በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 18

ለተደረገልህ ነገር አስታውሰህ ታመሰግናለህ?

ለተደረገልህ ነገር አስታውሰህ ታመሰግናለህ?

ዛሬ ምግብ በልተሃል?— ምግቡን ያዘጋጀው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?— ምግቡን ያዘጋጀችው እናትህ ልትሆን ትችላለች፤ አለዚያም ሌላ ሰው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ለምግቡ አምላክን ማመስገን ያለብን ለምንድን ነው?— ምክንያቱም አትክልቶች እንዲበቅሉ በማድረግ ለምግብ የሚሆኑ ነገሮችን የሚሰጠን አምላክ ነው። ይሁን እንጂ ምግቡን ያዘጋጀልንን ወይም ያቀረበልንን ሰው ጭምር ማመስገን ይኖርብናል።

ሰዎች ጥሩ ነገር ሲያደርጉልን አንዳንድ ጊዜ ማመስገን እንረሳለን፣ አይደል? ታላቁ አስተማሪ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ማመስገን የረሱ የሥጋ ደዌ በሽተኞች ነበሩ።

የሥጋ ደዌ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— የሥጋ ደዌ ማለት ገላን የሚያቆስልና ሰውነት እየተቀረፈ እንዲወድቅ የሚያደርግ በሽታ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የሥጋ ደዌ በሽተኞች ከሌሎች ሰዎች ርቀው መኖር ይጠበቅባቸው ነበር። ይህ በሽታ ያለበት ሰው አንድ ሌላ ሰው ወደ እሱ አቅጣጫ ሲመጣ ካየ ሰውየው ወደ እሱ እንዳይቀርብ ለማስጠንቀቅ ገና ከሩቁ ጮክ ብሎ መናገር ነበረበት። ይህ የሚደረገው ሌሎች ሰዎች ወደ በሽተኛው በጣም እንዳይቀርቡና በሽታው እንዳይዛቸው ለመከላከል ሲባል ነበር።

ኢየሱስ ለሥጋ ደዌ በሽተኞች በጣም ደግ ነበር። አንድ ቀን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ላይ ሳለ በአንዲት ትንሽ ከተማ በኩል ያልፍ ነበር። ወደ ከተማይቱ ሲቃረብ የሥጋ ደዌ በሽተኞች ወደ እሱ መጡ። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ሁሉንም ዓይነት በሽታዎች ለመፈወስ የሚያስችል አምላክ የሰጠው ኃይል እንዳለው ሰምተው ነበር።

የሥጋ ደዌ በሽተኞቹ ወደ ኢየሱስ አልተጠጉም። ከዚህ ይልቅ ራቅ ብለው ቆሙ። ይሁንና ኢየሱስ ከበሽታው ሊያድናቸው እንደሚችል አምነው ነበር። ስለዚህ ታላቁን አስተማሪ ባዩት ጊዜ ጮክ ብለው ‘ኢየሱስ፣ መምህር፣ እርዳን!’ አሉት።

ለታመሙ ሰዎች ታዝናለህ?— ኢየሱስ ያዝንላቸው ነበር። ኢየሱስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ መሆን ምን ያህል የሚያሳዝን ነገር እንደሆነ ያውቅ ነበር። ስለዚህ “ሄዳችሁ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ” አላቸው።—ሉቃስ 17:11-14

ኢየሱስ እነዚህ የሥጋ ደዌ ያለባቸው ሰዎች ምን እንዲያደርጉ እየነገራቸው ነው?

ኢየሱስ ራሳቸውን ለካህናት እንዲያሳዩ የነገራቸው ለምንድን ነው? ይሖዋ ቀደም ሲል የሥጋ ደዌ በሽተኞችን በሚመለከት ለሕዝቡ ሕግ ሰጥቷቸው ስለነበር ነው። ይህ ሕግ ካህኑ የሥጋ ደዌ በሽተኛውን ገላ እንዲመረምር ያዛል። ሰውየው በሽታው ሙሉ በሙሉ ሲለቀው ካህኑ ከበሽታው እንደዳነ ይነግረዋል። ስለዚህ በሽተኛው ሙሉ በሙሉ ሲድን ጤነኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር አብሮ መኖር ይችል ነበር።—ዘሌዋውያን 13:16, 17

ኢየሱስ ራሳቸውን ለካህን እንዲያሳዩ ያዘዛቸው እነዚህ ሰዎች ግን በሽታው ገና አልለቀቃቸውም ነበር። ታዲያ ኢየሱስ እንደነገራቸው ወደ ካህን ሄዱ?— አዎ፣ ወዲያውኑ ሄደዋል። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ከበሽታቸው ሊያድናቸው እንደሚችል አምነው ነበር ማለት ነው። ታዲያ ምን አጋጥሟቸው ይሆን?

ገና ወደ ካህኑ በመሄድ ላይ ሳሉ በሽታው ለቀቃቸው። ገላቸው ተፈወሰ። ሙሉ በሙሉ ዳኑ! ኢየሱስ ባለው ኃይል ላይ ያሳዩት እምነት ጥሩ ውጤት አስገኝቶላቸዋል። ምን ያህል ተደስተው ይሆን! ሆኖም እነዚህ ሰዎች ምስጋናቸውን ለመግለጽ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?—

የሥጋ ደዌ ይዞት የነበረው ይህ ሰው ምን ነገር አስታውሶ አድርጓል?

ከተፈወሱት ሰዎች አንዱ ወደ ኢየሱስ ተመልሶ መጣ። ለይሖዋ ክብር መስጠትና አምላክን ማመስገን ጀመረ። ሰውየው አምላክን ማመስገኑ ተገቢ ነበር፤ ምክንያቱም እሱ የተፈወሰበት ኃይል የተገኘው ከአምላክ ነው። በተጨማሪም ሰውየው በታላቁ አስተማሪ እግር ሥር በመንበርከክ ምስጋናውን አቅርቧል። ኢየሱስ ላደረገለት ነገር በጣም አመስጋኝ ነበር።

ሌሎቹ ዘጠኝ ሰዎችስ? ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቀ:- ‘የነጹት አሥር የሥጋ ደዌ በሽተኞች አይደሉም እንዴ? ታዲያ ዘጠኙ የት አሉ? አምላክን ለማመስገን የተመለሰው አንዱ ብቻ ነው?’

እውነትም ለአምላክ ክብር የሰጠውና ኢየሱስን ለማመስገን የተመለሰው ከአሥሩ አንዱ ብቻ ነበር። ይህ ሰው ደግሞ ከሌላ አገር የመጣ ሳምራዊ ነበር። ሌሎቹ ዘጠኝ ሰዎች አምላክንም ሆነ ኢየሱስን አላመሰገኑም።—ሉቃስ 17:15-19

አንተ ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ እንደየትኛው ሰው ነህ? እንደ ሳምራዊው ሰው መሆን እንፈልጋለን፣ አይደል?— ስለዚህ አንድ ሰው በደግነት ተነሳስቶ አንድ ነገር ሲያደርግልን ምን ማስታወስ ይኖርብናል?— ምስጋናችንን መግለጽ ይኖርብናል። ብዙውን ጊዜ ሰዎች አመሰግናለሁ ማለት ይረሳሉ። ሆኖም አመሰግናለሁ ማለት ጥሩ ነገር ነው። የምናመሰግን ከሆነ ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ይደሰታሉ።

ወደ ኢየሱስ የተመለሰውን የሥጋ ደዌ በሽተኛ መምሰል የምትችለው እንዴት ነው?

ትንሽ ለማሰብ ብትሞክር ሰዎች ብዙ ነገር እንዳደረጉልህ ትዝ ይልህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ አሞህ ያውቃል?— እንደነዚያ አሥር የሥጋ ደዌ በሽተኞች ከባድ በሽታ ይዞህ ባያውቅ እንኳን ኃይለኛ ጉንፋን ይዞህ ወይም ሆድህን አሞህ ያውቅ ይሆናል። ታዲያ በዚያን ጊዜ እንክብካቤ ያደረገልህ ሰው ነበር?— እንክብካቤ ያደረጉልህ ሰዎች መድኃኒት ሰጥተውህ እንዲሁም ሌላ ነገር አድርገውልህ ይሆናል። ሕመሙ እንዲሻልህ ስለረዱህ አልተደሰትክም?—

ሳምራዊው ሰው እንዲድን ስለረዳው ኢየሱስን አመስግኖታል፤ ይህም ኢየሱስን አስደስቶታል። አንተም፣ እናትህም ሆነች አባትህ ላደረጉልህ ነገር አመሰግናለሁ ብትላቸው ደስ የሚላቸው አይመስልህም?— አዎ፣ ደስ ይላቸዋል።

አስታውሶ ማመስገን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

አንዳንድ ሰዎች በየቀኑ ወይም በየሳምንቱ ብዙ ነገር ያደርጉልሃል። ይህን የሚያደርጉልህ ሥራቸው ስለሆነ ሊሆን ይችላል። ይህን ሥራ በመሥራታቸውም ይደሰቱ ይሆናል። አንተ ግን አመሰግናለሁ ማለት ልትረሳ ትችላለህ። አስተማሪህ አንተን ለማስተማር ብዙ ጥረት ታደርግ ይሆናል። ይህ ሥራዋ ነው። ቢሆንም አንተ እንድትማር ስለምትረዳህ ብታመሰግናት ደስ ይላታል።

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ትንንሽ ነገሮች ያደርጉልህ ይሆናል። አንድ ሰው በር ከፍቶልህ ያውቃል? ወይም ደግሞ ምግብ በምትበላበት ሰዓት በጠረጴዛው ላይ ያለውን ምግብ አንስቶ ያቀበለህ ሰው አለ? ለእነዚህ ትንንሽ ነገሮችም እንኳ አመሰግናለሁ ማለት ጥሩ ነው።

በምድር ላይ ያሉ ሰዎችን አስታውሰን አመሰግናለሁ የምንል ከሆነ በሰማይ ያለውን አባታችንንም አስታውሰን እናመሰግነዋለን። ደግሞም ይሖዋን እንድናመሰግን የሚያደርጉን በጣም ብዙ ነገሮች አሉ! ይሖዋ ሕይወትንና ሕይወትን አስደሳች ለማድረግ የሚረዱ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ሰጥቶናል። ስለዚህ በየቀኑ ስለ አምላክ ጥሩ ነገሮችን በመናገር ለእሱ ክብር መስጠታችን ተገቢ ነው።

አመስጋኝ ስለመሆን የሚናገሩትን የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ:- መዝሙር 92:1፤ ኤፌሶን 5:20፤ ቆላስይስ 3:17፤ 1 ተሰሎንቄ 5:18