በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ፈጽሞ ሊሆን አይችልም!”

“ፈጽሞ ሊሆን አይችልም!”

በኒው ዮርክ (ዩ ኤስ ኤ) የሚኖር አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ልጄ ጆናታን ከእኛ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀው የሚገኙ ጓደኞቹን ለመጠየቅ ሄዶ ነበር። ባለቤቴ ቫለንቲና ወደዚያ መሄዱ አያስደስታትም። የመንገዱ ሁኔታ ሁልጊዜ ያስፈራታል። ይሁን እንጂ ኤሌክትሮኒክስ ነገሮችን በጣም ስለሚወድ የሥራ ልምድ ለማግኘት ወደ ጓደኞቹ ሱቅ ሄደ። እኔ በምዕራብ ማንሃተን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ቤቴ ውስጥ ነበርኩ። ባለቤቴ ደግሞ ዘመዶቿን ለመጠየቅ ወደ ፖርቶ ሪኮ ሄዳለች። ‘የጆናታን መምጫ ደርሷል’ ብዬ እያሰብኩ ሳለ የበሩ ደወል ተደወለ። ‘እሱ መሆን አለበት’ አልኩ። የመጣው ግን ልጄ አልነበረም። በሩ ላይ የቆሙት፣ ፖሊሶችና በአደጋ ወቅት የሕክምና እርዳታ የሚሰጡ ባለሙያዎች ነበሩ። ፖሊሱ ‘ይህ መንጃ ፈቃድ የማን እንደሆነ ያውቃሉ?’ ሲል ጠየቀኝ። ‘አዎ፣ የልጄ የጆናታን መንጃ ፈቃድ ነው’ አልኩት። እሱም ‘የመጣነው አንድ አሳዛኝ ዜና ልንነግርዎት ነው። አደጋ ተከስቶ ነበር። . . . ልጅዎ . . . ልጅዎ በአደጋው ሕይወቱን አጥቷል’ አለኝ። መጀመሪያ ላይ፣ ‘ፈጽሞ ሊሆን አይችልም!’ ብዬ አሰብኩ። ዓመታት ካለፉ በኋላም እንኳ ይህ አስደንጋጭ ሁኔታ በልባችን ውስጥ የፈጠረው ቁስል ገና አልሻረም።”

‘የመጣነው አንድ አሳዛኝ ዜና ልንነግርዎት ነው። አደጋ ተከስቶ ነበር። . . . ልጅዎ . . . ልጅዎ በአደጋው ሕይወቱን አጥቷል።’

በባርሴሎና (ስፔን) የሚኖር አንድ አባት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በ1960ዎቹ ዓመታት ስፔን ውስጥ አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት ነበረን። ከባለቤቴ ከማሪያ ጋር ሦስት ልጆች አፍርተናል፤ ዴቪድ፣ ፓኪቶና ኢዛቤል የተባሉት ልጆቻችን 13, 11 እና 9 ዓመታቸው ነበር።

“በመጋቢት ወር 1963 አንድ ቀን ፓኪቶ ‘ራሴን በጣም አሞኛል’ ብሎ ከትምህርት ቤት መጣ። ‘ምን ሆኖ ይሆን?’ ብለን ግራ ተጋባን፤ ይሁን እንጂ በዚህ ሁኔታ ብዙም አልቆየንም። ከሦስት ሰዓት በኋላ ፓኪቶ ሞተ። በጭንቅላቱ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት ሕይወቱ በድንገት ተቀጨ።

“ፓኪቶ ከሞተ 30 ዓመት አልፎታል። የእሱ ሞት በውስጣችን የፈጠረው ቁስል ግን እስከ ዛሬ ድረስ ጨርሶ አልዳነም። ወላጆች ልጃቸውን በሞት ካጡ በኋላ ምንም ያህል ጊዜ ቢያልፍ ወይም ምንም ያህል ብዙ ልጆች ቢኖሯቸው፣ የአካላቸው ክፋይ የሆነ ነገር እንደተነጠላቸው ምንጊዜም ሲሰማቸው ይኖራል።”

እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ያጡባቸው ሁለት አሳዛኝ ገጠመኞች፣ አንድ ልጅ ሲሞት የሚፈጠረው ቁስል ምን ያህል ከባድና የማይሽር እንደሚሆን ያሳያሉ። አንድ ዶክተር የጻፏቸው የሚከተሉት ቃላት በእርግጥም ትክክል ናቸው፦ “አብዛኛውን ጊዜ የልጅ ሞት ከትልቅ ሰው ሞት ይበልጥ ያሳዝናል እንዲሁም በጣም ይጎዳል፤ ምክንያቱም ከቤተሰብ አባላት መካከል ይሞታሉ ተብለው የማይጠበቁት ልጆች ናቸው። . . . አንድ ልጅ ሲሞት ወላጆቹ ከወደፊት ሕይወቱ ጋር በተያያዘ የሚጓጉላቸው ነገሮች፣ ዝምድናዎች [ልጃቸው፣ ምራታቸው፣ የልጅ ልጆቻቸው] እንዲሁም ክንውኖች . . . ሁሉ ሕልም ሆነው ይቀራሉ።” ፅንስ የተጨናገፈባት ሴትም ብትሆን እንዲህ ያለ መሪር ሐዘን ሊያጋጥማት ይችላል።

ባሏ የሞተባት አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ ራስል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በፓስፊክ የጦር ግንባር የጤና ረዳት ሆኖ ሠርቷል። በጣም አሰቃቂ የሆኑ ጦርነቶችን አሳልፏል። ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመልሶ ከመጣ በኋላ ሰላማዊ ኑሮ መኖር ጀመረ። ከጊዜ በኋላም የይሖዋ ምሥክር ሆነ። በ60ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለ የልብ ችግር እንዳለበት የሚጠቁሙ ምልክቶች መታየት ጀመሩ። ሕይወቱ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተሞላ እንዲሆን ለማድረግ ይጥር ነበር። ሆኖም በሐምሌ ወር 1988 አንድ ቀን ልቡ በድንገት ቀጥ በማለቱ ሞተ። እሱን በሞት ማጣቴ እጅግ በጣም አሳዝኖኛል። ልሰናበተው እንኳ አልቻልኩም። ራስል፣ ባሌ ብቻ ሳይሆን በጣም የምወደው ጓደኛዬም ነበር። ለ40 ዓመታት አብረን ኖረናል። ከዚህ ቀደም አጋጥሞኝ የማያውቅ ዓይነት የብቸኝነት ሕይወት ከፊቴ ተጋረጠብኝ።”

በመላው ዓለም በሚኖሩ ቤተሰቦች ላይ በየቀኑ ከሚደርሱት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አሳዛኝ ሁኔታዎች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ሞት ልጃችሁን፣ የትዳር አጋራችሁን ወላጃችሁን ወይም ወዳጃችሁን ሲነጥቃችሁ በእርግጥም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “የመጨረሻው ጠላት” እንደሆነ ትገነዘባላችሁ፤ ሐዘን የደረሰባቸው አብዛኞቹ ሰዎች በዚህ ይስማማሉ። አብዛኛውን ጊዜ፣ የሚወዱት ሰው የሞተባቸው ሰዎች መጀመሪያ መርዶውን ሲሰሙ “ፈጽሞ ሊሆን አይችልም! በጭራሽ አላምንም” ይላሉ። ከዚያም፣ ቀጥለን እንደምንመለከተው ሌሎች ስሜቶች ይከተላሉ።—1 ቆሮንቶስ 15:25, 26

ሐዘን የሚያስከትለውን ስሜት ከመመልከታችን በፊት ግን አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ጥያቄዎችን መልስ እስቲ እንመርምር። አንድ ሰው ከሞተ፣ በቃ አከተመለት ማለት ነው? የምንወዳቸውን ሰዎች እንደገና የማየት ተስፋ ይኖረን ይሆን?

አስተማማኝ ተስፋ አለ

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “የመጨረሻው ጠላት” ከተባለው ከሞት መገላገል የምንችልበት ተስፋ እንዳለ ሲገልጽ “ሞት ይደመሰሳል” ሲል ጽፏል። “በመጨረሻ የሚደመሰሰው ጠላት ሞት ነው።” (1 ቆሮንቶስ 15:26 የ1980 ትርጉም) ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ይህን ያህል እርግጠኛ የሆነው ለምንድን ነው? ጳውሎስን ያስተማረው ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 9:3-19) ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ የጻፈውም ለዚህ ነው፦ “ሞት የመጣው በአንድ ሰው [በአዳም] በኩል ስለሆነ የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው [በኢየሱስ ክርስቶስ] በኩል ነው። ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉና።”—1 ቆሮንቶስ 15:21, 22

ኢየሱስ በናይን የምትኖርን አንዲት መበለት ባገኘና የሞተውን ልጇን በተመለከተ ጊዜ በጣም አዝኖ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ታሪኩን እንደሚከተለው በማለት ይነግረናል፦ “[ኢየሱስ] ወደ ከተማዋ [ናይን] መግቢያ ሲቃረብ ሰዎች የአንድ ሰው አስከሬን ተሸክመው በመውጣት ላይ ነበሩ፤ ሟቹ ለእናቱ አንድ ልጇ ነበር። በተጨማሪም እናቱ መበለት ነበረች። ብዙ የከተማዋ ሕዝብም ከእሷ ጋር ነበር። ጌታ ባያት ጊዜ በጣም አዘነላትና ‘በቃ፣ አታልቅሺ’ አላት። ከዚያም ቀረብ ብሎ ቃሬዛውን ነካ፤ የተሸከሙት ሰዎችም ባሉበት ቆሙ፤ ኢየሱስም ‘አንተ ወጣት፣ ተነስ እልሃለሁ!’ አለ። የሞተውም ሰው ቀና ብሎ ተቀመጠና መናገር ጀመረ፤ ኢየሱስም ለእናቱ ሰጣት። በዚህ ጊዜ ሁሉም በፍርሃት ተውጠው ‘ታላቅ ነቢይ በመካከላችን ተነስቷል፤’ እንዲሁም ‘አምላክ ሕዝቡን አሰበ’ እያሉ አምላክን ያወድሱ ጀመር።” ኢየሱስ ለመበለቲቱ በጣም ስላዘነላት ልጇን እንዳስነሳላት ልብ እንበል! ይህ ተአምር፣ ወደፊት ምን እንደሚከናወን ይጠቁመናል!—ሉቃስ 7:12-16

ኢየሱስ በዓይን ምሥክሮች ፊት፣ ሊረሳ የማይችል ትንሣኤ አከናውኗል። ይህ ተአምር፣ ኢየሱስ ትንሣኤ እንደሚኖር ከዚያ ትንሽ ቀደም ብሎ ለተናገረው ትንቢት እንደ ናሙና ነው፤ ‘በአዲስ ሰማይ’ በሚተዳደር ምድር ላይ ሙታን እንደገና በሕይወት ይኖራሉ። ኢየሱስ “በዚህ አትደነቁ፤ በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣልና፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ደግሞ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ” ብሏል።—ራእይ 21:1, 3, 4፤ ዮሐንስ 5:28, 29፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

ትንሣኤ ሲከናወን የዓይን ምሥክሮች ከሆኑት ሰዎች መካከል፣ ጴጥሮስ እንዲሁም ከኢየሱስ ጋር አብረው ይጓዙ ከነበሩት 12ት ሐዋርያት አንዳንዶቹ ይገኙበታል። እንዲያውም እነዚህ ሰዎች፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲናገር ሰምተውታል። ዘገባው እንደሚከተለው ይላል፦ “ኢየሱስ ‘ኑ፣ ቁርሳችሁን ብሉ’ አላቸው። ጌታ መሆኑን አውቀው ስለነበር ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ‘አንተ ማን ነህ?’ ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም። ኢየሱስም መጥቶ ዳቦውን አነሳና ሰጣቸው፤ ዓሣውንም አንስቶ እንዲሁ አደረገ። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነበር።”—ዮሐንስ 21:12-14

በዚህ ምክንያት ጴጥሮስ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይወደስ፤ እሱ በታላቅ ምሕረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት ለሕያው ተስፋ እንደ አዲስ ወልዶናልና” ብሎ በልበ ሙሉነት መጻፍ ችሏል።—1 ጴጥሮስ 1:3

ሐዋርያው ጳውሎስም በእርግጠኝነት የሚያምንበትን ተስፋ እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “በሕጉና በነቢያት የተጻፉትን ነገሮች ሁሉ ስለማምን . . . እነዚህ ሰዎች ራሳቸው ተስፋ እንደሚያደርጉት ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 24:14, 15

ከዚህ አንጻር፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በሞት የተለዩዋቸው ወዳጆቻቸውና ዘመዶቻቸው እንደገና ሕያው ሆነው ከአሁኑ በጣም የተለየ ሁኔታ በሚኖራት ምድር ላይ ሲኖሩ የመመልከት እርግጠኛ ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል። ምድር የሚኖራት ከአሁኑ የተለየ ሁኔታ ምንድን ነው? በሞት ያጣናቸው ወዳጆቻችንና ዘመዶቻችን ስላላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋ፣ በዚህ ብሮሹር የመጨረሻ ክፍል ላይ በሚገኘው “ሙታን ያላቸው አስተማማኝ ተስፋ” በሚለው ርዕስ ሥር ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጥበታል።

መጀመሪያ ግን፣ የምትወደው ሰው ሞቶብህ ሐዘን ላይ የምትገኝ ከሆነ ሊፈጠሩብህ የሚችሉትን አንዳንድ ጥያቄዎች እንመልከት፦ ይህን ያህል ማዘኔ የጤና ነው? ከሐዘኔ ልጽናና የምችለው እንዴት ነው? ሌሎች ሐዘኔን እንድቋቋም ሊረዱኝ የሚችሉት እንዴት ነው? እኔስ ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች እንዴት ልረዳ እችላለሁ? ከሁሉ በላይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስላላቸው አስተማማኝ ተስፋ ምን ይላል? በሞት የተለዩኝን የምወዳቸው ሰዎች ዳግመኛ ማየት እችላለሁ? የማገኛቸውስ የት ነው?