በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 36

ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው? የሚኖሩትስ የት ነው?

ከሞት የሚነሱት እነማን ናቸው? የሚኖሩትስ የት ነው?

ባለፉት ሁለት ምዕራፎች ላይ ስንት ሰዎች ከሞት እንደተነሱ አንብበን ነበር?— አዎ፣ አምስት ሰዎች ከሞት እንደተነሱ አንብበናል። ከአምስቱ ውስጥ ስንቶቹ ልጆች ናቸው?— ሦስቱ ልጆች ናቸው። አራተኛው ደግሞ ወጣት ነበር። ይህ ምን የሚያሳይ ይመስልሃል?—

አምላክ ልጆችንና ወጣቶችን እንደሚወድ ያሳያል። ይሁን እንጂ አምላክ ሌሎች ብዙ ሰዎችንም ያስነሳል። አምላክ የሚያስነሳው ጥሩ ነገር የሠሩትን ሰዎች ብቻ ይሆን?— እንዲህ ይመስለን ይሆናል። ሆኖም ብዙ ሰዎች ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ልጁ እውነተኛውን ነገር ተምረው አያውቁም። በመሆኑም መጥፎ ነገር ስለተማሩ መጥፎ ነገር ሠርተዋል። ታዲያ ይሖዋ እንዲህ ዓይነቶቹን ሰዎች ከሞት የሚያስነሳቸው ይመስልሃል?—

መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ” ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) ጻድቃን ያልነበሩ ወይም ትክክል የሆነውን ነገር ያላደረጉ ሰዎች ከሞት የሚነሱት ለምንድን ነው?— ስለ ይሖዋ አምላክም ሆነ ይሖዋ ሰዎች ምን እንዲያደርጉ እንደሚፈልግ የመማር አጋጣሚ ስላላገኙ ነው።

አምላክ ትክክል የሆነውን ነገር ያላደረጉ አንዳንድ ሰዎችን ከሞት የሚያስነሳቸው ለምንድን ነው?

ሰዎች ከሞት የሚነሱት መቼ ይመስልሃል?— ኢየሱስ አልዓዛር በሞተ ጊዜ ለእህቱ ለማርታ “ወንድምሽ ይነሳል” በማለት የሰጣትን ተስፋ አስታውስ። ማርታ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” በማለት መልስ ሰጥታ ነበር። (ዮሐንስ 11:23, 24) ማርታ አልዓዛር “በመጨረሻው ቀን” ይነሳል ስትል ምን ማለቷ ነበር?—

ኢየሱስ ለሰውየው የነገረው ስለ የትኛው ገነት ነው?

ማርታ ‘በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ይወጣሉ’ በማለት ኢየሱስ የሰጠውን ተስፋ ሰምታ ነበር። (ዮሐንስ 5:28, 29) ስለዚህ ‘የመጨረሻው ቀን’ የተባለው አምላክ የሚያስባቸው ሙታን በሙሉ እንደገና ሕያው የሚሆኑበት ጊዜ ነው። ይህ የመጨረሻ ቀን የ24 ሰዓት ርዝመት ያለው ቀን አይደለም። አንድ ሺህ ዓመት ርዝማኔ ያለው ጊዜ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በዚህ ቀን ‘አምላክ በዓለም ሕዝቦች ሁሉ ላይ ይፈርዳል።’ ፍርድ ከሚሰጣቸው ሰዎች መካከል ደግሞ ከሞት የሚነሱት ሰዎች ይገኙበታል።—የሐዋርያት ሥራ 17:31፤ 2 ጴጥሮስ 3:8

ይህ ቀን ምን ያህል አስደሳች ጊዜ እንደሚሆን እስቲ አስበው! የሺህ ዓመት ርዝማኔ ባለው በዚህ ቀን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች እንደገና ሕያው ይሆናሉ። ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ከሞት ተነስተው የሚኖሩበትን ቦታ ገነት ብሎ ጠርቶታል። እስቲ ገነት የት እንደሚሆንና ምን እንደሚመስል እንመልከት።

ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ከመሞቱ ከሦስት ሰዓት በፊት ከጎኑ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ለነበረ ሰው ስለ ገነት ተናግሯል። ሰውየው በሠራው ወንጀል ምክንያት ሞት ተፈርዶበት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ወንጀለኛ ኢየሱስን ሲመለከትና ስለ እሱ የተባለውን ነገር ሲሰማ በኢየሱስ ማመን ጀመረ። ስለዚህ ወንጀለኛው ኢየሱስን “ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” አለው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት መልስ ሰጠው።—ሉቃስ 23:42, 43

ስለ ገነት ስናነብ በዓይነ ሕሊናችን ምን ሊታየን ይገባል?

ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ገነት የት ነው?— እስቲ ለማሰብ ሞክር። የቀድሞው ገነት የት ነበር?— አምላክ ለመጀመሪያው ሰው ለአዳምና ለሚስቱ እዚችው ምድር ላይ የሚኖሩበት ገነት ሰጥቷቸው እንደነበረ አስታውስ። ይህ ገነት የኤደን የአትክልት ቦታ ተብሎ ይጠራል። በገነት ውስጥ እንስሳት የነበሩ ቢሆንም በማንም ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አልነበሩም። በተጨማሪም ብዙ ዓይነት ጣፋጭ ፍሬዎች የሚያፈሩ ዛፎች እንዲሁም አንድ ትልቅ ወንዝ ነበር። ኤደን ገነት ለመኖር ምቹ የሆነ ጥሩ ቦታ ነበር!—ዘፍጥረት 2:8-10

ስለዚህ ይህ ወንጀለኛ በገነት እንደሚሆን ስለተሰጠው ተስፋ ስናነብ በዓይነ ሕሊናችን ይህች ምድር ውብ ወደሆነ መኖሪያነት ተለውጣ ልትታየን ይገባል። ኢየሱስ ድሮ ወንጀለኛ ከነበረው ከዚያ ሰው ጋር እዚችው ምድር ላይ በገነት ይኖራል ማለት ነው?— እንደዚያ ማለት አይደለም። ኢየሱስ እዚች ምድር ላይ የማይኖረው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ገነት የምትሆነውን ምድር የሚገዛው ሰማይ ላይ ሆኖ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ሰውየውን ከሙታን ስለሚያስነሳውና የሚያስፈልጉትን ነገሮች ስለሚያሟላለት ከእሱ ጋር እንደሆነ ያህል ይቆጠራል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ቀደም ሲል ወንጀለኛ የነበረን ሰው በገነት እንዲኖር የሚፈቅድለት ለምንድን ነው?— እስቲ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንሞክር።

ወንጀለኛው ከኢየሱስ ጋር ከመነጋገሩ በፊት ስለ አምላክ ዓላማዎች ያውቅ ነበር?— በፍጹም፣ አያውቅም ነበር። መጥፎ ነገር የሠራው ስለ አምላክ እውነተኛውን ነገር ስላላወቀ ነበር። በገነት ውስጥ ግን ስለ አምላክ ዓላማዎች ይማራል። ከዚያም የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም በእርግጥ ለእሱ ፍቅር እንዳለው ማረጋገጥ የሚችልበት አጋጣሚ ያገኛል።

ትንሣኤ የሚያገኙ ሁሉ በምድር ላይ በገነት ይኖራሉ ማለት ነው?— እንደዚያ ማለት አይደለም። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— አንዳንዶች ከሞት የሚነሱት ከኢየሱስ ጋር በሰማይ ለመኖር ስለሆነ ነው። እነዚህ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ነገሥታት ሆነው ገነት የምትሆነውን ምድር ይገዛሉ። ይህን ማወቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ሐዋርያቱን ‘በአባቴ ቤት በሰማይ ብዙ መኖሪያ አለ፤ እኔም ለእናንተ ቦታ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁ’ ብሏቸው ነበር። ከዚያም ኢየሱስ “እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል።—ዮሐንስ 14:2, 3

ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የሄደው ወዴት ነው?— አዎ፣ ከአባቱ ጋር ለመሆን ወደ ሰማይ ሄዷል። (ዮሐንስ 17:4, 5) ስለዚህ ኢየሱስ ሐዋርያቱንና ሌሎች ተከታዮቹን በሰማይ ከእሱ ጋር እንዲሆኑ ከሞት እንደሚያስነሳቸው ቃል ገብቶላቸዋል። እዚያ ሄደው ከኢየሱስ ጋር ምን ይሠራሉ?— መጽሐፍ ቅዱስ “በመጀመሪያው ትንሣኤ” ከሞት የሚነሱት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሰማይ እንደሚኖሩና “ከእሱ ጋር ነገሥታት ሆነው ለአንድ ሺህ ዓመት” በምድር ላይ እንደሚገዙ ይናገራል።—ራእይ 5:10፤ 20:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:12

“በመጀመሪያው ትንሣኤ” የሚነሱትና ከኢየሱስ ጋር ነገሥታት ሆነው የሚገዙት ቁጥራቸው ስንት ነው?— ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “አንተ ትንሽ መንጋ፣ አባታችሁ መንግሥቱን ሊሰጣችሁ ስለፈቀደ አትፍሩ” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 12:32) በሰማያዊው መንግሥት ከኢየሱስ ጋር ለመሆን ከሞት የሚነሱት የዚህ “ትንሽ መንጋ” አባላት ቁጥራቸው የተወሰነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ የሚሄዱት “አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ” እንደሆኑ ይገልጻል።—ራእይ 14:1, 3

ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች የሚኖሩት የት ነው? የሚሠሩትስ ነገር ምንድን ነው?

በምድር ላይ በገነት የሚኖሩት ሰዎች ስንት ናቸው?— መጽሐፍ ቅዱስ ቁጥራቸውን አይናገርም። ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት እያሉ አምላክ ልጆች እንዲወልዱና ምድርን እንዲሞሉ ነግሯቸው ነበር። እርግጥ ነው፣ እነሱ ይህን ሳያደርጉ ቀርተዋል። ይሁን እንጂ አምላክ ምድር በጥሩ ሰዎች እንድትሞላ ያወጣው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል።—ዘፍጥረት 1:28፤ ኢሳይያስ 45:18፤ 55:11

በገነት መኖር ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን እስቲ አስበው! መላዋ ምድር እንደ መናፈሻ ትሆናለች። ይህች ገነት ወፎችና እንስሳት የሞሉባት እንዲሁም በብዙ ዓይነት ዛፎችና አበቦች የተዋበች ትሆናለች። በገነት ውስጥ ታሞ የሚሠቃይ ወይም የሚሞት ሰው አይኖርም። ሁሉም ሰው እርስ በርሱ የሚዋደድ ይሆናል። በገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር ከፈለግን ለዚያ ጊዜ መዘጋጀት ያለብን አሁን ነው።

አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማ ይበልጥ ለማወቅ ምሳሌ 2:21, 22፤ መክብብ 1:4፤ ኢሳይያስ 2:4፤ 11:6-9፤ 35:5, 6 እና 65:21-24⁠ን አንብቡ።