በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ ስድስት

በጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ልጆቻችሁ በጥሩ ሁኔታ እንዲያድጉ እርዷቸው

በጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ልጆቻችሁ በጥሩ ሁኔታ እንዲያድጉ እርዷቸው

1, 2. አፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚያስገኘው ደስታና የሚያስከትላቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ከአምስት ዓመትም ሆነ ከአሥር ዓመት ልጅ በጣም የተለየ ነው። አፍላ የጉርምስና ዕድሜ የራሱ የሆኑ ፈታኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩትም ደስታና በረከትም ሊያስገኝ ይችላል። እንደ ዮሴፍ፣ ዳዊት፣ ኢዮስያስና ጢሞቴዎስ የመሳሰሉትን ጥሩ ምሳሌዎች ስንመለከት ወጣቶች እምነት የሚጣልባቸው ሆነው መገኘትና ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት እንደሚችሉ እንገነዘባለን። (ዘፍጥረት 37:​2-11፤ 1 ሳሙኤል 16:​11-13፤ 2 ነገሥት 22:​3-7፤ ሥራ 16:​1, 2) በዛሬው ጊዜም ይህን የሚያረጋግጡ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙ ወጣቶች አሉ። እናንተም ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን ሳታውቋቸው አትቀሩም።

2 ይሁን እንጂ አፍላ የጉርምስና ዕድሜ ለአንዳንዶቹ በጣም አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ስሜታቸው በጣም ይለዋወጣል። በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ከበፊቱ የበለጠ ነፃነት ማግኘት ሊፈልጉና ወላጆቻቸው ያስቀመጡላቸው ገደብ ሊያስከፋቸው ይችላል። ሆኖም እነዚህ ወጣቶች በዚህ ዕድሜያቸውም ቢሆን ገና ተሞክሮ ስለሚጎድላቸው ወላጆቻቸው በትዕግሥት ፍቅራዊ እርዳታ ሊያደርጉላቸው ይገባል። አዎ፣ አፍላ የጉርምስና ዕድሜ ለወላጆችም ሆነ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ልጆች አስደሳች ብቻ ሳይሆን ግራ የሚያጋባም ሊሆን ይችላል። በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

3. ወላጆች በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ልጆቻቸው ግሩም አጋጣሚ ሊፈጥሩላቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

3 የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር የሚከተሉ ወላጆች በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸው የሚያጋጥሟቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች በተሳካ ሁኔታ አልፈው እምነት የሚጣልባቸው ዐዋቂዎች መሆን ወደሚችሉበት ደረጃ እንዲደርሱ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ይረዷቸዋል። በየትኛውም ዘመን ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጋራ ሥራ ላይ ያዋሉ በየትኛውም አገር የሚኖሩ ወላጆችና ወጣቶች ጥረታቸው ተሳክቶላቸዋል።​—⁠መዝሙር 119:​1

ምንም ሳይደባበቁ ግልጽ በሆነ መንገድ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ

4. ልጆች በተለይ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው ምሥጢራቸውን ለወላጆቻቸው ማካፈላቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ “ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል” ይላል። (ምሳሌ 15:​22) ልጆቹ ትንንሾች በነበሩበት ጊዜ ወላጆቻቸውን በግል ማማከር ያስፈልጋቸው ከነበረ ከቤት ውጪ በትምህርት ቤትም ሆነ በሌላ ቦታ ከሚያገኟቸው ጓደኞቻቸው ጋር የበለጠ ጊዜ በሚያሳልፉበት በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው ምሥጢራቸውን በማካፈል ወላጆቻቸውን ማማከራቸው ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ልጆች ምንም ሳይደብቁ ምሥጢራቸውን ማካፈል የሚችሉበት ግልጽ የሆነ የሐሳብ ልውውጥ በወላጆችና በልጆች መካከል ከሌለ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ጋር በጣም እየተራራቁ ሊሄዱ ይችላሉ። ስለዚህ ይህ እንዳይሆን ክፍት የሆነ የሐሳብ ግንኙነት መስመር መዘርጋት የሚቻለው እንዴት ነው?

5. በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

5 በዚህ ረገድ ልጆችም ሆኑ ወላጆች የየበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል። እርግጥ ነው፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች በልጅነታቸው ጊዜ ያደርጉት እንደነበረው ከወላጆቻቸው ጋር እንደ ልብ መወያየት ሊከብዳቸው ይችላል። ሆኖም ‘መልካም ምክር ከሌለ ሕዝብ እንደሚወድቅና በመካሮች ብዛት ግን ደህንነት እንደሚገኝ’ መዘንጋት የለባቸውም። (ምሳሌ 11:​14) እነዚህ ቃላት ለወጣቶችም ሆነ ለትልልቅ ሰዎች ይሠራሉ። ይህን የሚገነዘቡ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ከቀድሞው ይበልጥ ውስብስብ የሆኑ ነገሮች የሚያጋጥሟቸው በመሆኑ በዚህ ዕድሜያቸውም ቢሆን ጥሩ አመራር እንደሚያስፈልጋቸው ያውቃሉ። አማኝ የሆኑ ወላጆቻቸው ከእነሱ የበለጠ የሕይወት ተሞክሮ ያላቸው ከመሆኑም በላይ ለእነሱ ያላቸውን ፍቅራዊ አሳቢነት ለብዙ ዓመታት ያሳዩ በመሆኑ ጥሩ ብቃት ያላቸው መካሪዎች መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ስለዚህ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አስተዋይ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ምክርና እርዳታ ይጠይቃሉ።

6. አስተዋይና አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆቻቸው ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግን በተመለከተ ምን አመለካከት ይኖራቸዋል?

6 ክፍት የሆነ የሐሳብ ግንኙነት መስመር እንዲኖር ማድረግ ማለት አንድ ወላጅ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጁ ሊያናግረው በሚፈልግበት ጊዜ ሁሉ ፈቃደኛ ይሆናል ማለት ነው። ወላጆች ከሆናችሁ ምንጊዜም ከልጃችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ፈቃደኞች ሁኑ። እንዲህ ማድረጉ ቀላል ላይሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፣ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:​7) በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ መናገር በሚፈልግበት ጊዜ እናንተ ደግሞ ዝም ማለት ትፈልጉ ይሆናል። ምናልባትም ያን ጊዜ ለግል ጥናት፣ ለመዝናናት ወይም ደግሞ ቤት ውስጥ የሚሠሩ አንዳንድ ነገሮችን ለመሥራት መድባችሁት ይሆናል። ያም ሆኖ ግን ልጃችሁ ሊያነጋግራችሁ ከፈለገ ልታደርጉ ያሰባችሁትን ነገር ትታችሁ ልጃችሁን ለማዳመጥ ጥረት አድርጉ። አለዚያ ግን ዳግመኛ እናንተን ለማነጋገር ላይሞክር ይችላል። የኢየሱስን ምሳሌ አስታውሱ። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ለማረፍ ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ሊሰሙት በዙሪያው በተሰበሰቡ ጊዜ ለማረፍ የነበረውን ሐሳብ ትቶ ያስተምራቸው ጀመር። (ማርቆስ 6:​30-34) በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ልጆች ወላጆቻቸው ሥራ እንደሚበዛባቸው ያውቃሉ፤ ሆኖም ሲፈልጉ ወላጆቻቸውን ማነጋገር እንደሚችሉ ትምክህት እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ስለዚህ ልጆቻችሁን ለማነጋገር ምን ጊዜም ፈቃደኞች ሁኑ፤ ችግራቸውንም ተረዱላቸው።

7. ወላጆች ማስወገድ ያለባቸው ነገር ምንድን ነው?

7 እናንተ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ የነበረውን ሁኔታ ለማስታወስ በመሞከር ተጫዋች መሆን ይኖርባችኋል። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጊዜ በማሳለፍ የሚደሰቱ መሆን አለባቸው። ወላጆች ትርፍ ጊዜ ሲኖራቸው ይህን ጊዜ የሚያሳልፉት እንዴት ነው? ሁልጊዜ በትርፍ ጊዜያቸው ቤተሰባቸውን የማያካትቱ ነገሮች ለማድረግ የሚፈልጉ ከሆነ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻቸው ይህን ለማስተዋል ጊዜ አይወስድባቸውም። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ከወላጆቻቸው ይልቅ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ከፍ ያለ ቦታ እንደሚሰጧቸው አድርገው ማሰብ ከጀመሩ ችግር ውስጥ መው​ደቃቸው አይቀርም።

ከልጆቻችሁ ጋር ልትነጋገሩበት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

8. ልጆች ሐቀኝነት፣ ታታሪነትና ተገቢ የሆነ ሥነ ምግባር የማሳየትን አስፈላጊነት ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

8 ወላጆች ሐቀኛ መሆንና ጠንክሮ መሥራት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ቀደም ሲል በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጽ አላደረጉ ከሆነ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው ይህን ሥልጠና የግድ መስጠት አለባቸው። (1 ተሰሎንቄ 4:​11፤ 2 ተሰሎንቄ 3:​10) በተጨማሪም ልጆቻቸው ንጹሕና ሥርዓታማ ኑሮ የመኖርን አስፈላጊነት ከልባቸው እንዲያምኑበት ማድረግ ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 20:​11) አንድ ወላጅ በአብዛኛው ይህን ማድረግ የሚችለው ጥሩ ምሳሌ በመሆን ነው። የማያምኑ ባሎች ‘አለቃል በሚስቶቻቸው አኗኗር ሊለወጡ’ እንደሚችሉ ሁሉ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆችም በወላጆቻቸው አኗኗር ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሊማሩ ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 3:​1) እርግጥ ልጆች ከቤት ውጪ ለብዙ መጥፎ ምሳሌዎችና በስፋት ለሚነዛው አታላይ የሆነ ፕሮፓጋንዳ የተጋለጡ በመሆናቸው የወላጆቻቸው ምሳሌ መሆን ብቻውን በቂ አይደለም። ስለዚህ አሳቢ የሆኑ ወላጆች ወጣት ልጆቻቸው ስለሚያዩትና ስለሚሰሙት ነገር ያላቸውን አመለካከት ማወቅ አለባቸው፤ ይህ ደግሞ ጥሩ ውይይት ማድረግ ይጠይቃል።​—⁠ምሳሌ 20:​5

9, 10. ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ጾታ ማስተማር ያለባቸው ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የሚችሉትስ እንዴት ነው?

9 በተለይ ከጾታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ ይህን ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው። ወላጆች፣ ከልጆቻችሁ ጋር ስለ ጾታ ማውራት ያሳፍራችኋልን? ልጆቻችሁ እናንተ ባትነግሯቸው ከሌላ መስማታቸው ስለማይቀር የምታፍሩ ቢሆን እንኳ በጉዳዩ ላይ ከልጆቻችሁ ጋር ውይይት ለማድረግ መጣር አለባችሁ። እናንተ የማትነግሯቸው ከሆነ ከሌላ ምንጭ ምን ዓይነት የተዛባ መረጃ ሊያገኙ እንደሚችሉ ማን ያውቃል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ከጾታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለመደበቅ አልሞከረም፤ ወላጆችም መደበቅ የለባቸውም።​—⁠ምሳሌ 4:​1-4፤ 5:​1-21

10 መጽሐፍ ቅዱስ ጾታን በተመለከተ ሊኖረን የሚገባውን አቋም የሚጠቁም ግልጽ መመሪያ ያለው መሆኑ የሚያስደስት ነው፤ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርም መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው መመሪያ በዘመናዊው ዓለም ውስጥም እንደሚሠራ የሚያሳዩ ብዙ ጠቃሚ ጽሑፎች አውጥቷል። እነዚህን ጽሑፎች ለምን አትጠቀሙባቸውም? ለምሳሌ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች ከተባለው መጽሐፍ ጥራዝ 1 እና 2 ላይ ከጾታ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ምዕራፎች መርጣችሁ ከሴትም ሆነ ከወንድ ልጃችሁ ጋር ለምን አታጠኑም? በውጤቱ ትደሰታላችሁ።

11. ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው ማስተማር የሚችሉበት ከሁሉ ይበልጥ ውጤታማ የሆነ መንገድ ምንድን ነው?

11 ወላጆችና ልጆች ሊወያዩበት የሚገባው ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ርዕሰ ጉዳይ ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው” ብሎ በጻፈ ጊዜ ይህ ርዕሰ ጉዳይ ምን እንደሆነ ጠቁሟል። (ኤፌሶን 6:​4) ልጆች ዘወትር ስለ ይሖዋ መማር አለባቸው። በተለይ ደግሞ ይሖዋን እንዲወዱትና እሱን የማገልገል ፍላጎት እንዲያድርባቸው ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህም ረገድ ጥሩ ምሳሌ በመሆን ልጆችን ብዙ ማስተማር ይቻላል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ወላጆቻቸው አምላክን ‘በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹም ነፍሳቸውና በፍጹም አሳባቸው’ እንደሚወዱትና ይህም በወላጆቻቸው ሕይወት ውስጥ መልካም ፍሬዎችን እንዳፈራ ከተገነዘቡ እነሱም እንዲሁ ለማድረግ ሊገፋፉ ይችላሉ። (ማቴዎስ 22:​37) በተመሳሳይም ወላጆቻቸው ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት በመያዝ የአምላክን መንግሥት እንደሚያስቀድሙ ከተመለከቱ እነርሱም እንደዚሁ ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ይነሳሳሉ።​—⁠መክብብ 7:​12፤ ማቴዎስ 6:​31-33

ቋሚ የሆነ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በጣም አስፈላጊ ነው

12, 13. የቤተሰብ ጥናቱ የተሳካ እንዲሆን ከተፈለገ የትኞቹን ነጥቦች ማስታወስ ይገባል?

12 ሳምንታዊ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መንፈሳዊ እሴቶችን ለወጣቶች ለማስተላለፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። (መዝሙር 119:​33, 34፤ ምሳሌ 4:​20-23) ይህን የመሰለ ቋሚ ጥናት መኖሩ በጣም አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 1:​1-3) ወላጆችም ሆኑ ልጆቻቸው ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለሌሎች ፕሮግራሞች ሳይሆን ለቤተሰብ ጥናት መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም የቤተሰብ ጥናቱ ውጤታማ እንዲሆን ትክክለኛ አመለካከት መያዝ ያስፈልጋል። አንድ አባት እንዲህ ብሏል:- “ቁልፉ መሪው በቤተሰብ ጥናቱ ወቅት ዘና ያለ፣ ሆኖም አክብሮት የተሞላበት መንፈስ እንዲኖር ማድረጉ ነው። አመራሩ በጣምም ጥብቅ፣ በጣምም ልል መሆን የለበትም። ሁልጊዜ ትክክለኛውን ሚዛን መጠበቅ ቀላል ላይሆን ይችላል፤ በተጨማሪም ወጣቶች በየጊዜው በአመለካከታቸው ላይ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። አንዴ ወይም ሁለቴ ሞክራችሁ ሁኔታው የተፈለገውን ያህል ባይሳካ ተስፋ ሳትቆርጡ በሚቀጥለው ጊዜ ለማስተካከል ጥረት አድርጉ።” ይኸው አባት ሁልጊዜ ጥናታቸውን ከመጀመራቸው በፊት፣ በጥናቱ ላይ የሚገኙት ሁሉ ትክክለኛ አመለካከት ይኖራቸው ዘንድ ይሖዋ እንዲረዳቸው በቀጥታ ጉዳዩን ጠቅሶ እንደሚጸልይ ተናግሯል።​—⁠መዝሙር 119:​66

13 አማኝ የሆኑ ወላጆች የቤተሰብ ጥናት የመምራት ኃላፊነት አለባቸው። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ወላጆች የማስተማር ተሰጥኦ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፤ በመሆኑም የቤተሰብ ጥናቱን አስደሳች ማድረግ የሚችሉበት መንገድ ይጠፋቸው ይሆናል። ሆኖም በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙትን ልጆቻችሁን “በሥራና በእውነት” የምትወዷቸው እስከሆነ ድረስ በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ በትሕትናና በሐቀኝነት መንፈስ ልትረዷቸው እንደምትፈልጉ የታወቀ ነው። (1 ዮሐንስ 3:​18) አልፎ አልፎ በአንዳንድ ነገሮች ያማርሩ ይሆናል፤ ቢሆንም ለእነርሱ ደህንነት ከልባችሁ እንደምታስቡ መረዳታቸው አይቀርም።

14. በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ለሚገኙ ልጆች መንፈሳዊ ነገሮችን በማስተላለፍ ረገድ ዘዳግም 11:​18, 19ን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

14 በመንፈሳዊ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለልጆቻችሁ ማስተላለፍ የምትችሉት በቤተሰብ ጥናት ወቅት ብቻ አይደለም። ይሖዋ ለወላጆች የሰጠውን ትእዛዝ ታስታውሳላችሁ? የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር:- “እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፤ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው፣ በዓይኖቻችሁም መካከል እንደ ክታብ ይሁኑ። ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም ስትነሣም አጫውቱአቸው።” (ዘዳግም 11:​18, 19፤ በተጨማሪም ዘዳግም 6:​6, 7ን ተመልከቱ።) ይህ ማለት ወላጆች ሁልጊዜ ለልጆቻቸው መስበክ አለባቸው ማለት አይደለም። ሆኖም አፍቃሪ የሆነ የቤተሰብ ራስ የቤተሰቡን መንፈሳዊ አመለካከት መገንባት የሚችልባቸውን አጋጣሚዎች ሁልጊዜ በንቃት መከታተል አለበት።

ተግሣጽና አክብሮት

15, 16. (ሀ) ተግሣጽ ምንድን ነው? (ለ) ተግሣጽ የመስጠት ኃላፊነት ያለው ማን ነው? ተግሣጹን የመከተል ኃላፊነት ያለበትስ ማን ነው?

15 ተግሣጽ እርማት የሚሰጥበት ማሠልጠኛ ነው፤ ይህ ደግሞ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግን ያጠቃልላል። ምንም እንኳ ቅጣት አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ሊኖር ቢችልም ተግሣጽ የሚለው ቃል ከቅጣት ይበልጥ እርማት መስጠትን የሚያመለክት ነው። ልጆቻችሁ ትንንሽ በነበሩበት ጊዜ ተግሣጽ ያስፈልጋቸው ነበር፤ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸውም ወቅት ቢሆን በሆነ መልኩ ምናልባትም ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ ተግሣጽ ያስፈልጋቸዋል። በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አስተዋይ የሆኑ ልጆች ይህ አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባሉ።

16 መጽሐፍ ቅዱስ “ሰነፍ የአባቱን ተግሣጽ ይንቃል፤ ዘለፋን የሚቀበል ግን አእምሮው የበዛ ነው” ይላል። (ምሳሌ 15:​5) ከዚህ ጥቅስ ብዙ እንማራለን። ጥቅሱ ተግሣጽ የሚሰጥ መሆኑን ያመለክታል። አንድ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ‘ተግሣጽን ሊቀበል’ የሚችለው ተግሣጽ ከተሰጠው ነው። ይሖዋ ተግሣጽ የመስጠትን ኃላፊነት ለወላጆች፣ በተለይ ደግሞ ለአባት ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ተግሣጹን የመስማት ኃላፊነት ያለበት ልጁ ነው። የአባቱንና የእናቱን ጥበብ የተሞላበት ተግሣጽ የሚከተል ከሆነ ብዙ ትምህርት የሚያገኝ ከመሆኑም በላይ እምብዛም ስህተት አይሠራም። (ምሳሌ 1:​8) መጽሐፍ ቅዱስ “ድህነትና ነውር ተግሣጽን ቸል ለሚሉ ነው፤ ዘለፋን የሚሰማ ግን ይከብራል” ይላል።​—⁠ምሳሌ 13:​18

17. ወላጆች ተግሣጽ በሚሰጡበት ጊዜ ምን ዓይነት ሚዛን ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ አለባቸው?

17 ወላጆች በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸውን በሚገስጹበት ጊዜ ሚዛናዊ መሆን አለባቸው። ልጆቻቸው እንዳይበሳጩ አልፎ ተርፎም በራስ የመተማመን መንፈሳቸውን እንዳያጡ ወላጆች በጣም ጥብቅ ከመሆን መቆጠብ ይኖርባቸዋል። (ቆላስይስ 3:​21) ሆኖም ወላጆች በጣም ልል በመሆን ልጆቻቸው ሊሰጣቸው የሚገባውን ማሠልጠኛ ሳያገኙ እንዲቀሩ ማድረግ የለባቸውም። በጣም ልል መሆን አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትል ይችላል። ምሳሌ 29:​17 “ልጅህን ቅጣ ዕረፍትንም ይሰጥሃል፤ ለነፍስህም ተድላን ይሰጣታል” ይላል። ሆኖም ቁጥር 21 ላይ “ባሪያውን ከሕፃንነቱ ጀምሮ በማቀማጠል የሚያሳድግ የኋላ ኋላ እንደ ጌታ ያደርገዋል” ይላል። ይህ ጥቅስ ስለ አገልጋይ የሚናገር ቢሆንም እንኳ በቤተሰብ ውስጥ ላለ ለየትኛውም ወጣት በእኩል ደረጃ ይሠራል።

18. ተግሣጽ የምን መግለጫ ነው? ወላጆች የማይለዋወጥ ተግሣጽ መስጠታቸው የትኛውን ችግር ለማስወገድ ይረዳቸዋል?

18 እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ተገቢ የሆነ ተግሣጽ ወላጆች ለልጃቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ ነው። (ዕብራውያን 12:​6, 11) ወላጆች ከሆናችሁ፣ ዘወትር ተለዋዋጭ ያልሆነ ምክንያታዊ ተግሣጽ መስጠት ከባድ መሆኑን እንደምታውቁ ግልጽ ነው። ግትር ከሆነ ልጅ ጋር ላለመጋጨት ሲባል የፈለገውን ነገር እንዲያደርግ መፍቀዱ ቀላል መስሎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ የሚያደርግ ወላጅ ውሎ አድሮ ቤተሰቡ ከቁጥጥር ውጪ ይሆንበታል።​—⁠ምሳሌ 29:​15፤ ገላትያ 6:​9

ሥራና ጨዋታ

19, 20. ወላጆች በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ልጆቻቸው መዝናኛ መምረጥን በተመለከተ ጥበብ የተሞላበት እርምጃ መውሰድ የሚችሉት እንዴት ነው?

19 ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዙውን ጊዜ ልጆች ቤት ውስጥ በማገልገል ወይም ደግሞ እርሻ ላይ ተሠማርተው በመሥራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ይጠበቅባቸው ነበር። ዛሬ ግን በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙዎቹ ልጆች ከወላጆቻቸው ቁጥጥር ውጪ ሆነው የሚያሳልፉት ብዙ ትርፍ ጊዜ አላቸው። የንግዱ ዓለም ይህን ጊዜያቸውን የሚሻሙ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ነገሮች ያቀርባል። በዚህ ላይ ደግሞ ዓለም ለመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምንም ዓይነት አክብሮት የለውም፤ እነዚህ ሁሉ ነገሮች አንድ ላይ ተዳምረው አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትሉ ይችላሉ።

20 ስለዚህ አስተዋይ የሆነ ወላጅ መዝናኛን በተመለከተ ሁኔታዎችን አመዛዝኖ ውሳኔ የመስጠት መብቱን ይጠቀማል። ሆኖም በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ እያደገ መሆኑን አትዘንጉ። ዓመት አልፎ ዓመት በተተካ ቁጥር ሁልጊዜ እንደ ልጅ እንዲታይ አይፈልግም። ስለዚህ አንድ ወላጅ መዝናኛን በተመለከተ የልጁ ምርጫ ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና እያደገ መሆኑን የሚያሳይ እስከሆነ ድረስ ልጁ እያደገ ሲሄድ ከበፊቱ የበለጠ መዝናኛን የመምረጥ ነፃነት መስጠቱ ጥበብ ነው። ልጁ አንዳንድ ጊዜ ሙዚቃን፣ ጓደኞችንና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮችን በተመለከተ የተሳሳተ ምርጫ ሊያደርግ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ወደፊት የተሻሉ ምርጫዎች ማድረግ እንዲችል ከልጁ ጋር መወያየት ያስፈልጋል።

21. በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ በመዝናኛ የሚያሳልፈውን ጊዜ በተመለከተ ምክንያታዊ መሆኑ ከአደጋ የሚጠብቀው እንዴት ነው?

21 ለመዝናኛ መዋል ያለበት ጊዜ ምን ያህል ነው? በአንዳንድ አገሮች ያሉት ሁኔታዎች በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ሁልጊዜ መዝናናት እንደሚችሉ አድርገው እንዲያስቡ ተጽዕኖ አሳድረውባቸዋል። በመሆኑም አንድ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ጊዜው ሁሉ በመዝናኛ እንዲያዝ ሊያደርግ ይችላል። ልጁ ጊዜውን ከቤተሰቡ ጋር ለመጫወት፣ ለግል ጥናት፣ በመንፈሳዊ ከጎለመሱ ሰዎች ጋር ለመቀራረብ፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ በቤት ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችን ለመሥራትና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ጉዳዮችንም ለማከናወን ሊጠቀምበት እንደሚገባ ማስተማር የወላጆች ኃላፊነት ነው። ይህን ማድረጉ ‘የአሁኑ ሕይወት ተድላ’ የአምላክን ቃል እንዳያንቅበት ይረዳዋል።​—⁠ሉቃስ 8:​11-15

22. በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ በሕይወቱ ውስጥ ለመዝናኛ የሚሰጠው ቦታ ከምን ነገር ጋር ሚዛኑን መጠበቅ ይኖርበታል?

22 ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ብሏል:- “ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።” (መክብብ 3:​12, 13) አዎ፣ ደስታ የሚዛናዊ ኑሮ አንዱ ክፍል ነው። ሆኖም ትጋት የተሞላበት ሥራም የሕይወታችን ክፍል መሆኑን መዘንጋት የለብንም። በአሁኑ ጊዜ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙ ልጆች ትጋት የተሞላበት ሥራ የሚሰጠውን ደስታ ወይም ደግሞ አንድን ችግር ተጋፍጦ ለችግሩ እልባት ማግኘት የሚፈጥረውን በራስ የመተማመን መንፈስ ጨርሶ አያውቁትም። አንዳንዶቹ በቀሪው ሕይወታቸው ራሳቸውን መርዳት የሚችሉበት ሙያ ወይም ችሎታ የሚያዳብሩበት አጋጣሚ አላገኙም። በወላጆች ፊት የሚደቀነው ትልቁ ፈታኝ ሁኔታ ይሄ ነው። ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች እንዲያገኝ ትረዱታላችሁን? ሥራን ከፍ አድርጎ እንዲመለከትና ከዚያም አልፎ የሥራ ፍቅር እንዲያድርበት ማድረግ ከቻላችሁ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በርካታ ጥቅም ሊያስገኝለት የሚችል ጤናማ አመለካከት ይኖረዋል።

ከአፍላ ጉርምስና ወደ ጉልምስና መሸጋገር

ለልጆቻችሁ ያላችሁን ፍቅርና አድናቆት ግለጹላቸው

23. ወላጆች በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸውን ማበረታታት የሚችሉት እንዴት ነው?

23 በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኘው ልጃችሁ ጋር አለመግባባት በሚፈጠርበትም ጊዜ እንኳ “ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም” የሚለው ጥቅስ ይሠራል። (1 ቆሮንቶስ 13:​8) ለልጆቻችሁ ያላችሁን ፍቅር ምንጊዜም ከመግለጽ አትታቀቡ። እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ:- ‘እያንዳንዱ ልጅ ላጋጠሙት ችግሮች እልባት ማግኘት በመቻሉ ወይም ደግሞ የተደነቀሩበትን እንቅፋቶች መወጣት በመቻሉ አድናቆቴን እገልጽለታለሁን? ለልጆቼ ያለኝን ፍቅርና አድናቆት መግለጽ የምችልባቸው አጋጣሚዎች ሳገኝ ወዲያው እጠቀምባቸዋለሁን?’ ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ አለመግባባት ሊፈጠር ቢችልም በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙት ልጆቻችሁ እንደምትወዷቸው ከተገነዘቡ እነርሱም በአጸፋው ለእናንተ ያላቸውን ፍቅር መግለጻቸው አይቀርም።

24. ልጆችን በማሳደግ ረገድ አጠቃላይ ደንብ ሆኖ የሚሠራው የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓት ነው? ሆኖም ምን ነገር ማስታወስ ይገባል?

24 እርግጥ ነው፣ ልጆች ወደ ጉልምስና እያደጉ ሲሄዱ አንዳንድ በጣም ከባድ የሆኑ ውሳኔዎች እንደሚወስኑ የታወቀ ነው። አንዳንድ ጊዜ ወላጆች በልጆቻቸው ውሳኔዎች ላይደሰቱ ይችላሉ። ልጃቸው ይሖዋ አምላክን ማገልገሉን ለማቆም ቢወስንስ? ይህ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው። አንዳንድ የይሖዋ መንፈሳዊ ልጆች እንኳ ሳይቀሩ የእሱን ምክር ለመስማት አሻፈረኝ በማለት ዓመፀኞች ሆነዋል። (ዘፍጥረት 6:​2፤ ይሁዳ 6) ልጆች እኛ በፈለግነው መንገድ ልናዛቸው የምንችል ኮምፒዩተሮች አይደሉም። ነፃ ምርጫ ያላቸውና ለሚወስዷቸው ውሳኔዎች በይሖዋ ፊት ተጠያቂ የሆኑ ፍጥረታት ናቸው። ያም ሆኖ ግን በምሳሌ 22:​6 ላይ ሠፍሮ የሚገኘው የሚከተለው ሐሳብ አጠቃላይ ደንብ ሆኖ ይሠራል:- “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም።”

25. ወላጆች ይሖዋ ለሰጣቸው የወላጅነት መብት አመስጋኝነታቸውን መግለጽ የሚችሉበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ምንድን ነው?

25 እንግዲያው ልጆቻችሁን በጣም እንደምትወዷቸው በተግባር አሳዩአቸው። ልጆቻችሁን በምታሳድጉበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመከተል የቻላችሁትን ሁሉ ጥረት አድርጉ። በአምላካዊ አኗኗር ረገድ ጥሩ ምሳሌ ሁኑላቸው። በዚህም መንገድ ልጆቻችሁ እምነት የሚጣልባቸውና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ሆነው እንዲያድጉ የሚረዳ ከሁሉ የተሻለ አጋጣሚ ትፈጥሩላቸዋላችሁ። ይህ ደግሞ ወላጆች ይሖዋ ለሰጣቸው የወላጅነት መብት ያላቸውን አመስጋኝነት የሚገልጹበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው።