በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 9

“ከዝሙት ሽሹ”

“ከዝሙት ሽሹ”

“በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው መጎምጀት ናቸው።”ቆላስይስ 3:5

1, 2. በለዓም በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ጉዳት ለማድረስ ተንኮል የሸረበው እንዴት ነው?

ዓሣ አጥማጁ አዘውትሮ ወደሚያጠምድበት ቦታ ሄዷል። ምን ዓይነት ዓሣ መያዝ እንደሚፈልግ አስቦበታል። መንጠቆው ላይ ዓሣውን የሚስብ ነገር አድርጎ ወደ ውኃው ይጥለዋል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ መንጠቆው የታሰረበት ገመድ ይወጠራል። ከዚያም ዓሣ አጥማጁ የያዘውን ዓሣ ጎትቶ ያወጣል። ፈገግ እያለ ‘ትክክለኛውን ማጥመጃ መርጫለሁ’ ይላል።

2 ይህ ሁኔታ በ1473 ከክርስቶስ ልደት በፊት የተፈጸመን አንድ ታሪክ ያስታውሰናል። በለዓም የተባለ አንድ ሰው ወጥመድ ሊሆን ስለሚችል ነገር እያሰበ ነው። ማጥመድ የፈለገው ግን በተስፋይቱ ምድር ድንበር በሚገኘው የሞዓብ ሜዳ ላይ የሰፈሩትን የአምላክ ሕዝቦች ነበር። በለዓም የይሖዋ ነቢይ ነኝ ይበል እንጂ እንደ እውነቱ ከሆነ እስራኤልን እንዲረግም የተቀጠረ ስግብግብ ሰው ነበር። ይሁንና ይሖዋ ስለከለከለው እስራኤልን ከመባረክ ሌላ አንዳች ነገር ማድረግ አልቻለም። እንደዚያም ሆኖ የተዘጋጀለትን ሽልማት ለመቀበል ቆርጦ ስለተነሳ ሕዝቡ ከባድ ኃጢአት እንዲሠሩ ማሳት ቢቻል አምላክ ራሱ ይረግማቸዋል ብሎ አሰበ። በለዓም ይህን ሐሳቡን ለማሳካት የሞዓብን ቆነጃጅት ማጥመጃ አድርጎ አቀረበ።ዘኍልቍ 22:1-7፤ 31:15, 16፤ ራእይ 2:14

3. የበለዓም ተንኮል ምን ያህል ሰመረለት?

3 ታዲያ ይህ እቅዱ ተሳካለት? አዎ፣ በመጠኑም ቢሆን ተሳክቶለታል። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ወንዶች ‘ከሞዓብ ሴቶች ጋር በማመንዘር’ በተዘጋጀላቸው ወጥመድ ወደቁ። የፌጎር በኣል ተብሎ የሚጠራውን የመራባት ወይም የወሲብ አምላክ ጨምሮ የሞዓባውያንን አማልክት ማምለክ ጀመሩ። በዚህም ምክንያት 24,000 የሚያክሉ እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ደፍ ላይ ደርሰው ሕይወታቸውን አጡ። ይህ በጣም የሚያሳዝን ነበር።ዘኍልቍ 25:1-9

4. በሺህ የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በዝሙት ወጥመድ ውስጥ የወደቁት ለምን ነበር?

4 ለዚህ እልቂት ያበቃቸው ምንድን ነው? ብዙዎቹ ከግብጽ ምድር ነፃ ካወጣቸው፣ በምድረ በዳ ከመገባቸውና ወደ ተስፋይቱ ምድር በሰላም ካደረሳቸው ከይሖዋ በመራቅ ክፉ ልብ በውስጣቸው እንዲያቆጠቁጥ ፈቅደው ነበር። (ዕብራውያን 3:12) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንኑ በማስታወስ “ከእነሱ አንዳንዶቹ ዝሙት ፈጽመው ከመካከላቸው ሃያ ሦስት ሺህ የሚሆኑት በአንድ ቀን እንደረገፉ እኛም ዝሙት የመፈጸም ልማድ አይጠናወተን” ሲል ጽፏል። *1 ቆሮንቶስ 10:8

5, 6. እስራኤላውያን በሞዓብ ሜዳ ስለሠሩት ኃጢአት የሚገልጸው ታሪክ ለእኛ ይጠቅመናል የምንለው ለምንድን ነው?

5 በዘኍልቍ መጽሐፍ ውስጥ ያለው ታሪክ ጥንት ከነበረችው ተስፋይቱ ምድር በእጅጉ ወደሚበልጥ አዲስ ምድር ለመግባት ደፍ ላይ ለሚገኙት የአምላክ ሕዝቦች የሚጠቅም ብዙ ትምህርት ይዟል። (1 ቆሮንቶስ 10:11) ለምሳሌ፣ በዛሬው ዓለም የሚታየው ለወሲብ ከፍተኛ ትኩረት የመስጠት አባዜ በጥንቷ ሞዓብ ከነበረው የተለየ አይደለም፤ እንዲያውም በዚያ ዘመን ከነበረው በጣም ይበልጣል። ከዚህም በላይ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች እስራኤላውያንን ባጠመደው የዝሙት ወጥመድ ይያዛሉ። (2 ቆሮንቶስ 2:11) በዛሬው ጊዜ በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚገኙ አንዳንድ ግለሰቦች፣ አንዲት ምድያማዊት ሴት ወደ እስራኤላውያን ሰፈር አምጥቶ በድፍረት ወደ ድንኳኑ እንዳስገባው እንደ ዘንበሪ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መጥፎ ተጽዕኖ አሳድረዋል።ዘኍልቍ 25:6, 14፤ ይሁዳ 4

6 ራስህን በዘመናዊው የሞዓብ ሜዳ ላይ እንዳለህ አድርገህ ትመለከታለህ? ሽልማትህ ይኸውም ለረዥም ጊዜ ስትጠብቀው የኖርከው አዲስ ዓለም ከፊትህ ይታይሃል? እንግዲያው “ከዝሙት ሽሹ” የሚለውን ምክር በመታዘዝ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ ለመኖር የተቻለህን ሁሉ አድርግ።1 ቆሮንቶስ 6:18

ከሞዓብ ሜዳ ባሻገር ያለውን መመልከት

ዝሙት ምንድን ነው?

7, 8. “ዝሙት” ምንድን ነው? ዝሙት የሚፈጽሙ ሁሉ የዘሩትን የሚያጭዱት እንዴት ነው?

7 በመጽሐፍ ቅዱስ አገባቡ “ዝሙት” (በግሪክኛ ፖርኒያ) የሚለው ቃል፣ በአምላክ ቃል ውስጥ ተቀባይነት ካለው ጋብቻ ውጭ የሚፈጸምን የተከለከለ የጾታ ግንኙነት ያመለክታል። ዝሙት ምንዝርን፣ ዝሙት አዳሪነትን፣ በጋብቻ ባልተሳሰሩ ግለሰቦች መካከል የሚፈጸመውን የጾታ ግንኙነት፣ እንዲሁም በአፍና በፊንጢጣ የሚደረግ ወሲብንና የትዳር ጓደኛ ያልሆነን ግለሰብ ብልት ማሻሸትን ያካትታል። በተጨማሪም ተመሳሳይ ጾታ ካላቸው ሰዎችና ከእንስሳት ጋር የሚደረገውን ግንኙነት ይጨምራል። *

8 በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መመሪያ ግልጽ ነው። ሴሰኞች ወይም ዝሙት የሚፈጽሙ ሰዎች የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ሆነው ሊቀጥሉም ሆነ የዘላለም ሕይወት ሊወርሱ አይችሉም። (1 ቆሮንቶስ 6:9፤ ራእይ 22:15) ከዚህም በላይ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ሌሎች እምነት ስለማይጥሉባቸው፣ ለራሳቸው አክብሮት ስለማይኖራቸው፣ ትዳራቸው ስለሚበጠበጥ፣ ሕሊናቸው ስለሚወቅሳቸው እንዲሁም ለማይፈለግ እርግዝና፣ ለበሽታ ይባስ ብሎም ለሞት ሊዳረጉ ስለሚችሉ አሁንም እንኳ የሚደርስባቸው ጉዳት ቀላል አይደለም። (ገላትያ 6:7, 8) እንዲህ ወዳለው ማጥ የሚያስገባ ጉዞ ለምን ትጀምራለህ? የሚያሳዝነው ግን ብዙዎች ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን እንደማየት ያለውን የመጀመሪያውን ስህተት ሲፈጽሙ ይህን ሁሉ አርቀው አይመለከቱም።

ወሲባዊ ሥዕሎችና ፊልሞች—የመጀመሪያው ስህተት

9. ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን ማየት አንዳንዶች እንደሚሉት ምንም ጉዳት የለውም? አብራራ።

9 በብዙ አገሮች ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ሥዕሎች፣ ፊልሞችና ጽሑፎች እንደ ጋዜጣ መሸጫ ባሉ ቦታዎች የሚገኙ ከመሆኑም በላይ በሙዚቃ እንዲሁም በቴሌቪዥን ይቀርባሉ፤ ኢንተርኔትም በእነዚህ ነገሮች የተሞላ ነው። * ታዲያ ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን ማየት አንዳንዶች እንደሚሉት ምንም ጉዳት የለውም? በጣም ጎጂ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን የሚመለከቱ ሰዎች ማስተርቤሽን (ስሜትን ለማርካት ተብሎ የጾታ ብልትን ማሻሸት) የመፈጸም ልማድ ሊጠናወታቸውና ‘አሳፋሪ የሆነ የፆታ ፍላጎት’ ሊያድርባቸው ይችላል። * ይህ ደግሞ ወሲብ ሱስ እንዲሆንባቸውና ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ የጾታ ምኞት እንዲያድርባቸው ሊያደርግ የሚችል ከመሆኑም በላይ እስከ ፍቺ ሊያደርስ የሚችል ከባድ የትዳር ቀውስ ያስከትልባቸዋል። (ሮም 1:24-27፤ ኤፌሶን 4:19) አንድ ተመራማሪ የወሲብ ሱስን ከካንሰር ጋር በማመሳሰል እንዲህ ብለዋል:- “ማደጉንና መሰራጨቱን ይቀጥላል። የመሻል አጋጣሚው በአብዛኛው በጣም አነስተኛ ነው። ማከምም ሆነ ማዳን በጣም አስቸጋሪ ነው።”

ኢንተርኔትን የቤተሰብ አባላት በማይጠፉበት ክፍል ውስጥ መጠቀም ጥበብ ነው

10. በያዕቆብ 1:14, 15 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ሥራ ላይ ልናውል የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (በተጨማሪም “ በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆኜ ለመኖር የሚያስችል ጥንካሬ አገኘሁ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

10 ያዕቆብ 1:14, 15 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ቃል ልብ በል። እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአት ደግሞ በተግባር ሲፈጸም ሞትን ያስከትላል።” ስለዚህ መጥፎ ምኞት ወደ አእምሮህ ከመጣ ቶሎ ለማውጣት አፋጣኝ እርምጃ ውሰድ! ለምሳሌ ያህል፣ የጾታ ስሜትን ለመቀስቀስ ተብሎ የተዘጋጀ ሥዕል ድንገት ብትመለከት ቶሎ ብለህ ፊትህን ወደ ሌላ አቅጣጫ አዙር ወይም ኮምፒውተሩን አጥፋ አሊያም የቴሌቪዥኑን ጣቢያ ቀይር። የጾታ ስሜትህ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ዝሙት ከመፈጸምህ በፊት አስፈላጊውን ሁሉ አድርግ።—ማቴዎስ 5:29, 30

11. መጥፎ ምኞቶችን ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል በይሖዋ እንደምንታመን እንዴት ማሳየት እንችላለን?

11 እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ የሚያውቀን አምላካችን እንደሚከተለው ሲል የመከረን አለበቂ ምክንያት አይደለም:- “በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው መጎምጀት ናቸው።” (ቆላስይስ 3:5) እርግጥ ነው፣ ይህን ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲረዳን ልንማጸነው የምንችል አፍቃሪና ታጋሽ አባት እንዳለን አስታውስ። (መዝሙር 68:19) ስለዚህ መጥፎ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ ሲመጡ ቶሎ ብለህ ወደ እሱ ጸልይ። ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ እንዲሰጥህ ጠይቀው እንዲሁም አእምሮህን በሌሎች ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አስገድደው።2 ቆሮንቶስ 4:7፤ 1 ቆሮንቶስ 9:27፤ በተጨማሪም በገጽ 104 ላይ የሚገኘውን “ ከመጥፎ ልማድ እንዴት መላቀቅ እችላለሁ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

12. ‘ልባችን’ ምንን ያመለክታል? ልንጠብቀው የሚገባንስ ለምንድን ነው?

12 ጠቢቡ ሰለሞን “ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ነውና” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 4:23) ‘ልባችን’ በአምላክ ዓይን ስንታይ ያለንን ውስጣዊ ማንነት የሚያመለክት ነው። ከዚህም በላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የምንበቃ መሆን አለመሆናችንን የሚወስነው ሌሎች ሰዎች ለእኛ ያላቸው ግምት ሳይሆን አምላክ ‘ለልባችን’ የሚሰጠው ዋጋ ነው። ነጥቡ ይኸው ነው፤ ምንም የተወሳሰበ ነገር የለውም። ይሁንና አቅልለን የምንመለከተው አይደለም። ታማኙ ኢዮብ ሴትን በምኞት ዓይን እንዳይመለከት ከዓይኖቹ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል ወይም ስምምነት አድርጓል። (ኢዮብ 31:1) ኢዮብ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል! አንድ መዝሙራዊም በተመሳሳይ “ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ” ሲል ጸልዮአል።መዝሙር 119:37

ዲና ያደረገችው ማስተዋል የጎደለው ምርጫ

13. ዲና ማን ነበረች? የጓደኛ ምርጫዋ ማስተዋል የጎደለው ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

13 በምዕራፍ 3 ላይ እንደተመለከትነው ጓደኞቻችን በጎም ይሁን መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይችላሉ። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) የያዕቆብ ልጅ ዲና ያጋጠማትን ሁኔታ ተመልከት። (ዘፍጥረት 34:1) ዲና ጥሩ አስተዳደግ የነበራት ብትሆንም ማስተዋል የጎደለው ምርጫ በማድረግ ከከነዓናውያን ሴት ልጆች ጋር ጓደኝነት መሠረተች። ከነዓናውያን ልክ እንደ ሞዓባውያን በሥነ ምግባር ብልግና ይታወቁ ነበር። (ዘሌዋውያን 18:6-25) ‘ከአባቱ ቤተሰብ ሁሉ እጅግ የተከበረውን’ ሴኬምን ጨምሮ ከነዓናውያን ወንዶች ዲናን ሲመለከቷት በቀላሉ በእጃቸው ልትገባ የምትችል ወጣት ሴት እንደሆነች ተሰምቷቸው ነበር።—ዘፍጥረት 34:18, 19

14. የዲና የጓደኛ ምርጫ አሳዛኝ ውጤት ያስከተለው እንዴት ነው?

14 ዲና ሴኬምን ስታገኘው ከእሱ ጋር የጾታ ግንኙነት የመፈጸም ሐሳብ አልነበራት ይሆናል። እሱ ግን ያደረገው አብዛኞቹ ከነዓናውያን የጾታ ፍላጎታቸው ሲነሳሳ የሚያደርጉትን ነገር ነበር። ዲና በመጨረሻ ሰዓት ላይ ከእጁ ለመውጣት ያደረገችው መፍጨርጨር ምንም ሊፈይድላት አልቻለም፤ ምክንያቱም ሴኬም “ይዞ በማስገደድ ደፈራት።” ሴኬም በኋላ ላይ ዲናን ‘በጣም የወደዳት’ ቢሆንም ይህ መጀመሪያ ያደረሰባትን በደል ሊለውጠው አይችልም። (ዘፍጥረት 34:1-4) በዚህ ምክንያት ችግር ላይ የወደቀችው ዲና ብቻ አልነበረችም። መጥፎ ጓደኞች መምረጧ በመላው ቤተሰቧ ላይ ውርደትና ነቀፋ ያስከተሉ ነገሮች እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኗል።ዘፍጥረት 34:7, 25-31፤ ገላትያ 6:7, 8

15, 16. እውነተኛ ጥበብ እንዴት ማግኘት እንችላለን? (በተጨማሪም “ በሚከተሉት ጥቅሶች ላይ አሰላስል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

15 ዲና ከዚህ ሁኔታ ትልቅ ትምህርት አግኝታ ሊሆን ይችላል፤ ቢሆንም የተማረችው ከመከራ ነው። ይሖዋን የሚወዱና የሚታዘዙ ሁሉ ለሕይወታቸው ጠቃሚ የሆኑ ትምህርቶችን በራሳቸው ላይ ከደረሰው ችግር መማር አይኖርባቸውም። አምላክ የሚላቸውን ስለሚያዳምጡ ‘ከጠቢባን ጋር ይሄዳሉ።’ (ምሳሌ 13:20ሀ) ይህን በማድረጋቸውም ‘መልካሙን መንገድ ሁሉ’ ስለሚገነዘቡ አላስፈላጊ ከሆኑ ችግሮችና መከራዎች ያመልጣሉ።ምሳሌ 2:6-9፤ መዝሙር 1:1-3

16 አምላካዊ ጥበብ ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸውና በጸሎት በመጽናት እንዲሁም የአምላክን ቃልና ታማኙ ባሪያ የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች አዘውትረው በማጥናት ይህንን ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚጥሩ ሰዎች የአምላክን ጥበብ ማግኘት ይችላሉ። (ማቴዎስ 24:45፤ ያዕቆብ 1:5) በተጨማሪም ትሕትና አስፈላጊ ነው። ይህ ባሕርይ አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ለመታዘዝ ፈቃደኛ እንዲሆን ያደርገዋል። (2 ነገሥት 22:18, 19) ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን ልቡ ተንኮለኛና አስቸጋሪ እንደሆነ ሊቀበል ይችላል። (ኤርምያስ 17:9) ይሁን እንጂ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ የሚሰጠውን ቀጥተኛ የሆነና ፍቅር የተንጸባረቀበት ምክርና እርዳታ በትሕትና ይቀበላል?

17. በቤተሰብ ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል? አንድ አባት ልጁን አሳማኝ በሆነ መንገድ ሊያስረዳት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

17 የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። አንድ አባት ሴት ልጁ ከአንድ ወጣት ክርስቲያን ወንድ ጋር ሆና ለብቻቸው ጊዜ እንዲያሳልፉ አይፈቅድላትም። ልጅቷ “አባዬ፣ አታምነኝም ማለት ነው? ምንም መጥፎ ነገር አናደርግም!” ትለዋለች። ይህች ልጅ ይሖዋን የምትወድና ምንም ዓይነት መጥፎ ሐሳብ የሌላት ብትሆንም ‘በአምላክ ጥበብ እየተመላለሰች’ ነው ሊባል ይችላል? ‘ከዝሙት እየሸሸች’ ነው? ወይስ በሞኝነት ‘በራሷ ልብ እንደምትታመን’ እያሳየች ነው? (ምሳሌ 28:26) አባትየውና ልጅቷ በጉዳዩ ላይ በሚገባ እንዲያስቡ ሊረዷቸው የሚችሉ ተጨማሪ መሠረታዊ ሥርዓቶች ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል።ምሳሌ 22:3፤ ማቴዎስ 6:13፤ 26:41ን ተመልከት።

ዮሴፍ ከዝሙት ሸሽቷል

18, 19. ዮሴፍ በሕይወቱ ውስጥ ምን ዓይነት ፈተና አጋጠመው? ፈተናውን የተቋቋመውስ እንዴት ነው?

18 አምላክን የሚወድ በመሆኑ ምክንያት ከዝሙት የሸሸ አንድ ወጣት አለ፤ እሱም የዲና ወንድም የነበረው ዮሴፍ ነው። (ዘፍጥረት 30:20-24) ዮሴፍ ገና ልጅ እያለ የእህቱ ስህተት ያስከተለውን አሳዛኝ ውጤት ተመልክቷል። ዮሴፍ ይህን ታሪክ ማስታወሱ እንዲሁም ከአምላክ ፍቅር ሳይወጣ ለመኖር ጠንካራ ፍላጎት የነበረው መሆኑ፣ ከበርካታ ዓመታት በኋላ በግብጽ ሳለ የጌታው ሚስት ከእሷ ጋር የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽም “በየቀኑ” ብትወተውተውም ጸንቶ እንዲቆም ረድቶታል። እርግጥ ነው፣ ዮሴፍ ባሪያ ስለነበር ሥራው ይቅርብኝ ብሎ እንዲያሰናብቱት ሊጠይቅ አይችልም። ሁኔታውን በጥበብና በድፍረት መቋቋም ነበረበት። ይህንንም ያደረገው ለጲጥፋራ ሚስት ፈቃደኛ አለመሆኑን በተደጋጋሚ በመግለጽና በመጨረሻም ከእሷ በመሸሽ ነው።ዘፍጥረት 39:7-12

19 እስቲ አስበው፣ ዮሴፍ ሴቲቱን በምኞት ዓይን የሚመለከታትና ስለ ጾታ ግንኙነት የማለም ልማድ የነበረው ቢሆን ኖሮ ታማኝነቱን ሊጠብቅ ይችል ነበር? ፈተናውን በታማኝነት የመወጣቱ አጋጣሚ አነስተኛ ይሆን ነበር። ዮሴፍ ወደ ኃጢአት የሚመሩ ሐሳቦችን ከማውጠንጠን ይልቅ ከይሖዋ ጋር ላለው ዝምድና ትልቅ ቦታ ይሰጥ እንደነበር ለጲጥፋራ ሚስት ከተናገረው ቃል መረዳት ይቻላል። ‘ጌታዬ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በአምላክ ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?’ አላት።ዘፍጥረት 39:8, 9

20. ይሖዋ የዮሴፍ ሁኔታ መልኩን እንዲቀይር ያደረገው እንዴት ነው?

20 ከቤተሰቦቹ በጣም ርቆ ይኖር የነበረው ወጣቱ ዮሴፍ በእያንዳንዱ ዕለት ከአቋሙ ፍንክች ሳይል መኖሩን ሲመለከት ይሖዋ ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን ገምት። (ምሳሌ 27:11) በኋላ ላይ ይሖዋ ዮሴፍ ከእሥር ቤት እንዲወጣ ብቻ ሳይሆን የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትርና የእህል አስተዳዳሪ እንዲሆን በማድረግ ሁኔታው መልኩን እንዲቀይር አደረገ። (ዘፍጥረት 41:39-49) “[ይሖዋን] የምትወዱ ክፋትን ጥሉ፤ እርሱ የታማኞቹን ነፍስ ይጠብቃልና፤ ከዐመፀኞችም እጅ ይታደጋቸዋል” የሚሉት የመዝሙር 97:10 ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው!

21. በአፍሪካ የሚኖር አንድ ወጣት ወንድም በድፍረት የሥነ ምግባር ንጽሕናውን የጠበቀው እንዴት ነው?

21 ዛሬም በተመሳሳይ ብዙ የአምላክ አገልጋዮች ‘ክፉውን እንደሚጠሉና መልካሙን እንደሚወዱ’ አሳይተዋል። (አሞጽ 5:15) በአንድ የአፍሪካ አገር የሚኖር ወጣት ወንድም አንዲት የክፍሉ ተማሪ በሂሣብ ፈተና ላይ ከረዳት ከእሱ ጋር የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ፈቃደኛ እንደምትሆን ነገረችው። እሱም “ወዲያውኑ ፈቃደኛ አለመሆኔን ገለጽኩላት” በማለት ተናግሯል። አክሎም “በአቋሜ መጽናቴ ከወርቅና ከብር የበለጠ ዋጋ ያለውን ክብሬንና ለራሴ ያለኝን ጥሩ ግምት እንደጠበቅሁ ለመኖር አስችሎኛል” ብሏል። ኃጢአት “ጊዜያዊ ደስታ” ሊሰጥ እንደሚችል አይካድም። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ቅጽበታዊ ደስታ ብዙ ጊዜ ከፍተኛ ሥቃይ ያስከትላል። (ዕብራውያን 11:25) ከዚህም በላይ ይሖዋን በመታዘዝ ከሚገኘው ዘላቂ ደስታ ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።—ምሳሌ 10:22

የምሕረት አምላክ የሚሰጠውን እርዳታ ተቀበል

22, 23. (ሀ) አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ቢሠራ ሁኔታው ምንም ተስፋ የሌለው የማይሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኃጢአት የሠራ ሰው ምን እርዳታ ሊያገኝ ይችላል?

22 ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት ሥጋዊ ምኞቶቻችንን ለማሸነፍና በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ለማድረግ መታገል ይኖርብናል። (ሮም 7:21-25) ይሖዋ ‘ትቢያ መሆናችንን ስለሚያስብ’ እንዲህ ያለ ትግል እንዳለብን ያውቃል። (መዝሙር 103:14) ይሁን እንጂ አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት የሚሠራበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ታዲያ ይህ ክርስቲያን ከዚያ በኋላ ምንም ተስፋ የለውም ማለት ነው? በፍጹም! ኃጢአት የሠራው ሰው ልክ እንደ ንጉሥ ዳዊት መራራ ፍሬ ማጨዱ የማይቀር ነው። ቢሆንም አምላክ በሥራቸው ተጸጽተው ኃጢአታቸውን ‘በግልጽ የሚናዘዙ’ ሰዎችን ‘ይቅር ለማለት’ ምንጊዜም ዝግጁ ነው።መዝሙር 86:5፤ ያዕቆብ 5:16፤ ምሳሌ 28:13

23 በተጨማሪም አምላክ፣ እርዳታ ለመስጠት ብቃትም ሆነ ፍላጎት ያላቸውን የጎለመሱ መንፈሳዊ እረኞች ለክርስቲያን ጉባኤ “ስጦታ አድርጎ” ሰጥቷል። (ኤፌሶን 4:8, 12፤ ያዕቆብ 5:14, 15) የእነዚህ እረኞች ዓላማ አንድ ኃጢአት የሠራ ሰው ከአምላክ ጋር የነበረውን ዝምድና መልሶ እንዲያጠናክር እንዲሁም በዚያው ኃጢአት ከመውደቅ የሚጠብቀውን ‘ማስተዋል እንዲያገኝ’ መርዳት ነው።ምሳሌ 15:32

‘ማስተዋልን አግኝ’

24, 25. (ሀ) በምሳሌ 7:6-23 ላይ የተገለጸው ወጣት ‘ማስተዋል የጎደለው’ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ‘ማስተዋልን ልናገኝ’ የምንችለው እንዴት ነው?

24 መጽሐፍ ቅዱስ ‘ማስተዋል ስለጎደላቸው’ ሰዎችና ‘ማስተዋልን ስለሚያገኙ’ ሰዎች ይናገራል። (ምሳሌ 7:7) አንድ ‘ማስተዋል የጎደለው ሰው’ በመንፈሳዊ ጎልማሳ ባለመሆኑና በአምላክ አገልግሎት ብዙ ተሞክሮ ስለሌለው የማመዛዘን ችሎታ ሊያንሰው ይችላል። በምሳሌ 7:6-23 ላይ እንደተገለጸው ወጣት በቀላሉ በከባድ ኃጢአት ሊሸነፍ ይችላል። በተቃራኒው ‘ማስተዋል የሚያገኝ ሰው’ በጸሎት እየታገዘ የአምላክን ቃል አዘውትሮ በማጥናት ውስጣዊ ማንነቱን ይመረምራል። ፍጹም ባይሆንም እንኳ አቅሙ በፈቀደለት መጠን አስተሳሰቡን፣ ምኞቶቹን፣ ስሜቱን እንዲሁም ግቦቹን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ያስማማል። በዚህ መንገድ ‘ነፍሱን እንደሚወድ’ ወይም የሚጠቅመውን እንደሚያደርግ ያሳያል፤ ስለሆነም “ይሳካለታል”።ምሳሌ 19:8

25 ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ትክክል እንደሆኑ ሙሉ በሙሉ አምናለሁ? እነዚህን መሥፈርቶች መከተል ከፍተኛ ደስታ እንደሚያስገኝስ ጽኑ እምነት አለኝ?’ (መዝሙር 19:7-10፤ ኢሳይያስ 48:17, 18) በዚህ ረገድ ቅንጣት ታክል እንኳን ጥርጣሬ ካለህ ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ ውሰድ። የአምላክን ሕጎች ችላ ማለት ስለሚያስከትለው መዘዝ አሰላስል። በተጨማሪም በእውነት በመመላለስና አእምሮህን ጤናማ በሆኑ ሐሳቦች በመሙላት፣ ማለትም እውነት፣ ጽድቅ፣ ንጹሕ፣ ተወዳጅና በጎ የሆኑ ነገሮችን በማሰብ ‘[ይሖዋ] ቸር መሆኑን ቀምሰህ እይ።’ (መዝሙር 34:8፤ ፊልጵስዩስ 4:8, 9) ይህን ባደረግህ መጠን ለይሖዋና እሱ ለሚወዳቸው ነገሮች ያለህ ፍቅር እንደሚጨምርና የሚጠላቸውን ነገሮች ይበልጥ እየጠላህ እንደምትሄድ ምንም ጥርጥር የለውም። ዮሴፍ ከማንኛችንም የተለየ ሰው አልነበረም። ይሁን እንጂ አምላክን የማስደሰት ፍላጎት ስለነበረው ለበርካታ ዓመታት ይሖዋ እንዲቀርጸው መፍቀዱ ‘ከዝሙት እንዲሸሽ’ አስችሎታል። አንተም እንደዚሁ እንዲሳካልህ እንመኛለን።ኢሳይያስ 64:8

26. ቀጥሎ የምንመለከተው የትኛውን አስፈላጊ ርዕሰ ጉዳይ ይሆናል?

26 ፈጣሪያችን የመራቢያ አካላችንን የሠራው መሰሎቻችንን እንድናፈራና በጋብቻ ውስጥ በሚገኘው መቀራረብ እንድንደሰት ለማስቻል እንጂ ቅጽበታዊ ደስታ ብቻ የሚያስገኝ መጫወቻ እንዲሆን አይደለም። (ምሳሌ 5:18) አምላክ ስለ ጋብቻ ያለው አመለካከት በሚቀጥሉት ሁለት ምዕራፎች ውስጥ ይብራራል።

^ አን.4 በዘኍልቍ መጽሐፍ ላይ የተገለጸው አኃዝ በእስራኤል ዳኞች የተገደሉትን 1,000 የሚሆኑ ‘የሕዝብ አለቆችና’ በቀጥታ በይሖዋ የተገደሉትን እንደሚያጠቃልል ግልጽ ነው።ዘኍልቍ 25:4, 5

^ አን.7 ርኩሰትና ብልግና ምን እንደሚያመለክቱ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው በሐምሌ 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ላይ ያለውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።

^ አን.9 “ወሲባዊ ሥዕሎችና ፊልሞች” የሚለው ሐረግ በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚያመለክተው የጾታ ስሜትን ለመቀስቀስ ታስበው የሚዘጋጁ ሥዕሎችን፣ ጽሑፎችን ወይም ድምፆችን ነው። ወሲባዊ ሥዕሎችና ፊልሞች የጾታ ስሜትን በሚያነሳሳ ሁኔታ የተነሳ የአንድ ሰው ፎቶግራፍ ከማሳየት ጀምሮ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ግለሰቦች እጅግ አስጸያፊ የሆነ የጾታ ግንኙነት ሲፈጽሙ የሚያሳዩ ሊሆኑ ይችላሉ።

^ አን.9 ማስተርቤሽንን በተመለከተ “የማስተርቤሽንን ልማድ ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?” በሚለው ተጨማሪ መረጃ ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል።