በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ተጨማሪ ክፍል

የዳንኤል ትንቢት መሲሑ የሚመጣበትን ጊዜ አስቀድሞ የተናገረው እንዴት ነው?

የዳንኤል ትንቢት መሲሑ የሚመጣበትን ጊዜ አስቀድሞ የተናገረው እንዴት ነው?

ነቢዩ ዳንኤል የኖረው ኢየሱስ ከመወለዱ ከ500 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ነው። ያም ሆኖ ይሖዋ፣ ኢየሱስ መሲሕ ወይም ክርስቶስ ሆኖ የሚቀባበትን ወይም የሚሾምበትን ጊዜ በትክክል ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል መረጃ ለዳንኤል ገልጦለት ነበር። ዳንኤል “ይህንን ዕወቅ፤ አስተውለውም፤ ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገዥው መሲሕ  እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ፣ ሰባት ሱባዔና ሥልሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል” ተብሎ ተነግሮት ነበር።—ዳንኤል 9:25

መሲሑ የሚመጣበትን ጊዜ ለይተን ለማወቅ በቅድሚያ ወደ መሲሑ የሚያደርሰን ዘመን መቼ እንደጀመረ ማወቅ ያስፈልገናል። በትንቢቱ መሠረት ይህ ዘመን የሚጀምረው “ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ” በሚወጣበት ጊዜ ነው። ‘ዐዋጁ የወጣው’ መቼ ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ነህምያ እንደገለጸው የኢየሩሳሌም ግንቦች ዳግመኛ እንዲገነቡ ዐዋጅ የወጣው “በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት በሃያኛው ዓመት” ነው። (ነህምያ 2:1, 5-8) የአርጤክስስ የግዛት ዘመን የጀመረው በ475 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደሆነ ታሪክ ጸሐፊዎች አረጋግጠዋል። ስለዚህ 20ኛው የግዛት  ዓመቱ 455 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። አሁን ዳንኤል መሲሑን አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት መፈጸም የጀመረው በ455 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደሆነ ተገንዝበናል።

ዳንኤል “ገዥው መሲሕ” እስከሚመጣበት ወቅት ድረስ ያለው የጊዜ ርዝማኔ ምን ያህል እንደሆነ አመልክቷል። ትንቢቱ “ሰባት ሱባዔና ሥልሳ ሁለት ሱባዔ” በድምሩ 69 ሱባዔ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ ጊዜ ምን ያህል ርዝማኔ አለው? በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እነዚህ ሱባዔዎች ሰባት ቀናትን ያቀፉ ሳምንታት ሳይሆኑ የዓመታት ሳምንታት እንደሆኑ ይገልጻሉ። ስለዚህ እያንዳንዱ ሳምንት ሰባት ዓመታትን ይወክላል ማለት ነው። ይህ የዓመታት ሳምንታት ወይም ዓመታትን በሰባት ዓመት የመክፈል ጽንሰ ሐሳብ በጥንት ዘመን ለነበሩት አይሁዶች አዲስ አልነበረም። ለምሳሌ ያህል በየሰባት ዓመቱ የሰንበት ዓመት ያከብሩ ነበር። (ዘፀአት 23:10, 11) ስለዚህ በትንቢት የተነገሩት 69 ሳምንታት እያንዳንዳቸው 7 ዓመታትን ያቀፉ 69 የዓመታት ክፍሎች ወይም በድምሩ 483 ዓመታት ናቸው።

አሁን የቀረን ነገር መቁጠር ብቻ ነው። ከ455 ከክርስቶስ ልደት በፊት ተነስተን 483 ዓመታት ብንቆጥር 29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ላይ እንደርሳለን። ይህ ኢየሱስ የተጠመቀበትና መሲሕ የሆነበት ዓመት ነው! * (ሉቃስ 3:1, 2, 21, 22) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የተፈጸመበት ሁኔታ እጅግ አያስደንቅም?

^ አን.2 ከ455 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ 1 ከክርስቶስ ልደት በፊት ድረስ 454 ዓመታት አሉ። ከ1 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ 1 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ አንድ ዓመት ነው። (ዜሮ የሚባል ዓመት የለም።) ከ1 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከ 29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ 28 ዓመት ነው። እነዚህን ሦስት አኃዞች ስንደምር 483 ዓመታት ይሆናሉ። ኢየሱስ ‘የተገደለው’ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ማለትም በ70ኛው የዓመታት ሳምንት ነው። (ዳንኤል 9:24, 26) የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 እና ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ከገጽ 899-901 ተመልከት። ሁለቱም ጽሑፎች የተዘጋጁት በይሖዋ ምሥክሮች ነው።