በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 8

አምላክ ንጹሕ የሆኑ ሰዎችን ይወዳል

አምላክ ንጹሕ የሆኑ ሰዎችን ይወዳል

“ከንጹሑ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ።”መዝሙር 18:26

1-3. (ሀ) አንዲት እናት ሁልጊዜ የልጇን ንጽሕና የምትጠብቀው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ አገልጋዮቹ ንጹሕ እንዲሆኑ የሚፈልገው ለምንድን ነው? እኛስ ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

አንዲት እናት ልጇን ይዛ ለመውጣት እያዘጋጀችው ነው። ገላውን አጥባ ንጹሕ ልብስ አልብሳዋለች። ንጽሕና ለልጇ ጤንነት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ታውቃለች። በተጨማሪም የልጇ አለባበስና ንጽሕና ስለ ወላጆቹ የሚናገረው ነገር እንዳለ ትገነዘባለች።

2 የሰማዩ አባታችን ይሖዋ አገልጋዮቹ ንጹሕ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ “ከንጹሑ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ” ይላል። * (መዝሙር 18:26) ይሖዋ ይወደናል፤ ንጽሕናችንን መጠበቃችንም በእጅጉ እንደሚጠቅመን ያውቃል። በተጨማሪም ምሥክሮቹ እንደመሆናችን መጠን እሱን እንድናስከብርና እንድናስመሰግን ይፈልጋል። በእርግጥም ንጹሕ የሆነው አለባበሳችንና መልካም ምግባራችን ይሖዋንና ቅዱስ ስሙን የሚያስነቅፍ ሳይሆን የሚያስከብር ይሆናል።ሕዝቅኤል 36:22፤ 1 ጴጥሮስ 2:12

3 አምላክ ንጹሕ የሆኑ ሰዎችን እንደሚወድ ማወቃችን ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ ያነሳሳናል። አምላክን ስለምንወደው አኗኗራችን እሱን የሚያስከብር እንዲሆን እንፈልጋለን። በተጨማሪም ከእሱ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር እንፈልጋለን። እንግዲያው ንጹሕ መሆን የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ፣ ንጹሕ መሆን ምን ነገሮችን እንደሚያካትትና ንጽሕናችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመርምር። እንዲህ ማድረጋችን በአንዳንድ ዘርፎች ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልገን እንደሆነ ለማየት ይረዳናል።

ንጹሕ መሆን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

4, 5. (ሀ) ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ንጹሕ መሆኑ በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ የተንጸባረቀው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ እኛን የሚመራበት አንደኛው መንገድ፣ ራሱ ምሳሌ በመሆን ነው። በዚህም ምክንያት ቃሉ “አምላክን የምትኮርጁ ሁኑ” ሲል ያሳስበናል። (ኤፌሶን 5:1) ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት፣ የምናመልከው አምላክ ይሖዋ በማንኛውም ረገድ ንጹሕና ቅዱስ መሆኑ ነው።ዘሌዋውያን 11:44, 45

5 የሚታዩት የይሖዋ ፍጥረታት ብዙዎቹን ባሕርያቱን እንደሚያንጸባርቁ ሁሉ ንጹሕ መሆኑንም በግልጽ ያሳያሉ። (ሮም 1:20) ምድር የተፈጠረችው የሰው ልጆች ንጹሕ መኖሪያ እንድትሆን ታስባ ነው። ይሖዋ የአየሩንና የውኃውን ንጽሕና የሚጠብቁ የተለያዩ ዑደቶችን አዘጋጅቷል። በዓይን የማይታዩ አንዳንድ ነፍሳት ቆሻሻዎችን ጉዳት ወደማያስከትሉ ነገሮች በመቀየር የንጽሕና አገልግሎት ይሰጣሉ። ሳይንቲስቶች፣ የሰው ልጅ ራስ ወዳድና ስግብግብ በመሆኑ ምክንያት የተፈጠሩትን የነዳጅ ዘይት ፍሳሾችና ሌሎች ብክለቶች ለማስወገድ በእነዚህ ፍጥረታት ተጠቅመዋል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የንጽሕና ጉዳይ ‘የምድርን ፈጣሪ’ ያሳስበዋል። (ኤርምያስ 10:12) እኛንም ሊያሳስበን ይገባል።

6, 7. የሙሴ ሕግ ይሖዋን የሚያመልኩ ሁሉ ንጹሕ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አጉልቶ ያሳየው እንዴት ነው?

6 ንጽሕናችንን መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነበት ሌላው ምክንያት ልዑሉ ገዥያችን ይሖዋ አምላኪዎቹ ንጹሕ እንዲሆኑ ስለሚፈልግ ነው። ይሖዋ ለእስራኤላውያን በሰጠው ሕግ ውስጥ ንጽሕናና አምልኮ የማይነጣጠሉ ነገሮች ነበሩ። በስርየት ቀን ሊቀ ካህናቱ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁለት ጊዜ እንዲታጠብ ሕጉ ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 16:4, 23, 24) ሥነ ሥርዓቱን እንዲፈጽሙ የተመደቡት ካህናትም ቢሆኑ ለይሖዋ መሥዋዕት ከማቅረባቸው በፊት እጃቸውንና እግራቸውን እንዲታጠቡ ይጠበቅባቸው ነበር። (ዘፀአት 30:17-21፤ 2 ዜና መዋዕል 4:6) ሕጉ አካላዊ ንጽሕናንና አምልኮን የሚያጎድፉ እንዲሁም የሚያረክሱ 70 የሚያክሉ ምክንያቶችን ዘርዝሯል። አንድ እስራኤላዊ ረክሶ እያለ በማንኛውም ዓይነት የአምልኮ ሥርዓት እንዲካፈል የማይፈቀድለት ሲሆን ይህን አድርጎ ቢገኝ በሞት ይቀጣ ነበር። (ዘሌዋውያን 15:31) ገላውንና ልብሶቹን ማጠብን የሚጨምረውን የመንጻት ሥርዓት ለመፈጸም እምቢተኛ የሆነ ማንም ሰው ‘ከማኅበረሰቡ ተለይቶ እንዲጠፋ’ ይደረግ ነበር።ዘኍልቍ 19:17-20

7 እኛ በሙሴ ሕግ ሥር ባንሆንም ስለ ሕጉ ማወቃችን አምላክ ስለ አንዳንድ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት እንድናስተውል ይረዳናል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሕጉ አምላክን የሚያመልኩ ሁሉ ንጹሕ መሆን እንዳለባቸው ያጎላል። ይሖዋ አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) አምልኳችን በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፈለግን “ንጹሕና ያልረከሰ” መሆን አለበት። (ያዕቆብ 1:27) ስለሆነም በዚህ ረገድ ምን እንደሚጠብቅብን ማወቅ ያስፈልገናል።

በአምላክ ዓይን ንጹሕ መሆን ምንን ይጨምራል?

8. ይሖዋ ንጹሕ እንድንሆን የሚፈልግብን በየትኞቹ ዘርፎች ነው?

8 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ንጹሕ መሆን የሚለው ሐሳብ የሚያመለክተው አካላዊ ንጽሕናን ብቻ አይደለም። በአምላክ ዓይን ንጹሕ መሆን ሁሉንም የሕይወታችንን ዘርፎች ይነካል። ይሖዋ በአራት መሠረታዊ ዘርፎች ማለትም በመንፈሳዊ፣ በሥነ ምግባር፣ በአእምሮና በአካል ንጹሕ እንድንሆን ይፈልግብናል። እስቲ እያንዳንዳቸው ምን ትርጉም እንዳላቸው እንመርምር።

9, 10. በመንፈሳዊ ንጹሕ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? እውነተኛ ክርስቲያኖች ከምን ይርቃሉ?

9 መንፈሳዊ ንጽሕና። በአጭር አነጋገር በመንፈሳዊ ንጹሕ መሆን ማለት እውነተኛውን አምልኮ ሐሰት ከሆነው ጋር አለመቀላቀል ማለት ነው። እስራኤላውያን ከባቢሎን ወጥተው ወደ ኢየሩሳሌም በተመለሱበት ወቅት “ከዚያ ውጡ፤ ርኵስ ነገር አትንኩ፤ . . . ንጹሓንም ሁኑ” ሲል አምላክ የሰጣቸውን ማሳሰቢያ መፈጸም ነበረባቸው። (ኢሳይያስ 52:11) እስራኤላውያን ወደ አገራቸው የተመለሱበት ዋነኛ ምክንያት የይሖዋን አምልኮ እንደገና ለማቋቋም ነበር። ይህ አምልኮ ንጹሕ መሆን፣ ማለትም አምላክን ከሚያዋርድ ከማንኛውም ዓይነት የባቢሎን ሃይማኖት ትምህርቶች፣ ልማዶችና ድርጊቶች የጸዳ መሆን ነበረበት።

10 ዛሬም እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በሐሰት ሃይማኖት እንዳንበከል ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። (1 ቆሮንቶስ 10:21) የሐሰት ሃይማኖት ተጽዕኖ በሁሉም ቦታ ስለሚገኝ በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በብዙ አገሮች ያሉ የተለያዩ ባሕሎች ወይም ልማዶች፣ ድርጊቶችና ሥነ ሥርዓቶች ‘ከሞት በኋላ በሕይወት የምትኖር ረቂቅ ነገር በውስጣችን አለች’ እንደሚለው ካሉት የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ጋር የተሳሰሩ ናቸው። (መክብብ 9:5, 6, 10) እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ጋር ግንኙነት ካላቸው ባሕሎች ወይም ልማዶች ይርቃሉ። * መጽሐፍ ቅዱስ ለንጹሕ አምልኮ ያወጣውን መሥፈርት በመከተል ረገድ ሌሎች አቋማችንን እንድናላላ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩብን አንፈቅድም።የሐዋርያት ሥራ 5:29

11. የሥነ ምግባር ንጽሕና ምንን ያካትታል? በዚህ ረገድ ንጽሕናችንን መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 የሥነ ምግባር ንጽሕና። በሥነ ምግባር ንጹሕ መሆን ከማንኛውም ዓይነት የጾታ ብልግና መራቅን ይጨምራል። (ኤፌሶን 5:5) የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖራችን እጅግ አስፈላጊ ነው። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንደምንመለከተው ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ከፈለግን ‘ከዝሙት መሸሽ’ ይኖርብናል። ዝሙት የሚፈጽሙ ሰዎች ንስሐ ካልገቡ “የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10, 18) በአምላክ ዓይን እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ‘በርኩሰታቸው አስጸያፊ ከሆኑት’ መካከል የሚፈረጁ ናቸው። ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን መጠበቅ ካልቻሉም “ዕጣ ፈንታቸው . . . ሁለተኛው ሞት” ነው።ራእይ 21:8

12, 13. በሐሳብና በድርጊት መካከል ምን ዝምድና አለ? የአእምሯችንን ንጽሕና መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

12 የአእምሮ ንጽሕና። ሐሳብ ወደ ድርጊት ይመራል። መጥፎ ሐሳቦችን በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ የምናውጠነጥን ከሆነ ይዋል ይደር እንጂ ንጹሕ ያልሆነ ድርጊት መፈጸማችን አይቀርም። (ማቴዎስ 5:28፤ 15:18-20) ይሁንና አእምሯችንን በንጹሕ ሐሳቦች የምንሞላ ከሆነ በንጹሕ ሥነ ምግባር ለመመላለስ እንገፋፋለን። (ፊልጵስዩስ 4:8) የአእምሯችንን ንጽሕና መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ አስተሳሰባችንን ሊበክል ከሚችል ከማንኛውም ዓይነት መዝናኛ መራቅ ያስፈልገናል። * በተጨማሪም የአምላክን ቃል አዘውትረን በማጥናት አእምሯችንን ንጹሕ በሆኑ ሐሳቦች መሙላት እንችላለን።መዝሙር 19:8, 9

13 ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር በመንፈሳዊ፣ በሥነ ምግባርና በአእምሮ ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖራችን አስፈላጊ ነው። እነዚህ የንጽሕና ዘርፎች በዚህ መጽሐፍ ሌሎች ምዕራፎች ላይ በስፋት ይብራራሉ። አሁን ግን አራተኛውን ዘርፍ ማለትም አካላዊ ንጽሕናን እንመርምር።

አካላዊ ንጽሕናችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

14. አካላዊ ንጽሕና ሌሎችን የማይመለከት የግል ጉዳይ ያልሆነው ለምንድን ነው?

14 አካላዊ ንጽሕና የሰውነታችንን፣ የአካባቢያችንንና የምንጠቀምባቸውን ነገሮች ንጽሕና መጠበቅን ይጨምራል። እንዲህ ያለው ንጽሕና ማንንም የማይመለከት የግል ጉዳይ ነው? ለይሖዋ አምላኪዎች እንደዚያ አይደለም። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው አካላዊ ንጽሕናችንን መጠበቃችን ለእኛ ስለሚጠቅመን ብቻ ሳይሆን ይሖዋን ሊያስከብረው ወይም ሊያስነቅፈው ስለሚችል የሰማዩን አባታችንን ያሳስበዋል። በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰውን ምሳሌ አስብ። አንድ ልጅ ሁልጊዜ እንደቆሸሸና እንደተዝረከረከ ብታየው ‘ምን ዓይነት ወላጆች ቢኖሩት ነው’ ብለህ ታስብ የለም? እኛም አለባበሳችን ወይም አኗኗራችን በማንኛውም መንገድ በሰማዩ አባታችን ላይ ነቀፌታ የሚያመጣ ወይም ሰዎች ለምንሰብከው መልእክት ያላቸውን ግምት የሚቀንስ እንዲሆን አንፈልግም። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል:- “አገልግሎታችን እንከን እንዳይገኝበት በምንም መንገድ ማሰናከያ የሚሆን ነገር እንዲኖር አናደርግም፤ ከዚህ ይልቅ በሁሉም መንገድ ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን።” (2 ቆሮንቶስ 6:3, 4) ታዲያ አካላዊ ንጽሕናችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

15, 16. ንጽሕናን በመጠበቅ ረገድ ጥሩ ልማድ ማዳበር ምንን ይጨምራል? ልብሳችንንስ እንዴት መያዝ ይኖርብናል?

15 የግል ንጽሕናና አለባበስ። የሰዎች ባሕልና የኑሮ ሁኔታ ከአገር ወደ አገር የተለያየ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ሰውነታችንን አዘውትረን ለመታጠብና የራሳችንንም ሆነ የልጆቻችንን ንጽሕና ለመጠበቅ የሚያስፈልግ በቂ ሳሙናና ውኃ ማግኘት አያቅተንም። ንጽሕናን በመጠበቅ ረገድ ጥሩ ልማድ ማዳበር ምግብ ከመመገባችን ወይም ከማዘጋጀታችን በፊት፣ ከመጸዳጃ ቤት ስንወጣ እንዲሁም የሕፃን ልጅ ሽንት ጨርቅ ከቀየርን በኋላ እጃችንን በሳሙናና በውኃ መታጠብን ይጨምራል። እጃችንን በሳሙናና በውኃ መታጠብ ከበሽታ ሊጠብቀን፣ እንዲያውም ከሞት እንኳ ሊያድነን ይችላል። በተጨማሪም ጎጂ ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች እንዳይዛመቱ ሊያደርግ ስለሚችል ለተቅማጥ መንስኤ ከሚሆኑ በሽታዎች ይጠብቀናል። የፍሳሽ ማስወገጃ በሌላቸው መኖሪያ ቤቶች የሚኖሩ ሰዎች የጥንቶቹ እስራኤላውያን ያደርጉ እንደነበረው ቆሻሻዎችን በመቅበር ማስወገድ ይችላሉ።ዘዳግም 23:12, 13

16 ልብሳችንም ንጹሕና ያማረ እንዲሆን ዘወትር መታጠብ ይኖርበታል። የአንድ ክርስቲያን ልብስ ውድ ዋጋ የወጣበት ወይም አዲሱን ፋሽን የተከተለ መሆን አያስፈልገውም፤ ሆኖም ሥርዓታማ፣ ንጹሕና ልከኛ መሆን ይገባዋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ አለባበሳችን ‘አዳኛችን የሆነውን አምላክ ትምህርት የሚያስውብ እንዲሆን’ እንፈልጋለን።ቲቶ 2:10

17. ቤታችንም ሆነ ንብረቶቻችን ንጹሕና በሥርዓት የተያዙ መሆን የሚገባቸው ለምንድን ነው?

17 መኖሪያ ቤታችን፣ አካባቢያችንና ንብረቶቻችን። መኖሪያ ቤታችን ልዩ የሆነ ውበት ያለው ላይሆን ይችላል። ቢሆንም ሁኔታው በፈቀደ መጠን ንጹሕና በሥርዓት የተያዘ መሆን ይገባዋል። በተመሳሳይም ወደ ስብሰባና ወደ መስክ አገልግሎት ለመሄድ መኪና የምንጠቀም ከሆነ መኪናችን ውጭውም ሆነ ውስጡ ንጹሕ እንዲሆን የተቻለንን እናደርጋለን። ቤታችንንና ንብረታችንን በንጽሕና መያዛችን በራሱ ምሥክርነት እንደሚሰጥ አንርሳ። ደግሞስ፣ ይሖዋ ንጹሕ አምላክ እንደሆነ፣ ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን እንደሚያጠፋ፣’ እንዲሁም መንግሥቱ መኖሪያችን የሆነችውን ምድር በቅርቡ ወደ ገነትነት እንደሚለውጥ እናስተምር የለም? (ራእይ 11:18፤ ሉቃስ 23:43) በእርግጥም ቤታችንንና ንብረቶቻችንን የምንይዝበት መንገድ ንጽሕናን በመጠበቅ ረገድ አሁንም እንኳ ለመጪው አዲስ ዓለም የሚስማማ ጥሩ ልማድ እንዳለን የሚያሳይ እንዲሆን እንፈልጋለን።

አካላዊ ንጽሕና ሰውነታችንንና የምንጠቀምባቸውን ነገሮች ማጽዳትን ይጨምራል

18. ለመንግሥት አዳራሻችን አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 ለአምልኮ የምንጠቀምባቸው ቦታዎች። ለይሖዋ ያለን ፍቅር በአካባቢያችን የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ለሆነው ለመንግሥት አዳራሻችን አክብሮት እንድናሳይ ይገፋፋናል። ወደ መንግሥት አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚመጡ ሰዎች ለምንሰበሰብበት ቦታ ጥሩ ስሜት እንዲያድርባቸው እንፈልጋለን። አዳራሹ ምንጊዜም የሚያምርና የሚማርክ እንዲሆን ከተፈለገ ዘወትር መጽዳትና መጠገን ያስፈልገዋል። በተቻለን መጠን የመንግሥት አዳራሻችንን ጥሩ አድርገን በመያዝ ለአምልኮ የምንጠቀምበትን ቦታ በአክብሮት እንደምንመለከተው እናሳያለን። የመንግሥት አዳራሻችንን ለማጽዳት እንዲሁም ‘ለመጠገንና ለማደስ’ ጊዜያችንን መሥዋዕት ማድረግ ትልቅ መብት ነው። (2 ዜና መዋዕል 34:10) ትላልቅ ስብሰባዎችን ለማድረግ የምንጠቀምባቸውን የመሰብሰቢያ አዳራሾችም ሆነ ሌሎች ቦታዎች በዚሁ መንገድ እንይዛቸዋለን።

ከሚያረክሱ ልማዶችና ድርጊቶች ራሳችንን እናንጻ

19. አካላዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ምን ማስወገድ ይኖርብናል? በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚረዳን እንዴት ነው?

19 አካላዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ እንደማጨስ፣ አልኮል ከመጠን በላይ እንደመጠጣትና ለሕክምና ካልሆነ በስተቀር ሱስ የሚያስይዙ ወይም አእምሮን የሚያደነዝዙ አሊያም የሚያነቃቁ መድኃኒቶችን እንደመውሰድ ከመሰሉ ሰውነትን የሚያረክሱ ልማዶችና ድርጊቶች መራቅ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዘመን ተስፋፍተው የሚገኙትን ርኩስና መጥፎ የሆኑ ልማዶች ወይም ድርጊቶች በሙሉ ባይዘረዝርም ይሖዋ ስለ እነዚህ ነገሮች ያለውን አመለካከት እንድናስተውል የሚረዱንን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዟል። የይሖዋን አመለካከት ስለምናውቅ ለእሱ ያለን ፍቅር በፊቱ ሞገስ የሚያስገኝልንን አካሄድ እንድንከተል ይገፋፋናል። አምስት መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንመልከት።

20, 21. ይሖዋ ከምን ዓይነት ልማዶች ነፃ እንድንሆን ይፈልጋል? ይህንን ለማድረግ የሚያነሳሳን ምን ጥሩ ምክንያት አለን?

20 “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እነዚህ ተስፋዎች ስላሉን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እንዲሁም አምላካዊ ፍርሃት በማሳየት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ።” (2 ቆሮንቶስ 7:1) ይሖዋ አካላችንን ከሚበክሉና መንፈሳችንን ወይም አስተሳሰባችንን ከሚያበላሹ ልማዶች ነፃ እንድንሆን ይፈልጋል። ስለዚህ ለአካላችንም ሆነ ለአእምሯችን ጤንነት ጎጂ እንደሆኑ ከሚታወቁ ልማዶች ወይም ድርጊቶች መራቅ ይኖርብናል።

21 መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እንድናነጻ’ የሚያነሳሳንን አንድ ጥሩ ምክንያት ይነግረናል። ሁለተኛ ቆሮንቶስ 7:1 “እነዚህ ተስፋዎች ስላሉን” ብሎ እንደሚጀምር ልብ በል። ይህ ጥቅስ ስለ የትኞቹ ተስፋዎች እየተናገረ ነው? ቀደም ባሉት ቁጥሮች ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ “እኔም እቀበላችኋለሁ። እኔ አባት እሆናችኋለሁ” ሲል ተስፋ ሰጥቷል። (2 ቆሮንቶስ 6:17, 18) እስቲ አስበው፣ ይሖዋ ጥበቃ ሊያደርግልህና አባት ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን እንደሚወድ ሊወድህ ቃል ገብቷል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህን ቃሉን የሚፈጽምልህ “ሥጋንና መንፈስን” ከሚያረክስ ነገር ራስህን ከጠበቅክ ብቻ ነው። ታዲያ ማንኛውም ዓይነት መጥፎ ልማድ ወይም ድርጊት ከይሖዋ ጋር እንዲህ ያለ ውድ ዝምድና እንዳትመሠርት እንቅፋት ቢሆንብህ ሞኝነት አይሆንም?

22-25. ርኩስ ከሆኑ ልማዶችና ድርጊቶች እንድንርቅ የሚረዱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?

22 “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።” (ማቴዎስ 22:37) ኢየሱስ ይህን ትእዛዝ ‘ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ’ ሲል ጠርቶታል። (ማቴዎስ 22:38) ይሖዋ እንዲህ ያለው ፍቅር ይገባዋል። እሱን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችንና ሐሳባችን ለመውደድ ዕድሜያችንን ሊያሳጥር ወይም አምላክ የሰጠንን የማሰብ ችሎታ ሊቀንስ ከሚችል ከማንኛውም ነገር መራቅ ይኖርብናል።

23 “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው [ይሖዋ ነው]።” (የሐዋርያት ሥራ 17:24, 25) ሕይወት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ነው። ሰጪውን ስለምንወደው ለስጦታው አክብሮት ማሳየት እንፈልጋለን። በጤንነታችን ላይ ጉዳት ከሚያስከትል ማንኛውም ዓይነት ልማድ ወይም ድርጊት እንርቃለን፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉትን ልማዶችና ድርጊቶች መፈጸም ለሕይወት ስጦታ አክብሮት እንደሌለን የሚያሳይ እንደሆነ እንገነዘባለን።—መዝሙር 36:9

24 “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ።” (ማቴዎስ 22:39) መጥፎ ልማዶችና ድርጊቶች አብዛኛውን ጊዜ የሚጎዱት አድራጊውን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ያሉትን ሰዎች ጭምር ነው። ለምሳሌ፣ በሲጋራ ጭስ የተበከለ አየር በማያጨሱ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በአካባቢው ያሉትን ሰዎች የሚጎዳ ነገር የሚያደርግ ሰው ጎረቤታችንን እንድንወድ የተሰጠንን መለኮታዊ ትእዛዝ ይጥሳል። በተጨማሪም አምላክን እወደዋለሁ ቢልም ተግባሩ ይህ አባባሉ ሐሰት መሆኑን ያጋልጥበታል።—1 ዮሐንስ 4:20, 21

25 ‘ለመንግሥታትና ለባለሥልጣናት ተገዙና ታዘዙ።’ (ቲቶ 3:1) በብዙ አገሮች አንዳንድ የዕፅ ዓይነቶችን ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም በሕግ የተከለከለ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን በሕግ የተከለከሉ ዕፆችን ወይም መድኃኒቶችን አንይዝም ወይም አንጠቀምም።ሮም 13:1

26. (ሀ) ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ምን ማድረግ ያስፈልገናል? (ለ) በአምላክ ዓይን ንጽሕናችንን ጠብቀን ከመኖር የተሻለ የሕይወት መንገድ ሊኖር የማይችለው ለምንድን ነው?

26 ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር በአንዱ ወይም በሁለቱ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ንጹሕ መሆን ያስፈልገናል። የሚያረክሱ ልማዶችንና ድርጊቶችን ማስወገድና ንጹሕ ሕይወት መምራት ቀላል ባይሆንም የማይቻል ነገር ግን አይደለም። * ይሖዋ ሁልጊዜ የሚያስተምረን የሚበጀንን ስለሆነ ከዚህ የተሻለ የሕይወት መንገድ ሊኖር አይችልም። (ኢሳይያስ 48:17) ከሁሉም በላይ ደግሞ ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖራችን የምንወደውን አምላካችንን እንዳስከበረው እንዲሁም ከፍቅሩ ሳንወጣ ለመኖር እንዳስቻለን ማወቃችን ያስደስተናል።

^ አን.2 “ንጹሕ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አካላዊ ንጽሕናን ብቻ ሳይሆን ሥነ ምግባራዊ ወይም መንፈሳዊ ንጽሕናን ጭምር ያመለክታል።

^ አን.26 በገጽ 94 ላይ የሚገኘውን “ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ብርቱ ትግል አደርጋለሁ?” የሚለውን ሣጥንና ‘ በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል’ የሚለውን ከላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.67 ስሟ ተቀይሯል።