በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 27

“ጥሩነቱ ምንኛ ታላቅ ነው!”

“ጥሩነቱ ምንኛ ታላቅ ነው!”

1, 2. የአምላክ ጥሩነት ምን ያህል ሰፊ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ባሕርይ ጎላ አድርጎ የሚገልጸውስ እንዴት ነው?

 በመጥለቅ ላይ ያለችው ፀሐይ የፈጠረችው ውብ እይታ አካባቢውን ግርማ ሞገስ አላብሶታል፤ በጣም የሚቀራረቡ ጥቂት ጓደኛሞች ይህን የተፈጥሮ ውበት እያደነቁና እርስ በርስ እየተጨዋወቱ ደጅ ላይ ቁጭ ብለው እየተመገቡ ነው። በሌላ ቦታ የሚገኝ አንድ ገበሬ ጥቁር ደመና ያዘለው ሰማይ ማንጠባጠብ በመጀመሩ እርሻው ዝናብ ሊያገኝ እንደሆነ በማሰብ እጅግ ተደስቷል። አንድ ባልና ሚስት ደግሞ ሕፃን ልጃቸው እየተውተረተረ ለመራመድ ሲሞክር በማየታቸው በጣም ተደስተዋል።

2 እነዚህ ሰዎች አወቁትም አላወቁት ይህን ደስታ ሊያጣጥሙ የቻሉት በይሖዋ አምላክ ጥሩነት ነው። የሃይማኖት ሰዎች ብዙ ጊዜ “እግዚአብሔር መልካም ነው” ብለው ሲናገሩ እንሰማለን። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የአምላክ ባሕርይ የሚገልጽበት መንገድ ግን የበለጠ ኃይል አለው፤ “ጥሩነቱ ምንኛ ታላቅ ነው!” ይላል። (ዘካርያስ 9:17) ሆኖም በዛሬው ጊዜ ይህ አባባል ምን ትርጉም እንዳለው የሚያስተውሉ ጥቂቶች ብቻ ናቸው ማለት ይቻላል። ለመሆኑ የይሖዋ አምላክ ጥሩነት ምን ነገሮችን ይጨምራል? ይህ የአምላክ ባሕርይ እያንዳንዳችንን የሚነካንስ እንዴት ነው?

የአምላክ ፍቅር አቢይ ገጽታ

3, 4. ጥሩነት ምንድን ነው? ጥሩነት የይሖዋ ፍቅር መግለጫ ነው ቢባል ይበልጥ ተስማሚ የሆነውስ ለምንድን ነው?

3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጸው ጥሩነት በዋነኝነት የሚያመለክተው ቀናነትን እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባርን ነው። በመሆኑም ጥሩነት የማይነካው የይሖዋ ማንነት ገጽታ የለም ማለት ይችላል። ኃይሉን፣ ፍትሑንና ጥበቡን ጨምሮ የይሖዋ ባሕርያት በሙሉ ጥሩነቱን የሚያሳዩ ናቸው። ከሁሉ ይበልጥ ግን ጥሩነት የይሖዋ ፍቅር መግለጫ ነው ቢባል ይበልጥ ተስማሚ ነው። ለምን?

4 ጥሩነት በተግባር የሚገለጽ ባሕርይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ከጽድቅ ይልቅ ጥሩነት በሰዎች ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ ባሕርይ እንደሆነ ገልጿል። (ሮም 5:7) ጻድቅ ሰው ሕጉ የሚጠይቅበትን ምንም ሳያጓድል ሊያደርግ ይችላል፤ ጥሩ ሰው ግን ከዚያ አልፎ ይሄዳል። በራሱ ተነሳስቶ ሌሎችን የሚጠቅም ነገር ለማድረግ ይጥራል። ቀጥሎ እንደምንመለከተው ከዚህ አንጻር ይሖዋ በእርግጥም ጥሩ ነው። ይህ ጥሩነቱ ወደር ከማይገኝለት ፍቅሩ የሚመነጭ እንደሆነ ግልጽ ነው።

5-7. ኢየሱስ “ጥሩ መምህር” ተብሎ መጠራት ያልፈለገው ለምንድን ነው? እግረ መንገዱን ምን መሠረታዊ እውነት ማስገንዘብ ፈልጎ ነበር?

5 ይሖዋ በጥሩነቱ ተወዳዳሪ የለውም። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ አንድ ሰው “ጥሩ መምህር ሆይ” ብሎ በመጥራት አንድ ጥያቄ አቀረበለት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ለምን ጥሩ ብለህ ትጠራኛለህ? ከአንዱ ከአምላክ በቀር ጥሩ የለም” በማለት መለሰለት። (ማርቆስ 10:17, 18) ይህ የኢየሱስ መልስ ግር ሊልህ ይችል ይሆናል። ኢየሱስ ሰውየውን ያረመው ለምንድን ነው? ደግሞስ ኢየሱስ “ጥሩ መምህር” አይደለም እንዴ?

6 ይህ ሰው “ጥሩ መምህር” የሚለውን መግለጫ የተጠቀመው እንዲሁ ኢየሱስን ለመካብ ሳይሆን አይቀርም። በመሆኑም ኢየሱስ ራሱን ዝቅ በማድረግ ይህን ክብር ማግኘት ያለበት በጥሩነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሰማያዊ አባቱ እንደሆነ አመልክቷል። (ምሳሌ 11:2) ሆኖም ኢየሱስ እግረ መንገዱንም አንድ መሠረታዊ እውነት ማስገንዘብ ፈልጎ ነበር። የመጨረሻው የጥሩነት መሥፈርት ይሖዋ ራሱ ነው። የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ እንደመሆኑ መጠን ጥሩና መጥፎ የሆነውን የመወሰን መብት ያለው እሱ ብቻ ነው። አዳምና ሔዋን መልካምና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ በመብላት በአምላክ ትእዛዝ ላይ ባመፁበት ወቅት ይህን መብት ለራሳቸው መውሰድ ፈልገው ነበር። ኢየሱስ ግን ይህን መሥፈርት የማውጣት መብት የአባቱ መሆኑን በትሕትና አምኖ ተቀብሏል።

7 ደግሞም ኢየሱስ የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ ይሖዋ መሆኑን ያውቅ ነበር። “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” የሚገኘው ከእሱ ነው። (ያዕቆብ 1:17) ይሖዋ በልግስና በመስጠት ጥሩ አምላክ መሆኑን ያሳየባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ማለቂያ የሌለውን የይሖዋ ጥሩነት የሚያሳይ ማስረጃ

8. ይሖዋ ለሰው ዘር በሙሉ ጥሩነቱን ያሳየው እንዴት ነው?

8 የይሖዋን ጥሩነት ያልቀመሰ አንድም ፍጡር የለም። መዝሙር 145:9 “ይሖዋ ለሁሉም ጥሩ ነው” ይላል። ሁሉን አቀፍ የሆነውን የይሖዋን ጥሩነት የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው? መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] ከሰማይ ዝናብ በማዝነብና ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት እንዲሁም የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና ልባችሁን በደስታ በመሙላት መልካም ነገር አድርጓል” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 14:17) ጥሩ ምግብ በልተህ የተደሰትክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? ይሖዋ በጥሩነቱ ተገፋፍቶ በምድር ላይ የማያቋርጥ የውኃ ዑደት እንዲኖርና የተትረፈረፈ እህል የሚመረትባቸው “ፍሬያማ ወቅቶች” እንዲፈራረቁ ባያደርግ ኖሮ እንዲህ ያለ ምግብ ማግኘት አትችልም ነበር። ይሖዋ ይህን ጥሩነት ያሳየው ለሚወዱት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነው። ኢየሱስ “እሱ በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣልና፤ በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ ያዘንባል” ሲል ተናግሯል።—ማቴዎስ 5:45

9. ፖም የይሖዋን ጥሩነት የሚያሳየው እንዴት ነው?

9 ብዙዎች ፀሐዩንም ሆነ ዝናቡን እንደ ልብ ስለሚያገኙ፣ ወቅቶችም ጊዜያቸውን ጠብቀው ስለሚፈራረቁ ይሖዋ ለሰው ልጆች ያደረገውን የተትረፈረፈ ልግስና አቅልለው ሊመለከቱት ይችላሉ። እስቲ ፖምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በወይና ደጋ አካባቢዎች በብዛት የሚገኝ ፍሬ ነው። ፖም ሲያዩት የሚማርክ፣ ሲገምጡት ጣፋጭና ውኃው የሚያረካ፣ ደግሞም ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች የሞሉበት ፍሬ ነው። ለመሆኑ በዓለም ዙሪያ 7,500 ገደማ የሚሆኑ የተለያዩ የፖም ዓይነቶች እንዳሉ ታውቃለህ? ቀይ፣ ወርቃማ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴና ሌሎች የተለያዩ ቀለማት አሉት፤ መጠኑም ቢሆን ከወይን ፍሬ ትንሽ ከፍ ከምትለዋ አነስተኛ ፖም አንስቶ ትልቅ ብርቱካን እስከሚያህለው ድረስ የተለያየ ነው። አንዲት የፖም ዘር እንዲሁ ስትታይ ብዙ የሚያስደንቅ ነገር የላትም። ሆኖም በዓለም ላይ በጣም ተወዳጅ ከሆኑት የዛፍ ዓይነቶች አንዱ የሚበቅለው ከዚህች አነስተኛ ዘር ነው። (መኃልየ መኃልይ 2:3) የፖም ዛፍ በጸደይ ወቅት በሚያማምሩ አበቦች የሚያሸበርቅ ሲሆን በመከር ወቅት ደግሞ ብዙ ፍሬ ያፈራል። እያንዳንዱ ዛፍ ለ75 ዓመታት ያህል በየዓመቱ 400 ኪሎ ገደማ ፍሬ ይሰጣል!

ይሖዋ ‘ከሰማይ ዝናብ ያዘንባል፤ ፍሬያማ ወቅቶችንም ይሰጠናል’

ከዚህች አነስተኛ ዘር የሚበቅለው ዛፍ ሰዎችን ለብዙ ዓመታት የሚመግብና የሚያረካ ፍሬ ይሰጣል

10, 11. የስሜት ሕዋሶቻችን የአምላክን ጥሩነት የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?

10 ይሖዋ ማለቂያ በሌለው ጥሩነቱ ተገፋፍቶ “ድንቅ” አካል ሰጥቶናል፤ አካላችን በአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ለመደሰት የሚያስችሉ የስሜት ሕዋሳት አሉት። (መዝሙር 139:14) በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የተገለጹትን ትዕይንቶች መለስ ብለህ ለማሰብ ሞክር። በደስታ የሚፍለቀለቀው ሕፃን፤ ማሳው ላይ ሿ እያለ የሚወርደው ዝናብ፤ ፀሐይ ስትጠልቅ በቀይ፣ በወርቃማና በሐምራዊ ቀለማት የሚያጌጠው ሰማይ። እነዚህን ነገሮች ማየት ልብን በሐሴት የሚሞላ አይደለም? የሰው ዓይን በመቶ ሺዎች ምናልባትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቀለማትን መለየት ይችላል! የመስማት የስሜት ሕዋሳችን የተለያዩ የድምፅ ቃናዎችን፣ በዛፎች መካከል የሚሰማውን የነፋስ ሽውታና የሕፃን ልጅን ሳቅ መለየት ይችላል። እንዲህ ባሉ እይታዎችና ድምፆች መደሰት የቻልነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዓይንን፣ ሁለቱንም የሠራው ይሖዋ ነው” ይላል። (ምሳሌ 20:12) ይሁንና እነዚህ ከስሜት ሕዋሶቻችን መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው።

11 የማሽተት የስሜት ሕዋሳችን ሌላው የይሖዋ ጥሩነት ማስረጃ ነው። የሰው አፍንጫ እጅግ በጣም ብዙ ሽታዎችን መለየት ይችላል፤ አንዳንዶች በሺዎች አልፎ ተርፎም በትሪሊዮኖች የሚቆጠሩ ሽታዎችን መለየት እንደሚችል ይገምታሉ። ለአብነት ያህል እስቲ እነዚህን አስብ፦ ሽታው ምራቅ የሚያስውጥ ምግብ፣ የአበቦች መዓዛ፣ የእርጥብ አፈር ሽታ፣ በክረምት ከብበን ከምንሞቀው እሳት የሚወጣው ጭስ። በተጨማሪም የመዳሰስ የስሜት ሕዋስ ባይኖርህ ኖሮ አንድ ሰው ሲስምህም ሆነ አቅፎ ሲያበረታታህ ልዩ የሆነ ስሜት ሊሰማህ አይችልም ነበር፤ አንድን ፍሬ በእጅህ በመዳበስ ልስላሴውን ማወቅ የምትችለውም ይህ የስሜት ሕዋስ ስላለህ ነው። ፍሬውን ገምጠህ ማጣጣም የምትችለው ደግሞ የመቅመስ የስሜት ሕዋስ ስላለህ ነው። በምላሳችን ላይ የሚገኙት ሕዋሳት በፍሬው ውስጥ በሚገኙ ኬሚካሎች የረቀቀ ውህደት የተፈጠሩትን ልዩ ልዩ ጣዕሞች መለየት ይችላሉ። በእርግጥም “ጥሩነትህ ምንኛ ብዙ ነው! አንተን ለሚፈሩ ጠብቀህ አቆይተኸዋል” ብለን እንድንናገር የሚገፋፋን በቂ ምክንያት አለን። (መዝሙር 31:19) ይሁንና ይሖዋ ለሚፈሩት ሰዎች ጥሩነቱን ጠብቆ ያቆየው እንዴት ነው?

ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ ጥሩነት

12. ይሖዋ ካደረገልን ዝግጅቶች መካከል ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የትኛው ነው? ለምንስ?

12 ኢየሱስ “‘ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:4) በእርግጥም ይሖዋ ያደረገልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች የዘላለም ሕይወት የሚያስገኙልን በመሆናቸው እሱ ከሰጠን ሰብዓዊ ምግብም ይበልጥ ጠቃሚ ናቸው። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ላይ ይሖዋ ለማደስ በሚጠቀምበት ኃይሉ አማካኝነት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት መንፈሳዊ ገነት እውን እንዲሆን እንዳደረገ ተመልክተናል። የዚህ መንፈሳዊ ገነት አንዱ ቁልፍ ገጽታ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ነው።

13, 14. (ሀ) ነቢዩ ሕዝቅኤል በራእይ ምን ተመልክቷል? ይህስ ራእይ ዛሬ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? (ለ) ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ያደረገው ሕይወት ሰጪ የሆነ መንፈሳዊ ዝግጅት ምንድን ነው?

13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ የተሃድሶ ትንቢቶች አንዱ፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል ዳግም የተገነባና ክብር የተጎናጸፈ ቤተ መቅደስ በራእይ እንደተመለከተ የሚገልጸው ነው። ከዚህ ቤተ መቅደስ ውኃ ይፈስ የነበረ ሲሆን ውኃው እየሰፋና ጥልቀቱ እየጨመረ ሄዶ ወንዝ ይሆናል። ወንዙ በሚፈስበት አቅጣጫ ሁሉ መልካም ነገር ያስገኛል። በወንዙ ዳርና ዳርም ለምግብነትና ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ብዙ ዛፎች በቅለዋል። ይህ ወንዝ ጨዋማና ሕይወት አልባ የሆነው የሙት ባሕር እንኳ ሕይወት እንዲገኝበት አድርጓል! (ሕዝቅኤል 47:1-12) ሆኖም የዚህ ሁሉ ትርጉም ምንድን ነው?

14 ስለ ቤተ መቅደሱ የሚገልጸው ራእይ ይሖዋ ንጹሑን አምልኮ መልሶ እንደሚያቋቁም የሚያመለክት ነው። ለይሖዋ የሚቀርበው አምልኮ እንደገና የእሱን የጽድቅ መሥፈርቶች የሚያሟላ ይሆናል። በራእዩ ላይ እንደታየው ወንዝ ሁሉ፣ አምላክ ለዘላለም ሕይወት ያደረገው ዝግጅትም በየጊዜው እየጨመረ ነው። ንጹሕ አምልኮ መልሶ ከተቋቋመበት ከ1919 ጀምሮ ይሖዋ ሕይወት ሰጪ በሆኑ ዝግጅቶች ሕዝቦቹን መባረኩን ቀጥሏል። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱሶች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች እንዲሁም የጉባኤና ትላልቅ ስብሰባዎች በጣም አስፈላጊ የሆኑ እውነቶች በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች እንዲደርሱ እያደረጉ ነው። ይሖዋ በእነዚህ ዝግጅቶች አማካኝነት ከሁሉ ስለላቀው ስጦታው ማለት ስለ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ለሰዎች በማስተማር ላይ ነው። ይሖዋን ከልብ የሚወዱና የሚፈሩ ሰዎች በፊቱ ንጹሕ አቋም እንዲያገኙና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው ያስቻለው ይህ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። a በመሆኑም ዓለም በመንፈሳዊ ጠኔ እየተሠቃየ ባለበት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋ ሕዝቦች የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ ላይ ናቸው።—ኢሳይያስ 65:13

15. በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የይሖዋ ጥሩነት ለታማኝ የሰው ልጆች የሚፈሰው በምን መንገድ ነው?

15 ሆኖም ይህ አሮጌ ሥርዓት ሲያከትም ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ወንዝም መፍሰሱን ያቆማል ማለት አይደለም። እንዲያውም በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት በይበልጥ መፍሰሱን ይቀጥላል። በዚያ ወቅት ይሖዋ በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት የኢየሱስ መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋል፤ በመሆኑም ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ። በዚያን ጊዜ በይሖዋ ጥሩነት ምን ያህል እንደምንፈነድቅ አስበው!

የይሖዋ ጥሩነት የተንጸባረቀባቸው ሌሎች መንገዶች

16. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ጥሩነት ሌሎች ባሕርያትንም ያቀፈ እንደሆነ የሚገልጸው እንዴት ነው? ከእነዚህስ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

16 ይሖዋ ጥሩ ነው ሲባል ለጋስ ነው ማለት ብቻ አይደለም። አምላክ ለሙሴ “እኔ ራሴ ጥሩነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ፤ ይሖዋ የተባለውንም ስሜን በፊትህ አውጃለሁ” ብሎት ነበር። በተጨማሪም ዘገባው እንደሚከተለው ይላል፦ “ይሖዋም በፊቱ እያለፈ እንዲህ ሲል አወጀ፦ ‘ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ቸር የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ።’” (ዘፀአት 33:19፤ 34:6 የግርጌ ማስታወሻ) ስለዚህ የይሖዋ ጥሩነት ሌሎች ግሩም ባሕርያትንም ያቀፈ ነው። ከእነዚህ መካከል ሁለቱን እስቲ እንመልከት።

17. ይሖዋ ፍጽምና ለጎደላቸው የሰው ልጆች ደግነትና ትሕትና የሚያሳየው እንዴት ነው?

17 “ቸር።” እዚህ ጥቅስ ላይ “ቸር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ሩኅሩኅ” ተብሎም የሚተረጎምበት ጊዜ አለ። ቃሉ የሚያመለክተው ባሕርይ፣ ይሖዋ ፍጥረታቱን ስለሚይዝበት መንገድ ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለ። ይሖዋ በሥልጣን ላይ እንዳሉ እንደ ብዙዎቹ ሰዎች ትሕትናና ፍቅራዊ ስሜት የጎደለው ወይም ጨቋኝ ሳይሆን ገርና ደግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ አብርሃምን “እባክህ ካለህበት ቦታ ሆነህ ዓይንህን አቅንተህ ወደ ሰሜን፣ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 13:14) ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “እባክህ” የሚለውን ቃል ይተዉታል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚሉት በበኩረ ጽሑፉ ላይ ዓረፍተ ነገሩ ቀጥተኛ ትእዛዝ የሚያስተላልፍ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በትሕትና የቀረበ ጥያቄ እንደሆነ የሚጠቁም ማያያዣ ቃል ጥቅሱ ላይ ይገኛል። ተመሳሳይ አገላለጽ የሚገኝባቸው ሌሎች ጥቅሶችም አሉ። (ዘፍጥረት 31:12፤ ሕዝቅኤል 8:5) የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እዚህ ግባ የማይባለውን የሰውን ልጅ “እባክህ” ብሎ በትሕትና ሲያናግር እስቲ አስበው! ኃይለኝነት በነገሠበትና ለሰው አክብሮት በጠፋበት በዚህ ዓለም ውስጥ የአምላካችንን የይሖዋን መልካምነት ወይም ደግነት ማሰብ የሚያጽናና አይደለም?

18. ይሖዋ “እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ” ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው? እነዚህ ቃላት የሚያጽናኑ የሆኑትስ ለምንድን ነው?

18 “እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ።” ዛሬ ሐቀኝነት ከምድር ላይ ጠፍቷል ሊባል ይችላል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ እንደ ሰው አይዋሽም” ይላል። (ዘኁልቁ 23:19) እንዲያውም ቲቶ 1:2 ‘አምላክ ሊዋሽ እንደማይችል’ ይገልጻል። ይሖዋ እጅግ ጥሩ አምላክ ስለሆነ በምንም ተአምር ሊዋሽ አይችልም። በመሆኑም ተስፋዎቹ ፍጹም አስተማማኝ ናቸው፤ ቃሉ ምንጊዜም መሬት ጠብ አይልም። እንዲያውም “የእውነት አምላክ” ተብሎ ተጠርቷል። (መዝሙር 31:5) ሐሰትን ከመናገር መቆጠብ ብቻ ሳይሆን እውነትን አትረፍርፎ ይሰጣል። እውነትን ሚስጥር አድርጎ የሚይዝ ወይም ትክክለኛውን መረጃ የሚደብቅ አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከማይነጥፈው የጥበብ ምንጩ ለታማኝ አገልጋዮቹ የእውቀት ብርሃን ይፈነጥቅላቸዋል። b አልፎ ተርፎም በዚህ እውነት በመመራት ‘በእውነት ውስጥ መመላለስ’ እንዴት እንደሚችሉ ያስተምራቸዋል። (3 ዮሐንስ 3) ታዲያ የይሖዋ ጥሩነት በግለሰብ ደረጃ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

“በይሖዋ ጥሩነት . . . ፊታቸው ይፈካል”

19, 20. (ሀ) ሰይጣን፣ ሔዋን በይሖዋ ጥሩነት ላይ ያላት እምነት እንዲሸረሸር ለማድረግ የሞከረው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከተለ? (ለ) የይሖዋ ጥሩነት በእኛ ላይ ምን ስሜት ሊያሳድርብን ይገባል? ለምንስ?

19 ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ ሔዋንን ሲፈትናት መጀመሪያ የወሰደው እርምጃ በይሖዋ ጥሩነት ላይ ያላት እምነት እንዲሸረሸር ማድረግ ነበር። ይሖዋ ለአዳም “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ዛፍ ሁሉ እስክትረካ ድረስ መብላት ትችላለህ” ብሎት ነበር። ይሖዋ፣ በገነት ውስጥ ከነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ የሚያማምሩ ዛፎች መካከል ማዕቀብ ያደረገው በአንዷ ላይ ብቻ ነው። ሆኖም ሰይጣን ለሔዋን ያቀረበላት የመጀመሪያ ጥያቄ ምን እንደሚል ልብ በል፦ “በእርግጥ አምላክ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሏችኋል?” (ዘፍጥረት 2:9, 16፤ 3:1) ሔዋን አምላክ ያስቀረባቸው አንድ መልካም ነገር እንዳለ እንዲሰማት ለማድረግ ሲል ይሖዋ የሰጠውን ትእዛዝ በረቀቀ መንገድ አጣምሞ አቅርቦታል። የሚያሳዝነው ሰይጣን የተንኮል ዘዴው ሰምሮለታል። ሔዋን ዛሬ እንዳሉት እንደ ብዙዎቹ የሰው ልጆች፣ ሁሉን ነገር የሰጣትን አምላክ ጥሩነት መጠራጠር ጀመረች።

20 ይህ ጥርጣሬ ምን ያህል ሥቃይና መከራ እንዳስከተለ እናውቃለን። ስለሆነም በኤርምያስ 31:12 ላይ የሚገኙትን “በይሖዋ ጥሩነት . . . ፊታቸው ይፈካል” የሚሉትን ቃላት ልብ እንበል። በእርግጥም በይሖዋ ጥሩነት መደሰት ይኖርብናል። በጥሩነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለትን አምላካችንን በፍጹም ልንጠራጠረው አይገባም። ለሚወዱት ምንጊዜም በጎ ነገር የሚመኝ አምላክ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ ልንታመንበት እንችላለን።

21, 22. (ሀ) የይሖዋ ጥሩነት ምን እንድታደርግ ያነሳሳሃል? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ስለ የትኛው ባሕርይ እንመለከታለን? ይህ ባሕርይ ከጥሩነት የሚለየውስ እንዴት ነው?

21 በተጨማሪም ለሌሎች ስለ አምላክ ጥሩነት መናገር የምንችልበት አጋጣሚ ስናገኝ እንደሰታለን። መዝሙር 145:7 ስለ ይሖዋ ሕዝቦች ሲገልጽ “የጥሩነትህን ብዛት ሲያስታውሱ በስሜት ያወራሉ” ይላል። የይሖዋን ጥሩነት ሳንቀምስ የምንውልበት አንድም ቀን የለም። በየዕለቱ ይሖዋ ያደረገልህን ጥሩ ነገር እየጠቀስክ ለምን አታመሰግነውም? ስለዚህ ባሕርይ ማሰላሰላችን፣ ይሖዋን ስለ ጥሩነቱ በየዕለቱ ማመስገናችንና ስለዚህ ባሕርይው ለሌሎች መናገራችን ጥሩ የሆነውን አምላካችንን እንድንኮርጅ ይረዳናል። እንደ ይሖዋ ለሌሎች መልካም ለማድረግ ስንጥር ደግሞ ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን። አረጋዊው ሐዋርያው ዮሐንስ “ወዳጄ ሆይ፣ መጥፎ የሆነውን አትከተል፤ ይልቁንም ጥሩ የሆነውን ተከተል። መልካም የሚያደርግ የአምላክ ወገን ነው” ሲል ጽፏል።—3 ዮሐንስ 11

22 የይሖዋ ጥሩነት ከሌሎች ባሕርያትም ጋር ዝምድና አለው። ለምሳሌ “ታማኝ ፍቅሩ . . . እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ እንደሆነ ተገልጿል። (ዘፀአት 34:6) ይሖዋ ለሁሉም ሰዎች ጥሩነቱን የሚያሳይ ቢሆንም ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ግን ታዛዥ ለሆኑ አገልጋዮቹ ብቻ መሆኑ ይህን ባሕርይ ልዩ ያደርገዋል። ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንመለከታለን።

a ከቤዛው ዝግጅት የበለጠ የይሖዋን ጥሩነት የሚያሳይ ነገር ሊኖር አይችልም። ይሖዋ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት መካከል ለእኛ ሲል እንዲሞት የመረጠው የሚወደውን አንድያ ልጁን ነው።

b መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ብዙ ጊዜ ከብርሃን ጋር ያዛምደዋል። መዝሙራዊው “ብርሃንህንና እውነትህን ላክ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 43:3) ይሖዋ ከእሱ ለመማር ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ መንፈሳዊ ብርሃኑን ቦግ አድርጎ ያበራላቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 4:6፤ 1 ዮሐንስ 1:5