በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰይጣንን ሳይሆን ይሖዋን አገልግል

ሰይጣንን ሳይሆን ይሖዋን አገልግል

ሁላችንም አንድ ምርጫ አለን። ይሖዋን አለዚያም ሰይጣንንና አጋንንቱን እናገለግላለን። ሁለቱንም ግን በአንድ ላይ ማገልገል አንችልም። ይሖዋን ማገልገል ምንኛ ጥበብ ነው!

ይሖዋ ጥሩ አምላክ ነው

ቀደም ብለን እንደተመለከትነው አጋንንት የሚደሰቱት ሰዎችን በማሠቃየትና በማታለል ነው። ይሖዋ ግን ከዚህ የተለየ ነው። የሰው ልጆችን ልክ አባት ልጆቹን እንደሚወድ ይወዳቸዋል። እሱ ‘የመልካም ስጦታ ሁሉና የፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ’ ሰጪ ነው። (ያዕቆብ 1:17) ማንኛውም መልካም ነገር፣ ከፍተኛ ኪሳራ የሚጠይቅበት እንኳ ቢሆን ለሰው ልጆች አይከለክልም።—ኤፌሶን 2:4-7

የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ሕመማቸውን በመፈወስ ለሰዎች ያለውን ፍቅር አሳይቷል

የአምላክ ልጅ ኢየሱስ በምድር ላይ ያደረጋቸውን ነገሮች እስቲ አስቧቸው። ዱዳዎች እንዲናገሩ አድርጓል፣ ለዓይነ ስውራንም ብርሃን ሰጥቷል። ሥጋ ደዌ የያዛቸውንና ሽባዎችን ፈውሷል። አጋንንትን አውጥቷል፣ ሁሉንም ዓይነት ሕመም ፈውሷል። ኢየሱስ በአምላክ ኃይል ሙታንን ሳይቀር አስነስቷል።—ማቴዎስ 9:32-35፤ 15:30, 31፤ ሉቃስ 7:11-15

አምላክ እኛን ለማሳሳት ሐሰትን በመናገር ፈንታ ሁልጊዜ እውነቱን ይነግረናል። እሱ ፈጽሞ ማንንም አያታልልም።—ዘኁልቁ 23:19

ርኩስ ተግባሮችን አስወግድ

የሸረሪት ድር ዝንብን ተብትቦ እንደሚይዛት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአጉል እምነትና በሐሰት ተተብትበዋል። ሙታንን ይፈራሉ። አጋንንትን ይፈራሉ። ስለ እርግማን፣ ስለ ገድ፣ ስለ ድግምትና የአስማት ኃይል አላቸው ተብለው ስለሚታመንባቸው ክታቦች፣ ብረታ ብረትና የመሳሰሉ ዕቃዎች ይጨነቃሉ። በሰይጣን ዲያብሎስ ውሸት ላይ በተመሠረቱ እምነቶችና ባሕሎች ታስረዋል። የአምላክ አገልጋዮች ግን ከእነዚህ ነገሮች በማንኛውም አልተጠመዱም።

ይሖዋ ከሰይጣን እጅግ በጣም የሚበልጥ ኃይል አለው። አንተም ይሖዋን የምታገለግል ከሆነ ከአጋንንት ይጠብቅሃል። (ያዕቆብ 4:7) ድግምት በአንተ ላይ ኃይል አይኖረውም። ለምሳሌ ያህል በናይጄሪያ ሦስት ኃይለኛ ጠንቋዮች ከከተማ ለቅቆ መሄድ እምቢ ያለ አንድ የይሖዋ ምሥክር ለመግደል ደገሙበት። ድግምቱ አልሠራ ሲል ከጠንቋዮቹ አንዱ ፈርቶ ወደ ምሥክሩ ዘንድ ሄዶ ይቅርታ ጠይቆታል።

የኤፌሶን ሰዎች የጥንቆላ መጽሐፎቻቸውን አቃጥለዋል

አጋንንት ካስቸገሩህ ይሖዋን በስሙ ልትጠራው ትችላለህ፣ እሱም ይጠብቅሃል። (ምሳሌ 18:10) ይሁን እንጂ የአምላክ ከለላ እንዲኖርህ ከተፈለገ ከመናፍስትነትና ከአጋንንት አምልኮ ጋር ግንኙነት ካለው ከማንኛውም ነገር ነፃ መሆን አለብህ። በጥንት ኤፌሶን የነበሩ አምላክን የሚያመልኩ ሰዎች እንዲሁ አድርገው ነበር። የጥንቆላ መጽሐፎቻቸውን ሁሉ ሰብስበው አቃጠሉ። (ሥራ 19:19, 20) በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮችም እንዲሁ ማድረግ አለባቸው። ከመተቶች፣ ከክፉ ነገር “ይጠብቃሉ” ከሚባሉ ክታቦች፣ የአስማት ኃይል እንዳላቸው ከሚታመንባቸው ከማናቸውም ዕቃዎች፣ ከጥንቆላ መጻሕፍትና ከመናፍስትነት ተግባር ጋር ግንኙነት ካለው ከማንኛውም ሌላ ነገር ሁሉ ራስህን ነፃ አድርግ።

እውነተኛው አምልኮ የሚፈልግብህን ፈጽም

አምላክን ለማስደሰት ከፈለግህ የሐሰት አምልኮ መተውና መጥፎ ነገሮች ከማድረግ መቆጠብ ብቻ በቂ አይሆንም። እውነተኛው አምልኮ የሚፈልግብህን በትጋት መፈጸም አለብህ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚፈለጉብንን ነገሮች እንደሚከተለው ይገልጻል፦

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ተካፈል።—ዕብራውያን 10:24, 25

መጽሐፍ ቅዱስን አጥና።—ዮሐንስ 17:3

ለሌሎች ስበክ።—ማቴዎስ 24:14

ወደ ይሖዋ ጸልይ።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ተጠመቅ።—የሐዋርያት ሥራ 2:41

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተቀራረብ

ሰይጣንና አጋንንቱ በምድር ላይ ስህተት የሆኑ ነገሮችን የሚያስተምሩና የሚያደርጉ ሕዝቦች አሏቸው። ይሖዋም የራሱ ሕዝብ አለው። እነሱም የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። (ኢሳይያስ 43:10) በምድር ዙሪያ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ምሥክሮች አሉ። ሁሉም ጥሩ ነገሮችን ለማድረግና ለሰዎችም እውነትን ለማስተማር ይጥራሉ። በአብዛኞቹ አገሮች በመንግሥት አዳራሾቻቸው ልታገኛቸው ትችላለህ። በዚያም በደስታ ይቀበሉሃል።

የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ሌሎች ሰዎች አምላክን እንዲያገለግሉ መርዳት ነው። ይሖዋን በትክክለኛው መንገድ እንዴት ማምለክ እንደሚቻል እንድታውቅ ለመርዳት በቤትህ መጽሐፍ ቅዱስ ሊያስጠኑህ ይችላሉ። ለዚህም የገንዘብ ክፍያ አትጠየቅም። ምሥክሮቹ ሰዎችንና ይሖዋ አምላክን ስለሚወዱ እውነትን ለማስተማር ደስተኞች ናቸው።

የይሖዋ ምሥክሮች አምላክን እንድታገለግል ይረዱሃል