በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ አራት

በእርጅና ዘመንም ተደጋግፎ መኖር

በእርጅና ዘመንም ተደጋግፎ መኖር

1, 2. (ሀ) ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ምን ለውጦች ይከሰታሉ? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ሰዎች በእርጅና ዘመናቸው እርካታ ያገኙት እንዴት ነው?

በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ ብዙ ለውጦች ይከሰታሉ። አካላችን እየደከመ ኃይላችን እየተሟጠጠ ይሄዳል። መልካችንን በመስታወት ስንመለከት ቆዳችን እየተሸበሸበ፣ ፀጉራችን እየሸበተ አልፎ ተርፎም እየሳሳ መሆኑን እናስተውላለን። አንዳንድ ነገር እየዘነጋን እንቸገር ይሆናል። ልጆች ሲያገቡና ከዚያም የልጅ ልጆች ሲመጡ አዳዲስ ዝምድናዎች ይፈጠራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ከሰብዓዊ ሥራቸው በጡረታ መገለላቸው የተለመደውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን ይለውጠዋል።

2 እውነቱን ለመናገር ከሆነ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ሁኔታዎች ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ። (መክብብ 12:​1-8) ያም ሆኖ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩትን የአምላክ አገልጋዮች ተመልከቱ። ምንም እንኳ በመጨረሻ ሞት ቢወስዳቸውም በእርጅና ዘመናቸው ትልቅ እርካታ ያመጣላቸውን ጥበብና ማስተዋል አግኝተዋል። (ዘፍጥረት 25:​8፤ 35:​29፤ ኢዮብ 12:​12፤ 42:​17) በእርጅና ዘመናቸውም ደስተኞች ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው? ዛሬ እኛ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የምናገኛቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ውስጥ በሥራ ላይ በማዋላቸው እንደሆነ ግልጽ ነው።​—⁠መዝሙር 119:​105፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17

3. ጳውሎስ በዕድሜ ለገፉ ወንዶችና ሴቶች ምን ምክር ሰጥቷል?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ጥሩ መመሪያ ሰጥቷል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሽማግሌዎች ልከኞች፣ ጭምቶች፣ ራሳቸውን የሚገዙ፣ በእምነትና በፍቅር በመጽናትም ጤናሞች እንዲሆኑ ምከራቸው፤ እንዲሁም አሮጊቶች ሴቶች አካሄዳቸው ለቅዱስ አገልግሎት የሚገባ፣ የማያሙ፣ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይገዙ፣ በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ።” (ቲቶ 2:​2, 3) ይህን ምክር መከተላችሁ በእርጅና ዘመን የሚያጋጥሟችሁን ፈታኝ ሁኔታዎች እንድትቋቋሙ ሊረዳችሁ ይችላል።

ልጆቻችሁ ራሳቸውን ችለው ሲወጡ ከሚፈጠረው ሁኔታ ጋር ራሳችሁን አስማሙ

4, 5. ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ ምን ይሰማቸዋል? አንዳንዶች ከተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ያስማሙት እንዴት ነው?

4 የኃላፊነት ለውጥ በሚኖርበት ጊዜ ራስን ከተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ጋር ማላመድ አስፈላጊ ነው። ለአካለ መጠን የደረሱ ልጆች ራሳቸውን ችለው ከቤት በሚወጡበትና በሚያገቡበት ጊዜ ይህን የማድረጉ አስፈላጊነት ጎልቶ ይታያል። ብዙ ወላጆች ዕድሜያቸው እየገፋ መሆኑን የሚያስታውሳቸው የመጀመሪያው ነገር ይህ ሁኔታ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው ለአካለ መጠን መድረሳቸው የሚያስደስታቸው ቢሆንም እንኳ ብዙውን ጊዜ ልጆቹ ራሳቸውን ችለው ለመኖር የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አድርጌያለሁ ወይስ አላደረግኩም የሚለው ነገር ያስጨንቃቸዋል። ልጆቻቸውን ከአጠገባቸው ማጣታቸውም ቅር ያሰኛቸዋል።

5 ወላጆች ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው ከቤት ከወጡም በኋላ ስለ ልጆቻቸው ደህንነት ማሰባቸው አይቀርም። “ብዙውን ጊዜ ደህንነታቸውን ከእነሱ መስማት መቻሌ ብቻ እንኳ ያስደስተኛል” ስትል አንዲት እናት ተናግራለች። አንድ አባት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ልጃችን ራሷን ችላ መኖር ስትጀምር በጣም ተረብሸን ነበር። ሁልጊዜ ማንኛውንም ነገር አብረን እንሠራ ስለነበር በጣም አጉድላናለች።” እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ከእነሱ መለየታቸው የፈጠረባቸውን አስቸጋሪ ሁኔታ የተቋቋሙት እንዴት ነው? በአብዛኛው ይህን ማድረግ የቻሉት ለሌሎች ሰዎች አሳቢነት በማሳየትና በመርዳት ነው።

6. በቤተሰብ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት ለመያዝ ሊረዳ የሚችለው ነገር ምንድን ነው?

6 ልጆች ሲያገቡ የወላጆቹ የኃላፊነት ቦታ ይለወጣል። ዘፍጥረት 2:​24 “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ሲል ይገልጻል። (በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ወላጆች ስለ ራስነት ሥልጣንና ስለ ሥርዓታማነት የሚገልጹትን አምላካዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች ማክበራቸው ለተፈጠሩት ሁኔታዎች ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 11:​3፤ 14:​33, 40

7. አንድ አባት ሴቶች ልጆቹ አግብተው መኖር ሲጀምሩ ምን ጥሩ አመለካከት አዳብሯል?

7 አንድ ባልና ሚስት ሁለት ሴቶች ልጆቻቸው አግብተው ከቤት ከወጡ በኋላ የብቸኝነት ስሜት ተሰማቸው። መጀመሪያ ላይ ባልየው በልጆቹ ባሎች አልተደሰተም ነበር። ሆኖም ስለ ራስነት ሥልጣን በሚናገረው መሠረታዊ ሥርዓት ላይ በሚገባ ሲያሰላስል በአሁኑ ጊዜ በየቤተሰባቸው ላይ ሥልጣን ያላቸው የልጆቹ ባሎች እንደሆኑ ተገነዘበ። ስለዚህ ልጆቹ ምክር ሲጠይቁት ባሎቻቸው በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሐሳብ በመጠየቅ በተቻለ መጠን የእነሱን ሐሳብ ለመደገፍ መጣር ጀመረ። በአሁኑ ጊዜ የልጆቹ ባሎች እንደ ጓደኛቸው የሚመለከቱት ከመሆናቸውም በላይ የሚሰጣቸውን ምክር በደስታ ይቀበላሉ።

8, 9. አንዳንድ ወላጆች ለአካለ መጠን የደረሱት ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው መኖር መጀመራቸው ካስከተለው ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ያስማሙት እንዴት ነው?

8 አዲስ ተጋቢዎች ቅዱስ ጽሑፉን የሚቃረን ነገር ባያደርጉም እንኳ ወላጆቻቸው የተሻለ ነው ብለው የሚያስቡትን ነገር ሳያደርጉ ቢቀሩስ? “ሁልጊዜ ጉዳዩን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር እንዲመለከቱት እንረዳቸዋለን” ሲሉ ያገቡ ልጆች ያሏቸው አንድ ባልና ሚስት ገልጸዋል፤ “ሆኖም በወሰዱት ውሳኔ ባንስማማ እንኳ ውሳኔያቸውን ተቀብለን ድጋፍና ማበረታቻ እንሰጣቸዋለን።”

9 በአንዳንድ የእስያ አገሮች አንዳንድ እናቶች ወንዶች ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው መኖራቸው አይዋጥላቸውም። ይሁን እንጂ ክርስቲያናዊ ሥርዓትንና የራስነትን ሥልጣን የሚያከብሩ ከሆነ ከምራቶቻቸው ጋር የሚኖራቸው ግጭት በጣም ይቀንሳል። አንዲት ክርስቲያን ሴት ወንዶች ልጆቿ ከቤተሰባቸው ተለይተው ራሳቸውን ችለው መኖር መጀመራቸው “ትልቅ የደስታ ምንጭ” ሆኖላታል። አዳዲስ ቤተሰቦቻቸውን የማስተዳደር ችሎታቸውን ማየቷ እጅግ አስደስቷታል። ይህ ደግሞ እሷም ሆነች ባሏ በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ ያለባቸው አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ሸክም እየቀለለላቸው እንዲሄድ ረድቷቸዋል።

የትዳራችሁን ማሰሪያ እንደ አዲስ ማጠናከር

10, 11. ሰዎች በዕድሜ ጠና እያሉ ሲሄዱ ራሳቸውን ከአንዳንድ ወጥመዶች መጠበቅ እንዲችሉ የሚረዳቸው የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ነው?

10 ሰዎች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የተለያዩ ነገሮችን ሲያደርጉ ይታያሉ። አንዳንዶቹ ወንዶች ወጣት መስለው ለመታየት ለየት ያለ አለባበስ ይለብሳሉ። ብዙ ሴቶች ማረጥ የሚያስከትላቸው ለውጦች ያስጨንቋቸዋል። የሚያሳዝነው አንዳንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ወንዶች ከወጣት ሴቶች ጋር በመቃበጥ የትዳር ጓደኞቻቸው ቅር እንዲሰኙና የቅናት ስሜት እንዲያድርባቸው ያደርጓቸዋል። ሆኖም ፊሪሃ አምላክ ያላቸው በዕድሜ የገፉ ወንዶች ትክክለኛ ያልሆኑ ፍላጎቶችን በመቆጣጠር “እንደ ባለ አእምሮ” ያስባሉ። (1 ጴጥሮስ 4:​7) የጎለመሱ ሴቶችም እንደዚሁ ለባሎቻቸው ባላቸው ፍቅርና ይሖዋን ለማስደሰት ባላቸው ፍላጎት ተገፋፍተው ትዳራቸው ጸንቶ እንዲቀጥል ጠንክረው ይሠራሉ።

11 ንጉሥ ልሙኤል በመንፈስ አነሳሽነት ተገፋፍቶ ‘ዕድሜዋን ሙሉ ለባሏ ክፉ ሳይሆን መልካም ለምታደርገው ባለሙያ ሚስት’ የምስጋና ቃላት ጽፏል። አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱ ዕድሜዋ እየገፋ ሲሄድ የሚያጋጥማትን ማንኛውንም ዓይነት የስሜት መረበሽ ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት እንዲሁ በቸልታ አያልፍም። ለእሷ ያለው ፍቅር ‘እንዲያመሰግናት’ ይገፋፋዋል።​—⁠ምሳሌ 31:​10, 12, 28

12. ባልና ሚስት ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ይበልጥ እየተቀራረቡ መሄድ የሚችሉት እንዴት ነው?

12 ልጅ በማሳደግ ባሳለፋችኋቸው ውጥረት የበዛባቸው ዓመታት ሁለታችሁም ልጆቻችሁ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ስትሉ የግል ፍላጎቶቻችሁን በደስታ ወደ ጎን አድርጋችሁ ሊሆን ይችላል። ልጆቻችሁ ራሳቸውን ችለው መኖር ከጀመሩ በኋላ ግን እንደገና በራሳችሁ የትዳር ሕይወት ላይ ታተኩራላችሁ። አንድ ባል “ሴቶች ልጆቼ ራሳቸውን ችለው መኖር ሲጀምሩ ከሚስቴ ጋር እንደ አዲስ መጠናናት ጀመርኩ” ሲል ተናግሯል። አንድ ሌላ ባል ደግሞ “አንዳችን ለሌላው ጤንነት የምናስብ ከመሆኑም በላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግን አስፈላጊነት አንዳችን ለሌላው እናሳስባለን” ሲል ተናግሯል። እሱና ሚስቱ የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማቸው ለሌሎቹ የጉባኤው አባላት የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ያሳያሉ። አዎ፣ ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት በረከት ያስገኛል። ከዚህም በላይ ይሖዋን ያስደስተዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​4፤ ዕብራውያን 13:​2, 16

13. ባልና ሚስት በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ ግልጽነትና ሐቀኝነት ምን ሚና ይጫወታሉ?

13 ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ በምታደርጉበት ጊዜ ምንም የምትደባበቁት ነገር መኖር የለበትም። በግልጽ ተነጋገሩ። (ምሳሌ 17:​27) “አንዳችን ሌላውን በመንከባከብና አሳቢ በመሆን በመካከላችን ያለውን ወዳጅነት አጠናክረነዋል” ሲል አንድ ባል ተናግሯል። ሚስቱ ከባሏ አባባል ጋር በመስማማት “ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ አብረን ሻይ የመጠጣት፣ የመጫወትና እርስ በርስ የመረዳዳት ልማድ አዳብረናል” ብላለች። ምንም ሳትደባበቁ በግልጽ መወያየታችሁ የትዳር ፀር የሆነው ሰይጣን የሚሰነዝራቸውን ጥቃቶች መቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ በመስጠት የትዳራችሁን ማሰሪያ እንድታጠብቁ ሊረዳችሁ ይችላል።

በልጅ ልጆቻችሁ ተደሰቱ

14. ጢሞቴዎስ ክርስቲያን ሆኖ እንዲያድግ በመርዳት ረገድ አያቱ ምን ሚና እንደተጫወተች ግልጽ ነው?

14 የልጅ ልጆች የአረጋውያን “አክሊል” ናቸው። (ምሳሌ 17:⁠6) ከልጅ ልጆች ጋር አብሮ ጊዜ ማሳለፍ የሚያስደስትና መንፈስን የሚያድስ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከልጅዋ ከኤውንቄ ጋር ሆና የልጅ ልጅዋ ለሆነው ለጢሞቴዎስ እምነቷን ስላካፈለችው ሎይድ ስለተባለች አረጋዊት ሴት ይናገራል። ይህ ወጣት ገና ከልጅነቱ ጀምሮ እናቱና አያቱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ ሊገነዘብ ችሏል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 1:​5፤ 3:​14, 15

15. የልጅ ልጆችን በተመለከተ አያቶች ምን ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ? ሆኖም ምን ከማድረግ መቆጠብ አለባቸው?

15 ስለዚህ የልጅ ልጆች ያሏቸው ወላጆች በዚህ ረገድ እጅግ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። የልጅ ልጆች ያሏችሁ ወላጆች ቀደም ሲል ስለ ይሖዋ ዓላማዎች የሚገልጸውን እውቀት ለራሳችሁ ልጆች አካፍላችሁ ነበር። አሁን ደግሞ ለሌላ ትውልድ ይህንኑ ማድረግ ትችላላችሁ! ብዙ ትንንሽ ልጆች አያቶቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ሲተርኩላቸው መስማት ያስደስታቸዋል። እርግጥ ነው፣ አባትየው በልጆቹ አእምሮ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በመቅረጽ ረገድ ያለበትን ኃላፊነት ትወስዳላችሁ ማለት አይደለም። (ዘዳግም 6:​7) ከዚህ ይልቅ ኃላፊነቱን በብቃት እንዲወጣ ትረዱታላችሁ። የሚከተለው የመዝሙራዊው ጸሎት የእናንተም ጸሎት ይሁን:- “እስካረጅም እስክሸመግልም ድረስ፣ ለሚመጣ ትውልድም ሁሉ ክንድህን ኃይልህንም ጽድቅህንም እስክነግር ድረስ፣ አቤቱ፣ አትተወኝ።”​—⁠መዝሙር 71:​18፤ 78:​5, 6

16. አያቶች በቤተሰባቸው ውስጥ ለግጭት መንስኤ እንዳይሆኑ ምን ከማድረግ መራቅ አለባቸው?

16 የሚያሳዝነው አንዳንድ አያቶች የልጅ ልጆቻቸውን በጣም ስለሚያሞላቅቋቸው በእነሱና በራሳቸው ልጆች መካከል ግጭት ይፈጠራል። ይሁን እንጂ የልጅ ልጆቻችሁ ከልባችሁ የምታሳዩአቸው ደግነት አንዳንድ ጉዳዮችን ለወላጆቻቸው መግለጽ በሚከብዳቸው ጊዜ እናንተን ማማከር እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ሊፈጥርላቸው ይችላል። አያቶቻቸው የሚያሞላቅቋቸው ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በሚጋጩበት ጊዜ አያቶቻቸው ከእነሱ ጎን እንደሚቆሙ አድርገው ያስባሉ። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? ጥበብ በመጠቀም የልጅ ልጆቻችሁ ለወላጆቻቸው ግልጽ እንዲሆኑ አበረታቷቸው። ይህ ይሖዋን እንደሚያስደስተው ልትገልጹላቸው ትችላላችሁ። (ኤፌሶን 6:​1-3) አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ወላጆቻቸውን ቀርባችሁ በማነጋገር ለልጆቹ መንገዱን ልታመቻቹላቸው ትችላላችሁ። በሕይወት ባሳለፋችኋቸው በርካታ ዓመታት የተማራችሁትን ነገር ለልጅ ልጆቻችሁ በግልጽ ንገሯቸው። ሐቀኝነታችሁና ግልጽነታችሁ ሊጠቅማቸው ይችላል።

ዕድሜያችሁ እየገፋ መሄዱ ከሚያስከትለው ሁኔታ ጋር ራሳችሁን አስማሙ

17. በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች የትኛውን የመዝሙራዊውን ቁርጥ ውሳኔ መከተል ይኖርባቸዋል?

17 ዕድሜያችሁ እየገፋ ሲሄድ ቀደም ሲል ታደርጓቸው የነበሩትን ወይም ደግሞ ልታደርጉ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ ማድረግ ይሳናችኋል። አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን የእርጅና ሂደት አምኖ መቀበልና መቋቋም የሚችለው እንዴት ነው? በውስጣችሁ ገና የ30 ዓመት ሰው እንደሆናችሁ ይሰማችሁ ይሆናል፤ ሆኖም መልካችሁን በመስታወት ስትመለከቱ እውነታው ሌላ ሆኖ ታገኙታላችሁ። ተስፋ አትቁረጡ። መዝሙራዊው ይሖዋን እንዲህ ሲል ተማጽኗል:- “በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፣ ጉልበቴም ባለቀ ጊዜ አትተወኝ።” የመዝሙራዊውን ዓይነት አቋም ለመውሰድ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። መዝሙራዊው “እኔ ግን ሁልጊዜ ተስፋ አደርጋለሁ፣ በምስጋናህም ሁሉ ላይ እጨምራለሁ” ብሏል።​—⁠መዝሙር 71:​9, 14

18. አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ጡረታ ሲወጣ ጊዜውን ጠቃሚ በሆነ መንገድ ሊጠቀምበት የሚችለው እንዴት ነው?

18 ብዙዎች ከሰብዓዊ ሥራቸው በጡረታ ከተገለሉ በኋላ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን ምስጋና ከፍ ለማድረግ አስቀድመው ዝግጅት አድርገዋል። “ሴት ልጃችን ትምህርቷን ከጨረሰች በኋላ የማደርገውን ነገር አስቀድሜ አቅጄ ነበር” ሲል በአሁኑ ጊዜ ጡረታ የወጣ አንድ አባት ገልጿል። “በሙሉ ጊዜ የስብከት አገልግሎት ለመሳተፍ ወስኜ ነበር፤ ይሖዋን ይበልጥ ሙሉ በሙሉ ለማገልገል የሚያስችል ነፃነት ለማግኘት ስል የንግድ ድርጅቴን ሸጥኩ። አምላክ መመሪያ እንዲሰጠኝ ጸለይኩ።” ጡረታ ወደምትወጡበት ዕድሜ እየተቃረባችሁ ከሆነ በሚከተለው የታላቁ ፈጣሪያችን መግለጫ ልትጽናኑ ትችላላችሁ:- “እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፣ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ።”​—⁠ኢሳይያስ 46:​4

19. በዕድሜ ለገፉት ምን ምክር ተሰጥቷል?

19 ከሰብዓዊ ሥራ በጡረታ መገለል ከሚያስከትለው ሁኔታ ጋር ራስን ማስማማት ቀላል ላይሆን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዕድሜ የገፉ ወንዶች “ልከኞች” እንዲሆኑ መክሯል። ይህም የተንደላቀቀ ኑሮ የመኖርን ፍላጎት በመቆጣጠር በሁሉም ነገር ቁጥብ መሆን ይጠይቃል። ጡረታ ከወጣችሁ በኋላ ከበፊቱ ይበልጥ የተደራጃችሁ መሆንና ራሳችሁን መገሰጽ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። እንግዲያው ራሳችሁን በሥራ አስጠምዱ፤ “ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና . . . የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” (1 ቆሮንቶስ 15:​58) ሌሎችን መርዳት እንድትችሉ እንቅስቃሴያችሁን አስፉት። (2 ቆሮንቶስ 6:​13) ብዙ ክርስቲያኖች ዕድሜያቸው በሚፈቅድላቸው መጠን በምሥራቹ ስብከት በቅንዓት በመሳተፍ ይህን በማድረግ ላይ ናቸው። በዕድሜ እየገፋችሁ ስትሄዱ “በእምነትና በፍቅር በመጽናትም ጤናሞች” ሁኑ።​—⁠ቲቶ 2:​2

የትዳር ጓደኛችሁን በሞት ማጣታችሁ የሚያስከትልባችሁን ሐዘን መቋቋም

20, 21. (ሀ) በዚህ ባለንበት ሥርዓት ውስጥ ባልና ሚስት በመጨረሻ በምን መለያየታቸው አይቀርም? (ለ) ሐና የትዳር ጓደኛቸው በሞት ለተለያቸው ሰዎች ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው እንዴት ነው?

20 ምንም እንኳ ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ቢሆንም በዚህ ባለንበት ሥርዓት ውስጥ የትዳር ጓደኛሞች በመጨረሻ በሞት መለያየታቸው አይቀርም። የትዳር ጓደኛቸው በሞት የተለያቸው ክርስቲያኖች የሚወዱት ጓደኛቸው በእንቅልፍ ላይ እንደሚገኝና ወደፊት ዳግመኛ እንደሚያገኙት እርግጠኞች ናቸው። (ዮሐንስ 11:​11, 25) ያም ሆኖ ግን የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣቱ ከባድ ሐዘን ያስከትላል። የትዳር ጓደኛውን በሞት ያጣው ሰው የደረሰበትን ሐዘን መቋቋም የሚችለው እንዴት ነው? *

21 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸች አንዲት ሴት ያደረገችውን ነገር ማስታወሱ ይረዳል። ሐና ባሏ በሞት የተለያት በተጋቡ በሰባት ዓመት ውስጥ ነበር፤ ስለ እሷ የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በተጻፈ ጊዜ 84 ዓመት ሆኗት ነበር። ቧላን በሞት ስታጣ እጅግ እንዳዘነች ጥርጥር የለውም። ይህን ሐዘን የተቋቋመችው እንዴት ነው? ቀንና ሌሊት በቤተ መቅደሱ ለይሖዋ አምላክ ቅዱስ አገልግሎት ታቀርብ ነበር። (ሉቃስ 2:​36-38) ሐና ከልብ የመነጨ አገልግሎት በማቅረብ ያሳለፈችው ሕይወት መበለት መሆኗ ያስከተለባትን ሐዘንና የብቸኝነት ስሜት መቋቋም እንድትችል በጣም እንደረዳት ምንም አያጠራጥርም።

22. የትዳር ጓደኞቻቸውን በሞት ያጡ አንዳንዶች የብቸኝነትን ስሜት የተቋቋሙት እንዴት ነው?

22 “ከሁሉ ይበልጥ ፈታኝ ሆኖብኝ የነበረው ላጫውተው የምችል ጓደኛ ማጣቴ ነው” ስትል ከአሥር ዓመታት በፊት ባሏ በሞት የተለያት አንዲት የ72 ዓመት ሴት ገልጻለች። “ባሌ ጥሩ አዳማጭ ነበር። ስለ ጉባኤያችንና በክርስቲያናዊ አገልግሎት ስለምናደርገው ተሳትፎ እንጫወት ነበር።” አንዲት ሌላ መበለት ደግሞ እንዲህ ብላለች:- “ጊዜ እያለፈ መሄዱ ራሱ ሐዘኑን የሚያቀል ቢሆንም እንኳ አንድ ሰው ከሐዘኑ መላቀቅ እንዲችል ይበልጥ የሚረዳው ነገር ባለው ጊዜ ተጠቅሞ የሚያደርገው ነገር ነው የሚል እምነት አለኝ። ያላችሁበት ሁኔታ ሌሎችን ለመርዳት የተሻለ አጋጣሚ ይፈጥርላችኋል።” ሚስቱን በሞት ያጣ አንድ የ67 ዓመት ሰው ከዚህ አባባል ጋር የሚስማማ ሐሳብ ሰጥቷል:- “ሌሎችን ማጽናናት የደረሰባችሁን ሐዘን መቋቋም እንድትችሉ የሚረዳ ጥሩ መንገድ ነው።”

በእርጅና ዘመናችሁ አምላክ ከፍ አድርጎ ይመለከታችኋል

23, 24. መጽሐፍ ቅዱስ በዕድሜ ለገፉት፣ በተለይ ደግሞ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ላጡ ምን ትልቅ መጽናኛ ይሰጣል?

23 ሞት የምትወዱትን የትዳር ጓደኛ ሊነጥቃችሁ ቢችልም ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችሁ ነው። “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት” ሲል በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ንጉሥ ዳዊት ዘምሯል፤ “እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፣ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።”​—⁠መዝሙር 27:​4

24 ሐዋርያው ጳውሎስ “በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​3) ከዚህ መመሪያ ቀጥሎ ያለው ምክር እንደሚጠቁመው የቅርብ ዘመዶች ለሌላቸውና የሚገባቸው ሆነው ለተገኙ መበለቶች ጉባኤው ቁሳዊ እርዳታ ማድረግ ሊያስፈልገው ይችላል። ሆኖም “አክብር” የሚለው መመሪያ ትርጉም እነዚህን መበለቶች ከፍ አድርጎ መመልከትንም ይጨምራል። የትዳር ጓደኞቻቸውን በሞት ያጡ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸውና እንደሚደግፋቸው ማወቃቸው በጣም ሊያጽናናቸው ይችላል!​—⁠ያዕቆብ 1:​27

25. በዕድሜ የገፉ ሰዎች አሁንም ቢሆን ምን ግብ አላቸው?

25 “የሽማግሌዎችም ጌጥ ሽበት ነው” ሲል በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል ይናገራል። “በጽድቅ መንገድ ሲገኝ የውበት ዘውድ ነው።” (ምሳሌ 16:​31 NW20:​29) እንግዲያው ባለ ትዳሮችም ሆናችሁ ዳግመኛ ነጠላ የሆናችሁ የይሖዋን አገልግሎት በሕይወታችሁ ውስጥ ማስቀደማችሁን ቀጥሉ። በዚህ መንገድ በአምላክ ፊት ጥሩ ስም ታተርፋላችሁ፤ በተጨማሪም እርጅና የሚያስከትለው መከራ በማይኖርበት ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ይኖራችኋል።​—⁠መዝሙር 37:​3-5፤ ኢሳይያስ 65:​20

^ አን.20 በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይበልጥ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የምትወዱት ሰው ሲሞት የተባለውን ብሮሹር ተመልከቱ።