በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 5

‘የሰማይና የምድር ፈጣሪ’—ለመፍጠር የሚጠቀምበት ኃይል

‘የሰማይና የምድር ፈጣሪ’—ለመፍጠር የሚጠቀምበት ኃይል

1, 2. ይሖዋ ለመፍጠር የሚጠቀምበትን ኃይል ለማስረዳት ፀሐይ እንደ ምሳሌ ልትጠቀስ የምትችለው ለምንድን ነው?

 በርዶህ እሳት ሞቀህ ታውቃለህ? እሳቱ አጠገብ ሆነህ እጆችህን ዘርግተህ እየሞቅክ ነው እንበል። በጣም ከተጠጋህ ወላፈኑ ሊያቃጥልህ ይችላል። በጣም ከራቅህ ደግሞ ይበርድሃል።

2 ቀን ቀን ሰውነታችንን የሚያሞቅ አንድ “እሳት” አለ። ይህ “እሳት” የሚገኘው ከእኛ 150 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ነው! a በእሳት የተመሰለችው ፀሐይ ያን ከሚያህል ርቀት ለእኛ ሙቀት መስጠት የቻለችው ምን ያህል ኃይል ቢኖራት እንደሆነ ገምት! ይሁንና ምድራችን ኃይለኛ እሳት የሚንቀለቀልባትን ይህችን ምድጃ የምትዞረው በትክክለኛ ርቀት ላይ ሆና ነው። ምድር ወደ ፀሐይ ቀረብ ብትል ኖሮ በላይዋ ላይ ያለው ውኃ ሁሉ ይተን ነበር። ከፀሐይ በጣም ብትርቅ ደግሞ በምድር ላይ ያለው ውኃ ሁሉ በረዶ ይሆናል። ስለዚህ ፕላኔታችን ለፀሐይ ትንሽ ብትቀርብም ሆነ ብትርቅ ሕይወት ያለው ነገር ሊኖርባት አይችልም። በተጨማሪም በምድር ላይ ላለው ሕይወት ወሳኝ የሆነው ይህ የፀሐይ ብርሃን፣ ምንም ዓይነት ብክለት የማያስከትልና ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ የሚውል ብሎም ደስ የሚያሰኝ ነው።—መክብብ 11:7

3. ፀሐይ ምን ሐቅ ታስገነዝበናለች?

3 ሰዎች ሕልውናቸው በፀሐይ ላይ የተመካ ቢሆንም እንኳ ፀሐይ ስለምትሰጠው ጥቅም የሚያስቡት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። በመሆኑም ከፀሐይ ሊማሩ የሚችሉት ቁም ነገር ያመልጣቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “ብርሃንንና ፀሐይን ሠራህ” ይላል። (መዝሙር 74:16) አዎን፣ ፀሐይ ‘የሰማይና የምድር ፈጣሪ’ የሆነውን የይሖዋን ክብር ትናገራለች። (መዝሙር 19:1፤ 146:6) ይሁንና ፀሐይ፣ ይሖዋ ለመፍጠር የሚያስችል ከፍተኛ ኃይል እንዳለው ከሚጠቁሙት የሰማይ አካላት መካከል አንዷ ብቻ ናት። እንግዲያው ትኩረታችንን ወደ ምድርና በላይዋ ወደሚኖሩት ሕያዋን ነገሮች ከማዞራችን በፊት ከእነዚህ የሰማይ አካላት መካከል አንዳንዶቹን እንመርምር።

ይሖዋ “ብርሃንንና ፀሐይን” ሠርቷል

“ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንስታችሁ ተመልከቱ”

4, 5. (ሀ) ፀሐይ ምን ያህል ኃይል አላት? ምን ያህልስ ግዙፍ ናት? (ለ) ፀሐይን ከሌሎች ከዋክብት ጋር ማነጻጸር የሚቻለው እንዴት ነው?

4 እንደምታውቀው ፀሐይ ራሷ ኮከብ ናት። ከሌሎቹ ከዋክብት አንጻር ሲታይ ለምድር ቀረብ ያለች ስለሆነች ትልቅ መስላ ትታየናለች። ለመሆኑ ፀሐይ ያላት ኃይል ምን ያህል ነው? የፀሐይ እምብርት 15,000,000 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ገደማ የሚደርስ ሙቀት አለው። ከፀሐይ እምብርት፣ ጤፍ የምታክል ቅንጣት ወስደህ ምድር ላይ ማስቀመጥ ብትችል ወደዚህች ቅንጣት ከ140 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ መቅረብ አትችልም! ፀሐይ በየሴኮንዱ ከብዙ መቶ ሚሊዮን የኑክሌር ቦምብ ፍንዳታዎች ጋር የሚመጣጠን ኃይል ታመነጫለች።

5 ፀሐይ እጅግ ግዙፍ ከመሆኗ የተነሳ ምድራችንን የሚያክሉ ከ1,300,000 የሚበልጡ ፕላኔቶችን መያዝ ትችላለች። እንዲህ ሲባል የመጨረሻዋ ግዙፍ ኮከብ ናት ማለት ነው? በፍጹም፤ እንዲያውም የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ትንሿ ቢጫ ኮከብ በማለት ይጠሯታል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የአንዱ ኮከብ ክብር ከሌላው ኮከብ ክብር ይለያል” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 15:41) ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የተነገሩት እነዚህ ቃላት ምን ያህል እውነት እንደሆኑ ብዙም የሚያውቀው ነገር አልነበረም። አሁን ፀሐይ የምትገኝበት ቦታ ላይ ቢሆን ኖሮ ምድራችንን ጭምር ሊሸፍን የሚችል ግዙፍ ኮከብ አለ። አንድ ሌላ ግዙፍ ኮከብ ደግሞ ፀሐይ ያለችበት ቦታ ላይ ቢሆን ሳተርን የተባለችው ፕላኔት እስከምትገኝበት ቦታ ሊደርስ ይችላል። ሳተርን ከምድር እጅግ ርቃ የምትገኝ ከመሆኗ የተነሳ አንዲት የጠፈር መንኮራኩር ከጥይት 40 ጊዜ እጥፍ በሚበልጥ ፍጥነት እየተወነጨፈች ሳተርን ላይ ለመድረስ አራት ዓመታት ፈጅቶባታል!

6. ከሰው ችሎታ አንጻር ሲታይ ከዋክብት ሊቆጠሩ እንደማይችሉ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው እንዴት ነው?

6 ከዋክብት ካላቸው መጠን ይበልጥ የሚያስገርመው ብዛታቸው ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ከዋክብት እንደ ‘ባሕር አሸዋ’ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ሊቆጠሩ እንደማይችሉ ይገልጻል። (ኤርምያስ 33:22) ይህ ጥቅስ በዓይናችን ልናያቸው ከምንችላቸው በላይ በጣም ብዙ ከዋክብት እንዳሉ ይጠቁማል። እንደ ኤርምያስ ያለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ በምሽት ወደ ሰማይ አንጋጦ በዓይኑ የሚያያቸውን ከዋክብት ለመቁጠር ቢሞክር ከሦስት ሺህ በላይ ሊቆጥር አይችልም። ምክንያቱም አንድ ሰው በጠራ ሰማይ ላይ ያላንዳች መሣሪያ እገዛ በዓይኑ ብቻ ከዚህ የበለጡ ከዋክብት ሊያይ አይችልም። ይህ ቁጥር ከአንድ እፍኝ አሸዋ ብዛት አይበልጥም። ይሁንና የከዋክብት ብዛት ልክ እንደ ባሕር አሸዋ ልንገምተው ከምንችለው በላይ ነው። b ለመሆኑ የባሕር አሸዋን ሊቆጥር የሚችል ይኖራል?

“ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል”

7. ተመራማሪዎች በፍኖተ ሐሊብ ጋላክሲ ውስጥ ስላሉት ከዋክብት ብዛትም ሆነ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ስላሉት ጋላክሲዎች ብዛት ምን ይገምታሉ?

7 ኢሳይያስ 40:26 እንዲህ ሲል መልስ ይሰጣል፦ “ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንስታችሁ ተመልከቱ። እነዚህን ነገሮች የፈጠረ ማን ነው? እንደ ሠራዊት በቁጥር የሚመራቸው እሱ ነው፤ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።” መዝሙር 147:4 “የከዋክብትን ብዛት ይቆጥራል” ይላል። ‘የከዋክብት ብዛት’ ስንት ነው? ይህ ከባድ ጥያቄ ነው። የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ምድራችን በምትገኝበት ፍኖተ ሐሊብ በመባል በሚታወቀው ጋላክሲ ውስጥ ብቻ እንኳ ከ100 ቢሊዮን የሚበልጡ ከዋክብት እንዳሉ ይገምታሉ። c አንዳንዶች ደግሞ ቁጥሩ ከዚህም በጣም እንደሚበልጥ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ፍኖተ ሐሊብ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሚገኙት በርካታ ጋላክሲዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው፤ እንዲያውም አብዛኞቹ ጋላክሲዎች ከዚህ የበለጠ ቁጥር ያላቸውን ከዋክብት ያቀፉ ናቸው። ለመሆኑ ስንት ጋላክሲዎች አሉ? ተመራማሪዎች በመቶ ቢሊዮኖች አልፎ ተርፎም በትሪሊዮኖች የሚቆጠሩ ጋላክሲዎች እንዳሉ ይገምታሉ። ስለሆነም የሰው ልጅ፣ በጋላክሲዎች ውስጥ የሚገኙትን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብት ብዛት ይቅርና የጋላክሲዎችን ብዛት እንኳ በትክክል ማወቅ የቻለ አይመስልም። ይሖዋ ግን ብዛታቸውን በትክክል ያውቃል። አልፎ ተርፎም ለእያንዳንዱ ኮከብ ስም አውጥቷል!

8. (ሀ) የፍኖተ ሐሊብን ስፋት እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ? (ለ) ይሖዋ የሰማይ አካላትን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው በምን አማካኝነት ነው?

8 ስለ ጋላክሲዎች ስፋት ስናስብ ለይሖዋ ያለን አክብሮትና አድናቆት ይጨምራል። ፍኖተ ሐሊብ የተሰኘው ጋላክሲ ከጫፍ እስከ ጫፍ 100,000 የብርሃን ዓመት ገደማ ርቀት እንዳለው ይገመታል። በሴኮንድ 300,000 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ አንድ የብርሃን ጨረር በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ይህ የብርሃን ጨረር ምድራችን የምትገኝበትን ጋላክሲ ለማቋረጥ 100,000 ዓመት ይፈጅበታል! አንዳንዶቹ ጋላክሲዎች ከዚህ ጋላክሲ ብዙ ጊዜ እጥፍ ይበልጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ሰማያትን እንደ መጋረጃ ‘እንደዘረጋቸው’ ይገልጻል። (መዝሙር 104:2) የእነዚህን አካላት እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረውም እሱ ነው። በጠፈር ላይ ካለችው አነስተኛ የአቧራ ቅንጣት አንስቶ እስከ ትልቁ ጋላክሲ ድረስ ያለው ነገር በሙሉ የሚንቀሳቀሰው አምላክ ባወጣው የቁስ አካል ሕግ መሠረት ነው። (ኢዮብ 38:31-33) በመሆኑም ሳይንቲስቶች ዝንፍ የማይለውን የሰማይ አካላት እንቅስቃሴ በጣም ውስብስብ ከሆነ የዳንስ ጥበብ ጋር አመሳስለውታል። እነዚህን ነገሮች ስለፈጠረው አምላክ ስታስብ እንዲህ ያለ ታላቅ ኃይል ያለው መሆኑ በአድናቆት ስሜት እንድትዋጥ አያደርግህም?

“ምድርን በኃይሉ የሠራ”

9, 10. ምድራችን የምትገኝበት ሥርዓተ ፀሐይ፣ ጁፒተር፣ ምድር ራሷና ጨረቃ የይሖዋን ታላቅ ኃይል የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?

9 የምንኖርባት ምድርም ይሖዋ ለመፍጠር የሚጠቀምበትን ኃይል በግልጽ ታሳያለች። በዚህ ሰፊ አጽናፈ ዓለም ውስጥ አምላክ ምድርን ያስቀመጣት በትክክለኛው ቦታ ላይ ነው። አንዳንድ ሳይንቲስቶች በብዙ ጋላክሲዎች ውስጥ እንደ ምድራችን ሕይወት ላላቸው ነገሮች ተስማሚ የሆኑ ፕላኔቶች እንደሌሉ ይናገራሉ። የፍኖተ ሐሊብ አብዛኛው ክፍል ሕይወት ላለው ነገር መኖሪያነት ምቹ ሆኖ የተፈጠረ አይደለም። የጋላክሲው ማዕከላዊ ክፍል በከዋክብት የታጨቀ ነው። በዚህም የተነሳ ኃይለኛ ጨረር የሚመነጭ ከመሆኑም በላይ በእነዚህ ከዋክብት መካከል ከፍተኛ የመሳሳብ ኃይል አለ። ወደ ጋላክሲው ጠረፍ አካባቢ ደግሞ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች አይገኙም። ምድራችን የምትገኝበት ሥርዓተ ፀሐይ ያለው በእነዚህ ሁለት ጽንፎች መካከል እጅግ ተስማሚ በሆነ ቦታ ላይ ነው።

10 ከመሬት በጣም ርቃ የምትገኘው ጁፒተር የተሰኘችው ፕላኔት ለምድራችን ትልቅ ከለላ ሆና ታገለግላለች። ጁፒተር ከመሬት ሺህ ጊዜ እጥፍ ስለምትበልጥ ከፍተኛ የሆነ የስበት ኃይል አላት። በመሆኑም ጠፈርን አቋርጠው የሚመጡ ተወርዋሪ አካላትን ስባ ታስቀራለች አሊያም አቅጣጫ ታስታለች። ሳይንቲስቶች እንደሚገምቱት ከሆነ ጁፒተር ባትኖር ኖሮ ወደ መሬት የሚዥጎደጎዱት ተወርዋሪ አካላት በምድራችን ላይ የሚያደርሱት ጉዳት 10,000 ጊዜ እጥፍ ይጨምር ነበር። የምንኖርባት ምድር አንዲት ለየት ያለች ሳተላይት አለቻት። ይህች ሳተላይት ማለትም ጨረቃ እንዲሁ ለምድር ውበት የምትጨምርና በሌሊት ብርሃን የምትሰጥ አካል እንደሆነች ብቻ አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ምድር ምንጊዜም ወደ አንድ ወገን ዘንበል ብላ እንድትኖር በማድረግ ወቅቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው እንዲፈራረቁ ትልቅ አስተዋጽኦ ታበረክታለች። ይህ ደግሞ በምድር ላይ ላለው ሕይወት በጣም ወሳኝ ነው።

11. የምድር ከባቢ አየር እንደ ከለላ ሆኖ የሚያገለግለው እንዴት ነው?

11 እያንዳንዱ የምድር ንድፍ ይሖዋ የተለያዩ ነገሮችን ለመፍጠር ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ምድርን እንደ ጃንጥላ የሚከልለውን ከባቢ አየር እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ፀሐይ ጠቃሚና ጎጂ የሆኑ ጨረሮችን ታመነጫለች። ጎጂዎቹ ጨረሮች በምድር ከባቢ አየር ላይ ሲያርፉ በከባቢ አየሩ ውስጥ የሚገኘው ኦክስጅን ወደ ኦዞን ይቀየራል። ይህ የኦዞን ሽፋን አብዛኞቹን ጎጂ ጨረሮች ውጦ ያስቀራል። በመሆኑም ፕላኔታችን የተፈጠረችው የራሷ የሆነ ከለላ እንዲኖራት ተደርጋ ነው።

12. በከባቢ አየር ውስጥ የሚካሄደው የውኃ ዑደት የፈጣሪን ኃይል የሚያሳየው እንዴት ነው?

12 በምድር ላይ ለሚኖሩ ፍጥረታት ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ ጋዞችን አቅፎ የያዘው ከባቢ አየር ሌሎችም አስደናቂ ገጽታዎች አሉት። ከእነዚህም መካከል አንዱ የውኃ ዑደት ነው። የፀሐይ ሙቀት ከውቅያኖስና ከባሕር በየዓመቱ 400,000 ኪሎ ሜትር ኩብ ውኃ ወደ ሰማይ እንዲተን ያደርጋል። የተነነው ውኃ ወደ ደመናነት የሚለወጥ ሲሆን ደመናው ደግሞ በከባቢ አየር ውስጥ በሚገኙ ነፋሳት ከቦታ ወደ ቦታ ይንቀሳቀሳል። ውኃው ከተጣራ በኋላ በዝናብና በበረዶ መልክ ተመልሶ ወደ ምድር ይመጣል። መክብብ 1:7 ይህን ዑደት “ጅረቶች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈስሳሉ፤ ሆኖም ባሕሩ አይሞላም። ጅረቶቹ እንደገና ይፈስሱ ዘንድ ወደሚነሱበት ወደዚያው ቦታ ተመልሰው ይሄዳሉ” ሲል ገልጾታል። እንዲህ ዓይነት ዑደት እንዲኖር ሊያደርግ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው።

13. የምድር ዕፀዋትና አፈር የፈጣሪን ኃይል የሚያሳዩት እንዴት ነው?

13 ሕይወት በአጠቃላይ የፈጣሪን ታላቅ ኃይል የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ከ30 ፎቅ የበለጠ ርዝማኔ ካለው ከግዙፉ ሴኮያ ዛፍ አንስቶ አብዛኛውን ኦክስጅን እስከሚያመነጩት ረቂቅ የባሕር ውስጥ ዕፀዋት ድረስ ያሉት ሕያዋን ነገሮች ይሖዋ ለመፍጠር የሚጠቀምበትን ታላቅ ኃይል ያንጸባርቃሉ። ሌላው ቀርቶ በአፈር ውስጥ እንኳ እንደ ትላትል፣ ፈንገስና ረቂቅ ተሕዋሲያን ያሉ ብዙ ሕያዋን ፍጥረታት ይገኛሉ። እነዚህ በአፈር ውስጥ የሚገኙ ፍጥረታት ለዕፀዋት እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ወይም አፈር ኃይል እንዳለው መናገሩ የተገባ ነው።—ዘፍጥረት 4:12 የግርጌ ማስታወሻ

14. በአንዲት አነስተኛ አተም ውስጥ እንኳ ምን ያህል የታመቀ ኃይል አለ?

14 በእርግጥም “ምድርን በኃይሉ የሠራው” ይሖዋ ነው። (ኤርምያስ 10:12) የአምላክ ኃይል በፈጠራቸው ጥቃቅን ነገሮች ላይ እንኳ ሳይቀር ታይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሚሊዮን አተሞች ጎን ለጎን ቢቀመጡ የአንዲት ፀጉር ያህል እንኳ ውፍረት አይኖራቸውም። በተጨማሪም አንድ አተም ተለጥጦ 14 ፎቅ ያለው ሕንፃ ርዝማኔ እንዲኖረው ቢደረግ እንኳ የአተሙ እምብርት (ኑክሊየስ) የሚኖረው መጠን በሕንፃው ሰባተኛ ፎቅ ላይ ካለች የጨው ቅንጣት አይበልጥም። ይሁን እንጂ ከባድ የኑክሌር ፍንዳታ የሚያስከትለው በዚህች እጅግ አነስተኛ የሆነች የአተም እምብርት ውስጥ ያለው ከፍተኛ ኃይል ነው!

“እስትንፋስ ያለው ሁሉ”

15. ይሖዋ የተለያዩ የዱር እንስሳትን በመጥቀስ ኢዮብን ምን አስተምሮታል?

15 ከዚህም በተጨማሪ በምድር ላይ ያሉት ስፍር ቁጥር የሌላቸው እንስሳት የፈጣሪን ኃይል የሚያሳዩ ጉልህ ማስረጃዎች ናቸው። መዝሙር 148 ይሖዋን የሚያወድሱ በርካታ ነገሮችን የሚዘረዝር ሲሆን ከእነዚህም መካከል በቁጥር 10 ላይ የተጠቀሱት “የዱር እንስሳትና የቤት እንስሳት” ይገኙበታል። ይሖዋ የሰው ልጅ ፈጣሪውን ሊፈራና ሊያከብር የሚገባው ለምን እንደሆነ ለኢዮብ በገለጸበት ወቅት እንደ አንበሳ፣ የሜዳ አህያ፣ የዱር በሬ፣ ብሄሞት (ወይም ጉማሬ) እና ሌዋታን (አዞ ሳይሆን አይቀርም) ያሉ እንስሳትን ጠቅሷል። እዚህ ላይ ይሖዋ በአጽንኦት ሊገልጽ የፈለገው ነገር ምንድን ነው? ሰው እነዚህን ለማላመድ አስቸጋሪ የሆኑ ኃይለኛ ፍጥረታት የሚፈራ ከሆነ እነሱን የፈጠረውን አምላክማ ምንኛ ሊፈራና ሊያከብር ይገባል!—ኢዮብ ምዕራፍ 38-41

16. ይሖዋ ከፈጠራቸው ወፎች መካከል አንዳንዶቹ ምን አስገራሚ ተሰጥኦ አላቸው?

16 መዝሙር 148:10 ‘ክንፍ ያላቸው ወፎችንም’ ይጠቅሳል። ስንት ዓይነት የአእዋፍ ዝርያዎች እንዳሉ አስብ! ይሖዋ ኢዮብን ባነጋገረበት ወቅት ስለ ሰጎን የጠቀሰለት ሲሆን “በፈረሱና በፈረሰኛው ላይ ትስቃለች” ብሎታል። በእርግጥም ሁለት ሜትር ተኩል ርዝማኔ ያላት ይህች ወፍ መብረር የማትችል ብትሆንም እንኳ በሰዓት 65 ኪሎ ሜትር መሮጥ የምትችል ሲሆን በአንድ እርምጃ ብቻ 4 ሜትር ተኩል ትወነጨፋለች! (ኢዮብ 39:13, 18) በሌላ በኩል ደግሞ አልበትሮስ የተባለችው ወፍ አብዛኛውን ጊዜዋን የምታሳልፈው በባሕር ላይ በማንዣበብ ሲሆን የክንፏ ርዝማኔ ከጫፍ እስከ ጫፍ 3 ሜትር ይሆናል። ክንፎቿን ምንም ሳታርገበግብ ቀጥ አድርጋ እንደዘረጋች በርከት ላሉ ሰዓታት አየር ላይ መንሳፈፍ ትችላለች። በአንጻሩ ግን ቢ ሃሚንግበርድ የተባለችው ወፍ ርዝማኔዋ አምስት ሴንቲ ሜትር ብቻ ሲሆን በዓለም ላይ ካሉት አእዋፍ ሁሉ አነስተኛዋ ናት። ክንፎቿን በሴኮንድ 80 ጊዜ ያህል ልታርገበግብ ትችላለች! ይህች ልክ እንደ ዕንቁ የምታብረቀርቅ ወፍ እንደ ሄሊኮፕተር በአየር ላይ መቆም የምትችል ከመሆኑም በላይ የኋልዮሽ መብረር ትችላለች።

17. ብሉ ዌል የተባለው ዓሣ ነባሪ ምን ያህል ግዙፍ ነው? ይሖዋ ስለፈጠራቸው እንስሳት ስናስብ ምን ለማድረግ እንገፋፋለን?

17 መዝሙር 148:7 “የባሕር ፍጥረታት” እንኳ ሳይቀር ይሖዋን እንደሚያወድሱ ይናገራል። በፕላኔታችን ላይ ከኖሩት እንስሳት ሁሉ በግዝፈቱ ተወዳዳሪ የለውም የሚባለውን ብሉ ዌል የተሰኘውን ዓሣ ነባሪ እስቲ እንመልከት። “ጥልቅ ውኃዎች” ውስጥ የሚገኘው ይህ ፍጥረት ርዝማኔው 30 ሜትር ወይም ከዚያ በላይ እንደሆነና ክብደቱ ደግሞ ከ30 ዝሆኖች ክብደት ጋር እንደሚመጣጠን ይገመታል። ምላሱ ብቻ የአንድ ዝሆን ያህል ክብደት አለው። ልቡ ደግሞ አንድ ትንሽ መኪና ያክላል። የዚህ እንስሳ ልብ በደቂቃ 9 ጊዜ ብቻ የሚመታ ሲሆን በአንጻሩ ግን ሃሚንግበርድ የተባለችው ወፍ ልብ በደቂቃ 1,200 ጊዜ ሊመታ ይችላል። ከዚህ ዓሣ ነባሪ የደም ሥሮች አንዱ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ሕፃን ልጅ በውስጡ ሊድህ ይችላል። ይህን ሁሉ ስናስብ ልባችን በአድናቆት ተሞልቶ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ ያህን ያወድስ” የሚሉትን በመዝሙር መጽሐፍ መደምደሚያ ላይ የሚገኙ ቃላት ለማስተጋባት አንገፋፋም?—መዝሙር 150:6

ይሖዋ ለመፍጠር ከተጠቀመበት ኃይል የምናገኘው ትምህርት

18, 19. ይሖዋ በምድር ላይ የፈጠራቸው ሕያዋን ነገሮች ብዛት ምን ያህል ነው? የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ስለ ሉዓላዊነቱ ምን ያስገነዝቡናል?

18 ይሖዋ መፍጠር የሚያስችለውን ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ምን ያስተምረናል? ስለፈጠራቸው ነገሮች ብዛትና ዓይነት ስናስብ በግርምት ፈዘን እንቀራለን። አንድ መዝሙራዊ “ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ብዙ ነው! . . . ምድር በፈጠርካቸው ነገሮች ተሞልታለች” ሲል በአድናቆት ተናግሯል። (መዝሙር 104:24) ይህ ሊታበል የማይችል ሐቅ ነው! የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች በምድር ላይ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ የሕያዋን ፍጥረታት ዝርያዎች እንዳሉ ደርሰውበታል። ይሁን እንጂ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዝርያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚገምቱም አሉ። አንድ የሥነ ጥበብ ሰው አእምሮው አዲስ የፈጠራ ሥራ ማመንጨት የሚሳነው ጊዜ አለ። በተቃራኒው ግን ይሖዋ አዲስ ነገር ለመፍጠር ያለው ችሎታ መቼም ቢሆን ሊነጥፍ አይችልም።

19 ይሖዋ መፍጠር የሚያስችለውን ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ስለ ሉዓላዊነቱ የሚያስተምረን ነገር አለ። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች ሁሉ “ፍጡራን” በመሆናቸው “ፈጣሪ” የሚለው ቃል ራሱ ይሖዋን ከሌሎች ይለየዋል። በፍጥረት ሥራ ወቅት “የተዋጣለት ሠራተኛ” የነበረው የይሖዋ አንድያ ልጅ እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ፈጣሪ’ ወይም ‘ረዳት ፈጣሪ’ የተባለበት ቦታ አናገኝም። (ምሳሌ 8:30፤ ማቴዎስ 19:4) ከዚህ ይልቅ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” እንደሆነ እናነባለን። (ቆላስይስ 1:15) ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን በአጽናፈ ዓለሙ ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ገዢ የመሆን መብቱ የተረጋገጠ ነው።—ሮም 1:20፤ ራእይ 4:11

20. ይሖዋ በምድር ላይ ያከናወናቸውን የፍጥረት ሥራዎች ካጠናቀቀ በኋላ ያረፈው ከምን አንጻር ነው?

20 ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም አዳዲስ ነገሮችን መፍጠሩን አቁሟል? መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በስድስተኛው የፍጥረት ቀን የፍጥረት ሥራዎቹን ካጠናቀቀ በኋላ “[በሰባተኛው] ቀን ይሠራው ከነበረው ሥራ ሁሉ ማረፍ ጀመረ” ይላል። (ዘፍጥረት 2:2) ሐዋርያው ጳውሎስ ሰባተኛው “ቀን” እሱ እስከነበረበት ዘመን ድረስ እንደዘለቀ በመግለጽ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ርዝማኔ እንዳለው አመልክቷል። (ዕብራውያን 4:3-6) ይሁን እንጂ ‘አረፈ’ ሲባል ጭራሽ መሥራት አቁሟል ማለት ነው? በፍጹም፣ ይሖዋ መሥራቱን አቁሞ አያውቅም። (መዝሙር 92:4፤ ዮሐንስ 5:17) ስለዚህ “ማረፍ” የሚለው አነጋገር በምድር ላይ የሚያከናውነውን የፍጥረት ሥራ እንዳቆመ ብቻ የሚያመለክት መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ዓላማውን ዳር ለማድረስ አሁንም ድረስ መሥራቱን አላቋረጠም። መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ ማስጻፉ የዚህ ሥራው አንድ አካል ነው። ከዓላማው ጋር በተያያዘ የሚያከናውነው ሥራ በምዕራፍ 19 ላይ በዝርዝር የምንመለከተውን “አዲስ ፍጥረት” ማስገኘትንም ይጨምራል።—2 ቆሮንቶስ 5:17

21. ይሖዋ ለመፍጠር የሚጠቀምበት ኃይል ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ምን አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል?

21 ይሖዋ በስድስቱ የፍጥረት ቀናት ማብቂያ ላይ እንደተናገረው ሁሉ አሁንም የእረፍቱ ቀን ሲያልቅ በምድር ላይ ያለው ሥራው ሁሉ “እጅግ መልካም” እንደሆነ መናገር ይችላል። (ዘፍጥረት 1:31) ከዚያ በኋላ፣ መፍጠር የሚያስችለውን ገደብ የለሽ ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ያም ሆነ ይህ በዚያን ጊዜም ቢሆን መፍጠር የሚያስችለውን ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ በአድናቆት እንድንዋጥ እንደሚያደርገን ምንም ጥርጥር የለውም። በፍጥረት ሥራዎቹ አማካኝነት ለዘላለም ስለ ይሖዋ መማራችንን እንቀጥላለን። (መክብብ 3:11) ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቅን መጠን ለእሱ ያለን አክብሮትና አድናቆት የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል። ይህ ደግሞ ከምንጊዜውም በበለጠ ወደ ታላቁ ፈጣሪያችን እንድንቀርብ ያደርገናል።

a ይህን ለመገመት የሚያስቸግር ርቀት ቀለል ባለ ሁኔታ ለመረዳት በሚከተለው መንገድ ማነጻጸር ይቻላል፦ በሰዓት 160 ኪሎ ሜትር በሚከንፍ መኪና በቀን 24 ሰዓት ብትጓዝ ይህን ርቀት ለመሸፈን ከመቶ ዓመት በላይ ይወስድብሃል!

b አንዳንዶች፣ በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ብዙም ያልተራቀቀ እንደ ቴሌስኮፕ ያለ መሣሪያ ይጠቀሙ እንደነበረ ይገምታሉ። ‘እንዲህ ያለ መሣሪያ ባይጠቀሙ ኖሮ ከዋክብት እጅግ ብዙ እንደሆኑና ሊቆጠሩ እንደማይችሉ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ?’ የሚል የመከራከሪያ ሐሳብ ያቀርባሉ። እንዲህ ያለው መሠረተ ቢስ መላ ምት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈውን ይሖዋን ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

c አንድ መቶ ቢሊዮን ከዋክብትን ለመቁጠር ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድብህ ገምት። በሴኮንድ አንድ ኮከብ እየቆጠርክ በቀን ለ24 ሰዓት ብትቆጥር 3,171 ዓመታት ይወስድብሃል!