በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ አንድ

አምላክን በተመለከተ ትክክለኛው ትምህርት የቱ ነው?

አምላክን በተመለከተ ትክክለኛው ትምህርት የቱ ነው?
  •  አምላክ በእርግጥ ስለ አንተ ያስባል?

  • አምላክ ምን ዓይነት አምላክ ነው? የራሱ የሆነ ስም አለው?

  • ወደ አምላክ መቅረብ ይቻል ይሆን?

1, 2. ብዙውን ጊዜ ጥያቄ መጠየቅ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

ሕፃናት ጥያቄ የሚጠይቁበትን መንገድ አስተውለህ ታውቃለህ? ብዙዎቹ ጥያቄ መጠየቅ የሚጀምሩት ገና አፋቸውን እንደፈቱ ነው። ለማወቅ ካላቸው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ዓይን ዓይንህን እያዩ ‘ሰማዩ መጨረሻው የት ጋር ነው? ኮከቦች የሚያበሩት ለምንድን ነው? ወፎች መብረር የቻሉት እንዴት ነው?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን ይጠይቁሃል። መልስ ለመስጠት የተቻለህን ያህል ጥረት ታደርግ ይሆናል፤ ሆኖም ይህን ማድረጉ ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። የተሻለ ነው ብለህ የምታስበው መልስም እንኳ ‘ለምን?’ የሚል ሌላ ጥያቄ ሊያስከትልብህ ይችላል።

2 ይሁንና ጥያቄ የሚያነሱት ሕፃናት ብቻ አይደሉም። ካደግንም በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎች እናነሳለን። የምንሄድበትን አቅጣጫ ለማወቅ፣ ልንርቃቸው የሚገቡ አደገኛ ሁኔታዎችን ለመለየት ወይም ደግሞ የማወቅ ፍላጎታችንን ለማርካት ስንል እንጠይቃለን። ሆኖም ብዙ ሰዎች ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎችን መጠየቅ የተዉ ይመስላል። አሊያም ደግሞ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ አይታይም።

3. ብዙዎች ይበልጥ አሳሳቢ ለሆኑ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸውን የሚያቆሙት ለምንድን ነው?

 3 በዚህ መጽሐፍ ሽፋንበመቅድሙ ወይም  በዚህ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ የቀረቡትን ጥያቄዎች ለማሰብ ሞክር። እነዚህ ልታነሳቸው ከምትችላቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው። ሆኖም ብዙዎቹ ሰዎች መልሶቹን ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት አቁመዋል። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል? አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸው መልሶች ለመረዳት አስቸጋሪ እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። ሌሎቹ ደግሞ ጥያቄ መጠየቅ ለኅፍረት ሊዳርገኝ ይችላል ብለው ይሰጋሉ። እነዚህን ጥያቄዎች ለሃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች መተዉ ይመረጣል ብለው የሚያስቡ ሰዎችም አሉ። አንተስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይሰማሃል?

4, 5. በሕይወት ውስጥ ልናነሳቸው ከምንችላቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? መልሳቸውን ለማወቅ መጣር ያለብንስ ለምንድን ነው?

4 በሕይወት ውስጥ ለሚነሱ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። አንዳንድ ጊዜ ‘የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? መወለድ፣ ማደግ፣ ማርጀትና መሞት ብቻ ነው? አምላክ ምን ዓይነት አምላክ ነው?’ እያልክ ማሰብህ አይቀርም። እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ከመሆኑም በላይ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢና አስተማማኝ መልስ እስክታገኝ ድረስ ጥረት ማድረግህን ማቆም የለብህም። ዝነኛው አስተማሪ ኢየሱስ ክርስቶስ “ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል” ሲል ተናግሯል።—ማቴዎስ 7:7

5 በጣም አስፈላጊ ለሆኑት ጥያቄዎች መልስ ‘መፈለግህን’ ከቀጠልክ ጥረትህ መልሶ ሊክስህ ይችላል። (ምሳሌ 2:1-5) ሌሎች ሰዎች ምንም አሉህ ምን እነዚህ ጥያቄዎች መልስ ያላቸው ከመሆኑም በላይ መልሶቹን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት ትችላለህ። መልሶቹ ለመረዳት አዳጋች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ተስፋና ደስታ የሚያስገኙ ናቸው። አልፎ ተርፎም በአሁኑ ጊዜም እንኳ አስደሳች ሕይወት መኖር እንድትችል ይረዱሃል። በመጀመሪያ እስቲ ብዙ ሰዎችን ግራ የሚያጋባ አንድ ጥያቄ እንመርምር።

አምላክ አሳቢነትና ርኅራኄ የጎደለው ነው?

6. ብዙ ሰዎች አምላክ በሰው ዘር ላይ እየደረሰ ያለው መከራ አያሳስበውም የሚል አመለካከት የሚያድርባቸው ለምንድን ነው?

6 ብዙ ሰዎች የዚህ ጥያቄ መልስ አዎን የሚል እንደሆነ አድርገው  ያስባሉ። ‘አምላክ አሳቢ ቢሆንማ ኖሮ ዓለማችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ላይ ባልተገኘች ነበር’ ይላሉ። የምንኖረው በጦርነት፣ በጥላቻና በመከራ በተሞላ ዓለም ውስጥ ነው። በተጨማሪም በግለሰብ ደረጃ እንታመማለን፣ እንሠቃያለን እንዲሁም የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት እናጣለን። በመሆኑም ብዙዎች ‘አምላክ ስለ እኛ የሚያስብና በእኛ ላይ የሚደርሱት ችግሮች የሚያሳስቡት ቢሆን ኖሮ እንዲህ ካሉ ነገሮች አይታደገንም ነበር?’ ይላሉ።

7. (ሀ) የሃይማኖት አስተማሪዎች፣ ብዙ ሰዎች አምላክ ርኅራኄ የጎደለው ነው የሚል አስተሳሰብ እንዲያድርባቸው ያደረጉት እንዴት ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ የሚደርሱብንን ፈተናዎች በተመለከተ ምን ያስተምራል?

7 ከዚህ የከፋው ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሰዎች አምላክ ርኅራኄ የጎደለው ነው ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጉ መሆናቸው ነው። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? አንድ አሳዛኝ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ አምላክ ያመጣው ነው ይላሉ። በተዘዋዋሪ መንገድ እነዚህ አስተማሪዎች በሰዎች ላይ ለሚደርሱት መጥፎ ነገሮች ተጠያቂው አምላክ ነው እያሉ ነው። አምላክን በተመለከተ ትክክለኛው ትምህርት ይህ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ያስተምራል? ያዕቆብ 1:13 “ማንም ሲፈተን፣ ‘እግዚአብሔር ፈተነኝ’ አይበል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም” በማለት መልስ ይሰጠናል። ስለዚህ በዓለም ላይ የምታየውን ክፋት ያመጣው አምላክ አይደለም። (ኢዮብ 34:10-12) አምላክ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ እንደፈቀደ አይካድም። ሆኖም አንድ ነገር እንዲደርስ በመፍቀድ እና ለዚያ ነገር መንስኤ በመሆን መካከል ትልቅ ልዩነት አለ።

8, 9. (ሀ) ክፋት እንዲኖር በመፍቀድና ለክፋት መንስኤ በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት በምሳሌ ማስረዳት የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ የሰው ልጆች የዓመጽ ጎዳና እንዲከተሉ በመፍቀዱ ልንወቅሰው የማንችለው ለምንድን ነው?

8 ለምሳሌ ያህል በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ያለው አንድ አስተዋይና አፍቃሪ የሆነ አባት አለ እንበል። ልጁ ከወላጆቹ ጋር ይኖር የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ዓመጸኛ ሆኖ ቤቱን ለቅቆ ለመውጣት በሚወስንበት ጊዜ አባትየው አይከለክለውም። ልጁ መጥፎ የአኗኗር ጎዳና በመከተሉ ችግር ውስጥ ይወድቃል። በልጁ ላይ ለደረሰው ችግር መንስኤው አባትየው ነው ሊባል ይችላል? በፍጹም። (ሉቃስ 15:11-13) በተመሳሳይም አምላክ ሰዎች መጥፎ ጎዳና ለመከተል በመረጡ ጊዜ አልከለከላቸውም፤ ሆኖም በዚህ ሳቢያ ለደረሰባቸው ችግር መንስኤው እሱ አይደለም። ስለዚህ በሰው  ዘር ላይ እየደረሱ ላሉት ችግሮች ሁሉ አምላክን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አይሆንም።

9 አምላክ የሰው ልጆች መጥፎ ጎዳና እንዲከተሉ የፈቀደበት በቂ ምክንያት አለው። ጥበበኛና ከፍተኛ ኃይል ያለው ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ይህን ያደረገበትን ምክንያት ለእኛ የመግለጽ ግዴታ የለበትም። ይሁን እንጂ ለእኛ ባለው ፍቅር በመገፋፋት ምክንያቱን ገልጾልናል። ይህን በተመለከተ በምዕራፍ 11 ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ታገኛለህ። ሆኖም እየደረሱብን ላሉት ችግሮች ተጠያቂው አምላክ እንዳልሆነ እርግጠኛ ሁን። ይልቁንም ከእነዚህ ችግሮች መላቀቅ የምንችልበትን ብቸኛ ተስፋ የሰጠን እሱ ነው!—ኢሳይያስ 33:2

10. አምላክ ክፋት ያስከተላቸውን ውጤቶች በሙሉ ያስወግዳል ብለን ልንተማመንበት የምንችለው ለምንድን ነው?

10 ከዚህም በላይ አምላክ ቅዱስ ነው። (ኢሳይያስ 6:3) ይህ ማለት አምላክ ንጹሕና ሙሉ በሙሉ ከክፋት የጠራ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ሙሉ በሙሉ ልንተማመንበት እንችላለን። የሰው ልጆች የሥነ ምግባር አቋማቸው ሊበላሽ ስለሚችል እንዲህ ያለ እምነት ልንጥልባቸው አንችልም። ብዙውን ጊዜ በጣም ሐቀኛ ነው የሚባል ሰብዓዊ ባለ ሥልጣንም እንኳ መጥፎ የሆኑ ሰዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ማስቀረት አይችልም። አምላክ ግን ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ኃይል አለው። ክፋት በሰው ዘሮች ላይ ያስከተላቸውን ውጤቶች በሙሉ ማስወገድ ይችላል ደግሞም ያስወግዳል። አምላክ ይህን እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ ክፋት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳል!—መዝሙር 37:9-11

አምላክ ስለሚደርስብን ግፍ ምን ይሰማዋል?

11. (ሀ) አምላክ ግፍን በተመለከተ ምን ይሰማዋል? (ለ) አምላክ በአንተ ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ በተመለከተ ምን ይሰማዋል?

11 እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን አምላክ በዓለም ላይም ሆነ በአንተ ሕይወት ላይ እየደረሰ ስላለው ነገር ምን ይሰማዋል? መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ፍትሕን ይወዳል” ሲል ያስተምራል። (መዝሙር 37:28) በመሆኑም ትክክልና ስህተት የሆነው ነገር በእጅጉ ያሳስበዋል። ማንኛውንም ዓይነት ግፍ ይጠላል። መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን ዓለም በክፋት በመሞላቱ አምላክ ‘ልቡ እጅግ እንዳዘነ’ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 6:5, 6) አምላክ አሁንም አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) አሁንም ቢሆን በዓለም ዙሪያ ያለውን መከራ ሲያይ  ያዝናል። በተጨማሪም ሰዎች ሲሠቃዩ ማየት አይፈልግም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘እርሱ ስለ እናንተ ያስባል’ ይላል።—1 ጴጥሮስ 5:7

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አፍቃሪ የሆነ የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ እንደሆነ ያስተምራል

12, 13. (ሀ) እንደ ፍቅር ያሉ ጥሩ ባሕርያት ሊኖሩን የቻሉት ለምንድን ነው? ፍቅር በዓለም ላይ ስላለው ሁኔታ ያለንን አመለካከት የሚነካውስ እንዴት ነው? (ለ) አምላክ በዓለም ላይ የሚታዩትን ችግሮች ለማስወገድ አንድ እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኛ ልትሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

12 አምላክ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ሲያይ እንደሚያዝን እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው? የሚከተለውን ተጨማሪ ማስረጃ ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ሰው በአምላክ መልክ እንደተፈጠረ ያስተምራል። (ዘፍጥረት 1:26) በመሆኑም ጥሩ ባሕርያት ሊኖሩን የቻለው አምላክ ጥሩ ባሕርያት ስላሉት ነው። ለምሳሌ ያህል ምንም ዓይነት ጥፋት ያልሠሩ ሰዎች ሥቃይ ሲደርስባቸው ስታይ ስሜትህ ይረበሻል? እንዲህ ዓይነቱ ግፍ አንተን የሚያሳስብህ ከሆነ አምላክን ደግሞ ይበልጥ እንደሚያሳስበው እርግጠኛ ሁን።

13 የሰው ልጆች ካሏቸው ጥሩ ተሰጥኦዎች አንዱ የመውደድ ችሎታ ነው። ይህም የአምላክን ባሕርይ ያንጸባርቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ሲል ያስተምራል። (1 ዮሐንስ 4:8) እኛ አፍቃሪ የሆንነው አምላክ አፍቃሪ ስለሆነ ነው። ለሌሎች ያለህ ፍቅር በዓለም ላይ ያለውን መከራና ግፍ እንድታስወግድ ይገፋፋሃል? ይህን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ቢኖርህ ኖሮ ታደርገው ነበር? እንደምታደርገው የታወቀ ነው! አምላክ መከራንና ግፍን እንደሚያስወግድ የዚያኑ ያህል እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። በዚህ መጽሐፍ መቅድም ላይ የተጠቀሱት ተስፋዎች የሕልም እንጀራ ወይም ከንቱ ቅዠት አይደሉም። አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች እንደሚፈጸሙ የተረጋገጠ ነው! ይሁን እንጂ እንዲህ ባሉ ተስፋዎች ላይ እምነት መጣል እንድትችል እነዚህን ተስፋዎች ስለሰጠው አምላክ ይበልጥ ማወቅ ይኖርብሃል።

 አምላክ ስለ እሱ ማንነት እንድታውቅ ይፈልጋል

አንድ ሰው እንዲተዋወቅህ በምትፈልግበት ጊዜ ስምህን እንደምትነግረው የታወቀ ነው። አምላክ ስሙን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ገልጾልናል

14. የአምላክ ስም ማን ነው? በስሙ ልንጠራው የሚገባውስ ለምንድን ነው?

14 አንድ ሰው እንዲተዋወቅህ ከፈለግክ ምን ታደርጋለህ? ስምህን እንደምትነግረው የታወቀ ነው። አምላክስ ስም አለው? ብዙዎቹ ሃይማኖቶች ስሙ “አምላክ” ወይም “ጌታ” ነው ይላሉ፤ ሆኖም እነዚህ የግል ስሞች አይደሉም። “ንጉሥ” እና “ፕሬዚዳንት” የሚሉት ቃላት የማዕረግ ስሞች እንደሆኑ ሁሉ እነዚህም የማዕረግ ስሞች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ብዙ የማዕረግ ስሞች እንዳሉት ይገልጻል። “አምላክ” እና “ጌታ” የሚሉት መጠሪያዎች ከእነዚህ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የግል ስም እንዳለውና ይህም ይሖዋ እንደሆነ ይገልጻል።  ይሖዋ ዘፀአት 6:3 [የ1879 ትርጉም] ላይ “ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ በስሜም እግዚእ ይሖዋ አልታወቅሁላቸውም” ብሏል። በምትጠቀምበት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ይህ ስም ከሌለ ይህ የሆነበትን ምክንያት ለማወቅ በዚህ መጽሐፍ ገጽ 195-197 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ልትመለከት ትችላለህ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የአምላክ ስም በእጅ በተጻፉ የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ጊዜያት ተጠቅሶ ይገኛል። ስለዚህ ይሖዋ ስሙን እንድታውቅና በስሙ እንድትጠራው ይፈልጋል። በሌላ አነጋገር ራሱን ለአንተ ለማስተዋወቅ መጽሐፍ ቅዱስን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል።

15. ይሖዋ የሚለው ስም ምን ያመለክታል?

15 አምላክ ለራሱ ያወጣው ስም ብዙ ትርጉም ያዘለ ነው። ይሖዋ የሚለው ስሙ አምላክ የገባውን ቃል ሁሉ መፈጸም እንዲሁም ያወጣውን ዓላማ ሁሉ ዳር ማድረስ እንደሚችል ያመለክታል። * የአምላክ ስም በዓይነቱ ልዩ የሆነና  ለእሱ ብቻ የተሰጠ ነው። ይሖዋ በብዙ መንገዶች ፈጽሞ የተለየ ነው። ይህ የሆነው እንዴት ነው?

16, 17. (ሀ) “ሁሉን ቻይ” (ለ) “የዘመናት ንጉሥ” (ሐ) “ፈጣሪ” የሚለው የማዕረግ ስም ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

16 መዝሙር 83:18 ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር ‘አንተ ብቻ ልዑል ነህ’ ይላል። በተመሳሳይም “ሁሉን ቻይ” ተብሎ የተጠራው ይሖዋ ብቻ ነው። ራእይ 15:3 “ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ ሆይ፤ ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው። የዘመናት ንጉሥ ሆይ፤ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው” ይላል። “ሁሉን ቻይ” የሚለው የማዕረግ ስም ይሖዋ ከማንም በላይ ኃያል መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል። ኃይሉ ተወዳዳሪና አቻ አይገኝለትም። “የዘመናት ንጉሥ” የሚለው የማዕረግ ስም ደግሞ ይሖዋ በሌላ መንገድ ፈጽሞ የተለየ መሆኑን እንድናስታውስ ያደርገናል። መዝሙር 90:2 “አንተ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላክ ነህ” በማለት እሱ ብቻ ምንጊዜም የነበረ አምላክ መሆኑን ይገልጻል። ይህ ታላቅ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብን አያደርግም?

17 ይሖዋ እሱ ብቻ ፈጣሪ መሆኑም የተለየ ያደርገዋል። ራእይ 4:11 “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና” ይላል። በሰማይ ካሉት የማይታዩ መንፈሳዊ ፍጥረታት አንስቶ በምሽት በሰማይ ላይ የምናያቸው ከዋክብት፣ በዛፎች ላይ የሚበቅሉ ፍራፍሬዎችም ሆኑ በውቅያኖሶችና በወንዞች ውስጥ የሚርመሰመሱት ዓሦች ሁሉ ሊኖሩ የቻሉት ይሖዋ ስለፈጠራቸው ነው።

ወደ ይሖዋ መቅረብ ትችላለህ?

18. አንዳንድ ሰዎች ፈጽሞ ወደ አምላክ መቅረብ እንደማይችሉ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል?

18 አንዳንድ ሰዎች ታላቅ አክብሮት እንዲያድርብን ስለሚያደርጉት የይሖዋ ባሕርያት ሲያነቡ በተወሰነ ደረጃ ፍርሃት ያድርባቸዋል። አምላክ እጅግ ከፍ ያለና ታላቅ ክብር የተላበሰ በመሆኑ ወደ እሱ መቅረብ እንደማይችሉ እንዲያውም ከቁብ ሊቆጥራቸው እንደማይችል አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰብ ትክክል ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ከዚህ ተቃራኒ ነው። ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 17:27) እንዲያውም “ወደ እግዚአብሔር  ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ሲል አጥብቆ ያሳስበናል።—ያዕቆብ 4:8

19. (ሀ) ወደ አምላክ ለመቅረብ በመጀመሪያ ልናደርገው የሚገባን ነገር ምንድን ነው? ይህስ ምን ጥቅም ያስገኛል? (ለ) ከአምላክ ባሕርያት መካከል አንተን ይበልጥ የሚስቡህ የትኞቹ ናቸው?

19 ወደ አምላክ መቅረብ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ አሁን እያደረግኸው ያለኸውን ማለትም ስለ አምላክ መማርህን ቀጥል። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ መማር “የዘላለም ሕይወት” እንደሚያስገኝ ያስተምራል! ቀደም ሲል እንደተገለጸው “እግዚአብሔር ፍቅር ነው።” (1 ዮሐንስ 4:16) ይሖዋ ግሩምና ማራኪ የሆኑ ሌሎች በርካታ ባሕርያትም አሉት። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “ሩኅሩኅ ቸር አምላክ . . . ለቊጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ” እንደሆነ ይገልጻል። (ዘፀአት 34:6) “ቸርና ይቅር ባይ” ነው። (መዝሙር 86:5) አምላክ ታጋሽ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:9) መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ባነበብክ መጠን ይሖዋ እነዚህና ሌሎች ማራኪ ባሕርያት እንዳሉት ያሳየው እንዴት እንደሆነ ትገነዘባለህ።

20-22. (ሀ) አምላክን ማየት የማንችል መሆናችን ወደ እሱ እንዳንቀርብ ሊያግደን ይችላል? አብራራ። (ለ) አንዳንድ ሰዎች በቅን ልቦና ተነሳስተው ምን እንድታደርግ ሊገፋፉህ ይችላሉ? ሆኖም ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

20 አምላክ በዓይን ሊታይ የማይችል መንፈስ በመሆኑ ልታየው እንደማትችል የታወቀ ነው። (ዮሐንስ 1:18፤ 4:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:17) ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ስለ እርሱ የምትማር ከሆነ እንደ አንድ አካል እውን ሆኖ ሊታይህ ይችላል። መዝሙራዊው እንዳለው ‘የእግዚአብሔርን ክብር ውበት ማየት’ ትችላለህ። (መዝሙር 27:4፤ ሮሜ 1:20) ስለ ይሖዋ ይበልጥ በተማርክ መጠን ይበልጥ እውን እየሆነልህ ይሄዳል እንዲሁም ይበልጥ እየወደድከውና እየቀረብከው ትሄዳለህ።

አንድ ጥሩ አባት ለልጆቹ ያለው ፍቅር በሰማይ ያለው አባታችን ለእኛ ያለውን የላቀ ፍቅር ያንጸባርቃል

21 መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን እንደ አባታችን አድርገን እንድንመለከተው የሚያስተምረን ለምን እንደሆነ ቀስ በቀስ እየተገነዘብክ ትሄዳለህ። (ማቴዎስ 6:9) ይሖዋ ሕይወትን ከመስጠት በተጨማሪ ማንኛውም አፍቃሪ አባት ለልጆቹ እንደሚመኘው ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት እንድንኖር ይፈልጋል። (መዝሙር 36:9) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች የይሖዋ ወዳጆች ሊሆኑ እንደሚችሉ  ያስተምራል። (ያዕቆብ 2:23) የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ወዳጅ መሆን መቻል ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው!

22 መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ እየተማርክ ስትሄድ አንዳንድ ሰዎች በቅን ልቦና ተነሳስተው ጥናትህን እንድታቆም ሊገፋፉህ ይችላሉ። እምነትህን ልትለውጥ ትችላለህ ብለው ይሰጉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ማንም ሰው ከሁሉ የላቀውን እንዲህ ያለ ወዳጅነት እንዳትመሠርት እንቅፋት እንዲሆንብህ መፍቀድ የለብህም።

23, 24. (ሀ) እየተማርከው ስላለው ነገር ጥያቄዎችን መጠየቅህን መቀጠል ያለብህ ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ የሚብራራው ርዕሰ ጉዳይ ምንድን ነው?

23 እርግጥ ነው፣ መጀመሪያ ላይ ግልጽ የማይሆኑልህ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። በዚህ ረገድ የሌሎችን እገዛ መጠየቅ ትሕትና ሊጠይቅብህ ይችላል፤ ሆኖም አፍረህ እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት የለብህም። ኢየሱስ ልክ እንደ ሕፃን ልጅ ትሑት መሆን ጠቃሚ እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴዎስ 18:2-4) ልጆች ደግሞ እንደምናውቀው ብዙ ጥያቄዎች ይጠይቃሉ። አምላክ ለጥያቄዎችህ መልስ እንድታገኝ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸውን ሰዎች አወድሷቸዋል። የሚማሩት ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በደንብ ይመረምሩ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 17:11

24 ስለ ይሖዋ ለመማር ከሁሉ የተሻለው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ የተለየ ነው። የተለየ የሆነው በምን መንገድ ነው? የሚቀጥለው ምዕራፍ ይህን ርዕሰ ጉዳይ ያብራራል።

^ አን.15 የአምላክን ስም ትርጉምና አጠራር በተመለከተ ከገጽ 195-197 ላይ በሚገኘው ተጨማሪ ክፍል ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይገኛል።