በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አጋንንት ሙታን በሕይወት አሉ ብለው በሐሰት ይናገራሉ

አጋንንት ሙታን በሕይወት አሉ ብለው በሐሰት ይናገራሉ

መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን “መላውን ዓለም እያሳሳተ” እንደሆነ ይናገራል። (ራእይ 12:9) ሰይጣንና አጋንንቱ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ እንድናምን አይፈልጉም። ሰዎች ሙታን በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ በሆነ ስፍራ በሕይወት ይኖራሉ ብለው እንዲያምኑላቸው ለማድረግ ይጥራሉ። ይህንንም የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

የሐሰት ሃይማኖት

ሰዎች፣ እንስሳት፣ ዓሦችና ወፎች ሁሉም ነፍሳት ናቸው

ብዙ ሃይማኖቶች እያንዳንዱ ሰው ሥጋዊ አካሉ ከሞተ በኋላ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ተሻግራ የምትኖር ነፍስ አለችው ብለው ያስተምራሉ። ሥጋ ሲሞት ነፍስ ግን አትሞትም ይላሉ። ከዚህም በላይ ነፍስ ልትሞት እንደማትችል ማለትም ሞት የማይበግራት ለዘላለም የምትኖር እንደሆነች ይናገራሉ።

የአምላክ ቃል ግን ይህን አያስተምርም። ነፍስ ማለት ሰው ራሱ እንደሆነ እንጂ በሰው ውስጥ ያለች ነገር እንዳልሆነች መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ የአዳምን አፈጣጠር ሲገልጽ “ይሖዋ አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ሠራው፤ በአፍንጫውም የሕይወትን እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውየውም ሕያው ነፍስ ሆነ” ይላል። (ዘፍጥረት 2:7 የግርጌ ማስታወሻ) ስለዚህ አዳም እሱ ራሱ ነፍስ ነበር እንጂ ነፍስ አልተሰጠውም።

እንስሳትም ነፍሳት ተብለው ተጠርተዋል።—ዘፍጥረት 1:20, 21, 24, 30

“ነፍስ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሰው ራሱ ማለት ስለሆነ ነፍሳት ሊሞቱ የሚችሉና የሚሞቱም መሆናቸውን ስንሰማ ሊያስገርመን አይገባም። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚከተለው ይላሉ፦

  • “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እሷ ትሞታለች።”ሕዝቅኤል 18:4

  • “[ሳምሶን] ‘ነፍሴ ከፍልስጤማውያን ጋር ትሙት!’ ብሎ ጮኸ።”—መሳፍንት 16:30፣ የግርጌ ማስታወሻ

  • “በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?”ማርቆስ 3:4 የግርጌ ማስታወሻ

ነፍስ ሟች መሆኗን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል

ሌሎች ጥቅሶችም ነፍስ ልትጠፋ (ዘፍጥረት 17:14)፣ በሰይፍ ልትገደል (ኢያሱ 10:37)፣ ልትታነቅ (ኢዮብ 7:15) እና በውኃ ውስጥ ልትሰጥም እንደምትችል ይገልጻሉ። (ዮናስ 2:6) ስለዚህ ነፍስ ትሞታለች።

መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ብታነበው “ነፍስ አትሞትም” የሚል አነጋገር ፈጽሞ አታገኝም። የሰው ነፍስ መንፈስ አይደለችም። ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም። ሰይጣንና አጋንንቱ ያመጡት ትምህርት ነው። ይሖዋ ማንኛውንም ሃይማኖታዊ ውሸት ይጠላል።—ምሳሌ 6:16-19፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1, 2

መናፍስት ጠሪዎች

አጋንንት የሙታንን መንፈስ መስለው ይቀርባሉ

ሰይጣን ሰዎችን የሚያስትበት ሌላው መንገድ በመናፍስት ጠሪዎች አማካኝነት ነው። መናፍስት ጠሪ የሚባለው ከመንፈሳዊው ዓለም መልእክት በቀጥታ ለመቀበል የሚችል ሰው ነው። በጣም ብዙ ሰዎች፣ መናፍስት ጠሪዎቹን ጨምሮ፣ እነዚህ መልእክቶች የሚመጡት ከሙታን መናፍስት እንደሆነ ያምናሉ። ይሁን እንጂ ይህ እንደማይቻል ከመጽሐፍ ቅዱስ ተመልክተናል።—መክብብ 9:5, 6, 10

ታዲያ እነዚህ መልእክቶች የሚመጡት ከማን ነው? ከአጋንንት ነው! አጋንንት አንድን ሰው በሕይወት ይኖር በነበረበት ጊዜ አነጋገሩን፣ መልኩን፣ ያደረጋቸውን ነገሮችና የሚያውቃቸውን ነገሮች ሊመለከቱና ሊያውቁ ይችላሉ። ስለዚህ የሞቱትን ሰዎች መስሎ መቅረብ ለእነሱ ቀላል ነገር ነው።—1 ሳሙኤል 28:3-19

የሐሰት ወሬዎች

ሰይጣን ሙታን በሕይወት ይኖራሉ የሚለውን ውሸት የሚያስፋፋበት ሌላው መንገድ ደግሞ በሐሰት ወሬዎች አማካኝነት ነው። እንደነዚህ ያሉት የሐሰት ወሬዎች አብዛኛውን ጊዜ ሰዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያርቋቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 4:4

አንዳንድ ሰዎች ከሙታን የተነሱ ሰዎችን ያዩ ይመስላቸዋል

በአፍሪካ ውስጥ ከሞቱ በኋላ ሕያው ሆነው ታዩ ስለሚባሉ ሰዎች ብዙ ወሬዎች ይናፈሳሉ። አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ እነዚህ ሰዎች ታዩ የሚባለው ከኖሩበት ቦታ በራቀ አካባቢ ነው። እስቲ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ሰው ከሞት ተመልሶ የመኖር ችሎታ ካለው ከቤተሰቡና ከወዳጆቹ ርቆ ወደሚገኝ ቦታ ይመለሳል ማለት ምክንያታዊ ነው?’

በተጨማሪም ሰውየው ታየ የተባለው መልኩ የሞተውን ሰው ስለመሰለ ብቻ ሊሆን አይችልም? ለምሳሌ ያህል በአንድ የገጠር አካባቢ ይሰብኩ የነበሩ ሁለት ክርስቲያን ሰባኪዎች አንድ ሽማግሌ ለረጅም ሰዓት ከኋላ ኋላቸው ይከተላቸው እንደነበረ ተገነዘቡ። ለምን እንደሚከተላቸው ሲጠይቁትም ከክርስቲያን ሰባኪዎቹ አንደኛው ከጥቂት ዓመታት በፊት የሞተውን ወንድሙን እንደመሰለው ሰውየው ነገራችው። በእርግጥ ሰውየው ተሳስቶ ነበር፤ ግን መሳሳቱን ለማመን አሻፈረኝ አለ። ይህ ሽማግሌ ለወዳጆቹና ለጎረቤቶቹ ምን ብሎ እንደነገራቸው ለመገመት ትችላለህ።

ቅዠት፣ ሕልምና ድምፅ

አጋንንት በሕልም፣ በቅዥትና በድምፅ አማካኝነት ሰዎችን ያሳስታሉ

ሰዎች ስላዩአቸው፣ ስለሰሟቸው ወይም በሕልም ስለተመለከቷቸው እንግዳ ነገሮች ሰምተህ እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም። እንዲህ ዓይነቶቹ ከተለምዶ ውጭ የሆኑ ተሞክሮዎች አብዛኛውን ጊዜ ያጋጠሟቸውን ሰዎች በጣም ያስፈሯቸዋል። በምዕራብ አፍሪካ የምትኖረው ማሬይን ሟች ሴት አያቷ ሁልጊዜ በሌሊት ሲጠሯት ትሰማ ነበር። ማሬይንም ደንግጣ ትጮኽና ቤተሰቧን በሙሉ ትቀሰቅስ ነበር። በመጨረሻም አእምሮዋን ሳተች።

ታዲያ ሙታን በእርግጥ በሕይወት የሚኖሩ ቢሆኑ ኖሮ የሚወዷቸውን ሰዎች ያስደነግጡ ነበር? በእርግጥ አያደርጉትም ነበር። የእንዲህ ዓይነቱ ጎጂ መልእክት ምንጮች አጋንንት ናቸው።

ይሁን እንጂ ጠቃሚና የሚያጽናኑ ስለሚመስሉ መልእክቶችስ ምን ሊባል ይቻላል? ለምሳሌ ያህል የሴራሊዮኗ ግባሴይ ታማ ነበር። በሕልሟ የሞቱት አባቷ ታዩአት። አባቷም ወደ አንድ ዛፍ ሄዳ ቅጠሉን ወስዳ ውኃ ውስጥ እንድትጨምረውና እንድትጠጣው ነገሯት። ከመጠጣቷ በፊት ለማንም እንዳትናገር ታዘዘች። እሷም እንደታዘዘችው አድርጋ ከሕመሟ ዳነች።

አንዲት ሌላ ሴት ባሏ ከሞተ በኋላ አንድ ቀን እንደታያት ተናገረች። እንዳማረበትና ጥሩ ጥሩ ልብሶች ለብሶ እንደነበረ ተናግራለች።

እንዲህ ዓይነቶቹ መልእክቶችና ሕልሞች ጥሩና ጠቃሚ ይመስላሉ። ታዲያ ከአምላክ የመጡ ናቸው? አይደሉም። ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ነው። (መዝሙር 31:5) እኛን ለማታለል ወይም ለማሞኘት ፈጽሞ አይፈልግም። ይህን የሚያደርጉት አጋንንት ብቻ ናቸው።

ሰይጣን ሔዋን እንደማትሞት ተናገረ። ሔዋንም አመነችው፤ በመጨረሻ ግን ሞተች

ታዲያ ጥሩ አጋንንት አሉ ማለት ነው? አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ለመርዳት ዝግጁ የሆኑ ሊመስሉ ቢችሉም ሁሉም መጥፎዎች ናቸው። ዲያብሎስ ከሔዋን ጋር በተነጋገረበት ጊዜ ወዳጅ መስሎ ቀርቧል። (ዘፍጥረት 3:1) ይሁን እንጂ ሔዋን ሰይጣንን ሰምታ የነገራትን ባደረገች ጊዜ ምን ደረሰባት? ሞተች።

አንድ መጥፎ ሰው ሊያታልለው ወይም ሊያሞኘው ለሚፈልገው ሰው ወዳጅ መስሎ መቅረቡ የተለመደ መሆኑን ታውቃለህ። አንድ የአፍሪካ ምሳሌ “ጥርሰ ነጭ፣ ልበ ጥቁር” እንደሚለው ነው። የአምላክ ቃልም “ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ ለመምሰል ራሱን ይለዋውጣል” ይላል።—2 ቆሮንቶስ 11:14

አምላክ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ካሉ ሰዎች ጋር የሚገናኘው በሕልም፣ በራእይ ወይም ከመንፈሳዊው ዓለም ድምፅ እንዲሰሙ በማድረግ አይደለም። ሰዎችን የሚመራቸውና የሚያስተምራቸው አንድን ሰው “ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ [የታጠቀ]” እንዲሆን በሚያደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:17

በመሆኑም ይሖዋ ከዲያብሎስ ማታለያዎች እንድንርቅ የሚያስጠነቅቀን ስለሚወደን ነው። አጋንንት አደገኛ ጠላቶች መሆናቸውን ያውቃል።