በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ አምስት

ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ

ቤዛው—ከሁሉ የላቀ የአምላክ ስጦታ
  • ቤዛው ምንድን ነው?

  • የተዘጋጀው እንዴት ነው?

  • ቤዛው ምን ጥቅሞች ሊያስገኝልህ ይችላል?

  • ለቤዛው ዝግጅት አመስጋኝ መሆንህን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

1, 2. (ሀ) አንድ ስጦታ ለአንተ በግልህ ትልቅ ዋጋ የሚኖረው መቼ ነው? (ለ) ቤዛው ልታገኛቸው ከምትችላቸው ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ዋጋ ያለው ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

እስካሁን ካገኘኻቸው ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ግምት የምትሰጠው ለየትኛው ነው? አንድን ስጦታ የላቀ ግምት የሚያሰጠው ውድ ዋጋ የሚያወጣ መሆኑ አይደለም። እንዲያውም የአንድ ስጦታ እውነተኛ ዋጋ የሚለካው የግድ በሚያወጣው ገንዘብ መጠን አይደለም። ከዚህ ይልቅ ስጦታው ደስታ ካስገኘልህ ወይም በሕይወትህ ውስጥ በጣም የሚያስፈልግህን ነገር ካሟላልህ ያ ስጦታ ለአንተ ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል።

2 ልትጓጓላቸው ከምትችላቸው በርካታ ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ቦታ የሚይዝ አንድ ስጦታ አለ። ይህም አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው ስጦታ ነው። ይሖዋ ብዙ ነገሮች የሰጠን ቢሆንም ከስጦታዎቹ ሁሉ የላቀውን ቦታ የሚይዘው ግን የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። (ማቴዎስ 20:28) በዚህ ምዕራፍ ውስጥ እንደምንመለከተው ቤዛው ይህ ነው የማይባል ደስታ የሚያስገኝልህና በጣም የሚያስፈልጉህን ነገሮች ሊያሟላልህ የሚችል በመሆኑ ልታገኛቸው ከምትችላቸው ስጦታዎች ሁሉ የላቀ ዋጋ ያለው ነው። በእርግጥም  ቤዛው ይሖዋ አንተን ምን ያህል እንደሚወድህ ከሁሉ በላቀ መንገድ የገለጸበት ዝግጅት ነው።

ቤዛው ምንድን ነው?

3. ቤዛው ምንድን ነው? ይህ ስጦታ ምን ያህል ዋጋ ያለው እንደሆነ ለመገንዘብ በቅድሚያ ልንረዳው የሚገባን ነገርስ ምንድን ነው?

3 በአጭር አነጋገር ቤዛው ይሖዋ የሰው ዘሮችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት ወይም ለማዳን ያደረገው ዝግጅት ነው። (ኤፌሶን 1:7) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያለውን ትርጉም ለመረዳት ወደኋላ መለስ ብለን በኤደን ገነት የተፈጸመውን ሁኔታ ማሰብ ያስፈልገናል። ቤዛው ለእኛ የላቀ ዋጋ ያለው መሆኑን ልንገነዘብ የምንችለው አዳም ኃጢአት በሠራበት ጊዜ ያጣውን ነገር ከተረዳን ብቻ ነው።

4. አዳም ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ተሰጥቶት ነበር ሲባል ምን ማለት ነው?

4 ይሖዋ አዳምን በፈጠረበት ወቅት በጣም ውድ የሆነ ነገር ይኸውም ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ሰጥቶት ነበር። ይህ ማለት አዳም ፍጹም የሆነ አካልና አእምሮ የተሰጠው በመሆኑ ፈጽሞ አይታመምም፣ አያረጅም ወይም አይሞትም ማለት ነው። ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስ አዳም “የእግዚአብሔር ልጅ” እንደነበረ ይገልጻል። (ሉቃስ 3:38) ስለዚህ አዳም ከይሖዋ አምላክ ጋር የነበረው ዝምድና አንድ ልጅ አፍቃሪ ከሆነ አባቱ ጋር ያለው ዓይነት በጣም የተቀራረበ ዝምድና ነበር። ይሖዋ ምድራዊ ልጁ የሆነውን አዳምን ያነጋግረው የነበረ ሲሆን አርኪ የሆነ ሥራ ሰጥቶታል እንዲሁም ከእሱ የሚጠበቀውን ነገር አሳውቆታል።—ዘፍጥረት 1:28-30፤ 2:16, 17

5. መጽሐፍ ቅዱስ አዳም የተፈጠረው “በእግዚአብሔር መልክ” ነበር ሲል ምን ማለቱ ነው?

5 አዳም የተፈጠረው “በእግዚአብሔር መልክ” ነበር። (ዘፍጥረት 1:27) ይህ ሲባል ግን አዳም መልኩ ከአምላክ ጋር ይመሳሰላል ማለት አይደለም። በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ላይ እንደተማርነው ይሖዋ ሊታይ የማይችል መንፈስ ነው። (ዮሐንስ 4:24) በመሆኑም ይሖዋ ሥጋና ደም ያለው አካል አይደለም። አዳም የተፈጠረው በአምላክ መልክ ነው ሲባል እንደ ፍቅር፣ ጥበብ፣ ፍትሕና ኃይል ያሉትን የአምላክ  ባሕርያት ማንጸባረቅ እንዲችል ተደርጎ ተፈጥሯል ማለት ነው። አዳምን ከአባቱ ጋር የሚያመሳስለው ሌላው ትልቁ ነገር የመምረጥ ነፃነት ያለው መሆኑ ነው። ስለሆነም አዳም፣ የተሠራበትን ዓላማ ብቻ ማከናወን እንደሚችል ማሽን ወይም ሮቦት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የራሱን ውሳኔ የማድረግና ጥሩና መጥፎ የሆነውን ነገር የመምረጥ ችሎታ ነበረው። አምላክን መታዘዝ መርጦ ቢሆን ኖሮ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ይችል ነበር።

6. አዳም የአምላክን ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ ያጣው ነገር ምንድን ነው? በዘሮቹስ ላይ ምን ውጤት አስከተለ?

6 እንግዲያው አዳም የአምላክን ትእዛዝ ሲጥስና ሞት ሲፈረድበት ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር እንዳጣ በግልጽ መረዳት ይቻላል። የሠራው ኃጢአት ፍጹም የሆነውን ሰብዓዊ ሕይወቱንና ይህ ሕይወት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች አሳጥቶታል። (ዘፍጥረት 3:17-19) የሚያሳዝነው ደግሞ አዳም፣ ራሱ ብቻ ሳይሆን ዘሮቹም ይህን ውድ ሕይወት እንዲያጡ ማድረጉ ነው። የአምላክ ቃል “ኀጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል” ይላል። (ሮሜ 5:12) አዎን፣ ሁላችንም ከአዳም ኃጢአትን ወርሰናል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ አዳም ራሱንና ዘሮቹን ለኃጢአትና ለሞት ባርነት ‘እንደሸጠ’ ይናገራል። (ሮሜ 7:14) አዳምም ሆነ ሔዋን ሆን ብለው የአምላክን ትእዛዝ ስለጣሱ ምንም ተስፋ የላቸውም። ይሁን እንጂ እኛን ጨምሮ ዘሮቻቸው ምን ተስፋ አላቸው?

7, 8. ቤዛ ምን ሁለት ነገሮችን ያመለክታል?

7 ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት የሰውን ዘር ለመታደግ ዝግጅት አደረገ። ቤዛ ምንድን ነው? በመሠረቱ ቤዛ ሁለት ነገሮችን ሊያመለክት ይችላል። በመጀመሪያ ደረጃ ቤዛ አንድን ነገር ለማስለቀቅ ወይም መልሶ ለማግኘት የሚከፈልን ዋጋ ያመለክታል። አንድን የጦር እስረኛ ለማስፈታት ከሚከፈል ዋጋ ጋር ሊነጻጸር ይችላል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ቤዛ የአንድን ነገር ወጪ ለመሸፈን የሚከፈልን ዋጋ ያመለክታል። በሆነ ምክንያት የደረሰን ጉዳት ለማካካስ ከሚከፈል ዋጋ ጋር  ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው አደጋ ቢያደርስ ካደረሰው ጉዳት ጋር የሚመጣጠን ወይም የሚተካከል ዋጋ መክፈል ይኖርበታል።

8 አዳም በሁላችንም ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ኪሳራ መሸፈንና ከኃጢአትና ከሞት ባርነት እንድንላቀቅ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ ያዘጋጀውን ቤዛና ይህ ቤዛ ምን ጥቅሞች ሊያስገኝልህ እንደሚችል እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀው እንዴት ነው?

9. የጠፋውን ሕይወት ለመተካት ምን ዓይነት ቤዛ ያስፈልግ ነበር?

9 የጠፋው ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት በመሆኑ የትኛውም ፍጽምና የጎደለው ሰው ሊቤዠው አይችልም። (መዝሙር 49:7, 8) በመሆኑም ከጠፋው ሕይወት ጋር እኩል ዋጋ ያለው ቤዛ ያስፈልግ ነበር። ይህም በአምላክ ቃል ውስጥ ሰፍሮ ከሚገኘው “ሕይወት በሕይወት” ከሚለው ፍጹም የሆነ ፍትሕ የተንጸባረቀበት መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይስማማል። (ዘዳግም 19:21) ታዲያ አዳም ያጣውን ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት ዋጋ ሊሸፍን የሚችለው ምንድን ነው? አዳም ላጣው ሕይወት ያስፈልግ የነበረው ተመጣጣኝ ቤዛ ሌላ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 2:6

10. ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀው እንዴት ነው?

10 ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀው እንዴት ነው? ፍጹም ከሆኑት መንፈሳዊ ልጆቹ መካከል አንዱን ወደ ምድር ላከው። ይሁን እንጂ ይሖዋ የላከው እንዲሁ አንዱን መንፈሳዊ ፍጡር መርጦ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ወደ ምድር የላከው እጅግ ተወዳጅ የሆነውን አንድያ ልጁን ነው። (1 ዮሐንስ 4:9, 10) ይህ የአምላክ ልጅ በፈቃደኝነት በሰማይ የሚገኘውን መኖሪያውን ትቶ ወደ ምድር መጣ። (ፊልጵስዩስ 2:7) ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተማርነው ይሖዋ የዚህን ልጅ ሕይወት ወደ ማርያም ማኅፀን በማዛወር ተአምር ፈጽሟል። ኢየሱስ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አማካኝነት ፍጹም ሰው ሆኖ በመወለዱ ከኃጢአት ቅጣት ነፃ ነበር።—ሉቃስ 1:35

ይሖዋ አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል

11. አንድ ሰው በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ቤዛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

11 አንድ ሰው ለብዙዎች እንዲያውም በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ  ሰዎች ቤዛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ኃጢአተኞች ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው? አዳም ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ውድ የሆነውን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን እንዳጣ አስታውስ። በመሆኑም ይህን ፍጹም ሕይወት ለዘሮቹ ማውረስ አልቻለም። ከዚህ ይልቅ ለዘሮቹ ማውረስ የቻለው ኃጢአትንና ሞትን ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የኋለኛው አዳም” ብሎ የሚጠራው ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት የነበረው ከመሆኑም በላይ ፈጽሞ ኃጢአት አልሠራም። (1 ቆሮንቶስ 15:45) ስለሆነም ኢየሱስ እኛን ለመታደግ ሲል የአዳምን ቦታ ተክቷል። ፍጹም ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠትና ሙሉ በሙሉ ለአምላክ በመታዘዝ አዳም ለሠራው ኃጢአት ዋጋ ከፍሏል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ለአዳም ዘሮች ተስፋ አስገኝቷል።—ሮሜ 5:19፤ 1 ቆሮንቶስ 15:21, 22

12. በኢየሱስ ላይ የደረሰው ሥቃይ ምን ነገር እንዲረጋገጥ አድርጓል?

12 መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት የደረሰበትን መከራ በዝርዝር ይገልጻል። በኃይል ተገርፏል እንዲሁም በእንጨት ላይ በአሠቃቂ ሁኔታ ተሰቅሎ ከተሠቃየ በኋላ ሕይወቱን አጥቷል። (ዮሐንስ 19:1, 16-18, 30ተጨማሪ ክፍል፣ ገጽ 204-206) ኢየሱስ ይህን ያህል መሠቃየቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ወደፊት እንደምንመለከተው ሰይጣን የአምላክ ሰብዓዊ አገልጋዮች ፈተና ቢደርስባቸው ለይሖዋ ታማኝ አይሆኑም የሚል ክርክር አንስቷል። ኢየሱስ ከፍተኛ ሥቃይ ቢደርስበትም በታማኝነት በመጽናት ሰይጣን ላነሳው ክርክር ከሁሉ የተሻለ መልስ ሰጥቷል። ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ ምንም አደረገ ምን የመምረጥ ነፃነት ያለው አንድ ፍጹም ሰው ፍጹም በሆነ መንገድ ከአምላክ ጎን በታማኝነት መቆም እንደሚችል አረጋግጧል። ይሖዋ ውድ ልጁ ባሳየው ታማኝነት እጅግ ተደስቶ መሆን አለበት!—ምሳሌ 27:11

13. ቤዛው የተከፈለው እንዴት ነው?

13 ቤዛው የተከፈለው እንዴት ነው? ይሖዋ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኒሳን በተባለው የአይሁዶች ወር 14ኛ ቀን ላይ ፍጹም የሆነውና ምንም ኃጢአት ያልሠራው ልጁ እንዲገደል ፈቀደ። በዚህ መንገድ  ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” መሥዋዕት አደረገ። (ዕብራውያን 10:10) በሞተ በሦስተኛው ቀን ይሖዋ ከሞት በማስነሳት ዳግመኛ መንፈሳዊ ሕይወት ሰጠው። ኢየሱስ ለአዳም ዘሮች ቤዛ እንዲሆን መሥዋዕት ያደረገውን የፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ዋጋ በሰማይ በአምላክ ፊት አቀረበ። (ዕብራውያን 9:24) ይሖዋ የኢየሱስን መሥዋዕት ዋጋ የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ለማውጣት የሚያስፈልግ ቤዛ አድርጎ ተቀበለው።—ሮሜ 3:23, 24

ቤዛው ምን ጥቅሞች ሊያስገኝልህ ይችላል?

14, 15. “የኀጢአት ይቅርታ” ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

14 ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ በቤዛው አማካኝነት በጣም ውድ የሆኑ በረከቶችን ልናገኝ እንችላለን። ከሁሉ የላቀው ይህ የአምላክ ስጦታ አሁንም ሆነ ወደፊት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

15 የኃጢአት ይቅርታ። በዘር በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ከባድ ትግል ይጠይቅብናል። ሁላችንም በምንናገረው ወይም በምናደርገው ነገር ኃጢአት እንሠራለን። ሆኖም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት “የኀጢአት ይቅርታ” ማግኘት እንችላለን። (ቈላስይስ 1:13, 14) ይሁን እንጂ ይህን ይቅርታ ለማግኘት ከልብ ንስሐ መግባት ይኖርብናል። በተጨማሪም በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባለን እምነት መሠረት ይቅር እንዲለን ይሖዋን በትሕትና መለመን አለብን።—1 ዮሐንስ 1:8, 9

16. አምላክን በንጹሕ ሕሊና እንድናመልከው የሚያስችለን ነገር ምንድን ነው? እንዲህ ያለው ሕሊናስ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

16 በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዞ መኖር። ሕሊናችን የሚወቅሰን ከሆነ በቀላሉ ተስፋ እንድንቆርጥና የከንቱነት ስሜት እንዲሰማን ሊያደርገን ይችላል። ይሁን እንጂ ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም እንኳ ይሖዋ በደግነት ተገፋፍቶ በቤዛው አማካኝነት በምናገኘው የኃጢአት ይቅርታ በንጹሕ ሕሊና እንድናመልከው ያስችለናል። (ዕብራውያን 9:13, 14) ይህም ይሖዋን ሳንሸማቀቅ የማናገር አጋጣሚ ይከፍትልናል። ስለዚህ በነፃነት በጸሎት ልናነጋግረው እንችላለን። (ዕብራውያን  4:14-16) ንጹሕ ሕሊና ካለን የአእምሮ ሰላም፣ ለራሳችን ተገቢ አክብሮትና ደስታ ይኖረናል።

17. ኢየሱስ ለእኛ ሲል በመሞቱ የትኞቹን በረከቶች ማግኘት የሚቻልበት አጋጣሚ ተከፍቷል?

17 ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ። ሮሜ 6:23 “የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነው” ሲል ይገልጻል። ይኸው ጥቅስ አክሎ ሲናገር “የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” ይላል። በዚህ መጽሐፍ ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ በቅርቡ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚፈስሱትን በረከቶች ተመልክተናል። (ራእይ 21:3, 4) ፍጹም የሆነ ጤንነት አግኝቶ ለዘላለም የመኖር ተስፋን ጨምሮ እነዚህን ሁሉ በረከቶች ማግኘት የሚቻልበት በር የተከፈተው ኢየሱስ ለእኛ ሲል በመሞቱ ነው። እነዚህን በረከቶች እንድናገኝ ለቤዛው ስጦታ አመስጋኝ መሆናችንን ማሳየት ይኖርብናል።

አመስጋኝ መሆንህን ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

18. ይሖዋ ቤዛውን ስላዘጋጀልን ልናመሰግነው የሚገባን ለምንድን ነው?

18 ይሖዋ ቤዛውን ስለሰጠን በእጅጉ ልናመሰግነው የሚገባን ለምንድን ነው? አንድ ስጦታ ጊዜ፣ ጉልበት ወይም ገንዘብ መሥዋዕት የተደረገበት መሆኑ ስጦታውን ይበልጥ ተወዳጅ ያደርገዋል። ስጦታው ሰጪው ለእኛ ያለውን ከልብ የመነጨ ፍቅር የሚያሳይ በሚሆንበት  ጊዜ ልባችን በጣም ይነካል። ቤዛው አምላክ ከሁሉ የላቀ መሥዋዕት የከፈለበት በመሆኑ ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ውድ ስጦታ ነው። ዮሐንስ 3:16 “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል” ይላል። ቤዛው ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ከሁሉ ይበልጥ ጉልህ የሆነ ማስረጃ ነው። ኢየሱስም ለእኛ ሲል ሕይወቱን በፈቃደኝነት አሳልፎ መስጠቱ ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያል። (ዮሐንስ 15:13) ስለዚህ የቤዛው ስጦታ ይሖዋና ልጁ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወዱን አምነን እንድንቀበል ሊያደርገን ይገባል።—ገላትያ 2:20

ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለማወቅ መጣር ለቤዛው ስጦታ አመስጋኝ መሆንህን የምታሳይበት አንዱ መንገድ ነው

19, 20. የአምላክ ስጦታ የሆነውን ቤዛውን እንደምታደንቅ ማሳየት የምትችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

19 ታዲያ የአምላክ ስጦታ የሆነውን ቤዛውን እንደምታደንቅ በተግባር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ታላቁ ሰጪ ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት አድርግ። (ዮሐንስ 17:3) በዚህ መጽሐፍ እገዛ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ ይህን ማድረግ እንድትችል ይረዳሃል። ስለ ይሖዋ ያለህ እውቀት እያደገ ሲሄድ ለእሱ ያለህ ፍቅር የዚያኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል። ይህ ፍቅር ደግሞ እሱን ለማስደሰት እንድትጥር ያነሳሳሃል።—1 ዮሐንስ 5:3

20 በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት እንዳለህ አሳይ። ኢየሱስን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ “በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው” ይላል። (ዮሐንስ 3:36) በኢየሱስ እንደምናምን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለው እምነት በቃላት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ያዕቆብ 2:26 ‘ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው’ ይላል። አዎን፣ እውነተኛ እምነት የሚረጋገጠው ‘በሥራ’ ማለትም በድርጊታችን ነው። በኢየሱስ እንደምናምን የምናሳይበት አንዱ መንገድ በምንናገረው ብቻ ሳይሆን በምናደርገውም ነገር እሱን ለመምሰል የተቻለንን ሁሉ ጥረት በማድረግ ነው።—ዮሐንስ 13:15

21, 22. (ሀ) በየዓመቱ በሚከበረው የጌታ እራት ላይ መገኘት ያለብን ለምንድን ነው?

21 በየዓመቱ በሚከበረው የጌታ እራት በዓል ላይ ተገኝ። ኢየሱስ ኒሳን 14፣ 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የጌታ እራት’  በማለት የሚጠራውን አንድ ልዩ በዓል አቋቁሟል። (1 ቆሮንቶስ 11:20፤ ማቴዎስ 26:26-28) ይህ በዓል የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በመባልም ይታወቃል። ኢየሱስ ይህን በዓል ያቋቋመው ሐዋርያቱም ሆኑ ከእነሱ በኋላ የሚመጡት እውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ፍጹም ሰው ሆኖ በመሞት ነፍሱን ወይም ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንደሰጠ እንዲያስታውሱ ለመርዳት ነው። ኢየሱስ ይህን በዓል አስመልክቶ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል። (ሉቃስ 22:19) ይህን የመታሰቢያ በዓል ማክበራችን ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ከቤዛው ጋር በተያያዘ ያሳዩንን ከፍተኛ ፍቅር እንድናስታውስ ያደርገናል። በየዓመቱ በሚከበረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ በመገኘት ለቤዛው አመስጋኝ መሆናችንን ማሳየት እንችላለን። *

22 ይሖዋ የሰጠን ቤዛ በእርግጥም በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ ስጦታ ነው። (2 ቆሮንቶስ 9:14, 15) ይህ ውድ ስጦታ የሞቱትንም ሰዎች እንኳ ሊጠቅም ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ምዕራፍ 6 እና 7 ላይ ይብራራል።

^ አን.21 የጌታ እራት ያለውን ትርጉም በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከገጽ 206-208 ላይ የሚገኘውን ተጨማሪ ክፍል ተመልከት።