በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ዓላማ ይህ ነበር?

የአምላክ ዓላማ ይህ ነበር?

የትኛውንም ጋዜጣ ብታነብ፣ ቴሌቪዥን ብትመለከት ወይም ሬዲዮ ብትሰማ የምታነበውም ሆነ የምታየው አሊያም የምትሰማው አብዛኛው ዘገባ ከወንጀል፣ ከጦርነትና ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ ነው! አንተ ራስህ ያሉብህንም ችግሮች እስቲ አስብ። ምናልባት በሕመም እየተሠቃየህ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ በጣም የምትወደውን ሰው በሞት በማጣትህ ከባድ ሐዘን ላይ ወድቀህ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ‘በመከራ ተዘፍቄአለሁ’ እንዳለው እንደ ጻድቁ ሰው እንደ ኢዮብ ዓይነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል።—ኢዮብ 10:15

እስቲ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:-

  • አምላክ ለእኔም ሆነ ለቀረው የሰው ዘር ያለው ዓላማ ይህ ነው?

  • ችግሮቼን ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ላገኝ የምችለው ከየት ነው?

  • በምድር ላይ ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሚከተሉትን ለውጦች በምድር ላይ እንደሚያመጣ ይናገራል።

  • “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም።”—ራእይ 21:4

  • “አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል።”—ኢሳይያስ 35:6

  • “የዕውር ዐይኖች ይገለጣሉ።”—ኢሳይያስ 35:5

  • “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ . . . ይወጣሉ።”—ዮሐንስ 5:28, 29

  • “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”—ኢሳይያስ 33:24

  • ‘በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፈረፋል።’—መዝሙር 72:16

 መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ትምህርት ተጠቀም

ቀደም ባሉት ገጾች ላይ የተገለጸው ሐሳብ እንዲሁ ምኞት ካልሆነ በስተቀር ሊፈጸም የማይችል ነገር ነው ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። አምላክ እነዚህን ነገሮች እንደሚፈጽም ቃል የገባ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ አምላክ እነዚህን ተስፋዎች እንዴት እንደሚፈጽም ይገልጽልናል።

ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህም ሌላ የሚያስገኘው ጥቅም አለ። በአሁኑ ጊዜም እንኳ አስደሳች የሆነ ሕይወት መኖር የምትችልበትን መንገድ ያስተምርሃል። እስቲ የሚያስጨንቁህንና የሚያሳስቡህን ነገሮች ለጥቂት ደቂቃዎች አስብ። እነዚህ ችግሮች ከገንዘብ፣ ከቤተሰብ፣ ከጤና ወይም በጣም የምትወደውን ሰው በሞት ከማጣት ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ እነዚህን ችግሮች መወጣት እንድትችል የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ እንደሚከተሉት ላሉት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት እፎይታ ሊያስገኝልህ ይችላል:-

  • መከራና ሥቃይ የሚደርስብን ለምንድን ነው?

  • ኑሮ የሚያስከትልብንን ጭንቀት መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?

  • የቤተሰባችንን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

  • ስንሞት ምን እንሆናለን?

  • በሞት ያጣናቸውን ሰዎች ዳግመኛ እናገኛቸው ይሆን?

  • አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ቃል የገባቸውን ነገሮች እንደሚፈጽም እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?

 ይህን መጽሐፍ እያነበብክ መሆኑ በራሱ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ትምህርት ማወቅ እንደምትፈልግ የሚያሳይ ነው። በዚህ ረገድ ይህ መጽሐፍ በእጅጉ ይረዳሃል። አንቀጾቹ በገጹ ግርጌ ላይ ጥያቄዎች እንዳሏቸው ልብ በል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መንገድ በጥያቄና መልስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በማጥናታቸው በጣም ተጠቅመዋል። አንተም እንደምትጠቀም ተስፋ እናደርጋለን። ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መማር የምትችልበትን ይህን አስደሳች አጋጣሚ ለመጠቀም በምታደርገው ጥረት የአምላክ በረከት እንዳይለይህ እንመኛለን!