በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 3

“ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው”

“ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው”

1, 2. ነቢዩ ኢሳይያስ ምን ራእይ ተመለከተ? ይህስ ራእይ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

 ኢሳይያስ ከአምላክ የመጣ አንድ ራእይ በተመለከተ ጊዜ ከፍተኛ አድናቆትና አምላካዊ ፍርሃት አድሮበት ነበር። ራእዩ በእውን ያለ ነገር ይመስል ነበር! ኢሳይያስ በኋላ ላይ እንደጻፈው ይሖዋን ከፍ ባለ ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ‘አይቶታል።’ የልብሱም ዘርፍ በኢየሩሳሌም ያለውን ሰፊ ቤተ መቅደስ ሞልቶት ነበር።—ኢሳይያስ 6:1, 2

2 በተጨማሪም የቤተ መቅደሱ መሠረት እስኪናጋ ድረስ በከፍተኛ ድምፅ ያስተጋባው መዝሙር ኢሳይያስን በአድናቆትና በፍርሃት እንዲዋጥ አድርጎታል። ይህን መዝሙር ያሰሙት ሱራፌል የተባሉት ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው መላእክት ናቸው። እነዚህ ሱራፌል “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው። መላዋ ምድር በክብሩ ተሞልታለች” በማለት የይሖዋን ታላቅ ግርማ አስደሳች በሆነ ዜማ አስተጋብተዋል። (ኢሳይያስ 6:3, 4) ይሖዋ በቅድስናው አቻ የማይገኝለት በመሆኑ አጽንኦት ለመስጠት ሲባል “ቅዱስ” የሚለው ቃል በመዝሙሩ ውስጥ ሦስት ጊዜ መጠቀሱ የተገባ ነው። (ራእይ 4:8) የይሖዋ ቅድስና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ጎላ ተደርጎ ተጠቅሷል። ብዙ ጥቅሶች የይሖዋን ስም ‘ከቅድስና’ ጋር አያይዘው ይገልጹታል።

3. ብዙዎች ስለ ይሖዋ ቅድስና ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት ወደ እሱ ከመቅረብ ይልቅ እንዲርቁት ያደረጋቸው እንዴት ነው?

3 ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ይሖዋ ስለ ማንነቱ እንድናውቅ ከሚፈልጋቸው አስፈላጊ ነገሮች አንዱ ቅድስናው ነው። ይሁንና በዘመናችን ያሉ ብዙ ሰዎች፣ ቅድስና የሚለው ሐሳብ ራሱ ብዙም ደስ አይላቸውም። አንዳንዶች ቅድስናን ራስን ከማመጻደቅ ወይም ለታይታ ከሚደረግ ሃይማኖተኝነት ጋር ያያይዙታል። ስለ ራሳቸው አፍራሽ አመለካከት ያላቸው ሰዎች አምላክ ቅዱስ መሆኑ ወደ እሱ እንዲቀርቡ ከመጋበዝ ይልቅ ጭራሽ እንዲሸሹት ያደርጋቸዋል። ቅዱስ ወደ ሆነው አምላክ ለመቅረብ ጨርሶ ብቁ እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። ስለሆነም ቅድስናውን በመፍራት ብዙዎች ከአምላክ ይርቃሉ። የአምላክ ቅድስና ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚጋብዝ አቢይ ምክንያት ሆኖ ሳለ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚሰማቸው መሆኑ የሚያሳዝን ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠታችን በፊት እውነተኛ ቅድስና ምን ማለት እንደሆነ እንመርምር።

ቅድስና ምንድን ነው?

4, 5. (ሀ) “ቅድስና” ምን ማለት ነው? ምን ማለትስ አይደለም? (ለ) ይሖዋ “የተለየ” ነው ሊባል የሚችለው በምን ሁለት መንገዶች ነው?

4 አምላክ ቅዱስ ነው ሲባል ኩሩ ወይም ሌሎችን የሚንቅ ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም እነዚህን ባሕርያት ይጠላል። (ምሳሌ 16:5፤ ያዕቆብ 4:6) ታዲያ “ቅዱስ” የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ ይህ ቃል “የተለየ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የመጣ ነው። ከአምልኮ ጋር በተያያዘ “ቅዱስ” የሚለው ቃል ለተራ አገልግሎት እንዳይውል ተለይቶ ለአምላክ የተሰጠን ወይም የተቀደሰን ነገር ያመለክታል። በተጨማሪም ቅድስና፣ ንጹሕ መሆን የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ታዲያ ይሖዋ ቅዱስ ነው ሲባል ምን ማለት ነው? ራሱን ፍጽምና ከጎደላቸው ሰዎች ‘ይለያል’ ወይም ንጹሕ ከመሆኑ የተነሳ ራሱን ከእኛ ያርቃል ማለት ነው?

5 በፍጹም። “የእስራኤል ቅዱስ” ተብሎ የተጠራው ይሖዋ ሕዝቡ ኃጢአተኛ ቢሆንም እንኳ በመካከላቸው እንደሚኖር ገልጿል። (ኢሳይያስ 12:6፤ ሆሴዕ 11:9) ስለዚህ ይሖዋ ቅዱስ መሆኑ ከሰዎች እንዲርቅ አያደርገውም። ታዲያ ይሖዋ “የተለየ” ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ፣ እሱ ብቻ ሉዓላዊ ጌታ በመሆኑ ከፍጥረታት ሁሉ የተለየ ነው። ንጽሕናው እንከን የማይወጣለትና ወደር የማይገኝለት ነው። (መዝሙር 40:5፤ 83:18) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ይሖዋ ከየትኛውም የኃጢአት ድርጊት ጋር ንክኪ የለውም፤ ይህን ማወቃችን እምነት እንድንጥልበት የሚያደርግ ነው። ለምን?

6. ይሖዋ ከየትኛውም የኃጢአት ድርጊት ጋር ንክኪ የሌለው መሆኑ እምነት እንድንጥልበት ሊያደርገን የሚችለው ለምንድን ነው?

6 ዛሬ የምንኖረው እውነተኛ ቅድስና በጠፋበት ዓለም ውስጥ ነው። ከአምላክ የራቀው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ በኃጢአት የተበከለና ፍጽምና የጎደለው ነው። ሁላችንም በውስጣችን ካለው የኃጢአት ዝንባሌ ጋር መዋጋት አለብን። በተጨማሪም ማንኛችንም ብንሆን ከተዘናጋን በኃጢአት ልንሸነፍ እንችላለን። (ሮም 7:15-25፤ 1 ቆሮንቶስ 10:12) ይሖዋ ግን ከየትኛውም የኃጢአት ዝንባሌ ሙሉ በሙሉ ነፃ በመሆኑ ፈጽሞ በኃጢአት ሊሸነፍ አይችልም። ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ጥሩ አባት ነው እንድንል የሚያደርገን አንዱ ምክንያትም ይህ ነው፤ እሱ ሙሉ በሙሉ እምነት የሚጣልበት ነው። ይሖዋ ቅዱስ ስለሆነ እንደ አንድ ኃጢአተኛ ሰብዓዊ አባት የሥነ ምግባር አቋሙ ሊበላሽ ወይም ሊለወጥ ይችላል ብሎ ማሰብ ፈጽሞ የማይመስል ነው። ቅድስናው ከምንም ነገር በላይ አስተማማኝ በመሆኑ ለሕዝቡ ዋስትና ለመስጠት በቅድስናው የማለባቸው ጊዜያት አሉ። (አሞጽ 4:2) ታዲያ ይህ በአምላክ እንድንተማመን የሚያደርግ አይደለም?

7. ቅድስናን ከይሖዋ ነጥሎ ማየት አይቻልም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

7 ቅድስናን ከይሖዋ ነጥሎ ማየት አይቻልም። ይህ ምን ማለት ነው? ለምሳሌ ያህል “ሰው” እና “አለፍጽምና” የሚሉት ቃላት የማይነጣጠሉ ናቸው። ስለ ሰው ስናስብ አለፍጽምና የሚለው ቃል አብሮ ይታወሰናል። አለፍጽምና አብሮን ያለ በመሆኑ በምናደርገው ነገር ሁሉ ላይ ተጽዕኖ ያሳድርብናል። “ይሖዋ” እና “ቅዱስ” የሚሉት ቃላትም ተመሳሳይ የሆነ ትስስር አላቸው። ይሖዋ ቅድስናን የተላበሰ አምላክ ነው። ሁለንተናው ንጹሕና የጠራ ነው። “ቅዱስ” የሚለውን ቃል ጥልቅ ትርጉም ሳንረዳ ይሖዋን ልናውቀው አንችልም።

“ቅድስና የይሖዋ ነው”

8, 9. ይሖዋ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎችን በመጠኑም ቢሆን ቅዱስ እንዲሆኑ እንደሚረዳቸው የሚያሳየው ምንድን ነው?

8 ይሖዋ ቅድስናን የተላበሰ አምላክ በመሆኑ የቅድስና ምንጭ ነው ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ ይህን ባሕርይ ለራሱ ብቻ ይዞ አልተቀመጠም፤ ለሌሎችም በልግስና ሰጥቷል። ሌላው ቀርቶ በእሳት ከተያያዘው ቁጥቋጦ መካከል በአንድ መልአክ አማካኝነት ሙሴን ባነጋገረው ጊዜ በቁጥቋጦው ዙሪያ ያለው መሬት ጭምር ቅዱስ ሆኖ ነበር።—ዘፀአት 3:5

9 ታዲያ ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ቅዱስ ሊሆኑ ይችላሉ? አዎን፣ በይሖዋ እርዳታ በመጠኑም ቢሆን ቅዱስ ሊሆኑ ይችላሉ። አምላክ ለእስራኤላውያን “ቅዱስ ብሔር ትሆናላችሁ” ሲል ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘፀአት 19:6) ቅዱስና ንጹሕ የሆነ የአምልኮ ሥርዓት ሰጥቷቸዋል። ቅድስና በሙሴ ሕግ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጎላ ብሎ የተጠቀሰው ለዚህ ነው። እንዲያውም ሊቀ ካህናቱ “ቅድስና የይሖዋ ነው” የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት ወርቅ በጥምጥሙ ላይ ፊት ለፊት ያስር ነበር። ብርሃን ሲያርፍበት አንጸባርቆ የሚታየው ይህ ጽሑፍ ለሁሉም ይነበብ ነበር። (ዘፀአት 28:36) ስለዚህ በአምልኳቸውም ሆነ በአኗኗራቸው ከፍተኛ የሆነ የንጽሕናና የቅድስና መሥፈርት አሟልተው መገኘት ይጠበቅባቸው ነበር። ይሖዋ “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል” ብሏቸዋል። (ዘሌዋውያን 19:2) እስራኤላውያን ፍጹም ባይሆኑም አቅማቸው በፈቀደ መጠን የአምላክን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እስከጣሩ ድረስ በአንጻራዊ ሁኔታ ቅዱስ ተደርገው ሊቆጠሩ ይችሉ ነበር።

10. በጥንት እስራኤላውያንና በዙሪያቸው በነበሩት አሕዛብ መካከል ቅድስናን በተመለከተ ምን ልዩነት ነበር?

10 የእስራኤላውያንን አምልኮ በዙሪያቸው ከነበሩት ብሔራት አምልኮ ጋር በማነጻጸር፣ ቅድስና በእስራኤል አምልኮ ውስጥ ምን ያህል የጎላ ስፍራ እንደነበረው መረዳት ይቻላል። እነዚህ አረማዊ ብሔራት የሚያመልኩት በእውን የሌሉ እንዲሁም ጨካኝ፣ ስግብግብና ሴሰኛ ተደርገው የሚገለጹ የሐሰት አማልክትን ነው። አማልክቱ ሁሉ ነገራቸው የረከሰ ነበር። ለእነሱ የሚቀርበው አምልኮ፣ አምላኪዎቻቸውም እንዲሁ የረከሱ እንዲሆኑ አድርጓል። በዚህም ምክንያት ይሖዋ አገልጋዮቹን ከእነዚህ አረማዊ ብሔራትና ከረከሰ አምልኳቸው እንዲርቁ አስጠንቅቋቸዋል።—ዘሌዋውያን 18:24-28፤ 1 ነገሥት 11:1, 2

11. (ሀ) መላእክት (ለ) ሱራፌል (ሐ) ኢየሱስ የይሖዋ ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ቅዱስ እንደሆነ ያሳዩት እንዴት ነው?

11 ይሁንና የይሖዋ ምርጥ ሕዝብ የነበሩት የጥንቶቹ እስራኤላውያን ምንም ያህል ቢጥሩ የአምላክን ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ያህል ቅድስናውን በሚገባ ሊያንጸባርቁ አይችሉም። አምላክን በታማኝነት የሚያገለግሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክት “አእላፋት ቅዱሳን” ተብለው ተጠርተዋል። (ዘዳግም 33:2፤ ይሁዳ 14) እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት አንጸባራቂ የሆነውንና ጥርት ያለውን የአምላክ ቅድስና ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባርቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ ኢሳይያስ በራእይ የተመለከታቸውን ሱራፌል አስታውስ። እነዚህ ኃያል መንፈሳዊ ፍጥረታት ያሰሙት መዝሙር፣ የይሖዋን ቅድስና በመላው አጽናፈ ዓለም በማስተጋባት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ ያሳያል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት ሁሉ በላቀ ደረጃ የይሖዋን ቅድስና የሚያንጸባርቀው የአምላክ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ነው። ስለሆነም “የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ” ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው።—ዮሐንስ 6:68, 69

ቅዱስ ስም፣ ቅዱስ መንፈስ

12, 13. (ሀ) የአምላክ ስም ቅዱስ መባሉ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የአምላክ ስም ከነቀፋ ነፃ መሆን ያስፈለገው ለምንድን ነው?

12 ከቅድስና ጋር በተያያዘ ስለ አምላክ ስምስ ምን ማለት ይቻላል? በምዕራፍ 1 ላይ እንዳየነው ይህ ስም ተራ መጠሪያ ወይም ስያሜ አይደለም። ይሖዋን ከነሙሉ ባሕርያቱ የሚወክል ስም ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ‘ስም ቅዱስ’ እንደሆነ ይናገራል። (ኢሳይያስ 57:15) የሙሴ ሕግ የአምላክን ስም የሰደበ ሰው እንዲገደል ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 24:16) እንዲሁም ኢየሱስ ባስተማረው ጸሎት ላይ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” በማለት በመጀመሪያ የጠቀሰው የአምላክን ስም ቅድስና እንደሆነ ልብ በል። (ማቴዎስ 6:9) አንድን ነገር መቀደስ ማለት ቅዱስ ለሆነ ነገር ብቻ እንዲውል መለየትና ልዩ ክብር መስጠት ማለት ነው። ይሁንና የአምላክ ስም ቀድሞውንም ቢሆን ቅዱስ ሆኖ ሳለ መቀደስ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

13 በአምላክ ላይ የተነዛው የሐሰት ወሬ ቅዱስ ስሙን አጉድፎታል። ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ የተናገረው ውሸት፣ ይሖዋ ጨቋኝ ገዢ ነው የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ነው። (ዘፍጥረት 3:1-5) የዚህ የረከሰ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አምላክን በተመለከተ ብዙ የሐሰት ወሬ እንዲነዛ አድርጓል። (ዮሐንስ 8:44፤ 12:31፤ ራእይ 12:9) የተለያዩ ሃይማኖቶች አምላክን አምባገነን፣ የማይቀረብ ወይም ጨካኝ እንደሆነ አድርገው ይገልጹታል። በሚያካሂዷቸው ደም አፋሳሽ ጦርነቶች አምላክ እንደሚደግፋቸው ይናገራሉ። የአምላክ ድንቅ የፍጥረት ሥራዎች በአጋጣሚ እንደተገኙ ወይም በዝግመተ ለውጥ እንደመጡ የሚናገሩም አሉ። በእርግጥም የይሖዋ ስም ክፉኛ ጎድፏል። ስሙ መቀደስና የቀድሞ ክብሩን መጎናጸፍ አለበት። ይሖዋ በስሙ ላይ የተሰነዘረውን ነቀፋ በማያዳግም መንገድ የሚያስወግድበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። ይህን የሚያደርገው በልጁ በሚመራው መንግሥት አማካኝነት ነው። በዚህ ታላቅ የይሖዋ ዓላማ ውስጥ የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት እንፈልጋለን።

14. የአምላክ መንፈስ፣ ቅዱስ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? መንፈስ ቅዱስን መሳደብ ይህን ያህል ከባድ ኃጢአት የሆነውስ ለምንድን ነው?

14 አብዛኛውን ጊዜ ቅዱስ እየተባለ የሚጠራ ከይሖዋ ተነጥሎ የማይታይ አንድ ሌላም ነገር አለ። ይህም የይሖዋ መንፈስ ወይም በሥራ ላይ ያለው ኃይሉ ነው። (ዘፍጥረት 1:2) ይሖዋ በማንም ወይም በምንም የማይበገረውን ይህን ኃይሉን ዓላማውን ለማስፈጸም ይጠቀምበታል። አምላክ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው ቅዱስና ንጹሕ በሆነ መንገድ ስለሆነ ይህ ኃይሉ፣ መንፈስ ቅዱስ ወይም የቅድስና መንፈስ ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው። (ሉቃስ 11:13፤ ሮም 1:4 አ.መ.ት) መንፈስ ቅዱስን መሳደብ የይሖዋን ዓላማ ሆን ብሎ እንደ መጻረር ስለሚቆጠር እንዲህ ያለው ኃጢአት ስርየት የለውም።—ማርቆስ 3:29

የይሖዋ ቅድስና ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚገፋፋን ለምንድን ነው?

15. የይሖዋ ቅድስና እሱን እንድንፈራው ሊያደርገን የሚገባው ለምንድን ነው? ይህ ፍርሃት ከምን የሚመነጭ ነው?

15 እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ቅድስና አምላክን ከመፍራት ጋር አያይዞ የሚገልጸው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግተንም። ለምሳሌ ያህል መዝሙር 99:3 “ሕዝቦች ታላቅ ስምህን ያወድሱ፤ ስምህ እጅግ የሚፈራና ቅዱስ ነውና” ይላል። ይህ ፍርሃት ከጥልቅ አክብሮትና አድናቆት የሚመነጭ ነው። የይሖዋ ቅድስና ከእኛ እጅግ የላቀ በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ፍርሃት ሊሰማን ይገባል። ይህ ቅድስና በጣም የጠራና ታላቅ ክብር የተላበሰ ቢሆንም ይሖዋን ፈርተን እንድንርቀው ሊያደርገን አይገባም። እንዲያውም ስለ አምላክ ቅድስና ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘታችን ወደ እሱ እንድንቀርብ ይገፋፋናል። ለምን?

16. (ሀ) ቅድስና ከክብር ወይም ከውበት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) ስለ ይሖዋ የሚገልጹ ራእዮች ንጽሕናንና ብርሃንን ጎላ አድርገው የሚገልጹት እንዴት ነው?

16 በመጀመሪያ ደረጃ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ቅድስናን ከውበት ጋር ያዛምደዋል። ኢሳይያስ 63:15 በሰማይ ስላለው የአምላክ መኖሪያ ሲናገር ‘ከፍ ያለው የቅድስናና የክብር [ወይም “የውበት፣” የግርጌ ማስታወሻ] መኖሪያህ’ ይላል። ክብር የተላበሱና ውብ የሆኑ ነገሮች ይማርኩናል። ለምሳሌ ያህል በገጽ 33 ላይ የሚገኘውን ምስል ተመልከት። ይህ ቦታ አያምርም? እንዲህ ማራኪ እንዲሆን ያደረገው ነገር ምንድን ነው? ውኃው እንዴት ኩልል ያለ እንደሆነ ተመልከት። ሰማዩ ጥርት ያለና ብሩህ ስለሆነ አየሩም ንጹሕ መሆን አለበት። ጅረቱ የተበከለ፣ አካባቢው በቆሻሻ የተሞላና አየሩ በጭስ የተመረዘ ቢሆን ኖሮ ይህ ቦታ እንደማይማርከን የታወቀ ነው፤ ጭራሽ እዚያ አካባቢ መድረስ እንኳ ይቀፈናል። ብዙውን ጊዜ አንድ ነገር ንጹሕ፣ ጥርት ያለና ብሩህ ከሆነ ውብ ሆኖ ይታየናል። እነዚሁ ነገሮች የይሖዋን ቅድስናም ለመግለጽ ሊያገለግሉ ይችላሉ። ስለ ይሖዋ የሚገልጹ ራእዮች እጅግ የሚመስጡን ለዚህ ነው። የቅዱሱ አምላካችን ክብር ወይም ውበት ብርሃን የሚፈነጥቅ፣ እንደ ከበሩ ድንጋዮች የሚያብረቀርቅ፣ እንደ ውድ ማዕድናት የሚያንጸባርቅና እንደ እሳት የደመቀ ነው።—ሕዝቅኤል 1:25-28፤ ራእይ 4:2, 3

እንደ ውበት ሁሉ ቅድስናም ሰውን የመማረክ ኃይል አለው

17, 18. (ሀ) ኢሳይያስ ያየው ራእይ መጀመሪያ ላይ ምን ስሜት አሳደረበት? (ለ) ይሖዋ በአንድ መልአክ አማካኝነት ኢሳይያስን ያጽናናው እንዴት ነው? መልአኩ ያደረገው ነገርስ ምን ትርጉም አለው?

17 ይሁን እንጂ አምላክ ቅዱስ መሆኑ ራሳችንን ዝቅ አድርገን እንድንመለከት ሊያደርገን ይገባል? አዎን፣ በሚገባ። ከይሖዋ አንጻር ስንታይ እዚህ ግቡ የምንባል አይደለንም፤ ይህ አሌ የማይባል ሐቅ ነው። ታዲያ ይህን መገንዘባችን ከእሱ እንድንርቅ ያደርገናል? ሱራፌል የይሖዋን ቅድስና ባወጁበት ጊዜ ኢሳይያስ ምን ተሰምቶት እንደነበር ተመልከት። “በዚህ ጊዜ እንዲህ አልኩ፦ ‘ወዮልኝ! ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው ስለሆንኩና የምኖረውም ከንፈራቸው በረከሰ ሕዝብ መካከል ስለሆነ በቃ መሞቴ ነው፤ ዓይኖቼ ንጉሡን፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ራሱን አይተዋልና!’” (ኢሳይያስ 6:5) አዎን፣ ወደር የሌለው የይሖዋ ቅድስና ኢሳይያስ ምን ያህል ኃጢአተኛና ከፍጽምና የራቀ መሆኑን እንዲያስብ አድርጎታል። ይህ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ መጀመሪያ ላይ የተስፋ መቁረጥ ስሜት አድሮበት ነበር። ይሁንና ይሖዋ ዝም ብሎ አልተመለከተውም።

18 ከሱራፌል አንዱ ወዲያውኑ እየበረረ መጥቶ ነቢዩን አጽናናው። እንዴት? መልአኩ ከመሠዊያው ላይ ፍም ወስዶ የኢሳይያስን ከንፈር በፍሙ ነካው። ‘ታዲያ ይህ ያቃጥለዋል እንጂ እንዴት ያጽናናዋል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው ራእይ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብሃል። ታማኝ አይሁዳዊ የነበረው ኢሳይያስ የኃጢአት ስርየት ለማግኘት በቤተ መቅደሱ መሠዊያ ላይ በየዕለቱ መሥዋዕቶች እንደሚቀርቡ ያውቃል። መልአኩ ቀጥሎ ለነቢዩ አንድ የሚያጽናና ሐሳብ ነገረው። ፍጽምና የጎደለውና ‘ከንፈሮቹ የረከሱ’ a ቢሆንም እንኳ በአንጻራዊ ሁኔታም ቢሆን ይሖዋ እሱን ንጹሕ ወይም ቅዱስ አድርጎ ለመመልከት ፈቃደኛ እንደሆነ ገለጸለት።—ኢሳይያስ 6:6, 7

19. ፍጹማን ባንሆንም እንኳ በአንጻራዊ ሁኔታ ቅዱስ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

19 ይሖዋ ዛሬ ላለነው ለእኛም ተመሳሳይ ነገር ያደርግልናል። በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች በሙሉ ኢየሱስ በ33 ዓ.ም. ላቀረበው ከሁሉ የላቀ ፍጹም መሥዋዕት ጥላ ነበሩ። (ዕብራውያን 9:11-14) ከልብ ንስሐ ገብተን ከተሳሳተ ጎዳና ከተመለስንና በዚህ መሥዋዕት ካመንን ምሕረት እናገኛለን። (1 ዮሐንስ 2:2) እንዲህ ካደረግን አምላክ እኛንም ንጹሕ አድርጎ ሊመለከተን ፈቃደኛ ነው። በመሆኑም ሐዋርያው ጴጥሮስ “‘እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል አሳስቦናል። (1 ጴጥሮስ 1:16) ይሁን እንጂ ይሖዋ የእኔን ያህል ቅዱስ መሆን አለባችሁ እንዳላለ ልብ በል። ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም። (መዝሙር 103:13, 14) ከዚህ ይልቅ እሱ ቅዱስ ስለሆነ እኛም ቅዱስ እንድንሆን እየነገረን ነው። ፍጹማን ባንሆንም እንኳ አቅማችን የሚፈቅደውን ያህል፣ ‘እንደተወደዱ ልጆች’ እሱን ለመምሰል እንጥራለን። (ኤፌሶን 5:1) ስለዚህ ቅድስና በአንድ ጀምበር የሚገኝ ሳይሆን ቀስ በቀስ የምናዳብረው ባሕርይ ነው። በመንፈሳዊ እድገት የምናደርግ ከሆነ ከዕለት ወደ ዕለት “ቅድስናችንን ፍጹም” እያደረግን እንሄዳለን።—2 ቆሮንቶስ 7:1

20. (ሀ) በቅዱሱ አምላካችን ዓይን ንጹሕ መሆን እንደምንችል ማወቃችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኢሳይያስ ኃጢአቱ እንደተሰረየለት ማወቁ በአመለካከቱ ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል?

20 ይሖዋ ንጹሕና ጽድቅ የሆነውን ነገር ይወድዳል። በአንጻሩ ደግሞ ኃጢአትን ይጠላል። (ዕንባቆም 1:13) ይሁን እንጂ እኛን አይጠላንም። ይሖዋ ለኃጢአት ያለውን አመለካከት በመኮረጅ ክፉውን የምንጠላና መልካሙን የምንወድድ እንዲሁም ፍጹም የሆነውን የክርስቶስ ኢየሱስን ፈለግ ለመከተል የምንጥር ከሆነ ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል። (አሞጽ 5:15፤ 1 ጴጥሮስ 2:21) በቅዱሱ አምላካችን ዓይን ንጹሕ መሆን እንደምንችል መገንዘባችን በአመለካከታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ኢሳይያስ የይሖዋን ቅድስና ሲያይ የእሱ ኃጢአት ጎልቶ እንደታየው አስታውስ። “ወዮልኝ!” በማለት የተሰማውን ስሜት ገልጿል። ይሁንና ኃጢአቱ እንደተሰረየለት ሲያውቅ አመለካከቱ ተለወጠ። ይሖዋ አንድ ተልእኮ የሚያከናውንለት ፈቃደኛ ሰው በፈለገ ጊዜ ኢሳይያስ ተልእኮው ምን እንደሆነ ባያውቅም እንኳ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ!” በማለት ለዚህ ሥራ ዝግጁ መሆኑን ወዲያውኑ ገልጿል።—ኢሳይያስ 6:5-8

21. የቅድስናን ባሕርይ የማዳበር ችሎታ እንዳለን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

21 ቅዱስ በሆነው አምላክ አምሳያ የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን የእሱን ባሕርያት የማንጸባረቅና መንፈሳዊ ነገሮችን የመፈለግ ችሎታ ተሰጥቶናል። (ዘፍጥረት 1:26) በመሆኑም ሁላችንም ቅድስናን የማንጸባረቅ ችሎታ አለን። የቅድስናን ባሕርይ ለማዳበር በምናደርገው ጥረት ይሖዋ እኛን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። እንዲህ ስናደርግ ወደ ቅዱሱ አምላካችን ይበልጥ እየቀረብን እንሄዳለን። ከዚህም በተጨማሪ በሚቀጥሉት ምዕራፎች ላይ የይሖዋን ባሕርያት በምንመረምርበት ጊዜ ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚገፋፉ በርካታ አሳማኝ ምክንያቶች እናገኛለን!

a ከንፈር ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌያዊ ሁኔታ ንግግርን ወይም ቋንቋን ለማመልከት ስለሚሠራበት “ከንፈሮቼ የረከሱ” የሚለው አገላለጽ ተስማሚ ነው። ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ኃጢአት የሚሠሩት በአንደበት አጠቃቀማቸው ነው።—ምሳሌ 10:19፤ ያዕቆብ 3:2, 6