በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ተጨማሪ ክፍል

“ነፍስ” እና “መንፈስ”—የእነዚህ ቃላት ትርጉም ምንድን ነው?

“ነፍስ” እና “መንፈስ”—የእነዚህ ቃላት ትርጉም ምንድን ነው?

“ነፍስ” እና “መንፈስ” የሚሉትን ቃላት ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ነገር ምንድን ነው? ብዙ ሰዎች እነዚህ ቃላት በውስጣችን የምትኖርን በዓይን የማትታይና የማትሞት ረቂቅ ነገር እንደሚያመለክቱ አድርገው ያስባሉ። አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ይህች ረቂቅ ነገር ከሰውየው ሥጋ ተለይታ መኖሯን ትቀጥላለች ብለው ያምናሉ። ይህ እምነት በእጅጉ የተስፋፋ በመሆኑ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ እንደማያስተምር ሲገነዘቡ በጣም ይገረማሉ። ታዲያ የአምላክ ቃል በሚለው መሠረት ነፍስ ምንድን ነው? መንፈስስ ምንድን ነው?

“ነፍስ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት እንዴት ነው?

በመጀመሪያ እስቲ ነፍስ ምን እንደሆነ እንመልከት። አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በመጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥና በግሪክኛ እንደሆነ ሳታስታውስ አትቀርም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ ነፍስ ሲጽፉ የተጠቀሙት ነፈሽ የተባለውን የዕብራይስጥ ቃል ወይም ፕስኺ የተባለውን የግሪክኛ ቃል ነው። እነዚህ ሁለት ቃላት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከ800 ጊዜ በላይ የሚገኙ ሲሆን የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም እነዚህን ቃላት በሁሉም ቦታዎች ላይ “ነፍስ” እያለ ተርጉሟቸዋል። “ነፍስ” ወይም “ነፍሳት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበትን መንገድ ስትመረምር ይህ ቃል (1) ሰዎችን፣ (2) እንስሳትን ወይም (3) አንድ ሰው አሊያም እንስሳ ያለውን ሕይወት እንደሚያመለክት  በሚገባ ትረዳለህ። እነዚህን ሦስት ትርጉሞች የሚያሳዩ አንዳንድ ጥቅሶችን እንመልከት።

ሰዎች። ‘እነዚህ ነፍሳት በኖኅ ዘመን በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ።’ (1 ጴጥሮስ 3:20) እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ነፍሳት” የሚለው ቃል ሰዎችን ማለትም ኖኅን፣ ሚስቱን፣ ሦስት ወንዶች ልጆቹንና ሚስቶቻቸውን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። ዘፀአት 16:16 [የ1954 ትርጉም] እስራኤላውያን መና የሚሰበስቡበትን ሁኔታ በተመለከተ የተሰጠውን መመሪያ ይጠቅሳል። “በድንኳኑ ባሉት ነፍሶች ቁጥር . . . ውሰዱ” ተብለው ታዘው ነበር። ስለዚህ የሚሰበሰበው መና መጠን በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ባለው የሰዎች ቁጥር ላይ የተመካ ነበር። “ነፍስ” ወይም “ነፍሳት” የሚለው ቃል ሰውን አሊያም ሰዎችን ለማመልከት እንደተሠራበት የሚያሳዩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ዘፍጥረት 46:18፤ ኢያሱ 11:11፤ የሐዋርያት ሥራ 27:37 እና ሮሜ 13:1 ላይ ይገኛሉ። (እነዚህ ጥቅሶች የተወሰዱት ከ1954 ትርጉም ነው።)

እንስሳት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የፍጥረት ዘገባ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርም አለ:- ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ፣ ወፎችም ከምድር በላይ ከሰማይ ጠፈር በታች ይብረሩ። እግዚአብሔርም አለ:- ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን [“ሕያው ነፍስ፣” የ1879 ትርጉም] እንደ ወገኑ፣ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፣ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ።” (ዘፍጥረት 1:20, 24 የ1954 ትርጉም) እዚህ ጥቅስ ላይ ዓሣ፣ የቤት እንስሳትና የዱር አራዊት በአንድ ቃል “ነፍስ” ተብለው ተጠርተዋል። ወፎችና ሌሎች እንስሳት በዘፍጥረት 9:12 [የ1954 ትርጉም]፤ በዘሌዋውያን 11:46 [የ1879 ትርጉም] እና በዘኍልቁ 31:28 [የ1879 ትርጉም] ላይ ነፍሳት ተብለው ተጠርተዋል።

የሰው ሕይወት። አንዳንድ ጊዜ “ነፍስ” የሚለው ቃል የአንድን ሰው ሕይወት ያመለክታል። ይሖዋ ሙሴን “ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋል” ብሎት ነበር። (ዘፀአት 4:19 የ1954 ትርጉም) የሙሴ ጠላቶች ይሹ የነበረው ነገር ምንድን ነው? የሙሴን ሕይወት ማጥፋት ይፈልጉ ነበር። ከዚህ ቀደም ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ራሔል ብንያም የተባለውን ልጅዋን ስትወልድ ‘ሕይወቷ እንዳለፈች [‘ነፍሷ እንደወጣች፣’ የ1954 ትርጉም]’ ይናገራል። (ዘፍጥረት 35:16-19) በዚህ ወቅት ራሔል ሞታለች። የሚከተሉትን የኢየሱስ ቃላትም ተመልከት:- “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።” (ዮሐንስ 10:11 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ ነፍሱን ወይም ሕይወቱን ለሰው ዘር ሰጥቷል። በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ “ነፍስ” የሚለው ቃል  የሰውን ሕይወት እንደሚያመለክት በግልጽ መረዳት ይቻላል። “ነፍስ” የሚለው ቃል የሰውን ሕይወት ለማመልከት እንደተሠራበት የሚያሳዩ ተጨማሪ ምሳሌዎችን 1 ነገሥት 17:17-23፤ ማቴዎስ 10:39 [የ1954 ትርጉም]፤ ዮሐንስ 15:13 [የ1954 ትርጉም] እና የሐዋርያት ሥራ 20:10 [የ1954 ትርጉም] ላይ ታገኛለህ።

የአምላክን ቃል ይበልጥ ስትመረምር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የማይሞት” ወይም “ዘላለማዊ” የሚሉት ቃላት “ነፍስ” ከሚለው ቃል ጋር ተያይዘው የተገለጹበት ቦታ እንደሌለ ትገነዘባለህ። ከዚህ ይልቅ ቅዱሳን ጽሑፎች ነፍስ እንደሚሞት ይገልጻሉ።—ሕዝቅኤል 18:4, 20

“መንፈስ” የሚለው ቃል ምን ያመለክታል?

አሁን ደግሞ “መንፈስ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት እንደተሠራበት እንመልከት። አንዳንድ ሰዎች “መንፈስ” የሚለው ቃል “ነፍስ” ከሚለው ቃል ጋር አንድ ዓይነት ትርጉም እንዳለው አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ይህ ትክክል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “መንፈስ” እና “ነፍስ” የሚሉት ቃላት ሁለት የተለያዩ ነገሮችን እንደሚያመለክቱ በግልጽ ያሳያል። ልዩነታቸው ምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ “መንፈስ” ሲጽፉ የተጠቀሙት ሩአህ የተባለውን የዕብራይስጥ ቃል ወይም ፕኒውማ የተባለውን የግሪክኛ ቃል ነው፤ የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ቃል “እስትንፋስ” ብሎም ተርጉሞታል። ቅዱሳን ጽሑፎች ራሳቸው የሩአህ እና የፕኒውማ ትክክለኛ ትርጉም ምን እንደሆነ ይጠቁሙናል። ለምሳሌ ያህል መዝሙር 104:29 “እስትንፋሳቸውንም [ሩአህ] ስትወስድባቸው ይሞታሉ፤ ወደ ዐፈራቸውም ይመለሳሉ” ሲል ይገልጻል። ያዕቆብ 2:26 ደግሞ “ከመንፈስ [ፕኒውማ] የተለየ ሥጋ የሞተ [ነው]” ይላል። እነዚህ ጥቅሶች ላይ የገቡት ሩአህ እና ፕኒውማ የተባሉት ቃላት እንዲሁ አንድ ሰው የሚተነፍሰውን አየርም ሆነ ነፍስን የሚያመለክቱ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ሥጋን ሕያው የሚያደርገውን ኃይል በምሳሌያዊ ሁኔታ የሚያመለክቱ ናቸው። ይህ መንፈስ ወይም የሕይወት ኃይል የሌለው ሥጋ የሞተ ነው። ይህን ሁኔታ ይሖዋ በኖኅ ዘመን የደረሰውን የጥፋት ውኃ አስመልክቶ ከተናገረው ቃል መረዳት ይቻላል:- “እኔም ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ [ሩአህ] ያለባቸውን ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ለማጥፋት እነሆ፤ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ።” (ዘፍጥረት 6:17፤ 7:15, 22) ስለዚህ “መንፈስ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ የሚያንቀሳቅሰውን በዓይን የማይታይ ኃይል ነው።

ነፍስና መንፈስ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። አንድ ሬዲዮ መሥራት እንዲችል የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሰውነትም መንቀሳቀስ እንዲችል መንፈስ ያስፈልገዋል። ነጥቡን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ፣ አንድ ትንሽ ሬዲዮ ውስጥ  ባትሪ ጨምረህ ሬዲዮውን ስትከፍተው በባትሪዎቹ ውስጥ የታመቀው የኤሌክትሪክ ኃይል ሬዲዮው እንዲሠራ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ ባትሪ ከሌለው ሬዲዮው ሊሠራ አይችልም። ከኤሌክትሪክ ሶኬት ላይ የተነቀለ ሌላ ዓይነት ሬዲዮም ቢሆን እንዲሁ ነው። በተመሳሳይም ሰውነታችንን ሕያው የሚያደርገው ኃይል መንፈስ ነው። ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል መንፈስም ምንም ዓይነት ስሜት የሌለው ከመሆኑም በላይ ሊያስብ አይችልም። የራሱ የሆነ ስብዕና ወይም ባሕርይ የሌለው ኃይል ነው። ሆኖም መዝሙራዊው እንደገለጸው ሰውነታችን ይህ መንፈስ ወይም የሕይወት ኃይል ከሌለው ‘ይሞታል፤ ወደ ዐፈርም ይመለሳል።’

መክብብ 12:7 የሰውን ሞት አስመልክቶ ሲናገር ‘[የሥጋው] ዐፈር ወደ መጣበት መሬት ይመለሳል፣ መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል’ ይላል። መንፈሱ ወይም የሕይወቱ ኃይል ከሥጋው ሲለይ ሥጋው ይሞትና ወደመጣበት መሬት ይመለሳል። በአንጻሩ ደግሞ የሕይወቱ ኃይል ወደመጣበት ማለትም ወደ አምላክ ይመለሳል። (ኢዮብ 34:14, 15፤ መዝሙር 36:9) እንዲህ ሲባል ግን የሕይወቱ ኃይል ቃል በቃል ወደ ሰማይ ይሄዳል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው ሲሞት የወደፊት ሕይወት ተስፋው ሙሉ በሙሉ በይሖዋ አምላክ ላይ የተመካ መሆኑን የሚያመለክት ነው። በሌላ አነጋገር ሕይወቱ በአምላክ እጅ ነው ማለት ነው። አንድ ሰው ዳግመኛ ሕያው መሆን እንዲችል መንፈሱን ወይም የሕይወቱን ኃይል መልሶ ሊሰጠው የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።

አምላክ “መቃብር ውስጥ” ላሉት ሙታን ይህን የሚያደርግ መሆኑን ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! (ዮሐንስ 5:28, 29) በትንሣኤ ወቅት ይሖዋ በሞት ላንቀላፉት ሰዎች አዲስ ሥጋዊ አካል የሚፈጥርላቸው ከመሆኑም በላይ መንፈስ ወይም የሕይወት ኃይል በመስጠት ይህን ሥጋዊ አካል ሕያው ያደርገዋል። ያ ጊዜ ምንኛ አስደሳች ይሆናል!

“ነፍስ” እና “መንፈስ” የሚሉትን ቃላት በተመለከተ ተጨማሪ ግንዛቤ ማግኘት ከፈለግክ ስንሞት ምን እንሆናለን? በተባለው ብሮሹር እና ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 374-382 ላይ ጠቃሚ የሆነ መረጃ ማግኘት ትችላለህ። ሁለቱም ጽሑፎች የተዘጋጁት በይሖዋ ምሥክሮች ነው።