በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 8

‘ሁሉንም ነገር አዲስ የሚያደርገው’ ይሖዋ—ለማደስ የሚጠቀምበት ኃይል

‘ሁሉንም ነገር አዲስ የሚያደርገው’ ይሖዋ—ለማደስ የሚጠቀምበት ኃይል

1, 2. በዛሬው ጊዜ ሰዎች ምን ነገሮችን ሊያጡ ይችላሉ? ይህስ ምን ስሜት ያሳድርባቸዋል?

 አንድ ሕፃን በጣም የሚወደው መጫወቻ ሲጠፋበት ወይም ሲሰበርበት ሆድ በሚያባባ ሁኔታ ምርር ብሎ ያለቅሳል። ይሁን እንጂ ወላጁ የጠፋውን መጫወቻ ሲያገኝለት ወይም የተሰበረውን ሲጠግንለት የሕፃኑ ፊት ምን ያህል እንደሚፈካ መገመት ትችላለህ። ይህ ለወላጁ ቀላል ሥራ ሊሆን ይችላል። ሕፃኑ ግን ዳግመኛ እንደማያገኘው ሆኖ ተሰምቶት የነበረውን መጫወቻ መልሶ በማግኘቱ በጣም ሊገረምና ፍንድቅድቅ ሊል ይችላል!

2 ከሁሉ የላቀው አባት ይሖዋ በምድር ላይ ያሉት ልጆቹ ዳግመኛ እንደማያገኙት ሆኖ የተሰማቸውን ነገር መልሰው እንዲያገኙ ማድረግ የሚያስችል ኃይል አለው። እርግጥ ነው እንዲህ ስንል ስለ ተራ መጫወቻዎች መናገራችን አይደለም። በዚህ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ ብዙዎቻችን በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ግምት የምንሰጣቸውን የተለያዩ ነገሮች እናጣለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በዛሬው ጊዜ ሰዎች እንደ ቤት፣ ንብረት፣ ሥራና ጤና የመሳሰሉትን በጣም የሚሳሱላቸውን ነገሮች ሊያጡ የሚችሉበት አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም በተፈጥሮ ሀብት ላይ እየደረሰ ስላለው ውድመትና በዚህ ሳቢያ እየጠፉ ስላሉት ብዙ ዝርያዎች ስናስብ በጣም ልንጨነቅ እንችላለን። ሆኖም የምንወደውን ሰው በሞት የማጣትን ያህል ቅስማችንን የሚሰብር ነገር የለም። በዚህ ጊዜ የሚሰማን የከንቱነት ስሜት በጣም ከባድ ነው።—2 ሳሙኤል 18:33

3. በሐዋርያት ሥራ 3:21 ላይ ምን የሚያጽናና ተስፋ ተገልጿል? ይሖዋ ይህን ተስፋ የሚፈጽመውስ በምን አማካኝነት ነው?

3 በመሆኑም ይሖዋ አንድን ነገር ለማደስ ወይም ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! ቀጥለን እንደምንመለከተው አምላክ በምድር ላሉት ልጆቹ በርካታ ነገሮችን መልሶ ይሰጣቸዋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን” ለማምጣት ዓላማ እንዳለው ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 3:21) ይህን የሚያከናውነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው መሲሐዊ መንግሥት አማካኝነት ነው። ማስረጃዎቹ እንደሚያሳዩት ይህ መንግሥት በ1914 በሰማይ መግዛት ጀምሯል። a (ማቴዎስ 24:3-14) ይሁንና የሚታደሰው ነገር ምንድን ነው? ይሖዋ ከሚያከናውናቸው ታላላቅ የተሃድሶ ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት። ከእነዚህ የተሃድሶ ሥራዎች መካከል አንዱ በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ወደፊት በስፋት ይከናወናሉ።

ንጹሑን አምልኮ መልሶ ማቋቋም

4, 5. በ607 ዓ.ዓ. የአምላክ ሕዝቦች ምን ደርሶባቸው ነበር? ይሖዋስ ምን ተስፋ ሰጣቸው?

4 ይሖዋ ንጹሑን አምልኮ መልሶ አቋቁሟል። ይህ ያስፈለገበትን ምክንያት ለመረዳት ወደ ኋላ መለስ ብለን የይሁዳን መንግሥት ታሪክ በአጭሩ እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋ አንድን ነገር ለማደስ የሚያስችለውን ኃይሉን በምን መንገድ ሲጠቀምበት እንደቆየ ለማስተዋል ይረዳናል።—ሮም 15:4

5 በ607 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌም ስትጠፋ ታማኝ አይሁዳውያን ምን ተሰምቷቸው ሊሆን እንደሚችል ገምት። በጣም የሚወዷት ከተማቸው ከመጥፋቷም በላይ ግንቦቿ ፈራርሰዋል። ከዚህ ሁሉ የከፋው ደግሞ በምድር ላይ ብቸኛው የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ማዕከል የነበረው ሰለሞን የገነባው ዕፁብ ድንቅ ቤተ መቅደስ እንዳልነበር መሆኑ ነው። (መዝሙር 79:1) በሕይወት የተረፉት አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን በግዞት በመወሰዳቸው የትውልድ አገራቸው የአራዊት መፈንጫ ሆነች። (ኤርምያስ 9:11) በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ ሁሉ ነገር ያበቃለት ይመስል ነበር። (መዝሙር 137:1) ይሁን እንጂ ይህ ጥፋት እንደሚደርስ ከረጅም ጊዜ በፊት የተናገረው ይሖዋ የተሃድሶ ዘመን እንደሚመጣም ተስፋ ሰጥቶ ነበር።

6-8. (ሀ) ዕብራውያን ነቢያት በጻፏቸው መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ ምን ነገር ተጠቅሶ እናገኛለን? ይህስ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (ለ) ስለ ተሃድሶ የተነገሩት በርካታ ትንቢቶች በዘመናችን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የተፈጸሙት እንዴት ነው?

6 እንዲያውም ዕብራውያን ነቢያት በጻፏቸው መጻሕፍት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ የተሃድሶ ትንቢት ተጠቅሶ እናገኛለን። b ይሖዋ ምድራቸው ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ እንደምትመለስ፣ በነዋሪዎች እንደምትሞላ፣ ለም እንደምትሆንና ከዱር አራዊትም ሆነ ከጠላት ጥቃት እንደምትጠበቅ በእነዚህ ነቢያት አማካኝነት ቃል ገብቶላቸው ነበር። ምድራቸው እንደ ኤደን ገነት እንደምትሆን ገልጾላቸዋል! (ኢሳይያስ 65:25፤ ሕዝቅኤል 34:25፤ 36:35) ከሁሉም በላይ ደግሞ ንጹሕ አምልኮ ተመልሶ ይቋቋማል፣ ቤተ መቅደሱም ዳግመኛ ይገነባል። (ሚክያስ 4:1-5) እነዚህ ትንቢቶች በግዞት ለነበሩት አይሁዳውያን ተስፋ በመስጠት በባቢሎን የኖሩባቸውን 70 ዓመታት በጽናት እንዲያሳልፉ ረድተዋቸዋል።

7 በመጨረሻም በትንቢት የተነገረው ተሃድሶ የሚከናወንበት ጊዜ ደረሰ። አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ነፃ ወጥተው ወደ ኢየሩሳሌም በመመለስ የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሰው ገነቡ። (ዕዝራ 1:1, 2) ከንጹሕ አምልኮ ፈቀቅ ሳይሉ በኖሩባቸው ዘመናት ሁሉ ይሖዋ የባረካቸው ከመሆኑም በላይ ምድራቸውን ለምና ፍሬያማ አድርጎላቸዋል። በተጨማሪም ከጠላቶቻቸውም ሆነ ለበርካታ ዓመታት በምድራቸው ላይ ሲፈነጩ ከነበሩት አራዊት ጠብቋቸዋል። ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም ሁሉን ነገር ስላደሰላቸው እጅግ ተደስተው መሆን አለበት! ይሁን እንጂ እነዚህ የተሃድሶ ትንቢቶች በዚያን ጊዜ ፍጻሜያቸውን ያገኙት በተወሰነ ደረጃ ብቻ ነበር። የላቀ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት፣ አስቀድሞ የተነገረለት የንጉሥ ዳዊት ዘር በሚነግሥበት “በዘመኑ መጨረሻ” ማለትም በእኛ ዘመን ነው።—ኢሳይያስ 2:2-4፤ 9:6, 7

8 ኢየሱስ በ1914 በሰማይ በሚገኘው መንግሥት ላይ ከነገሠ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በምድር ያሉት ታማኝ የአምላክ ሕዝቦች ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። በ537 ዓ.ዓ. ድል አድራጊው የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ቀሪዎቹን አይሁዳውያን ከባቢሎን ነፃ እንዳወጣ ሁሉ ኢየሱስም ቀሪዎቹን መንፈሳዊ አይሁዳውያን ማለትም ተከታዮቹን በዓለም ላይ ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች ከምታመለክተው “ታላቂቱ ባቢሎን” ተጽዕኖ አላቅቋቸዋል። (ራእይ 18:1-5፤ ሮም 2:29) በ1919 ይሖዋ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ንጹሑን አምልኮ መልሶ አቋቁሞላቸዋል። (ሚልክያስ 3:1-5) ከዚያን ጊዜ አንስቶ የይሖዋ ሕዝቦች በጸዳው መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ማለትም አምላክ ለንጹሕ አምልኮ ባደረገው ዝግጅት አማካኝነት አምልኳቸውን በማከናወን ላይ ናቸው። በዛሬው ጊዜ ይህ ለእኛ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

መንፈሳዊ ተሃድሶ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9. ከሐዋርያት ዘመን በኋላ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በእውነተኛው አምልኮ ላይ ምን ፈጽመዋል? ይሁን እንጂ ይሖዋ በዘመናችን ምን እርምጃ ወስዷል?

9 እስቲ የንጹሕ አምልኮን ታሪክ መለስ ብለን እንመልከት። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ብዙ መንፈሳዊ በረከት አግኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያት እውነተኛው አምልኮ እንደሚበረዝና እንደሚጠፋ ተንብየው ነበር። (ማቴዎስ 13:24-30፤ የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) ከሐዋርያት ዘመን በኋላ ሕዝበ ክርስትና ብቅ አለች። ቀሳውስቷ የአረማውያንን ትምህርቶችና ልማዶች ማስተማር ጀመሩ። አምላክ ሥላሴ እንደሆነ አድርገው በመግለጽ እንዲሁም ሰዎች ለቀሳውስት እንዲናዘዙና ወደ ይሖዋ ከመጸለይ ይልቅ ወደ ማርያም ወይም ወደ ሌሎች “ቅዱሳን” እንዲጸልዩ በማስተማር ከአምላክ እንዲርቁ አድርገዋል። ንጹሕ አምልኮ በዚህ መንገድ ለብዙ መቶ ዘመናት ተበክሎ ከቆየ በኋላ ይሖዋ ምን እርምጃ ወሰደ? በሐሰት ሃይማኖት በተጥለቀለቀውና አምላክ በሚያወግዛቸው መጥፎ ልማዶች በተበከለው በዚህ ዓለም ውስጥ እጁን ጣልቃ በማስገባት ንጹሑን አምልኮ መልሶ አቋቁሟል! ይህ ተሃድሶ በዘመናችን ከተፈጸሙት ታላላቅ ክንውኖች አንዱ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

10, 11. (ሀ) መንፈሳዊው ገነት ምን ሁለት ዋና ዋና ገጽታዎች አሉት? ይህስ ለአንተ ምን ጥቅም ያስገኛል? (ለ) ይሖዋ ወደ መንፈሳዊው ገነት የሰበሰበው ምን ዓይነት ሰዎችን ነው? ምን መብትስ ያገኛሉ?

10 በመሆኑም በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ይገኛሉ፤ ይህ ገነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተዋበ ነው። ይህ መንፈሳዊ ገነት ምን ነገሮችን ያቀፈ ነው? ሁለት ዋና ዋና ገጽታዎች አሉት። አንደኛው ገጽታ የእውነተኛው አምላክ የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ነው። ይሖዋ ከሐሰትና ከተሳሳቱ ትምህርቶች የጸዳ የአምልኮ ሥርዓት በማቋቋም ባርኮናል። በተጨማሪም መንፈሳዊ ምግብ አትረፍርፎ ሰጥቶናል። ይህም በሰማይ ስላለው አባታችን እንድናውቅ፣ እሱን ለማስደሰት እንድንጥርና ወደ እሱ እንድንቀርብ ያስችለናል። (ዮሐንስ 4:24) ሁለተኛው የመንፈሳዊ ገነት ገጽታ ደግሞ በውስጡ ካሉት ሰዎች ጋር የተያያዘ ነው። ኢሳይያስ በትንቢት እንደተናገረው ይሖዋ “በዘመኑ መጨረሻ” ሕዝቦቹን የሰላምን ጎዳና አስተምሯቸዋል። በመካከላችን ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል። ምንም እንኳ ፍጹም ባንሆንም “አዲሱን ስብዕና” እንድንለብስ ይረዳናል። ግሩም ባሕርያት እንድናፈራ የሚያስችለንን ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ጥረታችንን ይባርክልናል። (ኤፌሶን 4:22-24፤ ገላትያ 5:22, 23) ከአምላክ መንፈስ ጋር የሚስማማ ነገር የምታደርግ ከሆነ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ መኖር ትችላለህ።

11 ይሖዋ ወደዚህ መንፈሳዊ ገነት የሰበሰበው የሚወዳቸውን ሰዎች ማለትም እሱን የሚወዱ፣ ሰላምን የሚወዱና “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ” ሰዎችን ነው። (ማቴዎስ 5:3) የሰው ዘርም ሆነ መላዋ ምድር ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ የሚመለሱበትን ይበልጥ አስደናቂ የሆነ የተሃድሶ ዘመን ለማየት የሚታደሉት እንዲህ ያሉ ሰዎች ናቸው።

“እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ”

12, 13. (ሀ) ስለ ተሃድሶ የተነገሩት ትንቢቶች ሌላም ፍጻሜ አላቸው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በኤደን ገነት በገለጸው መሠረት ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው? ይህስ ምን ተስፋ ይሰጠናል?

12 ስለ ተሃድሶ የተነገሩት አብዛኞቹ ትንቢቶች የሚያመለክቱት መንፈሳዊ ተሃድሶን ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ያህል ኢሳይያስ የታመሙ፣ አንካሶች፣ ዓይነ ስውራንና መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንደሚፈወሱ አልፎ ተርፎም ሞት ራሱ ለዘላለም እንደሚዋጥ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 25:8፤ 35:1-7) እነዚህ ትንቢቶች በጥንት እስራኤል ቃል በቃል ፍጻሜያቸውን አላገኙም። በእኛም ዘመን ቢሆን ፍጻሜያቸውን ያገኙት በመንፈሳዊ ሁኔታ ነው፤ ወደፊት ግን ቃል በቃል በስፋት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ ብለን እንድናምን የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለን። እንዲህ ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?

13 ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ በኤደን ገነት ውስጥ አስታውቆ ነበር። ዓላማው ምድር ደስተኛና ጤናማ በሆኑ እንዲሁም አንድነት ባላቸው የሰው ልጆች እንድትሞላ ነው። የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ምድርንም ሆነ በላይዋ ያሉትን ፍጥረታት የመንከባከብና መላዋን ፕላኔት ወደ ገነትነት የመለወጥ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) በአሁኑ ጊዜ ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። ይሁን እንጂ የይሖዋ ዓላማ እንዳይፈጸም ሊያግድ የሚችል አንዳች ነገር እንደሌለ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ኢሳይያስ 55:10, 11) ይሖዋ የሾመው መሲሐዊው ንጉሥ ኢየሱስ መላዋን ምድር ወደ ገነትነት ይለውጣታል።—ሉቃስ 23:43

14, 15. (ሀ) ይሖዋ “ሁሉንም ነገር አዲስ” የሚያደርገው እንዴት ነው? (ለ) በገነት ውስጥ የሚኖረው ሕይወት ምን ይመስላል? አንተን ይበልጥ የሚያጓጓህ ምንድን ነው?

14 መላዋ ምድር ወደ ገነትነት ስትለወጥ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት! ይሖዋ ያንን ጊዜ አስመልክቶ ሲናገር “እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ” ብሏል። (ራእይ 21:5) ይህ ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል አስብ። ይሖዋ ኃይሉን ተጠቅሞ ይህን ክፉ አሮጌ ሥርዓት ሲያጠፋ “አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር” ይተካሉ። በሌላ አነጋገር አንድ አዲስ መንግሥት፣ ይሖዋን የሚወዱና ፈቃዱን የሚያደርጉ ሰዎችን ያቀፈውን አዲስ ምድራዊ ኅብረተሰብ ከሰማይ ሆኖ ያስተዳድራል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ሰይጣንና አጋንንቱ ምንም ማድረግ እንዳይችሉ ይታገዳሉ። (ራእይ 20:3) ከብዙ ሺህ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ልጆች ሰይጣንና አጋንንቱ ከሚያሳድሩት መጥፎና ጎጂ ተጽዕኖ ነፃ ይሆናሉ። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ እፎይታ ነው!

15 አምላክ መጀመሪያ ካወጣው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ይህችን ውብ ምድር መንከባከብ እንጀምራለን። ምድር በተፈጥሮዋ ራሷን በራሷ የማደስ ኃይል አላት። ለብክለት መንስኤ የሆኑት ነገሮች ከጠፉ የተበከሉ ሐይቆችና ወንዞች በውስጣቸው ያለውን መርዝ በማስወገድ ራሳቸውን ማጥራት ይችላሉ፤ ጦርነቶች ቢቆሙ በጦር መሣሪያ የተጎዱ መልክዓ ምድሮች የቀድሞ ውበታቸውን መልሰው መላበስ ይችላሉ። በዚህ የተፈጥሮ ሥርዓት በመጠቀም ምድርን ወደ ገነትነት መለወጥና ስፍር ቁጥር በሌላቸው ዕፀዋትና እንስሳት እንድትሞላ አስተዋጽኦ ማድረግ መቻል እንዴት የሚያስደስት ነው! የሰው ልጅ እንስሳትንና ዕፀዋትን ያለርኅራኄ መጨፍጨፉን አቁሞ በምድር ላይ ካሉ ፍጥረታት ሁሉ ጋር በሰላም መኖር ይጀምራል። ሕፃናትም እንኳ ቢሆኑ የዱር አራዊትን የሚፈሩበት ምንም ምክንያት አይኖርም።—ኢሳይያስ 9:6, 7፤ 11:1-9

16. ታማኝ የሆኑ ሰዎች በሙሉ በገነት ውስጥ በግለሰብ ደረጃ የሚታደሱት እንዴት ነው?

16 እኛም በግለሰብ ደረጃ በተለያየ መንገድ እንታደሳለን። ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተአምራዊ ፈውስ ሲካሄድ ይመለከታሉ። ኢየሱስ በምድር ሳለ እንዳደረገው በዚያን ጊዜም አምላክ የሰጠውን ኃይል በመጠቀም የዓይነ ስውራንን ዓይን ያበራል፣ መስማት የተሳናቸውን ጆሮ ይከፍታል እንዲሁም ሽባዎችን ይፈውሳል። (ማቴዎስ 15:30) አረጋውያን ጉልበታቸውና ጤንነታቸው ታድሶ ወደ ወጣትነታቸው ይመለሳሉ። (ኢዮብ 33:25) በእርጅና ምክንያት የሚመጣ የቆዳ መጨማደድ አይኖርም፤ የተኮማተሩ ጡንቻዎችና ጅማቶችም ይፍታታሉ። ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ኃጢአትና አለፍጽምና ያስከተሉባቸው ችግሮች ቀስ በቀስ ከላያቸው ሲወገዱ ይመለከታሉ። ይሖዋ አምላክ አስደናቂ የሆነውን ኃይሉን በመጠቀም እንዲህ ያለ ፈውስ ሲያደርግልን ምንኛ እናመሰግነው ይሆን! በዚህ አስደናቂ የተሃድሶ ዘመን የሚፈጸመውን ይበልጥ አስደሳች የሆነ አንድ ክንውን እስቲ እንመልከት።

ሙታንን ወደ ሕይወት መመለስ

17, 18. (ሀ) ኢየሱስ ሰዱቃውያንን የወቀሳቸው ለምንድን ነው? (ለ) ኤልያስ ይሖዋ ምን እንዲያደርግለት ጠየቀ? ለምንስ?

17 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የነበሩ ሰዱቃውያን በመባል የሚታወቁ አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በትንሣኤ አያምኑም ነበር። ኢየሱስ “እናንተ ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ስለማታውቁ ተሳስታችኋል” ሲል ወቅሷቸዋል። (ማቴዎስ 22:29) አዎን፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም የሞቱ ሰዎችን ወደ ሕይወት መመለስ እንደሚችል ይናገራሉ። እንዴት?

18 በኤልያስ ዘመን የተፈጸመን አንድ ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። አንዲት መበለት የምትወደው አንድያ ልጇ እጇ ላይ ሞቶባታል። በመበለቲቱ ቤት በእንግድነት ተቀምጦ የነበረው ነቢዩ ኤልያስ በጣም ደንግጦ መሆን አለበት። ቀደም ሲል ኤልያስ ይህን ልጅ ከረሃብ ታድጎት የነበረ ከመሆኑም በላይ ለልጁ ልዩ ፍቅር አድሮበት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። እናቱ ልቧ በሐዘን ተሰብሯል። በሞት ላጣችው ባሏ ያላት ምትክ ይህ አንድ ልጇ ብቻ ነበር። አድጎ ይጦረኛል ብላ ተስፋ የምታደርገው እሱን ነው። በጣም ከመረበሿና ግራ ከመጋባቷ የተነሳ በፈጸመችው ኃጢአት ሳቢያ አምላክ እየቀጣት እንዳለ አድርጋ አስባ ነበር። ኤልያስ የእናቲቱን ሁኔታ ሲመለከት አንጀቱ ተንሰፈሰፈ። የልጁን አስከሬን ከእናቲቱ እቅፍ ተቀብሎ በእንግድነት ወዳረፈበት ክፍል ከወሰደው በኋላ ወደ ሕይወት እንዲመልሰው ይሖዋን ተማጸነው።—1 ነገሥት 17:8-21

19, 20. (ሀ) አብርሃም፣ ይሖዋ አንድን ነገር ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል ኃይል እንዳለው እንደሚያምን ያሳየው እንዴት ነው? እንዲህ ዓይነት እምነት እንዲኖረው ያደረገውስ ምንድን ነው? (ለ) ኤልያስ ላሳየው እምነት ይሖዋ ወሮታ የከፈለው እንዴት ነው?

19 ከኤልያስ ዘመን በፊትም በትንሣኤ የሚያምኑ የአምላክ አገልጋዮች ነበሩ። ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት የኖረው አብርሃም ይሖዋ አንድን ነገር ለማደስ ወይም ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ያምን ነበር። እንዲህ ዓይነት እምነት ሊኖረው የቻለው ያለምክንያት አይደለም። አብርሃም 100 ዓመት፣ ሣራ ደግሞ 90 ዓመት ሞልቷቸው በነበረበት ወቅት ዘር የመተካት ችሎታቸውን መልሶ በመስጠት ሣራ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ልጅ እንድትወልድ አድርጓል። (ዘፍጥረት 17:17፤ 21:2, 3) ልጁ አድጎ ለአቅመ አዳም ሲደርስ አብርሃም ልጁን መሥዋዕት እንዲያደርግለት ይሖዋ ጠየቀው። አብርሃም የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን ይሖዋ መልሶ ሕያው ሊያደርግለት እንደሚችል እምነት ነበረው። (ዕብራውያን 11:17-19) ልጁን መሥዋዕት ለማድረግ ወደ ተራራው ከመውጣቱ በፊት ከይስሐቅ ጋር ተመልሰው እንደሚመጡ ለአገልጋዮቹ በእርግጠኝነት የነገራቸው እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት ስለነበረው ሊሆን ይችላል።—ዘፍጥረት 22:5

“ይኸው፣ ልጅሽ ሕያው ሆኗል”!

20 በጊዜው ይሖዋ ይስሐቅን መሥዋዕት ከመሆን እንዲተርፍ ስላደረገው በትንሣኤ ማስነሳት አላስፈለገውም። የመበለቲቱ ልጅ ግን ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሞቶ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ ልጁን ከሞት በማስነሳት ኤልያስ ላሳየው እምነት ወሮታ ከፍሎታል። ኤልያስም “ይኸው፣ ልጅሽ ሕያው ሆኗል” በማለት ልጁን ለእናቱ ሰጣት።—1 ነገሥት 17:22-24

21, 22. (ሀ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ከሞት ስለተነሱ ሰዎች የሚገልጹት ዘገባዎች ምን ይጠቁማሉ? (ለ) በገነት ውስጥ የሚፈጸመው ትንሣኤ ምን ያህል ስፋት ይኖረዋል? ይህን የሚያከናውነውስ ማን ነው?

21 ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም ሞቶ የነበረን ሰው መልሶ ሕያው እንዳደረገ የሚገልጸው የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይህ ነው። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ለኤልሳዕ፣ ለኢየሱስ፣ ለጳውሎስና ለጴጥሮስም ይህን ኃይል በመስጠት የሞቱ ሰዎችን እንዲያስነሱ አድርጓል። እርግጥ ነው፣ በዚያን ጊዜ ተነስተው የነበሩ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ሞተዋል። ሆኖም እንዲህ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ወደፊት የሚፈጸመውን ተስፋ ከወዲሁ የሚያመላክቱ ናቸው።

22 ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ሲል የገባውን ቃል በገነት ውስጥ በተግባር ይፈጽማል። (ዮሐንስ 11:25) በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሞት በማስነሳት በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንዲያገኙ ያደርጋል። (ዮሐንስ 5:28, 29) ሰዎች በሞት ተለይተዋቸው ከነበሩ ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው ጋር ዳግም ሲገናኙና ተቃቅፈው በደስታ ሲላቀሱ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት! ይሖዋ እንዲህ ያለ ኃይል ያለው አምላክ በመሆኑ ሰዎች ሁሉ ያወድሱታል።

23. ይሖዋ ኃይሉን ከሁሉ በላቀ መንገድ ያሳየው እንዴት ነው? ይህስ ለወደፊቱ ተስፋችን ዋስትና የሚሆነው እንዴት ነው?

23 ይሖዋ ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም አስተማማኝ ዋስትና ሰጥቷል። ልጁን ኢየሱስን ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር አድርጎ ከሞት በማስነሳትና ከእሱ ቀጥሎ ያለውን ማዕረግ በመስጠት ኃይሉን ከሁሉ በላቀ መንገድ አሳይቷል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አይተውታል። (1 ቆሮንቶስ 15:5, 6) በትንሣኤ ለሚጠራጠሩ ሰዎች እንኳ ይህ በቂ ማስረጃ ነው። ይሖዋ ዳግም ሕያው ለማድረግ የሚያስችል ኃይል አለው።

24. ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን እንደሚያስነሳ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? የትኛውን ተስፋስ ከፍ አድርገን ልንመለከተው ይገባል?

24 ይሖዋ ሰዎችን ከሞት ለማስነሳት የሚያስችል ኃይል ብቻ ሳይሆን ፍላጎትም አለው። ታማኙ ኢዮብ ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት እንደሚናፍቅ በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ ተናግሯል። (ኢዮብ 14:15) ይሖዋ ኃይሉን እንዲህ ባለ ፍቅራዊ መንገድ የሚጠቀምበት መሆኑ ወደ እሱ እንድትቀርብ አይገፋፋህም? ይሁን እንጂ ትንሣኤ ይሖዋ ከሚያከናውነው ታላቅ የተሃድሶ ሥራ ውስጥ አንዱ ብቻ መሆኑን አስታውስ። እንግዲያው ከምንጊዜውም ይበልጥ ወደ ይሖዋ ቅረብ፤ እንዲሁም አምላክ “ሁሉንም ነገር አዲስ [ለማድረግ]” የገባው ቃል ሲፈጸም የማየት ተስፋህን ከፍ አድርገህ ተመልከት።—ራእይ 21:5

a “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን” የጀመረው መሲሐዊው መንግሥት ተቋቁሞ የታማኙ ንጉሥ የዳዊት ወራሽ ዙፋን ላይ በተቀመጠበት ጊዜ ነው። ይሖዋ ለዳዊት፣ ዘሩ ለዘላለም እንደሚገዛ ቃል ገብቶለት ነበር። (መዝሙር 89:35-37) ይሁን እንጂ ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. በባቢሎን ከጠፋች በኋላ በአምላክ ዙፋን ላይ የነገሠ የዳዊት ዘር አልነበረም። ሆኖም የዳዊት ዘር ሆኖ በምድር ላይ የተወለደው ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ሲሾም አስቀድሞ በትንቢት የተነገረለት የዙፋን ወራሽ ሆኗል።

b ለምሳሌ ያህል ሙሴ፣ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ሆሴዕ፣ ኢዩኤል፣ አሞጽ፣ አብድዩ፣ ሚክያስና ሶፎንያስ እንዲህ ዓይነት መልእክት የያዘ ትንቢት ተናግረዋል።