በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 10

በኃይል አጠቃቀም ረገድ “አምላክን የምትመስሉ ሁኑ”

በኃይል አጠቃቀም ረገድ “አምላክን የምትመስሉ ሁኑ”

1. ፍጽምና የጎደለው የሰው ልጅ ብዙውን ጊዜ ሥልጣኑን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?

 “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል።” ይህ የተለመደ አባባል ሥልጣንና ኃይል ሰዎችን ሊያባልግ እንደሚችል የሚያሳይ ነው። ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ብዙውን ጊዜ ሥልጣናቸውን አላግባብ ሲጠቀሙበት ይታያል። በእርግጥም በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንደታየው “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።” (መክብብ 8:9) የሰው ልጅ ሥልጣኑንና ኃይሉን አላግባብ መጠቀሙ ያስከተለው ሰቆቃ በቃላት ሊገለጽ አይችልም።

2, 3. (ሀ) ይሖዋ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ያለን ኃይል ምን ነገሮችን የሚጨምር ሊሆን ይችላል? ይህን ኃይላችንንስ እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል?

2 ይሖዋ አምላክ ገደብ የለሽ ኃይል ያለው ቢሆንም እንኳ ይህን ኃይሉን አላግባብ ተጠቅሞበት የማያውቅ መሆኑ የሚያስደንቅ አይደለም? ቀደም ባሉት ምዕራፎች ላይ እንዳየነው ለመፍጠር፣ ለማጥፋት፣ ለመጠበቅም ሆነ ለማደስ የሚያስችለውን ኃይሉን የሚጠቀምበት ፍቅር ከሚንጸባረቅባቸው ዓላማዎቹ ጋር በሚስማማ መንገድ ነው። ኃይሉን እንዴት እንደሚጠቀምበት ስናሰላስል ወደ እሱ ለመቅረብ እንገፋፋለን። ይህ ደግሞ ኃይላችንን በአግባቡ በመጠቀም ‘አምላክን ለመምሰል’ እንድንጣጣር ሊያነሳሳን ይችላል። (ኤፌሶን 5:1) ይሁንና እዚህ ግቡ የማንባል እኛ የሰው ልጆች ምን ኃይል አለን?

3 የሰው ልጅ “በአምላክ መልክ” እና አምሳል እንደተፈጠረ አስታውስ። (ዘፍጥረት 1:26, 27) በመሆኑም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ኃይል አለን። ያለን ኃይል የተለያዩ ነገሮች ለማከናወን የሚያስችል አቅምን፣ በሌሎች ላይ የሚኖረንን ሥልጣን፣ በሰዎች ላይ በተለይ ደግሞ በሚወዱን ሰዎች ላይ የምናሳድረውን ተጽዕኖ፣ አካላዊ ጥንካሬን (ጉልበትን) ወይም ቁሳዊ ሀብትን የሚጨምር ሊሆን ይችላል። መዝሙራዊው ስለ ይሖዋ ሲናገር “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነው” ብሏል። (መዝሙር 36:9) ስለዚህ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የኃይላችን ምንጭ አምላክ ነው። ስለሆነም ይህን ኃይላችንን እሱን በሚያስደስት መንገድ ልንጠቀምበት ይገባል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ቁልፉ ፍቅር ነው

4, 5. (ሀ) ኃይልን በአግባቡ ለመጠቀም የሚረዳው ቁልፍ ምንድን ነው? አምላክ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ይህን የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው? (ለ) ፍቅር ያለንን ኃይል በአግባቡ እንድንጠቀም የሚረዳን እንዴት ነው?

4 ኃይልን በአግባቡ ለመጠቀም ቁልፉ ፍቅር ነው። አምላክ ኃይሉን የሚጠቀምበት መንገድ ይህን የሚያንጸባርቅ አይደለም? በምዕራፍ 1 ላይ የአምላክን አራት ዋና ዋና ባሕርያት ማለትም ኃይሉን፣ ፍትሑን፣ ጥበቡንና ፍቅሩን አስመልክቶ የተሰጠውን ማብራሪያ አስታውስ። ከእነዚህ አራት ባሕርያት መካከል ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው የትኛው ነው? ፍቅር ነው። አንደኛ ዮሐንስ 4:8 “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። አዎን፣ ይሖዋ ሁለንተናው ፍቅር ስለሆነ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተገፋፍቶ ነው። በማንኛውም ጊዜ ኃይሉን የሚጠቀመው በፍቅር ተነሳስቶ ሲሆን ይህንንም የሚያደርገው የሚወዱትን ሁሉ ለመጥቀም ሲል ነው።

5 እኛም ያለንን ኃይል በአግባቡ እንድንጠቀምበት የሚረዳን ፍቅር ነው። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር “ደግ ነው። . . . የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) በመሆኑም ፍቅር ካለን በእኛ ሥልጣን ሥር ያሉትን ሰዎች አናንገላታም ወይም አንጨቁንም። ከዚህ ይልቅ ለሌሎች አክብሮት የምናሳይ ከመሆኑም በላይ ለእነሱ ፍላጎትና ስሜት ቅድሚያ እንሰጣለን።—ፊልጵስዩስ 2:3, 4

6, 7. (ሀ) አምላክን መፍራት ሲባል ምን ማለት ነው? ይህስ ባሕርይ ሥልጣንንና ኃይልን አላግባብ ከመጠቀም እንድንቆጠብ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አምላክን ላለማሳዘን መፍራትና አምላክን መውደድ ምን ዝምድና እንዳላቸው በምሳሌ አስረዳ።

6 ፍቅር ያለንን ኃይል በአግባቡ እንድንጠቀምበት ሊረዳን ከሚችል ሌላም ባሕርይ ጋር ዝምድና አለው። ይህ ባሕርይ ለአምላክ ያለን ፍርሃት ነው። አምላክን መፍራታችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ምሳሌ 16:6 “[ሰው] ይሖዋን በመፍራት ከክፋት ይርቃል” ይላል። ልንርቃቸው ከሚገቡ ክፉ ነገሮች አንዱ ኃይልን አላግባብ መጠቀም ነው። አምላክን መፍራታችን በእኛ ሥልጣን ሥር ያሉ ሰዎችን እንዳንበድል ያግደናል። እንዴት? በመጀመሪያ ደረጃ፣ በእነዚህ ሰዎች ላይ የምንፈጽመው ነገር በአምላክ ፊት እንደሚያስጠይቀን እንገነዘባለን። (ነህምያ 5:1-7, 15) ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ፍርሃት ሌላም የሚጨምረው ነገር አለ። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “ፍርሃትን” ለመግለጽ የተጠቀሱት ቃላት ብዙውን ጊዜ ከጥልቅ አድናቆትና አክብሮት የመነጨ ፍርሃትን ያመለክታሉ። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ አምላካዊ ፍርሃትን ለእሱ ካለን ፍቅር ጋር አዛምዶ ይገልጸዋል። (ዘዳግም 10:12, 13) ይህ ከአድናቆት የመነጨ አክብሮት አምላክን ላለማሳዘን ስንል የምናሳየውን ትክክለኛ ፍርሃት ይጨምራል። እንዲህ ዓይነት ፍርሃት የምናሳየው ይቀጣናል ብለን በመስጋት ሳይሆን አምላክን ከልብ ስለምንወደው ነው።

7 ይህን ለማስረዳት በአንድ ትንሽ ልጅና በአባቱ መካከል የሚኖረውን ጥሩ ግንኙነት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ልጁ አባቱ እንደሚወደው በሚገባ ያውቃል። ይሁን እንጂ አባቱ ከእሱ ምን እንደሚጠብቅና ቢያጠፋ ሊቀጣው እንደሚችልም ያውቃል። እንዲህ ሲባል ግን አባቱን በመፍራት እየተሸማቀቀ ይኖራል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አባቱን ከልብ እንደሚወደው የታወቀ ነው። ልጁ አባቱን የሚያስደስት ነገር ለማድረግ ይጥራል። አምላክን የሚፈራ ሰው የሚያደርገውም እንዲሁ ነው። ሰማያዊ አባታችን የሆነውን ይሖዋን ስለምንወደው ‘ልቡን የሚያሳዝን’ ነገር ላለማድረግ እንጠነቀቃለን። (ዘፍጥረት 6:6) ከዚህ ይልቅ ልቡን ለማስደሰት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን። (ምሳሌ 27:11) ያለንን ሥልጣንና ኃይል በአግባቡ ለመጠቀም የምንጥረውም ለዚህ ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመርምር።

በቤተሰብ ውስጥ

8. (ሀ) ባል በቤተሰብ ውስጥ ምን ሥልጣን አለው? ሥልጣኑንስ እንዴት ሊጠቀምበት ይገባል? (ለ) አንድ ባል ሚስቱን እንደሚያከብራት ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?

8 በመጀመሪያ እስቲ በቤተሰብ ክልል ውስጥ ያለውን ሁኔታ እንመልከት። ኤፌሶን 5:23 “[ባል] የሚስቱ ራስ ነው” ሲል ይገልጻል። አንድ ባል አምላክ የሰጠውን ይህን ሥልጣን ሊጠቀምበት የሚገባው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ባሎችን “[ከሚስቶቻችሁ] ጋር በእውቀት አብራችሁ ኑሩ። . . . ከእናንተ ይበልጥ እንደ ተሰባሪ ዕቃ የሆኑትን ሴቶችን አክብሯቸው” በማለት ይመክራቸዋል። (1 ጴጥሮስ 3:7) እዚህ ጥቅስ ላይ “አክብሮት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ዋጋ፣ ግምት፣ . . . ማዕረግ” ማለት ነው። የዚህ ቃል ርቢ “ስጦታ” እና “ክቡር” ተብሎም ተተርጉሟል። (የሐዋርያት ሥራ 28:10፤ 1 ጴጥሮስ 2:7) ሚስቱን የሚያከብር ባል አይደበድባትም ወይም በማዋረድና በማንቋሸሽ የከንቱነት ስሜት እንዲሰማት አያደርግም። ከዚህ ይልቅ ከፍ ያለ ዋጋ እንዳላት በመገንዘብ በአክብሮት ይይዛታል። ለእሱ ምን ያህል ውድ ወይም ክቡር እንደሆነች በግልም ይሁን በሰው ፊት በቃልና በድርጊት ይገልጽላታል። (ምሳሌ 31:28) እንዲህ ያለው ባል የሚስቱን ፍቅርና አክብሮት ብቻ ሳይሆን የአምላክንም ሞገስ ያገኛል።

ባሎችና ሚስቶች አንዳቸው ለሌላው ፍቅርና አክብሮት በማሳየት ኃይላቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይችላሉ

9. (ሀ) ሚስት በቤተሰብ ውስጥ ምን ቦታ አላት? (ለ) አንዲት ሚስት ያላትን ችሎታ ባሏን ለመደገፍ እንድትጠቀምበት ሊረዳት የሚችለው ምንድን ነው? ይህስ ምን ውጤት አለው?

9 ሚስቶችም በቤተሰብ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የራስነት ሥልጣንን ሳይጥሱ በባሎቻቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ ስላሳደሩ ወይም ባሎቻቸው የተሳሳተ ውሳኔ እንዳያደርጉ ስለረዱ አምላክን የሚፈሩ ሴቶች ይናገራል። (ዘፍጥረት 21:9-12፤ 27:46 እስከ 28:2) አንዲት ሚስት ከባሏ ይበልጥ ፈጣን የሆነ አእምሮ ወይም እሱ የሌሉት አንዳንድ ችሎታዎች ይኖሯት ይሆናል። ሆኖም ባሏን ‘በጥልቅ ማክበር’ ያለባት ከመሆኑም በላይ ‘ለጌታ እንደምትገዛ ሁሉ ለባሏ መገዛት’ ይኖርባታል። (ኤፌሶን 5:22, 33) አምላክን ለማስደሰት ያላት ፍላጎት ባሏን ከመናቅ ወይም በባሏ ላይ ለመሠልጠን ከመሞከር ይልቅ ያላትን ችሎታ እሱን ለመደገፍ እንድትጠቀምበት ሊያነሳሳት ይችላል። እንዲህ ያለች “ጥበበኛ ሴት” ከባሏ ጋር በመተባበር ቤተሰቧን ለመገንባት ትጥራለች። እንዲህ በማድረግ ከአምላክ ጋር ያላትን ሰላም ጠብቃ ትኖራለች።—ምሳሌ 14:1

10. (ሀ) አምላክ ለወላጆች ምን ሥልጣን ሰጥቷል? (ለ) “ተግሣጽ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው? እንዴትስ መሰጠት ይኖርበታል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

10 አምላክ ለወላጆችም የሰጠው ሥልጣን አለ። መጽሐፍ ቅዱስ “አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው” የሚል ምክር ይሰጣል። (ኤፌሶን 6:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተግሣጽ” የሚለው ቃል “ኮትኩቶ ማሳደግን፣ ማሠልጠንንና ማስተማርን” ሊያመለክት ይችላል። ልጆች በጥሩ ሁኔታ ተኮትኩተው እንዲያድጉ ከተፈለገ በግልጽ የተቀመጡ መመሪያዎችና ደንቦች ሊሰጧቸው ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን ተግሣጽ ወይም ማሠልጠኛ ከፍቅር ጋር አያይዞ ይገልጸዋል። (ምሳሌ 13:24) ስለሆነም “የተግሣጽ በትር” የልጆችን ስሜትም ሆነ አካል የሚጎዳ መሆን የለበትም። a (ምሳሌ 22:15፤ 29:15) ድርቅ ያለ ሕግ ማውጣት ወይም ፍቅርና ርኅራኄ የሌለው ተግሣጽ መስጠት የወላጅነት ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም ከመሆኑም በላይ የልጁን ስሜት ሊጎዳ ይችላል። (ቆላስይስ 3:21) በሌላ በኩል ግን ልጆች በተገቢው መንገድ ሚዛናዊ የሆነ ተግሣጽ የሚሰጣቸው ከሆነ ወላጆቻቸው እንደሚወዷቸው እንዲሁም ጥሩ ልጆች ሆነው እንዲያድጉ የሚፈልጉ መሆኑን እንዲገነዘቡ ያደርጋቸዋል።

11. ልጆች ኃይላቸውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው?

11 ልጆችስ ያላቸውን ኃይል በአግባቡ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው? ምሳሌ 20:29 “የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው” ይላል። በእርግጥም ወጣቶች ያላቸውን ጉልበትና ኃይል በተሻለ መንገድ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ‘ታላቁን ፈጣሪያቸውን’ ሲያገለግሉ ብቻ ነው። (መክብብ 12:1) ወጣቶች የሚያደርጉት ነገር በወላጆቻቸው ስሜት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዳለ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 23:24, 25) ልጆች ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ወላጆቻቸውን ሲታዘዙና በትክክለኛው የሕይወት ጎዳና ላይ ሲጓዙ የወላጆቻቸውን ልብ ደስ ያሰኛሉ። (ኤፌሶን 6:1) እንዲህ ማድረጋቸው “ጌታን ያስደስተዋል።”—ቆላስይስ 3:20

በጉባኤ ውስጥ

12, 13. (ሀ) ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ሥልጣን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? (ለ) ሽማግሌዎች መንጋውን በርኅራኄ መያዝ ያለባቸው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

12 ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሚመሩ የበላይ ተመልካቾችን ሾሟል። (ዕብራውያን 13:17) ለዚህ ኃላፊነት የበቁ ወንዶች አምላክ የሰጣቸውን ሥልጣን ለመንጋው አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግና መንጋውን በመንፈሳዊ ለመንከባከብ ሊጠቀሙበት ይገባል። ሽማግሌዎች ሥልጣናቸውን የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለመጫን ሊጠቀሙበት ይገባል? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ በጉባኤው ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራቸው የሚገባ ከመሆኑም በላይ ራሳቸውን ከፍ አድርገው ማየት የለባቸውም። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) መጽሐፍ ቅዱስ ለበላይ ተመልካቾች “በገዛ ልጁ ደም የዋጀውን ጉባኤውን እረኛ ሆናችሁ [ጠብቁ]” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል። (የሐዋርያት ሥራ 20:28) ይህ ማሳሰቢያ ሽማግሌዎች እያንዳንዱን የመንጋው አባል በርኅራኄ እንዲይዙ ሊገፋፋቸው ይገባል።

13 ይህን ሁኔታ በሚከተለው መንገድ በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል። የቅርብ ጓደኛህ አንድ ውድ ዕቃ እንድትይዝለት በአደራ ሰጠህ እንበል። ይህን ዕቃ በውድ ዋጋ እንደገዛው ታውቃለህ። በመሆኑም ዕቃውን በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደምትይዘው የታወቀ ነው። በተመሳሳይም አምላክ ለሽማግሌዎች ውድ ዋጋ ያለው ንብረት ማለትም በበጎች የተመሰሉ አባላትን ያቀፈ ጉባኤ በአደራ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 21:16, 17) ይሖዋ በጎቹን በጣም ስለሚወዳቸው በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ውድ ደም ገዝቷቸዋል። ይሖዋ ለበጎቹ ከሁሉ የላቀውን ውድ ዋጋ ከፍሏል። ትሑት የሆኑ ሽማግሌዎች ይህን ስለሚገነዘቡ የይሖዋን በጎች በእንክብካቤ ይይዛሉ።

‘የአንደበት ኃይል’

14. አንደበት ምን ኃይል አለው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ “አንደበት የሞትና የሕይወት ኃይል አላት” ይላል። (ምሳሌ 18:21) በእርግጥም አንደበት ብዙ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። አሳቢነት በጎደለው ወይም ክብርን ዝቅ በሚያደርግ አነጋገር ስሜቱ ያልቆሰለ ማን አለ? ይሁን እንጂ አንደበት የመፈወስም ኃይል አለው። ምሳሌ 12:18 “የጥበበኞች ምላስ . . . ፈውስ ነው” ይላል። አዎን፣ የሚያበረታታና መንፈስን የሚያድስ ቃል የልብን ቁስል እንደሚጠግንና እንደሚፈውስ ዘይት ነው። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

15, 16. አንደበታችንን ሌሎችን ለማበረታታት ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?

15 አንደኛ ተሰሎንቄ 5:14 “የተጨነቁትን አጽናኗቸው” የሚል ምክር ይሰጣል። አዎን፣ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ሊያጋጥማቸው ይችላል። እንዲህ ያሉትን ሰዎች መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? በይሖዋ ፊት ውድ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ለመርዳት ጥሩ ጎናቸውን ለይተህ በመጥቀስ ከልብ አመስግናቸው። ይሖዋ ‘ልባቸው ለተሰበረና መንፈሳቸው ለተደቆሰ’ ሰዎች እንደሚያስብና እንደሚጨነቅ እንዲሁም እንደሚወዳቸው የሚያሳዩ ጥቅሶችን አንብብላቸው። (መዝሙር 34:18) አንደበታችንን ሌሎችን ለማጽናናት የምንጠቀምበት ከሆነ ‘ተስፋ የቆረጡትን የሚያጽናናውን’ ሩኅሩኅ አምላካችንን እንደምንመስል እናሳያለን።—2 ቆሮንቶስ 7:6 ሕያው ቃል

16 በተጨማሪም አንደበታችን ያለውን ኃይል ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ቀርበን ለማበረታታት ልንጠቀምበት እንችላለን። የቅርብ ዘመድ ወይም ወዳጅ የሞተባቸው ወንድሞች ወይም እህቶች አሉ? እንደምናስብላቸውና የሐዘናቸው ተካፋይ እንደሆንን የሚያሳዩ ቃላትን ብንናገር ሊጽናኑ ይችላሉ። ፈላጊ እንደሌላቸው የሚሰማቸው በዕድሜ የገፉ ወንድም ወይም እህት አሉ? የታሰበባቸው ቃላት በመናገር እንደሚወደዱና እንደሚፈለጉ እንዲሰማቸው መርዳት እንችላለን። በከባድ ሕመም የሚሠቃይ ሰው ካለ ደግሞ ስልክ ደውለህ፣ ካርድ ልከህ ወይም በአካል ተገኝተህ ብታበረታታው እጅግ ሊጽናና ይችላል። አንደበታችን ያለውን ኃይል ሌሎችን ‘ለማነጽ’ ስንጠቀምበት ፈጣሪያችን እጅግ ይደሰታል።—ኤፌሶን 4:29

17. አንደበታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ ያለብንስ ለምንድን ነው?

17 አንደበታችን ያለውን ኃይል ከሁሉ በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ስንናገር ነው። ምሳሌ 3:27 “ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል አቅም ካለህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል” ይላል። ሕይወት አድን የሆነውን ምሥራች ለሰዎች የመንገር ግዴታ አለብን። ይሖዋ በደግነት የሰጠንን አስቸኳይ መልእክት ለራሳችን ብቻ ይዘን መቀመጥ ተገቢ አይሆንም። (1 ቆሮንቶስ 9:16, 22) ሆኖም ይሖዋ በዚህ ሥራ እንድንካፈል የሚፈልገው እስከ ምን ድረስ ነው?

ምሥራቹን ለሌሎች መስበክ ኃይላችንን በአግባቡ መጠቀም የምንችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው

‘በሙሉ ኃይላችን’ ይሖዋን ማገልገል

18. ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው?

18 ለይሖዋ ያለን ፍቅር በክርስቲያናዊው አገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ እንድናደርግ ይገፋፋናል። በዚህ ረገድ ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ምንድን ነው? ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ሁላችንም ልናደርግ የሚገባውን ሲገልጽ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ እንደምታደርጉት በማሰብ በሙሉ ነፍሳችሁ አድርጉት።” (ቆላስይስ 3:23) ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጠውን ትእዛዝ አስመልክቶ ሲናገር “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ” ብሏል። (ማርቆስ 12:30) አዎን፣ ይሖዋ እያንዳንዳችን በሙሉ ነፍሳችን እንድንወደውና እንድናገለግለው ይፈልጋል።

19, 20. (ሀ) ነፍስ የሚለው ቃል ልብን፣ አእምሮንና ኃይልን የሚያጠቃልል ከሆነ በማርቆስ 12:30 ላይ እነዚህ ነገሮች ተለይተው የተጠቀሱት ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ምን ማለት ነው?

19 በሙሉ ነፍስ አምላክን ማገልገል ሲባል ምን ማለት ነው? ነፍስ የሚለው ቃል አካላዊና አእምሯዊ ችሎታን ጨምሮ የአንድን ሰው ሁለንተና ያመለክታል። ነፍስ ልብን፣ አእምሮንና ኃይልን የሚያጠቃልል ከሆነ በማርቆስ 12:30 ላይ እነዚህ ነገሮች ተለይተው የተጠቀሱት ለምንድን ነው? አንድ ምሳሌ እንመልከት። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ሰው ራሱን (ነፍሱን) ለባርነት ሊሸጥ ይችል ነበር። ሆኖም ባሪያው ጌታውን በሙሉ ልብ ላያገለግለው ይችላል፤ አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ችሎታውን ሙሉ በሙሉ ተጠቅሞ ጌታውን ለማገልገል ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። (ቆላስይስ 3:22) በመሆኑም ኢየሱስ ልብን፣ አእምሮንና ኃይልን ለይቶ መጥቀስ የፈለገው ምንም ነገር ሳንቆጥብ አምላክን ማገልገል እንዳለብን ጎላ አድርጎ ለመግለጽ መሆን አለበት። አምላክን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ሲባል ያለንን ኃይልና ጉልበት ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ራሳችንን ለእሱ አገልግሎት ማዋል ማለት ነው።

20 በሙሉ ነፍስ ማገልገል አለብን ሲባል ሁላችንም ለአገልግሎት የምናውለው ጊዜና ጉልበት እኩል መሆን አለበት ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ምክንያቱም የእያንዳንዳችን ሁኔታና ችሎታ ይለያያል። ለምሳሌ ያህል፣ ጥሩ ጤንነትና ጉልበት ያለው አንድ ወጣት በዕድሜ መግፋት ሳቢያ አቅሙ ውስን ከሆነ ሰው ይበልጥ በስብከቱ ሥራ ብዙ መሥራት ይችል ይሆናል። ትዳር ያልያዘና የቤተሰብ ኃላፊነት የሌለበት አንድ ሰው የቤተሰብ ኃላፊነት ካለበት ሰው ይበልጥ ማገልገል ይችል ይሆናል። በስብከቱ ሥራ ይበልጥ ለማገልገል የሚያስችል አቅምና ሁኔታ ካለን ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል! እርግጥ ነው፣ በዚህ ረገድ ራሳችንን ከሌሎች ጋር በማወዳደር የምንተችና የምንነቅፍ መሆን የለብንም። (ሮም 14:10-12) ከዚህ ይልቅ ኃይላችንን ሌሎችን ለማበረታታት ልንጠቀምበት ይገባል።

21. ኃይላችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?

21 ይሖዋ ያለውን ኃይል በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ፍጹም ምሳሌያችን ነው። ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ብንሆንም እሱን ለመምሰል የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። በእኛ ሥልጣን ሥር ያሉትን ሁሉ በአክብሮት በመያዝ ኃይላችንን በአግባቡ ልንጠቀምበት እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የሰጠንን ሕይወት አድን የሆነ የስብከት ሥራ በሙሉ ነፍሳችን ማከናወን ይኖርብናል። (ሮም 10:13, 14) አቅምህ የሚፈቅደውን ሁሉ በማድረግ በሙሉ ነፍስህ እሱን ለማገልገል የምታደርገው ጥረት ይሖዋን እንደሚያስደስተው አስታውስ። አቅምህንና ሁኔታህን የሚረዳልህን እንዲህ ያለውን አፍቃሪ አምላክ ለማገልገል አትነሳሳም? ኃይልህን መጠቀም የምትችልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ይህ ነው።

a “በትር” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ እረኛ በጎቹን ለመምራት የሚጠቀምበትን ዱላ ወይም ዘንግ ያመለክታል። (መዝሙር 23:4) በተመሳሳይም ወላጆች የሚጠቀሙበት “በትር” በፍቅር መመሪያ መስጠትን እንጂ በጭካኔ ወይም በኃይል መደብደብን አያመለክትም።