በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 33

ኢየሱስ ሊጠብቀን ይችላል

ኢየሱስ ሊጠብቀን ይችላል

ኢየሱስን የምትመለከተው እንዴት ነው? —እንደ ኃያል ንጉሥ ነው ወይስ ራሱን መርዳት እንደማይችል ሕፃን?

ኢየሱስ ካደገ በኋላ በሕፃንነቱ እንዴት ጥበቃ እንደተደረገለት ሲያውቅ ይሖዋን በጸሎት ያመሰገነው አይመስልህም?— ኢየሱስ እንዳይገደል ማርያምና ዮሴፍ ወደ ግብፅ ይዘውት ሄደው እንደነበረ ከጊዜ በኋላ ሲያውቅ ምን የሚላቸው ይመስልሃል?—

እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ አሁን ሕፃን አይደለም። በተጨማሪም እንደዚያን ጊዜው አሁን በምድር ላይ እየኖረ አይደለም። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን በግርግም የተኛ ሕፃን እንደሆነ አድርገው እንደሚያስቡት አስተውለሃል?— በገና ወቅት ኢየሱስን እንደ ሕፃን አድርገው የሚያሳዩ ሥዕሎች በብዙ ቦታዎች የሚታዩ መሆናቸው ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው።

ኢየሱስ አሁን በምድር ላይ እየኖረ ባይሆንም ሕያው እንደሆነ ታምናለህ?— አዎ፣ ኢየሱስ ከሞት የተነሳ ሲሆን አሁን በሰማይ ኃያል ንጉሥ ሆኗል። የሚያገለግሉትን ሰዎች ለመጠበቅ ምን ማድረግ የሚችል ይመስልሃል?— ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በምድር ሳለ የሚወዱትን ሰዎች እንዴት መጠበቅ እንደሚችል አሳይቷል። አንድ ቀን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በጀልባ ተሳፍሮ ሲሄድ የሚወዱትን ሰዎች መጠበቅ የቻለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ቀኑ ሊመሽ ተቃርቦ ነበር። ኢየሱስ 20 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 12 ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው የገሊላ ባሕር በሚባለው ሐይቅ ዳርቻ ቀኑን ሙሉ ሲያስተምር ውሏል። ከዚያም ደቀ መዛሙርቱን “ወደ ሐይቁ ማዶ እንሻገር” አላቸው። ስለዚህ በጀልባ ሆነው ወደ ማዶ ለመሻገር መጓዝ ጀመሩ። ኢየሱስ በጣም ስለደከመው ወደ ጀልባዋ ኋለኛ ክፍል ሄዶ ትራስ ተንተርሶ ተኛ። ወዲያውኑም ኃይለኛ እንቅልፍ ወሰደው።

ኢየሱስ ነፋሱንና ማዕበሉን ምን እያለው ነው?

ደቀ መዛሙርቱ ጀልባዋን እየቀዘፉ ስለነበር አልተኙም። ለጊዜው ሁሉም ነገር ደህና ይመስል ነበር፤ ይሁን እንጂ በድንገት ኃይለኛ ነፋስ መጣ። ነፋሱ በኃይል ሲነፍስ ማዕበሉ እየጨመረ ሄደ። ማዕበሉ ከጀልባዋ ጋር እየተላተመ ወደ ውስጥ ይገባ ስለነበር ጀልባዋ በውኃ መሞላት ጀመረች።

ደቀ መዛሙርቱ ልንሰምጥ ነው ብለው ፈሩ። ኢየሱስ ግን አልፈራም። እሱ አሁንም በጀልባዋ ኋለኛ ክፍል እንደተኛ ነው። በመጨረሻም ደቀ መዛሙርቱ ቀሰቀሱትና ‘መምህር፣ መምህር አድነን፤ ማዕበሉ ሊያጠፋን እኮ ነው’ አሉት። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ተነሳና ነፋሱንና ማዕበሉን “ጸጥ በል! ረጭ በል!” አለው።

ወዲያውኑ ነፋሱ ቆመ፤ ሐይቁም ረጭ አለ። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተገረሙ። ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ነገር አይተው አያውቁም ነበር። እርስ በርሳቸው “ነፋስንና ውኃን እንኳ የሚያዝ፣ እነሱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ይባባሉ ጀመር።—ሉቃስ 8:22-25፤ ማርቆስ 4:35-41

አንተ ኢየሱስ ማን እንደሆነ ታውቃለህ?— ታላቅ ኃይሉን ያገኘው ከየት እንደሆነ ታውቃለህ?— ኢየሱስ ተራ ሰው ስላልነበረ ደቀ መዛሙርቱ ከእሱ ጋር እያሉ መፍራት አልነበረባቸውም። ሌላ ሰው ሊያደርጋቸው የማይችላቸውን ድንቅ ነገሮች የማድረግ ችሎታ ነበረው። አንድ ቀን በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ላይ ያደረገውን ሌላ ነገር ልንገርህ።

ይህ የሆነው ከላይ የተጠቀሰው ሁኔታ ከተፈጸመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው። ሲመሽ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በጀልባ ተሳፍረው ወደ ባሕሩ ማዶ ቀድመውት እንዲሻገሩ ነገራቸው። ከዚያም ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ወደ ተራራው ወጣ። ተራራው ወደ አባቱ ወደ ይሖዋ አምላክ ሊጸልይ የሚችልበት ጸጥ ያለ ቦታ ነበር።

ደቀ መዛሙርቱ ጀልባዋ ላይ ተሳፍረው ወደ ማዶ ለመሻገር መቅዘፍ ጀምረዋል። ነገር ግን ወዲያው ነፋስ መንፈስ ጀመረ። የነፋሱ ኃይል እየጨመረ የሄደ ሲሆን ምሽቱ ደግሞ በጣም ገፍቶ ሌሊት ሆኗል። ሰዎቹ የጀልባዋን ሸራ አውርደው እንዲሁ መቅዘፍ ጀመሩ። ይሁን እንጂ ኃይለኛው ነፋስ ከፊታቸው ወደ እነሱ አቅጣጫ ይነፍስ ስለነበር ወደ ፊት ብዙ መሄድ አልቻሉም። ጀልባዋ በከፍተኛ ማዕበል ወደ ኋላና ወደ ፊት ትወዛወዝ ጀመር፤ ውኃውም ወደ ውስጥ ይገባ ጀመር። ሰዎቹ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም አልቻሉም።

ኢየሱስ ግን አሁንም ብቻውን ተራራው ላይ ነበር። እዚያ ረዘም ላለ ጊዜ ቆየ። አሁን ግን ደቀ መዛሙርቱ በኃይለኛው ማዕበል የተነሳ አደጋ ሊደርስባቸው እንደሆነ ተመለከተ። ስለዚህ ከተራራው ወርዶ ወደ ባሕሩ ዳርቻ መጣ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለመርዳት ስለፈለገ በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ መጣ!

በውኃ ላይ ለመሄድ ብትሞክር ምን ትሆናለህ?— ውኃው ውስጥ ልትጠልቅና ሰምጠህ ልትሞት ትችላለህ። ኢየሱስ ግን የተለየ ነው። እሱ ልዩ ኃይል አለው። ኢየሱስ ወደ ጀልባው ለመድረስ ረጅም ርቀት መጓዝ ነበረበት። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በውኃ ላይ እየተራመደ ወደ እነሱ ሲመጣ ያዩት ሊነጋ አካባቢ ነበር። ይሁን እንጂ ያዩትን ነገር ማመን አልቻሉም። በጣም ስለደነገጡ በፍርሃት ጮኹ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።

ኢየሱስ ተአምራት የፈጸመው ለምን ነበር?

ኢየሱስ ጀልባው ላይ እንደወጣ ነፋሱ ጸጥ አለ። ደቀ መዛሙርቱ አሁንም ተገረሙ። በኢየሱስ ፊት ተደፍተው “አንተ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነህ” አሉት።—ማቴዎስ 14:22-33፤ ዮሐንስ 6:16-21

በዚያን ጊዜ ኖረን ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ሲያደርግ ብናይ ጥሩ ነበር፣ አይደል?— ኢየሱስ እነዚያን ተአምራዊ ነገሮች ይፈጽም የነበረው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— እነዚያን ተአምራት ይፈጽም የነበረው ደቀ መዛሙርቱን ስለሚወዳቸውና ሊረዳቸው ይፈልግ ስለነበረ ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እነዚያን ተአምራት የፈጸመው ታላቅ ኃይል እንዳለውና የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በሚሆንበት ጊዜ ይህን ኃይሉን እንደሚጠቀምበት ለማሳየት ጭምር ነው።

ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ተከታዮቹን የሚጠብቃቸው እንዴት ነው?

ሰይጣን የኢየሱስ ተከታዮች ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች እንዳይናገሩ እንቅፋት ለመፍጠር ጥረት የሚያደርግ በመሆኑ በዛሬው ጊዜም እንኳ ኢየሱስ ተከታዮቹን ከዚህ የሰይጣን ተጽዕኖ ለመጠበቅ ኃይሉን ይጠቀምበታል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ኃይሉን ደቀ መዛሙርቱ እንዳይታመሙ ለማድረግ አለዚያም ሲታመሙ ለመፈወስ አይጠቀምበትም። የኢየሱስ ሐዋርያትም እንኳ ከጊዜ በኋላ አንድ በአንድ ሞተዋል። የዮሐንስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ የተገደለ ሲሆን ዮሐንስ ራሱም እስር ቤት ገብቶ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 12:2፤ ራእይ 1:9

በዛሬው ጊዜም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ሰዎች ይሖዋን የሚያገለግሉ ሆኑም አልሆኑ ሁሉም ሊታመሙ እንዲሁም ሊሞቱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በቅርቡ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ምድርን በሚገዛበት ወቅት አሁን ያሉት ሁኔታዎች ሁሉ ይለወጣሉ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ የሚታዘዙትን ሁሉ ለመባረክ ኃይሉን ስለሚጠቀምበት ማንም ሰው የሚፈራበት ምክንያት አይኖርም።—ኢሳይያስ 9:6, 7

አምላክ በመንግሥቱ ላይ ገዥ አድርጎ የሾመውን የኢየሱስን ታላቅ ኃይል የሚያሳዩት ሌሎች ጥቅሶች የሚከተሉት ናቸው:- ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 28:18፤ ኤፌሶን 1:20-22