በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ነፍስ

ነፍስ

ፍቺ:- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ነፍስ” የሚለው ቃል የተተረጐመው ከዕብራይስጡ ነፈሽ እና ከግሪክኛው ፕስሂ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም መሠረት ነፍስ ሰውዬው ራሱ ወይም አንድ እንስሳ ወይም ያ ሰው ወይም እንስሳ ያለው ሕይወት ማለት ነው። ይሁን እንጂ ለብዙ ሰዎች “ነፍስ” ማለት ሰው ከሞተ በኋላ ከሥጋው ተለይታ በሕይወት የምትኖር ረቂቅ ነገር ወይም የሰው አካል ክፍል የሆነች መንፈስ ማለት ነው። ሌሎች ደግሞ ነፍስ ሕይወትን የሚያንቀሳቅሰው ኃይል ነው ይላሉ። የኋለኞቹ ሁለት አመለካከቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አይደሉም።

መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ ምን እንደሆነች ለማወቅ የሚረዳን ምን ሐሳብ ይዟል?

ዘፍ. 2:7 የ1879 እትም:- “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ፈጠረ፤ መሬት ከምድር። ባፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት። ሰውም ሕይወት ያለበት ነፍስ ሆነ።” (ሰው ነፍስ እንዳልተሰጠው፤ ከዚህ ይልቅ ሰው እርሱ ራሱ ነፍስ ሆነ ብሎ እንደሚናገር ልብ በል።) (እዚህ ላይ “ነፍስ” ተብሎ የተተረጐመው ቃል ዕብራይስጡ ነፈሽ ነው። ኪጄ፣ አስ እና ዱዌይ ጥቅሱን የተረጐሙት በዚሁ መንገድ ሲሆን ሪስ፣ ጀባ፣ ኒአባ፣ ኒኢ እና የ1980 ትርጉም “ፍጡር” ብለውታል። ኖክስ “ሰው” ይላል።)

1 ቆሮ. 15:45:- “ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ።” (ስለዚህ የግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎችም በነፍስ ምንነት ረገድ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ይስማማሉ።) (እዚህ ላይ “ነፍስ” ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል ጠቃሽ አመልካች የተጨመረበት ፕስሂ ነው። ኪጄ፣ አስ፣ ዱዌይ፣ ጀባ፣ ኒአባ እና ኖክስ “ነፍስ” ሲሉ ሪስ፣ ኒኢ እና ቱኢቨ “ፍጡር” ይላሉ። የ1980 ትርጉም “ሕያው ፍጡር” ይላል።)

1 ጴጥ. 3:20:- “[በኖኅ ዘመን] ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ [ከውኃ ዳኑ።]” (እዚህ ላይ “ነፍስ” ተብሎ የተተረጐመው የግሪክኛ ቃል ፕስሂ የተባለው ቃል የብዙ ቁጥር የሆነው ፕሲሀይ ነው። ኪጄ፣ አስ፣ ዱዌይ እና ኖክስ “ነፍስ” ይላሉ። ጀባ፣ ቱኢቨ፣ ሪስ፣ ኒኢ እና ኒአባ “ሰዎች” ይላሉ።)

ዘፍ. 9:5 አዓት:- “ከዚህም በተጨማሪ የነፍሶቻችሁንም [ወይም “ሕይወታችሁን”፤ በዕብራይስጥ ነፈሽ ] ደም ከእናንተ እጠይቃለሁ።” (እዚህ ላይ ነፍስ ደም እንዳለው ተነግሯል።)

ኢያሱ 11:11:- “በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ [በዕብራይስጥ ነፈሽ ] በሰይፍ ስለት ገደሉ።” (እዚህ ላይ ነፍስ በሰይፍ ሊገደል የሚችል ነገር እንደሆነ ተገልጿል። ስለዚህ እነዚህ ነፍሳት መናፍስት ሊሆኑ አይችሉም።)

መጽሐፍ ቅዱስ እንስሳት ነፍሳት እንደሆኑ የሚናገረው የት ላይ ነው?

ዘፍ. 1:20, 21, 24, 25:- “እግዚአብሔርም አለ:- ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን [“ሕያው ነፍሳት የሆኑ” አዓት ] ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፣ . . . እግዚአብሔርም ታላላቆች አንበሪዎችን፣ ውኃይቱ እንደ ወገኑ ያስገኘቻቸውንም ተንቀሳቃሾቹን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፣ እንደ ወገኑ የሚበሩትንም ወፎች ሁሉ ፈጠረ፤ . . . እግዚአብሔርም አለ:- ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ . . . ታውጣ፤ . . . እግዚአብሔር የምድር አራዊትን እንደ ወገኑ አደረገ፣ እንስሳውንም እንደ ወገኑ፣ የመሬት ተንቀሳቃሾችንም እንደ ወገኑ አደረገ።” (እዚህ ላይ የተጠቀሰው የዕብራይስጥ ቃል ነፈሽ ነው። ሮዘ “ነፍስ” ይላል። አንዳንድ ትርጉሞች “ፍጥረታት” ብለው ተርጉመውታል።)

ዘሌ. 24:17, 18:- “ሰውንም [“የሰውን ነፍስ” አዓት፤ በዕብራይስጥ ነፈሽ ] እስኪሞት ድረስ የሚመታ ፈጽሞ ይገደል። እንስሳንም [“የእንስሳንም ነፍስ” አዓት፤ በዕብራይስጥ ነፈሽ ] እስኪሞት ድረስ የሚመታ ሕይወት በሕይወት ፋንታ ካሣውን ይክፈል።” (የእንስሳትንም ሆነ የሰዎችን ነፍስ ለማመልከት ያገለገለው የዕብራይስጥ ቃል አንድ ነው።)

ራእይ 16:3:- “እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፣ በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ።” (ስለዚህ የግሪክኛ የክርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎችም እንስሳት ነፍስ እንደሆኑ ያመለክታሉ።) (እዚህ ላይ የተጠቀሰው የግሪክኛ ቃል ፕስሂ ነው። ኪጄ፣ አስ እና ዱዌይ “ነፍስ” ብለው ተርጉመውታል። አንዳንድ ትርጉሞች “ፍጥረት” ወይም “ነገር” ብለው ተርጉመውታል።)

የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሌሎች ምሁራን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ የሚናገረውን እንደዚያው አድርገው ይረዱታልን?

“በብሉይ ኪዳን ውስጥ በነፍስና በሥጋ መካከል መከፋፈል [መለያየት] የለም። አንድ እስራኤላዊ ሁለቱን አንድ አድርጎ ስለሚመለከት ሰዎች አንድ አካል እንደሆኑ እንጂ የሁለት ነገሮች ጥምር እንደሆነ አድርጎ አይመለከትም ነበር። ነፈሽ የተባለው ቃል ነፍስ ተብሎ ቢተረጎምም ከሥጋ ወይም ከግለሰቡ አካል የተለየ ነገር ነው ማለት አይደለም። . . . የነፈሽ ተመሳሳይ የሆነው የአዲስ ኪዳን ቃል [ፕስሂ ] ነው። ይህም ቃል ሕይወትን የሚያንቀሳቅሰውን ኃይል፣ ራሱን ሕይወትን ወይም ሕያው የሆነውን ሰው ሊያመለክት ይችላል።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (1967)፣ ጥራዝ 13፣ ገጽ 449, 450

“ሙሴ ‘ነፍስ’ ተብሎ የተተረጎመውን የዕብራይስጥ ቃል (ነፈሽ፣ የሚተነፍስ) ‘ሕያው የሆነ ነገርን’ እንዲሁም ሰብዓዊ ፍጡር ያልሆኑ ነገሮችን ለማመልከት ተጠቅሞበታል። . . . አዲስ ኪዳንም ፕስሂ (‘ነፍስ’) የተባለውን ቃል የተጠቀመበት መንገድ ከነፈሽ የተለየ አይደለም።”—ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ (1976)፣ ማክሮፔድያ፣ ጥራዝ 15፣ ገጽ 152

“ነፍስ ሥጋ ከጠፋ በኋላ በሕይወት ትኖራለች የሚለው እምነት በተራ እምነት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በፍልስፍና ወይም በሃይማኖታዊ ግምት ላይ የተመሠረተ ነው። በቅዱሳን ጽሑፎች ላይም ቢሆን በየትኛውም ስፍራ አልተገለጸም።”—ዘ ጁውሽ ኢንሳይክሎፔድያ (1910)፣ ጥራዝ 6፣ ገጽ 564

የሰው ነፍስ ልትሞት ትችላለችን?

ሕዝ. 18:4:- “ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፤ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፤ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።” (ዕብራይስጡ “ነፈሽ ” ይላል። ኪጄ፣ አስ፣ ሪስ፣ ኒኢ እና ዱዌይ “ነፍስ” ብለው ተርጉመውታል። አንዳንድ ትርጉሞች ደግሞ “ሰው” ወይም “ሰውዬው” ብለው ተርጉመውታል።)

ማቴ. 10:28:- “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን [ወይም “ሕይወትን”] መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ።” (ግሪክኛው ጠቃሽ አመልካች የተጨመረበት ፕስሂ ነው። ኪጄ፣ አስ፣ ሪስ፣ ኒኢ፣ ቱኢቨ፣ ዱዌይ፣ ጀባ እና ኒአባ ሁሉም “ነፍስ” ብለው ተርጉመውታል።)

ሥራ 3:23:- “ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ [በግሪክኛ ፕስሂ ] ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች።”

ሰብዓዊ ነፍሳት (ሰዎች ) ለዘላለም ሊኖሩ ይችላሉን?

በገጽ 243–247 ላይ “ሕይወት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።

ነፍስና መንፈስ አንድ ናቸውን?

መክ. 12:7 አዓት:- “ያን ጊዜ አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ይመለሳል፤ መንፈስም [ወይም የሕይወት ኃይል፤ በዕብራይስጥ ሩዋሕ] ወደ ሰጠው ወደ እውነተኛው አምላክ ይመለሳል።” (ነፍስ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ነፈሽ ሲሆን፣ መንፈስ ተብሎ የተተረጎመው ግን ሩዋሕ መሆኑን አስተውል። ይህ ጥቅስ ሰው በሚሞትበት ጊዜ መንፈሱ አምላክ ወደሚገኝበት ስፍራ እንደሚጓዝ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ሰውዬው እንደገና የመኖሩ ተስፋ በአምላክ ላይ የተመካ ይሆናል ማለት ነው። በተመሳሳይ አነጋገር አንድን ንብረት የገዛ ሰው የሚፈለግበትን ገንዘብ በሙሉ ካልከፈለ ንብረቱ ለቀድሞው ባለቤቱ “ይመለሳል” እንላለን።) (ኪጄ፣ አስ፣ ሪስ፣ ኒኢ እና ዱዌይ ሁሉም ሩዋሕ የሚለውን “መንፈስ” ብለው ተርጉመውታል። ኒአባ “የሕይወት እስትንፋስ” ብሎታል።)

መክ. 3:19 አዓት:- “የሰው ልጆችና የእንስሳ ዕድል ፈንታ አንድ ዓይነት ነው። አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ ሁለቱም አንድ ዓይነት መንፈስ [በዕብራይስጥ ሩዋሕ ] አላቸው።” (ስለዚህ ሰዎችም ሆኑ አራዊት አንድ ዓይነት ሩዋሕ ወይም መንፈስ እንዳላቸው ተገልጿል። ስለቁጥር 20, 21 የተሰጠውን ሐሳብ በገጽ 381, 382 ላይ ተመልከት።)

ዕብ. 4:12:- “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና [በግሪክኛ ፕሳይህስ፤ “ሕይወት” ኒኢ ] መንፈስንም [በግሪክኛ ፕነቭማቶስ ] ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፣ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” (“መንፈስ” የተባለው የግሪክኛ ቃል “ነፍስ” ተብሎ ከተተረጐመው ጋር አንድ አለመሆኑን አስተውል።)

የአንድ ሰው መንፈስ ከሥጋው ከወጣ በኋላ በሕይወት የሚኖር ነገር ይኖራልን?

መዝ. 146:4 አዓት:- “መንፈሱ [በዕብራይስጥ ሩዋሕ] ይወጣል፣ ወደ መሬቱም ይመለሳል፤ በዚያ ቀን ሐሳቡ ሁሉ ይጠፋል።” (ኒአባ፣ ሮዘ፣ ያን እና ዱዌይ [145:4] ሩዋሕ የሚለውን ቃል እዚህ ላይ “መንፈስ” ብለው ሲተረጉሙት አንዳንድ ትርጉሞች ደግሞ “እስትንፋስ” ብለውታል።) (በተጨማሪም መዝሙር 104:29⁠ን አዓት ተመልከት።)

ረቂቅና የማትሞት ነፍስ አለች የሚለው የሕዝበ ክርስትና ትምህርት ከየት የመጣ ነው?

“በአምላክ የተፈጠረና አንድ ሰው በሚፀነስበት ጊዜ ሰውዬውን ሕያው ለማድረግ ወደ ሥጋ እንድትገባ የምትደረግ መንፈሳዊት ነፍስ አለች የሚለው የክርስቲያኖች ፅንሰ ሐሳብ በረዥም ጊዜ ውስጥ የዳበረ የፍልስፍና ፍሬ ነው። ነፍስ መንፈሳዊ አካል መሆኑና የፍልስፍና ፅንሰ ሐሳብነቱ ተቀባይነት ያገኘው በምሥራቁ ዓለም በኦሪገን ዘመን [በ254 እዘአ የሞተ] ሲሆን በምዕራቡ ዓለም ደግሞ በቅዱስ አውጉስቲን ዘመን [በ430 እዘአ የሞተ] ነው። . . . [የአውጉስቲን] መሠረተ ትምህርት . . . ድክመቶቹን ጭምር የወረሰው ከፕላቶ ፍልስፍና ነው።”—ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ (1967)፣ ጥራዝ 13፣ ገጽ 452, 454

“ያለመሞት ፅንሰ ሐሳብ የመነጨው ከግሪካውያን አስተሳሰብ ሲሆን የትንሣኤ ተስፋ ግን አይሁዳዊ አስተሳሰብ ነው። . . . ከእስክንድር ወረራ በኋላ አይሁዳዊው እምነት ቀስ በቀስ የግሪካውያንን ፅንሰ ሐሳቦች መቀበል ጀመረ።”—ዲክሲዮኔር ኦንሲክሎፔዲክ ደ ላ ቢብል (ቫለንስ፣ ፈረንሳይ፤ 1935) በአሌክሳንደር ዌስትፋል የተዘጋጀ፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 557

“የነፍስ አለመሞት በጥንቶቹ ምሥጢራዊ አምልኮቶች የተፀነሰና ፕላቶ በተባለው ፈላስፋ የተብራራ ግሪካዊ ፅንሰ ሐሳብ ነው።”—ፕሪስቢቴሪያን ላይፍ፣ ግንቦት 1, 1970፣ ገጽ 35

“ሞት የሚባል ነገር እንዳለ እናምናለንን? . . . የነፍስና የሥጋ መለያየት አይደለምን? ሞት የእነዚህ ነገሮች መፈጸም ነው። ነፍስ ብቻዋን መኖር ስትጀምርና ከሥጋ ስትለይ ሥጋም ከነፍስ ሲላቀቅ ሞት ነው እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? . . . ነፍስ ሞትን ትቀበላለችን? በፍጹም አትቀበልም። እንግዲያው ነፍስ የማትሞት ናትን? አዎ።”—የፕላቶ “ፋይዶ”፣ ክፍል 64, 105፣ ግሬት ቡክስ ኦቭ ዘ ዌስተርን ዎርልድ (የምዕራቡ ዓለም ታላላቅ መጻሕፍት) በተባለው መጽሐፍ ላይ የወጣ በአር ኤም ሀቺንስ የተዘጋጀ፣ ጥራዝ 7፣ ገጽ 223, 245, 246

“ያለመሞት ጥያቄ የባቢሎናውያን ሃይማኖታዊ ሊቆችን ትኩረት የሳበ እንደነበረ ተመልክተናል። . . . ሕዝቦቹም ሆኑ የሃይማኖታዊ አስተሳሰብ መሪዎች አንድ ጊዜ በሕይወት የኖረ ነገር ፈጽሞ ሊጠፋ የሚችል መሆኑን ለመቀበል አይፈልጉም ነበር። ሞት ወደ ሌላ ዓይነት ሕይወት መዘዋወር እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።”—ዘ ሪሊጅን ኦቭ ባቢሎኒያ ኤንድ አሲሪያ (የባቢሎንና የአሦር ሃይማኖት)፣ (ቦስተን፣ 1898)፣ ጁንየር ኤም ጃስትሮው፣ ገጽ 556

በተጨማሪም በገጽ 99–101 ላይ “ሞት” በሚለው ርዕስ ሥር ተመልከት።