ለውጥ (ሚዩቴሽን) የተነሣ ሊሆን አይችልምን?

ሳይንስ ዳይጀስት እንዲህ ይላል:- “የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ከላሾች እመርታው እንዲፈጸም ያደረገው ቁልፍ በሆኑ ጂኖች ወይም የዘር ባሕርያት ተሸካሚዎች ላይ የተከናወኑት ቅጽበታዊ ለውጦች (ሚዩቴሽን) ናቸው ብለው ያምናሉ።” ይሁን እንጂ መጽሔቱ የብሪታንያ የእንስሳት ሕይወት አጥኚ የሆኑት ኮሊን ፓተርሰን የተናገሩትን በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “ይህ አስተሳሰብ በነፃ ግምት ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው። ስለነዚህ ቁልፍ የሚባሉ የዘር ተቆጣጣሪና የዘር ባሕርያት ተሸካሚዎች (ጂኖች) የምናውቀው ነገር የለም።” (የካቲት 1982፣ ገጽ 92) በሌላ አባባል ንድፈ ሐሳቡን የሚደግፍ መረጃ አልተገኘም።

ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንዲህ ብሏል:- “በሕያዋን ነገሮች የዘር ባሕርያት ተሸካሚዎች ላይ (በጂኖች ላይ) የሚከናወነው ቅጽበታዊ ታላቅ ለውጥ (ሚዩቴሽን) ጐጂ ሆኖ ስለተገኘ ዝግመተ ለውጥ የሚያስፈልገውን ጥሬ ነገር የሚያቀርበው በዘር ባሕርያት ተሸካሚዎች ላይ (በጂኖች ላይ) የሚደርሰው ቅጽበታዊ ለውጥ (ሚዩቴሽን) ነው ከሚለው ሐሳብ ጋር ማስታረቅ ከባድ የሚሆን ይመስላል። በባዮሎጂ ማስተማሪያ መጻሕፍት ቅጽበታዊ ለውጥ አሳይተዋል ተብለው የሚቀርቡት ምሳሌዎች በመረጃ ላይ ያልተመሠረቱና የማይታመኑ ናቸው። ቅጽበታዊ ለውጥ (ሚዩቴሽን) ከመገንባት ይልቅ የማፍረስ ባሕርይ ያለው ይመስላል።”—(1977)፣ ጥራዝ 10፣ ገጽ 742

በትምህርት ቤት መማሪያ መጻሕፍት፣ በኢንሳይክሎፔድያዎችና በሙዚየሞች ተስለው ስለሚገኙት “ሰው መሰል ጦጣዎች” ምን ሊባል ይቻላል?

“እንደገና ተገጣጥመው የተሠሩት ሰው መሰል ጦጣዎች የአካልና የፀጉር ሁኔታ ግምት ብቻ ነው። . . . ከታሪክ ዘመናት በፊት ስለነበሩት ስለ እነዚህ ፍጡሮች የቆዳ ቀለም፣ የፀጉር ቀለም፣ የፀጉር ቅርጽ፣ የፀጉር ሥርጭት፣ የፊት ቅርጽና ገጽታ ምንም የምናውቀው ነገር የለም።”—ዘ ባዮሎጂ ኦቭ ሬስ (የዘር ሥነ ሕይወት)፣ (ኒው ዮርክ፣ 1971)፣ ጄምስ ሲ ኪንግ፣ ገጽ 135, 151

“የአብዛኞቹ ሰዓሊዎች ሥራ በግምት ላይ እንጂ በመረጃ ላይ የተመሠረተ አይደለም። . . . ሰዓሊዎቹ በጦጣና በሰው መካከል የሆነ አንድ ፍጥረት መፍጠር ነበረባቸው። የተገኘው ቅሪተ አካል በጣም የቆየ ነው ከተባለ ይበልጥ ጦጣ እንዲመስል አድርገው ይስሉታል።”—ሳይንስ ዳይጀስት፣ ሚያዝያ 1981፣ ገጽ 41

“የጥንት ሰዎች ያልሰለጠኑ አለመሆናቸውን ቀስ በቀስ እንደተማርን ሁሉ በበረዶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት የጥንት ሰዎችም ጨካኝ አውሬዎች ወይም ግማሽ ጦጣዎች ወይም አካላቸው የጎበጠ፣ አእምሯቸው ያልዳበረ እንዳልነበሩ መገንዘብ ይኖርብናል። እንግዲያውስ ቅሪተ አካሎችን በማገጣጠም የኒያንደርታል ወይም የፔኪንግ ሰውን ለመሥራት የሚደረገው ሙከራ በቃላት መግለጽ ከሚቻለው በላይ ቂልነት ነው።”—ማን፣ ጎድ ኤንድ ማጂክ (ሰው፣ አምላክና አስማት)፣ (ኒው ዮርክ፣ 1961)፣ ኢቫር ሊስነር፣ ገጽ 304

የመማሪያ መጻሕፍት ዝግመተ ለውጥን የተረጋገጠ እውነት አድርገው ያቀርቡት የለምን?

“ብዙ ሳይንቲስቶች የሐሳበ ግትርነትና የቀኖናዊነት ባሕርይ ይታይባቸዋል። . . . ስለ ፍጥረታት አመጣጥ የተነሣው ጥያቄ ያለቀለትና የተረጋገጠ እንደሆነ ተደርጎ ተደጋግሞ ቀርቧል። ይሁን እንጂ ነገሩ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው። . . . ቢሆንም ሐሳበ ግትርነት ወይም በግድ እመኑ የማለት ዝንባሌ ተስፋፍቶ ይገኛል። ይህ ደግሞ የሳይንስን ዓላማ የሚያራምድ አይደለም።”—ዘ ጋርዲያን፣ ለንደን፣ ኢንግላንድ፣ ታኅሣሥ 4, 1980፣ ገጽ 15

ነገር ግን በዚህች ምድር ላይ የሚገኙ ነገሮች ሁሉ የተፈጠሩት በስድስት ቀን ውስጥ ነው ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነውን?

አንዳንድ የሃይማኖት ቡድኖች አምላክ ሁሉንም ነገሮች የፈጠረው እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀኖች ውስጥ ነው ብለው ያስተምራሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ አይልም።

ዘፍጥረት 1:3–31 አምላክ አስቀድሞ የፈጠራትን መሬት ለሰው መኖሪያ እንድትሆን እንዴት እንዳዘጋጃት ይገልጻል። ይህ የተከናወነው በስድስት ቀኖች ውስጥ እንደሆነ ይናገራል እንጂ እነዚህ ስድስት ቀኖች እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝመት እንዳላቸው አይገልጽም። አንድ ሰው “በአያቴ ዘመን (ቀን)” ብሎ ቢናገር እንግዳ ነገር አይሆንም። ይህም አያቱ በሕይወት የኖሩበትን ጊዜ ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስም “ቀን” የሚለውን ቃል ረጅም ጊዜን ለመግለጽ ብዙ ጊዜ ይጠቀምበታል። (ከ⁠2 ጴጥሮስ 3:8 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ላይ የተጠቀሱት ‘ቀኖች’ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ሊሆኑ ይችላሉ።

ለተጨማሪ መረጃ ገጽ 87⁠ን ተመልከት።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘የማምነው በዝግመተ ለውጥ ነው’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘የዝግመተ ለውጥን ሂደት በመቆጣጠር ረገድ የአምላክ እጅ አለበት ብለው ያምናሉ ወይስ የሕይወት አመጣጥና እድገት ከመጀመሪያ ጀምሮ በአጋጣሚ ብቻ የተከናወነ ነው ብለው ያምናሉ? (ሰውዬው በሚሰጡት መልስ መሠረት ውይይትህን ቀጥል።)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠን ሳይንሳዊ ሐቅ መካድ ትክክል አይሆንም። . . . ይህንን ነጥብ በተመለከተ አንዳንድ ሳይንቲስቶች የሰጧቸው ጥሩ ጥሩ አስተያየቶች አሉኝ። ( በገጽ 121, 122 “ዝግመተ ለውጥ በእርግጥ ሳይንሳዊ ነውን?” ወይም  በገጽ 122, 123 ላይ “የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አራማጆች እርስ በርስ ይስማማሉን? . . .” በሚለው ሥር የቀረቡትን ሐሳቦች ተጠቀምባቸው።)’

ሌላ አማራጭ:- ‘አንድ ነገር እውነት መሆኑን የሚያረጋግጥ የተጨበጠ መረጃ ሲገኝ ሁላችንም ያን ነገር ማመን ይኖርብናል። . . . ተማሪ ሳለሁ በተማርኩባቸው መጻሕፍት ላይ የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ ለመደገፍ ቅሪተ አካላትን የሚያሳዩ ሥዕሎች ቀርበው እንደነበረ ትዝ ይለኛል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሳይንቲስቶች ቅሪተ አካላትን በተመለከተ የሰጧቸውን አንዳንድ አስተያየቶች አንብቤአለሁ። (በገጽ  123, 124 ንዑስ ርዕስ ሥር “የቅሪተ አካላት መረጃ የትኛውን አመለካከት ይደግፋል?” የሚለውን ሐሳብ ተጠቀምበት።)’

ተጨማሪ ሐሳብ:- ‘እርስዎ ሕይወትን እንደ አመጣጡ ለመቀበል የሚወዱና ከሐቁ ለመሸሽ የማይፈልጉ ሰው ነዎት ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። . . . እኔም እንደርስዎ ነኝ።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ገጠር ብሄድና አንድ ከጭቃና ከድንጋይ የተሠራ ቤት ባይ ከእኔ በፊት በዚያ ቦታ አንድ ሰው እንደነበረና ቤት እንደሠራ በግልጽ መረዳት አልችልም? . . . ነገር ግን ከቤቱ ዙሪያ የበቀሉት አበቦች በአጋጣሚ የመጡ ናቸው ብዬ ብናገር ምክንያታዊና ትክክለኛ እሆናለሁ እንዴ? እንደዚህ የሚሰማኝ ከሆነ ውስብስብ የሆነውን የአበባ ንድፍ ቀረብ ብዬ ማየት ያስፈልገኛል። ምክንያቱም ንድፍ ካለ ንድፍ አውጪ መኖሩ የታወቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠ዕብራውያን 3:4 ላይ የሚነግረንም ይህንኑ ነው።’

ወይም እንዲህ ብለህ ልትመልስ ትችላለህ (ትልቅ ሰው ከሆኑ):- ‘ከዝግመተ ለውጥ መሠረተ ሐሳቦች አንዱ ሰው ዛሬ ከሚገኝበት የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ የቻለው ብዙ መሻሻል አድርጎ ነው ይላል። ልክ አይደለሁም?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘እርስዎ ረዘም ላሉ ዘመናት ኖረዋል። ልጅ በነበሩበት ጊዜ ነገሮች ሁሉ እንዴት እንደነበሩ ያስታውሳሉ? የዛሬውን ያህል ወንጀል ይበዛ ነበር? . . . ሁልጊዜ በር ትቆልፉ ነበር? . . . ያን ጊዜ የነበሩ ሰዎች ከዛሬዎቹ የበለጠ ለጐረቤቶቻቸው፣ ለሽማግሌዎችና ለባልቴቶች አያስቡም ነበር? . . . ሰዎች በቴክኒክ መስኮች ትልቅ መሻሻል ቢያሳዩም ከዚህ የበለጠ ዋጋ ያላቸውን ባሕርያት እየጣሏቸው የመጡ ይመስላል። ይህ ለምን ሆነ?’ (2) ‘እነዚህ ያየናቸው የሕይወት ትክክለኛ እውነታዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በ⁠ሮሜ 5:12 ላይ ከተጻፈው ነገር ጋር የሚስማሙ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። . . . ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ የምናየው የነገሮችን መሻሻል ሳይሆን እየዘቀጡ መሄዳቸውን ነው።’ (3) ‘ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ እንዴት እንደሚለወጥ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። (ዳን. 2:44፤ ራእይ 21:3, 4)’

‘አምላክ ሰውን የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ነው ብዬ አምናለሁ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘የእርስዎ ዓይነት አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር ተነጋግሬአለሁ። በአምላክ ላይ የጠነከረ እምነት ያለዎት ሰው ነዎት ብዬ ብደመድም ትክክል ሳልሆን አልቀርም፤ አይደለም? . . . በሕይወትዎ ውስጥ ቀዳሚ ቦታ የያዘው እምነትዎ ነው። ሌሎች ነገሮችን ሁሉ የሚገመግሙት እምነትዎን መመሪያ በማድረግ ነው። አይደለም እንዴ? . . . የእኔም አመለካከት ከእርስዎ የተለየ አይደለም።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘የማምንበት ነገር በእርግጥ እውነት ከሆነ ከተረጋገጠ ሳይንሳዊ ሐቅ ጋር እንደማይቃረን አውቃለሁ። የአምላክ ቃል የሚናገረውንም ችላ ብል ሞኝነት እንደሚሆንብኝ እረዳለሁ። ምክንያቱም አምላክ ስለሠራቸው ነገሮች ከማንም የበለጠ ያውቃል። በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠ዘፍጥረት 1:21 የተናገረው በጣም ነክቶኛል። (“እንደ ወገኑ” የሚለውን አጉላ)’ (2) ‘በ⁠ዘፍጥረት 2:7 ላይ አምላክ ሰውን ከቀድሞዎቹ እንስሳት ሳይሆን ከምድር አፈር እንዳበጀው እንረዳለን።’ (3) ‘በቁጥር 21, 22 ላይ ደግሞ ሔዋን የተፈጠረችው ከእንስሳት ሳይሆን ከአዳም የጐን አጥንቶች አንዷ ተወስዳ መሆኑን እንረዳለን።’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘(ከላይ እንደቀረበው በጋራ የምትስማሙበትን ነጥብ መንደርደሪያ ካደረግህ በኋላ . . . ) አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው አዳም እውነተኛ ሰው ሳይሆን ምሳሌያዊ ሰው እንደሆነ አድርጎ ነው ይላሉ። ይህ እውነት ከሆነ ወደ የትኛው መደምደሚያ ይመራል?’ (1) ‘በ⁠ሮሜ 5:19 የተገለጸውን ልብ ይበሉ:- “በአንድ ሰው [በአዳም] አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፣ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ [በኢየሱስ ክርስቶስ] መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” በተመሳሳይ 1 ቆሮንቶስ 15:22 እንዲህ ይላል:- “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉ።” አዳም የተባለ “አንድ ሰው” ካልነበረ ይህ ሰው ኃጢአት አልሠራም ማለት ነው። ኃጢአት ካልሠራና ለዘሮቹ ኃጢአት ካላወረሰ ደግሞ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል ሕይወቱን መስጠት አያስፈልገውም ነበር ማለት ነው። ክርስቶስ ለእኛ ሲል ሕይወቱን ካልሰጠ ከአሁን በኋላ ከሚቀሩን ጥቂት ዓመታት ሌላ በሕይወት የመኖር ተስፋ አይኖረንም ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ ክርስቲያንነት ምንም ጥቅም አይኖረውም ማለት ነው።’ (2) ‘ይሁን እንጂ በየትኛውም ቦታ ከሚገኙት የበለጡ የሥነ ምግባር መመሪያዎች የሚገኙት በክርስትና እምነት ውስጥ ነው። ስለ እውነትና ስለታማኝነት የሚያስተምሩት እጅግ መልካም የሆኑ ትምህርቶች መሠረታቸው ውሸት ከሆነ ነገር ሊመነጩ ይችላሉ?’ (በተጨማሪ በገጽ 27–29 ላይ “አዳምና ሔዋን” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር ተመልከት።)

‘ነገር ግን ከፍተኛ ትምህርት ያላቸው ሰዎችም በዝግመተ ለውጥ ያምናሉ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ይህ እውነት ነው። ይሁን እንጂ እናምንበታለን የሚሉትም ቢሆኑ ከሌሎቹ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ጋር እንደማይስማሙ ተረድቻለሁ። ( ገጽ 122, 123 ላይ የተገለጹትን ምሳሌዎች ጥቀስ።) ከዝግመተ ለውጥና ከፍጥረት አንደኛውን ለመምረጥ እንድንችል በየግላችን መረጃዎቹን መመርመር ይኖርብናል።’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ይህ እውነት ነው። ይሁን እንጂ ከፍተኛ ትምህርት ያላቸው ሆነው በዝግመተ ለውጥ የማያምኑ ሰዎችም እንዳሉ አውቃለሁ።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ይህ ልዩነት ለምን ተፈጠረ? ሁሉም ስለ ዝግመተ ለውጥ የሚቀርቡትን መረጃዎች ያውቃሉ። ለዚህ ልዩነት መፈጠር ምክንያት የሆነው የልብ ፍላጎት መለያየቱ ይሆን? ምናልባት ሊሆን ይችላል።’ (2) ‘ከሁለቱ ወገኖች የትኛውን ያምናሉ? በቡድን መልክ ስንመለከታቸው (ግለሰቦችን ሳትነቅፍ) የትኛው ቡድን የበለጠ ታማኝ ነው ብለው ያምናሉ? ሰው በአምላክ የተፈጠረ ስለሆነ ለአምላክ ተጠያቂነት አለበት ብለው የሚያምኑትን ወይስ ሰው የአጋጣሚ ውጤት ስለሆነ ተጠያቂነታችን ለራሳችን ብቻ ነው የሚሉትን?’ (3) ‘እንግዲያው ስለ ሕይወት አጥጋቢ መልስ የሚሰጠው ፍጥረት ወይም ዝግመተ ለውጥ መሆኑን ለማየት መረጃውን በየግላችን መመርመር ይኖርብናል።’