በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ምዕራፍ አሥራ ስምንት

ጥምቀትና ከአምላክ ጋር ያለህ ዝምድና

ጥምቀትና ከአምላክ ጋር ያለህ ዝምድና
  • የክርስቲያን ጥምቀት የሚከናወነው እንዴት ነው?

  • ለጥምቀት ብቁ እንድትሆን ምን እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልግሃል?

  • አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ የሚወስነው እንዴት ነው?

  • መጠመቅ አስፈላጊ የሆነበት ልዩ ምክንያት ምንድን ነው?

1. ኢትዮጵያዊው የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣን ለመጠመቅ የጠየቀው ለምንድን ነው?

“እነሆ፤ ውሃ እዚህ አለ፤ ታዲያ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” ይህን ጥያቄ ያነሳው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣን ነው። ፊልጶስ የተባለ አንድ ክርስቲያን አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ ኢየሱስ መሆኑን አስረድቶት ነበር። ኢትዮጵያዊው ሰው ከቅዱሳን ጽሑፎች የተማረው  ትምህርት ልቡን ነክቶት ስለነበር እርምጃ ለመውሰድ ተነሳሳ። መጠመቅ እንደሚፈልግ ገለጸ!—የሐዋርያት ሥራ 8:26-36

2. ጥምቀትን በቁም ነገር ልታስብበት የሚገባህ ለምንድን ነው?

2 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ቀደም ያሉ ምዕራፎች ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር በደንብ አጥንተሃቸው ከሆነ አሁን ‘እኔ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው?’ ብለህ መጠየቅ እንደምትችል ይሰማህ ይሆናል። እስካሁን ባደረግከው ጥናት በገነት ውስጥ የሚኖረውን የዘላለም ሕይወት አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸውን ተስፋ ተምረሃል። (ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 21:3, 4) ከዚህም በተጨማሪ ሙታን ስለሚገኙበት ትክክለኛ ሁኔታና ስለ ትንሣኤ ተስፋ ተምረሃል። (መክብብ 9:5፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ምናልባትም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት እውነተኛውን ሃይማኖት በሕይወታቸው ላይ እንዴት እንደሚያንጸባርቁ አስተውለህ ይሆናል። (ዮሐንስ 13:35) ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ አምላክ ጋር የግል ዝምድና መሥርተህ መሆን አለበት።

3. (ሀ) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ምን ትእዛዝ ሰጥቷል? (ለ) የውኃ ጥምቀት የሚከናወነው እንዴት ነው?

3 አምላክን ማገልገል እንደምትፈልግ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ተከታዮቹን “ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ . . . እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል አዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:19) ኢየሱስ ራሱ በውኃ በመጠመቅ ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ የተጠመቀው ውኃ በመረጨት ወይም ጥቂት ውኃ ራሱ ላይ እንዲፈስ በማድረግ አይደለም። (ማቴዎስ 3:16) “ማጥመቅ” የሚለው ቃል “ማጥለቅ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው። ስለዚህ የክርስቲያን ጥምቀት ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅን ወይም መግባትን የሚያመለክት ነው።

4. የውኃ ጥምቀት ምን ያሳያል?

4 ከይሖዋ አምላክ ጋር መዛመድ የሚፈልጉ ሁሉ በውኃ መጠመቅ አለባቸው። ጥምቀት አምላክን ለማገልገል ያለህን ፍላጎት በሰዎች ፊት የምታሳይበት ነው። የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ እንደሚያስደስትህ በግልጽ ያሳያል። (መዝሙር 40:7, 8) ይሁን እንጂ ለጥምቀት ብቁ ለመሆን ልትወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎች አሉ።

 እውቀትና እምነት ያስፈልጋል

5. (ሀ) ለጥምቀት ብቁ ለመሆን ሊወሰድ የሚገባው የመጀመሪያው እርምጃ ምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?

5 አንደኛውን እርምጃ መውሰድ ጀምረሃል። እንዴት? አንድ ወጥ የሆነ ሥርዓት በተከተለ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት እየቀሰምክ ነው። (ዮሐንስ 17:3) ሆኖም ገና ብዙ የምትማረው ነገር አለ። ክርስቲያኖች ‘በአምላክ ፈቃድ ትክክለኛ እውቀት መሞላት’ ይኖርባቸዋል። (ቈላስይስ 1:9) በይሖዋ ምሥክሮች የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህ በዚህ ረገድ በእጅጉ ይረዳሃል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መገኘት በጣም አስፈላጊ ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25) በስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ መገኘትህ ስለ አምላክ ያለህ እውቀት እንዲያድግ ይረዳሃል።

የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ለጥምቀት ብቁ ለመሆን የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ነው

6. ለጥምቀት ብቁ መሆን እንድትችል ምን ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያስፈልግሃል?

6 እርግጥ ነው፣ ለጥምቀት ብቁ ለመሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ ማወቅ አያስፈልግህም። ኢትዮጵያዊው የቤተ መንግሥት ባለ ሥልጣን የተወሰነ እውቀት ነበረው፤ ሆኖም አንዳንድ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎችን መገንዘብ እንዲችል እርዳታ አስፈልጎት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 8:30, 31) በተመሳሳይ አንተም ብዙ የምትማረው ነገር ይኖራል። እንዲያውም ስለ አምላክ የምትማረው ትምህርት ማብቂያ አይኖረውም። (መክብብ 3:11) ይሁን እንጂ ለጥምቀት ብቁ መሆን እንድትችል በቅድሚያ ቢያንስ ቢያንስ መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መማርና አምነህ መቀበል ያስፈልግሃል። (ዕብራውያን 5:12) እነዚህ ትምህርቶች ሙታን የሚገኙበትን ትክክለኛ ሁኔታ ማወቅን እንዲሁም የአምላክን ስምና የመንግሥቱን አስፈላጊነት መገንዘብን ይጨምራሉ።

7. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ በአንተ ላይ ምን ውጤት ሊያመጣ ይገባል?

7 ይሁንና “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት” ስለማይቻል እውቀት ብቻውን በቂ አይደለም። (ዕብራውያን 11:6) በጥንቷ የቆሮንቶስ ከተማ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያኖች የሚሰብኩትን መልእክት ሲሰሙ ‘አምነው እንደተጠመቁ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽልናል። (የሐዋርያት ሥራ 18:8) በተመሳሳይ አንተም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ  መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል እንደሆነ እንድታምን ሊያደርግህ ይገባል። በተጨማሪም የምታደርገው ጥናት አምላክ ቃል በገባቸው ተስፋዎችና የኢየሱስ መሥዋዕት ባለው የማዳን ኃይል ላይ እምነት እንዲኖርህ ሊረዳህ ይገባል።—ኢያሱ 23:14፤ የሐዋርያት ሥራ 4:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች መንገር

8. የተማርከውን ለሌሎች ለመንገር እንድትነሳሳ የሚያደርግህ ምንድን ነው?

8 እምነት በልብህ ውስጥ እያደገ ሲሄድ የተማርከውን ነገር ለራስህ ብቻ ይዘህ መቀመጥ አያስችልህም። (ኤርምያስ 20:9) ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ለሌሎች ሰዎች ለመናገር በእጅጉ ትነሳሳለህ።—2 ቆሮንቶስ 4:13

እምነት፣ የምታምንባቸውን ነገሮች ለሌሎች እንድትናገር ሊገፋፋህ ይገባል

9, 10. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለእነማን መንገር ልትጀምር ትችላለህ? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች በሚያካሂዱት የተደራጀ የስብከት ሥራ መካፈል የምትፈልግ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

9 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለዘመዶችህ፣ ለጓደኞችህ፣ ለጎረቤቶችህና ለሥራ ባልደረቦችህ በዘዴ መንገር ልትጀምር ትችላለህ። ከጊዜ በኋላ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያካሂዱት የተደራጀ የስብከት ሥራ የመካፈል ፍላጎት ያድርብሃል። በዚህ ጊዜ ይህን ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስን እያስተማረህ ካለው የይሖዋ ምሥክር ጋር በግልጽ ተወያይበት። መደበኛ በሆነ መንገድ በስብከቱ ሥራ መካፈል የምትችልበት ደረጃ ላይ ከደረስክ አንተና የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪህ ከሁለት የጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ተገናኝታችሁ ውይይት ማድረግ የምትችሉበት ዝግጅት ይደረጋል።

10 ይህም የአምላክን መንጋ ከሚጠብቁ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅ ያስችልሃል። (የሐዋርያት ሥራ 20:28፤ 1 ጴጥሮስ 5:2, 3) እነዚህ ሽማግሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች እንደተገነዘብክና እንደምታምንባቸው፣ አምላክ ካወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተህ እንደምትኖር እንዲሁም የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ልባዊ ፍላጎት እንዳለህ ካስተዋሉ ያልተጠመቅክ የምሥራቹ አስፋፊ ሆነህ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብቁ እንደሆንክ ያሳውቁሃል።

11. አንዳንዶች በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብቁ መሆን እንዲችሉ በቅድሚያ ምን ለውጦች ማድረግ ሊያስፈልጋቸው ይችላል?

 11 በሌላ በኩል ደግሞ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብቁ እንድትሆን በአኗኗርህና ባሉህ ልማዶች ረገድ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል። ይህም ከሌሎች ደብቀህ ያቆየሃቸውን አንዳንድ ልማዶች መተውን የሚጨምር ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ያልተጠመቅክ አስፋፊ ለመሆን ጥያቄ ከማቅረብህ በፊት እንደ ጾታ ብልግና፣ ስካር እንዲሁም አደገኛ ዕፆችንና መድኃኒቶችን አላግባብ መውሰድ የመሳሰሉ ከባድ ኃጢአቶችን ማስወገድ ይኖርብሃል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ገላትያ 5:19-21

ንስሐ መግባትና መለወጥ

12. ንስሐ መግባት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ለጥምቀት ብቁ እንድትሆን ልትወስዳቸው የሚገቡ ሌሎች እርምጃዎችም አሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ” ሲል ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19) ንስሐ መግባት ማለት በፈጸምከው ድርጊት ከልብ መጸጸት ማለት ነው። ብልሹ የሆነ ሕይወት የነበረው ሰው ንስሐ መግባቱ ተገቢ እንደሆነ የታወቀ ነው፤ ይሁንና በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በሥነ ምግባር ንጹሕ የሆነ ሕይወት የነበረው ሰውም ቢሆን ንስሐ መግባት ያስፈልገዋል። ለምን? ምክንያቱም ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ ስለሆነ የአምላክ ይቅርታ ያስፈልገዋል። (ሮሜ 3:23፤ 5:12) መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናትህ በፊት የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ አታውቅም ነበር። ይህን እውቀት ከማግኘትህ በፊት ሙሉ በሙሉ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምተህ ትኖር እንዳልነበረ የታወቀ ነው። ስለዚህ ንስሐ መግባት አስፈላጊ ነው።

13. መለወጥ ሲባል ምን ማለት ነው?

13 ንስሐ የገባ ሰው ደግሞ መለወጥ ወይም ‘ከመንገዱ መመለስ’ አለበት። መጸጸትህ ብቻውን በቂ አይሆንም። ቀደም ሲል የነበረህን አኗኗር እርግፍ አድርገህ መተውና ከአሁን ጀምሮ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ቁርጥ አቋም መውሰድ ያስፈልግሃል። ከመጠመቅህ በፊት ንስሐ መግባትና መለወጥ ያስፈልግሃል።

 ራስህን ለአምላክ መወሰን

14. ከመጠመቅህ በፊት ምን አስፈላጊ የሆነ እርምጃ መውሰድ አለብህ?

14 ከመጠመቅህ በፊት ልትወስደው የሚገባ ሌላ በጣም አስፈላጊ የሆነ እርምጃ አለ። ራስህን ለይሖዋ አምላክ መወሰን አለብህ።

በጸሎት አማካኝነት በግል ራስህን ለአምላክ ወስነሃል?

15, 16. ራስህን ለአምላክ መወሰን ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ሰው ይህን እንዲያደርግ የሚገፋፋው ነገርስ ምንድን ነው?

15 ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረብ ራስህን ለይሖዋ አምላክ ስትወስን ለዘላለም ለእሱ ብቻ ያደርክ ለመሆን ቃል ትገባለህ። (ዘዳግም 6:15) ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንዲህ ለማድረግ ቃል የሚገባው ለምንድን ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ሰው ከአንዲት ሴት ጋር ለትዳር መጠናናት ጀመረ እንበል። ይበልጥ እያወቃት ሲሄድና ጥሩ ጥሩ ባሕርያት እንዳሏት ሲገነዘብ የዚያኑ ያህል እየወደዳት ይሄዳል። ከጊዜ በኋላ ለጋብቻ እንደሚጠይቃት የታወቀ ነው። እርግጥ ነው፣ ትዳር መመሥረት ተጨማሪ ኃላፊነቶች ያስከትላል። ሆኖም ለእሷ ያለው ፍቅር ይህን ትልቅ እርምጃ እንዲወስድ ይገፋፋዋል።

16 አንተም ይሖዋን ስታውቀውና ስትወደው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እሱን ለማገልገል ወይም ያለምንም ገደብ እሱን ለማምለክ ትነሳሳለህ። የአምላክ ልጅ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል የሚፈልግ ሁሉ ‘ራሱን መካድ’ ይኖርበታል። (ማርቆስ 8:34) የግል ፍላጎቶቻችንና ግቦቻችን አምላክን ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ በምናደርገው ጥረት ምንም ዓይነት እንቅፋት እንዲፈጥሩብን ባለመፍቀድ ራሳችንን እንደካድን እናሳያለን። እንግዲያው ከመጠመቅህ በፊት የሕይወትህ ዋና ዓላማ የይሖዋ አምላክን ፈቃድ ማድረግ ሊሆን ይገባል።—1 ጴጥሮስ 4:2

ባይሳካልኝስ የሚለውን ፍርሃት ማሸነፍ

17. አንዳንዶች ራሳቸውን ለአምላክ ከመወሰን ወደኋላ የሚሉት ለምንድን ነው?

17 አንዳንዶች እንዲህ ያለ ከባድ እርምጃ መውሰድ ስለሚያስፈራቸው ራሳቸውን ለይሖዋ ለመወሰን ያመነታሉ። ራሳቸውን ለአምላክ ከወሰኑ በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ስለሚሰማቸው ይህን እርምጃ መውሰድ ያስፈራቸዋል። ሳይሳካልኝ ቀርቶ ይሖዋን ላሳዝን እችላለሁ ብለው ስለሚፈሩ ራሳቸውን ለአምላክ ከመወሰን መታቀብን ይመርጣሉ።

18. ራስህን ለይሖዋ እንድትወስን ሊገፋፋህ የሚችለው ምንድን ነው?

 18 ለይሖዋ ፍቅር እያደረብህ ስትሄድ ራስህን ለእሱ ለመወሰንና የገባኸውን ቃል ጠብቀህ ለመኖር ትነሳሳለህ። (መክብብ 5:4) ራስህን ለአምላክ ከወሰንክ በኋላ ‘ለጌታ እንደሚገባ መኖርና በሁሉም እሱን ደስ ማሰኘት’ እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። (ቈላስይስ 1:10) አምላክን ስለምትወደው ፈቃዱን ማድረግ በጣም ከባድ እንደሆነ አድርገህ አታስብም። “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም” ሲል ከጻፈው ከሐዋርያው ዮሐንስ ሐሳብ ጋር እንደምትስማማ አያጠራጥርም።—1 ዮሐንስ 5:3

19. ለአምላክ ራስህን መወሰን ሊያስፈራህ የማይገባው ለምንድን ነው?

19 ራስህን ለአምላክ ለመወሰን ፍጹም መሆን አያስፈልግህም። ይሖዋ ያለብህን የአቅም ገደብ የሚያውቅ ከመሆኑም በላይ ከምትችለው  በላይ እንድታደርግ አይጠብቅብህም። (መዝሙር 103:14) እንዲሳካልህ የሚፈልግ በመሆኑ ይረዳሃል እንዲሁም ይደግፍሃል። (ኢሳይያስ 41:10) በሙሉ ልብህ በይሖዋ ከታመንክ ‘ጎዳናህን ቀና እንደሚያደርገው’ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ምሳሌ 3:5, 6

ራስህን ለአምላክ መወሰንህን በጥምቀት ማሳየት

20. አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ በሚወስንበት ጊዜ ውሳኔው የግል ጉዳይ ሆኖ ሊቀር የማይችለው ለምንድን ነው?

20 አሁን የተወያየንባቸውን ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባትህ በጸሎት አማካኝነት በግልህ ራስህን ለይሖዋ እንድትወስን ሊረዳህ ይችላል።  ከዚህም በተጨማሪ አምላክን የሚወድ ሁሉ መዳን ይችል ዘንድ እምነቱን በሰዎች ፊት መግለጽ አለበት። (ሮሜ 10:10) ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ጥምቀት ለቀድሞው አኗኗራችን መሞትና የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሕያው መሆን ማለት ነው

21, 22. እምነትህን በሰዎች ፊት መግለጽ የምትችለው እንዴት ነው?

21 መጠመቅ እንደምትፈልግ ለጉባኤህ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ማሳወቅ ይኖርብሃል። የተወሰኑ ሽማግሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች የሚዳስሱ ጥያቄዎችን አብረውህ እንዲከልሱ ዝግጅት ያደርጋል። እነዚህ ሽማግሌዎች ለመጠመቅ ብቁ እንደሆንክ ከተስማሙ በቀጣዩ ትልቅ ስብሰባ ላይ መጠመቅ እንደምትችል ይነግሩሃል። * ብዙውን ጊዜ በእነዚህ የጥምቀት ሥነ ሥርዓቶች ላይ የጥምቀትን ትርጉም የሚከልስ ንግግር ይሰጣል። ከዚያም ተናጋሪው የጥምቀት ዕጩዎቹ በሙሉ ሁለት ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ይጋብዛቸዋል። ይህም እምነታቸውን በሰዎች ፊት በአንደበታቸው መግለጽ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ነው።

22 ራስህን ለአምላክ ወስነህ የይሖዋ ምሥክር እንደሆንክ በሰዎች ፊት በግልጽ የሚያሳውቀው ጥምቀቱ ራሱ ነው። የጥምቀት ዕጩዎች ራሳቸውን ለይሖዋ እንደወሰኑ በይፋ ለማሳየት ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ ጠልቀው ይወጣሉ።

ጥምቀትህ ያለው ትርጉም

23. “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” መጠመቅ ማለት ምን ማለት ነው?

23 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” እንደሚጠመቁ ተናግሯል። (ማቴዎስ 28:19) ይህ ማለት አንድ የጥምቀት ዕጩ የይሖዋ አምላክንና የኢየሱስ ክርስቶስን ሥልጣን አምኖ ይቀበላል ማለት ነው። (መዝሙር 83:18፤ ማቴዎስ 28:18) በተጨማሪም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም ኃይል የሚያከናውነውን ሥራ ይገነዘባል።—ገላትያ 5:22, 23፤ 2 ጴጥሮስ 1:21

24, 25. (ሀ) ጥምቀት ምን ያመለክታል? (ለ) መልስ ልናገኝለት የሚገባው ጥያቄ የትኛው ነው?

24 ይሁን እንጂ ጥምቀት እንዲሁ ውኃ ውስጥ ጠልቆ ከመውጣት  ያለፈ ትርጉም አለው። የአንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ተምሳሌት ነው። ውኃ ውስጥ መጥለቅህ ለቀድሞ አኗኗርህ እንደሞትክ ያሳያል። ከውኃው ውስጥ መውጣትህ ደግሞ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሕያው መሆንህን ያመለክታል። ከዚህም በተጨማሪ ራስህን የወሰንከው ለይሖዋ አምላክ እንጂ ለአንድ ሥራ፣ ዓላማ፣ ለሌሎች ሰዎች ወይም ለድርጅት እንዳልሆነ አስታውስ። ራስህን ለአምላክ መወሰንህና መጠመቅህ ከይሖዋ ጋር የቅርብ ወዳጅነትና ዝምድና እንደመሠረትክ የሚያሳይ ነው።—መዝሙር 25:14

25 ጥምቀት ለመዳን ዋስትና አይሆንም። ሐዋርያው ጳውሎስ “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 2:12) ጥምቀት የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ጥያቄው ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ መኖር የምትችለው እንዴት ነው? የሚለው ነው። የመጨረሻው ምዕራፍ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

^ አን.21 የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ በሚያካሂዷቸው ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ዘወትር የጥምቀት ሥነ ሥርዓቶች ይዘጋጃሉ።