በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዓላት

በዓላት

ፍቺ:- አብዛኛውን ጊዜ አንድ ድርጊት የተፈጸመበትን ዕለት ለማክበር ሲባል ዓለማዊ መሥሪያ ቤቶችና ትምህርት ቤቶች ዝግ የሚሆኑባቸው ቀናት ናቸው። በእነዚህ ቀኖች ቤተሰቦችና የተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ግብዣ ያዘጋጃሉ። አክባሪዎቹ በዓላቱን ሃይማኖታዊ ወይም ማኅበረሰባዊ ወይም ደግሞ ሕዝባዊ በዓላት እንደሆኑ አድርገው ሊያከብሯቸው ይችላሉ።

የገና በዓል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነውን?

በዓሉ የሚከበርበት ቀን

የማክሊንቶክና የስትሮንግ ሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል:- “የገና በዓል መለኮታዊ ትእዛዝ የተሰጠበት ወይም ከአዲስ ኪዳን የተገኘ አይደለም። ክርስቶስ የተወለደበትን ቀን ከአዲስ ኪዳንም ሆነ ከሌላ ምንጭ ማረጋገጥ አይቻልም።”—(ኒው ዮርክ፣ 1871)፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 276

ሉቃስ 2:8–11 ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ የበግ እረኞች በሌሊት በሜዳ ላይ እንደነበሩ ይናገራል። ዴይሊ ላይፍ ኢን ዘ ታይም ኦቭ ጂሰስ (በኢየሱስ ዘመን የነበረው የየዕለቱ ኑሮ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “መንጐቹ . . . ክረምቱን (የቅዝቃዜውን ወቅት) በቤት ውስጥ ሆነው ያሳልፉ ነበር፤ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ እረኞች በሜዳ ላይ እንደነበሩ ወንጌሉ ስለሚናገር በተለምዶ በክረምት ወቅት [በጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ታኅሣሥ 25ም ሆነ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29] የሚከበረው የገና በዓል ትክክል ሊሆን እንደማይችል ከዚህ ብቻ እንኳን ለማየት ይቻላል።”—(ኒው ዮርክ፣ 1962)፣ ሄነሪ ዳንኤል– ሮፕስ፣ ገጽ 228

ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ታኅሣሥ 25 የገና በዓል የሚከበርበት ቀን ሆኖ የተወሰነበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንም ይህ ቀን የተመረጠበት ምክንያት የቀኑ መርዘምና የክረምቱ ወራት ማለቅ በሚጀምርበት ጊዜ ከሚከበረው ‘የፀሐይ ዳግመኛ ልደት’ ጋር እንዲጋጠም ታስቦ ነው ይባላል። . . . የሮማውያን የሳተርናልያ (የእርሻ አምላክ የሆነው ሳተርንና እንደገና የታደሰው የፀሐይ ኃይል የሚከበርበት) በዓልም የሚከበረው በዚህ ጊዜ ነበር። በዚህም ምክንያት አንዳንድ የገና አከባበር ልማዶች የተወረሱት ከዚህ ጥንታዊ የአረማውያን በዓል ነው ተብሎ ይታሰባል።”—(1977)፣ ጥራዝ 6፣ ገጽ 666

ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል:- “ክርስቶስ የተወለደበት ቀን አይታወቅም። ወንጌሎች የተወለደበትን ቀንም ሆነ ወር አይገልጹም። . . . በኤች ኡስነር በቀረበው መላ ምት መሠረትና . . . በብዙ ምሁራንም ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘው የክርስቶስ ልደት በክረምት ወራት ማብቂያ ላይ እንዲውል የተደረገው (በጁሊያን የዘመን አቆጣጠር ታኅሣሥ 25 ሲሆን በግብፃውያን የዘመን አቆጣጠር ጥር 6) በዚህ ቀን ፀሐይ ወደ ሰሜን ንፍቀ ክበብ ሰማይ መመለስ ስለምትጀምር ሚትራንን ያመልኩ የነበሩት አረማውያን ዳይስ ናታሊስ ሶሊስ ኢንቪክቲ (ወይም የማትበገረውን ፀሐይ የልደት ቀን) ያከብሩ ስለነበረ ነው። ኦሬልየን የተባለው ንጉሥ ታኅ. 25 ቀን 274 የፀሐይ አምላክ የሮማ ግዛት የበላይ ጠባቂ መሆኗን አውጆ ካምፓስ ማርቲውስ በተባለው ሥፍራ የተሠራውን መቅደስ መረቀ። የገና በዓል መከበር የጀመረው የፀሐይ አምልኮ በሮማ ግዛት በጣም ተስፋፍቶ በነበረበት ዘመን ነው።”—(1967) ጥራዝ 3፣ ገጽ 656

ኮከብ የመራቸው ከምሥራቅ የመጡ ጠቢባን ወይም ሰብአ ሰገል

እነዚህ የምሥራቅ ሰዎች ኮከብ ቆጣሪዎች ነበሩ። (ማቴ. 2:1, 2 አዓት፣ ኒኢ፣ የ1980 ትርጉም ) ዛሬም ቢሆን ኮከብ ቆጠራ በብዙ ሰዎች ዘንድ የተለመደ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ አጥብቆ ያወግዘዋል። (በገጽ 145 ላይ “ዕድል” በሚለው ዋና ርዕስ ሥር ተመልከት።) አምላክ እርሱ የሚያወግዘውን ሥራ የሚሠሩትን ሰዎች አዲስ ወደ ተወለደው ኢየሱስ ሊመራቸው ይችላልን?

ማቴዎስ 2:1–16 እንደሚገልጸው ኮከቡ እነዚህን ኮከብ ቆጣሪዎች የመራቸው በመጀመሪያ ወደ ንጉሥ ሔሮድስ ከዚያም ወደ ኢየሱስ ነበር። ሔሮድስም ኢየሱስን ለመግደል ተነሣ። ከኮከብ ቆጣሪዎቹ በስተቀር “ኮከቡን” ያየ ሌላ ሰው ስለመኖሩ የተጠቀሰ ነገር የለም። ኮከብ ቆጣሪዎች ከሄዱ በኋላ የይሖዋ መልአክ የሕፃኑን ሕይወት ለማዳን ዮሴፍን ወደ ግብጽ እንዲሄድ አስጠነቀቀው። ያ ‘ኮከብ’ ከአምላክ ዘንድ የተሰጠ ምልክት ነበር ወይስ የአምላክን ልጅ ለማጥፋት ይፈልግ ከነበረ ከሌላ አካል የመጣ?

ኮከብ ቆጣሪዎች ሕፃኑን ኢየሱስን በከብቶች በረት ውስጥ እንዳገኙት ተደርጎ በዘልማድ በገና ሥዕሎች ላይ ቢሳልም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ይህን እንደማይናገር ልብ ማለት ይገባል። ኮከብ ቆጣሪዎች በደረሱ ጊዜ ኢየሱስና ወላጆቹ እቤት ውስጥ ነበሩ። ሄሮድስ በዚያን ጊዜ ስለ ኢየሱስ ዕድሜ ከኮከብ ቆጣሪዎቹ ጠይቆ በተረዳው መሠረት በቤተልሔም አውራጃ ዕድሜያቸው ሁለትና ከዚያ በታች የነበሩትን ወንድ ሕፃናት እንዲገድሉ አዝዞ እንደነበረ አስታውስ።—ማቴ. 2:1, 11, 16

የገና በዓል ክፍል የሆነው ስጦታ የመለዋወጥ ልማድ፣ ስለ ሳንታ ክላውስ ወይም ስለ ገና አባት የሚነገሩ ተረቶች ወዘተ

በገና በዓል የሚደረገው ስጦታ የመለዋወጥ ልማድ የመጣው ኮከብ ቆጣሪዎቹ ካደረጉት በመነሣት አይደለም። ከላይ እንዳየነው ኮከብ ቆጣሪዎች ወደ ኢየሱስ የመጡት በተወለደበት ጊዜ አልነበረም። ከዚህም በላይ ኮከብ ቆጣሪዎቹ እርስ በርሳቸው ስጦታ አልተለዋወጡም፤ ከዚህ ይልቅ በዘመኑ እውቅ የሆኑ ሰዎችን ለመጠየቅ ሲኬድ ይደረግ የነበረውን ልማድ በመከተል ስጦታ የሰጡት ለሕፃኑ ለኢየሱስ ነበር።

ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንዲህ ይላል:- “የሳተርናሊያ በዓል በሚከበርበት ጊዜ . . . ግብዣ ይደረግ ነበር፣ ስጦታ መለዋወጥም የተለመደ ነበር።” (1977፣ ጥራዝ 24፣ ገጽ 299) በገና ስጦታዎች የሚንጸባረቀው መንፈስም ከዚህ የተለየ አይደለም። በዚህ በዓል ሰዎች ስጦታ ይለዋወጣሉ። እንዲህ ባለው የስጦታ ልውውጥ የሚታየው መንፈስ በ⁠ማቴዎስ 6:3, 4 እና 2 ቆሮንቶስ 9:7 ላይ ያሉትን ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለሚጥስ እውነተኛ ደስታ አያመጣም። አንድ ክርስቲያን ለሌሎች ያለውን ፍቅር ለመግለጽ በዓመቱ ውስጥ በማንኛውም ቀን የፈለገውን ያህል ጊዜ ስጦታ መስጠት ይችላል።

ልጆች እንደሚኖሩበት አካባቢ ስጦታዎቹ የመጡላቸው ከሳንታ ክላውስ፣ ከቅዱስ ኒኮላስ፣ ከገና አባት፣ ከፔር ኖኤል፣ ከክኔክት ሩፕሬክት፣ ከሰብአ ሰገል (ከማጂ)፣ ከኤልፍ ጁልቶሜቴን (ወይም ከጁሊኒሲን) ወይም ላ ቤፋና ከተባለች ጠንቋይ እንደሆነ ይነገራቸዋል። (ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ፣ 1984፣ ጥራዝ 3፣ ገጽ 414) ከእነዚህ ታሪኮች አንዳቸውም ቢሆኑ እውነት አይደሉም። እንደነዚህ የመሰሉትን ታሪኮች መናገር ልጆች ለእውነት አክብሮት እንዲኖራቸው ያደርጋልን? እንዲህ የመሰለውስ ድርጊት አምላክ በእውነት ሊመለክ ይገባዋል ብሎ ያስተማረውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያስከብረዋልን?—ዮሐ. 4:23, 24

በሃይማኖታዊ ምክንያቶች እስካልተደረገ ድረስ ክርስቲያናዊ አመጣጥ በሌላቸው በዓሎች ላይ መካፈሉ ስህተት ነውን?

ኤፌ. 5:10, 11:- “ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፣ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፣ ይልቁን ግለጡት እንጂ።”

2 ቆሮ. 6:14–18:- “ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? . . . ስለዚህም ጌታ:- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኩስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ:- እኔም እቀበላችኋለሁ፣ . . . እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል።” (አንድ ሰው ለይሖዋ ያለው እውነተኛ ፍቅርና እርሱን ለማስደሰት ያለው ጠንካራ ፍላጐት ስሜታዊ ከሆኑና ክርስቲያናዊ ካልሆኑ ተግባሮች እንዲላቀቅ ይረዳዋል። ይሖዋን የሚያውቅና የሚያፈቅር ሰው የሐሰት አማልክትን የሚያከብሩትን ወይም ሐሰትን ከፍ ከፍ የሚያደርጉትን ተግባሮች በመተው ደስታ እንደቀረበት ሆኖ አይሰማውም። እውነተኛ ፍቅር በዓመፅ ሳይሆን ከእውነት ጋር እንዲደሰት ያደርገዋል። 1 ቆሮንቶስ 13:6⁠ን ተመልከት።)

ከ⁠ዘጸአት 32:4–10 ጋር አወዳድር። እስራኤላውያን የግብፃውያንን ሃይማኖታዊ ልማድ ወስደው “የእግዚአብሔር በዓል” የሚል አዲስ ስም እንደሰጡት ልብ በል። ነገር ግን ይሖዋ በዚህ አድራጐታቸው ክፉኛ ቀጥቷቸዋል። ዛሬ የምናየው የሃያኛውን መቶ ዘመን ከበዓሎች ጋር የተያያዙ ልማዶች ነው። አንዳንዶች ምንም ጉዳት የሌላቸው ሊመስሉ ይችላሉ። ይሖዋ ግን የእነዚህ በዓሎች መነሻ የሆኑት አረማዊ የሃይማኖት ልማዶች በተጀመሩበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ተመልክቷል። እኛን የሚያሳስበን ጉዳይ የእርሱ አመለካከት ሊሆን አይገባውምን?

ምሳሌ:- ሰዎች ተሰባስበው ወደ አንድ ሰው ቤት ሄዱና ልደትህን ልናከብር መጥተናል አሉት እንበል። እርሱ ግን የልደት በዓሉ እንዲከበር አይፈልግም። ሰዎች ያለልክ እንዲበሉና እንዲጠጡ ወይም እንዲሰክሩ ወይም እንዲዳሩ አይፈልግም። ሰዎቹ ግን እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደርጋሉ። ሁሉም እርስ በርሳቸው የሚለዋወጧቸውን ስጦታዎች አምጥተዋል። ለሰውዬው ግን ምንም ስጦታ አልያዙለትም። ከዚህም በላይ የልደቱ በዓል እንዲከበር የመረጡት ቀን የሰውዬው ጠላት የሆነ ሰው የተወለደበትን ቀን ነው። ሰውዬው ምን ይሰማዋል? አንተስ እንደዚህ ባለው ድርጊት ተካፋይ ለመሆን ትፈልጋለህን? በገና በዓል የሚደረጉት ነገሮች ልክ ይህንን የሚመስሉ ናቸው።

የበዓለ ትንሣኤና (ፋሲካ) ከእርሱ ጋር የተያያዙት ልማዶች መነሻ ምንድን ነው?

ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ በማለት አስተያየት ሰጥቷል:- “በአዲስ ኪዳን ውስጥ ወይም በሐዋርያዊ አባቶች ጽሑፎች ውስጥ በዓለ ትንሣኤ (የፋሲካ በዓል) ይከበር እንደነበረ የሚገልጽ ምንም ፍንጭ የለም። የተለዩ ጊዜያትን ቅዱስ አድርጎ ማክበር በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አእምሮ ውስጥ ያልነበረ ሐሳብ ነው።”—(1910)፣ ጥራዝ 8፣ ገጽ 828

ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ከፀደይ ወራት መምጣት ጋር የተያያዙ ብዙ አረማዊ ልማዶች የፋሲካ አከባበር ክፍል ሆነዋል። እንቁላሉ በፀደይ ወራት መጀመሪያ ላይ ለሚያቆጠቁጠው ሕይወት ምሳሌ ነው። . . . ጥንቸል የአረማውያን ምልክት ስትሆን ሁልጊዜ የምታመለክተው ፍሬ የማስገኘትን ወይም የመራባትን ችሎታ ነው።”—(1913)፣ ጥራዝ 5፣ ገጽ 227

ዘ ቱ ባቢሎንስ (ሁለቱ ባቢሎኖች) የተባለው የአሌክሳንደር ሂስሎፕ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “(ፋሲካ፣ በዓለ ትንሣኤ ተብሎ የተተረጎመው) ኢስተር የተባለው ቃል ራሱ ምን ማለት ነው? ክርስቲያናዊ ስያሜ አይደለም። ቃሉ ራሱ ከከለዳውያን የተገኘ ስያሜ መሆኑን ይናገራል። ኢስተር ከአስታሮት የተለየ አይደለም። አስታሮት የሰማይ ንግሥት ከሆነችው ከቤልቲስ የማዕረግ ስሞች አንዱ ነው፤ . . . ስሟ ኢሽታር ይባል እንደነበር ሌያርድ በአሦራውያን ሐውልቶች ላይ ያገኙት ጽሑፍ ያመለክታል። . . . የኢስተር ታሪክ ይህ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ በበዓሉ ላይ በሰፊው የሚታዩት ልማዳዊ የአከባበር ሥርዓቶች ባቢሎናዊ ጠባይ የሚንፀባረቅባቸው መሆኑን የታሪክ ምሥክርነት በሚገባ ያረጋግጣል። በስቅለት ዕለት የሚዘጋጀው የመስቀል ቅርጽ ያለው ዳቦ፣ ለፋሲካ ዕለት የሚዘጋጁት ቀለም የተቀቡ እንቁላሎች፣ በጥንቱ የከለዳውያን የአምልኮ ሥርዓትም ውስጥ አሁን ያላቸውን የመሰለ ቦታ ነበራቸው።”—(ኒው ዮርክ፣ 1943)፣ ገጽ 103, 107, 108፤ ከ⁠ኤርምያስ 7:18 ጋር አወዳድር።

የዘመን መለወጫን በዓል ማክበር በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ነውን?

ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚለው “ሮማውያን ይህንን ቀን [በአውሮፓውያን አቆጣር ጥር 1⁠ን] የሰጡት የመግቢያዎች፣ የበሮችና፣ የማናቸውም ነገሮች መጀመሪያ አምላክ ለሚባለው ለጃኑስ ነበር። የጥር ወር (ጃኑዋሪ) ስያሜውን ያገኘው ወደ ፊትና ወደ ኋላ የሚመለከቱ ሁለት ፊቶች ካሉት ጃኑስ ከተባለው የጣዖት አምላክ ነው።”—(1984)፣ ጥራዝ 14፣ ገጽ 237

አዲስ ዓመት የሚከበርበት ቀንና ከአዲስ ዓመት ጋር የተያያዙት ልማዶች ከአገር አገር ይለያያሉ። በብዙ ቦታዎች በዓሉ የሚከበረው በመጠጥ፣ በጭፈራና በፈንጠዝያ ነው። ይሁን እንጂ ሮሜ 13:13 እንዲህ በማለት ይመክራል:- “በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፣ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፣ በክርክርና በቅናት አይሁን።” (በተጨማሪ 1 ጴጥሮስ 4:3, 4፤ ገላትያ 5:19–21⁠ን ተመልከት።)

“የሙታንን መናፍስት” ለማስታወስ የሚከበሩት በዓላት ምንጫቸው ምንድን ነው?

በ1910 የታተመው ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- የነፍሳት ሁሉ ቀን . . . ወደ ሰማይ የሄዱትን ታማኝ ሰዎች ለማስታወስ በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ቀን ነው። የበዓሉ አከባበር የተመሠረተው ታማኝ ሰዎች ሲሞቱ ነፍሶቻቸው ከቀላል ኃጢአቶች ካልነጹ ወይም ላለፈው ኃጢአታቸው ይቅርታና ዕርቅ ካላገኙ ወደ ብፅዓት ቦታ ሊገቡ አይችሉም። ወደዚህ የብፅዓት ቦታ ለመግባት እንዲችሉ በጸሎትና በሥርዓተ ቅዳሴ ላይ በሚቀርበው መሥዋዕት መርዳት ይቻል ይሆናል በሚለው ትምህርት ላይ ነው። . . . ከነፍሳት ሁሉ ቀን ጋር ዝምድና ያላቸው አንዳንድ በሕዝብ ዘንድ የታወቁ እምነቶች ምንጫቸው አረማዊና በጣም ጥንታዊ ነው። የካቶሊክ እምነት በተስፋፋባቸው በብዙ አገሮች የሚኖሩ የገጠር ሰዎች የነፍሳት ሁሉ ቀን በሚከበርበት ምሽት ሙታን ድሮ ይኖሩ ወደነበሩበት ቤት ተመልሰው በመምጣት በሕይወት ያሉት ከሚበሉት ምግብ ይካፈላሉ ብለው ያምናሉ።”—ጥራዝ 1፣ ገጽ 709

ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንዲህ ይላል:- “ከቅዱሳን ቀን አከባበር ጋር የተያያዙት አንዳንድ ልማዶች ከክርስትና ዘመን በፊት ይደረጉ ከነበሩት የጥንት የሴልቲክ ካህናት የአስማትና የጥንቆላ ሥርዓት አከባበር የመጡ ናቸው። ሴልቶች የፀሐይ አምላክና የሙታን አምላክ (ሳምሃይን) ለተባሉ ሁለት ዋና ዋና አማልክት በዓል ያደርጉ ነበር። በዓሉ ይውል የነበረው የሴልቲክ አዲስ ዓመት መጀመሪያ በነበረው ኅዳር 1 ላይ ነበር። የሙታን በዓል አከባበር ቀስ በቀስ ወደ ክርስትና የበዓል አከባበር ውስጥ ገባ።”—(1977)፣ ጥራዝ 13፣ ገጽ 725

ዘ ወርሽፕ ኦቭ ዘ ዴድ (የሙታን አምልኮ) የተባለው መጽሐፍ ስለ ሙታን በዓል አጀማመር እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የጥንት ሕዝቦች አፈ ታሪኮች ሁሉ ከጥፋት ውኃ ታሪኮች ጋር የተሳሰሩ ናቸው። . . . ለዚህ አባባል ጠንካራ ማስረጃ የሚሆነው ለሙታን መታሰቢያነት የሚከበረው በዓል እርስ በርሳቸው ሊገናኙ በሚችሉ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን በረዥም ዘመናትና በሰፋፊ ውቅያኖሶች በተራራቁ ሕዝቦች መከበሩ ነው። በተጨማሪም ይህ በዓል በሁሉም ሕዝቦች የሚከበረው ሙሴ በጻፈው መሠረት የጥፋት ውኃው በደረሰበት ጊዜ ይኸውም በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ቀን ወይም በዚህ ቀን አካባቢ ሲሆን ይህም ዛሬ ኅዳር ወር ከምንለው ጋር ከሞላ ጐደል ይገጥማል።” (ለንደን፣ 1904፣ ኰሎኔል ጄ ጋርኒር፣ ገጽ 4) እነዚህ በዓሎች የተጀመሩት በመጥፎ ሥራቸው የተነሣ አምላክ በኖኅ ዘመን ያጠፋቸውን ሕዝቦች ለማክበር ነው።—ዘፍ. 6:5–7፤ 7:11

“የሙታን መንፈስ” በሌላ ዓለም ሕያው ሆኖ እንደሚኖር በማሰብ ሙታንን ለማክበር የሚደረጉት እነዚህን የመሰሉ በዓሎች ሞት ማለት ፈጽሞ ምንም ነገር የማይታወቅበት የበድንነት ሁኔታ ነው ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ ጋር ይቃረናል።—መክ. 9:5, 10፤ መዝ. 146:4 አዓት

የሰው ነፍስ አትሞትም ስለሚለው እምነት በገጽ 100, 101 ላይ “ሞት” በሚለው ዋና ርዕስና በገጽ 377, 378 ላይ “ነፍስ” በሚለው ሥር ተመልከት።

የቫለንቲን ቀን አመጣጥ ምንድን ነው?

ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “የቫለንቲን ቀን የሚከበረው ቫለንቲን የተባሉ ሁለት የተለያዩ ክርስቲያን ሰማዕታትን ለማስታወስ ነው። በዚህ ቀን የሚፈጸሙት ልማዶች ግን . . . በየዓመቱ የካቲት 15 ቀን ሉፐርካሊያ እየተባለ ይከበር ከነበረው ከጥንት የሮማውያን በዓል የተገኙ ሳይሆኑ አይቀሩም። በዓሉ ጁኖ የተባለችውን የሮማውያን የሴቶችና የጋብቻ አምላክ እንዲሁም ፓን የተባለውን የተፈጥሮ አምላክ ለማክበር ይደረግ የነበረ ነው።”—(1973)፣ ጥራዝ 20፣ ገጽ 204

እናቶች የሚከበሩበት ቀን የመጣው ከየት ነው?

ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ይህ በዓል በጥንትዋ ግሪክ ከነበረው እናቶችን የማምለክ ልማድ የተገኘ ነው። በመላው የታናሽቱ እስያ አገሮች በጥንቱ የሮማውያን የዘመን አቆጣጠር መጋቢት 15 ቀን መደበኛ የሆነ የእናት አምልኮ ከመፈጸሙም በተጨማሪ ታላቋ የአማልክት እናት ትባል ለነበረችው ለሳይቤል ወይም ለሪያ ክብረ በዓል ይደረግ ነበር።”—(1959)፣ ጥራዝ 15፣ ገጽ 849

በአንድ አገር የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙት ነገሮችን በማስታወስ ስለሚከበሩት በዓሎች የክርስቲያኖችን አመለካከት የሚገልጹት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?

ዮሐ. 18:36:- “ኢየሱስም [ለሮማዊው ገዥ] መልሶ:- መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ . . . አለው።”

ዮሐ. 15:19:- “[እናንተ የኢየሱስ ተከታዮች] ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።”

1 ዮሐ. 5:19:- “ዓለምም በሞላው በክፉው [ተይዟል።]” (ከዮሐንስ 14:30፣ ራእይ 13:1, 2 እና ከዳንኤል 2:44 ጋር አወዳድር። )

አካባቢያዊና ብሔራዊ የሆኑ ሌሎች በዓሎች

ብዙ አካባቢያዊና ብሔራዊ በዓሎች አሉ። እዚህ ላይ ሁሉንም መግለጽ አይቻልም። ነገር ግን ከላይ የቀረበው ታሪካዊ መረጃ ማናቸውንም በዓል በተመለከተ ሰዎች ምን ነገሮችን ማየት እንደሚኖርባቸው ፍንጭ ይሰጣል። ቀደም ሲል የተብራሩት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ቀዳሚ ምኞታቸው በይሖዋ ፊት ደስ የሚያሰኘውን ማድረግ ለሆነ ሰዎች በቂ መመሪያ ሊሆኑ ይችላሉ።