በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 4

‘ይሖዋ ኃይሉ ታላቅ ነው’

‘ይሖዋ ኃይሉ ታላቅ ነው’

1, 2. ኤልያስ በተለያዩ ጊዜያት ምን አስገራሚ ነገሮች አይቷል? ይሁን እንጂ በኮሬብ ተራራ በሚገኝ ዋሻ ውስጥ ሳለ የተመለከተው ይበልጥ አስደናቂ የሆነ ክስተት ምንድን ነው?

 ኤልያስ ከዚህ ቀደም ብዙ አስገራሚ ነገሮችን ተመልክቷል። በአንድ ሸለቆ ውስጥ ተደብቆ በነበረበት ወቅት ቁራዎች በቀን ሁለት ጊዜ መግበውታል። ለረጅም ጊዜ በዘለቀው ረሃብ ወቅት በማድጋው ውስጥ የነበረው ትንሽ ዱቄትና በማሰሮው ውስጥ የነበረው ጥቂት ዘይት ለዚያን ያህል ጊዜ መበርከቱ የሚያስገርም ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ወደ ይሖዋ በመጸለይ እሳት ከሰማይ እንዲወርድ ማድረግ ችሏል። (1 ነገሥት ምዕራፍ 17, 18) ይሁንና ኤልያስ ከእነዚህ ሁሉ ይበልጥ አስገራሚ የሆነ አንድ ሌላ ነገር ተመልክቷል።

2 በኮሬብ ተራራ በሚገኝ አንድ ዋሻ መግቢያ ላይ ተሸሽጎ ሳለ አስገራሚ ክስተቶችን ተመለከተ። በመጀመሪያ ጆሮ የሚያደነቁር ኃይለኛ ድምፅ ያለው ነፋስ ነፈሰ። ይህ ነፋስ እጅግ ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ተራሮቹ ተሰነጣጠቁ እንዲሁም ዓለቶቹ ተሰባበሩ። ከዚያም ከፍተኛ የምድር መናወጥ ሆነ። በመጨረሻም እሳት ነደደ። እሳቱ አካባቢውን ሲያቃጥለው ወላፈኑ ኤልያስንም ገርፎት ሊሆን ይችላል።—1 ነገሥት 19:8-12

3. ኤልያስ ያያቸው ክስተቶች የትኛውን የአምላክ ባሕርይ የሚያንጸባርቁ ናቸው? ይህ ባሕርይ የተገለጸበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?

3 ኤልያስ ያያቸው እነዚህ ክስተቶች አንድ የጋራ ባሕርይ አላቸው፤ ሁሉም የይሖዋን ታላቅ ኃይል የሚያንጸባርቁ ናቸው። እርግጥ ነው፣ አምላክ ይህ ባሕርይ እንዳለው ለማወቅ ተአምር ማየት ያስፈልገናል ማለት አይደለም። ፍጥረት ራሱ የይሖዋ ‘ዘላለማዊ ኃይልና አምላክነት’ መግለጫ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሮም 1:20) ኃይለኛ ነጎድጓድና የመብረቅ ብልጭታ፣ ግርማ ሞገስ የተላበሰ ፏፏቴ እንዲሁም በከዋክብት የተሞላ የተንጣለለ ሰማይ ስትመለከት አምላክ ምን ያህል ታላቅ ኃይል እንዳለው አትገነዘብም? ይሁን እንጂ ዛሬ ብዙዎች ይህን የአምላክ ኃይል አያስተውሉም። የሚያስተውሉ ቢኖሩም ደግሞ ትክክለኛ ግንዛቤ ያላቸው ጥቂቶች ናቸው። ይህን መለኮታዊ ባሕርይ በትክክል መገንዘባችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ያደርገናል። በዚህ በክፍል አንድ ላይ፣ አቻ የማይገኝለትን የይሖዋ ኃይል በጥልቀት እንመረምራለን።

“ይሖዋ እያለፈ ነበር”

መሠረታዊ የሆነ የይሖዋ ባሕርይ

4, 5. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ስም ምን ይላል? (ለ) ይሖዋ ኃይሉን ለመግለጽ በሬን እንደ ምሳሌ አድርጎ መጠቀሙ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?

4 ይሖዋ አቻ የማይገኝለት ኃይል አለው። ኤርምያስ 10:6 “ይሖዋ ሆይ፣ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም። አንተ ታላቅ ነህ፤ ስምህም ታላቅና ኃያል ነው” ይላል። የይሖዋ ስም፣ ታላቅና ኃያል ተብሎ እንደተገለጸ ልብ በል። ይህ ስም ደግሞ “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም እንዳለው አስታውስ። ይሖዋ የሚፈልገውን ማንኛውንም ነገር ለመፍጠር እንዲሁም መሆን የሚሻውን ሁሉ ለመሆን የሚያስችለው ምንድን ነው? አንዱ ነገር ኃይሉ ነው። ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ያለው ችሎታ ገደብ የለውም። ይህ ኃይል ከዋና ዋናዎቹ የአምላክ ባሕርያት መካከል የሚጠቀስ ነው።

5 ይሖዋ፣ ኃይሉ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ሊገባን ስለማይችል በቀላሉ እንድንረዳው ለማድረግ ሲል ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። ቀደም ሲል እንዳየነው ኃይሉን ለመግለጽ በሬን እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። (ሕዝቅኤል 1:4-10) በሬ ግዙፍና ኃይለኛ ፍጡር ስለሆነ የይሖዋ ኃይል በበሬ መመሰሉ ተስማሚ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በፓለስቲና ምድር ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከበሬ ይበልጥ ጉልበት ያለው እንስሳ እምብዛም አያውቁም ነበር ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ አውራከስ ስለሚባለው አስፈሪ የሆነ የዱር በሬ ያውቁ ነበር፤ ይህ እንስሳ አሁን ከምድር ገጽ ጠፍቷል። (ኢዮብ 39:9-12) የሮም ገዢ የነበረው ጁሊየስ ቄሳር እነዚህ የዱር በሬዎች ከዝሆን ምንም ያህል እንደማያንሱ ገልጿል። “ጉልበታቸውም ሆነ ፍጥነታቸው አስገራሚ ነው” ሲል ጽፏል። እንዲህ ያለው እንስሳ አጠገብ ብትቆም ምን ያህል ትንሽና አቅመ ቢስ ሆነህ እንደምትታይ ገምት!

6. “ሁሉን ቻይ” ተብሎ ሊጠራ የሚገባው ይሖዋ ብቻ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

6 በተመሳሳይም ሰው፣ ታላቅ ኃይል ካለው ከይሖዋ አንጻር ሲታይ ኢምንትና አቅመ ቢስ ነው። ኃያላን መንግሥታት እንኳ በይሖዋ ፊት በሚዛን ላይ እንዳለ አቧራ ናቸው። (ኢሳይያስ 40:15) ገደብ የለሽ ኃይል ያለው ይሖዋ ብቻ በመሆኑ ከእሱ በስተቀር “ሁሉን ቻይ” ተብሎ ሊጠራ የሚችል የለም። a (ራእይ 15:3) ይሖዋ ‘ገደብ የሌለው ብርቱ ጉልበትና የሚያስደምም ኃይል’ አለው። (ኢሳይያስ 40:26) ምንጊዜም የማይነጥፍ የኃይል ምንጭ ነው። “ብርታት የአምላክ” ስለሆነ ከሌላ ምንጭ ኃይል ማግኘት አያስፈልገውም። (መዝሙር 62:11) ይሁንና ይሖዋ ኃይሉን የሚገልጠው በምን አማካኝነት ነው?

ይሖዋ ኃይሉን የሚገልጠው በምን አማካኝነት ነው?

7. የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ምንድን ነው? በበኩረ ጽሑፉ ላይ የገቡት ቃላትስ ምን ያመለክታሉ?

7 ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ያለ ገደብ ይሰጣል። መንፈስ ቅዱስ በሥራ ላይ የዋለ የአምላክ ኃይል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 1:2 ላይ ይህን መንፈስ ‘የአምላክ ኃይል’ ሲል ይጠራዋል። በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኙት “መንፈስ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት በሌሎች ጥቅሶች ላይ “ነፋስ” እና “እስትንፋስ” ተብለው ተተርጉመዋል። የመዝገበ ቃላት አዘጋጆች የዕብራይስጡና የግሪክኛው ቃላት፣ በሥራ ላይ የዋለን የማይታይ ኃይል እንደሚያመለክቱ ይገልጻሉ። ነፋስን ማየት እንደማንችል ሁሉ የአምላክን መንፈስም ማየት አንችልም፤ ሆኖም የሚያከናውናቸውን ነገሮች ማየት እንችላለን።

8. የአምላክ መንፈስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌያዊ ሁኔታ ምን ተብሎ ተገልጿል? ይህ ንጽጽርስ ተስማሚ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

8 የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የማያከናውነው ነገር የለም። ይሖዋ ዓላማውን ሁሉ ዳር ለማድረስ ሊጠቀምበት ይችላል። ስለሆነም የአምላክ መንፈስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌያዊ ሁኔታ የአምላክ “ጣት፣” “ብርቱ እጅ” ወይም ‘የተዘረጋ ክንድ’ ተብሎ መጠራቱ ተስማሚ ነው። (ሉቃስ 11:20፤ ዘዳግም 5:15፤ መዝሙር 8:3) አንድ ሰው የተለያየ ጉልበት ወይም ችሎታ የሚጠይቁ በርካታ ሥራዎችን በእጁ ማከናወን እንደሚችል ሁሉ አምላክም መንፈሱን በመጠቀም የተለያዩ ነገሮችን ማከናወን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በጣም ረቂቅ የሆነችውን አተም ለመፍጠር ወይም ቀይ ባሕርን ለመክፈል አሊያም ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች በልሳን እንዲናገሩ ለማድረግ ተጠቅሞበታል።

9. ይሖዋ ኃይሉን የሚገልጥበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?

9 በተጨማሪም ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እንደመሆኑ መጠን ይህን ሥልጣኑን በሚጠቀምበት መንገድ ኃይሉን ይገልጣል። የምትሰጣቸውን ማንኛውንም ትእዛዝ ለመፈጸም ዝግጁ ሆነው የሚጠባበቁ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተገዢዎች ቢኖሩህ ምን ይሰማሃል? ይሖዋ እንዲህ ያለ ከፍተኛ ሥልጣን አለው። ትእዛዙን የሚፈጽሙ ብዙ ሰብዓዊ አገልጋዮች ያሉት ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ሠራዊት ተብለው ተጠርተዋል። (መዝሙር 68:11፤ 110:3) ይሁን እንጂ ሰው ከመላእክት አንጻር ሲታይ ደካማ ፍጡር ነው። ለምሳሌ የአሦር ሠራዊት በአምላክ ሕዝብ ላይ ጥቃት በሰነዘረበት ጊዜ አንድ መልአክ በአንድ ሌሊት 185,000 ወታደሮችን ገድሏል! (2 ነገሥት 19:35) የይሖዋ መላእክት “ብርቱዎችና ኃያላን” ናቸው።—መዝሙር 103:19, 20

10. (ሀ) ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ የሠራዊት ጌታ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? (ለ) ከይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ ይበልጥ ኃያል የሆነው ማን ነው?

10 ይሖዋ የፈጠራቸው መላእክት ምን ያህል ናቸው? ነቢዩ ዳንኤል ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ መላእክት በሰማይ በይሖዋ ዙፋን ፊት ቆመው በራእይ ተመልክቷል፤ ሆኖም በሰማይ ያሉት መላእክት እነዚህ ብቻ እንደሆኑ የሚጠቁም ምንም ነገር የለም። (ዳንኤል 7:10) ስለዚህ በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መላእክት ሊኖሩ ይችላሉ። ስለሆነም ይሖዋ የሠራዊት ጌታ ተብሎ ተጠርቷል። ይህ የማዕረግ ስም አምላክ በሚገባ የተደራጁትን ብዛት ያላቸው ኃያላን መላእክት በበላይነት እንደሚቆጣጠርና እንደሚያዝ ያመለክታል። “የፍጥረት ሁሉ በኩር” የሆነውን የሚወደውን ልጁን በእነዚህ መላእክት ላይ አዛዥ አድርጎ ሾሞታል። (ቆላስይስ 1:15) ኢየሱስ የሱራፌል፣ የኪሩቤልና የመላእክት ሁሉ አለቃ በመሆኑ ከይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ ይበልጥ ኃያል ነው።

11, 12. (ሀ) የአምላክ ቃል ኃይል እንዳለው የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ኃይል ምን ምሥክርነት ሰጥቷል?

11 ይሖዋ ኃይሉን የሚገልጥበት ሌላም መንገድ አለ። ዕብራውያን 4:12 “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው” ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የአምላክ ቃል ወይም በመንፈስ መሪነት የተነገረው መልእክት አስደናቂ ኃይል እንዳለው አስተውለሃል? ሊያጠነክረን፣ እምነታችንን ሊገነባና በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን እጅግ ብልሹ በሆነ አኗኗር ከተጠመዱ ሰዎች እንዲርቁ ካሳሰበ በኋላ “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ” ብሏቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) አዎን፣ “የአምላክ ቃል” ኃይል ያለው በመሆኑ እነዚህ ሰዎች አኗኗራቸውን እንዲለውጡ ረድቷቸዋል።

12 የይሖዋ ኃይል እጅግ ታላቅ በመሆኑ ማንኛውንም ነገር ከማከናወን ሊያግደው የሚችል አይኖርም። ኢየሱስ “በአምላክ ዘንድ . . . ሁሉ ነገር ይቻላል” ብሏል። (ማቴዎስ 19:26) ይሖዋ ኃይሉን የሚጠቀምበት ለምን ዓላማ ነው?

ይሖዋ ኃይሉን የሚጠቀመው በዓላማ ነው

13, 14. (ሀ) ይሖዋ ግዑዝ የኃይል ምንጭ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ኃይሉን ምን ለማድረግ ይጠቀምበታል?

13 የይሖዋ መንፈስ ከማንኛውም ኃይል እጅግ የላቀ ነው። ይሖዋ ግዑዝ የሆነ የኃይል ምንጭ አይደለም። ኃይሉን በፈለገው መንገድ መቆጣጠርና መጠቀም የሚችል አምላክ ነው። ይሁንና ኃይሉን እንዲጠቀምበት የሚያነሳሳው ምንድን ነው?

14 ወደፊት አንድ በአንድ እንደምንመለከተው አምላክ ኃይሉን ለመፍጠር፣ ለማጥፋት፣ አገልጋዮቹን ለመጠበቅ፣ አንድን ነገር ለማደስና በአጠቃላይ ፍጹም የሆነውን ዓላማውን ሁሉ ለማስፈጸም ይጠቀምበታል። (ኢሳይያስ 46:10) አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም፣ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያቱንና መሥፈርቶቹን ይገልጣል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ፈቃዱን ለመፈጸም ይኸውም በመሲሐዊ መንግሥቱ አማካኝነት ስሙን ለማስቀደስ እና የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የላቀ መሆኑን ለማሳየት ይጠቀምበታል። ይህን ዓላማ ሊያከሽፍ የሚችል ምንም ነገር የለም።

15. ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ጋር በተያያዘ ኃይሉን ምን ለማድረግ ይጠቀምበታል? ይህስ ኤልያስ ባጋጠመው ሁኔታ የታየው እንዴት ነው?

15 በተጨማሪም ይሖዋ ኃይሉን እኛን በግለሰብ ደረጃ ለመርዳት ይጠቀምበታል። ሁለተኛ ዜና መዋዕል 16:9 “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን ያሳይ ዘንድ የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ” ይላል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የኤልያስ ታሪክ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ነው። ይሖዋ መለኮታዊ ኃይሉን አስፈሪ በሆነ መንገድ የገለጸለት ለምንድን ነው? ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል ኤልያስን ለማስገደል ምላ ነበር። ነቢዩ ነፍሱን ለማዳን እግሬ አውጪኝ ብሎ ሸሸ። ከመፍራቱና ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ልፋቱ ሁሉ ከንቱ እንደሆነና ብቻውን እንደቀረ ሆኖ ተሰማው። ይሖዋ እጅግ የተጨነቀውን ኤልያስን ለማጽናናት መለኮታዊ ኃይሉን ሕያው በሆነ መንገድ ገለጸለት። ነፋሱ፣ የምድር መናወጡና እሳቱ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ በላይ ኃያል የሆነው አምላክ እንደሚረዳው ለኤልያስ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ናቸው። ኤልያስ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከጎኑ እያለ ኤልዛቤልን የሚፈራበት ምን ምክንያት አለው?—1 ነገሥት 19:1-12 b

16. ስለ ይሖዋ ታላቅ ኃይል ማሰላሰላችን ሊያጽናናን የሚችለው ለምንድን ነው?

16 ምንም እንኳ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ተአምር የማይሠራ ቢሆንም በኤልያስ ዘመን የነበረው አምላክ አሁንም አልተለወጠም። (1 ቆሮንቶስ 13:8) ዛሬም ቢሆን ኃይሉን በመጠቀም የሚወዱትን ሰዎች ለመርዳት ዝግጁ ነው። ሊደረስበት በማይችል መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ የሚኖር ቢሆንም ከእኛ የራቀ አይደለም። ኃይሉን ርቀት አይገድበውም። “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ . . . ቅርብ ነው።” (መዝሙር 145:18) በአንድ ወቅት ነቢዩ ዳንኤል የይሖዋን እርዳታ እየጠየቀ ሳለ ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ አንድ መልአክ ተገልጦለታል! (ዳንኤል 9:20-23) ይሖዋ የሚወዳቸውን ሰዎች ከመርዳትና ከማበረታታት ሊያግደው የሚችል ነገር የለም።—መዝሙር 118:6

አምላክ ያለው ኃይል ሰዎች እንዳይቀርቡት የሚያደርግ ነው?

17. የይሖዋ ኃይል ፍርሃት የሚያሳድርብን ከምን አንጻር ነው? ይሁን እንጂ ምን ዓይነት ፍርሃት ሊያሳድርብን አይገባም?

17 አምላክ ያለው ኃይል እንድንፈራው ሊያደርገን ይገባል? ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ይገባልም፣ አይገባምም የሚል መሆን አለበት። ልንፈራው ይገባል የምንለው ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ በአጭሩ እንደተመለከትነው ይህ የይሖዋ ባሕርይ ከአድናቆትና ከጥልቅ አክብሮት የመነጨ አምላካዊ ፍርሃት ስለሚያሳድርብን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለው ፍርሃት “የጥበብ መጀመሪያ” እንደሆነ ይገልጻል። (መዝሙር 111:10) ልንፈራው አይገባም የምንለው ደግሞ አምላክ ያለው ኃይል በፍርሃት እንድንርድ ወይም ከእሱ እንድንርቅ የሚያደርግ ስላልሆነ ነው።

18. (ሀ) ብዙዎች በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን የማያምኑት ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ሥልጣኑን አላግባብ እንደማይጠቀምበት እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

18 በ1887 እንግሊዛዊው ታሪክ ጸሐፊ ሎርድ አክተን “ሥልጣን ያባልጋል፤ ገደብ የሌለው ሥልጣን ደግሞ የባሰ ያባልጋል” ሲሉ ጽፈው ነበር። ይህ አባባል በብዙዎች ዘንድ የማይታበል ሐቅ እንደሆነ ስለሚታመን በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ይሰማል። ታሪክ በተደጋጋሚ እንዳረጋገጠው ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሥልጣናቸውን አላግባብ ይጠቀሙበታል። (መክብብ 4:1፤ 8:9) በዚህም ምክንያት ብዙዎች በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ስለማያምኗቸው ይርቋቸዋል። ይሖዋ ገደብ የለሽ ሥልጣን አለው። ታዲያ ይህን ሥልጣኑን አላግባብ ይጠቀምበታል? በፍጹም! ቀደም ሲል እንዳየነው ይሖዋ ቅዱስ ስለሆነ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት አይፈጽምም። በዚህ በተበላሸ ዓለም ውስጥ በሥልጣን ላይ ካሉ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ፈጽሞ የተለየ ነው። በሥልጣኑ አላግባብ ተጠቅሞ አያውቅም፤ ወደፊትም አይጠቀምም።

19, 20. (ሀ) ይሖዋ ኃይሉን የሚጠቀመው ከየትኞቹ ሌሎች ባሕርያት ጋር በሚጣጣም መንገድ ነው? ይህስ የሚያጽናናን ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ራሱን የሚገዛ አምላክ መሆኑን በምሳሌ ማስረዳት የምትችለው እንዴት ነው? ይህ ባሕርይው የሚማርክህስ ለምንድን ነው?

19 ይሖዋ ኃይል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ባሕርያትም እንዳሉት አስታውስ። ወደፊት ፍትሑን፣ ጥበቡንና ፍቅሩን እንመረምራለን። ይሁን እንጂ ይሖዋ እነዚህን ባሕርያቱን በተናጠል እንደሚጠቀም አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ በቀጣዮቹ ምዕራፎች ላይ እንደምንመለከተው ይሖዋ ምንጊዜም ኃይሉን የሚጠቀመው ከፍትሑ፣ ከጥበቡና ከፍቅሩ ጋር በሚጣጣም መንገድ ነው። በተጨማሪም አምላክ አብዛኞቹ የዓለም መሪዎች የሚጎድላቸው አንድ ባሕርይ አለው፤ ይህም ራስን መግዛት ነው።

20 ሲያዩት በሚያስፈራ አንድ ግዙፍ ሰው ፊት ስትቀርብ ምን እንደሚሰማህ አስብ። ይሁን እንጂ ስትቀርበውና ስታውቀው ደግ ሰው እንደሆነ ትገነዘባለህ። ሰዎችን በተለይ ደግሞ አቅም የሌላቸውን መርዳትና መንከባከብ ያስደስተዋል። ኃይሉን ሌሎችን ለመጉዳት አይጠቀምበትም። ሰዎች ስሙን አላግባብ ሲያጠፉ እንኳ ባሕርይው አይለወጥም። በቁጣ ከመገንፈል ይልቅ የተፈጠረውን ችግር በረጋ መንፈስ አልፎ ተርፎም በደግነት ለመፍታት ጥረት ያደርጋል። ‘እኔ ብሆን ኖሮ የዚህን ሰው ያህል አካላዊ ጥንካሬ እያለኝ እንዲህ ያለ ባሕርይ አሳይ ነበር?’ ብለህ ራስህን መጠየቅህ አይቀርም። እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ያለውን ሰው በሚገባ ስታውቀው ይበልጥ ወደ እሱ ለመቅረብ አትገፋፋም? ሁሉን ቻይ ወደሆነው አምላክ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ የሚገፋፋን ከዚህ የበለጠ ጠንካራ ምክንያት አለን። የዚህ ምዕራፍ ርዕስ የተመሠረተበት ጥቅስ ምን እንደሚል ተመልከት፦ “ይሖዋ ለቁጣ የዘገየ ነው፤ ኃይሉም ታላቅ ነው።” (ናሆም 1:3) ይሖዋ ክፉ በሆኑ ሰዎችም ላይ እንኳ ሳይቀር ኃይሉን ለመጠቀም አይቸኩልም። ነገሮችን በእርጋታ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ደግ ነው። ሊያስቆጡት የሚችሉ ሁኔታዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት ቢያጋጥሙትም “ለቁጣ የዘገየ” መሆኑን አስመሥክሯል።—መዝሙር 78:37-41

21. ይሖዋ ሰዎች ፈቃዱን እንዲያደርጉ የማያስገድደው ለምንድን ነው? ይህ ስለ እሱ ምን ያስተምረናል?

21 ይሖዋ ራሱን እንደሚገዛ ያሳየበትን ሌላ ሁኔታም ተመልከት። ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ኃይል ቢኖርህ ኖሮ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች አንድን ነገር አንተ በፈለግኸው መንገድ ብቻ እንዲያከናውኑ ለማስገደድ ልትፈተን ትችል እንደነበር ይሰማሃል? ይሖዋ ታላቅ ኃይል ያለው አምላክ ቢሆንም ሰዎች እንዲያገለግሉት አያስገድድም። የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችለው እሱን በማገልገል ብቻ ቢሆንም ይሖዋ እንድናገለግለው አያስገድደንም። ከዚህ ይልቅ ለእያንዳንዱ ሰው የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷል። መጥፎ ምርጫ ምን መዘዝ እንደሚያስከትልና ጥሩ ምርጫ ደግሞ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝ አስቀድሞ ያሳውቃል። ምርጫውን ግን ለእኛ ይተወዋል። (ዘዳግም 30:19, 20) ይሖዋ ተገድደን ወይም ታላቅ ኃይሉ በሚያሳድርብን ፍርሃት ተሸብረን ሳይሆን በፍቅር ተነሳስተን በፈቃደኝነት እንድናገለግለው ይፈልጋል።—2 ቆሮንቶስ 9:7

22, 23. (ሀ) ይሖዋ ለሌሎች ሥልጣንና ኃይል መስጠት እንደሚያስደስተው የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለ ምን ጉዳይ እንመረምራለን?

22 ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ታላቅ ኃይል ያለው መሆኑ እንድንፈራና እንድንንቀጠቀጥ ሊያደርገን የማይገባው ለምን እንደሆነ የሚጠቁም ተጨማሪ ምክንያት እንመልከት። ሰዎች ሥልጣንን ለሌሎች ማጋራት ያስፈራቸዋል። ይሖዋ ግን ታማኝ ለሆኑ አምላኪዎቹ ሥልጣን መስጠት ያስደስተዋል። ለምሳሌ ያህል ለልጁ ከፍተኛ ሥልጣን ሰጥቶታል። (ማቴዎስ 28:18) በተጨማሪም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ኃይል ይሰጣል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ታላቅነት፣ ኃያልነት፣ ውበት፣ ግርማና ሞገስ የአንተ ነው፤ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነው። . . . ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው፤ እጅህ ሁሉንም ታላቅ ማድረግና ለሁሉም ብርታት መስጠት ይችላል።”—1 ዜና መዋዕል 29:11, 12

23 አዎን፣ ይሖዋ ኃይል ለመስጠት ዝግጁ ነው። እንዲያውም እሱን ማገልገል ለሚፈልጉ ሁሉ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጣቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ይሖዋ ኃይሉን በአግባቡና አሳቢነት በተሞላበት መንገድ የሚጠቀም አምላክ ነው። ታዲያ ይህ እንድትወድደውና ወደ እሱ እንድትቀርብ አይገፋፋህም? በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይሖዋ የተለያዩ ነገሮችን ለመፍጠር ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት እንመለከታለን።

a “ሁሉን ቻይ” የሚል ፍቺ የተሰጠው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “በሁሉ ላይ የሚገዛ፣ የሥልጣን ሁሉ ባለቤት” ማለት ነው።

b መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ‘በነፋሱ፣ በምድር መናወጡም ሆነ በእሳቱ ውስጥ እንዳልነበረ’ ይገልጻል። በአፈ ታሪክ የሚነገሩ አማልክትን የሚያመልኩ ሰዎች አምላክ በተፈጥሮ ኃይሎች ውስጥ እንዳለ አድርገው ያስባሉ። የይሖዋ አገልጋዮች ግን እንዲህ ዓይነት አመለካከት የላቸውም። እጅግ ታላቅ አምላክ በመሆኑ እሱ በፈጠራቸው ነገሮች ውስጥ ሊኖር አይችልም።—1 ነገሥት 8:27