በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥር

የቤተሰብ አባል ሲታመም

የቤተሰብ አባል ሲታመም

1, 2. ሰይጣን የኢዮብን የጸና አቋም ለማስለወጥ አሳዛኝ ክስተቶችንና በሽታን መሣሪያ አድርጎ የተጠቀመው እንዴት ነው?

ኢዮብ አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት ከነበራቸው ሰዎች አንዱ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ “በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ” ይላል። ሰባት ወንዶች ልጆችና ሦስት ሴቶች ልጆች፣ በድምሩ አሥር ልጆች ነበሩት። ቤተሰቡን በሚገባ ማስተዳደር የሚችልበት ጥሩ ገቢ ነበረው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ቤተሰቡን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በግንባር ቀደምትነት ይመራ የነበረ ከመሆኑም በላይ ልጆቹ በይሖዋ ፊት ስላላቸው አቋም በጣም ያስብ ነበር። ይህ ሁሉ ቤተሰቡ በጠበቀና አስደሳች በሆነ ዝምድና እርስ በርሱ እንዲተሳሰር አድርጎታል።​—⁠ኢዮብ 1:​1-5

2 ኢዮብ የነበረው አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት የይሖዋ አምላክ ቀንደኛ ጠላት ከሆነው ከሰይጣን እይታ አላመለጠም ነበር። የአምላክን አገልጋዮች የጸና አቋም ለማስለወጥ ዘወትር ጉድጓድ የሚቆፍረው ሰይጣን ደስተኛ ቤተሰቡን በማጥፋት በኢዮብ ላይ ጥቃት ሰነዘረ። “ኢዮብንም ከእግሩ ጫማ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቁስል መታው።” በዚህ መንገድ ሰይጣን የኢዮብን የጸና አቋም ለማስለወጥ አሳዛኝ ክስተቶችንና በሽታን መሣሪያ አድርጎ ተጠቀመ።​—⁠ኢዮብ 2:​6, 7

3. ኢዮብ በሽታው እንዴት አድርጎት ነበር?

3 መጽሐፍ ቅዱስ ኢዮብ ይዞት የነበረውን በሽታ ስም አይጠቅስም። በሽታው እንዴት አድርጎት እንደነበረ ግን ይነግረናል። ቁስሉ ተልቶ ነበር፤ ቆዳውም እያፈከፈከ ይነሳና ይመግል ነበር። ትንፋሹ መጥፎ ጠረን ነበረው፤ ሰውነቱም በጣም ይሸት ነበር። በሽታው እጅግ አሠቃይቶታል። (ኢዮብ 7:​5፤ 19:​17፤ 30:​17, 30) ኢዮብ ሥቃዩ ስለበዛበት በአመድ መካከል ተቀምጦ በገል ሰውነቱን ይፍቅ ነበር። (ኢዮብ 2:​8) በእርግጥም በጣም ያሳዝን ነበር!

4. እያንዳንዱ ቤተሰብ አልፎ አልፎ ምን ያጋጥመዋል?

4 በእንዲህ ዓይነት ከባድ በሽታ ተጠቅተህ ቢሆን ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር? በዛሬው ጊዜ ሰይጣን የአምላክን አገልጋዮች እንደ ኢዮብ በበሽታ አይመታም። ሆኖም በሰብዓዊ አለፍጽምና፣ ዕለታዊው ኑሮ በሚፈጥረው ጭንቀትና ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተበላሸ በሚሄደው አካባቢያችን የተነሳ አልፎ አልፎ የቤተሰብ አባሎች እንደሚታመሙ የታወቀ ነው። የኢዮብን ያህል ለከፋ ሕመም የሚጋለጡት ጥቂቶች ቢሆኑም ሁላችንም አንዳንድ የመከላከያ እርምጃዎችን እየወሰድንም እንኳ መታመማችን አይቀርም። በሽታ ወደ ቤተሰባችን ሰርጎ ሲገባ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንደምንወድቅ የታወቀ ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ከምንጊዜውም ይበልጥ በስፋት ተንሠራፍቶ የሚገኘውን የሰው ዘር ጠላት ለመቋቋም እንዴት ሊረዳን እንደሚችል እንመልከት።​—⁠መክብብ 9:​11፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16

ምን ዓይነት ስሜት ያድርባችኋል?

5. ብዙውን ጊዜ የቤተሰብ አባላት ጊዜያዊ ሕመምን በተመለከተ ምን ይሰማቸዋል?

5 መንሥኤው ምንም ይሁን ምን ሰላማዊው የዕለት ተዕለት ሕይወት ሲደፈርስ፣ በተለይ ደግሞ ለረጅም ጊዜ በሚዘልቅ በሽታ ሲበጠበጥ ሁኔታውን መቋቋም አስቸጋሪ ይሆናል። ለትንሽ ጊዜ የሚቆይ ሕመም እንኳ ማስተካከያና የአመለካከት ለውጥ ማድረግ እንዲሁም መሥዋዕትነት መክፈል ይጠይቃል። የታመመው የቤተሰብ አባል ጥሩ ዕረፍት እንዲያገኝ ሲሉ ጤናማዎቹ የቤተሰቡ አባላት ዝም ማለት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። አንዳንድ ሥራዎችንና እንቅስቃሴዎችን መተው ሊኖርባቸው ይችላል። ያም ሆኖ ግን በአብዛኞቹ ቤተሰቦች ውስጥ ያሉ ትንንሽ ልጆች እንኳ፣ አሳቢነት እንዲያሳዩ አልፎ አልፎ ማሳሰቢያ ሊያስፈልጋቸው ቢችልም ለታመመው ወንድማቸው ወይም እህታቸው ወይም ደግሞ ወላጃቸው የመራራት ዝንባሌ አላቸው። (ቆላስይስ 3:​12) በሽታው ጊዜያዊ በሚሆንበት ጊዜ ቤተሰቡ በአብዛኛው አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በሚታመምበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት አሳቢነት እንደሚያሳዩት ያውቃል።​—⁠ማቴዎስ 7:​12

6. አንዳንድ ጊዜ አንድ የቤተሰብ አባል ከባድና ዘላቂ በሆነ በሽታ ሲያዝ ምን ዓይነት ስሜት ሊንጸባረቅ ይችላል?

6 ይሁን እንጂ በሽታው ሥር የሰደደ ቢሆንና የሚፈጥረውም ችግር ከባድና ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ዓይነት ቢሆንስ? ለምሳሌ አንድ የቤተሰባችሁ አባል ድንገት ሽባ ቢሆን፣ አልትስሃይመርዝ ዲዚዝ በተባለው በሽታ የተነሳ የማስታወስ ችሎታውን ቢያጣ ወይም በሌላ በሽታ ሰውነቱ እየመነመነ ቢሄድስ? ወይም ደግሞ አንድ የቤተሰባችሁ አባል ስኪትሰፍሪኒያ በሚባለው ዓይነት የአእምሮ በሽታ ቢያዝስ? የቤተሰቡ አባላት መጀመሪያ የሚሰማቸው ስሜት ሐዘን ነው፤ የሚወዱት የቤተሰባቸው አባል ከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ በመውደቁ እጅግ ያዝናሉ። ይሁን እንጂ ይህ ሐዘን በሌላ ስሜት ሊተካ ይችላል። የቤተሰቡ አባላት በታመመው ሰው ሳቢያ የራሳቸው ሕይወት በጣም ሲነካና ነፃነታቸው ውስን ሲሆን በጣም ሊበሳጩ ይችላሉ። “ይህ በእኔ ላይ የደረሰው ለምንድን ነው?” ብለው ሊያስቡ ይችላሉ።

7. የኢዮብ ሚስት ለበሽታው ምን ምላሽ ሰጥታ ነበር? ይህስ የትኛውን ነገር መዘንጋቷን ያሳያል?

7 የኢዮብ ሚስትም እንዲህ ዓይነት ስሜት አድሮባት የነበረ ይመስላል። መጀመሪያ ላይ ልጆቿን በሞት እንዳጣች አስታውሱ። እነዚያ አሳዛኝ ሁኔታዎች ደረጃ በደረጃ ሲከሰቱ ይበልጥ እያዘነችና እየተከፋች እንደሄደች ጥርጥር የለውም። በመጨረሻ ደግሞ በአንድ ወቅት ጤናማና ጠንካራ የነበረው ባሏ በጣም በሚያሰቃይና በሚዘገንን በሽታ ተይዞ ስታየው ከዚህ ሁሉ አሳዛኝ መከራ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባውን ትልቁን ነገር ማለትም እሷም ሆነች ባሏ ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ዘነጋች። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ሚስቱም:- እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት አለችው።”​—⁠ኢዮብ 2:​9

8. አንድ የቤተሰብ አባል በጣም በሚታመምበት ጊዜ ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው የትኛው ጥቅስ ሊረዳቸው ይችላል?

8 ብዙዎች በሌላ ሰው መታመም የተነሳ በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሲከሰት ከመበሳጨትም አልፈው ይቆጣሉ። ሆኖም በጉዳዩ ላይ በጥሞና የሚያስብ ክርስቲያን ይህ ሁኔታ ለታመመው ሰው ያለውን እውነተኛ ፍቅር የሚያሳይበት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆንለት መገንዘቡ አይቀርም። እውነተኛ ፍቅር “ይታገሣል፣ ቸርነትንም ያደርጋል፤ . . . የራሱንም አይፈልግም፣ . . . ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል።” (1 ቆሮንቶስ 13:​4-7) ስለዚህ አፍራሽ የሆነ ስሜት እንዲነግሥብን ከመፍቀድ ይልቅ ይህን ስሜት ለመቆጣጠር የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው።​—⁠ምሳሌ 3:​21

9. አንድ የቤተሰብ አባል በጠና በሚታመምበት ጊዜ ቤተሰቡን በመንፈሳዊና በስሜታዊ ሁኔታ ሊረዳ የሚችል ምን ዋስትና ተሰጥቷል?

9 አንድ የቤተሰብ አባል በጠና በሚታመምበት ጊዜ የቤተሰቡን መንፈሳዊና ስሜታዊ ደህንነት ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይቻላል? እርግጥ እያንዳንዱ በሽታ የራሱ የሆነ እንክብካቤና ሕክምና ያስፈልገዋል፤ የትኛውንም ዓይነት ሕክምና ሆነ በቤት ውስጥ የሚሰጥ የጤና አገልግሎት በዚህ ጽሑፍ ውስጥ መጠቆሙ አግባብ አይሆንም። ሆኖም በመንፈሳዊ ሁኔታ ይሖዋ “የወደቁትንም ያነሣቸዋል።” (መዝሙር 145:​14) ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል። እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፣ ሕያውም ያደርገዋል፣ . . . እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል።” (መዝሙር 41:​1-3) ይሖዋ አገልጋዮቹ በስሜታዊ ሁኔታ ከአቅማቸው በላይ በሚፈተኑበት ጊዜም እንኳ በመንፈሳዊ ሕያው ሆነው እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:​7) የቤተሰባቸው አባል በጠና የታመመባቸው ብዙ ቤተሰቦች “እጅግ ተቸገርሁ፤ አቤቱ፣ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ” የሚሉትን የመዝሙራዊው ቃላት አስተጋብተዋል።​—⁠መዝሙር 119:​107

ፈዋሽ መንፈስ

10, 11. (ሀ) አንድ ቤተሰብ በቤተሰቡ አባል ላይ የተከሰተውን በሽታ መቋቋም እንዲችል ሊረዳው የሚችለው በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር ምንድን ነው? (ለ) አንዲት ሴት የባልዋ በሽታ የፈጠረውን ሁኔታ መቋቋም የቻለችው እንዴት ነው?

10 “የሰው ነፍስ [“መንፈስ፣” NW] ሕመሙን ይታገሣል፤” ሲል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ይናገራል፤ “የተቀጠቀጠን መንፈስ ግን ማን ያጠነክረዋል?” (ምሳሌ 18:​14) የሥነ ልቦና ቀውስ የቤተሰብን መንፈስም ሆነ ‘የሰውን መንፈስ’ ሊጎዳ ይችላል። ሆኖም “ሰላም ያለው አእምሮ ለሰውነት ጤንነትን ያስገኛል።” (ምሳሌ 14:​30 የ1980 ትርጉም) አንድ ቤተሰብ በመካከሉ የተከሰተውን ከባድ ሕመም በተሳካ ሁኔታ መቋቋም መቻል አለመቻሉ በአብዛኛው የተመካው በቤተሰቡ አባላት አመለካከት ወይም መንፈስ ላይ ነው።​—⁠ከ⁠ምሳሌ 17:​22 ጋር አወዳድሩ።

11 አንዲት ክርስቲያን ሴት ባሏ በተጋቡ በስድስት ዓመት ውስጥ በአንጎሉ ውስጥ ደም ፈስሶ ሽባ በመሆኑ የደረሰባትን ከባድ ሐዘን መቋቋም ነበረባት። “ባሌ የመናገር ችሎታው ክፉኛ በመስተጓጎሉ ፈጽሞ ማነጋገር አይቻልም ነበር ማለት ይቻላል” ስትል ታስታውሳለች። “እንደ ምንም ብሎ አንድ ነገር ለመናገር በሚታገልበት ጊዜ ምን ለማለት እንደፈለገ ለመረዳት የምታደርጉት ጥረት ከባድ የአእምሮ ውጥረት ይፈጥርባችኋል።” ባሏም ምን ያህል ይሰቃይና ይበሳጭ እንደነበረ ገምቱት። ባልና ሚስቱ ምን አደረጉ? ምንም እንኳ ቤታቸው ከክርስቲያን ጉባኤው በጣም ሩቅ ቢሆንም ይህች እህት አዳዲስ ድርጅታዊ መመሪያዎችን በሚገባ በመከታተልና በየጊዜው በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች አማካኝነት የሚቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆና ለመቀጠል የምትችለውን ሁሉ ጥረት አድርጋለች። እንዲህ ማድረጓ ውድ ባለቤቷን ከአራት ዓመታት በኋላ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ በሚገባ ለማስታመም የሚያስችል መንፈሳዊ ጥንካሬ ሰጥቷታል።

12. በኢዮብ ሁኔታ ላይ እንደታየው አንዳንድ ጊዜ የታመመው ሰው ምን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል?

12 በኢዮብ ሁኔታ ግን ጠንካራ ሆኖ የቀጠለው በበሽታ እየተሰቃየ የነበረው ኢዮብ ራሱ ነበር። ሚስቱን “ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፣ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን?” ሲል ጠይቋታል። (ኢዮብ 2:​10) ከጊዜ በኋላ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ኢዮብን የትዕግሥትና የጽናት ታላቅ ምሳሌ አድርጎ መጥቀሱ ምንም አያስደንቅም! በ⁠ያዕቆብ 5:​11 ላይ እንዲህ እናነባለን:- “ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፣ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።” ዛሬም በተመሳሳይ አንድ የታመመ የቤተሰብ አባል የሚያሳየው ድፍረት የተሞላበት አቋም ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት አዎንታዊ የሆነ አመለካከት እንዲይዙ ረድቷቸዋል።

13. የቤተሰቡ አባል በጠና የታመመበት አንድ ቤተሰብ ራሱን ከሌሎች ጋር በምን መልኩ ማወዳደር የለበትም?

13 የቤተሰባቸው አባል የታመመባቸው አብዛኞቹ ሰዎች እንደሚስማሙበት መጀመሪያ ላይ የቤተሰቡ አባላት እውነታውን ለመቀበል በጣም ይቸገራሉ። በተጨማሪም አንድ ሰው ለሁኔታው የሚኖረው አመለካከት በጣም ወሳኝ እንደሆነ ይናገራሉ። መጀመሪያ ላይ የቤተሰቡን የተለመደ አሠራር መለወጥና ማስተካከል አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከልቡ ጥረት ካደረገ አዲሱን ሁኔታ ሊላመደው ይችላል። ይህን በምናደርግበት ጊዜ የእኛን ሁኔታ የታመመ የቤተሰብ አባል ከሌለባቸው ቤተሰቦች ሁኔታ ጋር በማወዳደር የእነሱ ሕይወት ከችግር ነፃ እንደሆነና ‘ይህ ደግሞ አግባብ እንዳልሆነ’ አድርገን ማሰብ የለብንም! እውነቱን ለመናገር ከሆነ፣ ሌሎች ምን ዓይነት ሸክም እንዳለባቸው የሚያውቅ የለም። ሁሉም ክርስቲያኖች በሚከተሉት የኢየሱስ ቃላት ይጽናናሉ:- “ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ።”​—⁠ማቴዎስ 11:​28

ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ማስቀደም

14. ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ማስቀደም የሚቻለው እንዴት ነው?

14 የቤተሰብ አባሉ በጠና የታመመበት አንድ ቤተሰብ ‘መካሮች በበዙበት የታሰበው ይጸናል’ የሚሉትን በመንፈስ አነሳሽነት የተነገሩ ቃላት ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። (ምሳሌ 15:​22) የቤተሰቡ አባላት አንድ ላይ ተሰባስበው በሽታው ስላስከተለው ሁኔታ መወያየት ይችላሉን? አንድ ላይ ተሰባስቦ በጉዳዩ ላይ በጥልቀት መነጋገርና መመሪያ ለማግኘት ወደ አምላክ ቃል ዞር ማለት ተገቢ ነው። (መዝሙር 25:​4) ልትወያዩበት የሚገባው ነገር ምንድን ነው? ውሳኔ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ሕክምናን፣ ገንዘብንና ቤተሰቡን የሚመለከቱ ጉዳዮች አሉ። የታመመውን የቤተሰብ አባል በዋነኛነት ማን ያስታም? በማስታመም ረገድ ሌሎቹ የቤተሰብ አባላት ሊተባበሩ የሚችሉት እንዴት ነው? የሚደረጉት ዝግጅቶች እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል የሚነኩት እንዴት ነው? በዋነኛነት የሚያስታምመው የቤተሰብ አባል የሚያስፈልጉትን መንፈሳዊና ሌሎች ነገሮች ማሟላት የሚቻለው እንዴት ነው?

15. ይሖዋ ከባድ በሽታ ለገጠማቸው ቤተሰቦች ምን ዓይነት ድጋፍ ያደርጋል?

15 ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠን አጥብቀን መጸለያችን፣ በቃሉ ላይ ማሰላሰላችንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን መንገድ በድፍረት መከተላችን ብዙውን ጊዜ ከጠበቅነው በላይ ብዙ በረከት እንድናገኝ ይረዳናል። የታመመው የቤተሰብ አባል በሽታው እንዲቀልለት ማድረግ አይቻል ይሆናል። ሆኖም በማንኛውም ሁኔታ ሥር በይሖዋ መደገፍ ምንጊዜም ከሁሉ የተሻለ ውጤት ያስገኛል። (መዝሙር 55:​22) መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አቤቱ፣ ምሕረትህ ረዳኝ። አቤቱ፣ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።”​—⁠መዝሙር 94:​18, 19፤ በተጨማሪም መዝሙር 63:​6-8ን ተመልከቱ።

ልጆቹን መርዳት

ቤተሰቡ አንድ ላይ ተባብሮ ሲሠራ ችግሮቹን መቋቋም ይችላል

16, 17. ትንንሽ ልጆች ስለ ወንድማቸው ወይም ስለ እህታቸው በሽታ በሚነገራቸው ጊዜ ምን ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል?

16 ከባድ ሕመም በቤተሰቡ ውስጥ ባሉት ልጆች ላይ አንዳንድ ችግሮች ሊፈጥር ይችላል። ወላጆች የተከሰተውን ችግር ለልጆቻቸው ማስረዳትና ልጆቹ በዚህ ረገድ ምን እርዳታ ማበርከት እንደሚችሉ ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል። የታመመው የቤተሰብ አባል ልጅ ከሆነ ለልጁ ልዩ ትኩረትና እንክብካቤ የሚያደርጉት ከእነሱ አስበልጠው ስለሚወዱት እንዳልሆነ ወንድሞቹና እህቶቹ እንዲገነዘቡ መርዳት ያስፈልጋል። ሌሎቹ ልጆች ቅሬታ ወይም የፉክክር መንፈስ እንዲያድርባቸው ከመፍቀድ ይልቅ ወላጆች በሽታው የፈጠረውን ሁኔታ ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ልጆቹ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በሚያደርጉበት ጊዜ እርስ በርሳቸው የጠበቀ ዝምድናና ልባዊ ፍቅር እንዲኖራቸው ሊረዷቸው ይችላሉ።

17 ወላጆች ትንንሽ ለሆኑ ልጆች ስለ በሽታው ሁኔታ ረጅም ወይም የተወሳሰበ ትንተና ከመስጠት ይልቅ ልጆቹ ሊያሳዩት ስለሚገባው ስሜት ቢገልጹላቸው ብዙውን ጊዜ ልጆቹ ይበልጥ አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ። ስለዚህ የታመመው የቤተሰብ አባል ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳለ በአጭሩ ሊገልጹላቸው ይችላሉ። የታመመው ልጅ እነርሱ አቅልለው የሚመለከቷቸውን ብዙ ነገሮች ማከናወን እንዳይችል በሽታው እንዴት እንቅፋት እንደሆነበት ከተገነዘቡ ይበልጥ ‘ወንድማዊ ፍቅር ሊያሳዩና ርኅሩኆች’ ሊሆኑ ይችላሉ።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:​8

18. ትልልቆቹ ልጆች በሽታው ያስከተላቸውን ችግሮች እንዲገነዘቡ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው? ይህስ እነሱን ሊጠቅማቸው የሚችለው እንዴት ነው?

18 ትልልቆቹ ልጆች በቤተሰቡ ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳለና ይህም እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል መሥዋዕትነት እንዲከፍል የሚጠይቅበት መሆኑን እንዲገነዘቡ መርዳት ያስፈልጋል። ለዶክተሮች የሚከፈለው ገንዘብና ለሕክምና የሚወጣው ወጪ ቀላል ባለመሆኑ ወላጆች ሌሎቹ ልጆች የሚፈልጉትን ሁሉ ማድረግ አይችሉ ይሆናል። ልጆቹ በዚህ ቅር ይሰኛሉ? የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደተነፈጉ ሆኖስ ይሰማቸዋል? ወይስ ሁኔታውን ተረድተው አስፈላጊውን መሥዋዕት ለመክፈል ዝግጁ ናቸው? ውይይቱ የተካሄደበት መንገድና በቤተሰቡ ውስጥ ያለው መንፈስ ለዚህ በጣም ወሳኝ ነው። እንዲያውም በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ የታመመ የቤተሰብ አባል መኖሩ ልጆች የሚከተለውን የጳውሎስ ምክር እንዲከተሉ ለማሠልጠን ጥሩ አስተዋጽኦ አበርክቷል:- “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር፤ እንያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ።”​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​3, 4

ሕክምናን በተመለከተ ሊኖረን የሚገባው አመለካከት

19, 20. (ሀ) አንድ የቤተሰብ አባል በሚታመምበት ጊዜ በቤተሰብ ራሶች ላይ ምን ኃላፊነት ይወድቃል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መጽሐፍ ባይሆንም እንኳ በሽታን መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ መመሪያ የሚሰጠው እንዴት ነው?

19 ሚዛናዊ የሆኑ ክርስቲያኖች ከአምላክ ሕግ ጋር እስካልተጋጨ ድረስ ሕክምናን አይቃወሙም። የቤተሰባቸው አባል በሚታመምበት ጊዜ የሕመምተኛውን ሥቃይ የሚያስታግስ እርዳታ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ያም ሆኖ ግን ልናመዛዝናቸው የሚገቡ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ የሕክምና አስተያየቶች ሊኖሩ ይችላሉ። በተጨማሪም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አዳዲስ በሽታዎች ድንገት ብቅ እያሉ ነው፤ ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያገኘ የሕክምና ዘዴ የላቸውም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ በሽታውን ለይቶ ማወቁ ራሱ አስቸጋሪ ይሆናል። በዚህ ጊዜ አንድ ክርስቲያን ምን ማድረግ አለበት?

20 ምንም እንኳ አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ሐኪም የነበረ ቢሆንና ሐዋርያው ጳውሎስም ለጓደኛው ለጢሞቴዎስ ጠቃሚ የሆነ የሕክምና ምክር ሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ቅዱስ ጽሑፉ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ መመሪያ እንጂ የሕክምና መጽሐፍ አይደለም። (ቆላስይስ 4:​14፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​23) ስለዚህ ከሕክምና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ የክርስቲያን ቤተሰብ ራሶች የራሳቸውን ሚዛናዊ ውሳኔዎች መወሰን ይኖርባቸዋል። ምናልባትም የተለያዩ ባለሙያዎችን ማማከር እንዳለባቸው ሆኖ ይሰማቸው ይሆናል። (ከ⁠ምሳሌ 18:​17 ጋር አወዳድሩ።) የታመመው የቤተሰባቸው አባል ከሁሉ የተሻለውን እርዳታ እንዲያገኝ ይፈልጋሉ፤ እናም አብዛኞቹ እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ ማግኘት የሚፈልጉት ከመደበኛዎቹ የሕክምና ዶክተሮች ነው። አንዳንዶች ደግሞ ሌሎች የሕክምና ዘዴዎችን መጠቀም ይመርጣሉ። ይህም የግል ውሳኔ ነው። ሆኖም ክርስቲያኖች ለጤና ችግር እርዳታ ለማግኘት በሚጥሩበት ጊዜ ‘የአምላክን ሕግ ለእግራቸው መብራት ለመንገዳቸውም ብርሃን’ አድርገው ይጠቀሙበታል። (መዝሙር 119:​105) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን መመሪያዎች መከተላቸውን ይቀጥላሉ። (ኢሳይያስ 55:​8, 9) በመሆኑም ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ከሚመሳሰል የምርመራ ዘዴም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ከሚያስጥሱ ሕክምናዎች ይርቃሉ።​—⁠መዝሙር 36:​9፤ ሥራ 15:​28, 29፤ ራእይ 21:​8

21, 22. አንዲት እስያዊት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ተጠቅማ አንድ ውሳኔ ላይ የደረሰችው እንዴት ነው? ከእሷ ሁኔታ አንጻር ውሳኔዋ ትክክል ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

21 አንዲት እስያዊት ወጣት ያጋጠማትን ሁኔታ ተመልከቱ። ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር በማጥናት መጽሐፍ ቅዱስን መማር ከጀመረች ከጥቂት ጊዜ በኋላ 1,470 ግራም ብቻ የምትመዝን ልጅ አለጊዜዋ ወለደች። የሕፃኗ እድገት በጣም ዘገምተኛ እንደሚሆንና ፈጽሞ በእግሯ መሄድ እንደማትችል ዶክተሩ ሲነግራት ሴትየዋ ቅስሟ ተሰበረ። ዶክተሩ ሕፃኗን ለአካል ጉዳተኞች ማሳደጊያ ተቋም እንድትሰጣት መከራት። ባሏ ምን እንደሚያደርግ ግራ ገብቶት ነበር። ታዲያ ማንን ታማክር?

22 እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “‘ልጆች የይሖዋ ስጦታ እንደሆኑና የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ እንደሆነ’ ከመጽሐፍ ቅዱስ መማሬን አስታውሳለሁ።” (መዝሙር 127:​3) ስለዚህ ይህችን “ስጦታ” ወደ ቤቷ ወስዳ ራሷ ለማሳደግ ወሰነች። በመጀመሪያ ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ ሆኖም በአካባቢው ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የሚገኙ ክርስቲያን ጓደኞቿ ባደረጉላት ድጋፍ ሴትየዋ ልጅቷ የሚያስፈልጋትን ልዩ እርዳታ መስጠት ችላለች። ከአሥራ ሁለት ዓመታት በኋላ ልጅቷ በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት እዚያ ከምታገኛቸው ልጆች ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት በቅታለች። እናትየው እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ትክክል የሆነውን ነገር እንዳደርግ ስለገፋፉኝ በጣም ደስተኛ ነኝ። መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ አምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረኝና ዕድሜ ልኬን ሲጸጽተኝ የሚኖር ነገር ከማድረግ እንድቆጠብ ረድቶኛል።”

23. መጽሐፍ ቅዱስ ለታመሙና የታመሙትን ለሚንከባከቡ ሰዎች ምን ማጽናኛ ይሰጣል?

23 በሽታ ለዘላለም አብሮን የሚኖር ነገር አይደለም። ነቢዩ ኢሳይያስ ‘ታምሜአለሁ የሚል ሰው የማይኖርበት’ ጊዜ እንደሚመጣ አመልክቷል። (ኢሳይያስ 33:​24) ይህ ተስፋ በፍጥነት እየቀረበ ባለው አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጻሜውን ያገኛል። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ከበሽታና ከሞት ጋር እየታገሉ መኖር ግድ ነው። የአምላክ ቃል መመሪያና እርዳታ የሚሰጠን መሆኑ ያስደስታል። የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሠረታዊ መመሪያዎች ዘላቂ ከመሆናቸውም በላይ ፍጹም ያልሆኑት የሰው ልጆች ከሚሰጧቸው ተለዋዋጭ አስተያየቶች እጅግ የላቁ ናቸው። በመሆኑም ጥበበኛ የሆነ ሰው እንዲህ ሲል ከጻፈው መዝሙራዊ ጋር ይስማማል:- “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር [“ማሳሰቢያ፣” NW] የታመነ ነው፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል። . . . የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ነው። . . . ባሪያህ . . . በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል።”​—⁠መዝሙር 19:​7, 9, 11