በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቤዛ

ቤዛ

ፍቺ:- ከአንድ ዓይነት ግዴታ ወይም ካልተፈለገ ሁኔታ ለማስለቀቅ የሚከፈል ዋጋ ነው። ከሁሉ የበለጠ ግምት የሚሰጠው የቤዛ ዋጋ የፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው። ኢየሱስ የዚህን ቤዛ ዋጋ በሰማይ ስለከፈለ የአዳም ልጆች በሙሉ ከአባታችን ከወረስነው ኃጢአትና ሞት ነፃ የምንወጣበትን መንገድ ከፍቶልናል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በሰማዕትነት ከሞቱት ሌሎች ሰዎች ሞት የሚለየው በምንድን ነው?

ኢየሱስ ፍጹም ሰው ነበር። ከማንኛውም ዓይነት የኃጢአት እድፈት ነፃ ሆኖ ተወልዷል። ይህንን ፍጽምና እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ጠብቋል። “እርሱ ኃጢአትን አላደረገም።” “ነውር የሌለበት ከኃጢአተኞች የተለየ” ነበር።—1 ጴጥ. 2:22፤ ዕብ. 7:26

እርሱ ብቸኛው የአምላክ ልጅ ነው። ይህንንም አምላክ ራሱ ከሰማይ ሰዎች እየሰሙት መስክሯል። (ማቴ. 3:17፤ 17:5) ይህ ልጁ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ይኖር ነበር። አምላክ በመላው ጽንፈ ዓለም ውስጥ የተፈጠሩትን ሰዎችና ነገሮች ወደ ሕልውና ያመጣው በእርሱ በኩል ነው። አምላክ ፈቃዱን ለማስፈጸም ሲል የዚህን ልጁን ሕይወት በተአምር ወደ አንዲት ድንግል ማኅፀን አዛውሮ ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲወለድ አደረገ። ኢየሱስ በእርግጥ ሰው የመሆኑ ሐቅ እንዲተኮርበት ሲል ራሱን የሰው ልጅ እያለ ጠርቷል።—ቆላ. 1:15–20፤ ዮሐ. 1:14፤ ሉቃስ 5:24

በገዳዮቹ ላይ ምንም ለማድረግ የማይችል ደካማ ሰው አልነበረም። “ነፍሴን ደግሞ . . . በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም” ብሏል። (ዮሐ. 10:17, 18) መላእክት ጣልቃ ገብተው ስለ እርሱ እንዲዋጉለት ለመጠየቅ አልፈለገም። (ማቴ. 26:53, 54) ክፉ ሰዎች ሴራቸውን ለመፈጸም እንዲገድሉት ቢፈቀድላቸውም ሞቱ መሥዋዕታዊ ሞት ነበር።

የፈሰሰው ደሙ ለሌሎች መዳንን የሚያስገኝ ዋጋ ነበረው። “የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” (ማር. 10:45) ስለዚህ የእርሱ ሞት ፍጹም አቋሙን ላለማበላሸት ተብሎ የተፈጸመ ሰማዕታዊ ሞት አልነበረም።

በተጨማሪም ገጽ 265, 266 ላይ “መታሰቢያ በዓል” ከሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ቤዛው በዚህ መንገድ መቅረቡ አስፈላጊ የሆነው ለምን ነበር?

ሮሜ 5:12:- “ኃጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] ወደ ዓለም ገባ፣ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።” (የቱንም ያህል ትክክል እየሠራን ለመኖር ብንጥር ሁላችንም ከተወለድንበት ቀን ጀምሮ ኃጢአተኞች ነን። [መዝ. 51:5] ለዘላለም መኖር የድካም ዋጋ ሆኖ እንዲከፈለን የሚያስችል ምንም ዓይነት መንገድ የለም።)

ሮሜ 6:23:- “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው።”

መዝ. 49:6–9:- “በኃይላቸው የሚታመኑ፣ በባለጠግነታቸውም ብዛት የሚመኩ፤ ወንድም ወንድሙን አያድንም፣ ሰውም አያድንም፤ ቤዛውን ለእግዚአብሔር አይሰጥም፣ ለዘላለም እንዲኖር፣ ጥፋትንም እንዳያይ፤ የነፍሳቸው ለውጥ ከብሮአልና፣ [“(ነፍሳቸውን ለመዋጀት የሚከፈለው ዋጋ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ቤዛ ሊገኝላቸው አልቻለም)” አዓት ] ለዘላለም ቀርቶአልና። [“ለዘላለም እንዲኖርና መቃብር እንዳያይ ሊያደርጉ አይችሉም።” አዓት ]” (ፍጹም ያልሆነ ማንም ሰው ሌላውን ሰው ከኃጢአትና ከሞት ለማላቀቅ የሚያስችል መንገድ የለውም። ገንዘቡ የዘላለም ሕይወት ሊገዛ አይችልም። ኃጢአተኛ በመሆኑ የኃጢአትን ደመወዝ ለመክፈል የሚሞተውም ሞት ቢሆን ማንንም ከኃጢአት ለማስፈታት የሚበቃ ዋጋ አይሆንም።)

አዳምና ሔዋን በሠሩት ዓመፅ ምክንያት ቢሞቱም አምላክን ለመታዘዝ የሚመርጡ ልጆቻቸው ሁሉ በቀላሉ ለዘላለም እንዲኖሩ ፈቅጃለሁ ብሎ አምላክ ለምን አይናገርም ነበር?

ይሖዋ ‘ጽድቅንና ፍትሕን የሚወድ’ ስለሆነ ነው። (መዝ. 33:5፤ ዘዳ. 32:4፤ ኤር. 9:24) ስለዚህ ለተፈጠረው ችግር አምላክ ያስገኘው መፍትሔ ጽድቁን የሚያስከብር ፍጹም ፍትሕ የሚጠይቀውን የሚያሟላና ፍቅሩንና ምሕረቱን የሚያጎላ ነው። ይህ የሆነው እንዴት ነው?

(1) አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት አንድም ልጅ አልወለዱም ነበር። ስለዚህ ፍጹም ሆኖ የተወለደ ሰው አልነበረም። የአዳም ልጆች በሙሉ የተወለዱት በኃጢአት ነው። ኃጢአት ደግሞ ወደ ሞት ይመራል። ይሖዋ ይህንን ዝም ብሎ ቢተወው ኖሮ የራሱን የጽድቅ ደረጃዎች ማፍረስ ይሆንበታል። አምላክ እንዲህ በማድረግ የዓመፅ ተባባሪ ለመሆን አይችልም። ፍጹም ፍትሕ የሚጠይቀውን ወደ ጎን ገሸሽ አላደረገም። ስለዚህ በዚህ ረገድ ማንም ፍጡር ጉድለት ሊያገኝበት አይችልም።—ሮሜ 3:21–26

(2) ፍትሕ ችላ ሳይባል ለይሖዋ ፍቅራዊ ታዛዥነት የሚያሳዩትን የአዳም ልጆች ለማዳን ምን ዝግጅት ማድረግ ይቻል ይሆን? ፍጹም የሆነ ሰው መሥዋዕት ሆኖ ቢሞት ይህ ፍጹም ሕይወት ይህን ዝግጅት በእምነት የሚቀበሉትን ሰዎች ኃጢአት ሊሸፍን ይችላል። መላውን የሰው ልጅ ቤተሰብ ኃጢአተኛ ለመሆን ያበቃው የአንድ ሰው (ማለትም የአዳም) ኃጢአት ስለሆነ የሌላ ፍጹም ሰው (ማለትም የሁለተኛው አዳም) መሥዋዕት ሆኖ የሚፈስ ደም ከአዳም ጋር የሚተካከል ዋጋ ስለሚኖረው የፍትሕን ሚዛን ለማስተካከል ይችላል። አዳም ሆን ብሎ ኃጢአት የሠራ ሰው ስለሆነ የዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ አይሆንም። የአዳም ልጆች ግን ለዚህ ኃጢአት የሚከፍሉት ቅጣት በሌላ ሰው ስለተከፈለላቸው ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ሊወጡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ፍጹም ሰው አልነበረም። የሰው ልጆች ይህ ፍጹም ፍትሕ የሚጠይቀውን ብቃት ሊያሟሉ አይችሉም። በዚህ ምክንያት ይሖዋ አስደናቂ ፍቅሩን በማሳየት ከፍተኛ ኪሣራ የሚጠይቅ ዋጋ ከፍሎ ራሱ ይህን ነገር አዘጋጀ። (1 ቆሮ. 15:45፤ 1 ጢሞ. 2:5, 6፤ ዮሐ. 3:16፤ ሮሜ 5:8) አንድያው የአምላክ ልጅ የበኩሉን ለመፈጸም ፈቃደኛ ነበር። ራሱን ዝቅ አድርጎ በሰማይ የነበረውን ክብሩን በመተው ፍጹም ሰው ሆነና ለሰው ልጆች ሁሉ ሞተ።—ፊልጵ. 2:7, 8

ምሳሌ:- አንድ የቤተሰብ ራስ ወንጀል ሠርቶ የሞት ፍርድ ተፈረደበት እንበል። ልጆቹ ምንም መተዳደሪያ የሌላቸው ሆነው ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ ይዘፈቁ ይሆናል። የሚወዳቸው አያታቸው ግን በጉዳዩ ጣልቃ ይገባና አብሮት የሚኖር ልጁ ዕዳቸውን ከፍሎ አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩ ያደርጋል። እርግጥ ልጆቹ ከዚህ ደግነት ለመጠቀም ከፈለጉ ዝግጅቱን መቀበል ይኖርባቸዋል። አያትየው ልጆቹ የአባታቸውን መንገድ እንዳይከተሉ ለማድረግ የሚፈልግባቸው ግዴታ ሊኖር ይችላል።

የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ መሥዋዕት ዋጋ ተጠቃሚዎች እነማን ነበሩ? ዓላማውስ ምን ነበር?

ሮሜ 1:16:- “በወንጌል [ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና እርሱ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስላለው ሚና በሚገልጸው ወንጌል] . . . አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፣ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው።” (በክርስቶስ በኩል ከመጣው የመዳን ዝግጅት እንዲጠቀሙ በመጀመሪያ የተጋበዙት አይሁዳውያን ነበሩ። ከዚያም አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች።)

ኤፌ. 1:11–14:- “[“እኛ” አዓት ] [አይሁዳውያን፣ ሐዋርያው ጳውሎስን ጨምሮ] አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን [የትኛው ርስት? የሰማያዊ መንግሥት ርስት] ተቀበልን። ይኸውም፣ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። እናንተም ደግሞ [በኤፌሶን እንደነበሩት እንደ ብዙዎቹ ሰዎች ከአሕዛብ የመጡት ክርስቲያኖች] የእውነትን ቃል፣ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፣ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፣ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፣ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፣ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።” (ይህ ውርሻ በ1 ጴጥሮስ 1:4 ላይ እንደተመለከተው በሰማይ የተጠበቀ ነው። ራእይ 14:1–4 በዚህ ውርሻ የሚካፈሉት 144,000 እንደሆኑ ያመለክታል። እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ሆነው ለ1,000 ዓመት በሰዎች ልጆች ላይ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። በዚህ ጊዜ ውስጥ አምላክ ምድር ገነት እንድትሆንና ፍጹም በሆኑ የአዳምና ሔዋን ልጆች እንድትሞላ ያለውን ዓላማ ይፈጸማል።)

በዘመናችን ከኢየሱስ መሥዋዕት ተጠቃሚ የሆኑት ሌሎች ሰዎች እነማን ናቸው?

1 ዮሐ. 2:2:- “እርሱ [ኢየሱስ ክርስቶስ] የኃጢአታችን [የሐዋርያው ዮሐንስና በመንፈስ የተቀቡ የሌሎች ክርስቲያኖች ኃጢአት] ማስተስርያ ነው፣ ለኃጢአታችን ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ [ወደፊት በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለሚያገኙት ለሌሎቹ የሰው ልጆች] ኃጢአት እንጂ።”

ዮሐ. 10:16:- “ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፣ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል። ድምፄንም ይሰማሉ፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ።” (እነዚህ “ሌሎች በጐች”፣ የመንግሥቱ ወራሾች የሆኑት ‘የታናሹ መንጋ’ ቀሪዎች ገና እዚህ ምድር ላይ እያሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅራዊ ጥበቃ ሥር ይሆናሉ። ይህም በመሆኑ “ሌሎች በጎች” ‘የአንዱ መንጋ’ ክፍል በመሆን ከመንግሥቱ ወራሾች ጋር ይቀላቀላሉ። ከኢየሱስ መሥዋዕት የሚያገኙት ጥቅም ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት ባይሆንም በብዙዎቹ ጥቅሞች ይካፈላሉ። ውርሻቸው ግን የተለያየ ነው።)

ራእይ 7:9, 14:- “ከዚህ በኋላ አየሁ፣ እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ . . . እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፣ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።” (ስለዚህ የእነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች አባላት ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ በሕይወት ይኖራሉ። በቤዛው ስለሚያምኑ በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም አላቸው። በዚህም ምክንያት ጻድቅ ሆነው መቆጠራቸው ከታላቁ መከራ በሕይወት እንዲያልፉ ያስችላቸዋል።)

በቤዛው ምክንያት ወደፊት ምን ዓይነት በረከቶች ይመጣሉ?

ራእይ 5:9, 10:- “መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፣ [በጉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ] ታርደሃልና፣ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፣ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።” (ከክርስቶስ ጋር የሚገዙት ሰማያዊ ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ የከፈተላቸው ዋነኛ ነገር ቤዛው ነው። በቅርቡ የአዲሲቱ ምድር መንግሥት ገዥዎች በሰማያዊ ዙፋናቸው ላይ ይቀመጣሉ።)

ራእይ 7:9, 10:- “እነሆም፣ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ [እንደ ተሠዋ በግ በሞተው በኢየሱስ ክርስቶስ] ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮኹ:- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።” (እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች ከታላቁ መከራ በሕይወት እንዲያልፉ ያስቻላቸው አንዱ ቁልፍ ነገር በክርስቶስ መሥዋዕት ማመናቸው ነው።)

ራእይ 22:1, 2:- “በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ወንዝ አሳየኝ። በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፣ የዛፉም ቅጠሎች የሕዝብ መፈወሻ ነበሩ።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) (ስለዚህ አምላክ የሰው ልጆችን ኃጢአት ካመጣባቸው ጉድለት ሁሉ ለመፈወስና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ለማስቻል ከሚያደርጋቸው ነገሮች አንዱ የአምላክ በግ የኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት ዋጋ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ ነው።)

ሮሜ 8:21:- “ተስፋውም ፍጥረት ራሱ [የሰው ልጅ] ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።”

ፍጹም ከሆነው የኢየሱስ መሥዋዕት ዘላቂ ጥቅም እንድናገኝ ምን ይፈለግብናል?

ዮሐ. 3:36:- “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይሆናል እንጂ ሕይወትን አያይም።”

ዕብ. 5:9 የ1980 ትርጉም:- “ፍጹም ሆኖ ከተገኘም በኋላ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ለሚታዘዙት ሁሉ ለዘላለም ደኅንነት ምክንያት ሆነላቸው።”

የቤዛው ዝግጅት አምላክ ስለሰው ልጆች ምን እንደሚሰማው ይገልጽልናል?

1 ዮሐ. 4:9, 10:- “በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።”

ሮሜ 5:7, 8 የ1980 ትርጉም:- “በጻድቅ ምትክ ሆኖ የሚሞት ሰው ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ሆኖም በደግ ሰው ምትክ ለመሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን እኛ ኃጢአተኞች ሆነን ሳለ ክርስቶስ በእኛ ምትክ ሞቶአል፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ምን ያህል ታላቅ መሆኑን ያስረዳል።”

ይህ ዝግጅት በአኗኗራችን ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ሊያስከትል ይገባል?

1 ጴጥ. 2:24:- “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፣ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ።” (ይሖዋና ልጁ እኛን ከኃጢአት ለማንጻት ይህን ያህል ዋጋ ከከፈሉ የኃጢአት ዝንባሌዎችን ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ኃጢአት እንደሆነ የምናውቀውን ምንም ነገር ሆን ብለን መፈጸም ጨርሶ ልናስበው እንኳን የማይገባን ነገር መሆን አለበት!)

ቲቶ 2:13, 14:- “ኢየሱስ ክርስቶስ . . . ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፣ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፣ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል።” (ለዚህ አስደናቂ ዝግጅት ያለን አድናቆት ክርስቶስ ለእውነተኛ ተከታዮቹ በሰጠው ሥራ በቅንዓት እንድንካፈል ሊያነሣሣን ይገባል።)

2 ቆሮ. 5:14, 15:- “ይህን ስለ ቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።”