በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጨረሻ ቀኖች

የመጨረሻ ቀኖች

ፍቺ:- መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻ ቀኖች’ የሚለውን ሐረግ የሚጠቀምበት የአንድ የነገሮች ሥርዓት ማክተሚያ ወደሚሆን መለኮታዊ ጥፋት ወደሚፈጸምበት ጊዜ የሚያደርሰውን የመደምደሚያ ዘመን ለማመልከት ነው። በኢየሩሳሌም ይገኝ በነበረው ቤተ መቅደስ ማዕከልነት የተቋቋመው የአይሁድ ሥርዓትና አምልኮ የመጨረሻ ቀን በ70 እዘአ በመጣው ጥፋት ላይ አክትሟል። በዚያ ጊዜ የተፈጸመው ሁኔታ ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሁሉም ሕዝቦች ላይ ለሚደርሰውና ከአምላክ ለሚመጣው ታላቅ የቅጣት ፍርድ ምሳሌ ነው። በመላው ዓለም ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘው የአሁኑ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ወደ መጨረሻ ቀኖቹ የገባው በ1914 ነው። በዚያ ዘመን ይኖሩ ከነበሩት ሰዎች መካከል በሕይወት ቆይተው ክፉው የነገሮች ሥርዓት “በታላቁ መከራ” ሲጠፋ ሊመለከቱ የሚችሉ ይኖራሉ።

ዛሬ የምንኖረው ‘በመጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ መሆኑን የሚጠቁምልን ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ቀን መለያ ምልክት የሆኑትን ድርጊቶችና ሁኔታዎች ይገልጻል። “ምልክቱ” ብዙ ማስረጃዎችን አጣምሮ የያዘ ነው። ስለዚህ የመጨረሻው ቀኖች ምልክቶች በአንድ ትውልድ ዘመን ውስጥ በግልጽ መታየት አለባቸው። የምልክቱ የተለያዩ ገጽታዎች በ⁠ማቴዎስ ምዕራፍ 24, 25፣ ማርቆስ 13 እና ሉቃስ 21 ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ። ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎች በ⁠2 ጢሞቴዎስ 3:1–5፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4 እና ራእይ 6:1–8 ላይ ይገኛሉ። የዚህን ምልክት ዋና ዋና ክፍል የሆኑ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመለከታለን።

ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል” (ማቴ. 24:7 )

ለአያሌ ሺህ ዓመታት ጦርነቶች የዚችን ምድር ሕይወት አጨልመውት ኖረዋል። አንዱ አገር ከሌላው አገር ጋር፤ እንዲሁም በአንዱ አገር ውስጥ ባሉ በተቀናቃኝ ወገኖች መካከል ጦርነት ተካሂዷል። በ1914 ግን አንደኛው የዓለም ጦርነት ጀመረ። ይህ ጦርነት በሁለት ሠራዊቶች መካከል የተደረገ ተራ ጦርነት አልነበረም። የዓለም ዋና ዋና ኃይሎች በሙሉ የተሳተፉበት ጦርነት ነበር። የየአገሩ ሕዝቦች በሙሉ፣ ሲቪሎችም ጭምር ለጦርነቱ ድጋፍ እንዲሰጡ ተደርጎ ነበር። ጦርነቱ ባከተመበት ጊዜ ከዓለም ሕዝቦች በሙሉ 93 በመቶ የሚያክሉት በጦርነቱ ተካፍለው እንደነበረ ተገምቷል። (1914 ታሪካዊ ዓመት ስለመሆኑ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት  ገጽ 239, 240⁠ን ተመልከት።)

በራእይ 6:4 ላይ አስቀድሞ እንደተነገረው ‘ሰላም ከምድር ላይ ተወስዷል።’ ከ1914 ጀምሮ ዓለም በብጥብጥ ስትናወጥ ቆይታለች። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከ1939 እስከ 1945 ተደረገ። በጡረታ ላይ የሚገኙት አድሚራል ዥን ላ ሮክ እንደተናገሩት ከ1945 ጀምሮ እስከ 1982 ድረስ ሌሎች 270 ጦርነቶች ተደርገዋል። በዚህ መቶ ዘመን ከ100 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በጦርነት አልቀዋል። በ1982 ታትሞ የወጣው ወርልድ ሚሊተሪ ኤንድ ሶሻል ኤክስፔንዲቸርስ እንደገለጸው በዚሁ ዓመት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ 100 ሚልዮን ሰዎች በውትድርና ሥራዎች ተካፍለዋል።

ይህ የትንቢት ክፍል በትክክል ተፈጽሟል ለማለት ከዚህ የበለጠ ነገር መፈጸም ይኖርበታልን? በቅጽበት ሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች አሉ። መንግሥታት ከኑክሌር የጦር መሣሪያዎቻቸው ጥቂቱን እንኳን ቢጠቀሙ ሥልጣኔና መላው የሰው ዘር ይጠፋል በማለት የታወቁ ሳይንቲስቶች ተናገረዋል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲህ ዓይነት እልቂት እንደማይደርስ ያመለክተናል።

ራብም . . . በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል” (ማቴ. 24:7 )

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ብዙ ጊዜ ረሀብ ደርሷል። ይሁን እንጂ በ20ኛው መቶ ዘመን ረሀብ ምን ያህል ተስፋፍቷል? የዓለም ጦርነት በአውሮፓና በእስያ ረሀብ እንዲስፋፋ አድርጓል። አፍሪካ በአስከፊ ድርቅ በመመታቷ ምክንያት ተርባለች። በ1980 መጨረሻ ላይ 450 ሚልዮን ሰዎች ለሞት በሚያደርስ ረሀብ ተጐድተው እንደነበርና እስከ አንድ ቢልዮን የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ በቂ ምግብ እንዳልነበራቸው የምግብና የእርሻ ድርጅት ገምቷል። ከእነዚህ ውስጥ በአንድ ዓመት ውስጥ 40 ሚልዮን (በአንዳንድ ዓመታት እስከ 50 ሚልዮን ይደርሳል) የሚያክሉት ይሞታሉ።

ይህ በዚህ ዘመን የሚታየው የምግብ እጥረት የተለየ ባሕርይ አለውን? አዎ፤ አለው። የምግብ እጥረት ያለው እህል ሳይጠፋ ነው። አንዳንድ አገሮች እጅግ የተትረፈረፈ እህል አላቸው፤ እህሉን ለተቸገሩት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማድረስም ዘመናዊ መጓጓዣ አላቸው። ይሁን እንጂ ብሔራዊ ፖሊሲና የንግድ ጥቅም ጋሬጣ ሆነዋል። እንዲያውም በሚልዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸው ተርበው እያሉ ምርጥ እህላቸውን የተትረፈረፈ እህል ላላቸው አገሮች ይሸጣሉ። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ስፋት ያለው ነው። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በ1981 እንዲህ በማለት ገልጾ ነበር:- “የኑሮ ደረጃ መሻሻሉና በዓለም ዙሪያ የምግብ ተፈላጊነት እየጨመረ መሄዱ የምግብ ዋጋ ከፍ እንዲል ተጽዕኖ በማድረጉ ድሀ አገሮች የምግብ ፍላጎታቸውን ከውጪ አገሮች በማስመጣት ለማሟላት ከብዶባቸዋል።” በብዙ አገሮች በዘመናዊ ሳይንስ የሚታገዘው የምግብ ምርት በየጊዜው ከሚጨምረው የሕዝብ ቁጥር ጋር በሚተካከል መጠን ሊያድግ አልቻለም። ዘመናዊ የምግብ ኤክስፐርቶች ለችግሩ ምንም ዓይነት ትክክለኛ መፍትሔ አላገኙም።

ታላቅም የምድር መናወጥ . . . ይሆናል” (ሉቃስ 21:11 )

ባለፉት መቶ ዘመናት ትልልቅ የመሬት መንቀጥቀጦች ደርሰው እንደነበር እውነት ነው። በተጨማሪም ሳይንቲስቶች በመሣሪያዎች አማካይነት በየዓመቱ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ የመሬት መንቀጥቀጦችን ይመዘግባሉ። ታላላቅ የምድር መናወጦች መድረሳቸውን ለማወቅ ግን ልዩ መሣሪያ አያስፈልገም።

ከ1914 ወዲህ የተከሰቱት የምድር መናወጦች ብዛት ጨምሯልን? በኮሎራዶ ቦልደር ከሚገኘው ብሔራዊ የጂኦፊዚካል የመረጃ ማዕከልና ከሌሎች የመረጃ ምንጮች የተገኙትን ተጨማሪ መረጃዎች በመውሰድ በሬክተር መለኪያ 7.5 ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ወይም አምስት ሚልዮን ዶላር ወይም ከዚያ በላይ የሚገመት የንብረት ጥፋት ያደረሱ ወይም ለ100 ሰዎች ወይም ከዚያ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሕልፈት ምክንያት የሆኑ የመሬት መንቀጥቀጦች ብቻ በሰንጠረዥ ተዘርዝረው በ1984 ቀርበው ነበር። ከ1914 በፊት በነበሩት የ2,000 ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንዲህ የመሰሉ የመሬት መንቀጥቀጦች 856 ጊዜ ደርሰው ነበር። ከ1914 ወዲህ ባሉት 69 ዓመታት ውስጥ ብቻ 605 ተመሳሳይ የመሬት መንቀጥቀጦች እንደደረሱ ይኸው ሰንጠረዥ ያሳያል። ይህም ማለት ከ1914 ወዲህ በአንድ ዓመት ውስጥ በአማካይ የደረሱት የመሬት መንቀጥቀጦች ከ1914 በፊት ከነበሩት 2,000 ዓመታት ጋር ሲወዳደሩ 20 ጊዜ ይበልጣሉ ማለት ነው።

በልዩ ልዩ ሥፍራ ቸነፈር . . . ይሆናል” (ሉቃስ 21:11 )

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ ስፓኒሽ ፍሉ (በኢትዮጵያ የኅዳር በሽታ የሚባለው) በዓለም ላይ በመሰራጨት በበሽታ ታሪክ ውስጥ አቻ በማይገኝለት ፍጥነት ከ20 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል። የሕክምና ሳይንስ ትልቅ እድገት ቢያደርግም በየዓመቱ በካንሰር፣ በልብ ሕመም፣ ዓይነታቸው በርካታ በሆኑት የአባለዘር በሽታዎች፣ የሰውነት ክፍሎችን በሚያደርቁ በሽታዎች፣ በወባ፣ በሪቨር ብላይንድነስ እና በቻጋስ በሽታ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።

‘የዓመፃ መብዛት፤ እንዲሁም የብዙ ሰዎች ፍቅር መቀዝቀዝ’ (ማቴ. 24:11, 12 )

ስለ ወንጀል ምርምር የሚያደርጉ አንድ ባለሙያ በዓለም ደረጃ የሚፈጸመውን ወንጀል ስትመለከቱ የሚያስደነግጣችሁ ነገር በየቦታው የሚፈጸመው ወንጀል እየተስፋፋ መሄዱና ከቁጥጥር ውጭ መሆኑ ነው። ወንጀል ያልተስፋፋባቸው ገለልተኛ አካባቢዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። እነርሱም ቢሆኑ እየጨመረ በሚሄደው የወንጀል ጎርፍ መጥለቅለቃቸው አይቀርምብለዋል። (ዘ ግሮውዝ ኦቭ ክራይም (የወንጀል መብዛት)፣ ኒው ዮርክ፣ 1977፣ ሰር ሊዎን ራድዚኖቪች እና ጆአን ኪንግ፣ ገጽ 4, 5) ያለማጋነን ወንጀል ጨምሯል። ጭማሪው ወንጀሎች ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ ሪፖርት የሚደረጉ በመሆናቸው የመጣ አይደለም። ባለፉት ትወልዶችም ቢሆን ወንጀለኞች እንደነበሩ አይካድም። ይሁን እንጂ እንደ አሁኑ ወንጀል በየቦታው የተስፋፋበት ጊዜ አልነበረም። በዕድሜ የገፉት ሰዎች ይህንን ከግል ተሞክሯቸው አረጋግጠዋል።

በትንቢቱ ውስጥ የተጠቀሰው ዓመፅ ሰዎች ለታወቁት የአምላክ ሕጎች ንቀት ማሳየታቸውንና በሕይወታቸው ቀዳሚውን ቦታ የሚሰጡት ለአምላክ ሳይሆን ለራሳቸው መሆኑን ይጨምራል። እንዲህ ዓይነት አቋም በመስፋፋቱ የተነሣ ፍቺ በጣም እየጨመረ ሄዷል። ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ ሩካቤ ሥጋና ግብረ ሰዶም በሰፊው ተቀባይነት አግኝተዋል። በየዓመቱ በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ውርጃ ይፈጸማል። ይህ ዓመፅ (በ⁠ማቴዎስ 24:11, 12 ላይ የተጠቀሰው) የራሳቸውን ትምህርት ከአምላክ ቃል አስበልጠው የአምላክን ቃል ወደ ጎን ገሸሽ ካደረጉት የሐሰተኛ ነቢያት ተጽዕኖ ጋር ይዛመዳል። ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ የእነርሱን ፍልስፍና መከተላቸው ፍቅር የለሽነት በዓለም በሙሉ እንዲስፋፋ አስተዋፅኦ አድርጓል። (1 ዮሐ. 4:8) ስለዚህ ጉዳይ በ⁠2 ጢሞቴዎስ 3:1–5 ላይ የሚገኘውን መግለጫ አንብብ።

የሚያስፈራም ምልክት ይሆናል” (ሉቃስ 21:11 )

ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት “ዛሬ በሕይወታችን ላይ የሰለጠነው ትልቅ ስሜት ፍርሃት ነው” ብሏል። (ጥቅምት 11, 1965፣ ገጽ 144) ሆርሱ የተባለው የጀርመን መጽሔት ደግሞ ሰዎች እንደ ዛሬው በፍርሃት የተዋጡበት ጊዜ የለምብሏል።—ቁጥር 25፣ ሰኔ 20, 1980፣ ገጽ 22

ለዚህ ዓለም አቀፍ የሆነ የፍርሃት አየር አስተዋጽኦ ያደረጉ ብዙ ነገሮች አሉ። ከምክንያቶቹ መካከል ኃይል የታከለበት ወንጀል፣ ሥራ አጥነት፣ ብዙ አገሮች ሊወጡ በማይችሉት ዕዳ ውስጥ በመዘፈቃቸው ምክንያት የመጣው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ ዓለም አቀፍ የአካባቢ መበከል፣ ጠንካራ መተሳሰርና ፍቅር የሰፈነበት ቤተሰብ አለመኖሩ፣ በሰው ልጅ ላይ ያንዣበበው የኑክሌር እልቂት ይገኙባቸዋል።

‘የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች በስሙ ምክንያት በሁሉም ሕዝቦች ዘንድ የተጠሉ ይሆናሉ’ (ማቴ. 24:9 )

የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ስደት የሚደርስባቸው በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ገብተው ስለሚዘባርቁ ሳይሆን ‘ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም’ ነው። ተከታዮቹ የይሖዋን መሲሐዊ ንጉሥ ስለሚከተሉ፣ ከማንኛውም ምድራዊ ገዥ አስበልጠው ክርስቶስን ስለሚታዘዙ፣ ለመንግሥቲቱ በታማኝነት ስለሚቆሙና በሰብዓዊ መንግሥታት ጉዳዮች ጣልቃ ስለማይገቡ ይሰደዳሉ። የዘመናችን ታሪክ እንደሚያረጋግጠው የይሖዋ ምሥክሮች በሁሉም የምድር ክፍሎች ስደት ደርሶባቸዋል።

‘ይህ የመንግሥት ወንጌል ምሥክር እንዲሆን በዓለም ሁሉ ይሰበካል’ (ማቴ. 24:14 )

የሚሰበከው መልእክት በኢየሱስ ክርስቶስ የምትመራው የአምላክ መንግሥት ከሰማይ መግዛት እንደጀመረችና በቅርቡ ጠቅላላውን ክፉ የነገሮች ሥርዓት እንደምታጠፋ፣ በዚች መንግሥት አገዛዝ ሥር የሰው ዘር ወደ ፍጽምና እንደሚደርስና ምድር ገነት እንደምትሆን ነው። ዛሬ ይህ የምሥራች ከ200 በሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እየተሰበከ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠር ሰዓት ለዚህ ሥራ የሚያጠፉ ሲሆን እያንዳንዱ ሰው ይህን የምሥራች የመስማት አጋጣሚ ለማግኘት እንዲችል ደጋግመው ከቤት ወደ ቤት ይሄዳሉ።

እነዚህ በመጨረሻ ቀኖች የተከሰቱ ሁኔታዎች በሙሉ ምን ያመለክታሉ?

ሉቃስ 21:31, 32:- ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች [ማለትም መንግሥቲቱ የአሁኑን ክፉ ዓለም የምታጠፋበትና የምድርን ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ የምትቆጣጠርበት ጊዜ እንደደረሰ] እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።(በ1914 ምልክቱ መፈጸም ሲጀምር በሕይወት የነበረው “ትውልድ” አሁን በዕድሜ በጣም ገፍቷል። የቀረው ጊዜ በጣም አጭር መሆን አለበት። የዓለም ሁኔታዎች ይህ እውነት መሆኑን ያሳያሉ።)

የይሖዋ ምሥክሮች “የመጨረሻ ቀኖች” የጀመሩት በ1914 ነው የሚሉት ለምንድን ነው?

1914 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተጠቆመ ዓመት ነው። ስለዘመናት አቆጣጠር ዝርዝር መረጃ ለማግኘት በገጽ 94–97 ላይ የዘመናት ስሌት በሚለው ዋና ርዕስ ሥር የተገለጸውን ተመልከት። ይህ ጊዜ ተለይቶ ስለሚታወቅባቸው የዓለም ሁኔታዎች የተነገሩት ትንቢቶች ከ1914 ጀምረው በትክክል መፈጸም መጀመራቸው የዘመኑን ትክክለኛነት ያሳያል። ከላይ የቀረቡት ማስረጃዎችም ይህን የሚያረጋግጡ ናቸው።

  ዓለማዊ ታሪክ ጸሐፊዎች 1914⁠ን እንዴት ይመለከቱታል?

አሁን ካለንበት ሁኔታ መለስ ብለን ወደኋላ ስንመለከት አንደኛው የዓለም ጦርነት አርኖልድ ቶይንቢ የተባሉት እንግሊዛዊ ታሪክ ጸሐፊ ‘የችግር ዘመን’ ሲሉ ለገለጹት ሃያኛው መቶ ዓመት መባቻ ሆኗል። ሥልጣኔአችን በምንም መንገድ ከዚህ አዘቅት ሊወጣ አልቻለም። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ባለፈው ግማሽ መቶ ዘመን የደረሱት ችግሮች በ1914 የተጀመሩ ናቸው።ዘ ፎል ኦቭ ዘ ዳይናስቲስ፣ ዘ ኮላፕስ ኦቭ ዘ ኦልድ ኦርደር (የሥርወ መንግሥታት ውድቀት፣ የአሮጌው ሥርዓት መንኮታኮት) (ኒው ዮርክ፣ 1963)፣ ኤድሞንድ ቴለር፣ ገጽ 16

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ትውልድ፣ ማለትም የኔ ትውልድ፣ ይህ ጦርነት ለአዲስ የታሪክ ምዕራፍ መክፈቻ እንደሆነ አድርጎ ያስባል። . . . የራሳችንን ከንቱነት፣ ይኸውም ከታሪክ ጋር ፊት ለፊት የመጋጠማችንን ሐቅ መቀበል ይገባናል። ይሁን እንጂ በማኅበራዊ ኑሮ ረገድ ይበልጥ ወሳኝ የሆነ ለውጥ የተደረገው ከአንደኛው ዓለም ጦርነት በኋላ መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል። ለበርካታ መቶ ዘመናት ሲገነቡ የቆዩት ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሥርዓቶች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የፈራረሱት በዚህ ጊዜ ነበር። አንዳንዶቹ ሁኔታዎች ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ ሊመለሱ በማይችሉበት መልክ ተለውጠዋል። ለብዙ ዘመናት የቆዩት የተረጋጉ ሁኔታዎች የተናጉት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ነበር። . . . ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ደግሞ ይህንን ለውጥ ገፋበት፣ አረጋገጠው፣ አጠናከረው። ከማኅበራዊ ኑሮ አንፃር ከታየ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የአንደኛው ዓለም ጦርነት መጠናቀቂያ ነበር።ዘ ኤጅ ኦቭ አንሰርቴኒቲ (መተማመን የጠፋበት ዘመን)፣ (ቦስተን፣ 1977) ጆን ኬ ጋልብሬዝ፣ ገጽ 133

አሁን ግማሽ መቶ ዘመን የሚያክል ጊዜ አልፎአል፣ ይሁን እንጂ የትልቁ ጦርነት [በ1914 የፈነዳው አንደኛው ዓለም ጦርነት] አሳዛኝ ሁኔታ በሕዝቦች አካልና ነፍስ ላይ የተወው ጠባሳ ገና አልጠፋም። . . . ይህ መዓት በአካልና በሥነ ምግባር ላይ ያስከተለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ምንም ነገር እንደ ድሮው ሊሆን አልተቻለም። መላው ኅብረተሰብ፣ የመስተዳድር ሥርዓቶች፣ ብሔራዊ ወሰኖች፣ ሕጎች፣ የጦር ኃይሎች፣ በብሔራት መካከል ያሉት ግንኙነቶች፣ ርዕዮተ ዓለም፣ የቤተሰብ ኑሮ፣ ሀብት፣ ሥልጣን፣ ሰብዓዊ ግንኙነቶች፣ ማንኛውም ነገር ከላይ እስከታች ተለውጧል። . . . የሰው ልጅ ሚዛኑን ሳተ፤ እስከ ዛሬም የድሮው ቦታው አልተመለሰም።”—ጄነራል ቻርለስ ደ ጎል፣ በ1968 የተናገሩት (ለ ሞንድ፣ ኅዳር 12, 1968፣ ገጽ 9)

የአሁኑ ዓለም ሥርዓት ከጠፋ በኋላ በምድር ላይ የሚተርፍ ሰው ይኖር ይሆን?

አዎ ይኖራል። የአሁኑ ዓለም ሥርዓት ይጠፋል። የሚጠፋው ግን በኑክሌር ጦርነት አማካኝነት በሚመጣ የጅምላ ፍጅት ሳይሆን ‘ሁሉን ማድረግ የሚችለው አምላክ’ የሚያካሂደውን ታላቁን የጦርነት ቀን በሚጨምረው ታላቅ መከራ ነው። (ራእይ 16:14, 16) ይህ ጦርነት ምድርንም ሆነ ሰዎችን በሙሉ አያጠፋም።

ማቴ. 24:21, 22:- በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና። እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።(ስለዚህ ከጥፋቱ የሚተርፍ ጥቂት ‘ሥጋ ለባሽ’ ይኖራል ማለት ነው።)

ምሳሌ 2:21, 22:- ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኃጥኣን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።

መዝ. 37:29, 34:- ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ። እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፣ መንገዱንም ጠብቅ፣ ምድርን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ።

አምላክ ክፉዎችን ሳያጠፋ ይህን ያህል ጊዜ የቆየው ለምንድን ነው?

2 ጴጥ. 3:9:- ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ [“ይሖዋ” አዓት] ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።

ማር. 13:10:- አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል።

ማቴ. 25:31, 32, 46:- የሰው ልጅ [ኢየሱስ ክርስቶስ] በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፣ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛ በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፣ እነዚያም [የክርስቶስ መንፈሳዊ ወንድሞች የሆኑትን የንጉሡ ወኪሎች እንደሆኑ አድርገው ያልተቀበሉት] ወደ ዘላለም ቅጣት [“ጥፋት” አዓት]፣ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።

በተጨማሪ ገጽ 362, 363⁠ን እና 428–430⁠ን ተመልከት።

አንድ ሰው እንዲህ ቢልስ:-

‘ዛሬ ያሉት ሁኔታዎች ከቀድሞው የተለዩ አይደሉም። ጦርነት፣ ረሀብ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ወንጀል ጠፍቶ አያውቅም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ለምን እንደዚያ ሊሰማዎት እንደቻለ ይገባኛል። እኛ የተወለድነው እነዚህ ነገሮች ዕለታዊ ዜና በሆኑበት ዓለም ውስጥ ነው። ይሁን እንጂ 20ኛው መቶ ዘመን ልዩ የሚሆንበት የራሱ ባሕርይ እንዳለው ታሪክ ጸሐፊዎች ይናገራሉ። ( በገጽ 239, 240 ላይ የተጠቀሱትን ሐሳቦች አንብብ።)’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘ነገሩን ልዩ የሚያደርገው ጦርነት፣ ረሀብ፣ የመሬት መንቀጥቀጥና ወንጀል መኖራቸው አይደለም። ኢየሱስ የሰጠው ምልክት ብዙ ነገሮችን አጣምሮ የያዘ መሆኑን ያውቁ ነበር?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ኢየሱስ አንድ ድርጊት ብቻውን “በመጨረሻው ቀንውስጥ እንደምንገኝ ያረጋግጣል ብሎ አልተናገረም። ልዩ ትርጉም የሚኖረው ምልክቶቹ በሙሉ መታየታቸው ነው። በተለይ ምልክቶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመን አቆጣጠር ተለይቶ በሚታወቅ ዓመት ጀምሮ በመላው ዓለም መታየቱ ልዩ ትርጉም የሚያሰጠው ነው።’ ( ገጽ 234–238⁠ን እንዲሁም ገጽ 94–97⁠ን ተመልከት።)

‘ማን ያውቃል፤ ትንቢቱ የበለጠ የሚፈጸምበት ሌላ ትውልድ ቢመጣስ?’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ይህ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። መልሱም ‘በመጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ የምንኖር መሆናችንን ጐላ አድርጎ ያሳያል። እንዴት? ኢየሱስ የሰጠው ምልክት በሕዝቦችና በመንግሥታት መካከል ጦርነት እንደሚኖር ይናገራል። ይህ ምልክት የሚፈጸመው በኃያላን መንግሥታት መካከል በሚደረግ ሌላ አጠቃላይ ጦርነት ነው ብንል ምን ይሆን ነበር? እንዲህ የመሰለ ጦርነት ቢነሣ በሕይወት የሚተርፍ ሰው አይኖርም። ስለዚህ ከእልቂት የሚተርፉ ሰዎች እንዲኖሩ የአምላክ ዓላማ መሆኑ ወደዚህ አሮጌ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም መቅረባችንን ያሳያል።’

ወይም እንዲህ ማለት ትችላለህ:- ‘የዓለምን ሁኔታዎች ከዚህ ትንቢት ጋር ማዛመድ የጣት አሻራን ከአሻራው ባለቤት ጋር እንደማዛመድ ነው። ይህን ዓይነት አሻራ የሚኖረው ሌላ ሰው ሊኖር አይችልም። በተመሳሳይም በ1914 የጀመሩት ሁኔታዎች ወደፊት በሚመጣ ትውልድ ውስጥ አይደገሙም።’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘የዚህ ምልክት ክፍል የሆኑት ነገሮች ሁሉ በግልጽ እየታዩ ነው።’ (2) ‘መቼም በኖኅ ዘመን እንደነበሩት ሰዎች መሆን እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። (ማቴ. 24:37–39)’

‘መጨረሻው በእኛ የሕይወት ዘመን አይመጣም’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ይሁን እንጂ አንድ ወቅት ላይ አምላክ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ እንደሚወስድ ያምናሉ፤ አይደለም?’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- (1) ‘ይህ የሚሆንበትን ጊዜ ማወቅ የምንችለው አምላክ ከገለጸልን ብቻ ነው። ቀኑን ወይም ሰዓቱን ማንም ማወቅ እንደማይችል ኢየሱስ በግልጽ አስረድቷል። ቢሆንም ይህ ጥፋት በሚመጣበት ጊዜ በሚኖረው ትውልድ ዘመን ስለሚሆኑት ነገሮች በዝርዝር ገልጿል።’ (2) ‘ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ የሰጠው መግለጫ እርስዎ በግል የሚያውቋቸውን ነገሮች ይጨምራል። (ከተቻለ ቀደም ባሉት ገጾች ላይ የተሰጡትን ሐሳቦች በመጠቀም ስለ ምልክቱ በዝርዝር ግለጽ።)’

‘ስለ እነዚህ ነገሮች አልጨነቅም፤ እኔ የማስበው ስለዛሬው ቀን ብቻ ነው’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘ስለወደፊቱ ጊዜ ከመጠን በላይ አለመጨነቅ ጥሩ ነው። ሆኖም ግን ሁላችንም በራሳችንም ሆነ በምንወዳቸው ሰዎች ላይ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ ለመኖር ዕቅድ ለማውጣት እንሞክራለን። ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ዕቅድ ማውጣት ተገቢ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከፊታችን አስደናቂ ነገሮች እንደሚጠብቁን ይናገራል። በእነዚህ አስደናቂ ነገሮች ለመጠቀም የሚያስችለንን ዕቅድ ብናወጣ ጥበበኞች እንሆናለን። (ምሳሌ 1:33፤ 2 ጴጥ. 3:13)’

‘ስለ እነዚህ መጥፎ ሁኔታዎች ማሰብ አልፈልግም። ስለወደፊቱ ሁኔታ ብሩህ አመለካከት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ’

እንዲህ በማለት ልትመልስ ትችላለህ:- ‘እንዲያውም ባይገርምዎ፤ ኢየሱስ በዘመናችን የሚኖሩት ተከታዮቹ ስለወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያስችል ምክንያት እንደሚኖራቸው ተናግሯል። (ሉቃስ 21:31)’ ከዚያም ምናልባት እንዲህ በማለት ልትቀጥል ትችላለህ:- ‘ይሁን እንጂ በዓለም የሚሆኑትን ነገሮች እንዳያዩ ዓይናቸውን ጨፍነው እንዲደሰቱ እንዳልነገራቸው ልብ ይበሉ። በጥሩ ምክንያት ላይ የተመሠረተ ተስፋ እንደሚኖራቸው ተናግሯል። የዓለምን ሁኔታዎች ትርጉም ስለሚረዱና ውጤታቸውም ምን እንደሚሆን ስለሚያውቁ ተስፋቸው ጽኑ መሠረት አለው።’