በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 14

ይሖዋ “በብዙ ሰዎች ምትክ . . . ቤዛ” አዘጋጀ

ይሖዋ “በብዙ ሰዎች ምትክ . . . ቤዛ” አዘጋጀ

1, 2. መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ያሉበትን ሁኔታ የሚገልጸው እንዴት ነው? ብቸኛው መፍትሔስ ምንድን ነው?

 “ፍጥረት ሁሉ . . . አብሮ በመቃተትና በመሠቃየት ላይ [ይገኛል]።” (ሮም 8:22) ሐዋርያው ጳውሎስ የሰው ልጆች የሚገኙበትን አሳዛኝ ሁኔታ በዚህ መንገድ ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። በሰብዓዊ ዓይን ሲታይ ሥቃይ፣ ኃጢአትና ሞት ምንም ዓይነት መፍትሔ የሌላቸው ነገሮች ሊመስሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንደ ሰዎች አቅሙ ውስን አይደለም። (ዘኁልቁ 23:19) የፍትሕ አምላክ የሆነው ይሖዋ ከሥቃይና ከመከራ ለመገላገል የሚያስችለንን ቤዛ አዘጋጅቶልናል።

2 ቤዛው ይሖዋ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ነው። ከኃጢአትና ከሞት ባርነት መላቀቅ የምንችልበትን መንገድ ከፍቶልናል። (ኤፌሶን 1:7) በሰማይም ሆነ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋችን የተመካው በቤዛው ዝግጅት ላይ ነው። (ሉቃስ 23:43፤ ዮሐንስ 3:16፤ 1 ጴጥሮስ 1:4) ለመሆኑ ቤዛው ምንድን ነው? ወደር የለሽ ስለሆነው የይሖዋ ፍትሕስ ምን ያስተምረናል?

ቤዛ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

3. (ሀ) ቤዛ ያስፈለገው ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ በአዳም ዘሮች ላይ የተበየነውን የሞት ፍርድ እንዲሁ መሰረዝ የማይችለው ለምንድን ነው?

3 ቤዛ ያስፈለገው አዳም በሠራው ኃጢአት ምክንያት ነው። አዳም በአምላክ ላይ በማመፁ ለዘሮቹ በሽታን፣ ሐዘንን፣ ሥቃይንና ሞትን አውርሷል። (ዘፍጥረት 2:17፤ ሮም 8:20) አምላክ ለእኛ በማዘን የሞት ፍርዱን እንዲሁ መሰረዝ አይችልም። እንዲህ ቢያደርግ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው” የሚለውን ራሱ ያወጣውን ሕግ ችላ እንዳለ ያስቆጥርበታል። (ሮም 6:23) በተጨማሪም ይሖዋ በዚህ መንገድ ፍትሐዊ ሕጎቹን የሚሽር ቢሆን ኖሮ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ሥርዓት አልበኝነትና ሕገ ወጥነት ይነግሥ ነበር!

4, 5. (ሀ) ሰይጣን የአምላክን ስም ያጠፋው እንዴት ነው? ይሖዋ እነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለበት የተሰማውስ ለምንድን ነው? (ለ) ሰይጣን የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች በተመለከተ ምን ክስ አቅርቧል?

4 ምዕራፍ 12 ላይ እንደተመለከትነው በኤደን የተፈጸመው ዓመፅ ትላልቅ ጥያቄዎችንም አስነስቷል። ሰይጣን የአምላክን መልካም ስም አጉድፏል። ይሖዋ ውሸታም እንደሆነና ፍጥረታቱን ነፃነት የሚነፍግ ጨካኝና አምባገነን ገዢ እንደሆነ አድርጎ ከሶታል። (ዘፍጥረት 3:1-5) በተጨማሪም ሰይጣን፣ ይሖዋ ምድርን ጻድቅ በሆኑ ሰዎች ለመሙላት ያለው ዓላማ የተሰናከለ እንዲመስል በማድረግ ያሰበውን ማሳካት የማይችል አምላክ እንደሆነ አድርጎ ለማቅረብ ሞክሯል። (ዘፍጥረት 1:28፤ ኢሳይያስ 55:10, 11) ይሖዋ እነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ባይፈቅድ ኖሮ የማሰብ ችሎታ ያላቸው አብዛኞቹ ፍጥረታቱ በእሱ አገዛዝ ላይ ያላቸውን አመኔታ ሊያጡ ይችሉ ነበር።

5 ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች አምላክን የሚያገለግሉት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ብቻ እንደሆነና ችግር ቢደርስባቸው ሁሉም አምላክን እንደሚክዱ በመግለጽ ስማቸውን አጥፍቷል። (ኢዮብ 1:9-11) አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው እነዚህ የላቀ ግምት የሚሰጣቸው አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ሲል ነው። ይሖዋ፣ ሰይጣን ያቀረባቸው የሐሰት ክሶች መልስ እንዲያገኙ ማድረግ እንዳለበት ተሰምቶታል። ይሁን እንጂ አምላክ እነዚሁ አከራካሪ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙና የሰው ልጆች እንዲድኑ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?

ቤዛ ምንድን ነው?

6. አምላክ የሰው ልጆችን ለማዳን ያደረገው ዝግጅት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምን የተለያዩ መንገዶች ተገልጿል?

6 ይሖዋ ያቀረበው መፍትሔ ታላቅ ምሕረትና ፍጹም የሆነ ፍትሕ የተንጸባረቀበት ነው። ሰዎች መቼም ቢሆን እንዲህ ያለ ግሩም መፍትሔ ሊያመጡ አይችሉም። ይሁንና ይሖዋ ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ የተጠቀመበት ዝግጅት በሚያስደንቅ ሁኔታ በጣም ቀላል ነው። ይህ ዝግጅት መዋጀት፣ ማስታረቅና ማስተሰረይ ተብሎ በተለያየ መንገድ ተገልጿል። (ዳንኤል 9:24፤ ገላትያ 3:13፤ ቆላስይስ 1:19, 20) ይሁን እንጂ ይህን ዝግጅት በተሻለ መንገድ የሚገልጸው ኢየሱስ ራሱ የተጠቀመበት ቃል ነው። “የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ [በግሪክኛ ሊትሮን] አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም” ሲል ተናግሯል።—ማቴዎስ 20:28

7, 8. (ሀ) “ቤዛ” የሚለው ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ምን ትርጉም አለው? (ለ) ቤዛ የሚለው ቃል ተመጣጣኝ የሆነን ነገር የሚያመለክተው በምን መንገድ ነው?

7 ቤዛ ምንድን ነው? ቤዛን ለመግለጽ የገባው የግሪክኛ ግስ “መፍታት፣ መልቀቅ” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ቃል የጦር እስረኞችን ለማስለቀቅ የሚከፈልን ገንዘብ ለማመልከት ይሠራበት ነበር። እንግዲያው ቤዛ፣ አንድን ነገር መልሶ ለማግኘት የሚከፈል ዋጋ እንደሆነ ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል። በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ቤዛ” (ኮፌር) የሚለው ቃል “መሸፈን” የሚል ትርጉም ካለው ግስ የመጣ ነው። ይህም መቤዠት የሚለው ቃል ኃጢአትን መሸፈን የሚል ትርጉም እንዳለውም እንድንገነዘብ ይረዳናል።

8 ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት ይህ ቃል (ኮፌር) “ምንጊዜም ተመጣጣኝ የሆነን ነገር እንደሚያመለክት” ይገልጻል። በመሆኑም ኃጢአትን ለመቤዠት ወይም ለመሸፈን የሚከፈለው ዋጋ በኃጢአቱ ሳቢያ የጠፋውን ነገር ሙሉ በሙሉ የሚያካክስ ወይም የሚሸፍን መሆን አለበት። በዚህም ምክንያት አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ “ሕይወት ስለ ሕይወት፣ ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ እንዲሁም እግር ስለ እግር ይሁን” ሲል ይገልጻል።—ዘዳግም 19:21

9. የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የእንስሳት መሥዋዕቶች ያቀርቡ የነበረው ለምንድን ነው? ይሖዋስ ለእነዚህ መሥዋዕቶች ምን አመለካከት ነበረው?

9 ከአቤል አንስቶ በምድር ላይ የኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ የእንስሳት መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። ይህን ማድረጋቸው ኃጢአት እንዳለባቸውና መቤዠት እንደሚያስፈልጋቸው እንደተገነዘቡ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ አምላክ ‘በዘሩ’ አማካኝነት ነፃ ለማውጣት በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያመለክት ነው። (ዘፍጥረት 3:15፤ 4:1-4፤ ዘሌዋውያን 17:11፤ ዕብራውያን 11:4) ይሖዋ እንዲህ ያሉትን መሥዋዕቶች የተቀበለ ሲሆን እነዚህን ሰዎች አገልጋዮቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል። ይሁንና የአምላክ አገልጋዮች ያቀርቧቸው የነበሩት የእንስሳት መሥዋዕቶች ውስጣዊ ስሜታቸውን ለመግለጽ ያህል ብቻ የሚያገለግሉ ነበሩ። እንስሳት ከሰዎች ያነሱ በመሆናቸው የሰውን ኃጢአት ሊሸፍኑ አይችሉም። (መዝሙር 8:4-8) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልም” ይላል። (ዕብራውያን 10:1-4) እንዲህ ያሉት መሥዋዕቶች ለእውነተኛው ቤዛዊ መሥዋዕት እንደ ምሳሌ ሆነው የሚያገለግሉ ነበሩ።

“ተመጣጣኝ ቤዛ”

10. (ሀ) ቤዛው ከማን ጋር የሚመጣጠን መሆን አለበት? ለምንስ? (ለ) አንድ ሰው ብቻ መሥዋዕት መሆኑ በቂ የሚሆነው ለምንድን ነው?

10 ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ” ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:22) በመሆኑም የቤዛው ክፍያ፣ ፍጹም ሰው ከነበረው ከአዳም ጋር የሚመጣጠን ሕይወት ነው። (ሮም 5:14) ታዲያ ይህን የፍትሕ መሥፈርት ሊያሟላ የሚችለው ማን ነው? አዳም ባጠፋው ፍጹም ሕይወት ምትክ “ለሁሉ ተመጣጣኝ ቤዛ” ሊሆን የሚችለው በአዳም ላይ ከተበየነው የሞት ፍርድ ነፃ የሆነ ፍጹም ሰው ብቻ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:6) ለእያንዳንዱ የአዳም ዘር ተመጣጣኝ የሆነ ቤዛ ለመክፈል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መሥዋዕት መሆን አያስፈልጋቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ “በአንድ ሰው [በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ” ሲል ገልጿል። (ሮም 5:12) “ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል ስለሆነ” አምላክ “በአንድ ሰው በኩል” የሰውን ዘር ለመቤዠት ዝግጅት አድርጓል። (1 ቆሮንቶስ 15:21) እንዴት?

“ለሁሉ ተመጣጣኝ ቤዛ”

11. (ሀ) ቤዛውን የሚከፍለው ሰው ‘ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን የሚቀምሰው’ እንዴት ነው? (ለ) አዳምና ሔዋን ከቤዛው ተጠቃሚ ሊሆኑ የማይችሉት ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

11 ይሖዋ አንድ ፍጹም ሰው በፈቃደኝነት ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ዝግጅት አደረገ። ሮም 6:23 እንደሚገልጸው “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው።” ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበው ሰው “ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን [ይቀምሳል]።” በሌላ አነጋገር ለአዳም ኃጢአት ደሞዝ ይከፍላል። (ዕብራውያን 2:9፤ 2 ቆሮንቶስ 5:21፤ 1 ጴጥሮስ 2:24) ይህ ከሕግ አንጻር ትልቅ ትርጉም አለው። ቤዛው ታዛዥ በሆኑ የአዳም ዘሮች ላይ የተበየነውን የሞት ፍርድ በመሻር የኃጢአትን መዘዝ ከሥሩ ነቅሎ ያስወግዳል። aሮም 5:16

12. አንድ ዕዳ መከፈሉ ለብዙ ሰዎች ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም በምሳሌ አስረዳ።

12 ይህን ሁኔታ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በምትኖርበት ከተማ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ነዋሪዎች በአንድ ትልቅ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ናቸው እንበል። አንተም ሆንክ ጎረቤቶችህ ይህ ፋብሪካ በሚከፍላችሁ ደሞዝ ጥሩ ኑሮ ትኖራላችሁ። የሚያሳዝነው ግን ይህ ፋብሪካ ተዘጋ። ለምን? የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ በሙስና በመዘፈቁና ድርጅቱን ለኪሳራ በመዳረጉ ነው። አንተም ሆንክ አብረውህ የሚሠሩት ሰዎች በድንገት ከሥራ በመውጣታችሁ የተለያዩ ወጪዎቻችሁን የምትሸፍኑበት ገንዘብ በማጣት ችግር ላይ ወደቃችሁ። አንድ ሰው በፈጸመው ሙስና ሳቢያ የትዳር ጓደኛችሁ፣ ልጆቻችሁና ለፋብሪካው በዱቤ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ተቋማት ሳይቀሩ ለችግር ተዳርገዋል። ይህ ሁኔታ መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ ይኖር ይሆን? አዎን! አንድ ባለጸጋ ሰው የፋብሪካውን ጥቅም በመገንዘብና ችግር ላይ ለወደቁት ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው በማዘን ፋብሪካውን ከደረሰበት ኪሳራ ለመታደግ እርምጃ ይወስዳል። የፋብሪካውን ዕዳ በሙሉ በመክፈል እንደገና ተከፍቶ ሥራ እንዲጀምር ያደርጋል። ይህ ዕዳ መከፈሉ በዚያ ተቀጥረው ይሠሩ ለነበሩ በርካታ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለፋብሪካው አበዳሪዎች ትልቅ እፎይታ ያስገኛል። በተመሳሳይም አዳም ያመጣው ዕዳ መከፈሉ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ትልቅ በረከት ያስገኛል።

ቤዛውን ሊያቀርብ የሚችለው ማን ነው?

13, 14. (ሀ) ይሖዋ ለሰው ዘር ቤዛ ያቀረበው እንዴት ነው? (ለ) ቤዛው የተከፈለው ለማን ነው? ቤዛው በዚህ መንገድ መከፈሉስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ‘የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደውን በግ’ ሊያቀርብ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ዮሐንስ 1:29) ይሁን እንጂ አምላክ የሰውን ዘር ለማዳን እንዲሁ አንድ መልአክ አልላከም። ከዚህ ይልቅ ሰይጣን በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ላቀረበው ክስ የማያዳግም ምላሽ መስጠት የሚችለውን መልአክ መርጦ ልኳል። አዎን፣ ይሖዋ ‘ልዩ ደስታ እንዲሰማው የሚያደርገውን’ አንድያ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ተወዳዳሪ የሌለው መሥዋዕት ከፍሏል። (ምሳሌ 8:30) የአምላክ ልጅ በሰማይ የነበረውን ሕይወት በፈቃደኝነት በመተው ‘ራሱን ባዶ አደረገ።’ (ፊልጵስዩስ 2:7) ይሖዋ የበኩር ልጁን ሕይወት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ማርያም ወደምትባል አይሁዳዊት ድንግል ማህፀን አዛወረው። (ሉቃስ 1:27, 35) ይህ የአምላክ አንድያ ልጅ ሰው ከሆነ በኋላ ኢየሱስ ተብሎ ቢጠራም ከአዳም ጋር ፍጹም ተመጣጣኝ ስለሆነ ከሕግ አንጻር ሁለተኛው አዳም ተብሎ ሊጠራ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 15:45, 47) በመሆኑም ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ኃጢአተኛ ለሆነው የሰው ዘር ቤዛ ሊሆን ይችላል።

14 ይህ ቤዛ የተከፈለው ለማን ነው? መዝሙር 49:7 ይህ ቤዛ የተከፈለው “ለአምላክ” እንደሆነ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ቤዛውን ያዘጋጀው ራሱ ይሖዋ አይደለም? አዎን፣ እሱ ነው፤ እንዲህ ሲባል ግን ቤዛው ገንዘብን ከአንድ ኪስ አውጥቶ ወደ ሌላ ኪስ የመክተት ያህል ትርጉም የለሽ ነገር እንደሆነ አድርገን ማሰብ የለብንም። ቤዛው የተከፈለው ፍትሕ የሚጠይቀውን መሥፈርት ለማሟላት እንጂ እንዲሁ አንድን ነገር በሌላ ለመተካት ብቻ ተብሎ አይደለም። ይሖዋ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ቢጠይቅበትም እንኳ ቤዛውን በመክፈል ፍጹም ለሆነው ፍትሑ ያለውን የጸና አቋም አሳይቷል።—ዘፍጥረት 22:7, 8, 11-13፤ ዕብራውያን 11:17፤ ያዕቆብ 1:17

15. ኢየሱስ መከራ መቀበሉና መሞቱ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

15 በ33 ዓ.ም. ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛውን ለመክፈል ሲል ራሱን በፈቃደኝነት ለመከራ አሳልፎ ሰጠ። በሐሰት ክሶች ተወንጅሎ ተያዘ፣ ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ተፈረደበት፣ በመጨረሻም በእንጨት ላይ በሚስማር ተቸነከረ፤ ኢየሱስ እነዚህ ነገሮች እንዲደርሱበት ፈቅዷል። ኢየሱስ ይህን ያህል መከራ መቀበሉ አስፈላጊ ነበር? አዎን፣ ምክንያቱም የአምላክ አገልጋዮችን የታማኝነት አቋም በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ መልስ ማግኘት ነበረበት። አምላክ፣ ኢየሱስ ሕፃን እያለ ሄሮድስ እሱን ለመግደል ያደረገውን ሙከራ አክሽፏል። (ማቴዎስ 2:13-18) ካደገ በኋላ ግን ኢየሱስ፣ ሰይጣን ለሚሰነዝርበት ጥቃት ምላሽ የሰጠው የተነሱትን አከራካሪ ጉዳዮች በሚገባ ተገንዝቦ ነው። b ይህ ነው የማይባል ግፍ ቢደርስበትም እንኳ “ታማኝ፣ ቅን የሆነ፣ ያልረከሰ፣ ከኃጢአተኞች የተለየ” ሆኖ እስከ መጨረሻው ድረስ በመጽናት ይሖዋ መከራ እየደረሰባቸውም ቢሆን በታማኝነት ጸንተው የሚቆሙ አገልጋዮች እንዳሉት በማያሻማ ሁኔታ አስመሥክሯል። (ዕብራውያን 7:26) ኢየሱስ ሊሞት በተቃረበበት ወቅት “ተፈጸመ!” ብሎ በድል አድራጊነት ስሜት መናገሩ ምንም አያስገርምም።—ዮሐንስ 19:30

የመቤዠት ተልእኮውን ከፍጻሜ ማድረስ

16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ሰዎችን እንዲቤዥ የተሰጠውን ተልእኮ ማከናወኑን የቀጠለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ “ስለ እኛ በአምላክ ፊት ይታይ ዘንድ” መቅረቡ አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

16 ይሁንና ኢየሱስ ሰዎችን እንዲቤዥ የተሰጠውን ተልእኮ ገና አላጠናቀቀም ነበር። በሞተ በሦስተኛው ቀን ይሖዋ ከሞት አስነሳው። (የሐዋርያት ሥራ 3:15፤ 10:40) ይሖዋ ይህን በማድረግ ልጁ ላከናወነው የታማኝነት አገልግሎት ወሮታ ከመክፈሉም በላይ የአምላክ ሊቀ ካህናት ሆኖ የተሰጠውን የመቤዠት ተልእኮ ከፍጻሜ ማድረስ የሚችልበትን አጋጣሚም ከፍቶለታል። (ሮም 1:4፤ 1 ቆሮንቶስ 15:3-8) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ክርስቶስ . . . ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ . . . ወደ ቅዱሱ ስፍራ የገባው የፍየሎችንና የወይፈኖችን ደም ይዞ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የገዛ ራሱን ደም ይዞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ፤ ደግሞም ለእኛ ዘላለማዊ መዳን አስገኘልን። ክርስቶስ የገባው በሰው እጅ ወደተሠራውና የእውነተኛው ቅዱስ ስፍራ አምሳያ ወደሆነው ስፍራ አይደለምና፤ ከዚህ ይልቅ አሁን ስለ እኛ በአምላክ ፊት ይታይ ዘንድ ወደ ሰማይ ገብቷል።”—ዕብራውያን 9:11, 12, 24

17 ክርስቶስ ቃል በቃል ደሙን ወደ ሰማይ ይዞ ሊሄድ አይችልም። (1 ቆሮንቶስ 15:50) ከዚህ ይልቅ ወደ ሰማይ ይዞ የሄደው ደሙ የሚወክለውን ነገር ማለትም መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበውን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ዋጋ ነው። ከዚያም የሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ ኃጢአተኛ ለሆኑት የሰው ልጆች ቤዛ አድርጎ በአምላክ ፊት አቀረበ። ይሖዋ ይህን መሥዋዕት ተቀብሎታል? አዎን፣ ተቀብሎታል። በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም በነበሩት 120 ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ መውረዱ ለዚህ ማስረጃ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) በዚያን ጊዜ የተከናወነው ነገር እጅግ የሚያስደስት ቢሆንም ቤዛው የሚያስገኘው አስደናቂ ጥቅም በዚህ ብቻ የሚወሰን አልነበረም።

ቤዛው የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

18, 19. (ሀ) በክርስቶስ ደም አማካኝነት ከአምላክ ጋር የመታረቅ አጋጣሚ የተከፈተላቸው ሁለት ቡድኖች የትኞቹ ናቸው? (ለ) “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አሁንም ሆነ ወደፊት በቤዛው አማካኝነት የሚያገኟቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

18 ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አምላክ፣ ኢየሱስ በእንጨት ላይ ባፈሰሰው ደም አማካኝነት ሰላም በመፍጠር ሌሎቹን ነገሮች ሁሉ በክርስቶስ በኩል ከራሱ ጋር ለማስታረቅ እንደወደደ ገልጿል። በተጨማሪም ጳውሎስ ይህ እርቅ ሁለት የተለያዩ ቡድኖችን ማለትም “በሰማያት ያሉትን ነገሮች” እና ‘በምድር ያሉትን ነገሮች’ እንደሚያጠቃልል አብራርቷል። (ቆላስይስ 1:19, 20፤ ኤፌሶን 1:10) የመጀመሪያው ቡድን በሰማይ ካህናት ሆኖ የማገልገልና ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ነገሥታት ሆነው በምድር ላይ የመግዛት ተስፋ ያላቸውን 144,000 ክርስቲያኖች ያቀፈ ነው። (ራእይ 5:9, 10፤ 7:4፤ 14:1-3) እነዚህ ነገሥታትና ካህናት በሺው ዓመት የግዛት ዘመን፣ ቤዛው የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ቀስ በቀስ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች እንዲዳረሱ ያደርጋሉ።—1 ቆሮንቶስ 15:24-26፤ ራእይ 20:6፤ 21:3, 4

19 ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ የተባሉት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም የሆነ ሕይወት የሚያገኙት ሰዎች ናቸው። ራእይ 7:9-17 እነዚህ ሰዎች በቅርቡ ከሚመጣው ‘ታላቅ መከራ’ በሕይወት የሚተርፉ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” እንደሆኑ ይገልጻል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ከቤዛው ለመጠቀም የሺው ዓመት ግዛት እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ መጠበቅ አለባቸው ማለት አይደለም። ገና ከአሁኑ “[ልብሳቸውን] በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።” በቤዛው ስለሚያምኑ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ከዚህ ፍቅራዊ ዝግጅት መንፈሳዊ ጥቅሞችን በማግኘት ላይ ናቸው። የአምላክ ወዳጆች በመሆን እንደ ጻድቃን ተቆጥረዋል። (ያዕቆብ 2:23) ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ስለከፈለ “ያለምንም ፍርሃት ወደ ጸጋው ዙፋን [መቅረብ]” ይችላሉ። (ዕብራውያን 4:14-16) ስህተት በሚሠሩበት ጊዜም አምላክ በዚህ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር ይላቸዋል። (ኤፌሶን 1:7) ምንም እንኳ ፍጹም ባይሆኑም ንጹሕ ሕሊና ይኖራቸዋል። (ዕብራውያን 9:9፤ 10:22፤ 1 ጴጥሮስ 3:21) በመሆኑም በዛሬው ጊዜም እንኳ ሰዎች ከአምላክ ጋር እርቅ በመፍጠር ላይ ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 5:19, 20) በሺው ዓመት የግዛት ዘመን ደግሞ ቀስ በቀስ “ከመበስበስ ባርነት ነፃ [ወጥተው] የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” ያገኛሉ።—ሮም 8:21

20. በቤዛው ዝግጅት ላይ ማሰላሰልህ ምን እንድታደርግ ይገፋፋሃል?

20 የቤዛውን ዝግጅት ስላደረገልን “በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል [የሚታደገን] አምላክ የተመሰገነ ይሁን!” (ሮም 7:25) የቤዛው ዝግጅት እንዲሁ ሲታይ ቀላል ሊመስል ቢችልም ከምናስበው በላይ አስገራሚ ነው። (ሮም 11:33) በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልተን በዚህ የቤዛ ዝግጅት ላይ ካሰላሰልን ልባችን በጥልቅ ሊነካና የፍትሕ አምላክ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ልንገፋፋ እንችላለን። በተጨማሪም “ጽድቅንና ፍትሕን ይወዳል” ብለን እንደ መዝሙራዊው ይሖዋን ለማወደስ እንገፋፋለን።—መዝሙር 33:5

a አዳምና ሔዋን ከቤዛው ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም። የሙሴ ሕግ ሆን ብሎ ነፍስ የሚያጠፋን ሰው በተመለከተ የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት አስቀምጧል፦ “ሞት ለሚገባው ነፍሰ ገዳይ ሕይወት ቤዛ አትቀበሉ።” (ዘኁልቁ 35:31) አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ያመፁት ሆን ብለው ስለሆነ ሞት ይገባቸዋል። በዚህም ምክንያት ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን አጥተዋል።

b ኢየሱስ ለአዳም ኃጢአት ተመጣጣኝ ቤዛ ሊሆን የሚችለው ሕፃን ሆኖ ሳይሆን ሙሉ ሰው ከሆነ በኋላ ሲሞት ነው። አዳም ኃጢአት የሠራው፣ ድርጊቱ የሚያስከትልበትን መዘዝ እያወቀ ሆን ብሎ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ስለዚህ ኢየሱስም “የኋለኛው አዳም” ለመሆንና የአዳምን ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን በራሱ ምርጫና ውሳኔ ከይሖዋ ጎን መቆሙን ማስመሥከር የሚችልበት ዕድሜ ላይ መሆን ነበረበት። (1 ቆሮንቶስ 15:45, 47) በመሆኑም መሥዋዕታዊ ሞቱን ጨምሮ ኢየሱስ በታማኝነት ያሳለፈው ሕይወት ሰዎችን “ከበደል ነፃ የሚያደርግ አንድ ድርጊት” ሆኖ አገልግሏል።—ሮም 5:18, 19 የግርጌ ማስታወሻ