በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገለልተኝነት

ገለልተኝነት

ፍቺ:- ገለልተኝነት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ተፃራሪ ቡድኖች ኖረው ከአንዱም ወገን የማይሰለፉ ወይም አንዱንም የማይደግፉ ሰዎች የሚወስዱት አቋም ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ጥንትም ሆነ ዛሬ፣ በማንኛውም አገርና ሁኔታ ቢኖሩ በዚህ ዓለም አንጃዎች መካከል በሚነሡ ግጭቶች በሙሉ ገለልተኛ ሆነው ለመኖር ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው የታሪክ ሐቅ ነው። ሌሎች ሰዎች የአርበኝነት በዓላትን በማክበር፣ ወይም የጦር ኃይል አባል ሆኖ በማገልገል፣ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል በመሆን፣ ወይም ለፖለቲካ ሥልጣን በመወዳደር፣ ወይም የፖለቲካ ባለሥልጣኖችን በመምረጥ ረገድ ለሚያደርጉት ተሳትፎ ክርስቲያኖች ጣልቃ በመግባት አድርጉ ወይም አታድርጉ አይሉም። እነርሱ ራሳቸው ግን የመጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ብቻ ያመልካሉ። ለዚህም አምላክ ሕይወታቸውን ሳይቆጥቡ ሙሉ በሙሉ ወስነዋል። ለመንግሥቱም ሙሉ ድጋፍ ይሰጣሉ።

ክርስቲያኖች ለዓለማዊ መንግሥታት ሥልጣን ላላቸው አቋም መመሪያ ሆነው የሚያገለግሏቸው የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?

ሮሜ 13:1, 5–7:- “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች [የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች] ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ . . . ስለ ቁጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው። . . . ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፣ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ።” (ያለ አምላክ ፈቃድ ሊኖር የሚችል መንግሥት የለም። እውነተኛ ክርስቲያኖች ባለሥልጣኖች በግለሰብ ደረጃ ምንም ዓይነት አኗኗር ቢኖራቸው በቦታቸው ምክንያት ያከብሯቸዋል። ለምሳሌ ያህል መንግሥት የሚሰበስበውን ቀረጥ ባለሥልጣኖች ለምንም ነገር ቢያውሉት ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ ለሚያገኙት አገልግሎትና ጥቅም ግብር በሐቅ ይከፍላሉ።)

ማር. 12:17:- “ኢየሱስም መልሶ:- የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው።” (ስለዚህ ክርስቲያኖች ዓለማዊ መንግሥታት የሚጠይቋቸውን ግብር ከመክፈል በተጨማሪ አምላክ የሚፈልግባቸውን የላቀ ግዴታ መፈጸም እንደሚኖርባቸው ምን ጊዜም የነበራቸው አቋም ነው።)

ሥራ 5:28, 29:- “[አንድ የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቃል አቀባይ:-] በዚህ ስም [በኢየሱስ ክርስቶስ] እንዳታስተምሩ [እናንተን ሐዋርያትን] አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፣ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ:- ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል።” (በሰብዓዊ ገዥዎች ትእዛዝና በአምላክ ትእዛዝ መካከል ቀጥተኛ ግጭት ሲፈጠር እውነተኛ ክርስቲያኖች በቅድሚያ አምላክን በመታዘዝ የሐዋርያትን ምሳሌ ተከትለዋል።)

እውነተኛ ክርስቲያኖች በጦርነት በመካፈል ረገድ ሊኖራቸው ስለሚገባው አቋም ምን ጊዜም መመሪያ ሆነው ያገለገሏቸው የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?

ማቴ. 26:52:- “ኢየሱስ እንዲህ አለው:- ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ።” (ውጊያ ትክክል ቢሆን ኖሮ የአምላክን ልጅ ከጠላቶቹ ለመከላከል ከመዋጋት የበለጠ ለውጊያ የሚያበቃ ምክንያት ሊኖር ይችል ነበርን? አዎ፣ ኢየሱስ እዚህ ላይ ደቀ መዛሙርቱ ለጦርነት በሚያገለግሉ የጦር መሣሪያዎች መጠቀም እንደማይገባቸው አመልክቷል።)

ኢሳ. 2:2–4:- “በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ . . . በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፣ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” (በብሔራት ውስጥ ያሉት ግለሰቦች የትኛውን መንገድ መከተል እንደሚገባቸው ራሳቸው መወሰን ይኖርባቸዋል። የይሖዋን ፍርድ በቁም ነገር የሚመለከቱ ሁሉ አምላካቸው ይሖዋ መሆኑን የሚያረጋግጥ ተግባር ይፈጽማሉ።)

2 ቆሮ. 10:3, 4:- “በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፣ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፣ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው።” (ጳውሎስ እዚህ ላይ የገለጸው ጉባኤውን ከሐሰት ትምህርቶች ለመጠበቅ የማታለልና የጉረኝነት አነጋገር፣ ወይም ሥጋዊ የጦር መሣሪያዎችንና የመሳሰሉትን እንዳልተጠቀመ ነበር።)

ሉቃስ 6:27, 28:- “ለእናንተ ለምትሰሙ [እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ] እላችኋለሁ፣ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፣ የሚረግሙአችሁን መርቁ፣ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ።”

የጥንቶቹ እስራኤላውያን ጦርነት እንዲያደርጉ ይሖዋ ፈቅዶላቸው የለምን?

ይሖዋ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ርስት አድርጎ የሰጣቸውን ምድር ለመውረስ በጦርነት እንዲጠቀሙና በመጥፎ ድርጊቶቻቸውና እውነተኛውን አምላክ በመናቃቸው ምክንያት ይሖዋ መኖር እንደማይገባቸው የወሰነባቸውን ሕዝቦች እንዲያጠፉ አዝዞ ነበር። (ዘዳ. 7:1, 2, 5፤ 9:5፤ ዘሌ. 18:24, 25) ይሁን እንጂ ረዓብና ገባኦናውያን በይሖዋ ማመናቸውን የሚያሳይ ተግባር ስላሳዩ ምሕረት ተደርጎላቸዋል። (ኢያሱ 2:9–13፤ 9:24–27) አምላክ በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ ከውጊያ ነፃ ስለሚያደርጉ ደንቦችና ውጊያው እንዴት መካሄድ እንደሚኖርበት በመግለጽ እርሱ የሚፈቅደው ውጊያ እንዴት ያለ መሆን እንደሚገባው ደንግጐ ነበር። በእርግጥም እነዚህ ጦርነቶች የይሖዋ ቅዱስ ጦርነቶች ነበሩ። የትኛውም አገር ቢሆን ዛሬ የሚያካሂደው ጦርነት የይሖዋ ቅዱስ ጦርነት ሊሆን አይችልም።

የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም አዲስ ሁኔታ ተፈጠረ። ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር አይደሉም። የክርስቶስ ተከታዮች ከሁሉም ብሔራት ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ታዘው ነበር። በዚህም ምክንያት ከጊዜ በኋላ እውነተኛውን አምላክ የሚያመልኩ ሰዎች በሁሉም አገሮች ይኖራሉ። ይሁን እንጂ ብሔራት የሚዋጉበት ዓላማ ምንድን ነው? የመላዋን ምድር ፈጣሪ ፈቃድ ለማድረግ ነው ወይስ ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ? በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሌላውን አገር ለመውጋት ቢዘምቱ የእምነት ወንድሞቻቸውንና እነርሱ የሚጸልዩለት አምላክ እንዲረዳቸው የሚጸልዩ ሰዎችን መውጋት ይሆንባቸዋል። ክርስቶስ ሰይፋቸውን እንዲያስቀምጡ ተከታዮቹን አዟል፤ ይህም ተገቢ ነው። (ማቴ. 26:52) ከእንግዲህ ለእውነተኛው አምላክና ለቃሉ ክብር የማይሰጡትን ሰዎች ተዋግቶ የሚያጠፋው በሰማያት ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—2 ተሰ. 1:6–8፤ ራእይ 19:11–21

የጥንት ክርስቲያኖች በጦር ኃይሎች ውስጥ ገብቶ በማገልገል ረገድ ስለነበራቸው አቋም ዓለማዊ ታሪክ ምን ያስረዳል?

“መረጃዎች ሁሉ በጥንቃቄ ሲመረመሩ እስከ ማርከስ ኦሪሊየስ ዘመነ መንግሥት ድረስ [ከ161 እስከ 180 እዘአ የገዛው ሮማዊ ንጉሠ ነገሥት] ወታደር የሆነ ክርስቲያንና ክርስቲያን ከሆነ በኋላ በውትድርና አገልግሎት የቀጠለ ወታደር አልነበረም።”—ዘ ራይዝ ኦቭ ክርስቲያኒቲ (የክርስትና አነሣሥ) (ለንደን፣ 1947)፣ ኢ ደብልዩ ባርነስ፣ ገጽ 333

“እኛ በጦርነት፣ እርስ በርስ በመተራረድና በክፋት ሁሉ ተሞልተን የነበርን ሰዎች በምድር ሁሉ ላይ የጦር መሣሪያዎቻችንን በሙሉ ማለትም ሰይፋችንን ማረሻ፣ ጦራችንን መቆፈሪያ መሣሪያ አድርገን ለውጠናል። ከአብ ከራሱና በተሰቀለው በኩል ያገኘናቸውን ባሕርያት፣ ማለትም ታማኝነትን፣ ጽድቅን፣ ወንድማማችነትን፣ እምነትንና ተስፋን እንኮተኩታለን።”—ጀስቲን ማርቲር “ትራይፎ ከተባለ አይሁዳዊ ጋር ያደረገው ውይይት” ላይ የጠቀሰው (2ኛው መቶ ዘመን እዘአ)፣ ዘ አንቲ ናይሲየን ፋዘርስ (ግራንድ ራፒድስ፣ ሚቺጋን፣ ከ1885 የኢድንበርግ እትም እንደገና የታተመ) በኤ ሮበርትስ እና ጄ ዶናልድሰን የተዘጋጀ፣ ጥራዝ 1፣ ገጽ 254

“[ክርስቲያኖች] በሲቪል አስተዳደር ወይም ውትድርና ውስጥ ገብተው ለሮማ ግዛት ለመከላከል እምቢ ብለዋል። . . . ክርስቲያኖች ብልጫ ያለውን ቅዱስ ተግባር ካልተዉ በቀር ወታደሮች፣ የሕግ ባለ ሥልጣኖች ወይም መሣፍንት ሊሆኑ አይችሉም ነበር።”—ሂስትሪ ኦቭ ክርስቲያኒቲ (የክርስትና ታሪክ) (ኒው ዮርክ፣ 1891)፣ ኤድዋርድ ጊበን፣ ገጽ 162, 163

እውነተኛ ክርስቲያኖች በፖለቲካ ጉዳዮችና እንቅስቃሴዎች በመካፈል ረገድ ሊኖራቸው ስለሚገባው አቋም ምንጊዜም መመሪያ ሆነው ያገለገሏቸው የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?

ዮሐ. 17:16:- “እኔ [ኢየሱስ] ከዓለም እንዳይደለሁ [እነርሱም] ከዓለም አይደሉም።”

ዮሐ. 6:15 የ1980 ትርጉም:- “ሰዎቹ ግን [አይሁዳውያን] በግድ ወስደው ሊያነግሡት እንዳሰቡ ባወቀ ጊዜ ኢየሱስ ብቻውን እንደገና ራቅ ብሎ ወደ ኮረብታ ሄደ።” ከጊዜ በኋላ ለሮማዊው አገረ ገዥ እንዲህ ብሎት ነበር:- “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ መንግሥቴስ ከዚህ ዓለም ብትሆን፣ ወደ አይሁድ እንዳልሰጥ ሎሌዎቼ ይዋጉልኝ ነበር፤ አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም።”—ዮሐ. 18:36

ያዕ. 4:4:- “አመንዝሮች ሆይ፣ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” (ጉዳዩ ይህን ያህል አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም 1 ዮሐንስ 5:19 “ዓለምም በሞላው በክፉው [ተይዟል]” ይላል። ኢየሱስ በ⁠ዮሐንስ 14:30 ላይ ሰይጣንን “የዓለም ገዥ” ብሎታል። ስለዚህ አንድ ሰው የትኛውንም ወገን ቢደግፍ ዞሮ ዞሮ በማን ቁጥጥር ሥር ይሆናል?)

የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የሚባሉት በፖለቲካ ጉዳዮች በመካፈል ረገድ ስለነበራቸው አቋም ዓለማዊ ታሪክ ጸሐፊዎች ምን ገልጸዋል?

“የክርስትና እምነት እንደጀመረ አካባቢ አረማዊውን ዓለም ይገዙ የነበሩት ባለ ሥልጣኖች ዓላማውን በትክክል ያልተረዱለትና የተጠላ እምነት ነበር። . . . ክርስቲያኖች ሮማውያን ዜጎች የሚፈጽሟቸውን አንዳንድ ግዳጆች አይፈጽሙም ነበር። . . . የፖለቲካ ሹመት አይቀበሉም።ኦን ዘ ሮድ ቱ ሲቪላይዜሽን፣ ኤ ወርልድ ሂስትሪ (ወደ ሥልጣኔ በሚደረግ ጉዞ የዓለም ታሪክ) (ፊላደልፊያ፣ 1937)፣ ኤ ሔክልና ጄ ሲግማን፣ ገጽ 237, 238

“ክርስቲያኖች የካህናትና የመንፈሳውያን ዘር ሆነው ከመንግሥት ጉዳዮች የራቁና ጣልቃ የማይገቡ ነበሩ። የሕዝቡ ሕይወት በክርስትና ይነካ የነበረው በንጽሕናውና በአገሩ ዜጎች ላይ የቅድስና ስሜት ለማሳደር በሚያደርገው ጥረት ብቻ እንደሆነ ለመቀበል እንገደዳለን።”—ዘ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ክርስቲያን ሪሊጅን ኤንድ ቸርች ዲዩሪንግ ዘ ፈርስት ስሪ ሴንቸሪስ (የክርስትና ሃይማኖት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት) (ኒው ዮርክ፣ 1848)፣ አውጉስተስ ኒያንደር፣ በኤች ጄ ሮዝ ከጀርመንኛ የተተረጎመ፣ ገጽ 168

እውነተኛ ክርስቲያኖች ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙሮችን በተመለከተ ሊኖራቸው ስለሚገባው አቋም ምንጊዜም መመሪያ ሆነው ያገለገሏቸው ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?

1 ቆሮ. 10:14:- “ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ።” (በተጨማሪ ዘጸአት 20:4, 5)

1 ዮሐ. 5:21:- “ልጆች ሆይ፣ ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ።”

ሉቃስ 4:8:- “ኢየሱስም መልሶ:- ለጌታ [“ለይሖዋ” አዓት] ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል አለው።”

በተጨማሪ ዳንኤል 3:1–28⁠ን ተመልከት።

እንደነዚህ ያሉት የጀግንነት ምልክቶችና የአከባበር ሥነ ሥርዓቶች በእርግጥ ሃይማኖታዊ መንፈስ አላቸውን?

“በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች የሚፈጸመው የሰንደቅ ዓላማ አከባበርና የመሐላ ሥርዓት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው በማለት [ታሪክ ጸሐፊው] ካርልተን ከብዙ ዓመታት በፊት ገልጸዋል። . . . እነዚህ በየዕለቱ የሚፈጸሙ የአከባበር ሥርዓቶች ሃይማኖታዊ መንፈስ ያላቸው መሆኑን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀረቡለት በርካታ ክሶች ላይ አረጋግጧል።”—ዘ አሜሪካን ካራክተር (ኒው ዮርክ፣ 1956)፣ ዲ ደብልዩ ብሮጋን፣ ገጽ 163, 164

“የጥንቶቹ ሰንደቅ ዓላማዎች ሙሉ በሙሉ ሃይማኖታዊ የሆነ ባሕርይ ነበራቸው። . . . ለብዙ መቶ ዘመናት የእንግሊዝ ብሔራዊ አርማ ሆኖ የቆየው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀይ መስቀል ሃይማኖታዊ አርማ ነው። እንዲያውም ብሔራዊ አርማዎች የቅዱስነት ባሕርይ እንዲያገኙ ለማድረግ የሃይማኖት እርዳታ ይፈለግ የነበረ ይመስላል። ብዙዎቹ ሰንደቅ ዓላማዎች ቅዱስ ተደርገው ይቆጠሩ ከነበሩ አርማዎች የተገኙ እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል።” ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ (1946)፣ ጥራዝ 9፣ ገጽ 343

“[የወታደራዊው ከፍተኛ] ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት በተገኙበት ኅዳር 19 ለብራዚል ሰንደቅ ዓላማ ክብረ በዓል ተደርጎለታል። . . . ሰንደቅ ዓላማው ከተሰቀለ በኋላ የጦር ሠራዊቱ ሚኒስቴር ጄኔራል ትሪስታኦ ደ አልንካር አራሪፔ ስለዚህ ዓይነቱ አከባበር ሲገልጹ:- ‘ . . . ሰንደቅ ዓላማዎች በአርበኝነት ሃይማኖት መለኮትነት ያላቸውና ሊመለኩ የሚገባቸው አርማዎች ሆነዋል። . . . ሰንደቅ ዓላማ እንደ ቅዱስ ነገር ተቆጥሮ ይከበራል፣ ይመለካልም። . . . አባት አገራችን እንደሚመለክ ሁሉ ሰንደቅ ዓላማም ይመለካል’ ብለዋል።”—ዳያሪዮ ዳ ጁስቲካ (የፌዴራሉ ዋና ከተማ፣ ብራዚል)፣ የካቲት 16, 1956፣ ገጽ 1906

የጥንት ክርስቲያኖች የሚባሉት የጀግንነት በዓሎችን በተመለከተ ስለነበራቸው አቋም ዓለማዊ ታሪክ ምን ይላል?

“ክርስቲያኖች ለንጉሠ ነገሥቱ ታላቅነት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ሲታዘዙ . . . እምቢ ይሉ ነበር። ይህም በዛሬው ጊዜ ለሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ ለመስጠት ወይም የታማኝነት ቃለ መሐላ ለማሰማት እምቢተኛ ከመሆን ጋር የሚተካከል ነው። . . . አብዛኛውን ጊዜ መሥዋዕቱን ለማቅረብ አመቺ እንዲሆን በአደባባዩ ላይ እሳት የሚነድበት መሠዊያ ተዘጋጅቶ የሚቀመጥ ቢሆንም መሥዋዕት ለማቅረብ የተስማሙ ክርስቲያኖች በጣም ጥቂቶች ናቸው። ከአንድ እስረኛ የሚፈለገው ጭብጥ እጣን በእሳቱ ላይ እንዲበትን ብቻ ነበር። ወዲያው መሥዋዕት ያቀረበ ስለመሆኑ ምሥክር ወረቀት ተሰጥቶት በነጻ ይለቀቃል። በተጨማሪም ንጉሠ ነገሥቱ የሮማ መንግሥት ራስ የበላይ በመሆኑ ያለውን የመለኮትነት ባሕርይ እንደሚቀበል ማመልከቱ እንጂ ንጉሠ ነገሥቱን ማምለኩ እንዳልሆነ በጥንቃቄ ይገለጽለት ነበር። ያም ሆኖ ግን ክርስቲያኖች ይህን ፈጽመው ከቅጣት ለመዳን ፈቃደኛ አልሆኑም።”—ዞስ አባውት ቱ ዳይ (ኒው ዮርክ፣ 1958)፣ ዲ ፒ ማኒክስ፣ ገጽ 135, 137

“የንጉሠ ነገሥት አምልኮ የሚፈጸመው በንጉሠ ነገሥቱ ምስል ፊት በቆመው መሠዊያ ላይ ጥቂት እጣን በመበተን ወይም ጥቂት የወይን ጠጅ በማፍሰስ ነበር። ከዚህ ሁኔታ በጣም ርቀን ለምንገኘው ለእኛ ይህ ድርጊት . . . ለሰንደቅ ዓላማ ወይም ለአንድ ለታወቀ የአገር ገዥ አክብሮትንና የአርበኝነት ስሜትን ለመግለጽ የእጅ ሰላምታ ከመስጠት ጋር ምንም ልዩነት አናይበት ይሆናል። በአንደኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እንደዚህ ተሰምቷቸው ሊሆን ቢችልም ለክርስቲያኖች ግን እንደዚህ አልነበረም። እነዚህ ክርስቲያኖች ይህን ማድረግ ንጉሠ ነገሥቱን እንደ አምላክ አድርጎ መቀበል ስለሚሆንና ይህም ለአምላክና ለክርስቶስ ያላቸውን ታማኝነት ማጓደል ስለሚሆንባቸው አድራጎቱን ከሃይማኖታዊ አምልኮ ለይተው አልተመለከቱም ነበር። መሥዋዕት ለማቅረብ አሻፈረኝ ብለዋል።”—ዘ ቢግኒንግስ ኦቭ ዘ ክርስቲያን ሪሊጅን (የክርስትና ሃይማኖት አጀማመር) (ኒው ሔቨን፣ ኮነስቲከት፤ 1958)፣ ኤም ኤፍ ኢሊር፣ ገጽ 208, 209

ክርስቲያኖች ገለልተኞች በመሆናቸው አብረዋቸው ለሚኖሩት ሰዎች ደህንነት ደንታ ቢሶች ናቸው ማለት ነውን?

እንደዚህ ማለት አይደለም። ኢየሱስ “ሰውን ሁሉ እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” ያለውን ትእዛዝ በሚገባ ያውቃሉ። ይህንንም ለመፈጸም ከልብ ይጥራሉ። (ማቴ. 22:39 የ1980 ትርጉም ) እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሰው ሁሉ በተለይ ደግሞ ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ” በማለት የጻፈውን ምክር ለመፈጸም ይጥራሉ። (ገላ. 6:10) ለሰው ሊያደርጉ ከሚችሉት መልካም ነገር ሁሉ የሚበልጠው በሰው ልጅ ላይ የተጫኑትን ችግሮች በሙሉ ለዘለቄታው ስለምታስወግደውና ለሚቀበሏት ሁሉ አስደናቂ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ስለምታስገኘው የአምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች መንገር እንደሆነ ያምናሉ።