በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ አራት

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?
  • ኢየሱስ የተሰጠው ልዩ ሚና ምንድን ነው?

  • የመጣው ከየት ነው?

  • ምን ዓይነት ሰው ነበር?

1, 2. (ሀ) አንድን ዝነኛ ሰው በስም ታውቀዋለህ ማለት ግለሰቡን በሚገባ ታውቀዋለህ ማለት ላይሆን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) ስለ ኢየሱስ ምን የተዘበራረቀ አመለካከት አለ?

በዓለም ውስጥ ዝነኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ። አንዳንዶች ታዋቂነት ያተረፉት በራሳቸው ማኅበረሰብ፣ ከተማ ወይም አገር ውስጥ ነው። ሌሎች ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ዝና አትርፈዋል። ይሁን እንጂ የአንድን ዝነኛ ሰው ስም ታውቃለህ ማለት ግለሰቡን በሚገባ ታውቀዋለህ ማለት ላይሆን ይችላል። ስለ አስተዳደጉም ሆነ ስለ ሰውየው ማንነት ዝርዝር ጉዳዮችን ላታውቅ ትችላለህ።

2 ምንም እንኳ ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ የኖረው ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ቢሆንም በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ስለ እሱ ሰምተዋል። ሆኖም ብዙዎቹ የኢየሱስን ትክክለኛ ማንነት በተመለከተ ግራ ተጋብተዋል። አንዳንዶች ተራ የሆነ አንድ ጥሩ ሰው እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ እንደማንኛውም ነቢይ አድርገው ይቆጥሩታል። ኢየሱስ አምላክ እንደሆነና ሊመለክ እንደሚገባው የሚያምኑ ሰዎችም አሉ። በእርግጥ ሊመለክ ይገባዋል?

3. ስለ ኢየሱስ እውነተኛውን ነገር ማወቅህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ስለ ኢየሱስ እውነተኛውን ነገር ማወቅህ በጣም አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ይላል። (ዮሐንስ 17:3) አዎን፣ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት መቅሰም በምድር ላይ በገነት የዘላለም  ሕይወት ሊያስገኝ ይችላል። (ዮሐንስ 14:6) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ እንዴት መኖርና ሌሎችን እንዴት መያዝ እንደሚገባ የሚያሳይ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል። (ዮሐንስ 13:34, 35) በዚህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ አምላክን በተመለከተ እውነተኛው ነገር ምን እንደሆነ ተብራርቷል። አሁን ደግሞ እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንደሚያስተምር እንመልከት።

አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ

4. “መሲሕ” እና “ክርስቶስ” የሚሉት የማዕረግ ስሞች ምን ትርጉም አላቸው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት አምላክ መሲሕ ወይም ክርስቶስ አድርጎ ስለሚልከው ሰው ተንብዮ  ነበር። “መሲሕ” (ከዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ ነው) እና “ክርስቶስ” (ከግሪክኛ ቃል የተወሰደ ነው) የሚሉት የማዕረግ ስሞች “የተቀባ” የሚል ትርጉም አላቸው። ይህ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ የተቀባ ማለትም አምላክ ለአንድ ልዩ ኃላፊነት የሾመው ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙት በኋለኞቹ ምዕራፎች ላይ መሲሑ አምላክ ቃል በገባቸው ተስፋዎች አፈጻጸም ረገድ ያለውን ትልቅ ቦታ እንመለከታለን። በተጨማሪም ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሊያስገኝልን የሚችለውን በረከት እንማራለን። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት ብዙዎች ‘መሲሕ የሚሆነው ማን ነው?’ ብለው ጠይቀው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

5. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ አምነው የተቀበሉት ነገር ምንድን ነው?

5 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ መሆኑን ሙሉ በሙሉ አምነው ተቀብለው ነበር። (ዮሐንስ 1:41) ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነው ስምዖን ጴጥሮስ የተባለው ሰው ኢየሱስን በግልጽ “አንተ ክርስቶስ . . . ነህ” ብሎታል። (ማቴዎስ 16:16) ይሁን እንጂ እነዚያ ደቀ መዛሙርትም ሆኑ እኛ ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ መሆኑን በእርግጠኝነት ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

6. ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ የመሲሑን ማንነት ለይተው ማወቅ እንዲችሉ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

6 ከኢየሱስ ዘመን በፊት የኖሩት የአምላክ ነቢያት ስለ መሲሑ በተናገሩት ትንቢት ላይ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን ጠቅሰዋል። እነዚህ መረጃዎች ሌሎች መሲሑን ለይተው ማወቅ እንዲችሉ ይረዷቸዋል። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- ሰው ወደሚበዛበት የአውቶቡስ መናኸሪያ ወይም ባቡር ጣቢያ አሊያም ደግሞ አውሮፕላን ማረፊያ ሄደህ ከዚህ ቀደም አይተኸው የማታውቀውን ሰው እንድትቀበል ተጠየቅህ እንበል። አንድ ሰው ስለምትቀበለው ግለሰብ አንዳንድ ዝርዝር መረጃዎች ቢሰጥህ ጠቃሚ አይሆንም? በተመሳሳይም ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት አማካኝነት መሲሑ ምን እንደሚያከናውንና ምን እንደሚደርስበት የሚገልጽ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቷል። የእነዚህ በርካታ ትንቢቶች ፍጻሜ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች መሲሑን ለይተው ማወቅ እንዲችሉ ይረዳቸዋል።

7. ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ ፍጻሜያቸውን ካገኙት ትንቢቶች መካከል ሁለቱ የትኞቹ ናቸው?

 7 ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ ተመልከት። በመጀመሪያ፣ ከ700 የሚበልጡ ዓመታት አስቀድሞ ነቢዩ ሚክያስ መሲሑ በይሁዳ ምድር በምትገኘው ቤተ ልሔም የተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ እንደሚወለድ ተንብዮ ነበር። (ሚክያስ 5:2) ኢየሱስ የተወለደው የት ነው? በዚህችው በቤተ ልሔም ከተማ ነው! (ማቴዎስ 2:1, 3-9) ሁለተኛ፣ ብዙ መቶ ዘመናት አስቀድሞ በዳንኤል 9:25 ላይ የተመዘገበው ትንቢት መሲሑ የሚገለጥበት ዓመት 29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደሚሆን ጠቁሞ ነበር። * የእነዚህና የሌሎች ትንቢቶች ፍጻሜ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ ኢየሱስ መሆኑን ያረጋግጣል።

ኢየሱስ ሲጠመቅ መሲሕ ወይም ክርስቶስ ሆኗል

8, 9. ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት መሲሕ መሆኑን የሚጠቁም ምን ነገር ተፈጽሟል?

8 በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መገባደጃ ላይ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሌላ ነገር ተፈጽሟል። ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ለመጠመቅ ወደ አጥማቂው ዮሐንስ የሄደው በዚህ ዓመት ነበር። ይሖዋ፣ ዮሐንስ መሲሑን ለይቶ ማወቅ እንዲችል ምልክት እንደሚያሳየው ቃል ገብቶለት ነበር። ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት ዮሐንስ ይህን ምልክት ተመልክቷል። መጽሐፍ ቅዱስ የተፈጸመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ኢየሱስም እንደ ተጠመቀ ከውሃው ወጣ፤ ወዲያውኑም ሰማይ ተከፍቶ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድበት አየ። እነሆ፣ ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።” (ማቴዎስ 3:16, 17) ዮሐንስ የተፈጸመውን ሁኔታ ካየና ከሰማ በኋላ ኢየሱስ በአምላክ የተላከ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል። (ዮሐንስ 1:32-34) ኢየሱስ በዚያ ዕለት የአምላክ መንፈስ ወይም ኃይል በላዩ ሲወርድበት መሪና ንጉሥ እንዲሆን የተሾመ መሲሕ ወይም ክርስቶስ ሆነ።—ኢሳይያስ 55:4

9 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜም ሆነ ይሖዋ አምላክ ራሱ የሰጠው ምሥክርነት ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው ከየት ነው?  ምን ዓይነት ሰውስ ነበር?’ ለሚሉት አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ሁለት ጥያቄዎችም መልስ ይሰጣል።

ኢየሱስ የመጣው ከየት ነው?

10. መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ስለነበረው ሕልውና ምን ያስተምራል?

10 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ይኖር እንደነበረ ያስተምራል። ሚክያስ መሲሑ በቤተ ልሔም እንደሚወለድና “አመጣጡ ከጥንት” እንደሆነ ተንብዮአል። (ሚክያስ 5:2) ኢየሱስ ራሱ ሰው ሆኖ ከመወለዱ በፊት በሰማይ ይኖር እንደነበረ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:13፤ 6:38, 62፤ 17:4, 5) ኢየሱስ መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ በሰማይ ይኖር በነበረበት ዘመን ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና ነበረው።

11. መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ እጅግ ተወዳጅ የሆነ የይሖዋ ልጅ እንደሆነ የሚገልጸው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ እጅግ ተወዳጅ የሆነ የይሖዋ ልጅ ነው፤ ይህም የሆነበት በቂ ምክንያት አለ። ከአምላክ የፍጥረት ሥራዎች የመጀመሪያው በመሆኑ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር” ተብሎ ተጠርቷል። * (ቈላስይስ 1:15) ይህን ልጅ ልዩ የሚያደርገው ሌላም ነገር አለ። ‘አንድያ ልጅ’ ነው። (ዮሐንስ 3:16) ይህም በአምላክ በቀጥታ የተፈጠረው ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። በተጨማሪም አምላክ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ሲፈጥር የተጠቀመው በኢየሱስ ብቻ ነው። (ቈላስይስ 1:16) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ “ቃል” ተብሎ ተጠርቷል። (ዮሐንስ 1:14) ይህም ለአባቱ መንፈሳዊም ሆኑ ሰብዓዊ ልጆች መልእክትና መመሪያ በማስተላለፍ አባቱን ወክሎ ይናገር እንደነበር የሚያመለክት ነው።

12. የበኩር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል እንዳልሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

12 አንዳንዶች እንደሚያስቡት ይህ የበኩር ልጅ ከአምላክ ጋር እኩል ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ አያስተምርም። ቀደም ባለው አንቀጽ  ላይ እንደተመለከትነው ወልድ ፍጡር ነው። ስለዚህ መጀመሪያ አለው ማለት ነው፤ ይሖዋ አምላክ ግን መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ የለውም። (መዝሙር 90:2) ይህ አንድያ ልጅ ከአምላክ ጋር ለመተካከል አስቦ እንኳ አያውቅም። መጽሐፍ ቅዱስ አብ ከወልድ እንደሚበልጥ በግልጽ ያስተምራል። (ዮሐንስ 14:28፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3) “ሁሉን ቻይ . . . አምላክ” ይሖዋ ብቻ ነው። (ራእይ 15:3) ስለዚህ እኩያ የለውም። *

13. መጽሐፍ ቅዱስ ወልድን “የማይታየው አምላክ አምሳል” ብሎ የሚጠራው ለምንድን ነው?

13 በከዋክብት የተሞሉት ሰማያትና ምድር ከመፈጠራቸው ከረጅም ጊዜ በፊት ይሖዋና አንድያ ልጁ በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት የዘለቀ የጠበቀ ወዳጅነት ነበራቸው። ምን ያህል እንደሚዋደዱ መገመት ይቻላል! (ዮሐንስ 3:35፤ 14:31) ይህ ውድ ልጅ ልክ እንደ አባቱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የማይታየው አምላክ አምሳል” ሲል የሚጠራው ለዚህ ነው። (ቈላስይስ 1:15) አዎን፣ አንድ ሰብዓዊ ልጅ ከአባቱ ጋር በብዙ መንገዶች በእጅጉ ሊመሳሰል እንደሚችል ሁሉ ይህ ሰማያዊ ልጅም የአባቱን ባሕርያት በሚገባ አንጸባርቋል።

14. የይሖዋ አንድያ ልጅ ሰው ሆኖ የተወለደው እንዴት ነው?

14 የይሖዋ አንድያ ልጅ በፈቃደኝነት ሰው ሆኖ ለመኖር ሰማይን ትቶ ወደ ምድር መጥቷል። ይሁን እንጂ ‘አንድ መንፈሳዊ ፍጡር እንዴት ሰው ሆኖ ሊወለድ ይችላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ይሖዋ ይህን ለማከናወን አንድ ተአምር ፈጽሟል። በሰማይ የነበረውን የበኩር ልጁን ሕይወት ማርያም ወደምትባል አንዲት አይሁዳዊት ድንግል ማኅፀን አዛወረው። ይህን ለማድረግ ሰብዓዊ አባት አላስፈለገም። በዚህ መንገድ ማርያም ፍጹም ልጅ የወለደች ሲሆን ስሙንም ኢየሱስ ብላ ጠራችው።—ሉቃስ 1:30-35

ኢየሱስ ምን ዓይነት ሰው ነበር?

15. በኢየሱስ አማካኝነት ስለ ይሖዋ ይበልጥ ማወቅ እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው?

15 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የተናገራቸውና ያደረጋቸው ነገሮች እሱን በሚገባ ማወቅ እንድንችል ይረዱናል። በይበልጥ ደግሞ በኢየሱስ  አማካኝነት ይሖዋን በተሻለ ሁኔታ ማወቅ እንችላለን። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ይህ ልጅ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ መሆኑን አስታውስ። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱን “እኔን ያየ አብን አይቶአል” ያለው በዚህ ምክንያት ነው። (ዮሐንስ 14:9) ወንጌሎች በመባል የሚታወቁት አራቱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ማለትም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ ስላከናወናቸው ነገሮችና ስለ ባሕርያቱ ብዙ ነገር ይነግሩናል።

16. ዋነኛው የኢየሱስ መልእክት ምን ነበር? ትምህርቱስ ከማን የመጣ ነው?

16 ኢየሱስ በብዙዎች ዘንድ ‘በመምህርነቱ’ ይታወቅ ነበር። (ዮሐንስ 1:38፤ 13:13) ያስተማረው ትምህርት ምንድን ነው? የትምህርቱ ዋነኛ መልእክት ‘የመንግሥቱ ምሥራች’ ነበር። ይህ መንግሥት መላውን ምድር የሚገዛውና ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ማብቂያ የሌለው በረከት የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ወይም ሰማያዊ መስተዳድር ነው። (ማቴዎስ 4:23) መልእክቱ የማን ነው? ኢየሱስ ራሱ “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን፣ ከላከኝ የመጣ ነው” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:16) ኢየሱስ፣ አባቱ የሰው ልጆች የመንግሥቱን ምሥራች እንዲሰሙ እንደሚፈልግ ያውቅ ነበር። ምዕራፍ 8 ላይ ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት ስለሚያከናውናቸው ነገሮች ይበልጥ እንማራለን።

17. ኢየሱስ ያስተማረው የት ነው? ሌሎችን ለማስተማር የተቻለውን ሁሉ ጥረት ያደረገውስ ለምንድን ነው?

17 ኢየሱስ ያስተምር የነበረው የት ነው? ሰዎችን በሚያገኝበት ቦታ ሁሉ ያስተምር ነበር። በገጠርም ሆነ በከተማ፣ በመንደሮች፣ በገበያ ሥፍራዎችና በቤታቸው አስተምሯል። ኢየሱስ ሰዎች ወደ እሱ እንዲመጡ ከመጠበቅ ይልቅ እነሱ ወዳሉበት በመሄድ ያስተምር ነበር። (ማርቆስ 6:56፤ ሉቃስ 19:5, 6) ኢየሱስ የተቻለውን ሁሉ ጥረት በማድረግ አብዛኛውን ጊዜውን በመስበክና በማስተማር ያሳልፍ የነበረው ለምንድን ነው? አምላክ ይህን እንዲያደርግ ይፈልግ ስለነበረ ነው። ኢየሱስ ምንጊዜም የአባቱን ፈቃድ ያደርግ ነበር። (ዮሐንስ 8:28, 29) ይሁን እንጂ ይህን መልእክት የሰበከበት ሌላም ምክንያት ነበረው። ወደ እሱ ይመጡ ለነበሩት በርካታ ሰዎች በእጅጉ ያዝን ነበር። (ማቴዎስ 9:35, 36) ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ እውነተኛውን ትምህርት የማስተማር ኃላፊነት  የነበረባቸው የሃይማኖት መሪዎቻቸው ችላ ብለዋቸው ነበር። ኢየሱስ ሕዝቡ የመንግሥቱን መልእክት መስማቱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር።

18. ይበልጥ ማራኪ ሆነው ያገኘሃቸው የኢየሱስ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?

18 ኢየሱስ ለሌሎች ከልብ የሚያስብ አፍቃሪ ሰው ነበር። በመሆኑም ሰዎች በቀላሉ የሚቀረብና ደግ ሰው ሆኖ አግኝተውታል። ሕፃናት እንኳ ሳይቀሩ ከእሱ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር። (ማርቆስ 10:13-16) ኢየሱስ የማያዳላ ከመሆኑም ሌላ ሙስናንና ኢፍትሐዊ የሆኑ ድርጊቶችን ይጠላ ነበር። (ማቴዎስ 21:12, 13) ሴቶች አክብሮትና የተለያዩ መብቶች ይነፈጓቸው በነበረበት ዘመን አክብሮት አሳይቷቸዋል። (ዮሐንስ 4:9, 27) ኢየሱስ ከልብ የመነጨ ትሕትና ነበረው። በአንድ ወቅት የሐዋርያቱን እግር በማጠብ አብዛኛውን ጊዜ ዝቅተኛ የሆነ አገልጋይ የሚያከናውነውን አገልግሎት ፈጽሟል።

ኢየሱስ ሰዎችን በሚያገኝበት ቦታ ሁሉ ይሰብክ ነበር

19. ኢየሱስ ለሌሎች ሰዎች ችግር ያስብ እንደነበር የሚያሳየው የትኛው ምሳሌ ነው?

19 ኢየሱስ የሌሎች ሰዎች ችግር ያሳስበው ነበር። ይህ ሁኔታ በተለይ በአምላክ መንፈስ ኃይል የተለያዩ ሰዎችን በመፈወስ በፈጸማቸው ተአምራት  ላይ በግልጽ ታይቷል። (ማቴዎስ 14:14) ለምሳሌ ያህል በሥጋ ደዌ በሽታ የተያዘ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” አለው። ኢየሱስ የዚህ ሰው ሕመምና ሥቃይ በጣም ተሰምቶት ነበር። በሐዘን ስሜት በመገፋፋት እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “እፈቅዳለሁ፣ ንጻ” አለው። በዚህ ጊዜ ታሞ የነበረው ሰው ተፈወሰ! (ማርቆስ 1:40-42) ሰውየው ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ?

እስከ መጨረሻው ታማኝ ሆኗል

20, 21. ኢየሱስ ለአምላክ በታማኝነት በመታዘዝ ረገድ ጥሩ ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?

20 ኢየሱስ ለአምላክ በታማኝነት በመታዘዝ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቷል። ሁሉም ዓይነት ተቃውሞና መከራ ቢደርስበትም በማንኛውም ሁኔታ ሥር ለሰማያዊ አባቱ ታማኝ ሆኗል። ኢየሱስ በአቋሙ በመጽናት የሰይጣንን ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ መቋቋም ችሏል። (ማቴዎስ 4:1-11) በአንድ ወቅት ከገዛ ራሱ ዘመዶች መካከል አንዳንዶቹ አላመኑበትም ነበር፤ እንዲያውም “አእምሮውን ስቶአል” ብለው ነበር። (ማርቆስ 3:21) ሆኖም ኢየሱስ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩበት አልፈቀደም፤ ከዚህ  ይልቅ የአምላክን ሥራ ማከናወኑን ቀጥሏል። ስድብና በደል ቢደርስበትም ራሱን በመግዛት በተቃዋሚዎቹ ላይ ጉዳት ለማድረስ ከመሞከር ታቅቧል።—1 ጴጥሮስ 2:21-23

21 ኢየሱስ በጠላቶቹ እጅ ከፍተኛ ሥቃይ ደርሶበት በአሰቃቂ ሁኔታ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በታማኝነት ጸንቷል። (ፊልጵስዩስ 2:8) ሰው ሆኖ ባሳለፈው የመጨረሻ ዕለት የደረሰበትን ሁኔታ ተመልከት። ተይዞ በሐሰት ከተመሠከረበት በኋላ ምግባረ ብልሹ በሆኑ ዳኞች ተፈረደበት፤ ሕዝቡ አፌዘበት እንዲሁም ወታደሮቹ አሠቃዩት። በእንጨት ላይ በምስማር ከተቸነከረ በኋላ “ተፈጸመ” ብሎ በመናገር ሕይወቱን አሳልፎ ሰጠ። (ዮሐንስ 19:30) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በሞተ በሦስተኛው ቀን ሰማያዊ አባቱ ከሞት በማስነሳት ዳግመኛ መንፈሳዊ ሕይወት ሰጠው። (1 ጴጥሮስ 3:18) ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ሰማይ ተመለሰ። በዚያም ‘በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ’ ንጉሣዊ ሥልጣኑን የሚቀበልበትን ጊዜ መጠባበቅ ጀመረ።—ዕብራውያን 10:12, 13

22. ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆን ያከናወነው ነገር ምንድን ነው?

22 ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆን ያከናወነው ነገር ምንድን ነው? የኢየሱስ ሞት ከመጀመሪያው የይሖዋ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበትን አጋጣሚ ከፍቶልናል። የኢየሱስ ሞት ይህን አጋጣሚ ሊከፍትልን የቻለው እንዴት እንደሆነ የሚቀጥለው ምዕራፍ ያብራራልናል።

^ አን.7 ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ ፍጻሜውን ያገኘውን የዳንኤል ትንቢት በተመለከተ ማብራሪያ ለማግኘት ከገጽ 197-199 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።

^ አን.11 ይሖዋ አባት ተብሎ የተጠራው ፈጣሪ ስለሆነ ነው። (ኢሳይያስ 64:8) ኢየሱስ የተፈጠረው በአምላክ ስለሆነ የአምላክ ልጅ ተብሏል። በዚሁ ምክንያት ሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታት አልፎ ተርፎም ሰው የሆነው አዳም የአምላክ ልጆች ተብለው ተጠርተዋል።—ኢዮብ 1:6 የግርጌ ማስታወሻ፤ ሉቃስ 3:38

^ አን.12 የበኩር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል እንዳልሆነ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ለማግኘት ከገጽ 201-204 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።