በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 3

ሁሉንም ነገሮች የሠራው ፈጣሪ

ሁሉንም ነገሮች የሠራው ፈጣሪ

ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ የሠራው ማን ነው?

አንድ አስደናቂ ነገር ልንገርህ፤ መስማት ትፈልጋለህ?— እስቲ እጅህን ተመልከት። ጣቶችህን እጠፋቸው። አሁን ደግሞ እስቲ አንድ ነገር አንሳ። በእጆችህ ብዙ ነገር መሥራት ትችላለህ፤ አብዛኛውን ነገር የምትሠራው ደግሞ በቀላሉ ነው። እጆቻችንን የሠራቸው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?—

አዎ፣ አፋችንን፣ አፍንጫችንንና ዓይናችንንም የፈጠረው የታላቁ አስተማሪ አባት የሆነው አምላክ ነው። አምላክ ዓይን ስለሰጠን ደስተኞች አይደለንም?— በዓይናችን ብዙ ነገር ማየት እንችላለን። አበቦችን ማየት እንችላለን። አረንጓዴውን ሣርና የጠራውን ሰማይ መመልከት እንችላለን። በሥዕሉ ላይ እንደሚታዩት ያሉ የተራቡ የወፍ ጫጩቶች ሲመገቡም ልናይ እንችላለን። በእርግጥም እንደነዚህ ያሉ ነገሮችን ማየት መቻላችን አስደናቂ ነገር ነው፣ አይደል?—

ታዲያ እነዚህን ነገሮች የሠራቸው ማን ነው? ሰው ሠርቷቸው ይሆን? በፍጹም። ሰዎች ቤት ሊሠሩ ይችላሉ። ነገር ግን ማንም ሰው ሣር ሊሠራ አይችልም። ሰዎች የወፍ ጫጩት፣ አበባ ወይም ማንኛውንም ዓይነት ሕይወት ያለው ነገር መፍጠር አይችሉም። ይህን ታውቃለህ?—

እነዚህን ነገሮች ሁሉ የፈጠረው አምላክ ነው። አምላክ ሰማይንና ምድርን ፈጥሯል። ሰዎችንም የፈጠረው እሱ ነው። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት እንደፈጠረ ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ተናግሯል።—ማቴዎስ 19:4-6

አምላክ ወንድንና ሴትን እንደፈጠረ ኢየሱስ እንዴት ሊያውቅ ቻለ? አምላክ ሰዎችን ሲፈጥር ኢየሱስ አይቷል?— አዎ፣ አይቷል። አምላክ ወንድንና ሴትን ሲፈጥር ኢየሱስ ከአምላክ ጋር ነበር። አምላክ ከሁሉ በፊት የፈጠረው ኢየሱስን ነው። ኢየሱስ መልአክ የነበረ ሲሆን ከአባቱ ጋር በሰማይ ይኖር ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ሰውን . . . እንሥራ” ብሎ እንደተናገረ ይገልጽልናል። (ዘፍጥረት 1:26) አምላክ ይነጋገር የነበረው ከማን ጋር እንደሆነ ታውቃለህ?— ከልጁ ጋር ነበር። አምላክ እየተነጋገረ የነበረው በኋላ ወደ ምድር መጥቶ ኢየሱስ ከሆነው ልጁ ጋር ነው።

አይገርምም? እስቲ አስበው! ለካስ ኢየሱስን ስናዳምጥ፣ አምላክ ምድርንና ሌሎችንም ነገሮች በሙሉ ሲፈጥር አብሮት ከነበረው ልጁ እየተማርን ነው ማለት ነው። ኢየሱስ በሰማይ ከአባቱ ጋር አብሮ በመሥራት ብዙ ነገር ተምሯል። ኢየሱስ ታላቅ አስተማሪ የሆነው ለዚህ ነው!

አምላክ ልጁን ከመፍጠሩ በፊት ብቻውን መሆኑ ያስጠላው ይመስልሃል?— በጭራሽ። ታዲያ ብቻውን መሆን ካላስጠላው ሕይወት ያላቸውን ብዙ ነገሮች የፈጠረው ለምንድን ነው?— ይህን ያደረገው አፍቃሪ አምላክ ስለሆነ ነው። ሌሎችም በመኖር እንዲደሰቱ ይፈልጋል። አምላክ ሕይወት ስለሰጠን ልናመሰግነው ይገባናል።

አምላክ የሠራው ነገር ሁሉ ፍቅሩን የሚያሳይ ነው። አምላክ ፀሐይን ፈጥሯል። ፀሐይ ብርሃን ትሰጠናለች፤ እንዲሁም ታሞቀናለች። ፀሐይ ባትኖር ኖሮ ሁሉም ነገር ስለሚቀዘቅዝ በምድር ላይ ምንም ዓይነት ሕይወት ሊኖር አይችልም ነበር። ታዲያ አምላክ ፀሐይን መፍጠሩ አያስደስትህም?—

አምላክ ዝናብ እንዲዘንብም ያደርጋል። ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ ውጪ መጫወት ስለማትችል ዝናብ አትወድ ይሆናል። ይሁን እንጂ ዝናብ አበቦች እንዲያድጉ ይረዳል። ስለዚህ የሚያምሩ አበቦች ስናይ ማንን ማመስገን አለብን?— አምላክን ማመስገን አለብን። የሚጣፍጡ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች በምንበላበት ጊዜ ማመስገን ያለብን ማንን ነው?— አትክልቶች የሚበቅሉት አምላክ በፈጠራቸው ፀሐይና ዝናብ አማካኝነት ስለሆነ አምላክን ማመስገን ይኖርብናል።

አንድ ሰው ‘ሰዎችንና እንስሳትንም የፈጠረው አምላክ ነው?’ የሚል ጥያቄ ቢያቀርብልህ ምን መልስ ትሰጣለህ?— “አዎ፣ ሰዎችንና እንስሳትንም የፈጠረው አምላክ ነው” ብለህ መልስ ከሰጠህ ትክክል ነህ። ይሁን እንጂ ሰውየው፣ አምላክ ሰዎችን እንደፈጠረ የማያምን ቢሆንስ? ‘ሰው ከእንስሳት ተሻሽሎ የመጣ ነው’ ቢልህስ? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አያስተምርም። ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ አምላክ እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዘፍጥረት 1:26-31

ቤት ሠሪ እንዳለው ሁሉ አበቦችን፣ ዛፎችንና እንስሳትን የሠራው ማን ነው?

ይሁን እንጂ አንድ ሰው ‘አምላክ የለም’ ይልህ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ምን ትለዋለህ?— አንድ ቤት አሳየው። ከዚያም ሰውየውን “ይህን ቤት የሠራው ማን ነው?” ብለህ ጠይቀው። ቤቱን አንድ ሰው ሠርቶት እንደሚሆን ሁሉም ሰው ያውቃል። ቤቱን የሠራው ሰው ነው እንጂ ቤቱ ራሱን በራሱ አልሠራም!—ዕብራውያን 3:4

ከዚያም ሰውየውን ወደ አንድ የአትክልት ቦታ ውሰደውና አበባ አሳየው። ከዚያም “ይህን አበባ የሠራው ማን ነው?” ብለህ ጠይቀው። ማንም ሰው አበባ ሊሠራ አይችልም። ቤቱ ራሱን እንዳልሠራ ሁሉ ደግሞ አበባውም ራሱን አልሠራም። አበባው ሠሪ አለው። እሱም አምላክ ነው።

ሰውየው የወፎችን ዝማሬ እንዲያዳምጥ ንገረው። ከዚያም “ወፎቹን የፈጠራቸውና መዘመር ያስተማራቸው ማን ነው?” ብለህ ጠይቀው። ወፎችን የፈጠራቸውና መዘመር ያስተማራቸው አምላክ ነው። ሰማይንና ምድርን እንዲሁም ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ የፈጠረው አምላክ ነው! ሕይወት የሚሰጠው እሱ ነው።

ሆኖም አንድ ሰው የሚያምነው የሚያየውን ነገር ብቻ እንደሆነ ይናገር ይሆናል። ‘ካላየሁት አላምንበትም’ ሊል ይችላል። ስለዚህ አንዳንድ ሰዎች አምላክን ሊያዩት ስለማይችሉ በእሱ እንደማያምኑ ይናገራሉ።

እርግጥ፣ አምላክን ልናየው አንችልም። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ‘አምላክን ማንም ሰው ሊያየው አይችልም’ ይላል። በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሰው፣ ወንድም ሆነ ሴት ወይም ሕፃን አምላክን ሊያየው አይችልም። ስለዚህ ማንም ሰው አምላክን ለመሣል ወይም የእሱን ምስል ለመሥራት መሞከር የለበትም። እንዲያውም አምላክ የእሱን ሥዕል ወይም ምስል እንዳንሠራ አዞናል። ስለዚህ እንዲህ ያሉ ነገሮችን በቤታችን ውስጥ ማስቀመጥ አምላክን አያስደስተውም።—ዘፀአት 20:4, 5፤ 33:20፤ ዮሐንስ 1:18

ታዲያ አምላክን ልታየው የማትችል ከሆነ መኖሩን እንዴት ታውቃለህ? እስቲ የሚከተለውን አስብ። ነፋስን ማየት ትችላለህ?— አትችልም። ነፋስን ማየት የሚችል ሰው የለም። ይሁን እንጂ ነፋስ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ማየት ትችላለህ። ነፋሱ በዛፍ ቅርንጫፎች መካከል በሚነፍስበት ጊዜ ቅጠሎቹ ሲንቀሳቀሱ ልታይ ትችላለህ። ስለዚህ ነፋስ መኖሩን ታምናለህ።

ነፋስ መኖሩን የምታውቀው እንዴት ነው?

ልክ እንደዚሁ አምላክ የሠራቸውን ነገሮችም ማየት ትችላለህ። አበባ ወይም ወፍ ስታይ አምላክ የሠራውን ነገር እያየህ ነው ማለት ነው። ስለዚህ በእርግጥ አምላክ እንዳለ ታምናለህ።

አንድ ሰው ‘ፀሐይንና ምድርን የፈጠረው ማን ነው?’ ብሎ ሊጠይቅህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:1) አዎ፣ እነዚህን አስደሳች ነገሮች ሁሉ የፈጠረው አምላክ ነው! አንተ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል?—

በሕይወት መኖር በጣም አስደሳች ነገር አይደለም? የወፎችን ጣፋጭ ዝማሬ መስማት እንችላለን። አበቦችንና አምላክ የፈጠራቸውን ሌሎች ነገሮችም ማየት እንችላለን። በተጨማሪም አምላክ የሰጠንን የተለያዩ ምግቦች መመገብ እንችላለን።

ለእነዚህ ሁሉ ነገሮች አምላክን ልናመሰግነው ይገባናል። ከሁሉ በላይ ግን ልናመሰግነው የሚገባን ሕይወት ስለሰጠን ነው። የእውነት አመስጋኞች ከሆን አንድ የምናደርገው ነገር አለ። ይህ ነገር ምንድን ነው?— አምላክን እናዳምጣለን፤ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያዘዘንን ሁሉ ተግባራዊ እናደርጋለን። በዚህ መንገድ ሁሉን ነገር የሠራውን አምላክ እንደምንወድ ማሳየት እንችላለን።

አምላክ ላደረገው ነገር ሁሉ አድናቆት ማሳየት ይኖርብናል። እንዴት? መዝሙር 139:14፤ ዮሐንስ 4:23, 24፤ 1 ዮሐንስ 5:21 እና ራእይ 4:11ን አንብቡ።