በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ የተነሳ ዓመፅ

በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ የተነሳ ዓመፅ

ሰይጣን በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን አነጋገራት፤ እሷም በአምላክ ላይ ባስነሳው ዓመፅ ተባበረችው

ይሖዋ የፈጠራቸው መንፈሳዊ ፍጡሮች በሙሉ ጥሩ ነበሩ። አንደኛው መልአክ ግን ከጊዜ በኋላ መጥፎ ሆነ። ይህ መልአክ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ሰይጣን በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ይሖዋን በማምለክ ፋንታ እርሱን እንዲያመልኩ ፈለገ። የተፈጸመው ነገር የሚከተለው ነበር፦

በኤደን የአትክልት ሥፍራ ጣፋጭ ፍሬ የሚያፈሩ ብዙ ዛፎች ነበሩ። ይሖዋ ለአዳምና ለሚስቱ ለሔዋን በኤደን የአትክልት ስፍራ ካሉት ዛፎች እንደፈለጉ ሊበሉ እንደሚችሉ ነግሯቸው ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ መብላት እንደሌለባቸው የነገራቸው አንድ ዛፍ ነበረ። ከዚህ ዛፍ ከበሉ በእርግጥ እንደሚሞቱ ነገራቸው።—ዘፍጥረት 2:9, 16, 17

አንድ ቀን ሔዋን ብቻዋን ሳለች እባብ አነጋገራት። በእርግጥ የተናገረው እባቡ አልነበረም፤ እባቡ የሚናገር እንዲመስል ያደረገው ሰይጣን ዲያብሎስ ነበር። ሔዋን ከተከለከለው ፍሬ ብትበላ እንደ አምላክ እንደምትሆን እንጂ ፈጽሞ እንደማትሞት ነገራት። የተናገረው ግን ሐሰት ነበር። ሆኖም ሔዋን ሰይጣንን አመነችና ፍሬውን በላች። በኋላም ለአዳም ሰጠችውና እሱም በላ።—ዘፍጥረት 3:1-6

ከዚህ እውነተኛ ታሪክ ሰይጣን ዓመፀኛና ሐሰተኛ መሆኑን እንገነዘባለን። ሔዋን የአምላክን ትእዛዝ ብትጥስ እንደማትሞት ነግሯት ነበር። ይህ ግን ሐሰት ነበር። እሷም ሆነች አዳም ሞተዋል። ሰይጣንም ኃጢአት ስለ ሠራ ውሎ አድሮ መሞቱ የማይቀር ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ በሕይወት ቆይቶ የሰው ልጆችን ማሳቱን ቀጥሏል። እስከ ዛሬም ሐሰተኛነቱን ስላልተወ ሰዎች የአምላክን ሕግ እንዲጥሱ ለማድረግ ይጥራል።—ዮሐንስ 8:44

ሌሎች መላእክትም ዓመፁ

ከጊዜ በኋላ ሌሎች መላእክትም መጥፎዎች ሆኑ። እነዚህ መላእክት በምድር ላይ ያሉ ቆንጆ ሴቶችን ተመለከቱና ከእነሱ ጋር የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ፈለጉ። ስለዚህ ወደ ምድር መጡና የወንድ ሰብአዊ አካል ለበሱ። ከዚያም ሴቶችን ለራሳቸው ወሰዱ። ይህ የአምላክን ዓላማ የሚጻረር ተግባር ነበር።—ዘፍጥረት 6:1, 2፤ ይሁዳ 6

ክፉ መላእክት ከሴቶች ጋር የፆታ ብልግና ለመፈጸም ብለው ወደ ምድር መጡ

መላእክቱ የፈጸሙት ነገር በሰው ልጆች ላይ ብዙ መከራ አስከትሏል። የእነዚህ መላእክት ሚስቶች ልጆች ወለዱ። የወለዷቸው ልጆች ግን ተራ ልጆች አልነበሩም። ባደጉ ጊዜ ዓመፀኞች፣ ግዙፍና ጨካኞች ሆኑ። በመጨረሻም ምድር በዓመፅ በጣም ከመሞላቷ የተነሳ ይሖዋ ክፉ ሰዎችን በታላቅ የውኃ መጥለቅለቅ ለማጥፋት ወሰነ። ከጥፋት ውኃው የዳኑት ሰዎች ጻድቁ ኖኅና ቤተሰቡ ብቻ ነበሩ።—ዘፍጥረት 6:4, 11፤ 7:23

ክፉዎቹ መላእክት ግን ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተመልሰው ሄዱ እንጂ አልሞቱም። ሆኖም ግን ተቀጥተዋል። ጻድቃን መላእክት ወዳሉበት የአምላክ ቤተሰብ እንዲመለሱ አልተፈቀደላቸውም። በተጨማሪም ዳግመኛ ሰብአዊ አካል እንዲለብሱ ይሖዋ አልፈቀደላቸውም። በመጨረሻም በታላቁ ፍርድ ቀን ይሞታሉ።—2 ጴጥሮስ 2:4፤ ይሁዳ 6

ሰይጣን ከሰማይ ተጥሏል

ሰይጣንና የእሱ ክፉ መላእክት ከሰማይ ወደ ምድር ተጥለዋል

በዚህ ባለንበት መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በሰማይ ጦርነት ተካሂዶ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ሁኔታውን እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል፦ “በሰማይም ጦርነት ተነሳ፦ ሚካኤልና [ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስና] [ጥሩ] መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና [መጥፎ] መላእክቱም ተዋጓቸው፤ ነገር ግን አልቻሏቸውም፤ ከዚያ በኋላም በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ስለሆነም ታላቁ ዘንዶ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ ወደ ታች ተወረወረ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም [ከእሱ ጋር የተባበሩት መጥፎ መላእክት] ከእሱ ጋር ተወረወሩ።”

ውጤቱስ ምን ሆነ? ታሪኩ በመቀጠል “ስለዚህ እናንተ ሰማያትና በውስጣቸው የምትኖሩ ሁሉ ደስ ይበላችሁ!” ይላል። ሰይጣንና መጥፎዎቹ መላእክት ወይም መናፍስት ከዚያ ወዲህ በሰማይ ለመሆን ባለመቻላቸው ጥሩዎቹ መላእክት ደስ ሊላቸው ችሏል። በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችስ? መጽሐፍ ቅዱስ “ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል” ይላል።—ራእይ 12:7-9, 12

አዎን፣ ሰይጣንና ክፉ ግብረ አበሮቹ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን እያሳቱና ወዮ የሚያሰኝ መከራ እያመጡባቸው ነው። እነዚህ ክፉ መላእክት አጋንንት ተብለው ይጠራሉ። እነሱ የአምላክ ጠላቶች ናቸው። ሁሉም ክፉዎች ናቸው።