በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁለቱ ነገሥታት ማንነታቸውን ይለዋውጣሉ

ሁለቱ ነገሥታት ማንነታቸውን ይለዋውጣሉ

ምዕራፍ አሥራ አራት

ሁለቱ ነገሥታት ማንነታቸውን ይለዋውጣሉ

1, 2. (ሀ) አንታይከስ አራተኛ ለሮማውያኑ ጥያቄ እጅ እንዲነሣ ያደረገው ምንድን ነው? (ለ) ሶርያ የሮማ ክፍለ ግዛት የሆነችው መቼ ነው?

የሶርያው ንጉሠ ነገሥት አንታይከስ አራተኛ ግብጽን ወርሮ ከያዘ በኋላ ራሱን የግብጽ ንጉሥ አድርጎ ሰየመ። ሮም ደግሞ የግብጹ ንጉሥ ቶሌሚ ስድስተኛ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት አምባሳደር ካየስ ፖፒሊየስ ሊናስን ወደ ግብጽ ላከች። የሄደው ብቻውን አልነበረም፤ ታላቅ ሠራዊት አስከትሎና ከሮማ ሴኔት የተሰጠውን፣ አንታይከስ አራተኛ የግብጽ ንጉሥ ነኝ የሚለውን ሐሳቡን ትቶ አገሪቱን እንዲለቅ የሚያዝዘውን መልእክትም ይዞ ነበር። ከእስክንድርያ ወጣ ብላ በምትገኘው ኢሉሰስ የሶርያው ንጉሥና የሮማው አምባሳደር በግንባር ተገናኙ። አንታይከስ አራተኛ ጉዳዩን ከአማካሪዎቹ ጋር ይነጋገርበት ዘንድ ጊዜ እንዲሰጠው ጠየቀ። ይሁን እንጂ ሊናስ በአንታይከስ ዙሪያ ክብ መሥመር ሠራና ከዚያ ውስጥ ሳይወጣ መልስ እንዲሰጠው ጠየቀ። አንታይከስ አራተኛ ውርደቱን ተከናንቦ በሮማውያን ጥያቄ መሠረት በ168 ከዘአበ ወደ ሶርያ ተመለሰ። በዚህ መንገድ በሶርያው የሰሜን ንጉሥና በግብጹ የደቡብ ንጉሥ መካከል የነበረው ፍጥጫ አበቃ።

2 በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ ከፍተኛ ሚና መጫወት የጀመረችው ሮም በሶርያ ላይ ያላትን የበላይነት ማሳየቷን ቀጥላለች። በመሆኑም አንታይከስ አራተኛ በ163 ከዘአበ ከሞተም በኋላ በሰሉሲድ ሥርወ መንግሥት ዙፋን ተቀምጠው በሶርያ ያስተዳደሩ ሌሎች ነገሥታት ቢኖሩም ‘የሰሜን ንጉሥ’ ወደ መሆን ደረጃ አልደረሱም። (ዳንኤል 11:15) በመጨረሻም ሶርያ በ64 ከዘአበ የሮማ ክፍለ ግዛት ሆናለች።

3. ሮም በግብጽ ላይ የበላይነት የተቀዳጀችው መቼና እንዴት ነው?

3 የግብጽ ቶሌሚያዊ ሥርወ መንግሥት ከአንታይከስ አራተኛ ሞት በኋላ ከ130 ብዙም ለማይበልጡ ዓመታት ‘የደቡብ ንጉሥ’ ሆኖ ቀጥሏል። (ዳንኤል 11:14) በ31 ከዘአበ በአክቲየም በተደረገው ውጊያ የሮማ ገዥ የሆነው ኦክታቪየን የመጨረሻዋን ቶሌሚያዊ ሥርወ መንግሥት ንግሥት ክሊዮፓትራ ሰባተኛንና የሮማዊ ፍቅረኛዋን የማርክ አንቶኒን ጥምር ኃይል ድል አድርጓል። በቀጣዩ ዓመት ክሊዮፓትራ የገዛ ሕይወቷን ካጠፋች በኋላ ግብጽም በሮማ ግዛት ሥር ስለተጠቀለለች የደቡብ ንጉሥ በመሆን የምትጫወተው ሚና አክትሟል። በ30 ከዘአበ ሮም በሶርያም በግብጽም ላይ የበላይነት ተቀዳጅታ ነበር። ታዲያ ከዚህ በኋላ ሌሎች ገዥዎች የሰሜንና የደቡብ ንጉሥ ሆነው ይነሣሉ ብለን መጠበቅ ይኖርብናልን?

አንድ አዲስ ንጉሥ “አስገባሪ” ላከ

4. የሰሜን ንጉሥ ሆኖ ብቅ የሚል ሌላ ኃይል ይኖራል ብለን መጠበቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

4 በ33 እዘአ የበልግ ወራት ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ እንደሚከተለው ብሏቸው ነበር:- “በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኵሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፣ . . . በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ።” (ማቴዎስ 24:15, 16) ኢየሱስ ከዳንኤል 11:31 በመጥቀስ ተከታዮቹን ‘ጥፋት የሚያስከትል ርኩሰት’ እንደሚመጣ አስጠንቅቋቸዋል። ከሰሜኑ ንጉሥ ጋር የተያያዘው ይህ ትንቢት የተነገረው የሰሜን ንጉሥ የነበረው የመጨረሻው የሶርያ ንጉሥ አንታይከስ አራተኛ ከሞተ በኋላ 195 ዓመታት ገደማ ቆይቶ ነበር። የሰሜን ንጉሥ ሆኖ የሚነሳ ሌላ ኃይል እንደሚኖር ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ ይህ ማን ይሆን?

5. በአንድ ወቅት በአንታይከስ አራተኛ ተይዞ የነበረውን ቦታ በመረከብ የሰሜን ንጉሥ ሆኖ ብቅ ያለው ማን ነው?

5 የይሖዋ መልአክ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “የዚያን ጊዜም በመንግሥቱ ክብር [“በባለ ግርማው መንግሥቱ፣” NW] አስገባሪውን የሚያሳልፍ በስፍራው [በአንታይከስ አራተኛ ስፍራ] ይነሣል፤ ነገር ግን በቁጣው ሳይሆን በሰልፍም ሳይሆን በጥቂት ቀን ይሰበራል።” (ዳንኤል 11:20) በዚህ መልኩ ‘የተነሣው’ አውግስጦስ ቄሣር በመባል የሚታወቀው የመጀመሪያው የሮማ ንጉሠ ነገሥት ኦክታቪየን ነው።—“አንዱ የተከበረ ሌላው የተናቀ” የሚለውን በገጽ 248 ላይ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።

6. (ሀ) “አስገባሪ” ‘በባለ ግርማ መንግሥቱ’ እንዲያልፍ የተደረገው መቼ ነበር? ይህስ ምን ጠቀሜታ ነበረው? (ለ) አውግስጦስ የሞተው ‘በቁጣም በጦርነትም’ አይደለም ለማለት የሚቻለው ለምንድን ነው? (ሐ) የሰሜኑን ንጉሥ ማንነት በሚመለከት ምን ለውጥ ታይቷል?

6 የአውግስጦስ “ባለ ግርማ መንግሥት” ‘የጌጧን ምድር’ ማለትም የሮማ ክፍለ ግዛት የሆነችውን ይሁዳን ይጨምር ነበር። (ዳንኤል 11:16) በ2 ከዘአበ አውግስጦስ የሕዝብ ምዝገባ ወይም ቆጠራ እንዲካሄድ በማዘዝ “አስገባሪ” ላከ። ይህን ያደረገው ለቀረጥና ለወታደራዊ ምልመላ ይረዳው ዘንድ የሕዝቡን ቁጥር ለማወቅ ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ትእዛዝ መሠረት ዮሴፍና ማርያም ለመመዝገብ ወደ ቤተ ልሔም በመጓዛቸው ኢየሱስ በትንቢት በተነገረለት ቦታ ሊወለድ ችሏል። (ሚክያስ 5:2፤ ማቴዎስ 2:1-12) በ14 እዘአ ነሐሴ ወር ላይ “በጥቂት ቀን” ወይም በሌላ አባባል የምዝገባው ድንጋጌ ከወጣ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አውግስጦስ “በቁጣ” ማለትም በገዳዮች እጅ ወይም “በጦርነት” ሳይሆን እንዲሁ ታምሞ በ76 ዓመት ዕድሜው ሞተ። በእርግጥም የሰሜኑ ንጉሥ ማንነት ተቀይሮ ነበር! በዚህ ጊዜ ይህ የሰሜን ንጉሥ የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ነበር።

‘የተናቀ ሰው ተነሣ’

7, 8. (ሀ) በአውግስጦስ ፋንታ የሰሜን ንጉሥ ሆኖ የተነሣው ማን ነው? (ለ) በአውግስጦስ ቄሣር ዙፋን ለተቀመጠው ሰው “የመንግሥቱ ክብር የተሰጠው” አማራጭ ስለጠፋ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

7 መልአኩ ትንቢቱን ሲቀጥል እንዲህ ብሏል:- “በእርሱም [በአውግስጦስ] ስፍራ የተጠቃ [“የተናቀ፣” NW] ሰው ይነሣል የመንግሥቱንም ክብር አይሰጡትም፤ በቀስታ መጥቶ መንግሥቱን በማታለል ይገዛል። የሚጎርፍም ሠራዊት [“የጎርፉ ክንዶች፣” NW] ከፊቱ ይወሰዳል፣ እርሱና [ክንዱና] የቃል ኪዳኑ አለቃም ይሰበራሉ።”—ዳንኤል 11:21, 22

8 ‘የተናቀ’ የተባለው ከሳልሳዊ አውግስጦስ ሚስት ከሊቪየ የተወለደው ጢባርዮስ ቄሣር ነው። (በገጽ 248 ላይ የሚገኘውን “አንዱ የተከበረ ሌላው የተናቀ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) አውግስጦስ ይህን የእንጀራ ልጁን በባሕርይው ምክንያት ይጠላው ስለነበር ቀጣዩ ቄሣር እርሱ እንዲሆን አልፈለገም። ‘የመንግሥቱም ክብር’ የተሰጠው የዙፋኑ ወራሽ ሊሆኑ የሚችሉት በሙሉ ከሞቱ በኋላ አማራጭ ሲጠፋ ነው። አውግስጦስ ጢባርዮስን በልጅነት የተቀበለው በ4 እዘአ ሲሆን የዙፋኑ ወራሽ አድርጎታል። አውግስጦስ ከሞተ በኋላ ‘የተናቀው’ የ54 ዓመቱ ጢባርዮስ የሮማ ንጉሠ ነገሥትና የሰሜን ንጉሥ ሆኖ ‘ተነሣ።’

9. ጢባርዮስ ‘መንግሥቱን በማታለል የገዛው’ እንዴት ነው?

9 ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “ጢባርዮስ ከሴኔቱ ጋር የፖለቲካ ድብብቆሽ በመጫወት [አውግስጦስ ከሞተ በኋላ] አንድ ወር ለሚያክል ጊዜ ንጉሠ ነገሥት የሚለውን ስያሜ እንዳይሰጡት ሲከላከል ቆይቷል።” ከአውግስጦስ በቀር የሮማን ግዛት የማስተዳደሩን ኃላፊነት ሊሸከም የሚችል ሰው የለም በማለት ለሴኔቱ ያስረዳ ሲሆን ሴናተሮቹ እንዲህ ያለውን ሥልጣን ለአንድ ግለሰብ ከሚሰጡ ይልቅ ለሰዎች ቡድን ሰጥተው ሪፑብሊካዊ መንግሥት ተመልሶ እንዲመሠረት እንዲያደርጉ ጠይቋል። ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት እንዳሰፈሩት ከሆነ ሴኔቱ “እርሱ እንዳለው ለማድረግ ስለከበደው ጢባርዮስ ሥልጣኑን ለመቀበል እስኪስማማ ድረስ እጅ ነስቷል።” ዱራንት አክለው እንዲህ ብለዋል:- “ሁለቱም ወገኖች ጥሩ ተዋንያን ነበሩ። ጢባርዮስ ፕሪንሲፔቱን ይፈልገው ነበር ወይም ደግሞ ሌላ የሚያመልጥበት መንገድ አግኝቶ መሆን አለበት። ሴኔቱ [ጢባርዮስን] ይፈራውና ይጠላው የነበረ ቢሆንም እንደ ጥንቱ ሉዓላዊ ሥልጣን ባላቸው ምክር ቤቶች ላይ የተመሠረተ ሪፑብሊክ መልሶ ለማቋቋም አልደፈረም።” በዚህ መንገድ ጢባርዮስ ‘መንግሥቱን በማታለል ገዝቷል።’

10. ‘የጎርፉ ክንዶች’ የተሰበሩት እንዴት ነበር?

10 ‘የጎርፉ ክንዶች’ ማለትም የአካባቢውን መንግሥታት ወታደራዊ ኃይል በሚመለከት መልአኩ ‘ይወሰዳሉ፣ ይሰበራሉም’ ሲል ተናግሯል። ጢባርዮስ የሰሜን ንጉሥ በሆነ ጊዜ የወንድሙ ልጅ ጀርማኒከስ ቄሣር በራይን ወንዝ አካባቢ የሚገኘው የሮማ ሠራዊት አዛዥ ነበር። በ15 እዘአ ጀርማኒከስ ሠራዊቱን በጀርመኑ አርበኛ በአርሚኒየስ ላይ በማዝመት የተወሰነ ድል ተቀዳጅቶ ነበር። ይሁን እንጂ የተወሰኑትም ድሎች የተገኙት በብዙ መሥዋዕትነት ስለነበር ከዚያ ወዲህ ጢባርዮስ በጀርመን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አቆመ። ከዚህ ይልቅ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲጫር በማድረግ የጀርመን ጎሳዎች አንድ እንዳይሆኑ ለማድረግ ሞክሯል። ጢባርዮስ በጥቅሉ ሲታይ ይከተለው የነበረው የውጭ ፖሊሲ ራስን በመከላከልና ወሰንን በማጠናከር ላይ ያተኮረ ነበር። ይህ የውጭ ፖሊሲ በመጠኑም ቢሆን የተሳካ ነበር። በዚህ መንገድ ‘የጎርፉ ክንዶች’ ተገተው ማለትም ‘ተሰብረው’ ነበር።

11. ‘የቃል ኪዳኑ አለቃ የተሰበረው’ እንዴት ነው?

11 ይሖዋ አምላክ የምድርን ቤተሰብ በሙሉ ለመባረክ ከአብርሃም ጋር የገባው ‘ቃል ኪዳን አለቃም’ እንዲሁ ተሰብሯል። በዚያ ቃል ኪዳን ውስጥ ተስፋ የተሰጠበት የአብርሃም ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ዘፍጥረት 22:18፤ ገላትያ 3:16) ኢየሱስ ኒሳን 14 ቀን 33 እዘአ ኢየሩሳሌም በሚገኘው በሮማዊው ገዥ ቤተ መንግሥት ውስጥ በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት ቀርቦ ነበር። የአይሁድ ካህናት ኢየሱስ ንጉሠ ነገሥቱን ከድቷል በማለት ወነጀሉት። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለጲላጦስ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም፤ . . . መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” ሲል መልሶለታል። ሮማዊው ገዥ ምንም ጥፋት የሌለበትን ኢየሱስን በነፃ እንዲያሰናብተው ያልፈለጉት አይሁዳውያን ግን “ይህንስ ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው እያሉ ጮኹ።” ኢየሱስ እንዲገደል በመጠየቅ ከጮሁ በኋላ “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለዋል። ጢባርዮስ በቄሣር ላይ የሚሰነዘረውን ማንኛውንም ዓይነት ነቀፋ እንዲያካትት አድርጎ ባስፋፋው “ግርማዊነትን መጋፋት” በሚለው የሕግ አንቀጽ መሠረት ጲላጦስ፣ ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ‘እንዲሰበር’ ወይም እንዲገደል አሳልፎ ሰጥቶታል።—ዮሐንስ 18:36፤ 19:12-16፤ ማርቆስ 15:14-20

‘የራሱን መሠሪ ሐሳብ የሚፈጥር’ አምባገነን

12. (ሀ) ከጢባርዮስ ጋር ሕብረት የፈጠሩት እነማን ናቸው? (ለ) ጢባርዮስ በጥቂት ሕዝብ የበረታውስ እንዴት ነው?

12 መልአኩ አሁንም ስለ ጢባርዮስ ትንቢት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከእርሱም ጋር ከተወዳጀ [“ሕብረት ከፈጠረ፣” NW] በኋላ ተንኮል ያደርጋል፤ ከጥቂትም ሕዝብ ጋር ወጥቶ ይበረታል።” (ዳንኤል 11:23) የሮማ ሴኔት አባላት በሕገ መንግሥቱ አማካኝነት ከጢባርዮስ ጋር ‘ኅብረት ፈጥረው’ የነበረ ሲሆን እርሱም የሚደገፈው በእነርሱ ላይ ነበር። ይሁን እንጂ ‘በጥቂት ሕዝብ የበረታ’ አታላይ ነበር። ጥቂት ሕዝብ የተባለው በከተማዋ ቅጥር አቅራቢያ የሚገኘው የሮማ የክብር ዘበኛ ነው። ዘቡ ቅርብ መሆኑ ሴኔቱን ለማስፈራራት ያገለገለ ከመሆኑም ሌላ ጢባርዮስም በሥልጣኑ ላይ ከሕዝቡ መካከል የሚነሣውን ማንኛውንም ዓመፅ ለመቆጣጠር የሚያስችለው ነበር። በመሆኑም ጢባርዮስ 10,000 በሚያክሉት ዘቦች አማካኝነት ኃያል ሆኖ ቆይቷል።

13. ጢባርዮስ አባቶቹ ያላደረጉትን ነገር ያደረገው እንዴት ነው?

13 መልአኩ እንደሚከተለው ሲል ጨምሮ ተንብዮአል:- “በቀስታም ከአገር ሁሉ ወደ ለመለመችው ክፍል ይገባል፤ አባቶቹና የአባቶቹ አባቶች ያላደረጉትንም ያደርጋል፤ ብዝበዛውንና ምርኮውንም ሀብቱንም በመካከላቸው ይበትናል፤ በምሽጎችም ላይ እስከ ጊዜው ድረስ አሳቡን [“የራሱን መሠሪ ሐሳብ፣” NW] ይፈጥራል።” (ዳንኤል 11:24) ጢባርዮስ በጣም ተጠራጣሪ ሰው የነበረ ሲሆን በግዛቱም ወቅት ብዙ ሰዎችን በትእዛዝ አስገድሏል። የኋለኛው የግዛት ዘመኑ ሲጄነስ ከተባለው የክብር ዘበኛው አዛዥ ተጽዕኖ የተነሣ ሽብር የሞላበት ነበር። በመጨረሻው ሲጄነስ ራሱ በመጠርጠሩ እንዲገደል ተደርጓል። ጢባርዮስ ሕዝቡን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በመግዛት አባቶቹ ያላደረጉትን ነገር አድርጓል።

14. (ሀ) ጢባርዮስ ‘ብዝበዛውን፣ ምርኮውንና ሃብቱን’ በሮማ ክፍለ ግዛቶች የበተነው እንዴት ነው? (ለ) ጢባርዮስ ሲሞት ምን ዓይነት ስም አትርፎ ነበር?

14 ይሁን እንጂ ጢባርዮስ ‘ብዝበዛውን፣ ምርኮውንና ሃብቱን’ በመላው የሮማ ግዛት በትኗል። እርሱ በሞተበት ጊዜ ተገዥዎቹ በሙሉ ባለ ጠጎች ሆነው ነበር። የሚከፈለው ቀረጥ ቀላል የነበረ ሲሆን ችግር ላይ ለወደቁ አካባቢዎችም ልግስና ያሳይ ነበር። ወታደሮች ወይም ባለ ሥልጣኖች የጨቆኑት ሰው ካለ ወይም ሐቀኝነት የጎደለው ነገር አድርገው ከሆነ ንጉሠ ነገሥታዊ የበቀል እርምጃ ይጠብቃቸው ነበር። ሥልጣኑን ሙጭጭ አድርጎ መያዙ የሕዝብ መረጋጋት ለማስፈን ያስቻለ ሲሆን የተሻለ የመገናኛ ዘዴ መኖሩም ለንግዱ ሥርዓት እገዛ አድርጓል። ጢባርዮስ በሮም ውስጥም ሆነ ከሮም ውጭ ጉዳዮች አድሏዊነት በሌለበት መንገድ ያለ ችግር መከናወናቸውን ይከታተል ነበር። አውግስጦስ ቄሣር የጀመረውን ተሃድሶ እርሱም ስለገፋበት ሕጎቹ ተሻሽለውና ማኅበራዊና ሥነ ምግባራዊ ድንጋጌዎች ጎልብተው ነበር። ይሁንና ጢባርዮስ ‘የራሱን መሠሪ ሐሳብ የሚፈጥር’ በመሆኑ ታሲተስ የተባለው ሮማዊ ታሪክ ጸሐፊ ያልሆነውን ሆኖ የሚገኝ ግብዝ ሰው ነው ሲል ገልጾታል። ጢባርዮስ በ37 እዘአ መጋቢት ወር ሲሞት ያተረፈው ስም አምባገነን ሰው ነበረ የሚል ነው።

15. ሮም በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻና በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ነበረች?

15 የሰሜን ንጉሥ የመሆን ድርሻ ከነበራቸው የጢባርዮስ ዙፋን ወራሾች መካከል ጋየስ ቄሣር (ካሊጉላ)፣ ቀዳማዊ ቀላውዴዎስ፣ ኔሮ፣ ቬስፔዚየን፣ ቲቶ፣ ደሚሸን፣ ነርቨ፣ ትሬጀን እንዲሁም ሄድሪየን ይገኙበታል። ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ እንዳለው ከሆነ “በአውግስጦስ ዙፋን የተቀመጡት ባብዛኛው የእርሱን የአስተዳደር ፖሊሲዎችና የግንባታ ፕሮግራም ተከትለዋል። ይሁንና ካከናወኑት ነገር ይልቅ ጉራቸው ይብስ ነበር።” ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ ጨምሮ እንዲህ ይላል:- “በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻና በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የሮም ክብር ገንኖና የሕዝብ ብዛቷም በእጅጉ ጨምሮ ነበር።” በዚህ ወቅት ሮም በአንዳንድ የግዛት ድንበሮቿ በኩል ችግር የነበረባት ቢሆንም በትንቢት የተነገረው ከደቡብ ንጉሥ ጋር የምታደርገው የመጀመሪያ ፍጥጫ ግን እስከ ሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ ሳይከሰት ቆይቷል።

በደቡብ ንጉሥ ላይ ተነሣ

16, 17. (ሀ) በ⁠ዳንኤል 11:25 መሠረት የሰሜን ንጉሥ ሆኖ ብቅ ያለው ማን ነው? (ለ) የደቡብ ንጉሥ ሆኖ የተተካው ማን ነው? ይህስ የሆነው እንዴት ነው?

16 የአምላክ መልአክ እንደሚከተለው በማለት ትንቢቱን ይቀጥላል:- “[የሰሜን ንጉሥ] በታላቅም ሠራዊት ሆኖ ኃይሉንና ልቡን በደቡብ ንጉሥ ላይ ያስነሣል፤ የደቡብም ንጉሥ በታላቅና በብዙ ሠራዊት ሆኖ በሰልፍ ይዋጋል፤ ነገር ግን አሳብ በእርሱ [በሰሜን ንጉሥ] ላይ ይፈጥራሉና [“ያሴራሉና፣” NW] አይጸናም። መብሉንም የሚበሉ ሰዎች ይሰብሩታል፤ ሠራዊቱም ይጎርፋል [“በጎርፍ ይወሰዳል፣” NW]፤ ብዙዎችም ተገድለው ይወድቃሉ።”—ዳንኤል 11:25, 26

17 ኦክታቪየን ግብጽን የሮማ ግዛት አድርጎ ከጠቀለላት 300 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ የሮማው ንጉሠ ነገሥት ኦሬሊየን የሰሜን ንጉሥ ሆኖ ብቅ አለ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሮማ ቅኝ ግዛት በሆነው በፓልሚራ የነበረችው ንግሥት ሴፕቲሚያ ዘኖቢያ የደቡብ ንጉሥ ሆነች። * (በገጽ 252 ላይ የሚገኘውን “ዘኖቢያ—የፓልሚራዋ ጦረኛ ንግሥት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።) በ269 እዘአ የፓልሚራ ሠራዊት የሮማን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው በሚል ሽፋን ግብፅን ተቆጣጠረ። ዘኖቢያ ፓልሚራን በምሥራቅ ያለች ገናና ከተማ የማድረግና የሮምን ምሥራቃዊ ክፍለ ግዛት የማስተዳደር ምኞት ነበራት። ይህን ሐሳቧን የተረዳው ኦሬሊየን ‘ኃይሉንና ልቡን’ በዘኖቢያ ላይ አነሳ።

18. የሰሜን ንጉሥ በነበረው በንጉሠ ነገሥት ኦሬሊየንና የደቡብ ንጉሥ በሆነችው በንግሥት ዘኖቢያ መካከል የተፈጠረው ግጭት ውጤት ምን ነበር?

18 በዘኖቢያ የሚመራው ኃይል ማለትም የደቡብ ንጉሥ ዜብዳስና ዜባይ በሚባሉት ሁለት ጄኔራሎች አመራር “በታላቅና በብዙ ሠራዊት” በሰሜን ንጉሥ ላይ ለጦርነት ‘ተነሣ።’ ይሁን እንጂ ኦሬሊየን ግብጽን በመቆጣጠር ወደ ትንሿ እስያና ወደ ሶርያም ገሰገሰ። ዘኖቢያ ኤሜሳ (ዛሬ ሆመስ) ተብላ በምትጠራው ቦታ ድል ተነሥታ ወደ ፓልሚራ አፈገፈገች። ኦሬሊየን ከተማዋን በከበበ ጊዜ ዘኖቢያ በጀብደኝነት ብትጋፈጠውም ሳይሳካላት ቀረ። እርሷና ወንድ ልጅዋ ወደ ፋርስ ቢሸሹም ኤፍራጥስ ወንዝ ሲደርሱ የሮማ ወታደሮች ያዟቸው። በ272 እዘአ ፓልሚራውያኑ ከተማቸውን ለወራሪው ኃይል አስረከቡ። ኦሬሊየን ዘኖቢያን ከነሕይወቷ አስመጥቶ በ274 እዘአ በሮም የተካሄደው የድል ሰልፍ ማድመቂያ አድርጓታል። የቀረውን የሕይወት ዘመኗን የሮማ እመቤት ሆና አሳልፋለች።

19. ኦሬሊየን ‘በተፈጸመበት ሴራ’ የወደቀው እንዴት ነው?

19 ኦሬሊየን ራሱም ‘ሴራ ስለተፈጸመበት ሳይጸና ቀርቷል።’ በ275 እዘአ በፋርሳውያን ላይ ዘመቻ ማካሄድ ጀመረ። ወደ ትንሿ እስያ የሚያሻግረውን የባሕር ወሽመጥ ለማቋረጥ በትሬስ ተቀምጦ አመቺ አጋጣሚ ሲጠብቅ ሳለ ‘መብሉን የበሉ’ ሰዎች በወጠኑት ‘ሴራ ተሰብሯል።’ የእርሱ ጸሐፊ የነበረው ኤሮስ የእምነት ማጉደል ተግባር በመፈጸሙ ኦሬሊየን ሊቀጣው አስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ኤሮስ ሊገደሉ የታሰቡ ናቸው በሚል በሐሰት የባለ ሥልጣኖች ስም ዝርዝር አዘጋጀ። ባለ ሥልጣኖቹም ይህንን የስም ዝርዝር ሲያዩ ኦሬሊየንን የሚገድሉበትን ሴራ ጠነሰሱ።

20. የሰሜን ንጉሥ ‘ሠራዊት በጎርፍ የተወሰደው’ እንዴት ነው?

20 ንጉሠ ነገሥት ኦሬሊየን ሞተ ማለት ግን የሰሜኑ ንጉሥ ሚና አከተመ ማለት አልነበረም። ሌሎች የሮማ ነገሥታትም ተነሥተዋል። ለተወሰነ ጊዜ በምዕራቡ ክፍል አንድ ንጉሠ ነገሥት፣ በምሥራቁ ክፍል ደግሞ ሌላ ንጉሠ ነገሥት ተነሥቶ ነበር። በእነዚህ ሰዎች አማካኝነት የሰሜን ንጉሥ ‘ሠራዊት’ ‘በጎርፍ ተወስዷል’ ወይም ‘ተበታትኗል።’ * ብዙዎቹም ከሰሜን ከተነሱት የጀርመኒክ ጎሳዎች ወረራ የተነሣ ‘ተገድለው ወድቀዋል።’ ጎቶች በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ላይ የሮማን ድንበር ጥሰው ገቡ። ወረራው አንድ በአንድ ቀጠለ። በ476 እዘአ የጀርመኑ መሪ ኦደዌሰር በሮም ይገዛ የነበረውን የመጨረሻ ንጉሠ ነገሥት ከሥልጣን አባረረ። በስድስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በምዕራብ በኩል የነበረው የሮማ ግዛት ተንኮታኩቶ የነበረ ሲሆን የጀርመን ነገሥታትም በብሪታንያ፣ በጋውል፣ በኢጣሊያ፣ በሰሜን አፍሪካና በስፔይን ያስተዳድሩ ነበር። የምሥራቁ ግዛት እስከ 15ኛው መቶ ዘመን ድረስ ዘልቋል።

አንድ ትልቅ ግዛት ተከፋፈለ

21, 22. በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ቆስጠንጢኖስ ምን ለውጦች አድርጓል?

21 የይሖዋ መልአክ ለብዙ መቶ ዘመናት ስለዘለቀው የሮማ ግዛት አወዳደቅ አላስፈላጊ ዝርዝር ከመስጠት ይልቅ በቀጥታ የሰሜንና የደቡብ ንጉሥ ስለሚፈጽሟቸው ተጨማሪ ጀብዱዎች መዘርዘሩን ቀጥሏል። ይሁን እንጂ በሮማ ግዛት ውስጥ ስለተከናወኑት አንዳንድ ነገሮች በአጭሩ መመልከታችን በኋለኛው ዘመን የሚነሱትን ተቀናቃኝ ነገሥታት ለይተን ለማወቅ እንድንችል ይረዳናል።

22 በአራተኛው መቶ ዘመን የሮማው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ለከሃዲዋ ክርስትና መንግሥታዊ እውቅና ሰጠ። አልፎ ተርፎም በ325 እዘአ በትንሿ እስያ በምትገኘው በኒቂያ የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ እንዲካሄድ ከመጥራቱም ሌላ ጉባኤውን በሊቀ መንበርነት መርቷል። ከጊዜ በኋላ ቆስጠንጢኖስ ንጉሣዊ መኖሪያውን ከሮም ወደ ባይዛንቲየም ወይም ኮንስታንቲኖፕል በማዛወር ከተማዋን አዲሷ መዲናው አደረጋት። ቀዳማዊ ቲየዶሺየስ እስከሞተበት እስከ ጥር 17, 395 እዘአ ድረስ የሮማ ግዛት በአንድ ንጉሠ ነገሥት ብቻ ሲተዳደር ቆይቷል።

23. (ሀ) ከቲየዶሺየስ ሞት በኋላ የሮማ ግዛት የተከፋፈለው እንዴት ነው? (ለ) የምሥራቁ ግዛት ወደ ፍጻሜው የመጣው መቼ ነው? (ሐ) በ1517 ግብጽን የገዛት ማን ነበር?

23 ከቲየዶሺየስ ሞት በኋላ የሮማ ግዛት ለወንዶች ልጆቹ ተከፋፈለ። ኸኖሪየስ ምዕራባዊውን ክፍል ሲረከብ አርካዴስ ደግሞ ኮንስታንቲኖፕልን መዲናው በማድረግ ምሥራቃዊውን ክፍል ተረክቧል። ብሪታንያ፣ ጋውል፣ ኢጣሊያ፣ ስፔይንና ሰሜን አፍሪካ የምዕራባዊው ክፍል ግዛቶች ነበሩ። መቄዶንያ፣ ትሬስ፣ ትንሿ እስያ፣ ሶርያና ግብጽ ደግሞ የምሥራቃዊው ክፍል ግዛቶች ነበሩ። በ642 እዘአ የግብጻውያኑ መዲና እስክንድርያ በሳራሰኖች (አረቦች) እጅ ወደቀችና ግብጽ የካሊፎች መቀመጫ ሆነች። በጥር 1449 ቆስጠንጢኖስ አሥራ አንደኛ የመጨረሻው የምሥራቁ ክፍል ንጉሠ ነገሥት ሆነ። በዳግማዊ ሱልጣን ሜሜት የሚመሩት ኦቶማን ቱርኮች ግንቦት 29 ቀን 1453 ኮንስታንቲኖፕልን ሲቆጣጠሩ ምሥራቃዊው የሮማ ግዛት አከተመ። በ1517 ግብጽ የቱርክ ክፍለ ግዛት ሆነች። ይሁንና ከጊዜ በኋላ የጥንቱ የደቡብ ንጉሥ ግዛት የነበረው ይህ አካባቢ ከምዕራባዊው ክፍል በሚነሳ ሌላ ንጉሠ ነገሥት ቁጥጥር ሥር ይውላል።

24, 25. (ሀ) አንዳንድ የታሪክ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ የቅድስት ሮማ ግዛት የጀመረው እንዴት ነው? (ለ) “ንጉሠ ነገሥት” የሚለው የቅድስት ሮማ ግዛት ስያሜ በመጨረሻ ምን ሆኗል?

24 በሮማ ግዛት ምዕራባዊ ክንፍ የሮማ ካቶሊክ ጳጳሳት የተነሱ ሲሆን በተለይ በአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የጵጵስናን ሥልጣን እንደደነገጉ የሚነገርላቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቀዳማዊ ሊዮ አንዱ ናቸው። ቆየት ብሎም የምዕራባዊውን ክፍል ንጉሠ ነገሥታት መሾም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሥራ ሆነ። ይህም የሆነው በ800 እዘአ በተከበረው የገና በዓል ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሳልሳዊ ሊዮ ለአዲሱ ምዕራባዊ የሮማ ግዛት ንጉሠ ነገሥት ለፍራንካዊው ንጉሥ ቻርልስ (ሻርልማኝ) ዘውድ በጫኑለት ጊዜ ነበር። ይህ የዘውድ መጫን በዓል በሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ እንዲያንሠራራ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ አንዳንድ የታሪክ ሰዎች እንደሚሉት የቅድስት ሮማን ግዛት መጀመር የሚያበስር ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክርስቲያን ነን የሚሉት ሁለት ግዛቶች ማለትም ምሥራቃዊው የሮማ ግዛትና ምዕራባዊው የቅድስት ሮማ ግዛት ተመሥርተዋል።

25 ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በሻርልማኝ ዙፋን የተቀመጡት ሰዎች እንዳልተሳካላቸው በግልጽ ይስተዋል ነበር። የንጉሠ ነገሥቱ ወንበር ባዶ የነበረበትም ጊዜ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ የጀርመን ንጉሥ ቀዳማዊ ኦቶ የኢጣሊያን አብዛኛውን ሰሜናዊና መካከለኛ ክፍል ተቆጣጥሮ ነበር። ራሱን የኢጣሊያ ንጉሥ አድርጎ ሾመ። በየካቲት 2, 962 እዘአ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን አሥራ ሁለተኛ፣ ቀዳማዊ ኦቶን የቅድስት ሮማ ግዛት ንጉሠ ነገሥት አድርገው ዘውድ ደፉለት። የግዛቲቱ መዲና ጀርመን ስትሆን ንጉሠ ነገሥቶቹም እንደ አብዛኞቹ ተገዥዎቻቸው ጀርመናውያን ነበሩ። ከአምስት መቶ ዓመታት በኋላ የኦስትሪያው የሃፕስበርግ ሸንጎ “ንጉሠ ነገሥት” የሚለውን ስም ተቀብሎ በአብዛኛዎቹ የቅድስት ሮማ ግዛት ዘመን እንዲቀጥል አድርጓል።

ሁለቱ ነገሥታት እንደገና ጎላ ብለው መታየት ጀመሩ

26. (ሀ) የቅድስት ሮማን ግዛት ፍጻሜ በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል? (ለ) የሰሜን ንጉሥ ሆኖ ብቅ ያለው ማን ነው?

26 ቀዳማዊ ናፖሊዮን በ1805 በጀርመን ላይ ከተቀዳጀው ድል በኋላ ለቅድስት ሮማ ግዛት ሕልውና እውቅና በመንፈግ እንዳልነበረች አድርጓታል። ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ፍራንሲስ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛቱን ለመከላከል ባለመቻሉ ነሐሴ 6, 1806 የሮማ ንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣኑን በፈቃዱ ለቅቆ ወደ ብሔራዊ መስተዳድሩ በመግባት የኦስትሪያ ንጉሠ ነገሥት ሆነ። ከ1,006 ዓመታት በኋላ የሮማ ካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሳልሳዊ ሊዮና ፍራንካዊው ንጉሥ ሻርልማኝ የመሠረቱት የቅድስት ሮማ ግዛት ወደ ፍጻሜው መጥቷል። በ1870 ሮም ከቫቲካን ተለይታ የኢጣሊያ ንጉሣዊ መንግሥት መዲና ሆነች። በቀጣዩ ዓመት ቄሣር የሚል ስያሜ በተሰጠው በቪልሄልም የሚመራ አንድ የጀርመን ግዛት ተመሠረተ። በዚህ መንገድ የዘመናችን የሰሜን ንጉሥ የሆነችው ጀርመን ወደ ዓለም መድረክ ብቅ አለች።

27. (ሀ) ግብጽ በብሪታንያ ሞግዚትነት የምትተዳደር አገር የሆነችው እንዴት ነው? (ለ) የደቡብ ንጉሥ ሆኖ ብቅ ያለውስ ማን ነው?

27 ይሁን እንጂ የዘመናችን የደቡብ ንጉሥ ማን ነው? ብሪታንያ በ17ኛው መቶ ዘመን ንጉሠ ነገሥታዊ ሥልጣን እንደጨበጠች ታሪክ ያረጋግጣል። ቀዳማዊ ናፖሊዮን የብሪታንያን የንግድ መስመር ለመቁረጥ በማሰብ በ1798 ግብጽን ተቆጣጥሮ ነበር። ጦርነት ተቀሰቀሰና በግጭቱ መነሻ ላይ የደቡብ ንጉሥ ሆኖ ብቅ ያለው የብሪታንያና የኦቶማን ጥምረት ፈረንሳዮችን ከግብጽ አባረረ። በቀጣዩ መቶ ዘመንም ብሪታንያ በግብጽ ላይ ያላት ተጽዕኖ እየጨመረ ሄዶ ነበር። ከ1882 በኋላ ግብጽ የብሪታንያ ጥገኛ ሆና ነበር። አንደኛው የዓለም ጦርነት በ1914 ሲፈነዳ ግብጽ በቱርክ ሥር ሆና በኬዲቭ ወይም በእንደራሴ ትተዳደር ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ጦርነት ቱርክ ከጀርመን ጋር ከወገነች በኋላ ብሪታንያ የኬዲቩን ሥርዓት በማስወገድ ግብጽ በእንግሊዝ ሞግዚትነት እንድትተዳደር አደረገች። ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ ቀስ በቀስ የጠበቀ ትስስር በመመሥረት የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል ሆኑ። ሁለቱ ኃይሎች በጋራ የደቡብ ንጉሥ ሆነው ብቅ ብለዋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.17 “የሰሜን ንጉሥ” እና “የደቡብ ንጉሥ” የሚለው ስያሜ እንዲሁ የማዕረግ ስም ብቻ ስለሆነ የትኛውንም የሥልጣን ኃይል፣ ንጉሥ፣ ንግሥት ወይም የብሔራት ሕብረት ሊያመለክት ይችላል።

^ አን.20 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉምባለ ማጣቀሻ መጽሐፍ ቅዱስ በ⁠ዳንኤል 11:26 ሥር ያሰፈረውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።

ምን አስተውለሃል?

• የሰሜን ንጉሥ ሆኖ የተነሣው የመጀመሪያው የሮማ ንጉሠ ነገሥት ማን ነው? “አስገባሪ” የላከውስ መቼ ነው?

• ከአውግስጦስ ቀጥሎ የሰሜን ንጉሥ ሆኖ የተነሣው ማን ነው? ‘የቃል ኪዳኑ አለቃስ የተሰበረው’ እንዴት ነው?

• የሰሜን ንጉሥ በነበረው በኦሬሊየንና የደቡብ ንጉሥ በነበረችው ዘኖቢያ መካከል የተፈጠረው ግጭት ውጤት ምን ነበር?

• የሮማ ግዛት ምን ሆነ? በ19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይስ የሁለቱን ነገሥታት ቦታ የያዙት እነማን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ከገጽ 248-251 የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንዱ የተከበረ ሌላው የተናቀ

አንዱ፣ አምባጓሮ የነገሠባትን ሪፑብሊክ ገናና ግዛት እንድትሆን አብቅቷታል። ሌላው ደግሞ በ23 ዓመት ውስጥ ብልጽግናዋን በሃያ እጥፍ አሳድጎታል። አንደኛው በሞተ ጊዜ ሲከበር ሌላኛው ግን ተንቋል። የእነዚህ ሁለት የሮም ንጉሠ ነገሥቶች የግዛት ዘመን ከኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ጋር ተገጣጥሟል። እነዚህ ነገሥታት እነማን ነበሩ? አንዱ ሲከበር ሌላው ያልተከበረውስ ለምንድን ነው?

‘በሸክላ ተሠርታ ያገኛትን ሮም እብነ በረድ አደረጋት’

በ44 ከዘአበ ጁሊየስ ቄሣር ሲገደል የእህቱ የልጅ ልጅ ጋየስ ኦክታቪየን ዕድሜው ገና 18 ዓመት ነበር። ጁሊየስ ቄሣር እንደ ልጁ ተቀብሎ ስላሳደገውና ዋናው የግል ወራሹ እርሱ ስለነበር ወጣቱ ኦክታቪየን ውርሱን ለመጠየቅ ወዲያው ወደ ሮም አቀና። እዚያም ሲደርስ ዋነኛ ወራሽ እሆናለሁ ብሎ ያስብ የነበረውና የቄሣር የቅርብ ረዳት የነበረው የማርክ አንቶኒ ተቃውሞ ገጠመው። በዚህ ጊዜ ዋነኛ ተቀናቃኝ ሆኖበታል። ከዚህ ጊዜ የጀመረው ፖለቲካዊ ደባና የሥልጣን ሽኩቻ ለ13 ዓመታት ያህል ዘልቋል።

ኦክታቪየን ያላንዳች ተቀናቃኝ የሮማ ግዛት ገዥ ሆኖ ብቅ ያለው የግብጿን ንግሥት የክሊዮፓትራንና የፍቅረኛዋን የማርክ አንቶኒን ጥምር ኃይል (በ31 ከዘአበ) ድል ካደረገ በኋላ ነበር። በቀጣዩ ዓመት አንቶኒና ክሊዮፓትራ የገዛ ሕይወታቸውን በማጥፋታቸው ኦክታቪየን ግብጽን ተቆጣጠረ። በዚህ መንገድ የግሪካውያን ግዛት ርዝራዥ በመወገዱ ሮም የዓለም ኃይል ሆነች።

ጁሊየስ ቄሣር ሥልጣኑን በማን አለብኝነት መጠቀሙ ለሞት እንዳበቃው የተገነዘበው ኦክታቪየን ተመሳሳይ ስህተት ለመድገም አልፈለገም። ሪፑብሊካዊ አስተዳደር የሚናፍቁትን ሮማውያን ላለማስቆጣት ሲል ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛቱን በሪፑብሊክ መጋረጃ አስውቦ አቅርቦላቸዋል። “ንጉሥ” እና “አፄ” የሚሉትን ስያሜዎች አልቀበልም አለ። ይባስ ብሎ በሁሉም ክፍለ ግዛቶች ላይ ያለውን ሥልጣን ለሮማ ሴኔት በማስረከብ ሥልጣኑን ለመልቀቅ እንደሚፈልግ አሳወቀ። ይህ ዘዴው ሠርቶለታል። በአመስጋኝነት ስሜት የተዋጠው ሴኔት ኦክታቪየን በሥልጣኑ እንዲቀጥልና አንዳንዶቹ ግዛቶች በእርሱ ሥር እንዲቆዩ ወተወተ።

ከዚህም በተጨማሪ ጥር 16 ቀን 27 ከዘአበ ሴኔቱ ለኦክታቪየን “አውግስጦስ” የሚለውን ማዕረግ የሰጠው ሲሆን ትርጉሙም “የተከበረ፣ ቅዱስ” ማለት ነው። ኦክታቪየን ማዕረጉን ከመቀበሉም ሌላ አንዱ ወር በስሙ እንዲጠራ በማድረግ የነሐሴ [ኦገስት] ወር በጁሊየስ ቄሣር ስም ከተሰየመው የሐምሌ [ጁላይ] ወር ጋር እኩል ቀን እንዲኖረው ሲል ከየካቲት ወር አንድ ቀን ወስዷል። በዚህ መንገድ ኦክታቪየን የመጀመሪያው የሮማ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ አውግስጦስ ቄሣር ወይም “ነሐሴ [ኦገስት] አንድ” የሚል መጠሪያ አግኝቷል። ቆየት ብሎም “ፖንቲፌክስ ማክሲመስ” (ሊቀ ካህናት) የሚለውን የማዕረግ ስም ያገኘ ሲሆን ኢየሱስ በተወለደበት ዓመት በ2 ከዘአበ ሴኔቱ ፓተር ፓትሪ ማለትም “የአገሩ አባት” የሚል የማዕረግ ስም ሰጥቶታል።

በዚያው ዓመት “ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች . . . ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ።” (ሉቃስ 2:1-3) ከዚህ ትእዛዝ የተነሣ ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት በቤተ ልሔም ሊወለድ ችሏል።—ዳንኤል 11:20፤ ሚክያስ 5:2

የአውግስጦስ መስተዳድር በመጠኑም ቢሆን ሐቀኝነት የሰፈነበትና የተረጋጋ የገንዘብ ልውውጥ ያለበት ነበር። በተጨማሪም አውግስጦስ ውጤታማ የፖስታ አገልግሎት ዘርግቶና መንገዶችን እንዲሁም ድልድዮችን ሠርቶ ነበር። ሠራዊቱን እንደ አዲስ አዋቅሮ እንዲሁም ቋሚ የባሕር ኃይልና ፕሬቶሪያን ዘብ በመባል የሚታወቅ የንጉሠ ነገሥታት የክብር ዘበኛ አዋቅሮ ነበር። (ፊልጵስዩስ 1:13) በእርሱ ደጋፊነት እንደ ቨርጀል እና ሆረስ ያሉት ጸሐፊዎች ብቅ ብቅ ያሉ ሲሆን የቅርጻ ቅርጽ ባለ ሙያዎችም ዛሬ እንደ ክላሲካል ዘይቤ ተደርገው የሚታዩትን ድንቅ የጥበብ ሥራዎች አስተዋውቀዋል። አውግስጦስ፣ ጁሊየስ ቄሣር ሳይጨርሳቸው የቀራቸውን የግንባታ ሥራዎች አጠናቅቋል፤ እንዲሁም ብዙ ቤተ መቅደሶችን አድሷል። እርሱ ያስተዋወቀው ፓክስ ሮማና (“የሮማ ሰላም”) ከ200 ለሚበልጡ ዓመታት ዘልቋል። አውግስጦስ ነሐሴ 19 ቀን 14 እዘአ በ76 ዓመቱ ከሞተ በኋላ እንደ አምላክ ተመልኳል።

አውግስጦስ ‘በሸክላ ተሠርታ ያገኛትን ሮም እብነ በረድ እንዳደረጋት’ በጉራ ይናገር ነበር። ሮም በብጥብጥ ትታመስ ወደነበረችበት የቀድሞው የሪፑብሊክ ዘመን እንዳትመለስ ሲል ቀጣዩን ንጉሠ ነገሥት ሊያዘጋጀው አስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ዙፋኑን የሚወርሰውን ሰው ለማማረጥ የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ አልነበረውም። የነበሩት አንድ የእህቱ ልጅ፣ ሁለት የልጅ ልጆች፣ አንድ አማችና አንድ የእንጀራ ልጅ ሞተው ስለነበር የቀረው ወራሹ የእንጀራ ልጁ የሆነው ጢባርዮስ ብቻ ነበር።

‘የተናቀው ሰው’

አውግስጦስ ከሞተ ከአንድ ወር ከሚያንስ ጊዜ በኋላ የሮማው ሴኔት የ54 ዓመቱን ጢባርዮስ ንጉሠ ነገሥት አድርጎ ሰየመው። ጢባርዮስ በሕይወት እስከነበረበት እስከ 37 እዘአ ድረስ ገዝቷል። በመሆኑም በኢየሱስ ሕዝባዊ አገልግሎት ወቅት የነበረው ንጉሠ ነገሥት እርሱ ነው።

ጢባርዮስ እንደ አንድ ንጉሠ ነገሥት ጥሩም መጥፎም ጎኖች ነበሩት። ከነበሩት በጎ ጎኖች መካከል ገንዘብን ለቅንጦት የማዋል ጉጉት ያልነበረው መሆኑ ነው። ከዚህም የተነሣ ግዛቱ በልጽጎ የነበረ ሲሆን ከተፈጥሮ አደጋዎች እንዲሁም ከክፉ ጊዜ ለማገገም የሚረዳ ተቀማጭ ገንዘብም ነበረው። ጢባርዮስ ራሱን እንደማንኛውም ሰው ይቆጥር የነበረና ብዙ የክብር ማዕረጎችን ለመቀበል አለመፈለጉ የሚያስመሰግነው ነው። በጥቅሉ የንጉሠ ነገሥቱ አምልኮ ለአውግስጦስ እንጂ ለእርሱ እንዲሰጠው አልፈለገም። እንደ አውግስጦስና ጁሊየስ ቄሣር ወር በስሙ እንዲሰየም አላደረገም። ሌሎችም በዚያ መንገድ ክብር እንዲሰጡት አልፈለገም።

ይሁን እንጂ የጢባርዮስ መጥፎ ጎን ከበጎ ጎኑ ይበዛል። ከሌሎች ጋር በነበረው ግንኙነት ከልክ በላይ ተጠራጣሪና ግብዝ የነበረ ሲሆን ታሪኩ በትእዛዝ ባስገደላቸው ሰዎች ደም የተጨማለቀ ነው። ከእነዚህ መካከል ብዙ የቀድሞ ጓደኞቹም ይገኙበታል። የሌዝ ማዤስቴን (ግርማዊነትን የመጋፋት) ሕግ በማስፋፋት ሕዝብን የማሳመፅ ድርጊትን ብቻ ሳይሆን በግል የእርሱን ስም እንደማጥፋት የሚቆጠሩ ነገሮችን መናገርንም የሚያካትት እንዲሆን አድርጎታል። ምናልባትም አይሁዳውያን፣ ሮማዊው ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ኢየሱስን እንዲያስገድልላቸው ተጽዕኖ ያደረጉበት ከዚህ ሕግ ጥንካሬ የተነሣ ሊሆን ይችላል።—ዮሐንስ 19:12-16

ጢባርዮስ የክብር ዘበኛውን ያከማቸው በሮም ከከተማዋ ቅጥር በስተ ሰሜን በኩል በገነባው የተመሸገ የወታደር ሰፈር ነበር። የክብር ዘበኛው በዚያ መኖር ለሥልጣኑ ያሰጋው ለነበረው ሴኔት ማስፈራሪያ ሆኖ ከማገልገሉም ሌላ በሕዝቡ መካከል የሚነሳውን ማንኛውንም ዓይነት የዓመፅ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር አስችሏል። አንዱ የአንዱ ጆሮ ጠቢ እንዲሆን ያበረታታ የነበረ ሲሆን የኋለኛው የግዛት ዘመኑ ሽብር የነገሠበት ሆኖ ነበር።

ጢባርዮስ በሞተ ጊዜ አምባገነን ነበር የሚል ስም አትርፏል። በእርሱ ሞት ሮማውያን እጅግ ተደስተው የነበረ ሲሆን ሴኔቱም አምልኮ እንዳይሰጠው ከልክሏል። በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ‘የተናቀ ሰው የሰሜን ንጉሥ ሆኖ ይነሣል’ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት በጢባርዮስ ላይ ፍጻሜውን አግኝቷል።—ዳንኤል 11:15, 21

ምን አስተውለሃል?

• ኦክታቪየን የመጀመሪያው የሮማ ንጉሠ ነገሥት ሊሆን የበቃው እንዴት ነው?

• የአውግስጦስ መስተዳድር ስላከናወናቸው ነገሮች ምን ማለት ይቻላል?

• የጢባርዮስ ጥሩና መጥፎ ጎኖች ምን ነበሩ?

• ‘የተናቀ ሰው’ የተባለውን ግለሰብ በሚመለከት የተነገረው ትንቢት በጢባርዮስ ላይ የተፈጸመው እንዴት ነው?

[ሥዕል]

ጢባርዮስ

[ከገጽ 252-255 የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ዘኖቢያ—የፓልሚራዋ ጦረኛ ንግሥት

“መልኳ የቀይ ዳማ፣ . . . ጥርሶቿ እንደ በረዶ የነጡ፣ እንደ ኮከብ የሚያበሩ ጎላ ጎላ ያሉ ዓይኖች ያሏትና ማራኪ ባሕርይዎቿ ውበት የጨመሩላት ሴት ነበረች። ድምጿ ኃይለኛና የራሱ ቅላጼ ያለው ነበር። ብልህ አመራሯ በእውቀት የተደገፈ ነበር። የላቲንን ቋንቋ ታውቅ የነበረ ሲሆን የግሪክን፣ የሲሪያክንና የግብጽን ቋንቋዎች እኩል አቀላጥፋ ትናገር ነበር።” ታሪክ ጸሐፊው ኤድዋርድ ጊቦን ይህን ሁሉ ውዳሴ ያጎረፉት የሶርያዋ ከተማ የፓልሚራ ጦረኛ ንግሥት ለነበረችው ለዘኖቢያ ነው።

ባሏ የሮማን ግዛት ወክሎ በፋርሳውያን ላይ ባካሄደው የተሳካ ዘመቻ የተነሣ በ258 እዘአ የሮማ ቆንስላ ሆኖ የተሾመው ባላባቱ አዲናተስ ነበር። ከሁለት ዓመታት በኋላ አዲናተስ ከሮማው ንጉሠ ነገሥት ጋሌነስ፣ ኮሬክተር ቶቲየስ ኦሪየንቲስ (የምሥራቅ ክፍል ሁሉ ገዥ) የሚል ማዕረግ አግኝቷል። ይህ ማዕረግ የተሰጠው በፋርሱ ንጉሥ ሳፖር ላይ የተቀዳጀውን ድል ምክንያት በማድረግ ነበር። የኋላ ኋላም አዲናተስ ራሱን “የነገሥታት ንጉሥ” ብሎ ሰይሟል። የዘኖቢያ ድፍረትና ብልሃት ለአዲናተስ ስኬት ከፍተኛውን ሚና ሳይጫወት አልቀረም።

ዘኖቢያ ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ለመመሥረት የነበራት ጉጉት

አዲናተስ ስሙ እጅግ ገንኖ በነበረበት በ267 እዘአ ከአልጋ ወራሹ ጋር ተገደለ። ወንድ ልጁ ገና ትንሽ ስለነበር ዘኖቢያ የባሏን ቦታ ወሰደች። ውብ፣ ልበ ትልቅና የአስተዳደር ተሞክሮ ያካበተች እንዲሁም በርካታ ቋንቋዎችን አቀላጥፋ የምትናገር ስለነበረች የተገዥዎቿን አክብሮትና ድጋፍ ለማግኘት አልተቸገረችም። ዘኖቢያ ለትምህርት ፍቅር ስለነበራት ዙሪያዋን የተከበበችው በምሁራን ነበር። ከአማካሪዎቿ አንዱ “ሕያው ቤተ መጽሐፍትና ተንቀሳቃሽ ቤተ መዘክር” ነው እየተባለ የሚነገርለት የፍልስፍና ምሁርና ድንቅ ተናጋሪ የነበረው ካሺየስ ሎንጃይነስ ነበር። ጸሐፊው ሪቻርድ ስቶንማን ባዘጋጁት ፓልሚራ ኤንድ ኢትስ ኢምፓየር—ዘኖቢያስ ሪቮልት አጌንስት ሮም የተባለ መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “አዲናተስ ከሞተ በኋላ በነበሩት አምስት ዓመታት ውስጥ . . . ዘኖቢያ የምሥራቅ እመቤት ነች የሚለውን ሐሳብ በሕዝቧ አእምሮና ልብ ውስጥ መትከል ችላ ነበር።”

በዘኖቢያ ግዛት በአንደኛው ወገን የነበረው እርሷና ባሏ ያሽመደመዱት ፋርስ ሲሆን በሌላው ወገን ደግሞ እየፈራረሰ የነበረው ሮም ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ጄ ኤም ሮበርትስ በወቅቱ በሮማ ግዛት ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “ሦስተኛው መቶ ዘመን . . . ሮም በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ ድንበሯ በኩል ፍዳዋን የቆጠረችበት ዘመን ነበር፤ በውስጥ ደግሞ አዲስ የእርስ በርስ ጦርነትና የሥልጣን ሽኩቻ ተጀምሮ ነበር። ሃያ ሁለት ንጉሠ ነገሥታት (እገሌ ነን እያሉ የተነሡትን ሳይጨምር) ተፈራርቀዋል።” በሌላ በኩል ደግሞ የሶርያዋ እመቤት በግዛቷ ውስጥ የተደላደለች ፍጹም አፄያዊ መንግሥት ሆና ነበር። ስቶንማን እንደሚሉት “የሁለት ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛቶችን [የፋርስና የሮምን] የኃይል ሚዛን በመቆጣጠር ሁለቱንም የሚያንበረክክ ሦስተኛ ግዛት የማቋቋም ሕልም ነበራት።”

በ269 እዘአ የሮማን ግዛት የሚቀናቀን አስመሳይ መንግሥት በግብጽ በተነሣ ጊዜ ዘኖቢያ ንጉሣዊ ሥልጣኗን የምታስፋፋበት አመቺ አጋጣሚ አገኘች። የዘኖቢያ ሠራዊት በፍጥነት ወደ ግብጽ በመዝመት ዓማፂዎቹን ደምስሶ አገሪቱን ተቆጣጠረ። ዘኖቢያ ራሷን የግብጽ ንግሥት አድርጋ በመሰየም ስሟ ያለበት ሣንቲም አስቀረጸች። በዚህ ጊዜ የመንግሥቷ ግዛት ከአባይ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ሆነ። ዘኖቢያ “የደቡብ ንጉሥ” ሆና ብቅ ያለችው በዚህ ወቅት ነበር።—ዳንኤል 11:25, 26

የዘኖቢያ መዲና

ዘኖቢያ መዲናዋን ፓልሚራን ከሮማውያኑ ዓለም ታላላቅ ከተሞች ጋር እስክትወዳደር ድረስ እጅግ አጠናክራትና አስውባት ነበር። የነዋሪዎቿ ብዛት 150,000 ደርሶ እንደነበር ይገመታል። የሚያማምሩ ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ሕንጻዎች፣ ቤተ መቅደሶች፣ መናፈሻዎች፣ ዓምዶችና ሐውልቶች ዙሪያው 21 ኪሎ ሜትር በሚገመት ግንብ የተከበበችውን ከተማ ሞልተዋት ነበር። በዋናው አውራ ጎዳና ላይ እያንዳንዳቸው 15 ሜትር ርዝማኔ ያላቸው 1,500 የቆሮንቶስ ሰዎች የጥበብ ሥራዎች የሆኑ ዓምዶች ተሰልፈው ይታዩ ነበር። ከተማዋ ውስጥ የጀግኖችና የባለውለታ ባለጠጎች ሐውልት እንዲሁም ጉርድ ምስል በየቦታው ይገኝ ነበር። በ271 እዘአ ዘኖቢያ የራሷንና የሟቹን ባሏን ሐውልት አቁማለች።

በፓልሚራ ከሚገኙት እጅግ ድንቅ የሕንጻ ሥራዎች መካከል አንዱ የፀሐይ ቤተ መቅደስ ሲሆን የከተማዋ ጉልህ ሃይማኖታዊ ገጽታ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ዘኖቢያ ራሷ የነበራት አምልኮ ከፀሐይ አምላክ ጋር የተዛመደ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ በሦስተኛው መቶ ዘመን የነበረችው ሶርያ የብዙ ሃይማኖቶች ምድር ነበረች። በዘኖቢያ ግዛት ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች፣ አይሁዶች እንዲሁም ፀሐይንና ጨረቃን የሚያመልኩ ሰዎች ነበሩ። ስለ እነዚህ የተለያዩ አምልኮዎች የነበራት አመለካከት ምንድን ነው? ጸሐፊው ስቶንማን እንዲህ ብለዋል:- “አንዲት ብልህ ገዥ ሕዝቧ ይበጀኛል ያለውን ልማድ አትንቅም። . . . አማልክት . . . በአንድ ላይ ለፓልሚራ እንደወገኑ ተደርጎ ይታመን ነበር።” ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ዘኖቢያ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ረገድ ሆደ ሰፊ ነበረች።

ዘኖቢያ በማራኪ ስብዕናዋ የብዙዎችን አድናቆት አትርፋለች። ከሁሉ ይበልጥ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ግን በዳንኤል ትንቢት ውስጥ የተጠቀሰውን ፖለቲካዊ ኃይል በመወከል የተጫወተችው ሚና ነው። ይሁን እንጂ ግዛቷ ከአምስት ዓመት ለበለጠ ጊዜ አልዘለቀም። የሮማው ንጉሠ ነገሥት ኦሬሊየን በ272 እዘአ ፓልሚራን ድል በማድረግ ዳግም እንዳትጠገን አድርጎ በዘበዛት። ዘኖቢያ ግን ምሕረት አግኝታለች። አንድ የሮማ ሴናተር አግብታ የቀረውን የሕይወት ዘመኗን በጡረታ ሳታሳልፍ እንዳልቀረች ይገመታል።

ምን አስተውለሃል?

• ስለ ዘኖቢያ ምን ተብሏል?

• ዘኖቢያ የፈጸመቻቸው አንዳንዶቹ ጀብዱዎች ምንድን ናቸው?

• ዘኖቢያ ስለ ሃይማኖት የነበራት አመለካከት ምንድን ነው?

[ሥዕል]

ንግሥት ዘኖቢያ ለወታደሮቿ ንግግር ስታደርግ

[በገጽ 246 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]

በዳንኤል 11:20-26 ላይ የተጠቀሱት ነገሥታት

የሰሜን ንጉሥ የደቡብ ንጉሥ

ዳንኤል 11:20 አውግስጦስ

ዳንኤል 11:21-24 ጢባርዮስ

ዳንኤል 11:25, 26 ኦሬሊየን ንግሥት ዘኖቢያ

አስቀድሞ በትንቢት ለጀርመኒክና የአንግሎ አሜሪካን

የተነገረው የሮማ ግዛት የዓለም ኃይል አስከትላ

ግዛት መፈራረ ብቅ ላለችው ብሪታንያ

መነሣት ምክንያት ሆኗል

[ሥዕል]

ጢባርዮስ

[ሥዕል]

ኦሬሊየን

[ሥዕል]

የሻርልማኝ ሐውልት

[ሥዕል]

አውግስጦስ

[ሥዕል]

የ17ኛው መቶ ዘመን የብሪታንያ የጦር መርከብ

[በገጽ 230 ላይ የሚገኝ ባለሙሉ ገጽ ሥዕል]

[በገጽ 233 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አውግስጦስ

[በገጽ 234 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጢባርዮስ

[በገጽ 235 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አውግስጦስ ባወጣው ትእዛዝ መሠረት ዮሴፍና ማርያም ወደ ቤተ ልሔም ተጉዘዋል

[በገጽ 237 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በትንቢት በተነገረው መሠረት ኢየሱስ ‘ተሰብሯል’ በሌላ አባባል ሞቷል

[በገጽ 245 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1. ሻርልማኝ 2. ቀዳማዊ ናፖሊዮን 3. ቀዳማዊ ቪልሄልም 4. የጀርመን ወታደሮች በአንደኛው የዓለም ጦርነት