በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 25

መጥፎ ነገር የሚሠሩ ሰዎች ሊለወጡ ይችላሉ?

መጥፎ ነገር የሚሠሩ ሰዎች ሊለወጡ ይችላሉ?

ሁሉም ሰው ጥሩ ነገር ቢሠራ አስደሳች አይሆንም ነበር?— ይሁን እንጂ ሁልጊዜ ጥሩ ነገር ብቻ የሚሠራ ሰው የለም። ሁላችንም ጥሩ ነገር መሥራት እየፈለግን አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ነገር የምንሠራው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ምክንያቱም ሁላችንም ኃጢአተኞች ሆነን ስለተወለድን ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ብዙ መጥፎ ነገሮች ይሠራሉ። እነዚህ ሰዎች ሌሎች ሰዎችን የሚጠሉ ከመሆኑም በላይ ሆን ብለው እነሱን የሚጎዳ ነገር ይፈጽማሉ። እነዚህ ሰዎች ተለውጠው ጥሩ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብለህ ታስባለህ?—

በሥዕሉ ላይ እስጢፋኖስን በድንጋይ እየወገሩ ያሉትን ሰዎች ልብስ የሚጠብቀውን ወጣት ተመልከት። የዕብራይስጥ ስሙ ሳኦል ሲሆን ሮማዊ ስሙ ደግሞ ጳውሎስ ነው። የታላቁ አስተማሪ ደቀ መዝሙር የሆነው እስጢፋኖስ እየተገደለ በመሆኑ ሳኦል ተደስቷል። ሳኦል እንደዚህ ያለ መጥፎ ነገር ይሠራ የነበረው ለምን እንደሆነ እንመልከት።

ሳኦል ፈሪሳውያን በመባል የሚታወቁትን ሰዎች ያቀፈ የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ ቡድን አባል ነበር። ፈሪሳውያን የአምላክ ቃል ነበራቸው፤ ነገር ግን የበለጠ ትኩረት የሚሰጡት የራሳቸው ሃይማኖታዊ መሪዎች ለሚያስተምሩት ትምህርት ነበር። ሳኦል መጥፎ ነገር እንዲሠራ ያደረገው ይህ ነው።

እስጢፋኖስ በኢየሩሳሌም በተያዘበት ጊዜ ሳኦልም እዚያው ነበር። እስጢፋኖስ ወደ ፍርድ ቤት የተወሰደ ሲሆን ከዳኞቹ መካከል ደግሞ አንዳንዶቹ ፈሪሳውያን ነበሩ። እስጢፋኖስ ስለ እሱ ብዙ መጥፎ ነገር ቢወራበትም አልፈራም። ከዚህ ይልቅ በድፍረት ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ለዳኞቹ ጥሩ ምሥክርነት ሰጠ።

ዳኞቹ ግን እስጢፋኖስ የተናገረውን ነገር አልወደዱትም። ቀድሞውኑም ቢሆን ስለ ኢየሱስ ብዙ ነገር ያውቁ ነበር። እንዲያውም ኢየሱስን ያስገደሉት ከጥቂት ጊዜ በፊት ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ይሖዋ ኢየሱስን ወደ ሰማይ ወስዶታል። ሆኖም ዳኞቹ አኗኗራቸውን ከመለወጥ ይልቅ በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቀጥለው ነበር።

ዳኞቹ እስጢፋኖስን ይዘው ከከተማው ውጪ ወሰዱት። እዚያም በኃይል መትተው ከጣሉት በኋላ በድንጋይ ይወግሩት ጀመር። በሥዕሉ ላይ እንደምትመለከተው ሳኦል ቆሞ እያያቸው ነበር። እስጢፋኖስን መግደል ተገቢ ነው ብሎ አስቦ ነበር።

ሳኦል እስጢፋኖስ መገደሉ ተገቢ ነው ብሎ ያሰበው ለምን ነበር?

ሳኦል እስጢፋኖስን መግደል ተገቢ ነው ብሎ ያሰበው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ሳኦል ለረጅም ጊዜ ፈሪሳዊ ሆኖ ኖሯል፤ ስለዚህ የፈሪሳውያን ትምህርቶች ትክክል ናቸው ብሎ ያምን ነበር። ፈሪሳውያንን ጥሩ ምሳሌ እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸው ስለነበር እነሱን ለመምሰል ይጥር ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 7:54-60

እስጢፋኖስ ከተገደለ በኋላ ሳኦል ምን አደረገ?— ይባስ ብሎ የቀሩትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጨርሶ ለማጥፋት ጥረት ማድረግ ጀመረ! ወደ ቤታቸው እየገባ ወንዶቹንም ሴቶቹንም እየጎተተ ያወጣቸው ነበር። ከዚያም ወደ እስር ቤት ያስገባቸው ነበር። ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርት ኢየሩሳሌምን ለቀው ለመሄድ ቢገደዱም ስለ ኢየሱስ መስበካቸውን ግን አላቆሙም።—የሐዋርያት ሥራ 8:1-4

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በደረሱበት ቦታ ሁሉ ስለ ኢየሱስ መስበካቸው ሳኦል የበለጠ እንዲጠላቸው አደረገው። ስለዚህ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ በመሄድ በደማስቆ ከተማ ያሉትን ክርስቲያኖች ለመያዝ የሚያስችል ፈቃድ ጠይቆ አገኘ። ሳኦል በደማስቆ ያሉትን ደቀ መዛሙርት አስሮ ወደ ኢየሩሳሌም በማምጣት እንዲቀጡ ማድረግ ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ ወደ ደማስቆ እየሄደ ሳለ በመንገድ ላይ አንድ አስገራሚ ነገር አጋጠመው።

ሳኦልን እያናገረው ያለው ማን ነው? ደግሞስ ሳኦልን ምን እንዲያደርግ ላከው?

ከሰማይ ብርሃን አንፀባረቀና አንድ ድምፅ “ሳኦል፣ ሳኦል፣ ለምን ታሳድደኛለህ?” አለው። ከሰማይ የመጣው ድምፅ የኢየሱስ ነበር። ብርሃኑ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ የሳኦልን ዓይን አሳወረው፤ ስለዚህ ከሳኦል ጋር የነበሩት ሰዎች እየመሩ ወደ ደማስቆ ወሰዱት።

ከሦስት ቀን በኋላ ኢየሱስ በደማስቆ ከሚኖሩት ደቀ መዛሙርቱ አንዱ ለሆነው ለሐናንያ በራእይ ታየው። ኢየሱስ፣ ሐናንያ ሳኦልን ሄዶ እንዲጠይቀው እንዲሁም ዓይኑን እንዲያበራለትና እንዲያነጋግረው ነገረው። ሐናንያ ሳኦልን ሲያነጋግረው ሳኦል ስለ ኢየሱስ የተነገረውን እውነት ተቀበለ። በተጨማሪም እንደገና ማየት ቻለ። ሳኦል አኗኗሩን ሙሉ በሙሉ ለውጦ የአምላክ ታማኝ አገልጋይ ሆነ።—የሐዋርያት ሥራ 9:1-22

ሳኦል መጥፎ ነገር ይሠራ የነበረው ለምን እንደሆነ አሁን ገባህ?— ሳኦል መጥፎ ነገር ይሠራ የነበረው ስህተት የሆኑ ነገሮችን ስለተማረ ነው። ለአምላክ ታማኝ ያልሆኑ ሰዎችን ይከተል ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የሰውን ሐሳብ ከአምላክ ቃል አስበልጠው የሚመለከቱ ሰዎች ቡድን አባል ነበር። ታዲያ ሌሎች ፈሪሳውያን አምላክን መቃወማቸውን የቀጠሉ ቢሆንም ሳኦል አኗኗሩን ለውጦ ጥሩ ነገር መሥራት የጀመረው ለምንድን ነው?— ሳኦል እውነትን የሚጠላ ሰው ስላልነበረ ነው። ስለዚህ ትክክል የሆነውን ነገር ሲማር እውነትን ለመታዘዝ ዝግጁ ነበር።

ሳኦል በኋላ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— አዎ፣ የኢየሱስ ሐዋርያ የሆነ ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ ተጠርቷል። ጳውሎስ ደግሞ ከማንም ሰው በላይ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎችን እንደጻፈ አስታውስ።

እንደ ሳኦል ያሉ መለወጥ የሚችሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ይህን ለውጥ ማድረግ ቀላል አይደለም፤ ምክንያቱም ሰዎች መጥፎ ነገር እንዲሠሩ ለማድረግ በጣም የሚጥር አንድ አካል አለ። እሱ ማን እንደሆነ ታውቃለህ?— ኢየሱስ ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ለሳኦል በተገለጠለት ጊዜ ስለ እሱ ነግሮታል። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከሰማይ ሳኦልን ሲያናግረው ‘የሰዎችን ዓይን እንድትከፍት እንዲሁም ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ አምላክ እንድትመልሳቸው እልክሃለሁ’ ብሎታል።—የሐዋርያት ሥራ 26:17, 18

አዎ፣ ሁሉም ሰው መጥፎ ነገር እንዲሠራ ለማድረግ እየጣረ ያለው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ አንዳንድ ጊዜ ከባድ ይሆንብሃል?— አንዳንድ ጊዜ ሁላችንም ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ከባድ ይሆንብናል። ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ሰይጣን ነው። ነገር ግን ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ቀላል የማይሆንበት ሌላም ምክንያት አለ። ይህ ምክንያት ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ኃጢአተኞች ሆነን ስለተወለድን ነው።

ብዙ ጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ይልቅ ስህተት የሆነውን ማድረግ እንዲቀለን የሚያደርገው ይህ ኃጢአት ነው። ስለዚህ ምን ማድረግ ያስፈልገናል?— አዎ፣ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ መታገል አለብን። ይህን ትግል ስናደርግ ኢየሱስ ስለሚወደን እንደሚረዳን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ፣ በፊት መጥፎ ነገር ሲሠሩ የነበሩ ቢሆኑም በኋላ የተለወጡ ሰዎችን ወዷቸዋል። እነዚህ ሰዎች ለመለወጥ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ያውቃል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከብዙ ወንዶች ጋር የጾታ ግንኙነት ይፈጽሙ የነበሩ ሴቶች ይገኙበታል። ይህ ደግሞ መጥፎ ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሴቶች ጋለሞቶች ወይም አመንዝሮች ብሎ ይጠራቸዋል።

ኢየሱስ መጥፎ ነገር ትሠራ የነበረችውን ይህችን ሴት ይቅርታ ያደረገላት ለምንድን ነው?

በአንድ ወቅት፣ አንዲት አመንዝራ ሴት ስለ ኢየሱስ ሰማችና እሱ ወደ ነበረበት ወደ አንድ ፈሪሳዊ ቤት መጣች። ከዚያም የኢየሱስን እግር ሽቶ ቀባችው፤ እንዲሁም እንባዋን ከእግሩ ላይ በፀጉሯ ጠረገች። በሠራችው ኃጢአት በጣም አዝና ስለነበር ኢየሱስ ይቅርታ አደረገላት። ፈሪሳዊው ግን ሴትየዋ ይቅርታ ሊደረግላት አይገባም ብሎ አስቦ ነበር።—ሉቃስ 7:36-50

ኢየሱስ በሌላ ወቅት ፈሪሳውያንን ምን እንዳላቸው ታውቃለህ?— “ጋለሞቶች ወደ አምላክ መንግሥት በመግባት ረገድ እየቀደሟችሁ ነው” አላቸው። (ማቴዎስ 21:31) ኢየሱስ ይህን የተናገረው እነዚህ ጋለሞቶች ወይም አመንዝሮች በእሱ ስላመኑና መጥፎ አኗኗራቸውን ስለለወጡ ነው። ፈሪሳውያን ግን በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ መጥፎ ነገር መሥራታቸውን ቀጥለው ነበር።

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እየሠራን ያለነው ነገር መጥፎ እንደሆነ የሚገልጽ ከሆነ ለመለወጥ ፈቃደኞች መሆን አለብን። ደግሞም ይሖዋ ምን እንድናደርግ እንደሚፈልግ ከተረዳን በተግባር ለማዋል ዝግጁ መሆን አለብን። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ የሚደሰትብን ከመሆኑም በላይ የዘላለም ሕይወት ይሰጠናል።

መጥፎ ነገር ከመሥራት እንድንቆጠብ የሚረዱንን የሚከተሉትን ጥቅሶች አብረን እናንብብ:- መዝሙር 119:9-11፤ ምሳሌ 3:5-7፤ 12:15