በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 22

‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ’ በአኗኗርህ እያንጸባረቅህ ነው?

‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ’ በአኗኗርህ እያንጸባረቅህ ነው?

1-3. (ሀ) ሰለሞን በሁለት ሴቶች መካከል የተነሳውን ጭቅጭቅ በዳኘበት ጊዜ አስደናቂ የሆነ ጥበብ እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ምን ቃል ገብቷል? ምን ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?

 ፍርድ ለመስጠት የሚያስቸግር ጉዳይ ነው፤ ሁለት ሴቶች በአንድ ሕፃን እየተጨቃጨቁ ነው። እነዚህ ሴቶች በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን ሁለቱም በጥቂት ቀናት ልዩነት ልጅ ወለዱ። ከተወለዱት ሕፃናት መካከል አንደኛው ሞተ፤ በመሆኑም ሁለቱ ሴቶች ‘በሕይወት ያለው ሕፃን የእኔ ነው’፣ ‘የእኔ ነው’ በሚል ጭቅጭቅ ፈጠሩ። a ሁኔታው ሲፈጠር ያየ አንድም የዓይን ምሥክር አልነበረም። ጉዳዩ ችሎት ፊት ቀርቦ የታየ ሊሆን ቢችልም እንኳ እልባት ሊያገኝ ባለመቻሉ የእስራኤል ንጉሥ ሰለሞን እንዲዳኘው ተደረገ። ንጉሡ ሐቁ እንዲወጣ ማድረግ ይችል ይሆን?

2 ሰለሞን የሴቶቹን ጭቅጭቅ ለተወሰነ ጊዜ ካዳመጠ በኋላ ሰይፍ እንዲያመጡለት አዘዘ። ከዚያም ሕፃኑ ለሁለት ተሰንጥቆ እንዲካፈሉት ትእዛዝ አስተላለፈ። እውነተኛዋ የሕፃኑ እናት ይህን ስትሰማ በጣም የምትወደው ልጇ ከሚቆረጥ ይልቅ ለሌላኛዋ ሴት እንዲሰጥ ንጉሡን ተማጸነች። ሌላኛዋ ሴት ግን ‘ሕፃኑ ለሁለት ተቆርጦ እንካፈል’ አለች። በዚህ ጊዜ ሰለሞን እውነቱ ተገለጠለት። አንዲት እናት የአብራኳ ክፋይ ለሆነው ልጇ ምን ያህል እንደምትራራ ስለሚያውቅ ይህን ዘዴ በመጠቀም ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ አደረገ። ሰለሞን ‘እናቱ እሷ ናት’ በማለት ልጁ እንዲሰጣት ሲወስን እናቲቱ ምን እንደተሰማት ልትገምት ትችላለህ።—1 ነገሥት 3:16-27

3 ይህ የሚያስደንቅ ጥበብ አይደለም? ሕዝቡ ሰለሞን ጉዳዩ እንዴት እልባት እንዲያገኝ እንዳደረገ ሲሰሙ “የአምላክን ጥበብ እንደታደለ ስለተመለከቱ” ለንጉሡ አክብሮታዊ ፍርሃት አደረባቸው። አዎን፣ ይህ የሰለሞን ጥበብ መለኮታዊ ስጦታ ነበር። ይሖዋ “ጥበበኛና አስተዋይ ልብ” ሰጥቶታል። (1 ነገሥት 3:12, 28) እኛስ የአምላክን ጥበብ ማግኘት እንችላለን? አዎን፣ ሰለሞን “ይሖዋ ራሱ ጥበብ ይሰጣል” ሲል በአምላክ መንፈስ ተነሳስቶ ጽፏል። (ምሳሌ 2:6) ይሖዋ ጥበብን ማለትም እውቀትንና ማስተዋልን በአግባቡ የመጠቀም ችሎታን ከልብ ለሚፈልጉት ሰዎች እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል። ታዲያ ከሰማይ የሆነውን ጥበብ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ጥበብ በአኗኗራችን ማንጸባረቅ የምንችለውስ እንዴት ነው?

“ጥበብን አግኝ”—እንዴት?

4-7. ጥበብ ለማግኘት ምን አራት ነገሮች ያስፈልጋሉ?

4 የአምላክን ጥበብ ለማግኘት የላቀ የማሰብ ችሎታ ወይም ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ሊኖረን ይገባል? በፍጹም። ዘራችን፣ ያለንበት የኑሮ ሁኔታ ወይም የትምህርት ደረጃችን ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ጥበቡን ሊሰጠን ፈቃደኛ ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:26-29) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበብን አግኝ” በማለት ስለሚመክረን ጥበብ ለማግኘት ከእኛም የሚጠበቅ ነገር አለ። (ምሳሌ 4:7) ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

5 በመጀመሪያ ደረጃ አምላክን መፍራት አለብን። ምሳሌ 9:10 “የጥበብ መጀመሪያ [“ጥበብን ለማግኘት የመጀመሪያው እርምጃ፣” ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል] ይሖዋን መፍራት ነው” በማለት ይናገራል። ይሖዋን መፍራት የእውነተኛ ጥበብ መሠረት ነው። ለምን? ጥበብ እውቀትን ውጤታማ በሆነ መንገድ የመጠቀም ችሎታን እንደሚያካትት አስታውስ። አምላክን መፍራት ሲባል በፍርሃት መራድ ማለት ሳይሆን በጥልቅ አክብሮት ተነሳስቶ ለእሱ መገዛት ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ፍርሃት ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ ለተግባር የሚያነሳሳ ነው። ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ ካለን እውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ እንድንኖር ይገፋፋናል። ይሖዋ ያወጣቸው መሥፈርቶች መመሪያውን ለሚከተሉ ሁሉ ምንጊዜም ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኙ በመሆናቸው እሱን መፍራታችን ከሁሉ የተሻለ የጥበብ መንገድ ነው።

6 በሁለተኛ ደረጃ ትሑት እና ልካችንን የምናውቅ መሆን አለብን። ትሑትና ልካችንን የምናውቅ ካልሆንን የአምላክን ጥበብ ማግኘት አንችልም። (ምሳሌ 11:2) ለምን? ትሑቶች እና ልካችንን የምናውቅ ከሆንን ሁሉን እንደምናውቅና እኛ ያልነው ሁልጊዜ ትክክል እንደሆነ አድርገን አናስብም፤ በተጨማሪም የይሖዋን አመለካከት ማወቅ እንደሚያስፈልገን እንገነዘባለን። ይሖዋ “ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤” ለትሑታን ግን ጥበብን ይሰጣል።—ያዕቆብ 4:6

7 በሦስተኛ ደረጃ በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክን ቃል ማጥናት አስፈላጊ ነው። የይሖዋ ጥበብ በቃሉ ውስጥ ተገልጿል። ይህን ጥበብ ለማግኘት ጥልቅ ምርምር ማድረግ ይኖርብናል። (ምሳሌ 2:1-5) በአራተኛ ደረጃ ደግሞ መጸለይ ያስፈልገናል። አምላክ ጥበብ እንዲሰጠን ከልብ ከለመንነው በልግስና ይሰጠናል። (ያዕቆብ 1:5) መንፈሱን እንዲሰጠን የምናቀርበውን ጸሎት ይሰማል። መንፈሱ ደግሞ ችግራችንን ለመወጣት፣ ራሳችንን ከአደጋ ለመጠበቅና ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችለንን በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ውድ ሀብት ፈልገን እንድናገኝ ይረዳናል።—ሉቃስ 11:13

የአምላክን ጥበብ ለማግኘት ጥልቅ ምርምር ማድረግ ይኖርብናል

8. አምላካዊ ጥበብ እንዳለን የሚታወቀው በምንድን ነው?

8 በምዕራፍ 17 ላይ እንደተመለከትነው የይሖዋ ጥበብ በተግባር የሚገለጽ ነው። ስለሆነም በእርግጥ የአምላክን ጥበብ ካገኘን ይህ በአኗኗራችን ይንጸባረቃል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ የመለኮታዊ ጥበብ ፍሬዎችን እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው።” (ያዕቆብ 3:17) እነዚህን የመለኮታዊ ጥበብ ገጽታዎች አንድ በአንድ ስንመረምር ‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ በአኗኗሬ እያንጸባረቅሁ ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን።

“ንጹሕ . . . ከዚያም ሰላማዊ”

9. ንጹሕ የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? ንጽሕና የጥበብ ገጽታ ከሆኑት ባሕርያት መጀመሪያ ተደርጎ መጠቀሱስ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

9 “በመጀመሪያ ንጹሕ ነው።” ንጹሕ የሚለው ቃል ውጫዊ ንጽሕናን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ንጽሕናንም ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብን ከልብ ጋር ያዛምደዋል፤ ይሁን እንጂ ከሰማይ የሆነው ጥበብ በክፉ ሐሳብ፣ ምኞትና ፍላጎት ወደተበከለ ልብ ሊገባ አይችልም። (ምሳሌ 2:10፤ ማቴዎስ 15:19, 20) ሆኖም አለፍጽምናችን በፈቀደልን መጠን ልባችን ንጹሕ ከሆነ ‘ከክፉ እንርቃለን፤ መልካሙንም እናደርጋለን።’ (መዝሙር 37:27፤ ምሳሌ 3:7) ንጽሕና የጥበብ ገጽታ ከሆኑት ባሕርያት መጀመሪያ ተደርጎ መጠቀሱ ተገቢ አይደለም? ደግሞስ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ንጹሕ ካልሆንን ከሰማይ የሆነውን ጥበብ ሌሎች ገጽታዎች እንዴት ማንጸባረቅ እንችላለን?

10, 11. (ሀ) ሰላማዊ መሆናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የእምነት ባልንጀራህን እንዳስቀየምክ ከተሰማህ ሰላም ፈጣሪ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

10 “ከዚያም ሰላማዊ።” ከሰማይ የሆነው ጥበብ የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆነውን ሰላምን አጥብቀን እንድንሻ ይገፋፋናል። (ገላትያ 5:22) የይሖዋን ሕዝብ አንድ ላይ የሚያስተሳስረውን “የሰላም ማሰሪያ” ከማደፍረስ እንቆጠባለን። (ኤፌሶን 4:3) ሰላም በሚደፈርስበት ጊዜ ደግሞ ዳግመኛ ሰላም እንዲሰፍን የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በሰላም መኖራችሁን ቀጥሉ፤ የፍቅርና የሰላም አምላክም ከእናንተ ጋር ይሆናል” በማለት ይገልጻል። (2 ቆሮንቶስ 13:11) ስለዚህ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እስከኖርን ድረስ የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል። ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት የምናሳየው ባሕርይ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በቀጥታ ይነካል። ታዲያ ሰላም ፈጣሪዎች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

11 የእምነት ባልንጀራህን እንዳስቀየምክ ከተሰማህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።” (ማቴዎስ 5:23, 24) ቀዳሚውን እርምጃ ወስደህ ወንድምህን በማነጋገር ይህን ምክር ልትሠራበት ትችላለህ። ይህን የምታደርግበት ዓላማ ምንድን ነው? ‘ከወንድምህ ጋር መታረቅ’ ነው። b ይህ እንዲሆን ደግሞ ቅር የሚያሰኘው ምንም ምክንያት እንደሌለው ከመግለጽ ይልቅ ስሜቱን እንደጎዳኸው አምነህ መቀበል ይኖርብሃል። ቀደም ሲል የነበራችሁን ሰላማዊ ግንኙነት የማደስ ግብ ይዘህ ካነጋገርከውና በውይይታችሁ ወቅትም ይህንን አመለካከት ካንጸባረቅህ በመካከላችሁ የነበረው አለመግባባት ተወግዶ ይቅር ልትባባሉ ትችላላችሁ። ቀዳሚውን እርምጃ በመውሰድ ከወንድምህ ጋር እርቅ ለመፍጠር መጣርህ በአምላክ ጥበብ እንደምትመራ ያሳያል።

“ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ”

12, 13. (ሀ) በያዕቆብ 3:17 ላይ “ምክንያታዊ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ፍቺ ምንድን ነው? (ለ) ምክንያታዊ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

12 “ምክንያታዊ።” ምክንያታዊ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ በያዕቆብ 3:17 ላይ “ምክንያታዊ” ተብሎ የተቀመጠውን የግሪክኛ ቃል መተርጎም አስቸጋሪ ነው። ቃሉ ‘እሺ ባይ መሆን’ የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ተርጓሚዎች ይህን ቃል “ገር፣” “ታጋሽ” እና “አሳቢ” ብለው ተርጉመውታል። ይህን ከሰማይ የሆነውን ጥበብ አንድ ገጽታ በአኗኗራችን ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

13 ፊልጵስዩስ 4:5 “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ይላል። ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ጥቅስ “ምክንያታዊ ናቸው የሚል ስም አትርፉ” ሲል ተርጉሞታል። (ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ፣ በጄ ቢ ፊሊፕስ) ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚገባው ነገር እኛ ለራሳችን ያለን አመለካከት ሳይሆን ሌሎች ለእኛ ያላቸው አመለካከት መሆኑን ልብ በል። ምክንያታዊ የሆነ ሰው ሕጉ ካልተከበረ ብሎ ድርቅ አይልም ወይም እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ አይሟገትም። ከዚህ ይልቅ የሌሎችን ሐሳብ ለመስማትና ተገቢ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ያሉትን ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆናል። በተጨማሪም ገርና የሚመች ባሕርይ ያለው ነው እንጂ አስቸጋሪ አይደለም። ይህ ባሕርይ ለሁሉም ክርስቲያኖች የሚያስፈልግ ቢሆንም በይበልጥ ግን ሽማግሌ ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች ይህን ባሕርይ ማንጸባረቅ ይጠበቅባቸዋል። ሽማግሌዎች ገር ከሆኑ ሌሎች በቀላሉ ሊቀርቧቸው ይችላሉ። (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8) ሁላችንም ‘አሳቢ፣ ምክንያታዊና ገር ነው የሚል ስም እያተረፍኩ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን።

14. “ለመታዘዝ ዝግጁ” መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 “ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ።” እንዲህ ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሌላ ቦታ ላይ አይገኝም። አንድ ምሁር እንደገለጹት ከሆነ ይህ ቃል “አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራበት ከወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ነው።” “በቀላሉ እሺ ብሎ የሚቀበል” እና “ታዛዥ” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ከሰማይ በሆነው ጥበብ የሚመራ ሰው ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን መመሪያ ያለምንም ማንገራገር ይታዘዛል። አንዴ አንድ ውሳኔ ላይ ከደረሰ ምንም ዓይነት ሐሳብ ቢቀርብለት የማይቀበል ሰው አይደለም። ከዚህ ይልቅ የተሳሳተ እርምጃ እንደወሰደ ወይም የተሳሳተ ውሳኔ እንደወሰነ የሚያሳይ አሳማኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ሲቀርብለት ወዲያውኑ አቋሙን ይለውጣል። አንተስ እንዲህ ዓይነት ስም አትርፈሃል?

“ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት”

15. ምሕረት ምንድን ነው? በያዕቆብ 3:17 ላይ “ምሕረት” እና “መልካም ፍሬዎች” አንድ ላይ መጠቀሳቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

15 “ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት።” c ከሰማይ የሆነው ጥበብ ‘ምሕረት የሞላበት’ እንደሆነ ስለተገለጸ ምሕረት የዚህ ጥበብ ወሳኝ ገጽታ ነው። “ምሕረት” እና “መልካም ፍሬዎች” አንድ ላይ እንደተጠቀሱ ልብ በል። ይህ መሆኑም የተገባ ነው፤ ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሕረት የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው እርምጃ በመውሰድ የሚገለጽ አሳቢነትን እንዲሁም ውጤቱ በደግነት ተግባሮች የሚታይን የርኅራኄ ስሜት ነው። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ምሕረት የሚለው ቃል “አንድ ሰው በደረሰበት መጥፎ ሁኔታ ማዘንንና ያንን ሰው ለመርዳት መሞከርን” እንደሚያመለክት ገልጿል። ስለሆነም የአምላክ ጥበብ ከአእምሮ ብቻ ሳይሆን ከልብ ጋርም የሚያያዝ ባሕርይ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጥበብ እንደ ርኅራኄ፣ አዘኔታና አሳቢነት ባሉት ስሜቶችም የሚመራ ነው። ታዲያ ምሕረት የሞላብን መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16, 17. (ሀ) ለአምላክ ካለን ፍቅር በተጨማሪ የስብከቱን ሥራ እንድናከናውን የሚያነሳሳን ምንድን ነው? ለምንስ? (ለ) ምሕረት የሞላብን መሆናችንን ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

16 ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች መናገር እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህን ሥራ እንድናከናውን የሚያነሳሳን ምንድን ነው? ዋነኛው ምክንያት ለአምላክ ያለን ፍቅር ነው። ሆኖም ምሕረትና ርኅራኄም እንዲህ እንድናደርግ ያነሳሳናል። (ማቴዎስ 22:37-39) በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው” ይገኛሉ። (ማቴዎስ 9:36) የሐሰት ሃይማኖት መሪዎች እነዚህን ሰዎች ችላ ያሏቸው ከመሆኑም በላይ በመንፈሳዊ እንዲታወሩ አድርገዋል። በዚህም ምክንያት ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ መመሪያም ሆነ በቅርቡ የአምላክ መንግሥት በዚህ ምድር ላይ የሚያመጣቸውን በረከቶች አያውቁም። እነዚህ ሰዎች በመንፈሳዊ የተራቡ እንደሆኑ ስናስብ ለእነሱ ያለን ርኅራኄ ስለ ይሖዋ ዓላማ እንዲያውቁ ለመርዳት የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ ያነሳሳናል።

ለሌሎች ምሕረት ወይም ርኅራኄ በማሳየት ‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ’ ማንጸባረቅ እንችላለን

17 ምሕረት የሞላብን መሆናችንን ማሳየት የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች ምንድን ናቸው? ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረውን ምሳሌ አስታውስ። ይህ ሳምራዊ፣ ተደብድቦና ተዘርፎ በመንገድ ዳር የወደቀ አንድ ሰው ሲያይ ስላዘነለት ‘ምሕረት በማሳየት ረድቶታል፤’ ቁስሎቹን ያሰረለት ሲሆን ተገቢውን እንክብካቤ አድርጎለታል። (ሉቃስ 10:29-37) ይህ ምሳሌ፣ ምሕረት ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች ተግባራዊ የሆነ እርዳታ ማድረግን የሚጨምር እንደሆነ የሚያሳይ አይደለም? መጽሐፍ ቅዱስ “ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም” እንድናደርግ ያበረታታናል። (ገላትያ 6:10) ይህን ልናደርግ የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ተመልከት። አንድ አረጋዊ ወንድም ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚያመላልሳቸው ሰው ይፈልጉ ይሆናል። በጉባኤህ ውስጥ ያለች አንዲት መበለት እህት ቤቷ ውስጥ አንዳንድ የጥገና ሥራዎች የሚያከናውንላት ሰው ትፈልግ ይሆናል። (ያዕቆብ 1:27) ተስፋ የቆረጠ አንድ ሰው “መልካም ቃል” በመናገር የሚያጽናናው ይፈልግ ይሆናል። (ምሳሌ 12:25) በእነዚህ መንገዶች ምሕረት ማሳየታችን ከሰማይ የሆነውን ጥበብ በአኗኗራችን እያንጸባረቅን እንዳለን ያረጋግጣል።

“አድልዎና ግብዝነት የሌለበት”

18. ከሰማይ በሆነው ጥበብ የምንመራ ከሆነ ምን ነገርን ከልባችን ነቅለን ለማስወገድ እንጥራለን? ለምንስ?

18 ‘አድልዎ የሌለበት።’ የአምላክ ጥበብ ያለው ሰው፣ የእሱ ዘር ወይም ብሔር ከሌሎች እንደሚበልጥ አያስብም። በዚህ ጥበብ የምንመራ ከሆነ ማንኛውንም ዓይነት የአድልዎ ስሜት ከልባችን ውስጥ ነቅለን ለማስወገድ እንጥራለን። (ያዕቆብ 2:9) የሰዎችን የትምህርት ደረጃ፣ የኑሮ ሁኔታ ወይም የጉባኤ ኃላፊነት በማየት አናዳላም፤ በተጨማሪም የእምነት ባልንጀሮቻችን በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚሰጣቸው ቦታ የቱንም ያህል ዝቅተኛ ቢሆን አንንቃቸውም። እነዚህን ሰዎች ይሖዋ እስከወደዳቸው ድረስ እኛም ልንወዳቸው ይገባል።

19, 20. (ሀ) “ግብዝ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በጥንት ዘመን ምን ለማመልከት ይሠራበት ነበር? (ለ) “ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ” ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ይህስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

19 “ግብዝነት የሌለበት።” “ግብዝ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አንድን ገጸ ባሕርይ ወክሎ የሚጫወትን ተዋናይ” ሊያመለክት ይችላል። በጥንት ዘመን የግሪክና የሮም ተዋናዮች በሚተውኑበት ወቅት ትላልቅ ጭምብሎችን ያጠልቁ ነበር። በመሆኑም “ግብዝ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አስመሳይ የሆነን ሰው ለማመልከት ይሠራበት ጀመር። “ግብዝነት የሌለበት” የሚለው የአምላክ ጥበብ ገጽታ ለሌሎች የምናደርገውን ነገር ብቻ ሳይሆን ለእነሱ ያለንን አመለካከትም ሊነካው ይገባል።

20 ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ለእውነት የምንታዘዝ’ ከሆነ “ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድ” እንደሚኖረን ገልጿል። (1 ጴጥሮስ 1:22) አዎን፣ ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ከአንገት በላይ መሆን የለበትም። ጭምብል በማጥለቅ ወይም በማስመሰል ሌሎችን ማታለል የለብንም። ፍቅራችን ከልብ የመነጨ መሆን አለበት። እንዲህ ከሆነ የእምነት ባልንጀሮቻችን እውነተኛ ማንነታችንን ስለሚያውቁ ያምኑናል። ክርስቲያኖች ግብዞች አለመሆናቸው በሐቀኝነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ከመሆኑም በላይ በጉባኤው ውስጥ የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን ያደርጋል።

“ጥበብን . . . ጠብቅ”

21, 22. (ሀ) ሰለሞን የነበረውን ጥበብ ጠብቆ ማቆየት ሳይችል የቀረው ለምንድን ነው? (ለ) ያለንን ጥበብ ጠብቀን ማቆየት የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ በማድረጋችን የምንጠቀመውስ እንዴት ነው?

21 የአምላክ ጥበብ ልንጠብቀው የሚገባ የይሖዋ ስጦታ ነው። ሰለሞን “ልጄ ሆይ፣ . . . ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን ጠብቅ” ሲል ተናግሯል። (ምሳሌ 3:21) የሚያሳዝነው ግን ሰለሞን ራሱ ይህን ምክር አልሠራበትም። ይሖዋን በታዘዘባቸው ዘመናት ሁሉ ጠቢብ ነበር። መጨረሻ ላይ ግን ያገባቸው የባዕድ አገር ሴቶች ልቡ ከይሖዋ ንጹሕ አምልኮ እንዲርቅ አደረጉት። (1 ነገሥት 11:1-8) እውቀት በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ምንም ፋይዳ እንደሌለው በሰለሞን ላይ የደረሰው ሁኔታ በግልጽ ያሳያል።

22 ያለንን ጥበብ ጠብቀን ማቆየት የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በማንበብ ብቻ ሳይሆን የተማርነውን ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት በማድረግ ጭምር ነው። (ማቴዎስ 24:45) መለኮታዊ ጥበብን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉ። በአሁኑ ጊዜ የተሻለ ሕይወት እንድንኖር ይረዳናል። ከዚህም በላይ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማለትም አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም የሚኖረውን ሕይወት እንድናገኝ ያስችለናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:19) ከሁሉ በላይ ደግሞ ከሰማይ የሆነውን ጥበብ ማዳበራችን የጥበብ ሁሉ ምንጭ ወደሆነው ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል።

a አንደኛ ነገሥት 3:16 ሁለቱ ሴቶች ዝሙት አዳሪዎች እንደሆኑ ይገልጻል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ያብራራል፦ “እነዚህ ሴቶች ዝሙት አዳሪዎች የተባሉት መተዳደሪያቸው ስለሆነ ሳይሆን ልጅ የወለዱት በዝሙት እንደሆነ ለመግለጽ ሊሆን ይችላል፤ ሴቶቹ አይሁዳውያን ምናልባትም የሌላ አገር ዝርያ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።”—በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

b “ታረቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ “ጠላትነትን አስወግዶ ወዳጅነት መመሥረት፣ እርቅ መፍጠር፣ ቀድሞ ወደነበረው ጥሩ ግንኙነት ወይም ስምምነት መመለስ” የሚል ትርጉም ያስተላልፋል። በመሆኑም ዓላማህ ከተቻለ፣ ቅር በተሰኘው ግለሰብ ልብ ውስጥ የተፈጠረውን መጥፎ ስሜት በማስወገድ ለውጥ ማምጣት ነው።—ሮም 12:18

c ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ርኅራኄና መልካም ተግባሮች የሞሉበት” ይላል።—ኤ ትራንስሌሽን ኢን ዘ ላንግዌጅ ኦቭ ዘ ፒፕል፣ በቻርልስ ቢ ዊልያምስ