በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 45

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? እንደምንፈልገው የምናሳየውስ እንዴት ነው?

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? እንደምንፈልገው የምናሳየውስ እንዴት ነው?

ኢየሱስ ለተከታዮቹ ያስተማረውን ጸሎት ታውቀዋለህ?— የማታውቀው ከሆነ ማቴዎስ 6:9-13ን አውጥተን አብረን ልናነበው እንችላለን። አብዛኞቹ ሰዎች አባታችን ሆይ ብለው በሚጠሩት በዚህ ጸሎት ውስጥ “መንግሥትህ ይምጣ” የሚሉት ቃላት ይገኙበታል። የአምላክ መንግሥት ምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

ንጉሥ አንድን አገር ወይም የግዛት ክልል የሚያስተዳድር ገዥ ነው። የንጉሡ የአገዛዝ ሥርዓት ደግሞ መንግሥት ተብሎ ይጠራል። በአንዳንድ አገሮች መንግሥቱን የሚመራው ሰው ፕሬዚዳንት ተብሎ ይጠራል። የአምላክ መንግሥት ገዥስ ምን ተብሎ ይጠራል?— ንጉሥተብሎ ይጠራል።

ይሖዋ አምላክ የመንግሥቱ ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው ማንን እንደሆነ ታውቃለህ?— ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ኢየሱስ ሰዎች ከሚመርጡት ከማንኛውም ገዥ የተሻለ የሆነው ለምንድን ነው?— ምክንያቱም ኢየሱስ አባቱን ይሖዋን በጣም ይወዳል። በመሆኑም ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ነገር ያደርጋል።

ኢየሱስ በቤተልሔም ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ መወለድ ትንቢት ከመናገሩም በላይ በአምላክ የተመረጠ ገዥ እንደሚሆን ገልጾ ነበር። ይህን በተመለከተ ኢሳይያስ 9:6, 7 ላይ የተገለጸውን እናንብብ። እንዲህ ይላል:- “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም . . . የሰላም ልዑል ይባላል። ለመንግሥቱ ስፋት፣ ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ የለውም።”

እዚህ ላይ የአምላክ መንግሥት ገዥ “ልዑል” የተባለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ልዑል የሚለው ቃል የንጉሥ ልጅን የሚያመለክት መጠሪያ ነው። ኢየሱስ ደግሞ የታላቁ ንጉሥ የይሖዋ ልጅ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ኢየሱስን ለሺህ ዓመት ምድርን በሚገዛው መንግሥቱ ላይ ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። (ራእይ 20:6) ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ “‘መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ’ እያለ ይሰብክ ጀመር።”—ማቴዎስ 4:17

ኢየሱስ መንግሥቱ እንደቀረበ የተናገረው ለምን ይመስልሃል?— ምክንያቱም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በሰማይ መግዛት የሚጀምረው ንጉሥ እዚያው ከእነሱ ጋር ስለነበረ ነው! ኢየሱስ ለሰዎች “የአምላክ መንግሥት በመካከላችሁ ነው” ብሎ የተናገረው ለዚህ ነው። (ሉቃስ 17:21) ይሖዋ የሾመው ንጉሥ አጠገብህ ቢሆንና ልትዳስሰው ብትችል ደስ አይልህም ነበር?—

እስቲ ንገረኝ፣ ኢየሱስ ወደዚህ ምድር የመጣው ምን አስፈላጊ ሥራ ለመሥራት ነበር?— ኢየሱስ “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” በማለት ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ ብቻውን ሊሠራው እንደማይችል ያውቅ ነበር። ታዲያ ምን ያደረገ ይመስልሃል?—

ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው የትኛውን ሥራ ለመሥራት ነው?

ኢየሱስ ሰዎችን ይዞ በመሄድ የስብከቱን ሥራ እንዴት እንደሚሠሩ አሳያቸው። በመጀመሪያ ያሠለጠነው ሐዋርያት እንዲሆኑ የመረጣቸውን 12 ሰዎች ነው። (ማቴዎስ 10:5, 7) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን ሥራ እንዲሠሩ ያሠለጠነው ሐዋርያቱን ብቻ ነበር? አልነበረም፤ ኢየሱስ ሌሎች ብዙ ሰዎችንም እንዲሰብኩ እንዳሠለጠነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ከጊዜ በኋላ እሱ ሊሄድ ወዳሰበባቸው ቦታዎች ሁለት ሁለት እያደረገ 70 ደቀ መዛሙርትን ልኮ ነበር። እነሱስ ለሰዎች ያስተማሩት ምን ነበር?— ኢየሱስ “‘የአምላክ መንግሥት ወደ እናንተ ቀርቧል’ ብላችሁም ንገሯቸው” በማለት ምን ማስተማር እንዳለባቸው ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 10:9) በዚህ መንገድ በዚያን ዘመን የነበሩት ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ማወቅ ችለው ነበር።

በጥንት ዘመን በእስራኤል ውስጥ አዳዲስ ነገሥታት ለሕዝቡ ለመታየት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጠው ወደ ከተማ ይገቡ ነበር። ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እንዲህ አድርጎ ነበር። ኢየሱስ ይህን ያደረገው የአምላክ መንግሥት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ ስለተቃረበ ነው። ነገር ግን ሕዝቡ ንጉሣቸው እንዲሆን ይፈልጉ ነበር?—

በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ሲመጣ አብዛኞቹ ሰዎች ከፊት ከፊት እየሄዱ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ ያነጥፉ ጀመር። ሌሎች ደግሞ የዛፍ ቅርንጫፎችን እየቆረጡ መንገድ ላይ ያደርጉ ጀመር። ይህን በማድረግ ኢየሱስ ንጉሣቸው እንዲሆን እንደሚፈልጉ አሳዩ። እንዲሁም “በይሖዋ ስም ንጉሥ ሆኖ የሚመጣ የተባረከ ነው!” እያሉ ጮኹ። ይሁን እንጂ የተደሰተው ሁሉም ሰው አልነበረም። እንዲያውም አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስን ‘ደቀ መዛሙርትህ ዝም እንዲሉ ንገራቸው’ እስከ ማለት ደርሰው ነበር።—ሉቃስ 19:28-40

ኢየሱስ ንጉሣቸው እንዲሆን ፈልገው የነበሩት ሰዎች በኋላ ሐሳባቸውን የለወጡት ለምን ነበር?

ከአምስት ቀናት በኋላ ኢየሱስ ተይዞ ወደ ቤተ መንግሥት ተወሰደና በገዥው በጳንጥዮስ ጲላጦስ ፊት ቀረበ። የኢየሱስ ጠላቶች እሱ ንጉሥ ነኝ እንደሚልና የሮማን መንግሥት እንደሚቃወም ተናገሩ። ስለዚህ ጲላጦስ ኢየሱስን ስለዚህ ጉዳይ ጠየቀው። ኢየሱስ የመንግሥትን ሥልጣን ለመውሰድ ሙከራ እያደረገ እንዳልሆነ ተናገረ። ጲላጦስን “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” አለው።—ዮሐንስ 18:36

ከዚያም ጲላጦስ ወደ ውጪ ወጣና በኢየሱስ ላይ ምንም ጥፋት እንዳላገኘበት ለሕዝቡ ነገራቸው። በዚህ ወቅት ግን ሕዝቡ ኢየሱስ ንጉሣቸው እንዲሆን አልፈለጉም ነበር። በነፃ እንዲለቀቅም አልፈለጉም። (ዮሐንስ 18:37-40) ጲላጦስ እንደገና ኢየሱስን ካነጋገረው በኋላ ምንም ጥፋት እንዳልሠራ እርግጠኛ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስን ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ውጪ ካወጣው በኋላ “እነሆ፣ ንጉሣችሁ!” አላቸው። ሕዝቡ ግን “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ።

ጲላጦስ “ንጉሣችሁን ልስቀለው?” ብሎ ጠየቃቸው። የካህናት አለቆቹ “ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱ። አይገርምም? እነዚህ ክፉ ካህናት ሕዝቡ ኢየሱስን እንዲቃወም አነሳስተው ነበር!—ዮሐንስ 19:1-16

በዛሬው ጊዜም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ኢየሱስ ንጉሣቸው እንዲሆን አይፈልጉም። በአምላክ እንደሚያምኑ ይናገሩ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ አምላክም ሆነ ክርስቶስ ምንም ነገር እንዲያዟቸው አይፈልጉም። እነሱ የሚፈልጉት በዚህ ምድር ላይ ያሉትን የራሳቸውን መንግሥታት ብቻ ነው።

እኛስ? ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት ስለሚያከናውናቸው አስደናቂ ነገሮች መማራችን ስለ አምላክ ምን እንዲሰማን ያደርጋል?— እንድንወደው ያደርገናል፣ አይደል?— ታዲያ አምላክን እንደምንወደውና በእሱ መንግሥት መገዛት እንደምንፈልግ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?—

ኢየሱስ የተጠመቀው ለምን ነበር? አምላክ በኢየሱስ መጠመቅ እንደተደሰተ ያሳየው እንዴት ነው?

ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ነው። ኢየሱስ ይሖዋን እንደሚወደው ለማሳየት ምን አድርጎ ነበር?— ‘ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን አደርጋለሁ’ በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:29) አዎ፣ ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ‘የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ’ እንዲሁም ‘ሥራውን ለመፈጸም’ ነው። (ዕብራውያን 10:7፤ ዮሐንስ 4:34) ኢየሱስ የስብከት ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ምን እንዳደረገ ተመልከት።

ኢየሱስ መጥምቁ ዮሐንስ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄደ። ሁለቱም ወደ ወንዙ ከገቡ በኋላ ዮሐንስ ኢየሱስን ውኃው ውስጥ ሙሉ በሙሉ አጥልቆ አወጣው። ዮሐንስ ኢየሱስን ያጠመቀው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?—

ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች መናገር የምንችለው የት ነው?

ኢየሱስ እንዲያጠምቀው ስለጠየቀው ነው። ይሁን እንጂ አምላክ፣ ኢየሱስ እንዲጠመቅ ይፈልግ እንደነበረ እንዴት እናውቃለን?— ይህን የምናውቀው ኢየሱስ ከውኃው ከወጣ በኋላ አምላክ ከሰማይ “አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” ብሎ ሲናገር ስለሰማ ነው። እንዲያውም አምላክ ቅዱስ መንፈሱ በርግብ መልክ በኢየሱስ ላይ እንዲወርድ አድርጓል። ስለዚህ ኢየሱስ በመጠመቁ በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ማለትም ለዘላለም ይሖዋን ለማገልገል እንደሚፈልግ አሳይቷል።—ማርቆስ 1:9-11

አሁን አንተ ገና ልጅ ነህ። ስታድግ ግን ምን ለማድረግ ታስባለህ?— አንተም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ትጠመቃለህ?— መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ‘የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችኋል’ በማለት ስለሚናገር እሱን መምሰል ይኖርብሃል። (1 ጴጥሮስ 2:21) በምትጠመቅበት ጊዜ በእርግጥ በአምላክ መንግሥት መገዛት እንደምትፈልግ ታሳያለህ። ይሁን እንጂ መጠመቅ ብቻውን በቂ አይደለም።

ኢየሱስ ያስተማረውን ነገር በሙሉ ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልገናል። ኢየሱስ ‘የዓለም ክፍል መሆን’ እንደሌለብን ተናግሯል። በዓለማዊ ጉዳዮች የምንካፈል ከሆነ እሱን እየታዘዝነው ነው ሊባል ይችላል? ኢየሱስና ሐዋርያቱ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች አይካፈሉም ነበር። (ዮሐንስ 17:14) ከዚህ ይልቅ ምን ያደርጉ ነበር?— ለሌሎች ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ይናገሩ ነበር። በሕይወታቸው ውስጥ ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ሥራ ይህ ነበር። እኛም ይህን ሥራ መሥራት እንችላለን?— አዎ፣ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ የምንጸልየው ከልባችን ከሆነ እኛም ይህን ሥራ እንሠራለን።

የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ እንደምንፈልግ ለማሳየት ምን ማድረግ እንደምንችል የሚገልጹትን የሚከተሉትን ጥቅሶች እባካችሁ አንብቡ:- ማቴዎስ 6:24-33፤ 24:14፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17፤ 5:3