በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 47

አርማጌዶን እንደቀረበ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

አርማጌዶን እንደቀረበ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ምልክት ምን እንደሆነ ታውቃለህ፣ አይደል?— ምዕራፍ 46 ላይ አምላክ ዓለምን ዳግመኛ በውኃ እንደማያጠፋ ለማሳየት ስለሰጠው ምልክት አንብበን ነበር። በተጨማሪም ሐዋርያት ኢየሱስ መመለሱንና የዓለም ፍጻሜ መቅረቡን ማወቅ የሚችሉበትን ምልክት እንዲሰጣቸው ጠይቀውት ነበር።—ማቴዎስ 24:3

ኢየሱስ በሰማይ ስለሚሆንና በዓይን ሊታይ ስለማይችል ሰዎች መግዛት መጀመሩን እንዲያውቁ እነሱ ሊያዩት የሚችሉት ምልክት ያስፈልግ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እዚህ ምድር ላይ በትኩረት ሊከታተሏቸው የሚገቡ ነገሮችን ነገራቸው። እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ እሱ እንደተመለሰና በሰማይ ንጉሥ ሆኖ መግዛት እንደጀመረ ማወቅ ይቻላል።

ኢየሱስ ነቅቶ የመጠበቅን አስፈላጊነት ለደቀ መዛሙርቱ ለማስተማር ሲል እንዲህ አላቸው:- “የበለስ ዛፍንና ሌሎች ዛፎችን ሁሉ ተመልከቱ፤ ዛፎቹ እንዳቆጠቆጡ ስታዩ በዚያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።” በጋ እንደቀረበ ማወቅ እንደምትችል ሁሉ ኢየሱስ የተናገራቸው ነገሮች ሲፈጸሙ ስታይም አርማጌዶን መቅረቡን ማወቅ ትችላለህ።—ሉቃስ 21:29, 30

በዚህና በቀጣዩ ገጽ ላይ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ ያመለክታሉ ብሎ የተናገራቸው ምልክቶች በሥዕል መልክ ቀርበዋል። ምዕራፍ 46 ላይ እንዳነበብነው እነዚህ ነገሮች በሙሉ ሲፈጸሙ በክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት የምድር መንግሥታትን በሙሉ ይደመስሳል።

ኢየሱስ ስለ በለስ ዛፍ የተናገረው ምን ለማስተማር ፈልጎ ነው?

ስለዚህ በእነዚህ ሁለት ገጾች ላይ የቀረቡትን ሥዕሎች በደንብ ተመልከታቸውና እንወያይባቸው። በእነዚህ ሥዕሎች ላይ የምታየውን ነገር ማቴዎስ 24:6-14 እና ሉቃስ 21:9-11 ላይ ማንበብ ትችላለህ። በተጨማሪም በእያንዳንዱ ሥዕል ላይ የተጻፈውን ቁጥር ልብ በል። ይኸው ቁጥር ሥዕሉን በሚያብራራው አንቀጽ መጀመሪያ ላይ ይገኛል። እስቲ አሁን፣ ኢየሱስ በሰጠው ምልክት ላይ የጠቀሳቸው አብዛኞቹ ነገሮች በዛሬው ጊዜ እየተፈጸሙ መሆን አለመሆኑን እንመልከት።

(1) ኢየሱስ “ጦርነትና የጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ፤ . . . ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል” ብሏል። ስለ ጦርነት ሲነገር ሰምተሃል?— የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የተካሄደው ከ1914 እስከ 1918 በነበረው ጊዜ ውስጥ ነው። ከዚያም ከ1939 እስከ 1945 ድረስ ባለው ጊዜ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተካሄደ። ከዚያ በፊት የዓለም ጦርነት ተካሂዶ አያውቅም ነበር! በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ጦርነቶች ይካሄዳሉ። በየቀኑ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ስለ ጦርነት እንሰማለን፤ እንዲሁም ጋዜጣ ላይ እናነባለን።

(2) በተጨማሪም ኢየሱስ “በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረት . . . ይከሰታል” ብሏል። እንደምታውቀው በቂ ምግብ የሚያገኘው ሁሉም ሰው አይደለም። በየቀኑ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በቂ ምግብ ባለማግኘታቸው ምክንያት ይሞታሉ።

(3) ኢየሱስ አክሎም “በተለያየ ስፍራም ቸነፈር . . . ይሆናል” ብሏል። ቸነፈር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ቸነፈር ብዙ ሰዎችን የሚገድል በሽታ ወይም ሕመም ነው። ስፓኒሽ ፍሉ ወይም የኅዳር በሽታ ተብሎ የሚጠራ አንድ ከባድ ቸነፈር ከአንድ ዓመት ብዙም በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ 20 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎችን ገድሏል። በዘመናችንም በኤድስ ምክንያት ከዚያ የሚበልጡ ሰዎች እንደሚሞቱ ይገመታል። ከዚህም በላይ በካንሰር፣ በልብ ሕመምና በሌሎች በሽታዎች በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይሞታሉ።

(4) ኢየሱስ “በተለያየ ስፍራ . . . የምድር ነውጥ ይከሰታል” ብሎ በመናገር የምልክቱን ሌላ ገጽታ ጠቅሷል። የምድር ነውጥ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— የምድር ነውጥ የቆምክበት መሬት እንዲንቀጠቀጥ ያደርጋል። የምድር ነውጥ በሚከሰትበት ጊዜ ቤቶች ይፈራርሳሉ፤ ብዙውን ጊዜም ሰዎች ይሞታሉ። ከ1914 ወዲህ በየዓመቱ ብዙ የምድር ነውጦች ተከስተዋል። ስለ ምድር ነውጥ ሰምተህ ታውቃለህ?—

(5) ኢየሱስ ሌላውን የምልክቱን ክፍል ሲጠቅስ ‘ክፋት እየበዛ እንደሚሄድ’ ተናግሯል። ሌብነትና ዓመፅ የበዛው ለዚህ ነው። የትም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ሌባ ቤታችንን ሰብሮ ሊገባ ይችላል ብለው ይፈራሉ። በመላው ዓለም የአሁኑን ጊዜ ያህል ወንጀልና ዓመፅ የበዛበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም።

(6) ኢየሱስ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” ብሎ በመናገር በጣም አስፈላጊ የሆነውን የምልክቱን ክፍል ጠቅሷል። (ማቴዎስ 24:14) ይህን “ምሥራች” የምታምንበት ከሆነ ስለዚህ ምሥራች ለሌሎች መናገር ይኖርብሃል። በዚህ መንገድ አንተም ይህን የምልክቱን ክፍል በመፈጸሙ ተግባር ልትካፈል ትችላለህ።

አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ የተነበያቸው ነገሮች ምንጊዜም ሲፈጸሙ የኖሩ ናቸው ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም እነዚህ ነገሮች በሙሉ በብዙ አገሮች ውስጥ እንዲሁም በተመሳሳይ ጊዜ የተፈጸሙበት ወቅት ኖሮ አያውቅም። ታዲያ ምልክቱ ምን ትርጉም እንዳለው አሁን ገባህ?— እነዚህ ነገሮች በሙሉ ሲፈጸሙ ከተመለከትን ይህ ክፉ ዓለም በአምላክ አዲስ ዓለም የሚተካበት ጊዜ ተቃርቧል ማለት ነው።

ኢየሱስ ይህን ምልክት በሰጠ ጊዜ በዓመት ውስጥ ስለሚከሰት አንድ ልዩ ወቅትም ተናግሮ ነበር። “ሽሽታችሁ በክረምት . . . እንዳይሆን ዘወትር ጸልዩ” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 24:20) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ይመስልሃል?—

አንድ ሰው ለጉዞ አስቸጋሪ ብሎም አደገኛ በሆነው የክረምት ወቅት ከአደጋ ለማምለጥ ቢሞክር ምን ሊያጋጥመው ይችላል?— ማምለጥ ቢችል እንኳን ከባድ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል። አንድ ሰው ሌሎች ነገሮችን በመሥራት ተጠምዶ ጉዞውን ቀደም ብሎ ባለመጀመሩ ምክንያት በክረምት ወቅት በሚከሰት ኃይለኛ ዝናብና ነፋስ ለአደጋ ተጋልጦ ቢሞት አያሳዝንም?—

ኢየሱስ በክረምት ወራት ለመሸሽ ስለመሞከር የተናገረው ምን ለማስተማር ፈልጎ ነው?

ኢየሱስ የክረምት ወቅት ሳይመጣ መሸሽ እንዳለባቸው ሲናገር ምን ለማለት እንደፈለገ ገብቶሃል?— ኢየሱስ ሊነግረን የፈለገው አርማጌዶን መቅረቡን እስካወቅን ድረስ አምላክን እንደምንወደው ለማሳየት እርምጃ ከመውሰድ መዘግየት እንደሌለብን ነው፤ አምላክን እንደምንወደው የምናሳየው ደግሞ እሱን በማገልገል ነው። እርምጃ ለመውሰድ ከዘገየን ግን ጊዜ ሊያልፍብን ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ የጥፋት ውኃ በመጣበት ዘመን ኖኅ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ቢሰሙም ወደ መርከቡ ሳይገቡ እንደቀሩት ሰዎች ልንሆን እንችላለን።

ቀጥሎ ደግሞ ታላቁ የአርማጌዶን ጦርነት ካለፈ በኋላ ስለሚሆነው ነገር እንወያያለን። አምላክ እሱን ለምንወደውና ለምናገለግለው ሰዎች በሙሉ ምን እንዳዘጋጀ እንማራለን።

የሚከተሉት ተጨማሪ ጥቅሶች አርማጌዶን እንደቀረበ ያሳያሉ:- 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ 2 ጴጥሮስ 3:3, 4